>
5:18 pm - Tuesday June 16, 9187

የዶ/ር አብይ አራት አማራጮች አገር ለማዳን ወይስ  በስልጣን ለመደላደል!? (ያሬድ ሀይለማርያም)

የዶ/ር አብይ አራት አማራጮች አገር ለማዳን ወይስ  በስልጣን ለመደላደል!?

 

 

ያሬድ ሀይለማርያም

 

 

አንዳንድ አስፈሪ እና ብዙ ኪሳራ የሚያስከትሉ አደጋዎች ከጀርባቸው ጥሩ እድልንም ይዘው ሊመጡ ይችላሉ። ትልቁ ቁምነገር ከመጣው አደጋ ጀርባ ያለውን መልካም እድል በቅጡ መረዳት መቻሉ ላይ እና በአግባቡም የመጠቀም ጥበብ ብቃት መኖሩ ላይ ነው። አጣብቂኝ ውስጥ ከወደቀ ሁለት አመት ላስቆጠረው የኢትዮጵያ ፖለቲካ አለምን እያተራመሰ ያለው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ በመከራ ውስጥ እድል ይዞ የመጣ ወይም ፈረንጆቹ እንደሚሉት A blessing in disguise ክስተት ይመስላል። ለነገሩ የኮቪድ ወረርሽ መምጣትን አስከትሎ ከዲሞክራሲያዊ ጎዳና ለመንሸራተት በቋፍ ያሉ መንግስታት አጋጣሚውን እንደ ፈጣን ሎተሪ ሲጠቀሙበት ሲሯሯጡ ማየት ከጀመርን ቆይተናል። ለዚህም የዩጋንዳው ዩዎሪ ሙሴቪኒ አንዱ ናቸው። የዛሬ ወር ግድም ኮሮና አውሮፓ እና አሜሪካ ገባ ሲባል አጅሬ ምርጫውን ለሁለት አመት አራዝመዋለሁ ሲሉ ተደምጠዋል። ለማንኛውም ወደ አገራችን ነባራዊ ሁኔታ ስንመለስ ኢትዮጵያም የኮቪድ ወረርሽኝ መከራን ብቻ ሳይሆን እድልም ይዞላቸው ከመጡት አገሮች አንዷ ናት ለማለት ይቻላል። መከራውን በስሱ የያዘልን ይመስላል እና በዚሁ ያዝልቅልን እያሉ መጸለዩ እና ተገቢውን ጥንቃቄ እያደረጉ ወረርሽኙን መከላከል የግድ ይላል። እድሉን ግን በጸሎት፣ በካድሬዎች ሆያሆዬ እና በፎቶ ድራማ ሳይሆን በእውቀት፣ በቅን ልቦና፣ ከሥልጣን ጥም ጋብ በማለት እና እጅግ ኃላፊነት በተሞላው የጥንቃቄ እርምጃ መጠቀም ይገባል።

የኢትዮጵያ ፖለቲካ የምርጫ አጣብቂኝ ውስጥ ከገባ ውሎ አድሯል። ምርጫው በአጭር ጊዜ ይካሄድ ወይስ እረዘም ያለ የዝግጅት ጊዜ ይሰጠው የሚለውም ክርክር ቢያንስ መንፈቅ አስቆጥሯል። የኮቪድ መምጣት ለምርጫው መራዘም ከበቂ በላይ አጥጋቢ ምክንያት ስለሆነ እዛ ላይ ውይይት አያስፈልገውም። ምናልባትም በዚህ አጋጣሚ ምርጫው ይራዘም ሲሉ ለቆዩት ተቃዋሚዎችም ሆነ ከአንገት በላይ ምርጫው ነሐሴ ላይ ካልተካሔደ እያለ ሲፎክር ለነበረው ገዢ ፓርቲም ጥሩ የእፎይታ ጊዜ የፈጠረ ይመስለኛል። ገዢው ፓርቲ ከአንገት በላይ ነው ምርጫው በነሐሴ እንዲካሔድ ሲያሳስብ የነበረው ያልኩት መሬት ላይ የነበረው ነባራዊ ሁኔታ ያንን ያመላክት ስለነበረ ነው። ነገርየውን ‘ሆድ ሲያውቅ ዶሮ ማታ’ ብለን እንለፈው እና ወደ ዋናው ቁምነገር እንመለስ። ዶ/ር አብይ የሕግ አማካሪያቸውን ይዘው በትላንትናው እለት ከተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጋር ያደረጉት ውይይት ላይ እናተኩር።

አዎ የኮቪድ ወረርሽኝ በብዙ አገሮች የኢኮኖሚ፣ የጤና፣ የፖለቲካ እና የማህበራዊ ሕይወት መናጋቶችን ያስከተለውን ያህል አዳዲስ እድሎችንም ይዞ መጥቷል። ይሁንና በአንዳንድ አገሮች፤ በተለይም ዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ባልዳበረባቸው እና ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል አንባገነናው ሥርዓት በተንሰራፋባቸው አገራት ወረርሽኙ አፈናን ለማጠናከር በክፉ አደጋ ውስጥ እንደተገኘ መልካም እድል ተደርጎ ተወስዷል። ይህን ወረርሽኝ ለመከላከል በሚል ሽፋን አገሮች የአስቸኳይ ጊዜዎችን በማወጅ የዜጎችን መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ለማጥበብ እና ለመጨፍለቅ ሲጠቀሙበት እየተስተዋለ ነው። ከአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ጋር በተያያዘ በሽታውን ከመከላከል ባለፈ ሂደቱን ለመብቶች ገፈፋ በመጠቀም ከሚወቀሱት አገሮች መካከል ኢትዮጵያም አንዷ እየሆነች ነው። የአዋጁን መውጣት እና አስፈላጊነት ምንም አያጠራጥርም። እሱን ተከትሎ ዜጎች ያለ በቂ ምክንያት ሲታሰሩ፣ የግለሰቦች መኖሪያዎችም በላያቸው ላይ እየፈረሰ መዳ ላይ ሲጣሉ እና አልፎ አልፎም በጸጥታ ኃይሎች የዜጎችን ሕይወት የሚቀጥፉ እና የአካል ጉዳት የሚያደርሱ እርምጃዎች ሲወሰዱ ግን እያየን ነው። ይህ አይነቶቹ እርምጃዎች የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የማህበረሰቡን ጤና ከማስጠበቅ ባለፈም የፖለቲካ ተልዕኮ እንዳለው ሲለሚያመለክት ነገሩን ከወዲሁ በቅጡ መያዝ ያስፈልጋል። ለዚህም በራሱ የመንግስት ተቋም በሆነው በሰብአዊ መብት ኮሚሽኑ የተሰጠውን ዝርዝር ማሳሰቢያ አዘል ምክረ ሃሳብ የአብይ አስተዳደር ልብ ቢለው መልካም ነው።

ትላንት በዶ/ር አብይ ወደቀረበው የመፍትሔ አቅጣጫ ወደያዘው ምክረ ሃሳብ ልመለስና የቀረቡት አራት አማራጮች አንዳቸውም አዲስ ነገር የላቸውም። ሁሉም ባለፉት ጥቂት ወራቶች ውስጥ በተለያዩ አካላት እንደ መፍትሔ ሲጠቆሙ እና አንዳንዴም መንግስት ከእነዚህ አቅጣጫዎች አንዱን ወይም ሁሉንም ሊከተል ይችላል የሚል የትንበያ ሃሳቦች ውስጥ ሲሰነዘሩ ቆይተዋል። እንደ እኔ ይህን ክፉ የወረርሽኝ አደጋ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ለማከም እንደ ጥሩ እድል መውሰዱ ስህተት አይደለም። ምናልባትም የጥሩ አመራር መገለጫ ሊሆን ይችላል። ይሁንና ዋናው ጥያቄ የሚሆነው በምን መልክ ነው ልንጠቀምበት ያሰብነው የሚለው ጉዳይ ግን ጥልቅ ውይይት ይጠይቃል። በአማራጭነት የቀረቡትም ሃሳቦች የአብይ አስተዳደር እድሉን በቅን ልቦና ውስጥ ሆኖ ለአገር በሚበጅ መልኩ ሊጠቀምበት አስቧል ወይስ የብልጣብልጥ ጨዋታውን ሊያደምቅበት ከጅሏል የሚለውንም አብሮ ማየት የግድ ይላል። ብልጣብልጥ ያልኩት የአብይ አካሄድ አለም ዛሬ ላለችበት ቀውስ እና ለከፍተኛ ውድቀት የዳረጋት የኒዮሊብራል ካፒታሊዝም ዋነኛ አቀንቃኝና የአለም አቀፍ የገንዘብ ድርጅቶችንም ሆነ እንደ አሜሪካ ያሉ አገራትን የኢኮኖሚ ፖሊሲ አቅጣጫ በማዝያዝ እና ከጀርባ ሆኖ በመዘወር ትልቅ ሚና የነበረው Milton Friedman ያቀነቅነው የነበረውን የ”shock therapy” እስትራቴኪካዊ አካሄድ ስላስታወሰኝ ነው።

የሚልተን ፍሬድማንን መሰሪያዊ እና የብልጣብልጥ አካሄድ በብዙ ገጾች በታጀበው መጽሐፏ በሚደንቅ መልኩ ላተተችው ለእውቋ ጋዜጠኛ እና ተመራማሪ Naomi Klein ምስጋና ይጋብት እና የፍሬድማንን የሸር ፖለቲካ The Shock Doctrine: The Rise of Disaster Capitalism በሚለው ድንቅ መጽሐፏ በዝርዝር እና በብዙ አገሮች ያስከተለውን ቀውስና መከራ በበቂ ማስረጃ እያስደገፈች አቅርባዋለች። የዚህ ጽሑፌ አላማ በሷ መጽሐፍ ላይ የተኮረ ባይሆንም አሁን አለም እና በተለይም ኢትዮጵያ ካለችበት አጣብቂኝ አንጻር አግባብነት አለው ብዮ ያሰብኩትን አጭር ነገር ላካፍላችውና ወደ ዋናው ጽሁፌ አተኩራለሁ። እንደ ናሆሚ አገላለጽ የፍሬድማን ስትራቴጂ ዋና ማጠንጠኛው በአገሮች ላይ በተፈጥሮ አደጋ፤ እንደ ሱናሜ አይነትም ሆነ ሌሎች ወይም ሆን ተብሎ በሚፈጠሩ ሰው ሰራሽ አደጋዎች ውስጥ እንዴት ትርፍ ማትረፍ እና አደጋዎቹን ለአንድ ሌላ የፖለቲካ ወይም የኢኮኖሚ ግብ መጠቀም እንደሚቻል የሚያትት ነው። ለምሳሌ በአሜሪካ፣ በኤዢያ እና በአንዳንድ የላቲን አገሮች በተከሰተው የሱናሜ አደጋ መንግስታት እንዴት እንዳተረፉበት ናሆሚ ጥሩ አድርጋ በመጽሐፏ ታሳያለች። በአንዳንድ ሱናሜ ባጠቃቸው የአሜሪካ ግዛቶች ሱናሜው ጠራርጎ ያነሳቸውን የድሃ መኖሪያዎች ቀድሞውንም መንግስት ሊያስነሳቸው እያሰበ ስለነበር እዝጌር የፈጠረው መልካም እድል ተብሎ በፖለቲከኞች ጭምር በይፋ መጠቀሱን ትገልጻለች። ሰው ሰራሽ ከሆኑት አደጋዎች ደግሞ፤ የሱማሊያ መፍረስ፣ የኢራቅ እና ሌሎች ኢላማ ተደርገው የተመቱ የአረብ አገራት መንኮታኮት ለምዕራቡ አለም የፈጠረውን ምቹ ሁኔታ ታስረዳለች። ከዛም አልፋ ሰቅጣጭ ከነበረው የ9/11 የሽምብር ጥቃት ከፈጠረው ድንጋጤ እና ቀውስ ጀርባ በፍሬድማን እሳቤ የአሜሪካ ፖለቲከኞች ምን እንዳተረፉ እና እንዴት እንደ ጥሩ እድልም እንደተቆጠረ ትገልጻለች።

በአጭሩ ከናሆሜ መጽሐፍ የምንረዳው ባለንበት የስግብግብ ፖለቲካ ዘመን የፍሬድማንን የፖለቲካ እስትራቴጂ የሚከተሉ ሰዎች ተፈጥሮ የሚያመጣውን አደጋ ቁጭ ብለው የሚጠብቁ ብቻ ሳይሆኑ እራሳቸውም አስፈላጊ ሲሆን አደጋውን መፍጠር እንደሚችሉ፤ ከፈጠሩትም አደጋ እንዴት ማትረፍ እንደሚችሉ ቀድመው የሚያሰሉ እና ባሰሉትም ልክ የሚያተርፉ ጮሌዎች መሆናቸውን ጭምር ነው። ከመጽሐፉዋ ውስጥ ከላይ ላነሳሁት ሃሳብ አግባብነት አለው ብዮ የማስበውን አጭር ነገር ጠቀስ ላድርግና ወደ ትርጉምም ሳልገባ መጽሐፉን ላላነበባችሁት እንድታነቡት እያበረታታሁ ወደ ተነሳሁበት ቁምነገር ልመለስ። የፍሬድማን ቀውሶችን የማከም የፖለቲካ ስልት ዋናው ቁልፍ ሃሳብ እንደ ናሆሚ አገላለጽ “… the exploitation of national crises (disasters or upheavals) to establish controversial and questionable policies, while citizens are excessively distracted (emotionally and physically) to engage and develop an adequate response, and resist effectively.” በማለት ትገልጸዋለች። አክላም እንዲህ ትላለች “The slogan for contemporary capitalism—fear and disorder are the catalysts for each new leap forward”.

እና ምን ለማለት ነው ዶ/ር አብይ አንድም ይችን መጽሐፍ በደንብ አንብበዋታል፤ አለያም ያነበበ ጥሩ አድርጎ መክሯቸዋል መሰለኝ ትላንት የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሰብስበው ከገባንበት ቅርቃር መውጫ ቀዳዳው እነዚህ አራት መንገዶች ናቸው ብለው ያመጡት ሃሳብ በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የፖለቲካ ቀውስ እና አለመረጋጋት እሳቸው እና ብልጽግና እንዴት ሊቀጥሉ እንደሚችሉ ከማመላከብት ባለፈ አገሪቱን ከአላስፈላጊ ቀውስ እና የእርስ በርስ ግጭት እንዴት ሊታደጉ እንደሚችሉ የሚያሳዩ አይደሉም። አራቱም የመፍትሔ ሃሳቦች በብልጽግና ሕልውና ላይ የተመሰረቱ ሆነው ነው የቀረቡት። የእያንዳንዱን የመፍትሔ ሃሳብ ሕጋዊ መሰረት እና የአፈጻጸም ሂደት በዚህ ጽሑፍ መተንተን ትርፉ የአንባቢዎችን ጊዜ ማባከን ነው። በዛ ላይ ሃሳብ አቅራቢው ም/ጠቅላይ አቃቤ ሕጉ ብልጽግናዊ በሆነ መንገድ የሕግ ትንታኔም ጭምር ስለሰጡበት እሱን ከሳቸው ሃተታ መረዳት ይቻላል። ለእኔ ዋና ፍሬ ነገሮች ከሃሳቦቹ ጀርባ ያለው እሳቤ እና የጠቅላይ ሃሳብ ቅቡል እንዲሆን እየተሄደበት ያለው መንገድ ነው። ከዚህ የሚከተሉትን አንዳንድ አሳሳቢ ጉዳዮች ላንሳ፤

+ በውይይቱ ላይ አንዳንድ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ሲናገሩ እንደሰማሁትም ሆነ በግሌ እንዳጣራሁት በዚህ ምክረ ሃሳብ ላይ የተቃዋሚ ፓርቲዎቹ የተጠሩበት መንገድ እራሱ ጥያቄ አጫሪ ነው። እንዲህ ያለ ከፍተኛ አገራዊ ፋይዳ ያለው ውይይት ለማካሄድ ፓርቲዎቹ ወይም የተወሰኑት ስብሰባው ሊካሄድ አንድ ቀን ሲቀረው፤ ሊያውም አመሻሹ ላይ ጥሪው የደረሳቸው መሆኑን ሰምቻለሁ። ለምን ከሳምንት ወይም ከቀናት በፊት የጥናት እና የመፍትሔ ሃሳቡን የያዘው ሰነድ ለሁሉም ፓርቲዎች ተልኮ መክረውበት እና ዘክረውበት፤ ባለሙያም አማክረው እና የአማራጭ ሃሳብ ይዘው እንዲመጡ ማድረግ አልተቻለም? እዛስ ከገቡ በኋላ ለምን ሰነዱ አልተሰጣቸውም?  ሰነዱ እንዲሰጣቸው የፓርቲ መሪዎቹ እዛው ስብሰባው ላይ ሲጠይቁ ሰምቻለሁ። ከፓርቲዎቹ እውቅና ውጪስ ጠቅላይ ይህን በባለሙያ የማስጠናቱን ሂደት ለምን በግላቸው ማከናወን መረጡ? እሳቸው በተሳተፉበት ልክ የሃሳቡን መነሻ ካቀረቡት ባለሙያዎች ጋር ሌሎቹም የፖለቲካ ድርጅቶች በቀጥታ የመመካከር እና ሃሳብ የመስጠት እድል ለምን አልተሰጣቸውም? በጥቅል የተገለጹት ባለሙያዎችስ ምን ያህል ከጠቅላዩ እና ከፓርቲያቸው ተጽዕኖ ነጻ ነበሩ?

+ አራቱም የቀረቡት የመፍትሔ ሃሳቦች እንደሚጠቁሙት የአገሪቱ እጣ ፈንታ ዛሬም፣ ነገም እና ምናልባትም ከምርጫውም በኋላ በብልጽግና መዳፍ ስር ነው የሚል አንድምታ የያዙ አይመስልም ወይ? በሁሉም አማራጮች ላይ አሉታዊ እና አወንታዊ የሆኑ ጎኖቻቸው ተዘርዝረዋል። ነገር ግን ደጋግመው ጠቅላዩም ሆኑ የሕግ አማካሪያቸው ለማሳሳብ የፈለጉት አገሪቱ ሁለት እና ከዛ በላይ አደጋዎች ተጋርጠውባታል፤ አንዱ ኮቪድ፣ ሌላው የህዳሴ ግድብን ተከትሎ የሚመጣው ውጫዊ የወረራ ስጋት እና በአገሪቱ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ቀውስ ነው። እዚህ ላይ fear and disorder are the catalysts የሚለውን ልብ ይለዋል። ለዛም ደጋግመው እንደጠቀሱት እነዚህን አደጋዎች ለመጋፈጥ እና በድል ለመወጣት ጠንካራ መንግስት ያስፈልጋል ብለዋል። እንግዲህ በግልጽ አነጋገር አሁን አገሪቱ ባለችበት ነባራዊ ሁኔታ ጠንካራው ኃይል በሥልጣል ላይ ያለው መንግስት ስለሆነ ከምርጫ በፊትም ሆነ ከምርጫ በኋላ እኔው ነኝ ይችን አገር ልታደጋት የምችል የምል ግልጽ እንድምታ ያለው የመፍትሔ ሃሳብ እንደማቅረብ ነው። የጽቅም፤ የኩነኔውም መንገድ እኔው ብቻ ነኝ እንደ ማለት ነው። አገሪቱ ዛሬ ላለችበት አጣብቂኝ ትልቁን ድርሻ ህውሃት/ወያኔ ይውሰድ እንጂ ዛሬ በብልጽግና ስም የሚጠራው አደረጃጀትም ዋና ተጠያቂ ነው። በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት አገሪቱ ውስይ ለታየው ሥርዓት አልበኝነት የአብይ አስተዳደር ዋና ተጠያቂ ነው። ሌሎች ጠንካራ ተቃዋሚዎችም እንዳይፈጠሩ የአገዛዝ ሥርዓቱ ለሃያ ሰባት አመት ብዙ ደክሟል። ዛሬ ጠንካራ ተቃዋሚ የለም እያሉ ማላዘኑ የዘሩትን እንደ ማጨድም ነው።

+ ዶ/ር አብይ ባለሁት ሁለት የሽግግር አመታት ውስጥ ለአገሪቱ ያበረከቷቸው በርካታ ነገሮች ያሉትን ያህል ያሳጧትም ብዙ እና ወሳኝ እድሎችም አሉ። አንዱ እና ዋነኛው ደጋግሜ የማነሳው፤ በእውነት ላይ የተመሰረተና ፍትሕን ማዕከል ያደረገ ብሔራዊ እርቅ ነው። ጠቅላዩ ይህን ሃሳብ ሲገፉት ቆይተው ዛሬ አገሪቱ ከነመረቀዘ ቁስሏ እዝህ አጣብቂኝ ውስጥ ወድቃለች። ብሔራዊ እርቅ ይካሔድ ማለት የሽግግር መንግስት መጠየቅ እንዳልሆነ በደንብ ይሰመርበት። ብሄራዊ እርቅን የገፉት ዶ/ር አብይ የኮቪድ መምጣትን ተከትሎ የሰሩት ፖለቲካዊ ድራማ አገሪቱን ባይጎዳም እና በግለሰቦች ልብ ውስጥ በጎ ነገርን ቢፈጥርም ሂደቱ ግን ያበሽቃል። ጉዳይን ሙሉ በሙሉ ወደ መንፈሳዊ መንገድ በመውሰድ የኃይማኖት አባቶችን እና እርሰ ብሔሯን በአንድ አዳራሽ ውስጥ አራርቀው በማስቀመጥ ንስሃ እንዲገቡ እና እርስ በርስ ይቅር እንዲባባሉ፤ ሕዝቡንም ይቅርታ እንዲጠይቁ፤ ሕዝቡም እርስ በርሱ ይቅርታ እንዲጠያየቅ አድርገዋል። እነኚህ የኃይማኖት አባቶች ነጋ ጠባ ንስሃ እንደገቡ እና ይቅርታን ሲማጸኑ የኖሩ ናቸው። አደጋውም ሆኑ የግጭት መርዙ ያለው ከፖለቲከኞቹ ዘንድ ሆኖ ሳለ ሕዝብን እና የኃይማኖት አባቶችን ይቅር ተባባሉ እያሉ እንዲማማሉ ማድረግ ከፖለቲካ ድራማ ያለፈ ቅርቃር ውስጥ የገባውን እና በቂም የተለወሰውን የአገሪቱን ፖለቲካ የመታደግ አቅም የለምው። እሱን በግላጭ ዛሬም እያየን ነው። አሁንም ይች አገር እውነተኛ ሕብሄራዊ እርቅ ያስፈልጋታል። አንዱን ጥሎ ሌላውን አንጠልጥሎ የሚደረገው የብልጽግና ጉዞ ብዙ እርቀት ሊሄድ አይችልም። ያኮረፉ አካላት በጠቅላላ በእርቅ ወደ መሃሉ ፖለቲካ እንዲጠጉ መደረግ አለበት።

+ ብሄራዊው እርቅ ይቅርና የአብይ አስተዳደር የሕግ የበላይነትን እና ተጠያቂነትን በአግባቡ ባለፉት ሁለት አመታት ማስፈን ባለመቻሉ ሌሎች አዳዲስ ቁርሾዎችም እንዲፈለፈሉ ምክንያት ሆኗል። ባለፉት ሁለት አመታት በርካታ በማንነት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶች ተፈጽመዋል፣ የተረኝነት እና የተገፊነት ስሜት ተፈጥሯል፤ ሕግ እና ሥርዓትም ተፋልሰው የመንደር ጉልበተኞእ እንደ አሸን እንዲፈለፈሉ አድርጓል። እንግዲህ አገሪቷ ዛሬ ከገጠሟት ሁለት ችግሮች መካከል አንዱ ኮቪድ በተፈጥሮ ከሚከሰቱ አደጋዎች ቢመደብ ቀሪው ሰው ሰራሽ እና የእሳቸው አስተዳደርም አስተዋጽዖ የታከለበት ነው። ለአጣብቂኙ ይዘውት የመጡት መፍትሔ ደግሞ አገሪቱን የሚታደግ ቢመስልም ሌሎች በርካታ መዘዞችን በውስጡ አዝሎም የመጣ ነው።

 

መፍትሔ       

እንደ እኔ አሁን ካለንበት የፖለቲካም አጣብቂኝ ለመውጣት መቅደም ያለባቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው፤

+ አንደኛ አገሪቷ እውነተኛ የሆነ እና ፍትሕን ያማከለ ብሔራዊ እርቅ ማድረግ ይጠበቅባላት። ይህን ለማድረግ የመንግስትን እና የዶ/ር አብይን ቅን ልቦና ብቻ ነው የሚጠይቀው። መንግስት በቀጣዮቹ ወራቶች ውስጥ በዚህ ጉዳይ ላይ አተኩሮ መስራት ቢችል ሌሎቹን እንደ መፍትሔ የተቀመጡትን አራቱን መንገዶች፤ ምክርቤቱን ማፍረስ፣ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ፣ ሕገ መንግስት ማሻሻል እና በሕገ መንግስቱ ላይ ትርጉም መጠየቅ፤ የምናይበትን አተያይ ይቀይረዋል። ይህ የብሄራዊ እርቅ ሂደት ከትግራይ ክልል አስተዳደርም ጋር ሆነ ከሌሎች በተቃርኖ ከቆሙ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር የተገባውን መፋጠጥ እና ንቁሪያ እልባት ሊሰጠው ይችላል።

+ ዶ/ር አብይ የሚያስተዳድሩት መንግስት ባለፉት ሁለት አመታትም ሆነ ዛሬም እራሱን እየቆጠረ ያለው በሕዝብ ተመርጦ እንደመጣ መንግስት ይመስላል። በዚህም ምክንያት ይመስላል አንድ የሽግግር ላይ ያለ መንግስት ሊወስዳቸው የማይገቡ እና ዘላቂ የአገሪቱን ጥቅም ሊጎዱ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ ፈላጭ ቆራጭ ሆነው የመታየት አዝማሚያ በብዙ እቅዶቻቸው እና አተገባበሮቻቸው ላይ በግልጽ ተደጋግሞ ይስተዋላል። እንደ ተፎካካሪ ፓርቲ በሥልጣን ለመቆየት መጣር እና መመኘት በጎ ቢሆንም ሽግግር ላይ ያለች አገር የሚመራ ድርጅት ግን እቅዱም ሆነ ሊከውናቸው የሚገቡ ነገሮች በሽግግሩ ሂደት ላይ ብቻ ያተኮሩ መሆን ነበረባቸው። ጠቅላዩ የምርጫን እና የሽግግሩን ጉዳይ ለተወሰኑ አካላት እርግፍ አድርገው ትተው እሳቸው በቀጣይ በሚመሯት አገር ላይ በሚሰሩ የአሥር እና የሃያመት እቅዶች ላይ ነበር ትኩረታቸው እና ብዙ ጊዜያቸውንም ያጠፉ የነበረው። በዚህም የተነሳ የሽግግር ሂደቱ በተፈለገው ፍጥነት እና ብቃት ሊዘልቅ አልቻለም። የምርጫን ጉዳይ ለወ/ት ብርቱካን እርግፍ አድርገው ትተው፣ የእርቅ፣ የፍትህን እና የሰላምን ጉዳይ ለሰየሟቸው ሌሎች ሰዎች እርግፍ አርገው ሰጥተው እሳቸው በምናብ ያስባቧት የነበረችውን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር ደፋ ቀና ሲሉ የሽግግር ጊዜው በተዝረከረከ መልኩ እዚህ ደረጃ ላይ ደርሷል። አሁንም ትኩረታቸው ሙሉ በሙሉ በሽግግሩ ሂደት ላይ ካልሆነ እንኳን ብልጽግናው ሽግግሩም እሩቅ አይሄድም። ሌሎች አገራዊ ሥራዎች እንደየ አግባቡ በሚመለከታቸው አካላት መከወናቸው እንዳለ ሆኖ እሳቸው ግን ሽግግሩን ቅድሚያ ሰጥተው እና በቂ ጊዜ እና ገንዘብ መድበው ሊመሩይ ይገባል።

+ አራቱ የመፍትሔ ሃሳቦችን በተመለከተም፤ እንደ እኔ ሁሉም አስፈላጊ ይመስሉኛል። ምክር ቤቱ ሥራውን ነሐሴ መጨረሻ ስለሚያጠናቅቅ ከዛ በኋላ አገሪቱ ልትቆይ የምትችለው በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሥር እንደሚሆን ከወዲሁ ግልጽ ነው። ስለዚህ ቢኖርም፣ ባይኖርም የማይጎዳውን ፓርላማችንን ከወዲሁ በጊዜ ሸኝቶ፣ ምርጫው ሊካሄድበት የሚችለውን በቂ ጊዜ ከወዲሁ በምክክር ወስኖ እና ምርጫው እስከሚካሄድበት ጊዜ ድረስ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጆ መቀጠል የግድ ይላል። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ውስጥ እና ከምርጫው በፊት ሁለቱን የቀሩትን የአማራጭ የመፍትሔ ሃሳቦች አብሮ ማስኬድ ይቻላል። ማለትም የሕገ መንግስት ትርጓሜ መጠየቅ እና ያንን ተንተርሶም አስፈላጊ የሆኑ የሕገ መንግስት ማሻሻያዎችን ማካሔድ። እንግዲህ እዚህ ላይ የሚነሳው ጥያዌ በአስቸኳይ ጊዜ ውስጥ ሆኖ ሕገ መንግስት የማሻሻያም ሆነ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል ዝግጅት ለማድረግ የሚያስችሉ ሁኔታዎችን መፍጠር ይቻላል ወይ የሚለው ነው። እንደ እኔ እምነት አዎ ይቻላል ነው። የዚህ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ዋነኛ አላማ መንግስታዊ ሥርዓቱ ሳይስተጓጎል የሽግግር ሂደቱ በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ ነው። አመጽን ለመከላከል የሚወጣው አይነት አዋጅ አይደለም። የኮቪድ ወረርሽኝ በተወሰነ ጊዜ የሚላቀቀን ከሆነ ከዚያ መለስ ያለው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሕዝባዊ ውይይቶችን እና የምክክር መድርኮችን የሚፈቅድ፣ ሃሳብን በነጻነት በመግለጽ፣ በመሰብሰብ እና በመደራጀት መብት ላይ ማዕቀብ የማይጥል፣ በአገር ጸጥታ እና ሰላም ማስከብር ላይ ያተኮረ እንዲሆን ብቻ እንዲሆን ማድረግ ይቻላል።

+ የመጨረሻው ነጥቤ በዚህ ለአገር የመፍትሔ ፍለጋ ሂደት ውስጥ ገዢው ፓርቲ እና ተፎካካሪዎቹ ዋና ተዋናይ ቢሆኑም ብቸኛ ባለድርሻ አካላት ግን አይደሉም። ስለዚህ ይህ አይነት ምክክሮች ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባሳተፈ መልኩ ከጅማሮው እስከ ፍጻሜው ወሳኝ የሆኑ ተቋማት እና ማህበራዊ አደረጃጀቶች፤ ምሁራን እና ገለልተኛ አማካሪዎች ሊሳተፉበት ይገባል።

 

ኮቪድን እየተዋጋን፣ ብሄራዊ እርቅ እያካሄድን ሽግግሩን በሰላም፣ ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ እና በስኬት እናጥናቅ፤

ቸር እንሰንብት!

Filed in: Amharic