>

ከፊታችን የተጋረጡ መላምታዊ እውነቶች! አሰፋ ሃይሉ

ከፊታችን የተጋረጡ መላምታዊ እውነቶች!

አሰፋ ሃይሉ
በኢትዮጵያ አሁን ያለው “ህገመንግሥት” ከቀጠለ:- “ባልካናይዜሽን” አዲሱ የኢትዮጵያ መጻዔ ፖለቲካዊ ክስተት ይሆናል? የክልሎችስ ቁጥር ከ38 እስከ 54 ሊያሻቅብ ይችላል? እንዴት? ለምን? መፍትሄውስ?
__________
Why is Woyane Not Admitting Its Constitutional Defeat and Seek an Alternative Path? Is a further Balkanization of Ethiopian Regional Polities a Real Possibility, and an Impending Peril? What’s the Way Out?
Many in the past have argued that the ethnic constitution was a future monster being bred by the Woyane. Believe it or not, it is now apparent that that same monster is threatening to devour Woyane itself. Judging from all angles, Woyane has become the prime victim of its own monster, the constitution. But only the Woyane doesn’t concede its defeat. And will not give in either.
___________
ብዙዎች የሚያሰምሩበት ሃቅ – ይሄ አሁን የምናየው ‹‹ህገመንግሥት›› – ወያኔ (ወይም ኦነግን ጨምሮ ወያኔ-ኢህአዴግ የሚባለው ጉልበተኛ ኃይል) በ1985 ገደማ የታጣፊ ክላሽና የታንክ አፈሙዞችን በቅርብ ርቀት ደግኖ ወዳሰኘው አቅጣጫ እየመራ ያሻውን እንደልቡ ያስፃፈበት ህገመንግሥት መሆኑን ነው፡፡ እና አሁንም ይሄ የአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ የሀገሪቱ ገዢ ህግ ሆኖ የቀረበበት ሰነድ – የሰብዓዊ መብት ድንጋጌዎቹን ብቻ አስቀርቶ –  ተቀዳዶ መጣል አለበት ብለው የሚከራከሩ ብዙ ናቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን አሁን ማንሳት የፈለግኩት ጉዳይ በመጪዎቹ ዓመታት ‹‹ህገመንግሥቱ›› እንዳለ ቢቀጥልስ – ምን ምን አዳዲስ ክስተቶችን ሊያስተናግድ የሚችልበት ዕድል አለ? – የትግራይ ሕዝብስ ይጠቅማል ወይ? የሚለውን መላምትን በእጅጉ የሚፈታተን ጥያቄ ነው፡፡
ወደ ጥያቄው ከመግባቴ በፊት ግን አንድ ሌላ ጥያቄ ላስቀድም! ያ ወያኔ አርቃቂዎቹን በባሩድ ጭስ እያጠነ ያስፃፈው ህገመንግሥት አሁን ላይ – በመጨረሻ – ለወያኔ አትርፎለት የተገኘው ነገር አለ ወይ ግን? የሚለውን አንድ ጥያቄ፡፡ መልሱ – ምንም የለም – የሚል ነው፡፡ በእርግጥ ያ ህገመንግሥት ያሰፈነው ሥርዓት የተዳከመችና አንድነቷ የላላን ኢትዮጵያ ፈጥሮለታል፡፡ ይህ መሆኑ ግን ለወያኔ በተናጠል ምን አትርፎለታል? ነው ጥያቄው፡፡ ምንም አላተረፈለትም፡፡ እንዲያውም – ወያኔ እወክለዋለሁ የሚለውን የትግራይ ህዝብ መጥቀም ቀርቶ – ቀድሞ ከህገመንግሥቱ በፊት ከተቆናጠጠበት እንደማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ እኩል ባለመብት ሆኖ የመቆጠር ታላቅ ታሪካዊና ዜጋዊ የመብት ሰገነቱ ላይ ተሽቀንጥሮ ወርዶ – ዛሬም ሆነ ወደፊት በሀገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሂደት ላይ ምንም የረባ የወሳኝነት ድምፅ ማሰማት ወደማይችል – በያዘው 38 የፓርላማ ወንበር ልክ ብቻ ታጥሮ ስለራሱ ቀበሌዎች ብቻ ለመተንፈስ ወደሚፈቀድለት አንድ አናሳ ነገድነት ደረጃ እንዲፈጠፈጥ አድርጎ ነው ያስቀረው የወያኔ ህገመንግሥቱ – የትግራይን ሕዝብ፡፡
አሁን ወደ መነሻዬ ልመለስና ያንኑ ጥያቄ ደግሜ ላንሳ፡- በመጪዎቹ ዓመታትም ይህ አቅመቢስ የጎሳ ኃይሎችን በማሰባሰብ የተመሠረተው የወያኔ ‹‹ህገመንግሥት›› እንዳለ ቢቀጥልስ? – እንዳለ ቢቀጥልስ ብቻ ሳይሆን ለዘለዓለሙስ የሚቀጥል ቢሆን? – የትግራይ ሕዝብ ይጠቀማል ወይ?
ምላሹ – በፍፁም! – ይሆናል፡፡ በፍፁም! የትግራይ ሕዝብ ከዚህ ‹‹የብሔሮች›› ህገመንግሥት መቀጠል የሚያተርፈው አንዳችም ነገር የለም!  እንዳልኩት ይሄ ህገመንግሥት በዚሁ ከቀጠለ – የትግራይ ሕዝብ ባለው የህዝብ ቁጥር አነስተኛነት የተነሳ – በሌሎች ብዙ ነዋሪ ባላቸው ክልሎች ሕዝቦች ተውጦ – እንደ ሕዝብ የጎሳ ወይም የብሔር ፖለቲካው እስከቀጠለ ድረስ ዘልዓለም-ዓለሙን በሌሎች ሲላላክና በሌሎች ሲገዛ ነው የሚኖረው፡፡ እንዲያውም – ይሄ በዘር (በ‹‹ብሔር››) ላይ የተመሠረተ የወያኔ ህገመንግሥት – በነበረው መልኩ በዚሁ በዘር መርሆው ላይ ተንጠላጥሎ ጉዞውን ይቀጥል ከተባለ – ለወደፊቱ ደግሞ – በትግራይ ህዝብ ላይ የሚደርስበት የአናሳነት-ገፈት አሁንም እየደረሰበት ካለው የከፋ ነው የሚሆነው፡፡ ለምን?
አሁን ወያኔ እወክለዋለሁ የሚለው የትግራይ ሕዝብ ከ9 ክልሎች ውስጥ አንደ አንዱ ነው፡፡ ወደፊትስ ግን? ወደፊትማ – ሌላ ሌላውን ትተን ቢያንስ ወያኔ ‹‹ደቡብ ብሔር ብሔረሰበች ሕዝቦች›› በሚል ስያሜ በርካታ ‹‹ብሔሮችን›› ጨፍልቆ ከሠራው ከአንዱ ክልል ውስጥ ብቻ – “የራሳችን ክልል ይኑረን” ብለው በክልልነት ብቅ የሚሉ (እና በእርግጥም ክልልነት የሚሰጣቸው) ገና መዓት (ከ20 የማያንሱ ‹‹ብሔሮች››!) ክልልነትን በሰልፍ እየተጠባበቁ ይገኛሉ፡፡ ይህ ማለት ምን ማለት ነው? ይሄ ምንን ያስከትላል? የህገመንግሥት ማሻሻያ ያስከትላል፡፡
ያለው ህገመንግሥት ይሻሻልና እነዚህ 20 አዳዲስ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ሲጨመሩበት – የክልሎች ቁጥር 9 መሆኑ ቀርቶ – 29 ክልሎች ይኖራሉ ማለት ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይህ የብሔር ህገመንግሥት የሚቀጥል ከሆነ – በማንኛውም ካልኩሌሽን ቢታይ – አሁን ‹‹ደቡብ›› በተባለው ክልል ውስጥ የሚኖሩ የተለያዩ ሕዝቦች – አንድ ላይ ተጨፍልቀው አንድ ክልል ሆነው ከሚቀርቡ ይልቅ – ብዙ ክልሎች ቢሆኑ አሁን ካለው ህገመንግሥታዊ ሥርዓት አሁን እያገኙት ካለው አድቫንቴጅ በላይ እጅግ ከፍ ያሉ ብዙ አድቫንቴጆችን እንደሚያገኙ ግልጽ ነው! (ይሄን መተንተን ካስፈለገ በሌላ ጊዜ እመለስበታለሁ፡፡)
ጥያቄው ግን – ከጥቅሙ አንፃር ባልካናይዜሽኑ – ወይም ወደ ብዙ ትንንሽ ራስ ገዝ አስተዳደሮች የመከፈሉ ጉዳይ – ወይም ወደፊት የሚያጋጥመው ክልልነትን ፍለጋ – በደቡብ ሕዝቦች ብቻ ተወስኖ ያበቃል ወይ? ነው፡፡ በብዙ ምክንያቶች አያበቃም፡፡ አዳዲስ ክልሎች መነሳታቸው አይቀሬ ነው፡፡
ከደቡብ ወጣ ብለን ሌሎችን እንይ እስቲ፡፡ ለምሳሌ – ወያኔ የብዙ የራሳቸው ነባር ታሪካዊ ሥረ-መሠረት ያላቸውን ህዝቦች ጨፍልቆ የፈጠረውንና – አንድ ትልቅ ዛፍ ባለበት ባንዲራ ሥር በቋንቋ ፊሽካ አሰባስቦ – በአንድ ክልል ሥር ያስጠለለበትን ‹‹ኦሮሚያ›› ተብሎ ለመጠራት የበቃ ክልል ብንመለከትስ? የኦሮሚያ ሕዝብስ ወደፊት አንድ ክልል መሆኑ ቀርቶ ወደ ብዙ ክልልነት የመለወጥ ዕድል ያጋጥመዋል ወይ? አዎ፡፡ በደንብ አድርጎ እንጂ!
አሁን ‹‹ኦሮሚያ›› እየተባለ የሚጠራው አንድ ክልል ወደፊት በትንሹ ወደ 8 የተለያዩ ክልሎች ራሱን መሸንሸኑ እንደማይቀር ብዙ ምልክቶች ያሳያሉ፡፡ ወለጋ፣ ከፋ፣ ኢሉባቦር፣ ባሌ፣ ቦረና፣ ሐረርጌ፣ አርሲ፣ ጉጂ፣ ዛይ፣ የወሎን አካባቢዎች ጨምሮ፣ የሸዋን አካባቢዎች ጨምሮ፣ … እንዲህ እየተባለ የየራሳቸው ክልል የሚኖራቸው ብዙ የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪ ሕዝቦች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ ከሌሎች ገፋፊ ምክንያቶች በተጨማሪ – ህገመንግሥቱ በዚሁ ከቀጠለ – ‹‹ኦሮሚያ›› የሚሰኘው ክልላዊ መስተዳድር ባለው ሥርዓት ‹‹አንድ ለናቱ›› ሆኖ ከሚቀጥል ይልቅ – ብዙ ክልሎችን ሆኖ ቢገኝ – በየክልሉ የሚኖሩት ብዙዎቹ ሕዝቦች ዘርፈ ብዙ ሥልጣኖችን፣ መብቶችንና ጥቅሞችን ማግኘታቸው ስለማይቀር – እነዚህ ጥቅሞች ከተለያዩ ታሪካዊ ዳራቸው ጋር ሲሰናኙ – በወደፊቷ ኢትዮጵያ ከኦሮሚያ እምብርት የሚወጡ የአዳዲስ ክልሎችን መፈጠር አይቀሬ ክስተት ያደርገዋል ሆነው፡፡
ይሄን ለማለት የደፈርነው ይህን ፍፃሜ የሚያመላክት አንዳንድ የፖለቲካ እንቅስቃሴ በኦሮሚያ ውስጥ እየተሰረፀ መሆኑን በማስተዋል ሲሆን – ይሄ የሚሆነው ግን ምናልባት በአንድ ቅድመ ሁኔታ ብቻ ነው፡፡ ይሄ እውን የሚሆነው – አሁን በኦሮሚያ እየጎለበቱ ከመጡት የፖለቲካ አሰላለፎች መሐል – የወያኔ ማኒፌስቶ የትግራይን ሪፓብሊክ እፈጥራለሁ ብሎ እንደተነሳው ሁሉ – ኦሮሚያንም “ራሱን የቻለ አንድ ሪፓብሊክ አደርገዋለሁ” ብሎ ከኢትዮጵያ ሊገነጥል የተነሳው የኦነግ ኃይል ያን የመገንጠል ፍላጎቱን ካልተወው ብቻ ነው፡፡ ለምሳሌ ኦነግ በካልኩሌሽኑ – 100 ዓመትም ይፍጅ ወይም 10 ዓመት – ሳልማት የኖርኳትን “ታላቋን የኦሮሚያ ሪፓብሊክ” የመመስረት አመቺ ሁኔታ እስኪፈጠርልኝ ድረስ – ‹‹ባይ ሁክ ኦር ክሩክ›› ኦሮሞን ሳልከፈፍል አንድ አድርጌ ማቆየት አለብኝ – ብሎ ይወስናል? ወይስ የመገንጠል ሃሳቡን እርግፍ አድርጎ ትቶት አሁን ባለው የብሔር ሕገመንግሥት ሥርዓት ውስጥ ኦሮሞዎች ይበልጥ የሚጠቀሙበትን (ማለትም ኦሮሚያን ወደ ብዙ ክልሎች የማብዛት) ስትራቴጂ መከተሉን ይመርጣል? የሚለው ጥያቄ ወሳኝነት ይኖረዋል፡፡
በሌላ በኩል ኦነጋዊው ኃይል የትኛውንም ስትራቴጂ ለመከተል ቢመርጥ ግን – አሁን ባለው ሥርዓት ውስጥ ራሱን የቻለ ክልል መሆን የሚያስገኘውን ከፍ ያለ ትርፍ የሚያሰላና የሚፈልግ የፖለቲካ ልሂቅ በኦሮሚያ በየሥፍራው ማቆጥቆጡን ከቀጠለ – እንደቀደመው የወያኔ ጊዜ እነዚህን ‹‹ታንጄብል›› ፍላጎቶች በጉልበት የሚደመጠጥጥና የሚከላከል ፈላጭ ቆራጭ ጉልነተኛ ኃይል ስለማይኖር – ይሄ የተጠቃሚነት አምሮት ከጥቂት ጊዜ በኋላ ኦሮሚያን አንድ ላይ ጨፍልቆ መቆየትን የሚመርጠውን ኦነጋዊ ኃይል ክልልነትን በሚያነሱት ኃይሎች ከፍተኛ ተፅዕኖ ውስጥ እንዲወድቅ ያደርገዋል፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ – ወደፊት – በኦሮሚያ ክልል ሥር እየተዳደረ ያለው የተለያየ ሕዝብ ራሱን ወደሚያዋጣው ወደ ብዙ ክልልነት መቀየርን መምረጡ አይቀርም፡፡
(በእርግጥ እዚህ ላይ ሳናነሳ የምናልፈው – ሌሎችስ ክልሎች ይህንን ነገር ይቀበሉታል ወይ? የሚለውን ጥያቄ ነው፡፡ ኦሮሚያ ክልል አንድ ክልል መሆኑ ቀርቶ – “6 ክልል ነኝ” ብሎ በህገመንግሥቱ መሠረት አጉል አድቫንቴጅ እወስዳለሁ ብሎ አፍጦ ቢመጣ – ለምሳሌ አማራው ክልል በእሺታ ይቀበለዋል ወይ? ሌሎቹስ? – ምላሹ – ወደው ነው ወይ? የሚል ነው፡፡ ወደው ሳይሆን ተገደው ይቀበሉታል፡፡ ምክንያቱም አልቀበልም በማለት እንደ ወያኔው ዘመን በባሩድ ጭስ እያጠነ የሚያስፈራራና አቅምም ያለው ብቸኛ ኃይል ስለሌለ – መብትን ከመቀበል ሌላ አማራጭ የለም!)
ወያኔ ‹‹አማራ›› ክልል ብሎ የፈጠረው ክልልስ? አማራ የተሰኘው ክልልስ ወደፊት ወደ ብዙ ክልልነት የመቀየር “ዕድል” (ወይም ዕጣ-ፈንታ) ሊያጋጥመው ይችላል ወይ? – መልሱ አዎ ነው፡፡ ምንም ጥርጥር የለውም! የአሁኑ የአማራ ክልል ራሱን ቢያንስ ወደ 6 ገደማ ክልሎች መከፋፈሉ የማይቀር የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ አሁን ያለው ህገመንግሥት በወደፊቱ መጪ ዘመን የሚቀጥል ከሆነ – ጎጃም፣ ጎንደር፣ ቅማንት፣ አገው፣ ወሎ፣ ሸዋ፣ ከሸዋም መንዝና መራቤቴ ይፋት እየተባለ ‹‹አማራ›› ከተሰኘው ነገድ ውስጥ ራሳቸውን ይበልጥ እንደ አንድ የሚቆጥር ታሪካዊ ሥረ-መሠረት ያላቸው – በትንሹ 6 የአማራ አካባቢዎች ሕዝቦች – የየራሳቸውን ክልል ይዘው መውጣታቸው አይቀርም፡፡ ምክንያቱም አማራ በዚህ ህገመንግሥት ሥር እንደከዚህ ቀደሙ አንድ ክልል ሆኖ ከሚቀጥል ይልቅ – በሥርዓቱ ውስጥ ሰፊ ስልጣንንና ጥቅምን የሚያስገኝለትን 6 ክልል ሆኖ ቢቀርብ ስለሚያዋጣው፡፡
እና በዚህ ዓይነት ከሄድን – ዝርዝር ጉዳዮችንና ዝርዝር የአድቫንቴጅ ዲዛድቫንቴጅ ካልኩሌሽኖችን እና ሌላ ሌላውን ሁሉ በይደር ትተን – በወደፊቷ የወያኔ የብሔር ህገመንግሥቱ እንዳለ በሚቀጥልባት ኢትዮጵያ – ቢያንስ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች ውስጥ ከያንዳንዳቸው 6 አዳዲስ ክልሎች ቢወጡ – ወደፊት ከሁለቱ ትላልቅ ክልሎች (ማለትም በእነርሱ ምትክ) – በድምሩ 12 አዳዲስ ክልሎች መፈጠራቸው አይቀርም፡፡ እነዚህ ቀደም ብዬ ከጠቀስኳቸው 20 የደቡብ ክልሎችና፣ ድሬዳዋንና አዲሳባን ጨምረው አሁን ካሉት ከ9ኙ ክልሎች ውስጥ ነባሮቹ ‹‹ኦሮሚያ፣ ደቡብና አማራ›› የሚባሉት 3 ክልሎች በአዳዲሶቹ ክልሎች ተተክተው ሲቀነሱ ከሚቀሩት 6 ክልሎች ጋር ሲደመሩ – ይሄ ህገመንግሥት በዚሁ ከቀጠለ – ቢያንስ በወደፊቷ ኢትዮጵያ – በቅርቡ – ራሳቸውን የቻሉ እና በህገመንግሥቱ የሚካተቱ በትንሹ 38 ክልሎችን ማግኘታችን አይቀርም፡፡ (ማለትም 20 ደቡብ + 12 ኦሮሚያና አማራ + 6 ነባር = 38 ክልሎች)፡፡
በሌላ በኩል ነገሩን ስናጤነው ደግሞ – ይሄ ጥያቄ ላቀረቡ ‹‹ብሔሮች›› ክልልነት እንደሚሰጣቸው የሚናገረው ህገመንግሥት (አሁን እየተባለ እንዳለው) ከነሙሉ ጥቅሙና ክብሩ እየተተገበረ ባለበት ፀንቶ የሚቆይ ከሆነ – አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ አንፃር ራሱ ቢገመገም – የትግራይም ክልል ቢሆን አዋጪነቱን አይቶ ወደፊት ራሱን ቢያንስ ወደ 6 የተለያዩ ክልሎች የመከፋፈል ዕድሉ ከፍ ያለ ነው፡፡ ትግሬ፣ ወልቃይት፣ ኢሮብ፣ እንደርታ፣ ራያ፣ ተምቤን፣ ወዘተ እየተባለ ከትግራይ ክልል ውስጥ በትንሹ 6 ክልሎች መውጣታቸው አይቀርም፡፡ አለበለዚያ ሌሎች በርካታ አዳዲስ ክልሎች እየበዙ በሚሄዱበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ወያኔ አንድ አናሳ ክልል ብቻ ታቅፎ ሊቀር ነው ማለት ነው፡፡
/በነገራችን ላይ… በአኳኋናቸው ሲታይ ወያኔ፣ ኦነግና አብን ለምሳሌ – ሶስቱም ከላይ ሲታዩ – አሁን በወያኔ በተዘረጋው ነባሩ ህገመንግሥት በአንድ ጥላ ሥር የተጠቃለለላቸውን የትግራይ፣ የኦሮሚያ እና የአማራ ሕዝብ ተከፋፍሎ ከማየት ይልቅ የዕለት ሞታቸውን ቢሰጣቸው የሚመርጡ ይመስላሉ፡፡ ነገር ግን ጥያቄው – እንዲህ ካደረጉ ደቡብ ክልል ራሱን ወደ ብዙ ክልልነት ቀይሮ በሥሩ ያሉትን ሕዝቦች የሥርዓቱ የተሻለ የኢኮኖሚና ፖለቲካ ቱሩፋት ተቋዳሽ ሲያደርግ – ነገ ደግሞ ቤኒሻንጉል ጉሙዝም፣ ጋምቤላም ሌላውም ይሄንኑ የማይቀር አርአያ ሲከተል – እነዚህ ራሳቸውን የመከፋፈል ፖቴንሻል ያላቸው ሶስት ሰፋፊ ክልሎች ግን ወያኔ ሰፍሮ በሰጣቸው ቁመናና ባስቀመጣቸው ሥፍራ ባሉበት እየረገጡ ሊቀሩ ነው ማለት ነው፡፡ ከብዙ ምክንያቶች አንፃር – በወደፊቷ ‹‹የብሔር ብሔረሰቦች ህዝቦች›› ኢትዮጵያ – ይህ አዋጪ የፖለቲካ መስመር አይመስልም፡፡ ነው ብለው ከመረጡስ? – እነዚህ ሶስቱ ኃይሎች አሁን የያዙትን የሥልጣን መደላድል አስጠብቀው ለማቆየት – የቀድሞውን ወያኔን የሚተካ አዲስ የጋራ አምባገነን የጥምረት ኃይል ፈጥረው – የደቡብንም ሆነ የሌሎችን ሕዝቦች በርካታ አዳዲስ የክልልነት ጥያቄዎች የግድ መጨፍለቅ ሊኖርባቸው ነው ማለት ነው! ይሄ ደግሞ የማይመስል ነገር ነው!፡፡ ስለዚህ በቀጣይ በሚፈጠረው አዲስ የፖለቲካ አሰላለፍ የሚኖራቸው አዋጪ ምርጫ ወይ ራሳቸውን ወደ ብዙ ክልልነት ማብዛት – አሊያም በሌሎች ራሳቸውን በሚያበዙ አዳዲስ የሥርዓቱ ተጠቃሚ ክልሎች ተውጦ መቅረት ነው!/
ይሄ ሁሉ ሲታይ – ይሄ ህገመንግሥት አሁን በያዘው የክልል አወቃቀር ላይ ተንጠልጥሎ ከቀረ – ወደፊት በሀገሪቱ ቁጥራቸው በትንሹ ከ38 እስከ 54 የሚደርስ አዳዲስ ክልሎች ይፈጠራሉ፡፡ ሕገመንግሥቱም በአማካይ የ45 ክልሎች ህገመንግሥት ስለሚሆን በዚሁ መሠረት እነዚህኑ እንዲያካትት ሆኖ መሻሻሉ አይቀርም፡፡ ይህም ሲታይ – አሁን ያለው የወያኔ-ኢህአዴግ ህገመንግሥት ቀድሞ የማዕዘን ራሱ አድርጎ በቀመረው ‹‹የብሔር›› ራስገዝ አስተዳደር መርህ ላይ እንደተንጠለጠለ የሚቀጥል ከሆነና – የህገመንግሥቱ መብቶች ያለምንም ከልካይ የጠብመንጃ አፈሙዝ በተግባር መዋል ከጀመሩ – ውጤቱ ከዚህ በፊት ከነበረው በበለጠ ሞገዳዊ መልኩ አሁን የምናያቸውን ክልላዊ መንግሥታት ወደ ብዙ ትንንሽ ክልላዊ መንግሥታትነት የሚቀይር አዲስ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ክስተት መፈጠር ይሆናል፡፡
የዚህ ህገመንግሥታዊ ሥርዓት ጉዞ አይቀሬ ፍፃሜው አዳዲስ የክልልነት ጥያቄዎችና አዲስ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ጥቅም ጠያቂ ሕዝብ መበራከት ይሆናል፡፡ በሌላ አነጋገር የዚህ ህገመንግሥት ፀንቶ መቆየት የመጨረሻ ውጤቱ:- “A new wave of Balkanization of regional governments swayed by peoples proclaiming better political and economic rights and freedoms as well as more politico-economic space and benefits from the existing national constitutional order”.
እና መፍትሄውስ ምንድነው? የሚለው ጥያቄ መመለስ ያለበት ወሳኝ ጥያቄ ይሆናል፡፡ What’s the way out? መፍትሄው? – መፍትሄው ቀላል፣ ሂደቱ ግን ከባድ ነው፡፡
_____________________________
/ማስታወሻ፡- የዚህ ዳሰሳና መላምት ምንጭ እንዳይጠቀስ በተጠየቀው መሠረት 32 ገጾች ካሉት ሰነድ ላይ ከላይ በቀረበው መልኩ ተጨምቆና ተተርጉሞ ቀርቧል፡፡/
Filed in: Amharic