>
5:09 pm - Monday March 3, 4775

አይ ሥልጣኔ¡¡¡ ኮሮናቫይረስ ስንቱን አሳየን?!? (ሳምሶም ጌታቸው)

አይ ሥልጣኔ¡¡¡ ኮሮናቫይረስ ስንቱን አሳየን?!?

 

ሳምሶም ጌታቸው
እነሱ በአፍሪካውያን መካከል የሚፈጠሩ ቀላል ግጭቶችን ሳይቀር ሆን ብለው እያባባሱና እያጋነኑ በመዘገብ፣ ድርጊቱ ከኋላቀርነትና ከመሃይመነት አንዳንዴም ከጥቁርነት የመነጩ ለማስመሰል ይጥራሉ። ዕውነታው ግን ሰለጠኑ የሚባሉት ራሳቸው እንዲህ እንደሰሞኑ ትንሽ ቀን ጎደል ያለ ጊዜ አብሮ መኖር፣ አብሮ ችግር ቀንን ማሳለፍ፣ መረዳዳት የሚባል ነገር የሚከብዳቸው  መሆናቸውን እያየን ነው!
***
 ስፔን  :- ካሪና የተባለችን ሴት ህልፈተ ሕይወት አስመልክቶ ሰንደቅ ዓላማዎች ዝቅ ብለው እንዲውለበለቡና የሶስት ቀናት ሀዘን እንዲሆን በስፔን አልማሶራ በተባለች ከተማ ተደንግጓል። በደህናው ጊዜ ቢሆን በዚህች በቫሌንሺያ ከተማ አቅራቢያ በምትገኝ አነስተኛ መንደር እንዲህ ያለው የከበደ ሀዘን ሲገጥም የአካባቢው ሕዝብ ነቅሎ ወጥቶ በቀብር ሥርዓት ላይ ይሳተፍ ነበር። ግን ዘመኑ የክፉ ወረርሽኝ ሆነና ሁሉም በነበር ቀረ። እናም የአካባቢው ነዋሪዎች ተዘግተው ከተቀመጡበት ቤታቸው ሆነው በየመስኮቶቻቸው ብቅ በማለትና ከየቤቶቻቸው በረንዳ ላይ በመቆም የሟችን አስክሬን በጥልቅ ሀዘን ሆነው ሽኝት አድርገውለታል።
የሟችን ሀዘን የከበደ ያደረገው የሞቷ ምክንያት ኮቪድ-19 ሆኖ አይደለም። ኧረ በጭራሽ። የሀዘኑ መበርታት መነሻው ሟች በሁለት ልጆቿ ፊት በባሏ የመገደሏ ነገር ነው። በአውሮፓ በቤት ውስጥ ተዘግቶ መቀመጥ የሚለው መመሪያ መተግበር ከጀመረ ወዲህ የቤት ውስጥ ጥቃት በእጅጉ እየጨመረ ስለመምጣቱ እየተነገረው ነው። በየቤቱ በሚፈጠረው የከረሩ ፀቦች ልጆችን ሳይቀር ለከፋ የስነ ልቦና ችግር እየዳረገ ነው ተብሏል። የካሪና ሞትም በዚህ ዓመት በስፔን ሀገር በባሎች የተገደሉ ሴቶችን ቁጥር 17 አድርሶታል። እንደሚባለው የቤት ውስጡ ጥቃት በስፔን ብቻ ተገድቦ የሚቆም ሳይሆን መላ አውሮፓን ያዳረሰ ችግር ነው።
አውሮፓ የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ለመከላከል በሚል ሙሉ በሙሉ ከተዘጋች ገና 1 ወር አካባቢ ቢሆናትም የቤት ውስጥ ትርምስ ከፍተኛ ደረጃ እየደረሰ መሆኑ ተስተውሏል። በአንድ ቤት የሚያድሩ እንጂ በአንድ ላይ ኖረው የማያውቁ የትዳር አጋሮች ለቀናት አብረው ሲውሉ ፈፅሞ የማይተዋወቁ ባዕዳን እየሆኑ ለመግባባት ተቸግረዋል ነው የተባለው።
በጣሊያንም ችግሩ ከስፔን የተለየ አይደለም። ለምሳሌ ሰሞኑን በቤት ተወስኖ የመቀመጥ ግዴታ ውስጥ ባለችው ጣሊያን አንዲት የ27 ዓመት ወጣት እንዲሁ አብራ በምትኖረው የወንድ ጓደኛዋ ተገድላለች። ልጅቷ በህክምና ትምህርት ልትመረቅ ጥቂት ቀናት የቀሯት ነበረች። አስክሬኗ ወደ ትውልድ መንደሯ ሲሲሊ ሲላክ ብዙ ሰዎችና የከተማዋ ከንቲባ ሳይቀሩ ለሟች ምስኪን ነፍስና በዕድሜ ዘመኗ ልትለብሰው ስትመኘው ለኖረችው ነጭ የህክምና ገዋኗ ተምሳሌት ይሁናት በሚል ነጭ ጨርቅ በማውለብለብና በጥልቅ ሀዘን ተውጠው ሸኝተዋታል።
በፈረንሳይም ኮቪድ-9ን ለመከላከል በቤት ተወስኖ መቀመጥ ከተወሰነ ወዲህ በቤት ውስጥ በሚደርስባቸው ጥቃት ድረሱልኝ ብለው የሚደውሉ ሴቶች ቁጥር ከወትሮው በ1/3ኛ የጨመረ ሲሆን፤ በዋና ከተማዋ ፓሪስ ደግሞ ችግሩ ጭራሽ ይከፋል ነው የተባለው።
በሩሲያም ነገሩ ተመሳሳይ እንደሆነ ተነግሯል። የአንዲትን ሴት ገጠመኝ በምሳሌነት ያነሳው ዘገባው፤ ሚስት የባሏ ፀባይ ልውጥውጥ ማለት የጀመረው ፕ/ት ፑቲን ድንገት ከቤት መውጣት ክልክል ነው ብለው ባወጁበት ቅፅበት ነው ብላ እንደምታምን ተናግራለች። የፑቲን መግለጫ እንደተሰማ ባሏ ቤት ከመቀመጡ ጋር ተያይዞ የገቢ መቀነስ እንደሚገጠመው በማሰብ መረበሽና መጨነቅ እንደ ጀመረ ትናገራለች። ወዲያውም በአስፈሪ ሁኔታ በብስጭት ዕቃ መሰባበርና ብሎም ወደ እሷና ልጆቿ ላይ ዞሮ መወርወር መጀመሩን ትገልፃለች። ነገሩ ለሕየወቷ ያሰጋት ሚስት ሰውዬው ቢራ ለመግዛት ከቤት ወጣ ሲልላት  ወደ ፖሊስ ጣቢያ ድረሱልኝ ስትል ትደውላለች። ፖሊሶቹ ነገሩን ከስር ከመሰረቱ ከሰሙ በኋላ ቤቱ የእሱ ስለሆነ ልናስወጣውም ሆነ ልናስርልሽ አንችልም። ስለዚህ ተስማሙ ብለዋታል። ችግሯን የምትነግረው ያጣችው ሴት የራሷንም ሆነ የልጆቿን ነፍስ ለማትረፍ የሆነ መደበቂያ (ማምለጫ) መፈለግ ፈንታዋ ነው።
በሀገረ ዴንማርክም ቤት ቆዩ ተብሎ ከታወጀ በኋላ የድረሱልኝ ጥሪ በአንዴ በዕጥፍ ጨምሯል። የሚሰማው ሁሉ ያሳሰበው አንድ የሴቶች መብት ተሟጋች ቡድን፣ በየቤቱ እየዞረ ለየቤተሰቡ ዓባላት በቂ ክፍሎች መኖሩን ማረጋገጥ ጀምረናል ብሏል። [የመብት ተሟጋቾቹ ምናልባት ሰዎች አንድ ላይ አንድ ክፍል ውስጥ ተፋጠው ሲቀመጡ “ተደባደቡ፣ ተደባደቡ” የሚል ስሜት ይመጣባቸዋል ብለው ሳያስቡ አልቀሩም]
በቤልጂየም ደግሞ ችግሩ የከፋ ነው የተባለው። ቤት ቁጭ በሉ ከተባለ ወዲህ በቤት ውስጥ በሚፈፀሙ ጥቃቶች የተነሳ የድረሱልኝ ጥሪዎች 3 ዕጥፍ ያህል ጨምሯል። አንድ የጥቃት ጊዜ የሚደወሉ ስልኮች ጥሪ ተቀባይ ሠራተኛ ሲያስረዳ፤ ለምሳሌ አንድ ሴትዮ ወደ ጥሪ ማዕከሉ እያለቀሰች ደውላ ባሏ ደጋግሞ እየደበደባት እንደሆነና አንድ ዓይኗን መግለጥ እስከማትችል ድረስ ፊቷ እንደበለዘ ገልፃ፣ “እባካችሁ ሳይገለኝ ድረሱልኝ” ስትል ተማፅናለች። ስልኩንም መደወል የቻለችው ባሏ ሲጋራ ለመግዛት ለ15 ደቂቃ ያህል ከቤት ወጣ ባለበት ሰአት መሆኑን በፍርሃት ተሸብራ በሚንቀጠቀጥ ድምፅ ተናግራለች።
                   **************
ይገርማል መቼም። የምዕራብውያን ሥልጣኔ ለመውደቅ እያዘመመ ይመስላል። አንዳንዴ ሥልጣኔ ማለት በኢኮኖሚ መበልፀግ፣ በዘመናዊ ትምህርት መመንደግ፣ በፅዱ ቤትና ሀገር መኖር አለመሆኑን ከላይ ያነበብናቸው የፈረንጆቹ ታሪክ ጥሩ ማሳያ ነው።
 እነሱ በአፍሪካውያን መካከል የሚፈጠሩ ቀላል ግጭቶችን ሳይቀር ሆን ብለው እያባባሱና እያጋነኑ በመዘገብ፣ ድርጊቱ ከኋላቀርነትና ከመሃይመነት አንዳንዴም ከጥቁርነት የመነጩ ለማስመሰል ይጥራሉ። ዕውነታው ግን ሰለጠኑ የሚባሉት ራሳቸው እንዲህ እንደሰሞኑ ትንሽ ቀን ጎደል ያለ ጊዜ አብሮ መኖር፣ አብሮ ችግር ቀንን ማሳለፍ፣ መረዳዳት የሚባል ነገር የሚከብዳቸው  መሆናቸውን እያየን ነው።
 ለምሳሌ እንግሊዝን የምታክል የስልጡኖች ሀገር በቤት ተዘግቶ መቀመጥ አዋጅ ሊተገበር ቀናት ሲቀሩት ያውም በዋና ከተማዋ ሎንዶን በየሱፐር ማርኬቶቿ የታየው የንጥቂያና የዝርፊያ ተግባር በራሱ ብዙ ነገርን ያሳያል። ብቻ ስለ ዕውነት ለመናገር በተለይ የእኛ ሀገር ሰው፤ ፖለቲከኞች ባያባሉት፣ ድህነት ባያጎሳቁለው በተፈጥሮው ለሥልጣኔ፣ በሕገ ልቦናው ደግሞ ለምግባርም፣ ለሰብአዊነትም የቀረበ ልባም ሕዝብ አይደል እንዴ?!
Filed in: Amharic