>
5:30 pm - Tuesday November 2, 2326

የብልፅግና ፓርቲ የበለፀገ አስተሳሰብ ውጤት ነው ( ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

የብልፅግና ፓርቲ የበለፀገ አስተሳሰብ ውጤት ነው

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ
ኮተቤ ሜትሮፖሊታን ዩኒቨርስቲ

 

ህወሃት አገር የማፍረስ የተንኮል አስተሳሰቡን “ኢህአዲግ ” በሚለው የብሄር ፓርቲ ስብስብ ሸብቦ ለሁለት አስርት አመታት በላይ ሲጠቀምበት የነበረ ቃል ሲሆን ለስርዓቱ ደጋፊዎች እንደ ድል ቀንዲል የሚጠቀሙበት ስያሜ ነበር፡፡ በአንፃሩ ደግሞ ኢትዬጲያዊነትን ለሚያራምዱ የነፃነት ታጋዬች “ኢህአዲግ ” የሚለው ቃል ፅዩፍ መጠሪያ ነበር፡፡ አንጋፋዋ ፀሀፊ ርዕዬት አለሙ በፀረ-ሽብር ወንጀል ተከሳ “አሸባሪ ብለው ሲጠሯት “ምንም ስያሜ ስጡኝ “ኢህአዲግ ” የሚለው ስያሜ ግን እንዳትለጥፉብኝ ያለችው አባባል ለዚህ ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ “ኢህአዲግ” ከሚለው መጠሪያ ጀርባ ያለውን የግፍ አሰራር በመፀየፍ ይህ ስያሜ እንዲለጠፍባት ርዕዬት አለሙ በዚህ ስም መጠራትን አልፈለገችም፡፡

ያ ጨቋኝና ከፋፋይ የ”ኢህአዲግ” ስርዓት ጊዜው ደርሶ እየከሰመ መምጣቱን ትክክለኛ ማሳያው መለስ በኃይለ ማሪያም ወይም ኃይለ ማሪያም በዶ/ር አብይ መተካቱ ሳይሆን ከብሄር የፓርቲ ግንባር ወደ አንድ አስተሳሰብን ማዕከል ወደ አደረገ የፖለቲካ ፓርቲ መቀየሩ ነው፡፡ የብሄር ፖለቲካ ወይም ብሄርን ያማከለ የፌደራል ስርዓት በየትኛውም አገር የማይተገበር፣ ግጭትን የሚጋብዝ፣ አገርን የሚከፋፍል፣ አንድነትን የሚያዳክም፣ ጥርጣሬን እና አለመተማመንን የሚያጎለብት እንደሆነ ከመነሻው በርካታ የዘርፉ ተመራማሪዎች ገልፀው ነበር፡፡ ዳሩ ግን የስርዓቱ መሰረታዊ ዓላማ አገርን ማፍረስ ስለሆን ይህን እኩይ ዓላማውን ለመተግበር የተጠቀመበት ብቸኛው ስልት የብሄር ፖለቲካን ማራመድ ነበር፤ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ይህንኑ እንዲያራምዱ እገዛ ሲደረግላቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ስርዓቱ የብሄር ፓርቲ መፈልፈያ ማሽን(Incubator) ሁኖ ቆይቷል፡፡ ስለሆነም ሰዎች በአስተሳሰባቸው ሳይሆን በብሄር ማንነታቸው እየተደራጁ ለአክራሪ የብሄር ፖለቲከኞች መሳሪያ ሁነው ቆይተዋል፡፡

አሁን ግን የድሮው “ኢህአዲግ ” የፓርቲ ውህደትን ፈጥሬ አንድ አገራዊ ፓርቲ ልሆን ነው ሲል ሊወደስ ሲገባው ለምን ይወቀሳል? ውህደቱ በፅንፈኞች የብሄር ፖለቲከኞች ላይ ለምን ስጋትን ፈጠረ?

ሀሳብ የሌላቸው ሰዎች በሀሳብ ልዩነት ላይ መደራጀት አይችሉም፡፡ ሀሳበ-ድኩማን የሆኑ ግለሰቦች ዕንቁ የሀሳብ ልዕልና አይታይባቸውም፤ ሀሳብ የመከነባቸውና የሀሳብ – መካን የሆኑ ዜጎች ዘርን/ብሄርን ባማከለ የፖለቲካ ስርዓት ውስጥ መዋኘትን ይሻሉ፤ በሀሳብ ልዩነት ላይ ከመደራጅት ይልቅ በብሄር መደራጀትን ይመርጣሉ፡፡ የብሄር አቀንቃኞች ወይም የብሄር አክቲቪስቶች የሰፈር የጎበዝ አለቃ መሆንን እንጅ ለአገር የጎበዝ አለቃነት ስለማይመጥኑ ነው፡፡

Filed in: Amharic