>

የዳግማዊ ምኒልክ አዋጅ!... ሠራተኛውን በሥራው የምትሰድብ ተወኝ!!! (ጳውሎስ ኞኞ)

የዳግማዊ ምኒልክ አዋጅ

 
ሠራተኛውን በሥራው የምትሰድብ ተወኝ!!!
ከዚህ ቀደም ብረት ቢሠራ ጠይብ ሸማ ቢሠራ ሸማኔ ቢጽፍ ጠንቋይ ቤተክርስቲያን ቢያገለግል ደብተራ እያላችሁ አርሶ ነጩን ከጥቁር የሚያገባውን አራሽ ከዘውድ ይበልጣል የሚባለውን ¨ገበሬ¨ እያላችሁ ነጋዴ ነግዶ ወርቁን ግምዣውን ይዞ ቢገባ ¨ አንተ ነጋዴ ገጣባ አጣቢ¨ እያላችሁ በየሥራው ሁሉ ትሳደባላችሁ፤ ልጁ ምናምን ሥራ የማያውቀው ሰነፉ ብልሁን እየተሳደበ አስቸገረ፤ ቀድሞም ይህ ሁሉ ፍጥረት የተገኘው ከአዳምና ከሄዋን ነው እንጂ ሌላ ሁለተኛ ፍጥረት የለም።
ይህ ሁሉ ካለመማር የተነሳ ነው፤ አዳምንም ብላ በአፈ ገጽከ ብሎታል ይህ ከቀረ ሁሉ ቦዘነተኛ ከሆነ መንግሥት የለ ሀገር የለ፤ በወዲያ ሀገር ግን በኤሮፓ ሁሉ አዲስ ሥራ አውጥቶ መድፍ፣ ነፍጥ፣ ባቡር ቢሠራ ሌላውንም እግዚአብሔር የገለጠለትን ሥራ ሁሉ ቢሠራ መሀንዲስ እየተባለ እየተመሰገነ ሠራተኛውም ብዙ ይጨመርለታል እንጂ በሥራው አይሰደብበትም፤ እናንተ ግን እንደዚህ እየተሳደባችሁ ሀገሬን ባዶ ልታደርጓትና ልታጠፏት ነው።
እንግዲህ ግን እንዲህ ብሎ የተሳደበ እኔን የሰደበ እንጂ ሌላውን መስደብ አይደለም፤ ዳግመኛ ግን ሲሳደብ የተገኘ መቀጫውን አንድ አንድ ዓመት ይታሰራል፤ ሹማምንትም አስረህ ዓመት ለማስቀመጥ የሚቸግርህ የሆነ እንደሆነ አስረህ ወዲህ ስደድልኝ።
ጥር ፲፯ ቀን ፲፱፻ ዓ.ም.
ከዚህ አዋጅ እንደምንረዳው የምኒልክ ሠራተኛ መውደድ ከማንኛውም ንጉሥ የበለጠ ነው፤ ማንኛውም ንጉሥ ከማንም በላይ ዘውድ ነው ሲል፤ ምኒልክ ግን ከዘውድ በላይ ገበሬ ነው ማለታቸው የተለየ ያደርጋቸዋል፤ ሠራተኛን የሰደበ እኔን ሰደበ ማለታቸውም ምኒልክ ምን ያህል ሠራተኛ ወዳድ እንደነበሩና ሠራተኛ እንደሆኑ ይገልጻል።
ምኒልክ ከእርሳቸው በፊት ያልነበረ ለሠራተኛ ደሞዝ መክፈል የጀመሩ ናቸው፤ የእንጀራ ቤት ሠራተኞች ማለት እንጀራ ጋጋሪዎች፣ ሥራ ቤቶች፣ አቡኪዎችና ይህንን የመሳሰለ ሥራ የሚሠሩ በዓመት ፲፯ ጥሬ ብርና ሦስት ሜትር አቡጀዲ ብትን ጨርቅ ለእያንዳንዳቸው ሲሰጥ በየወሩም ስድስት ቁና እህል ይሰጣቸዋል፤ በየቀኑም ጠቅላላው የቤተመንግሥቱ ተራ ሠራተኛ አንድ ጋሬና አንድ ማኛ እንጀራ አንድ ትልቅ ጭልፋ የሥጋ ወጥ (ጦም ከሆነ የክክ ወጥ) ለቁርስ ሲሰጥ ለምሳ ድርጎው ያው ሆኖ አንድ ኩባያ ጠላ ይጨመራል፤ ራትም እንደዚሁ ነው።
ብረት ቀጥቃጮች በየወሩ አንዳንድ ብር ደመወዝ ሲኖራቸው በዓመት ከ25 እስከ 33 ብር ድረስ በጉርሻ መልክ ይሠጣል የወር ቀለብ እህልና የዓመት ልብሳቸውም ከደሞዛቸው ሌላ ይሠጣል፤ ድንጋይ ጠራቢዎች በየወሩ አንዳንድ ጥሬ ብር ደሞዝና እህል ሲሰጣቸው በዓመት እያንዳንዱ ሦስት ሜትር አቡጀዲ ይታደላቸዋል።
ለድንጋይ ፈላጭ ወይም ቀጥቃጭ አለቆች በየወሩ ሦስት ብር ተኩል ሲከፈል፤ ድንጋይ አጠራረብን ለሚያስተምሩ ለሁለት አረቦች ለአንደኛው ዘጠና ብር ለአንደኛው መቶ ብር ይከፈል ነበር።
በሥጋጃ ሥራ ለተሰማሩ ሴት ሠራተኞች የወር ደሞዛቸው ሁለት ብርና አንድ አሞሌ ጨው ሲሆን በዓመት ሁለት ጊዜ ልብስ ይሰጣቸዋል።
***
የሥራ ማቆም አድማና የንጉሰ ነገስቱ ፍትሀዊ ምላሽ!!!
ሥራ የማቆም አድማ የተጀመረው በምኒልክ ዘመን ነው፤ የእንጦጦ ማርያም ቤተክርስትያን እንደገና ታድሳ በምትሠራበት በ1898 ዓ.ም. በታህሣሥ ወር ሳይታሰብ የቤተክርስቲያኑ ሥራ ቆመ፤ ሥራው በምን ምክንያት እንደቆመ ቢጠየቅ ሠራተኞቹ ግሪኮች ደሞዛቸው ስላልተከፈላቸው ሥራ ማቆማቸውን ምኒልክ ሰሙ፤ ወዲያውኑ ሥራ ያቆሙትን ግሪኮች አስጠርተው አባብለውና ደሞዛቸውን ከፍለው ሥራው እንዲጀመር አደረጉ፤ ሥራው ሳይቆም ደሞዛቸው እንዲከፈላቸው ለምን እንዳልጠየቁ ምኒልክ ግራ ገብቷቸው ሳለ፤ በአጠገባቸው የነበሩ የውጭ ሀገር ሰዎች “በፈረንጅ ሀገር ደንቡ ሥራ ማቆም ነው” አሏቸው፤ ምኒልክም “የፈረንጅ ፈሊጡ ሁሉ ድንቅ ነው፤ የጉልበቱን ዋጋ በጉልበቱ ለማግኘት ማሰቡ ነው” ብለው መለሱ።
ይህ የምኒልክ መልስ አሰጣጥ እንደ አዋጅ ሆኖ ስለተቆጠረ በአዲስ አበባ ያሉ ግንብ ገንቢዎች በሙሉ በ1899 ዓ.ም. በግንቦት ወር የመገንባት ሥራቸውን ከዳር እስከዳር አቆሙ፤
ቢጠየቁም “የምንገነባበት ዋጋ ስላነሰን ነው አሉ” ይህን የሰሙት ምኒልክም “አነሰን ካሉ ይበቃናል የሚሉትን እየሰጣችሁ አሠሯቸው” ብለው ስላዘዙ የገንቢዎች የመገንቢያ ዋጋ ከፍ አለ።
አጼ ምኒልክ
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic