>

የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ነገር (አልይ እንድሬ)

የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል ነገር

 

አልይ እንድሬ

የዓለም የኖቬል ተሸላሚውና የአረንጓዴው አቢዮት አባት በመባል የሚታወቀው ኖርማን ቦርሎግ “ሆዱ ባዶ የሆነ ህዝብ ይዘህ ሰላም የሆነች ዓለም መፍጠር አይቻልህም“(“You cannot create a peaceful world on empty stomachs,”) ማለቱ ይታወሳል፡፡ የምግብ ዋስትና አለመረጋገጥ የዓለማችን ዋና አሳሳቢ ችግር ሲሆን እንደ ስደት ለመሳሰሉ ተጨማሪ ችግሮች ማጋለጡ ደግሞ ችግሩን ይበልጥ ድርብርብ ያደርገዋል፡፡ የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ አለማቻል በተለይ በማደግ ላይ ያሉ ሀገሮች ከባድ ተግዳሮት እንደሆነ ቀጥሏል፡፡ የግብርናና ምግብ ድርጅት (FAO) እንደ እኤአ በ2017 ዓ.ም ባቀረበው ሪፖርት በዓለም 10.9%፣ በአፍሪካ 20.4% እንዲሁም በምስራቅ አፍሪካ 31.4% የሚሆነው ህዝብ በምግብ እጥረት የሚሰቃይ መሆኑን ገልጧል፡፡ በFAO (2018) ገለፃ መሰረት የምግብ ዋስትና አለ ወይም ተረጋገጠ የሚባለው እያንዳንዱ ዜጋ፣ በማናኛውም ወቅት ንቁና ጤናማ ህይወት ለመምራት አስፈላጊ የሆኑ ንጥረ ነገሮችና የምግብ አማራጮች በበቂ ሁኔታ ተሟልተውለት ሲገኝ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ኢትዮጲያን ስንመለከት 10% ኢትዮጲያውያን በከፋ የምግብ እጥረት የሚሰቃዩ ሲሆን ድርቅ ወይም የዝናብ አጥረት በሚከሰትበት ወቅት አሃዙ ወደ 15% ከፍ እንደሚል ተመልክቷል (FAO ,2018)፡፡ በተጨማሪም በ2018 ዓ.ም (እኤአ) ዘ ኢኮኖሚስት ኢንቴሊጀንስ ዩኒት(EIU) በመባል የሚታወቀው ድርጅት ባወጣው የዓለም የምግብ ዋስትና አመልካች(GFSI) ሰነድ መሰረት ንፅህናው በተጠበቀና ጥራት ባለው የምግብ አቅርቦት ራስን ከመቻል አኳያ ከ113 አገሮች ውስጥ ኢትዮጲያ 100ኛ ደረጃ ላይ መሆኗን አሳይቷል፡፡ በኢንቴሊጀንስ ዩኒት ኢንዴክስ (EIU index) መሰረት ኢትዮጲያ 28.8% የሚሆነው ህዝቧ ለምግብ እጥረት ተጋላጭ የሆነባት አገር ናት፡፡
እንግዲህ ይህንን ለመፍታት አንዱ መንገድ ግብርናውን ማዘመን ነው፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት ነው የደሴ ቲሹ ካልቸር ማዕከል በከፍተኛ ወጭ በክልሉ መንግስት የተገነባው፡፡ የማዕከሉ ግንባታ በ2011 ዓም የተጠናቀቀ ሲሆን የቀድሞው የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር አምባቸው መኮንን በተገኙበት ሰኔ 4 ቀን 2011 ዓም በይፋ ተመርቆ ወደስራ መግባቱ ይታወቃል፡፡

ማዕከሉ ምርታማና በገበያ ተፈላጊ የሆኑ የአትክልትና ፍራፍሬ ተክሎችን ጨምሮ በሌላ መንገድ በቀላሉ የማይራቡ ጠቃሚ እፅዋቶችን ከበሽታ ፅዱ በሆነ መንገድ በላቦራቶሪ በብዛትና በጥራት በማምረት ምርጥ ችግኞችን በሚፈልገው መጠንና በተመጣጣኝ ዋጋ ለአርሶ አደሩ በማቅረብና ጥራት ባለው የዘር (የችግኝ) አቅርቦት ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የአርሶ አደሩን ህይወት ማሻሻል ተቀዳሚ ዓላማው ሲሆን ከሀገር ውስጥ ፍጆታ የተረፈውን ለውጭ ገበያ በማቅረብ በገቢ ምንጭነትና የውጭ ምንዛሬን ማስቀረት ባይቻል እንኳን በመቀነስ ረገድ አስተዋፅኦ ማበርከት ተጨማሪ ዓላማው ነው፡፡ በተቀመጠለት ዓላማ ልክ ከተጓዘ ማዕከሉ የባዮቴክኖሎጅ የልህቀት ማዕከል ሆኖ ሊያገለግል እንደሚችልም ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ይህ ማዕከል እንዲቋቋም የበርካታ ሰዎች አስተዋፅኦ እንዳለበት እሙን ነው፡፡ ይሁን እንጅ ልጅ አድጎ ለሀገር-ለወገን ቤዛ ይሆናል በሚል ተስፋ የእድገቱ ሂደት እንዳይደናቀፍ ሊደረግለት በሚገባው ጥንቃቄና ክትትል ልክ (ምናልባትም ከዛ በላይ) የዚህ ተቋም ግንባታ ተጀምሮ እስኪጨረስ ድረስ ስራው እንዳይስተጓጎል ቅርብ ክትትል በማድረግ፣ ዘወትር በአካል ቦታው ድረስ ተገኝቶ የደረሰበትን ደረጃ በማየትና ጉድለቶች እንዲስተካከሉ በማድረግ ዛሬ ለደረሰበት ደረጃ እንዲደርስ የማይተካ እገዛ በማበርከት ደረጃ ግን የቀድሞውን ርዕሰ መስተዳድር አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ያህል አስተዋፅኦ ያበረከተ የለም፡፡

አቶ ገዱ እንዳይን ብሌናቸው ይመለከቱት የነበረው ይህ ማዕከል አሁን እሳቸው ለስራ ክልሉን ለቀው ከሄዱበት ጊዜ ጀምሮ በቅርብ እየተከታተለ ጉድለቶችን የሚያርምና እገዛ የሚያደርግ ሙሉ በሙሉ የለም ለማለት የማያስደፍረውን ያህል አለ ለማለትም ሆድ የሚያስነፋ አይደለም፡፡ በአሁኑ ሰዓት ማዕከሉ በቦረድ ይተዳደራል በዋና ስራአስኪያጅ ይመራል ከሚል ባለፈ ከሌሎች በሲቪል ሰርቪስ ከሚተዳደሩ መ/ቤቶች በተለየ ሁኔታ በቦርድ በመተዳደሩ ለማዕከሉ ሰራተኞች ያስቀመጠው ዝርዝር የመተዳደሪያ ደንብና መመሪያ (የሰራተኛው መብትና ግዴታዎች፣ የእርከን ጭማሪ፣ የደረጃ እድገት፣ … ፣ወ.ዘ.ተ) የለም፡፡

ጥቂት ባለሞያዎችን በመቅጠር ስራ የጀመረው ይህ ማዕከል የታለመለትን ዓላማ ከግብ ያደርስ ዘንድ በግልፅ የተቀመጠ ዝርዝር የመተዳደሪያ ደንብና መመሪያ ሊወጣለት ይገባል፡፡ አዳዲስ ብቁ ሰራተኞችን ለመሳብ ብቻ ሳይሆን አሁን ያለው ሠራተኛ ግዴታውን ለመወጣት መብቱንም ለማወቅና ለመጠቀም ይችል ዘንድ የማዕከሉ መዋቅራዊና አስተዳደራዊ ሁኔታ ትኩረት ያሻዋል ፡፡

Filed in: Amharic