>

ቴዎድሮሳዊነት ይለምልም!!! (ብርሀኑ ተክለአረጋይ)

ቴዎድሮሳዊነት ይለምልም!!!

 

ብርሀኑ ተክለአረጋይ
በእስር ቤት ሳለን እኔና የእስር ጓደኞቼ (በአንድ መዝገብ የተከሰስነው 4ታችንም) የፍርድ ቤት ቀጠሮ ሲኖረን ተመሳሳይ ቲሸርት እንለብስ ነበር። ያቺ ሁሉም እስረኛ ለምዷት መለያችን የነበረችው ቲሸርትም የአፄ ቴዎድሮስ ምስል ያለባት መይሳው ካሳ የሚል ፅሁፍ ያለባት ናት።  እኔ ከዞን 1 ፍቅረ ማርያም ከዞን 2 ደሴ ከዞን 3 ጄሪ ከቃሊቲ ሴቶች ክልል ቀጠሮአችንን ጠብቀን ለብሰናት ብቅ እንል ነበር።
በአንዲቷ የቀጠሮ እለታችን የፍርድ ቤት ቀጠሮ ያላቸው እስረኞች የሚሰለፉባት ቦታ ላይ በእኛና በጠባቂዎቻችን መሐል ግብግብ ተፈጠረ የግብግቡ ምክንያት ጠባቂዎቹ እኛን የለበሳችሁትን ቲሸርት ቀይሩ እኛ ደግሞ የለም አንቀይርም መብታችን ነው በማለታችን ነበር። ሁሉም ጠባቂ በአለቃው  ለመሞገስ ወደ እኛ እየመጣ መጮህና መዛት  ጀመረ።  ከእስረኞችም መካከል ገሚሱ “አይቀይሩም መብታቸው ነው” ገሚሱ “ኧረ እባካችሁ ቀይሩና እንሂድ” ይላል፤ እኛም “ብትፈልጉ ወደ ፍርድ ቤት አትውሰዱን እንጂ ቲሸርቱን አንቀይርም ” ብለን በአቋማችን ፀናን።
ድንገት ከጠባቂዎቻችን መሀል መሳሪያ የታጠቀ አጠር ያለና ንዴቱ ፊቱ ላይ የሚታይ ወታደር ከኛ በቅርብ ርቀት ሆኖ ልቀቁኝ እያለ ሲገለገል ጓደኞቹም ተው እያሉ ሲይዙት በመጨረሻም ጓደኞቹን ጣጥሶ ወደ እኛ ሲመጣ አብሮኝ ከታሰረው ከፍቅረ ማርያም ጋር በድንጋጤ ተያየን። ወታደሩ መሳሪያውን ዘቅዝቆ ይዞ በንዴት እያየን “ይህን ቲሸርት ወንድ የሆነ ያስወልቃችኋል መልበስ መብታችሁ ነው” አለ። ወደጓደኞቹና አለቆቹ ዞሮ “የመይሳውን ቲሸርት መልበስ በህግ ተከልክሏል? አልተከለከለም፤ስለዚህ አያወልቁም”ተብሎአል ተቆጣ። ሁሉም ዝም አለ። የድንጋጤ መልክ የሚታይበት የሽፍት መሪ “ተዋቸው በቃ ጫኑና ወደፍርድ ቤት ውሰዷቸው” ብሎ ውጥረቱን አረገበው።
መኪናው ውስጥ ሆነን ያ ቆፍጣና ወታደር ጮክ ብሎ “ስማ ብርሀኑ ገንዘብ ልስጥህና ቲሸርቱን አስመጣልኝ” አለኝ ግድ የለም እናስመጣልሀለን አልነው። ፍርድ ቤት ውስጥም ከቤተሰቦቻችን ጋር አሰተዋውቀነው  ቀጠሮአችንን ተቀብለን ተመለስን።
በሳምንቱ መጨረሻ እሁድ የቤተሰብ ጥየቃ ከተጠናቀቀ በኋላ “ብርሀኑ ተክለያሬድ በር ላይ አባል ይፈልግሀል” የሚል ጥሪ ሰምቼ ወደ በር ሄድኩ። ያ ቆፍጣና ቤተሰቦቻችን ገዝተው ያቀበሉትን የመይሳው ፣ካሳን ቲሸርት ለብሶ ቆሟል። “ይኸውልህ አፄ ቴዎድሮስ አውልቅ እንዳሉህ ሰዎች ዘረኛ አልነበረም የገዛው ኢትዮጵያን ነው የሞተውም ለኢትዮጵያ ነው ማንንም እንዳትፈራ ይግደሉን እንጂ አናወልቅም ስትፈልገኝ አስጠራኝ” ብሎ ስሙን ነግሮኝ ተለያየን።
የአብዱልጀሊልን “ኪነት ያገነነው አፄ ያነበብኩ ለት፣ ሰዎች ቴዎድሮስ ከዚህኛው ወይም ከዚያኛው ዘር ነው ብለው በተከራከሩ ጊዜ ወዘተ ይህ ቆፍጣና ትዝ ይለኛል።(አሁን ይህ ወታደር የከባድ መኪና ሹፌር መሆኑን ሰምቻለሁ)ዛሬም በንጉሱ መታሰቢያ እለት አዲሱን ገመድ ጉተታ በተመለከትኩ ጊዜ ይህን ወታደር አሰብኩት። ገመድ ጎታቾች ሆይ ጉተታውን ተዉየና ቴዎድሮሳዊነትን ተላበሱ!!!
ለመሆኑ አጼ ቴዎድሮስ እንደምን ያሉ መሪ ነበሩ!!!
-ህይወታቸውን በሙሉ ጥበብን ሲያሳድዱ የነበሩ
– ወታደሩን በስነምግባር ፣ በጦርመሳሪያ የታነጸ ለማድረግ እድሜ ልክ የጣሩ።
– ጦርመሳሪያን ከውጭ ሀገር ማስመጣት ሳይሆን እውቀትን ሀገር ውስጥ ለማስተማር የሻቱ
-ክርስትናን ለመስበክ የጣሩ ሚሲዮናዊያንን ክርስትና በገባ 1500 አመቱ ክርስትና መስበክ ምን ያደርጋል ይልቅ ጥበብ አስተምሩ እያሉ ያስገድዱ የነበሩ
-ከፕሮቶስታንቶች ጋር ቅርበት የነበራቸው በዚሁ በጥበባቸው ምክንያትን መሆኑ
– ወታደሩን በኢኮኖሚ ለመደገፍ ሲሉ ከቤተክህነት ጋር ውዝግብ ውስጥ የገቡ
-የባሶ የባርያ ገበያን አይተው ከዛን ግዜ በኋላ ባርያ ንግድ እንዲቀር ጥረት ያደረጉ፡ ወታደሮቻቸውም የማረኳቸውን እንዳይሸጡ ያዘዙ
–ለእንግሊዝ ጥልቅ ፍቅር የነበራቸው ቢሆንም በተቃራኒው እንግሊዝ የንግስና ዘመናቸውን ያሳጠረችባቸው ንጉስ መሆናቸው
– አብዝተው ጥበብን ስልጣኔን ሲፈልጉ ያኔ የነበረው ህዝብ ሲቃወማቸው  የሚረዳቸው (የሚገባው)  አጠው  ከገብርየ በቀር ህዝብ እምቢ ያላቸው የዘመናዊቷ ኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ነበሩ።
ስንት ስልጣኔና ጥበብ የያዙትን መሪ በመንደር ወሬ ዝቅ አታድርጓቸው።
Filed in: Amharic