>

ኦሮሞ ምኒልክን ማምለክ ይገባዋል! ማመስገን ሳይሆን ማምለክ!!! (ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ) 

ኦሮሞ ምኒልክን ማምለክ ይገባዋል! ማመስገን ሳይሆን ማምለክ!!!
 
ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ 
 
ከፍተኛ ተነባቢነት ለማግኘት ችላ የነበረችው “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ባልደረባና ሼር ሆልደር ነበር፡፡ በወቅቱ በጋዜጣው ላይ የሚወጡት በሳል ጽሑፎች ያልተመቸው አምባገነን ሥርዓት፣ በነፃው ፕሬስ ታሪክ ውስጥ ደማቅ ታሪክ የፃፈውን ጋዜጣና ሠራተኞቹን ለማጥፋት ያደረገውን ግፊት ተከትሎ በድንገት ከሀገር ሊወጣ ችሏል፡፡
አሜሪካን እንደደረሰ የትምህርት ዕድል ቢያገኝም፣ ከሀገሩ ለመውጣት አስቀድሞ የስልነቦና ዝግጅት ያልነበረው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ አንድ ዓመት ከመንፈቅ ያህል በቁጭትና በእልህ ውስጥ ለመቀመጥ ተገዷል፡፡በሀገር ቤት ቆይታው ለታሪክ፣ ለፍልስፍና፣ ለስነ መለኮት እና ለፖለቲካ ከፍተኛ ትኩረት ሲሰጥ ከመቆየቱ ጋር ተያይዞ፤ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በተለይም ከአብዮቱ መነሣት በኋላ፣ “የብሔር ጭቆና አለ”፣ “የኢትዮጵያ ታሪክ እኛን አይገልፅም” ለሚሉት ጥያቄዎች የተሠጠው አመላለስ ልክ ባይሆንም፣ የተስተጋቡት ጥያቄዎች ግን ተገቢነት እና ታሪካዊ አመጣጥ አላቸው የሚል ግምት አሳድሮበት እንደቆየም ያስታውሳል፡፡
አሁን ላይ ከብሔርተኝነት ፖለቲካ (በተለይም የኦሮሞ አክቲቪስቶች፣ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮችና ልሂቃኖች) ጋር በተያያዘ በሚጽፋቸው ጽሑፎች እና በሚሠጣቸው አስተያየቶች፣ ሀገራዊ አንድነትን አጥብቆ በማስቀደም የሚታወቀው ጋዜጠኛ ታምራት ነገራ፣ በርካቶች ዘንድ የኢትዮጵያ ሃገረ መንግሥታና ታሪክን የተመለከቱ ምልከታዎቹ አነጋጋሪ ናቸው፡፡ በኢትዮጵያ ፖለቲካም ሆነ ታሪካዊ ሁነቶች ዙርያ መረዳቶቹን በግልጽና በማያሻማ መንገድ በማስተጋባት የሚታወቀው ይህ ወጣት ጋዜጠኛ በወቅታዊና ሀገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ተከታዩን ቆይታ ከግዮን መጽሔት አድርጓል፡
ግዮን፡- የጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ስልጣን መያዝን ተከትሎ ከስደት ወደ አገር ቤት መጥተሃል፤ በቀጣይ “አዲስ ነገር” ጋዜጣ ዳግም ለሕትመት የምትበቃበት ዕድል ይኖር ይሆን?
ታምራት፡- ከአሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ ያደረኩት ሽግግር ላይ ባለቤቴ ሰላም በላይ ያላት ሚናን በቃል ልገልፀው አልችልም። በነገርህ ላይ በእሷ እና በእኔ መካከል ስለኢትዮጵያ ጉዳይ አንድ ያለው ልዩነት እኔ የዳግማዊ ምኒልክ አድናቂ መሆኔ እና እሷ ደግሞ የአፄ ቴዎድሮስ አምላኪ መሆኗ ብቻ ነው። ወደ ነጥቡ ስመለስ ፣ ውጭ አገር የመኖር ጉጉቱ የሌለኝ በመሆኑ ዕድሉ ሲፈጠር በፍጥነት ነው ወደ ኢትዮጵያ የመጣሁት፡፡ እዚህ ከገባሁ በኋላ ትዳር መስርቻለሁ፤ “ዋርካ”ን ከጓደኞቼ
ጋር አቋቁሚያለሁ፡፡ ሌሎች እየሰራኋቸው ያሉ ፕሮጀክቶች አሉ፤ የአዲስ ነገር ጋዜጣ ዳግም ለሕትመት መብቃት ላይ ግን ርግጠኛ መሆን ይቸግረኛል፡፡
እንደምታውቀው ሁላችንም ጓደኛሞች ነን፤ በፊት ሀገራችን ላይ አንድ ላይ የመኖር አድቫንቴጅ ነበረን፡፡ አሁን ላይ ግን መስፍን ነጋሽ ስዊድን፣ ዐቢይ ተ/ማርያም እንግሊዝ፣ ዳኝነት መኮንን አሜሪካ፣ ተስፋዓለም ጀርመን፣ ማስረሻ ሆላንድ ነው ያሉት፡፡ እዚህ ያለነው እኔና ግርማ ብቻ ነን፤ በዛ ላይ ሁሉም በያሉበት ሀገር በሥራ ላይ በመሆናቸው፣ እነዚህን ሰዎች ሰብስበህ “አዲስ ነገር”ን ዳግም ለሕትመት ማብቃት ከባድ ነው፡፡ይህ ማለት ግን አዲስ ነገር ጋዜጣ ከዚህ በኋላ አይወጣም፣ ቀርቷል ብዬ እየደመደምኩ አይደለም፡፡ በሆነ ወቅት ይህ ቡድን የሚሰበሰብበት ሁኔታ ከተፈጠረ፣ ጋዜጣዋ ለሕትመት የምታበቃበት ዕድል ይኖራል ብዬ አስባለሁ፡፡ አሁንም አንዳንድ መነሳሳቶች በኋደኞቼ ላይ እየታየ ነው፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በነበርክበት ጊዜ ከኦሮሞ ብሔርተኝነት ፖለቲካ አቀንቃኝነት ጋር በተያያዘ የደጋፊነት ስሜት ያላቸውን ሃሳቦች ትገልጽ ነበር ይባላል፡፡ ምን ምላሽ አለህ?
ታምራት፡- በብሔርተኝነት እንቅስቃሴ ላይ ተሳትፌ አላውቅም፤ የኦሮሞ አክቲቪስትም ሆኜ አላውቅም፡፡ የወጣሁበት ማኅበረሰብ ኦሮሞ ነው፤ ማንም ሠው የፈለገውን መለኪያ ቢያመጣ፣ አሁን ኦሮሞ ነኝ ብለው ከሚጮኹት የበለጠ ኦሮሞ ነኝ፡፡ በደም ብትሄድ፣ በቤተሰብ ብትመጣ ጭምር፡፡ በአመለካከት ግን የኦሮሞ ብሔርተኛ ሆኜ አላውቅም፤ ልሆንም አልችልም፡፡ የዛን ጊዜም ቢሆን “የኦሮሞ ሕዝብ ተጨቁኗል፣ በደልይደርስበታል” ብዬም አላውቅም፡፡በፖለቲካ ፓርቲ ውስጥ የነበረኝን ተሣትፎም ብትመለከት በኢድልና ቅንጅት በኩል ነው የመጣኹት፡፡ በየትኛውም መንገድ የብሔር ጭቆናን በተመለከተ ምንም ዓይነት እንቅስቃሴ
አድርጌ አላውቅም፡፡ የኢትዮጵያ ታሪክና ተረክ፣ ባህልና ቋንቋ አላሳተፈንም የሚሉ ሰዎች ጥያቄ፤ ቢያንስ ድምፃቸው ይሰማ የሚል ዓይነት ነገር ግን በጥቂቱ ነበረኝ፤ ምናልባት ይሄን እንደ ብሔርተኝነት ካልወሰድከው በስተቀር፡፡
ግዮን፡- ያ ጥያቄያቸው ተሰምቷል ብለህስ ታምናለህ?
ታምራት፡- አሁን ላይማ ከመስማት አልፎ ሌሎች እንዳይናገሩ የሀገሪቱ ሕልውና ላይ አደጋ ስለሆነ፣ እንደውም ይጨፍለቁ ባይ ነኝ፡፡ ከተማሪዎች ንቅናቄ ጋር ተያይዞ ያኔ በነበረችው ኢትዮጵያ ወስጥ የመጣው የእነ ዋለልኝ ጥያቄ፣ የተወሰደበት መንገድ በጣም በዛ እንጂ ጥያቄው ትክክል ነበር፡፡ አሁን ላይ ግን ጥያቄው ራሱ ተገቢ አይደለም፡፡
ግዮን፡- አሜሪካ በሄድክበት ጊዜ ጃዋር መሐመድ ዘንድ ነው ያረፍከው ይባላል፡፡ ምን ያህል እውነት ነው?
ታምራት፡- እንደሄድኩኝ ቤተሰብ ጋር ነበር ያረፍኩት፤ ጃዋር ደግሞ ቤተሰቤን ያውቃል፡፡ ከሀገር የወጣሁት ያለ ፍላጎቴ በመሆኑ በጣም እያመሸሁ ስለምገባ፣ ላሳረፈኝ ሰው ትንሽ አስቸጋሪ ስለሆንኩ አልተስማማንም፡፡ ያኔ ጃዋር ‹እኔ ጋር ና› አለኝ፡፡ በነገራችን ላይ በግለ ባህሪ ደረጃ ጃዋር በቀላሉ ልታገኘው የምትችለው፣ ደግ ሰው ነው፡፡በዚህ መንገድ ጃዋር ጋር ስሄድ እሱ እንጂ እኔ ሥራ የለኝም፡፡ የቤት ኪራይ፣ የምንበላውም ሆነ የምንጠጣውን የሚከፍለው እሱ ነው፡፡ ጃዋር
ያኔ ከኢትዮጵያዊነት ጋር ቀረቤታ ነበረው፤ አስር ወር እሱ ጋር ተቀምጫለሁ፡፡ በኋላ ለትምህርት ወደ ፊሊፒንስ ሲሄድ ነው የተለያየነው፡፡
ግዮን፡- አሁን ሁለታችሁ ፈፅሞ በማይጣጣሙ የፖለቲካ መስመር ውስጥ ነው ያላችኹት፤ ግን ትገናኛላችሁ?
ታምራት፡- አሁን አንገናኝም፡፡ የሚገርምህ እሱ የተማረበት ዩንቨርስቲ ስታንፎርድ፣ ጠንካራ መንግሥት መኖር አለበት ብሎ የሚያምን ነው፡፡ እነ ኮንዶ ሊዛራይዝ የነበሩበት ታላቅ ዩንቨርስቲ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ብዙ ሰዎች ጃዋርን ዝም ብው ሲንቁት ይገርመኛል፡፡ኢ.ሲ.ኤ በነበረ ስብሰባ ላይ “እኔ ምኹር ነኝ”
ያለው እኮ የምሩን ነው፡፡ በዛ ላይ ሲሪየስ ስትራጀቲስት ነው፡፡ እኔ ሳውቀው በፊት ከኢሳት ጋር በጣም ቀረቤታ ነበረው፣ ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኞች ጋር ቀረቤታ ነበረው፡፡ እኔና ጃዋርን ያስተዋወቀን ያሬድ ጥበቡ ነው፡፡ ያገኘኝ ቀን ቤተሰቦቼ በኦነግ ውስጥ የነበራቸውን ተሳትፎ ስለሚያውቅ፣ “ከእነሱ ቤት ወጥተህ ነው፤
የኢትዮጵያ ብሔርተኛ የሆንከው?” ሲል ነበር የጠየቀኝ፡፡ጃዋርን መጀመሪያ ስፖንሰር ያደረገው አትላንታ የሚኖር የአክስቴ ልጅ ነው፡፡ ቤተሰቤን ከማወቁ
አንፃር የኢትዮጵያ ብሔርተኛ መሆኔ ብዙ ጊዜ ይገርመው ነበር፡፡ እኔ ሳውቀው ጃዋር በአይዶሎጂው ኢትዮጵያን አደጋ ውስጥ በሚከት መልኩ የኦሮሞን ጥያቄ የሚያቀነቅን ሠው አልነበረም፡፡ በኮሚኒቲ ሴንተር ውስጥ በምናደርጋቸው ውይይቶች ውስጥም ቢሆን፣ ኦሮሞ የኢትዮጵያን ሕልውናና ጥቅም ማስጠበቅ
አለበት ዓይነት አቋም ነበረው፡፡እንደማንኛውም ልሂቃን የኦሮሞን መደራጀት ግን ይደግፍና ያበረታታ ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ፤ በወቅቱ “ኦነግ ሲያካሂድ የነበረው ፀረ ኦሕዴድ እንቅስቃሴ አስፈላጊ አይደለም” ብሎ ከማመን ባሻገር፤ ከኦሕዴድ ሹማምንት ጋርም ረዥም ቀረቤታ ነበረው፡፡ “ኦሮሞ ፈርስት” የምትለው ዕሳቤውን ይዞ በአልጀዚራ ቴሌቭዥን ላይ ትንታኔ ሲሰጥ፤ ያኔ ከጠበቀው በላይ ስሙ ተጋነነ፣ ተደነቀ፡፡ በዚህም የተነሳ ኦሮሞን እንደ አንደኛ ማንነት በመያዝ፣ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ መሣተፍ የጀመረው፡፡“ኦሮሞ ፈርስት” በሚል አመለካከት ከዛ በኋላ የተደረጉት ነገሮች ለእኔ የነገሩኝ፤ ጥያቄውና አካሄዱ እንደማይጠቅም፣ መቆሚያም እንደሌለው ነው፡፡ አውራ ጣትህን ብትሰጠው እጅ ይጠይቃል፣ እጅ ስትሰጠው ክርን ይጠይቃል፣ ክርን ስትሰጠው ሌላ እየጠየቀ የሚስፋፋ፣ ሀገሪቷም ሆነ መንግሥትም እንዲኖር የማይፈልግ አካሄድ ነው፡፡ እኔ ደግሞ የመንግሥትና የሀገርን ሕልውና አደጋ ውስጥ እስከ ከተተ ድረስ የኦሮሞ፣ የጉራጌ፣ የክርስቲያን
ይሁን የሙስሊም የማንንም ጥያቄ፤ አትቀበለው ብቻ ሣይሆን “ጨፍልቀው”፣ “አታስተናግደው” የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡አሁን ኢትዮጵያ ውስጥ ችግሩ ምንድን ነው? ካልከኝ፤ የትኛውን ጥያቄ እናስተናግድ? የትኛውን ጥያቄ ቅድሚያ ምላሽ እንስጥ? የትኛውን እንጨፍልቅ? የሚል ፕሮሰስ የለንም፡፡ ገዢ ሆኖ
የመጣው አካል መጀመሪያ መጥቶ ሥልጣኑን ማረጋገጥ አለበት፡፡ ሌሎች ሀገሮች ጥያቄ ከሚያስተናግዱበት መንገድ አልፈው፣ ገዢው ሥልጣኑን የሚጠበቅበትና የሚያስቀጥልበት፣ ጥያቄዎች ደግሞ ለብቻቸው የሚስተናገዱበት መንገዶች ሁሉ አሏቸው፡፡
ግዮን፡- ለምሣሌ?
ታምራት፡- ሥልጣን የማስጠበቅ መንገዱ፤ “መብቴ”፣ “ጭቆናዬ” ከሚሉ የውሸት ለቅሶዎች የምትለይበት አሠራር በእኛ ሀገር አልተበጀም፡፡ ሁሉም አልቃሻ፣ ተበደልኩ ባይና ሥልጣን ፈላጊ ነው የሚመስለው፡፡
ግዮን፡- እንደው ስለ ጃዋር ካነሳን አይቀር፤ የበፊትና የአሁን አቋሙ መሀል ያለው ግልፅ ያለ ልዩነት ምንድን ነው?
ታምራት፡- ጃዋር አቋሙ እዚህ ጋር ነው ብለህ በትክክል ልትደመድመው የማትችለው ሠው ነው፡፡ እስካሁን የተናገራቸው ነገሮች፣ የጻፋቸውን ጽሑፎችና ያደረጋቸውን ቃለምልልሶች ጨምቀህ፣ ይሄ ነው አቋሙ ማለት አትችልም፡፡ ሁለተኛ አሁን ያለውና ያኔ እኔ የማውቀው ጃዋር አንድ ዓይነት ሰዎች አይደሉም፡፡ ምክንያቱም አሁን ከትልልቅ ኦርጋናይዘሮች፣ ከኤርትራ፣ ሳዑዲ፣ ኳታር ከመሰሉ ከተለያዩ ሀገሮች ፤ እንዲሁም ከኢትዮጵያ ትልልቅ ነጋዴዎችና ባለስልጣናት
ጋር ግንኙነት ያለው ከመሆኑ ጋር ተያይዞ፤ የእሱ አቋም ይሄ ነው ማለት ያዳግተኛል፡፡ አሁን የማንን ፍላጎት እንደሚያራምድ መናገር ራሱ ይከብዳል፡፡
ግዮን፡- ፖለቲካ በራሱ አቋም ይፈልጋል?
ታምራት፡- ይፈልጋል፡፡ አቋምና ግልጽ ፍላጎት ከሌለህማ የምታራምደው ነገር የለም ማለት ነው፡፡ አሁን ጃዋር የዘውግ ፌዴራሊዝሙ እንዲቀጥል ይፈልጋል፤ ያለምንም ጥርጥር መናገር የምችለው ይሄን ብቻ ነው፡፡ እኔ ደግሞ እሱ እንዲቀጥል አልፈልግም፡፡ አብዛኞቻችን ይሄ የዘውግ ፌደራሊዝም ለሀገሪቱ አደጋ ነው ብለን እናምናለን፡፡
ግዮን፡- የዘመናዊት ኢትዮጵያን ሃገረ መንግሥት ምሥረታ እውን ያደረጉት አፄ ምኒልክ ናቸው የሚሉ ብዙ ምሁራን እንዳሉ ሁሉ፤ ሂደቱን ከቅኝ ግዛት ግር በማመሳሰል ወደ ተለያየ ቦታ ወረራ የፈጸሙትም ምኒልክ ናቸው ብለው የሚከሱ አሉ፡፡ የአንተስ አመለካከት በዚህ ዙሪያ ምንድነው?
ታምራት፡- በአጭሩ ልንገርህ፡፡ ሁሉም የአፍሪካ ሀገራት ምኒልክ ቢኖራቸው ኖሮ ያመልኩት ነበር፡፡ ሃይማኖት ሁሉ ይሆን ነበር ምንሊክ፡፡ እንኳን ምኒልክ ‹ራስ ተፈሪ› ተብሎ ኃይለ ሥላሴም ሃይማኖት ሆነዋል፡፡ እርሳቸው የተመለኩት እኮ በምኒልክ ሥራዎች ነው፡፡“ምኒልክ ጨቆነኝ” ለሚለው፤ አንደኛ በበ ሁኔታ አልጨቆኑህም በሚለው ነጥብ ነው የምከራከረው፡፡ የበለጠ ሊጨቁንህ ሲገባው ሩህሩህ ሆኖ አልጨቆነህም ነው አቋሜ፡፡ሌላውና ዋነኛው ነገር ኦሮሞ ምኒልክን ማምለክ
ይገባዋል፡፡ ማመስገን ሳይሆን ማምለክ፡፡ እያንዳንዱ ኦሮሞ በምኒልክ ሐውልት ስር ተንበርክኮ ሊያመልከው ይገባል፡፡ ምክንያቱም ኦሮሞ አሁን የያዘውን ማንነት እንዲይዝ ውለታ የዋለለት ምኒልክ ስለሆነ፡፡ ኦሮሞ ጣልያንኛ የማይናገረው በምኒልክ ምክንያት መሆኑን መርሣት የለበትም፡፡እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ እነ ሌንጮ አሁን ያለውን የኦሮሞ ትውልድና ራሳቸውን ሸውደዋል፡፡ ግን ርግጠኛ ሆኜ የምነግርህ የኦሮሞ ሕዝብ ወደፊትም ቢሆን ምኒልክን ማምለኩ አይቀርም፡፡
ግዮን፡- ለእዚህ አቋምህ መነሻ ምክንያትህ ምንድን ነው?
ታምራት፡- በኦሮሞ ልሂቃን ከተሠሩ ትልቅ ስህተቶች ውስጥ፤ የኦሮሞን ትግል ከጥቁር አሜሪካውያን ትግል ለማጣበቅ፣ በኦሮሞ ላይ የደረሰውን በደል በጥቁር አሜሪካውያን ላይ ከደረሰው በደል ጋር ተመሣሣይነት አለው የሚል ትረካ መንዛቱ ነው፡፡ አሜሪካ ሄደህ ስታይ በጣም ለማመን የሚከብድ በደል ነው ነጮች በጥቁሮች ላይ የሠሩት፡፡ በነገራችን ላይ ጥቁር አሜሪካዊየሚባል ሠው ነው የፈጠሩት፡፡ ከአንጎላ ጀምሮ እስከ ጋና ድረስ ያለው. አፍሪካዊ በብሔር፣ በሃይማኖትና በቋንቋ የማይገናኝ ቢሆንም ነጮቹ ቋንቋውን ቀምተው፣ ሃይማኖቱን በሙሉ ወስደው፣ የእነሱ ቋንቋ ተናጋሪና ክርስቲያን ብቻ እንዲሆን ጠፍጥፈው ነበር የሠሩት፡፡ ይሄን ለማድረግ የተጠቀሙበት አመፅና መንገድ ደግሞ ለማመን ይከብዳል፡፡ ሠው እንደ ውሻ ታስሯል፣ ማን ከማን ጋር እንደ ከብት ቢዳቀል ምን ዓይነት ዘር ይፈጠራል በሚል አጥንተው ነበር ያዋለዷቸው፡፡ኢንዱስትሪያል ሪቮሉሽን የሚሉት እኮ በባሪያ ጀርባ ላይ ነው የመጣው ፤ ስኳርና ጥጥ ለማምረት ሰው እየተጨፈለቀ እኮ ነው የተሠራው፡፡ ያን ዓይነት ወንጀል ኢትዮጵያ ተከስቶ ቢሆንማ ኖሮ ምንኛ ሀብታም በሆንን? እነሱ በዛ ብቻ አልቆሙም፡፡ ነጭና ጥቁር ብለው
የሚማሩበትን፣ የሚበሉበትን፣ የሚኖሩበትን፣ የሚቆሙበትን፣ የሚሳፈሩበትን ወንበር ጭምር ለይተዋል፡፡ እኛ ሀገር እንደዚህ ዓይነት ነገር አልነበረም፣ አልሰማንም፣ አላየንም፡፡ ይሄ ቢኖር ነበር ጭቆና የሚባለው፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ በተለየ ሁኔታ ኦሮሞ ተጨቁኗል ማለትስ ይቻላል?
ታምራት፡- ማንም በተለየ አልተጨቆነም፡፡ ጨቋኝ የነበረ ወይንም ተጠቃሚ የሆነ ልሂቅ አለ፣ ሁሉንም ሲጨፈለቅ የነበረ፡፡ የመሬት አሠራሩ ከሆነ ጊዜ በኋላ ልዩነት አለው፡፡ ልዩ ጭቆና በኦሮሞ ላይ ነበረ የሚለው የውሸት ትረካን ውጤቱን እኮ አየነው፡፡ እሱ አካሄድ እነ ሌንጮ ለታና የኦዴፓ ካድሬዎችን ወደ 4 ኪሎ ካምፕ ከማስፈንጠሪያነት ባሻገር፣ የኢትዮጵያን እውነተኛ ጥያቄዎች የምግብ፣ ውሃ ጤና አቅርቦትን ችግር አልፈታም፡፡ ዛሬም ሽንኩርት የምናመርተው ከመቶ ዓመት በፊት በሚመረትበት መንገድ ነው፡፡በልቶ ማደር በዚህች የአፍሪካ መዲና በምንላት አዲስ አበባ ውስጥ አስቸጋሪ ሆኗል፡፡ ልጆቻችን ማትሪክ መፈተናቸውን ርግጠኛ በማትሆንበት ሀገር ላይ እንደመሆናችን መጠን፤ በቅድሚያ እንዲህ ዓይነት ትክክለኛ ጥያቄዎችን ነው ማውራት ያለብን፡፡ ዋናው ጥያቄ ጭቆና አይደለም፣ ያነሣኋቸው መሰረታዊ ነጥቦች ከሠላምና መረጋጋት ጋር ሲስተናገዱ ብቻ ነው፡፡ መጀመሪያ ሳትበላ፣ ሳትጠጣና የጤናህ ዋስትና ሳይረጋገጥ፤ የትኛው ማንነት ኖሮህ ነው “ማንነቴ ተነካ” የምትለው?
ግዮን፡- የዘውግ ፌደራሊዝም ወይም የክልል አወቃቀር ኢትዮጵያን ምን ያህል ጎድቷታል?
ታምራት፡- የእሱን ምላሽ ለማግኘት ዝም ብለህ ዜና ማየት ይበቃል፡፡ በእኔና አንተ ዕድሜ እንኳን ድሮ ርግጠኛ ነበርንባቸው የምንላቸው ጥያቄዎችን ጨምሮ፣ ጠንካራ ማዕከላዊ መንግሥት እንዳይኖረን አድርጓል፡፡ የዘውግ ፌደራሊዝሙን እንተቻለን ማለት ፌደራሊዝምን እንተቻለን ማለት አይደለም፡፡ ከፈለግኽ ወደ
ወለጋ፣ ጎጃም ሄደህ እነኚህን ክልሎች ፌደራል ማድረግ ትችላለህ፡፡ኹለተኛ ትልቁ ጉዳት ኦሮሚያ፣ አማራ፣ ሶማሊያ ብትል ሌሎቹ ክልሎች ሁሉ የኢትዮጵያ ሕልውና
ላይ አደጋ ማምጣት እንደሚችሉ ያውቃሉ፣ ያምናሉ፡፡ የትኛውም ሀገር በዚህ መልኩ ሊቀጥል አይችልም፤ በጣም ጉዳት አለው፡፡
ግዮን፡- መፍትሔው ምንድን ነው?
ታምራት፡- ብዙ አማራጮች አሉ፤ ቀዳሚው ግን ክልሎችን መቀናነስ ነው፡፡ እውነት ለሕዝብ የምንጨነቅ ከሆነ ለወለጋም፣ ለሸዋም፣ ለሐረርም ራሣቸውን እንዲያስተዳድሩ ወደ ፌደራል መውሰድ ይቻላል፡፡ አዲስ አስተዳደርም መፍጠር ይገባል፡፡ ሕገ መንግሥቱ እኮ መጽሐፍ ቅዱስ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ቲዎሎጂ ካምፓስ ብትሄድ የእግዚአብሔር ቃል ነው የምንለው መጽሐፍ ቅዱስ ራሱ ጥያቄ ሲነሳበት ታያለህ፡፡ይሄ ፌደራሊዝምና ሕገ መንግስት ጥያቄ ውስጥ እንደገባ አምነን፣ በዛ መንገድ ነገሮችን ማስተካከሉ ራሱን የቻለ መፍትሔ ነው፡፡ ሌላው ብዙ የማይወራው ነገር የኦዴፓ (ኦሕዴድን) እንቅስቃሴ የመሩት ሰዎች “ድል” ብለው የሚመኩበት ነገር፣ ሕገ መንግሥቱን ጥያቄ ምልክት ውስጥ እንደከተተው አያውቁም፤ ለማወቅም አይፈቅዱም፡፡ ይሄንን የዘውግ ፌደራሊዝም ተጠቅመው ካሸነፉ በኋላ፣ ማስጠበቅ እንደሚችሉ ግን ማመን አልፈለጉም፤ አሁን በእሱ ውዝግብ ውስጥ ነው ያሉት፡፡
ግዮን፡- በምን መንገድ ማስጠበቅ ይችላሉ?
ታምራት፡- ከዚህ በኋላ ይሄን ሕገ መንግሥት ለማስጠበቅ ከባድ አቅም ይጠይቃል፡፡ ያንን ብታደርግ እንኳ ሕገ መንግሥቱ በራሱ ሀገሪቱን የሚያስቀጥል አይደለም፡፡ ያለው አማራጭ ሕገ መንግሥቱን እንደገና ማሻሻል ነው፡፡እሱን ለማድረግ ደግሞ ይሄን ቃል የገቡለትንና ያንጋጉትን መንጋ መቆጣጠር ይጠይቃል፡፡ ስለዚህም ግራ ገብቷቸዋል፡፡ ሥልጣን የያዙት ሕገ መንግሥቱን በማራገብ ነው፤ በነገራችን ላይ ሕገ መንግሥቱ እዚህ ድረስ ነው ሊያደርስ የሚችለው፡፡ ከዚህ በኋላ መውደቅ ነው ያለበት፣ ማመን ነው ያቃታቸው እሱን ነው፡፡
ግዮን፡- ሕገ መንግሥቱ ግን በትክክል ማሻሻል ይቻላል?
ታምራት፡- ይቻላል፡፡ ያለውን ሕገመንግስት እንዳለ አውጥቶ ከመጣል፣ የሕገመንግሥት ኮሚሽን አዋቅሮ፣ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል እና የክልሎቹን አወቃቀር እና እንደ ፌደሬሽን ም/ቤት ዓይነቱን መቀየር ይቻላል፡፡ እሱ ነው ትክክለኛው የፖለቲካ አቅጣጫ፡፡
ግዮን፡- ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ሁሉም የክልል ምክርቤቶች መስማማት አለባቸው፣ ከእነሱ ውስጥ አንድ ተቃውሞ ከቀረበ ውድቅ ይሆናል የሚል የሕገ መንግሥት ድንጋጌ አለ፡፡
ታምራት፡- እሱ ችግር የለውም፡፡ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ ለጉዳዩ ትኩረት ቢኖራቸው ማሻሻል ይችላሉ፡፡ ሕገ መንግሥቱ ይሻሻል ከተባለ ብዙ መንገዶች አሉ፤ በመጀመሪያ ይሄን ሂደቱን የሚመሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችን መቆጣጠር ይጠይቃል፡፡ ከዛ ደግሞ ከተቃዋሚዎች ጋር በግልፅ መተባበር ያስፈልጋል፡፡በተከታይ ደግሞ ይሄ ሕገ መንግሥት አይሻሻል ለሚሉት ደግሞ ካሮትም፣ ዱላም ያስፈልጋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግን ይሄን ከማድረግ ይልቅ የውስጥ ጽዳት፣ መደመር እያሉ ማውራት ላይ
ተጠምደዋል፡፡
ግዮን፡- አሁን ያለው የብሔርተኝነት ፖለቲካን ተከትሎ የክልልነት ጥያቄ ደጋግሞ እየተሰማ ከመሆኑ አኳያ ይሄን ችግር ለመቅረፍስ መንግሥት ምን ማድረግ አለበት?
ታምራት፡- በዋነኝነት ትኩረት ያሻል፤ ትኩረት ካለህ የምትፈልገውን ለማድረግ አቅም ይኖርሃል፡፡ የተባለውን አካሄድ ደጋፊዎችና ለመሥራትም ጭምር ፍቃደኛ የሆኑ በርካታ ሰዎች አሉ፡፡ ግን እነዛን ለሀገር ለመሥራት ፍቃደኛ የሆኑ ሰዎች ማሰባሰብ ይጠይቃል፡፡ አሁን ሥራ ላይ ነው ማተኮር ያለብን፡፡ የፖለቲካ ሥራ፣ የማደራጀት ሥራ፣ አገሪቷን የማንቃት ሥራ ያስፈልጋል፡፡ይሄ ማለት ደግሞ አዲስ ፓርቲ ማቋቋም ከሆነ ማቋቋም፣ ብሔራዊ ውትድርና ማዘጋጀት ከሆነ
ማዘጋጀት ሥራን ይጠይቃል፡፡ አሁን ላይ ግን በመንግሥት ያ ነገር እየተሠራ አይደለም፡፡
ግዮን፡- አዲስ አበባ ላይ የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች በተመለከተ ብዙዎች የተረኝነት ፖለቲካ መጥቷል የሚል ስጋት ላይ ወድቀዋል፤ ይሄንስ እንዴት ታየዋለህ?
ታምራት፡- ተረኝነት ሕገ – መንግሥቱ ውስጥ ነው የተቀረፀው፡፡ ሕገ መንግሥቱ በውስጡ ያስቀመጠው መዋቅር ሳትወድ በግድህ ተረኛ እንድትሆን ያደርግሃል፡፡ ተረኝነትን ማምለጥ የምትችለው ሕገ መንግሥቱን ስትቀይር ብቻ ነው፡፡ ይሄ ሕገ መንግሥት እስካለ ድረስ የምታደራጀው፣ የምትዋቀረው በፓርቲ ነው፡፡ ፓርቲህ ሲያሸንፍ ደግሞ የአንተ ብሔር ወይም የአንተ ቡድን፣ ሀገር መምራቱ አይቀርም፡፡ይሄ እኮ ግልጽ ነው፡፡ ተረኝነት የለም የሚሉት ሰዎች ምን ጠብቀው እንደሆነ አይገባኝም፡፡ በትክክል ተረኝነት አለ፡፡ ያኔ ሕወሓት የትግራይ የበላይነት የለም እያለ ሲቀልድ ነበር እኮ፡፡ ኢሕአዴግ የቀረፀው ሕገ መንግሥት ውስጥ ተረኝነት በግልጽ የተቀመጠ በመሆኑ፣ “ተረኝነት አለ” ከማለት ውጪ ምንም ልትለው አትችልም፡፡ሕወሓትን ኦዴፓ(ኦህዴድ) ሲገፋው የኦዴፓ ደጋፊ፣ አባላትና በድርጅቱ ዙሪያ የሚያጨበጭቡ ሰዎች የበላይ ተረኛ መሆናቸው አይቀርም፡፡
ግዮን፡- በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ከሚደርሱ ጥቃቶች ጋር በተያያዘ ሰሞኑን ጠንከር ያሉ ጽሑፎችን እየጻፍክ ትገኛለህ፤ እስኪ ስለዚህ ጉዳይ እያወራ?
ታምራት፡- ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃት አሁን አይደለም የጀመረው፡፡ አብዮቱ የለኮሰው አንዱ ነገር የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ከኢትዮጵያ መንግሥት ምስረታ ጋርና ከኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ጋር ከነበራት ቀረቤታ አንፃር፣ ቤተክርስቲያንን ከሃገረ መንግሥት የመለየት ሂደቱ ሲጀመር ነው፡፡ከሕወሓት/ኦነግ መምጣት ጋርና ከአዲሱ ፌደራሊዝም መዋቀር ጋር በተከታታይነት የመጣው “በእኛ ላይ ጭቆና ይደርሣል” የሚለው ነገር፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት ቀጥሎ የኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ላይ በማተኮሩ ነው፡፡ እነዚህ ሰዎች ደግሞ ችግራቸው ኢትዮጵያ ውስጥ ጥያቄያችን ተመልሶ፣ ኢትዮጵያ ትቀጥል ሣይሆን ትፍረስ ነው እያሉ ያሉት፡፡ኢትዮጵያን ለማፍረስ ደግሞ ምንጩ ጋር ነው እየመጡ ያሉት፡፡ በአሜሪካ ቆይታዬ ያተረፍኩት አንደኛው ነገር፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ
ቤተ ክርስቲያን ለኢትዮጵያ መንግሥት ምስረታና ዘለቄታዊነት እንዴት ዓይነት ትልቅ ባለውለታ እንደሆነች መረዳቴ ነው፡፡ ይሄን ስትረዳ ደግሞ ጉዳዩ በጣም ጥልቅ እንደሆነ ይገባሃል፡፡ በኢትዮጵያ ቤተክርስቲያን ዙሪያ ያሉ ጥያቄዎችና እየተካሄደ ያለው ሰልፍ ቤተክርስቲያኒቱ በግልፅ የመንግሥት ጠበቃ እንደሆነች ተረድተው ወደ እዛ እንዲመጡ እፈልጋለሁ፡፡ለምሣሌ ላሊበላ፣ አክሱም ፂዮን፣ አብያተ ክርስቲያኒቱ የማን ናቸው? ብትል፤ ቤተክርስቲያን የኢትዮጵያ፣ ኢትዮጵያም ቤተከርስቲያን የሆኑበት ጠንካራ ግንኙነት ያላቸው ለመሆኑ ማስረጃ ይሆንሃል፡፡ ይሄንን ለማመን የግድኦርቶዶክስ መሆን አይጠበቅብህም፡፡ አሁን ቤተክርስቲያን ላይ እየደረሰ ያለው ጥቃትን ተከትሎ እየተነሳ ያለው ጥያቄ መስተጋባቱ ተገቢ ነው፡፡
ይሄ ተነሳሽነት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ በኢትዮጵያ ውስጥ ያላት ሚና ምንድን ነው? የሚለው ጉዳይን በግልጽ ያሳያል፡፡ መንግሥት ከሃይማኖት መለየት አለበት የሚለው ነገር አሁን ላይ ተጀምሯል ማለት ይቻላል፡፡ ሙስሊሞች ድምፃችን ይሰማ ብለዋል፣ ክርስቲያኖች መብታችን ይከበር እያሉ ነው፤ ስለዚህ ግልፅ የሆነ ውይይት ያስፈልገናል፡፡ ኦሮሞ፣ አማራ ከሚለው የጎጠኝነት ጥያቄ ኢትዮጵያ ወደ ተመሰረተችበት ዋናው ጥያቄና አዎንታዊ መሠረት እየመጣን ይመስለኛል፡፡
ግዮን፡- የኦሮሞ ቤተ ክህነት እናቋቁማለን የሚለው አካሄድ ራሱ ኢትዮጵያን የማፍረስ ዓላማ የለውም?
ታምራት፡- እሱ ጥያቄ በቀጥታ ዓላማው ሀገር ማፈራረስ ነው፡፡ የኦሮሞ ቤተ ክህነት የሚባል ነገር የለም፣ መንግሥታት ቢፈልጉት እንኳ፡፡ የኦሮሚያ ክልል ም/ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስና ባለስልጣናቱ ይሄን ጥያቄ ድጋፍ እየሰጡት ነው የሚመስለው፡፡ ይሄ ነገር ከፍ እያለ ሄዶ፣ ኦሮሚያን ወደ መገንጠል ጥያቄ መምጣቱ
አይቀርም፡፡ ግቡም ኢትዮጵያን ማፈራረስ ነው የምንለው ለዛ ነው፡፡በነገራችን ላይ የተነሣው የቲኦሎጂ ጥያቄም አይደለም፤ የአማኞችና የሃይማኖት ጥያቄ
ሣይሆን፣ የፖለቲካ ጥያቄ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ የሚያስፈልገው የሃይማኖት መልስ ሳይሆን የፖለቲካ መልስ ነው፡፡
ግዮን፡- ታዲያ ይሄን የፖለቲካ መልስ ማን ይስጥ ትላለህ?
ታምራት፡- አደጋው ከታያቸው ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ናቸው በመጀመሪያ ደረጃ ምላሽ መስጠት ያለባቸው፡፡ ካልሆነ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ መልሱን ይሰጣል፡፡ በጦርነትም ሆነ በሠላማዊ መንገድ መልስ መስጠቱ አይቀርም፡፡እንደ እኔ ግን ኹሉቴ ሦስቴ ቆም ብለው ጉዳዩን ቢያስቡበት ይሻላል ባይ ነኝ፡፡ ካልሆነ ግን ማንም ቢሆን በዕምነቱ ላይ ስለማይደራደር ጥያቄው መልስ ያገኛል፡፡
ግዮን፡- ኢትዮጵያ ውስጥ የዜግነት ፖለቲካ የሚያራምዱ እንዳሉ ሁሉ፣ የብሔር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑትም በጣም በዝተዋል፡፡ ይሄ ነገርስ ወዴት ይወስደናል?
ታምራት፡- የዜግነት ፖለቲካ የሚባል ነገር የለም፡፡ አሁን ባለው መዋቅር የዜግነት ፖለቲካ ፓርቲ ማቋቋም፣ በተለይ አሁን ያለውን ሕገመንግሥት የምትቀበል ከሆነ አስፈላጊ አይደለም፡፡ ማህበራዊ ንቅናቄዎች ናቸው የሚያስፈልጉት፡፡ የድምፃችን ይሰማና የኦዴፓ ንቅናቄ ውጤታማ የሆኑት ከፓርቲ ውጭ ሕዝብን ያማከለ እንቅስቃሴ ስለሆኑ ነው፡፡ሥርዓቱን እየጠየቅህ እና ግፊት እያደረግህ ሄደህ የፓርቲ ቅርጽን በኋላ መመሥረት ትችላለህ፡፡ ስለዚህ አሁን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ
ፓርቲ ከማቋቋም ይልቅ ሕዝባዊ ንቅናቄ ነው የሚስፈልጋት፡፡
ግዮን፡- ጠ/ሚ/ሩ አጋር ድርጅቶችን ባዋሃደ መልኩ ወደ አንድ ወጥ ፓርቲነት እንመጣለን ብለዋል፤ ይሄን ደግሞ ህወሓት እየተቸ ነው፤ ውህደቱ ቀሜታነት አለው?
ታምራት፡- ገና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወደ ሥልጣን እንደወጡ ከጻፍኳቸው ጽሑፎች አንዱ ጠ/ሚኒስትሩ የመደመር ሀሳቡን ወደ ፓርቲ በመቀየር ኦሮሞ፣ አማራ የሚለውን እንቅስቃሴ ተጠቅመው ፤ያሉትን ፓርቲዎች በመጨፍለቅ አንድ ወጥ ፓርቲ መመስረት አለባቸው ብዬ ነበር፤ ግን ይሄን ለማድረግ ጊዜው
አልፏል፡፡መጀመሪያ ላይ ብአዴን እና ኦህዴድ መካከል የነበረው መተማመን ትልቅ መሠረት መሆን ይችል ነበር፤ በደጋፊዎቻቸው፣ በካድሬዎቻቸውም ሆነ
በአመራሮች ደረጃ ጥሩ መተማመን ነበራቸው፡፡ በዚህ የተነሣ ይሄን ሀሳብ ለመተግበር ጠ/ሚ/ር ዐቢይ በቂ ተቀባይነት የነበራቸው ከአንድ ዓመት በፊት ነው፡፡ አሁን ስታስበው ከመርፈዱ የተነሳ አስር ዓመት ይመስላል፡፡ያኔ በቅድሚያ ተደራድረው ዕውን ማድረግ የነበረባቸው ሥራ እሱ ነበር፡፡ በኦህዴድና ብአዴን
መሀል ያለውን መተማመን ተጠቅመው፣ ደ.ኢ.ሕዴን፣ ሶ.ህ.ዴ.ፓ.ንና የመሳሰሉትን ሌሎች አጋር ፓርቲዎችን በመያዝ፣ ከሕወሓትም የተወሰኑ ሰዎችን ገንጥለው አንድ ወጥ ፓርቲ መመስረት ይችሉ ነበር፡፡ አሁን ላይ ኢሕአዴጎች ምንም መተማመን በመሀላቸው በሌለበት፣ ያውም “ብልጽግና” የሚል ፀያፍ ስም ይዞ መምጣት ከባድ ነው፡፡
ግዮን፡- የኢትዮጵያ ብልፅግና ፓርቲ የሚለው ቃል ፀያፍነቱ ምኑ ላይ ነው?
ታምራት፡- የሥነ መለኮት ወይም ሃይማኖት ጥያቄን ትተን ብልፅግናን እንዲሁ ስናየው ፀያፍ ነው፡፡ ፀያፍን የሚወስነው አንድ ማኅበረሰብ ነው፤ በክርስትናም ሆነ በእስልምና ካየነው “ሀብታም መንግሥተ ሰማያት ከሚገባ፣ ግመል በመርፌ ቀዳዳ ቢሾልክ ይቀለዋል” ብሎ ነው የሚጀምረው፡፡ ብልፅግና ሲባል ደግሞ አንድ
ሰው ሊኖረው ከሚችለውና ለኑሮ ከሚገባው የባሰ፣ የተጥለቀለቀ ሀብት ሲኖረው ማለት ነው፡፡ ትኩረቱ ደግሞ ግለሰብ ላይ ብቻ ነው፡፡አሁን ለምሣሌ ልማታዊ ፓርቲ ስንል፤ ልማት የሚለው ቃል አንተ ላይ የሚፈጥረው ግለሰብን ሣይሆን የሚኖርበትን አካባቢ፣ ሰፈሩን ማህበረሰቡን ያካተተ ነው፡፡ ብልፅግና ግን የሰው ነው፤ አካባቢን ማህበረሰብን፣ ካልቸርን ያካተተ ቃል አይደለም፡፡ እንደ እኛ ዓይነት እርስ በርሱ የተቆራኘና የተዋሃደ የሕይወት ዘይቤን የሚከተል ማህበረሰብ ውስጥ፣ ይህን ስም በፓርቲነት መጠቀም ፀያፍ ነው የሚሆነው፡፡በዛ ላይ እንደምናየው ኦዴፓ ውስጥ ራሱ መስማማት የለም፡፡ ጠ/ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ መጀመሪያ ላይ የነበራቸው ዓይነት ተቀባይነት በአማራ፣ ትግራይ፣ ኦሮሚያ፣ ደቡብ ውስጥ የለም፡፡ ከማን ጋር ነው የሚመሠርቱት? ይሄን ነገር አብረው ጀምረውታል ከሚባሉት ጋር እንኳን እውነተኛ መግባባት የለም፡፡ ወይ አይደመጡ፣ ወይ አይከበሩ፣ ወይ አይፈሩ፡፡ መንግሥት ስትሆን መወደድ ካልቻልክ መፈራትና መከበር አለብህ፡፡ ሲሆን ሦስቱን፣ ካልሆነ አንዱን መያዝ ግድ ነው፡፡ እነኚህ ነገሮች በሌለህ ሁኔታ እንዴት ነው ፓርቲ የምትመሰርተው? ምን ዓይነት ፓርቲስ ነው የሚኖርህ?
ግዮን፡- ጠቅላይ ሚኒስትሩ ርእያቸውንም ይሁን “መደመር” ያሉትን ሃሳባቸውን ተግባራዊ. አድርገው ሀገሪቱን ቀጥተኛ በምትለው መስመር ለመምራት ምን ማድረግ ነበረባቸው ነው የምትለው?
ታምራት፡- ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ በኢሕአዴግ ውስጥ የተነሱባቸውን ሕወሐትንና መሰል የስልጣንም የርዕዮት ዓለምም ተቀናቃኞቻቸውን ዳግም በማያንሰራሩበት ሁኔታ በፖለቲካው አላንኮታኮቷቸውም። ተቀናቃኞችህን ለማንኮታኮት አንደኛ የራስህን ደጋፊዎች ከስር መሰረቱ መገንባት፣ ማደራጀት፣ መገናኘት… ይህንንም የሚያስችል መዋቅር ማደራጀት ይጠይቃል። ይህን ለማድረግ ወይ ያለውን የኢህአዴግ መዋቅር መጠቀም አልያም አዲስ የመደመር ኢትዮጵያዊ ማኅበር ብሎ መዋቀር መቅደም ነበረበት። አሁን እንደምናየው ግን ጠ/ሚ ዓብይ ያሳዩት ቸልተኝነት ወይንም ትኩረት ማጣት ሕወሃት እና መሰል ተቀናቃኞችን መንፈራገጫ ትንፋሽ ሰጥቷቸዋል። ሕወሃት ቀባሪ ያጣ ሙታን ቢሆንም ከፍተኛ ችግር የመፍጠር ጥልቅ አቅም ግን አለው።
ግዮን፡- ይሄ ለሕወሓት የተሻለ የልብ ልብ አይሰጥም?
ታምራት፡- ሕወሓት ሞቷል፣ ቀባሪ ነው ያጣው፡፡ ሁለት ሦስት ዓመት ቆይቶ ዳግም ድራሹ ይጠፋል፤ ዝም ብሎ ነው ለመውተርተር የሚሞከረው፡፡
ግዮን፡- አዲሱ ፓርቲም ዕድል ከሌለው፣ እንደ አንተ ምልከታ የኢትዮጵያ መጻዒ ሁኔታ ምን ይሆናል?
ታምራት፡- የሚቀጥሉት ከሦስት እስከ አምስት ዓመታት በጣም የጭንቅ ዓመታት ይሆናሉ፡፡ ግጭቱ እየጨመረ ይመጣል፡፡ አሁንም እንደሚታየው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት የሚሰባሰብ ይመስለኛል፡፡ በርግጥ የተወሰኑ ክልሎች ከቁጥጥሩ ውጭ ናቸው፤ በቀጣይም ከቁጥጥሩ ውጭ የሚሆነው ግዛት እየጨመረ
ይመጣል፡፡ ከዛ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት የሚሰባሰብ ይመስለኛል፡፡ ጊዜውን ጠብቆ የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት መልሶ ይነሳል፡፡ አይቀርም፤ ሦስትም ዓመትም ይሁን አስር ዓመት ይፍጅ ሪቫይቭ ያደርጋል፡፡ያኔ ግን እያንዳንዱ ጎጠኛ ምን ይውጠዋል? ኢትዮጵያን አንድ የሚያደርግ ዳግማዊ ምንሊክን እጠብቃለሁ፡፡ የምንናፍቀውን አንድነታችን የሚመልስ ሳልሣዊ ምንሊክ እጠብቃለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ታሪክ ትናንትናን ብቻ አይደለም ነገንም ነው የሚነግረን፡፡ ይሄ እውነታ ይደገማል ብዬ አምናለሁ፡፡
ግዮን፡- እናመሰግናለን፡፡
Filed in: Amharic