>
4:53 pm - Saturday May 24, 5986

ድሬ - እ- ዳዋ  (እንዳለጌታ ከበደ)

ድሬ – እ- ዳዋ 

እንዳለጌታ ከበደ
እንደመነሺያ
መገለጫቸው፣ ግልጽነት ነበር፤ ነጻነት ወዳድነት ነበር፤ አብዝቶ መጨነቅን አለመውደድ ነበር፤ ተካፍሎ መብላትን ነበር፡፡ እንደሚባለው፣ ሕዝቡ ተጠራጣሪነት የለውም፤ ንፉግነት የለውም፡፡ የትኛው ከያኒ ነው፣ በየኮንሰርቱና በየአልበሙ ውስጥ የድሬን ሰው፣ የሐረርን ሰው፣ የወሎን ሰው ያላሞካሸ?
….
ዛሬስ፣ እንደምነሽ ድሬ?
ድሬ ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ ከተሞች፣ ለብዙ ዓመታት የኖርኩባት ያህል ትመቸኛለች፡፡ እንግድነት አይሰማኝም፡፡ ከተማዋን በተደጋጋሚ ጊዜ የማየት ዕድል የገጠመኝ ቢሆንም፣ ሰሞኑን ግን፣ እንደአብዛኛው የኢትዮጵያ ከተሞች፣ ራሷን ከሚመጣው አደጋ ለመካከለል ምን ማድረግ እንዳለባት የምታስብ መስላ ነበር ያገኘኋት፡፡ የመጠራጠር መንፈስ በየአካባቢው ሰፍኗል፡፡ አባቶቻቸው ሃይማኖትና ዘር ሳይጠያያቁ፣ ምሰሶና ማገር እየተቀባበሉ ያነጹዋቸው ቤተ እምነቶች፣ ዛሬ ዛሬ ልጆቻቸው፣ ‹መሬቱ የእኛ ነበር› የሚል ምክንያት እያነሱ፣ ለከተማው ሰዎች ሀዘን፣ ለማኅበራዊ ሚዲያዎች የወሬ ምንጭ እየሆኑ ነው፡፡ ጥቂቱ በፈጠረውና በሚፈጥረው ሁከት፣ ከተማዋ ያልተገባ ስም እየተሰጣት፣ የቀደመ ክብሯንም እያደፈረሰባት ነው፡፡
እርግጥ ድሬዳዋ መልከ ብዙ ናት፤ ጽዱ ናት ደግሞ፡፡ በቆየሁባቸው ቀናት፣ አዕምሯቸው የታወከና መንገድ ዳር የሚያድሩ ግለሰቦች እንኳን፣ እነሱ ራሳቸው ቆሻሻ ለብሰው፣ ቆሻሻ መስለው፣ የሚቀመጡባትና የሚያድሩበት ቦታ ግን፣ ከቆሻሻ የጸዳ እንዲሆን፣ ጉልበታቸውን ሲያደክሙ በገረሜታ አስተውያለሁ፡፡ ይህንንም ዐይቼ፣ ‹ኅሊናቸው በአንዳች ነገር ታውኮ እንኳ፣ ለከተማቸው አንዳች ግዴታ እንዳለባቸው አልዘነጉም› ብያለሁ ለራሴ፡፡
….
ድሬ ስለ ማንነቷ ያልተነገረላት ከተማ
ወዳጄ ኮለኔል ልመንህ እምሩ፣ ስለድሬዳዋ ሕዝብ ጀግንነት ሲናገር በቁጭት ነው፡፡ ስለምስራቅ ጦርነት በተነሳ ቁጥር ጄኔራል እንቶኔ፣ ኮለኔል እገሌ እንዲህ አድርጎ፣ እንዲህ ዓይነቱን ጀብዱ ፈጽሞ ሲባል፣ ‹የድሬዳዋ ሕዝብ ተጋድሎስ ለምን አይነገርም?› ይላል፡፡ ኮለኔል ልመንህ እንደሚለው፣ በ1960ዎቹ መጨረሻ ሶማልያ በከፈተችው ጦርነት ሕዝቡ በባዶ እጁ፣ ስልጠና ሳይወስድ፣ ከኢትዮጵያ ጦር ጋር በመሆን፣ አኩሪ ገድል ፈጽሟል፤ መሳርያ ማርኮ ለወገን ጦር አስረክቧል፡፡ ‹ከእነዚያ ለድል ካበቁን ሰዎች መካከል እገሌ የተባለ አንድም ሰው አናውቅም፤ እሱም እወቁኝ ብሎ እጦሩ ፊት አልቀረበም፤ ላገሩ ብሎ ነውና ሰዉነቱን ያጎደለው፣ ደሙን ያፈሰሰው ሹመት ሽልማት እንዲሠጠው፣ ወይም ሌላ ጥቅማ ጥቅም ፍለጋ እኛ ፊት አልቀረበም፡፡ ጀግና ሕዝብ ነው፤ ተፈትኗል፤ የሚቆጨኝ እንደ ሕዝብ በመንግሥት በኩል የጀግንነት ሜዳሊያ አለመሸለሙ፡፡ አለመሸለሙ ብቻ አይደለም፤ አልታወቀለትም፡፡ እኛ፣ ያን ሁሉ ፍልሚያ ውስጥ ስንገባ፣ ሕዝቡ እንደሚሸሽና ጓዝ ጉዝጓዙን ሸክፎ እንደሚፈረጥጥ  እርግጠኞች ነበርን፤ ግን አላደረገውም፤ ከዚህ በላይ ጀግንነት ከየት አለ? ሰሜንም ምስራቅም ተዋግቻለሁ፤ ከበድ ባሉ የጦር አውድማዎች ተሳታፊ ሆኛለሁ፤ እንደ ድሬዳዋ ሕዝብ፣ የነጻነትን ምንነት የተገነዘበ፣ አገሩን መውደዱን በተግባር ያሳየ ኣላውቅም፤ እኛ ግን ድሉን ከሕዝቡ ነጥለን ለብቻችን ወሰድነው፡፡ › ብሎኛል፡፡
የድሬ ዳዋ ሕዝብ እንዲህ ዓይነቱን አባቶቹና ታላቅ ወንድሞቹ ስለሠሩት ጀብዱ የሚያውቅ አይመስልም፤ ወይም ለማወቅ ጋት የሚጓዝ አይመስልም፤ ወይም የሕዝቡ ታሪክ እንዳይታወቅ ሲደረግም ለምን ብሎ አልተከላከለም፡፡
….
ወጣቶቿን መታደግ ያልሆነላት ከተማ! 
ድሬ፣ ለስልጣኔ ባይተዋር አይደለችም፡፡ ከአዲስአበባ የተቀበለቻቸው ቴክኖሎጂዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ ለአዲስአበባ ፊደል ያስቆጠረቻቸው ስልጣኔዎችም አሏት፡፡ ከመቶ ዓመታት በፊት፣ ከአዲስ አበባ ቀድማ ማተሚያ ቤት ነበራት፤ ሚሲዮናውያን የሚያሳትሙት ጋዜጣም ነበራት፡፡ በእግር ኳሱም፣ በኪነቱም የደመቀ ስም ያላቸው ትጉሃንን ማፍራት የቻለች ናት፡፡ ሰዎቿም ስልጣኔን ለማጣጣም ቅርብ መሆናቸውን የአፈንዲ ሙተቂን፣ ‹ኡመተ ፈነናን ኡመተ ቀሽቲ› የተሰኘውን መጽሐፍ ማንበብ በቂ ነው፡፡ ድሬዳዋ ያበቀለቻቸው ከያንያን ብዙ ናቸው፡፡ በፊት በፊት እነእገሌ ተብለው የሚጠሩ ጉምቱ ስሞች ነበሯት፡፡ አሁንም፣ በየጥጋጥጉ ተወሽቀው ያሉ ከያንያን እንዳሏት ባውቅም፣ ከተማዋ የት እንዳሉ፣ ምን እንደሠሩና ሊሠሩ እንዳሰቡ ለማወቅ ግዴታዋ መሆኑን አላወቀችም፡፡ አልሠራችባቸውም፤ አልሠሯትምም፤ሙያቸውን የሚያዳብሩበት ስልጠና አይመቻችላቸውም፤ ከዩኒቨርስቲው ጋር በመተባር ነጻ የትምህርት ዕድል የሚያገኙበት መንገድም አትዘረጋላቸውም፡፡
….
ረብሻ በተነሳ ቁጥር፣ በተለይ ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ ከተሞች፣ ተማሪዎች የሚወጡበትን ሰዓት ጠብቀው፣ ተማሪዎቹ የተቃውሞው ወይም የድጋፍ ሰልፉ አባል እንዲሆኑና በሆታና በጭፈራ ታጅበው የእንዲሳተፉ የሚደረገውን ነገር ማቆሚያ ሊበጅለት ይገባል፡፡ በተለይ በኦሮሚያ ክልል በአንዳንድ ከተሞች ተማሪዎች መጠቀሚያ እየሆኑ ነው፤ በማይገባቸው ፖለቲካ ውስጥ የመሪ ተዋናይነት ሚና እንዲጫወቱ እየተገፋፉ ነው፡፡ ትምሕርት ቤቶቹ – የመንግሥትም ሆነ የግሎቹ – እምቢ ለማለት አቅም የላቸውም፡፡ ሰልፈኞቹ ከመንግሥት የበረታ ጡንቻ እንዳላቸውም ከማሳየት አይሰንፉም፡፡ የድሬዳዋ ተማሪዎችም ስለማያውቁት ጉዳይ፣ በቅጡ ስላተገነዘቡት ጥያቄ እንዲጮሁ እየተገደዱ ነው የሚል ቅሬታ ከየወላጆቹ አንደበት ይደመጣል፡፡
….
ኮንትሮባንዲስቶችና ‹ፖለቲከኞች›
ድሬ ዳዋ ከነበርኩባቸው በአንዱ ቀን፣ ወደ ከተማዋ ከሚያስገቡ በሮች መካከል አንዱ ተዘጋ፡፡ መንገዱ የተዘጋው ለውስን ደቂቃዎች ነበር፡፡ በሮቹ ሊዘጉ የቻሉት፣ ድሬ ከሚያዋስኗት መለስተኛ ከተሞች መካከል በአንዱ ጠብ ተነስቶ ነው፡፡ ጠቡ፣ በሁለት ብሄሮች መካከል የተለኮሰ ነው ተባለ፡፡ ቤቶችም ተቃጠሉ፤ ሳንጃዎችም ተመዘዙ፡፡ በኋላ፣ አንድ የከተማው ባለስልጣን እንደነገረኝ፣ የከተማው ጸጥታ አስከባሪና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት፣ ረብሻው እንደተፈጠረ፣ በፍጥነት ያመሩት ወደኬላ ነበር፤ ኬላውን ዘጉት፤ ታጣቂዎችም ጥብቅ ቁጥጥር አደረጉ፤ ምነው ቢባል በልምድ እንደቀሰሙት እንዲህ ዓይነቱ ረብሻ ሲነሳ፣ በኮንትርባንድ ሊያልፍ የተዘጋጀ ትልቅ ነገር አለ ማለት ነው፡፡ ኮንትሮባንዲስቶቹ፣ ለጥቂት ወጣቶች ገንዘብ ‹ይረጫሉ›፤ ገንዘብ ‹የተረጨላቸው› ሁለት ሦስት ሰዎች ደግሞ በወሳኝ ቦታዎች ቤቶችን ያቃጥላሉ፤ ረብሻ ይፈጥራሉ፤ ጠቡንም ‹ብሔር ተኮር› ያደርጉታል፤ በኦሮሞ ወይም በሶማሌ ያሳብባሉ፡፡ ከተማዋ ስትተራመስ ፖለሶችም ሆኑ፣ የአስተዳደር ሰዎች ቀልባቸው ሕዝቡን ወደማረጋጋት ሲያተኩር፣ በግርግሩ መሃል ኮንትሮባንዲስቶቹ  ያመልጣሉ፡፡ አሁን ግን የድሬ ዳዋና የአካባቢው ሰዎች፣ እንዲህ ያለውን የብልጣ ብልጥና ሌላውን የማስፈጀትና የማስፈረጅ መንገድ ‹ዕቁቡ የተበላ› ብለውታል፤ ቤት ሲቃጠል ተኩስ ሲጋጋል እየሮጡ ኬላውን ያጠናክራሉ፤ ተሳክቶላቸዋልም፡፡
….
ማጠቃለያ
ድሬዳዋ ድምጽ ትፈልጋለች፡፡ መታመሟን አውቆ የሚጮህላት ሰው ትፈልጋለች፡፡ በየሰዉ ፊትና ልብ ውስጥ የሆነ ሊፈነዳ የተቃረበ ነገር ያለ ይመስላል፡፡ አዳኝና ታዳኝ በሚፋጠጠቡበት ጠባብ መንገድ ላይ እርስ በርስ የተገናኙ ይመስል፣ በየጠረጴዛው ዙርያ የሚወራው፣ ስለስጋት ነው፡፡ ‹እገሌ የተባለው ብሔር እንዲህ ሊያደርግ ስላሰበ እገሌ የተባለው ብሄር ደግሞ ራሱን ለመካከል እየተዘጋጀ ነው› ይባላል፡፡ ወሬው ክንፍ አብቅሎ ይበራል፤ ከየት እንደመነጩ የማይታወቁ ወሬዎች ሕዝቡን ያሸብሩታል፡፡
ድሬ እዳ በዝቶባታል፡፡ ድሬ እዳዋን እንድትከፍል የምትገደደው ደግሞ ያልተበደረችውን ነው፡፡ ‹ፖለቲከኞቿ› አስጨንቀዋታል፡፡ ነግደው ሊያተርፉባት ቸኩለዋል፡፡
ያም ሆኖ ድሬ ‹ተመራጭም ተደማጭም› ከተማ የነበረችበት ጊዜ ተመልሶ እንደሚመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
Filed in: Amharic