>

ሰኔና ሰኞ ታሪካዊ አመጣጡና ያስከተላቸው ዳፋዎች! (ይታገሱ ዘውዱ)

ሰኔና ሰኞ ታሪካዊ አመጣጡና ያስከተላቸው ዳፋዎች!

ይታገሱ ዘውዱ
* መርዕድ አዝማች ልዑል ሰገድ መቼ እንደምሞት ንገረኝ ብለው ደብተራ ይጠይቃሉ። ሰኔ እና ሰኞ ሲገጠም አላቸው።
ልክ በዛን ቀን ሰኔ ፩ ቀን ሰኞ በአሽከራቸው እጅ ተገደሉ። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሰኔ ሰኞ ሲገጥም ይባላል።
 
ዓለም ከተፈጠረበት ወይም የቀን መቁጠሪያ ከተጀመረበት ጊዜ ጀምሮ ሰኔ እና ሰኞ በአስገራሚ መንገድ በየተወሰነ ዓመት ይገጥማሉ።
የሰኔ እና ሰኞ ነገር አስገራሚነቱ በዚ’ ይጀምራል።
ሌላ አስገራሚ ነገር እናክል።
ሰኔ እና ሰኞ በ5 እና በ6 አመታት ልዩነት ይመጣና ቀጥሎ በ5እና6 በመደመር በየ11 አመት ይመጣል፤ ይህም አንድ አበቅቴ ይሆናል።
ሰኔ እና ሰኞ ሌላም አስገራሚ ባህሪ አለው። በመቶ አመት ውስጥ ሁለት ጊዜ በጎዶሎ፤ ሁለት ጊዜ በሙሉ ቁጥር እያከታተለ ይመጣል።
ከሌሎች ወራት በተለየ፤ ሰኔ እና ሰኞ በፈረንጅ ካላንደር ከገጠመ፤ በሳምንቱም በኢትዮጵያ ካላንደርም ሰኔ እና ሰኞ መልሶ ይገጥማል።
የሰኔ እና ሰኞን ግጥምጥሞሽ… እንደዋዛ ፈዛዛ በጨዋታ መልክ የሚያልፉት ሰዎች የመኖራቸውን ያህል፤ በአውደ ቀመር የተካኑ፤ ስለመጥዕቅ በምጥቅ እና በጥልቅ የሚያውቁ የጥንት አባቶች ግን፤ ነገሩን በዋዛ የሚያዩት አይመስልም። ቀን ቆጥረውና አመታት አስልተው ሰኔ እና ሰኞ የሚገጥምበትን አመት፤ በጥንቃቄ እንድናልፈው ይመክሩናል። እኛም እንደሊቃውንት አባቶቻችን፤ የባህረ ሃሳብን እውቀት እና ቀመር መሰረት አድርገን በአገራችንና በአለማችን የተከሰቱ የሰኔ እና የሰኞ ግጥምጥሞሽን፤ ትንሽ በትንሽ እንጨዋወታለን።
በኢትዮጵያ ክፉ ቀን የምንለው… ረሃብ፣ በሽታ እና ጦርነትን ነው። የሰው ብቻ ሳይሆን የከብት በሽታ ጭምር… የኑሮ ሚዛን የሚያዛባበት አጋጣሚ አለ። በ1880 ዎቹ መጀመሪያ ላይ በኢትዮጵያ አስከፊ ረሃብ ሲቀሰቀስ፤ በስተበኋላም ብዙ ቸነፈር ሲወርድ፤ ሰኔ እና ሰኞ ገጥሞ ነበር። የከዋክብት ስነ ፈለግ እውቀት የነበራቸው አባቶችም፤ የሰኔ እና ሰኞን ግጥምጥሞሽ ከከዋክብቱ ተጽዕኖ ጋር ቀምረው፤ መጪውን የረሃብ ወይም የጦርነት ዘመን በትክክል ይተነብዩ ነበር። ዛሬ የምናደርገው… የቻልነውን ያህል አውደ ታሪክ ፈትሸን፤ “በእርግጥ ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም ምን ተፈጠረ?” የሚለውን ይሆናል።
ከዚያ በፊት ግን አጼ ምኒልክ፣ አባታቸው ንጉሥ ኃይለ መለኮት፣ ልጃቸው ንግሥት ዘውዲቱ፣ እቴጌ ምንትዋብ፣ እቴጌ መነን… ሁሉም ከሰኔ እና ሰኞ አንድ አመት በፊት ወይም በኋላ ነው ህይወታቸው ያለፈው። ይህን ያህል ስለደጋጎቹ ካወጋን፤ ሌላውን ታሪክ በግርድፍ ፈጠን ቀልጠፍ ብለን እናወጋችኋለን።
ወደ ዝርዝር አውደ ታሪካችን ከመግባታችን በፊት፤ ጥቂት ስለሰኔ እና ሰኞ አስገራሚ ባህሪ እንግለጽላቹህ። ሰኔ እና ሰኞ በ5 እና በ6 አመት፤ ከዚያም ከ11 አመታት በኋላ ይመጣል። ከ11 አመታት በኋላ የሚመጣው ሰኔ እና ሰኞ፤ በአገሪቱ ላይ የጦርነት ወይምየበሽታ ወይም የረሃብ ደመና ሊመጣ እንደሚችል ያመላክታል። እናም ለሚቀጥሉት አመታት ዝግጅት ካልተደረገ፤ በ3ኛው አመት ላይ የከፋ ቸነፈር ይወርዳል። ለምሳሌ ከ11 አመታት በኋላ… በ1880 ሰኔና ሰኞ ገጠመ። ዝግጅት ስላልተደረገ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት አመታት ከሃምሳ ሺህ በላይ ሰዎች በረሃብ ቸነፈር አለቁ። እንዲህ እንዲህ እያልን ባለፉት 200 አመታት የሆነውን ነገር አብረን እንመልከት።
ከአንቀጹ በፊት ያስቀመጥነው አመት ሁሉም እንደፈረንጆች የቀን አቆጣጠር ሲሆን፤ ዝርዝር ታሪኩን ደግሞ ስንገልጽ በኢትዮጵያ ቀን አቆጣጠር እያልን ጽፈነዋል።
>> የሰኔ እና ሰኞ መጥፎ ግጥምጥሞሽ ተምሳሌቶች ፦
1812 በዚህ አመት ሰኔ እና ሰኞ ገጠመ። የንጉሥ ሳህለስላሴ አባት …መርድ አዝማች ወሰንሰገድ በዚህ አመት ከጦርነት በኋላ በብርቱ ቆስለው ሞቱ።
1829 በኢትዮጵያ ከፍተኛ ረሃብ ሆነ። ረሃቡን ተከትሎ የኮሌራ በሽታ በመምጣቱ በተለይ በሸዋ እጅግ ብዙ ሰው ሞተ።
1846 የዚህን አመት ሰኔ እና ሰኞን ተከትሎ፤ የሸዋ ንጉሥ የነበሩት፤ የምኒልክ አያት ንጉሥ ሳህለስላሴ ከዚህ አለም በሞት ተለዩ።
1857 በ19ኛ ክፍለ ዘመን ከነበሩት የሰኔ እና ሰኞ አበቅቴዎች መካከል፤ ይሄኛው አንደኛውና ተጠቃሽ ዘመን ነው። በኢትዮጵያ አቆጠጠር 1849 ዓ.ም መሆኑ ነው። ጥንቃቄ፣ ዝግጅት፣ ጸሎት እና ግዝት ካልተደረገ በቀር፤ አበቅቴ ላይ የሚያርፈው ሰኔ እና ሰኞ በተከታታይ አመታት የሚያመጣው ቸነፈር ከበድ ያለ ይሆናል። ይህ ዘመን የአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ነው። በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1849 ሰኔ እና ሰኞ ከገጠመ በኋላ፤ አጼ ቴዎድሮስ በእጃቸው ያለውን እያጡ የነበረበት ፈታኝ ዘመን ነበር። በጎጃም ደጃች ተድላ ጓሉ፣ በሸዋ ሰይፉ መሸሻ፣ በሰቆጣ ዋግሹም ገብረ መድህን፣ በጎንደር ጋረድ ክንፉ እና ግንባሮ ካሳ፣ በትግራይ ደጃች ንጉሴ… አምጸውባቸው፤ ወሎ እና ቤጌምድርም አልገዛም ብሎ ያስቸገረበት ወቅት ነው። የጎንደር ቀሳውስት ተሰብስበው፤ ለአጼ ቴዎድሮስ አዲስ የመንግስት አሰራር እንዲከተሉ በድፍረት የተናገሩበት ሁኔታ ተከስቷል።
ከዚያ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ የሸዋ መኳንንት የሚገደሉት ተገድለው፤ የተቀሩት እጃቸውን የተቆረጡበትን አጋጣሚ እናስታውሳለን። ሌላው ቀርቶ በአመቱ የአጼ ቴዎድሮስ ሚስት፤ እቴጌ ምንትዋብ በ1851 ዓ.ም ሞቱ። ቀጥሎም የእንግሊዝ ወኪል ፕላውዴንን የአጼው ዘመድ ጋረድ ክንፉ በጦር ወግተው ገደሏቸው። ከዚያም እንግሊዛዊ አማካሪያቸው፤ ጆን ቤል ሞተ። ከዚህ በኋላ የነበረው ምስቅልቅል በቃላት ብቻ ተገልጾ የሚያልፍ አይደለም። ካልተዘጋጁበት በቀር፤ የአበቅቴው ሰኔ እና ሰኞ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ተከታታይ የችግር ቸነፈሮች አልፈዋል።
1863 በአሜሪካ ደግሞ የርስ በርስ ጦርነት የተጀመረበት፤ ሲሆን፤ በጦርነቱም ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ሞተዋል።
1868 አጼ ቴዎድሮስ April 17, 1868 (1860 ዓ.ም) ህይወታቸውን ያጠፉበት አመት፤ ሰኔ እና ሰኞ የገጠመበት አመት ነበር።
1891 – ከአንድ አበቅቴ ወይም ከ11 አመት በኋላ የሚመጣው የሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ አስፈሪ ነው። ከአበቅቴው በኋላ ጥንቃቄ እና ዝግጁነት ያስፈልጋል። ይህ ካልሆነ ግን በሁሉም የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እንደምናውየው አይነት የረሃብ እና የበሽታ ውሽንፍር ይከሰታል። በዚህ ዘመን በቂ ዝግጅት እና ጥንቃቄ ባለመደረጉ በአገሪቱ ታይቶ የማይታወቅ አስከፊ ነገር ሆነ። ይህ ዘመን በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ “ክፉ ዘመን” በመባል ይታወቃል። በሰሜን ከአክለ ጉዛይ ጀምሮ ቤጌምድርን ጨምሮ፤ ሸዋ እና ሃረር… እንዲሁም እስከ ደቡብ ድረስ የዘለቀ ረሃብ እና በሽታ ተስፋፋ። የአምበጣ መንጋ ሳር ቅጠሉን፣ ጥሬ እህሉን ሁሉ ጨረሰ። በዚህ እንዳይበቃ… የኮሌራ፣ የተስቦ እና የፈንጣጣ በሽታ ህዝቡን እያሰቃየ ጨረሰው። በዚህ ምክንያት የአጼ ምኒልክ የንግሥና በአል ጭምር ለሌላ ጊዜ ተዛወረ።
1896 ሰኔ እና ሰኞ የገጠመበት፤ የኢትዮጵያ እና የጣልያን ጦርነት ተቀስቅሶ፤ በአምባላጌ፣ በመቀሌ እና በአድዋ በብዙ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን የሞቱበት ዘመን ነው። ምንም እንኳን ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢደመደምም የጦርነት መልካም ስለሌለው የሰው ልጅ ህይወት የተገበረበት፤ የሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥም ውጤት ነው።
1914 – ሰኔ እና ሰኞ ከመግጠሙ አንድ አመት በፊት የሚሞቱ ሰዎች ከደጋጎቹ አባቶች የሚመደቡበት አጋጣሚ አለ። ለዚህም ይሆናል… አጼ ምኒልክ ህይወታቸው ያለፈው፤ አንድ አመት ቀደም ብለው ታህሳስ 3 ቀን፣ 1906 ሲሆን፤ የንጉሠ ነገሥቱ ሞት ይፋ አልተደረገም ነበር። አባታቸው ንጉሥ ኃይለመለኮት በተመሳሳይ ሁኔታ ከሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ አንድ አመት ቀደም ብለው እንደአውሮጳ አቆጣጠር በ1856አረፉ።
በዚህ አመት ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም፤ በዚያው ወር ብዙ ደስ የማይሉ የጦርነት ነገሮች በአውሮጳ ይከሰቱ ጀመር። ፈረንሳይ፣ እንግሊዝ፣ ጀርመን፣ ጃፓን እርስ በርሳቸው ተበጣብጠው፤ በመቸረሻ የአንደኛው አለም ጦርነት በዚሁ አመት ተጀመረ።
1925 ይህ የአበቅቴ ሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥም አመት ቢሆንም፤ ህዝቡ ከህዳር በሽታ ገና ማገገሙ ነበር። የህዳር በሽታ… በንፋስ መጥቶ አርባ ሺህ ህዝብ ጨረሰ። አልጋ ወራሹና ንግሥቲቱ ጭምር ታመው አገገሙ። ህዝቡም ወደ ፈጣሪው እግዚኦታውን አበዛ። ሆኖም በዚህ አመት፤ ማለትም በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1917 ዓ.ም ሰኔ እና ሰኞ ስለሚገጥም፤ “ምን ይሰማ ይሆን ጆሮ?” ተብሎ ሲጠበቅ፤ አስገራሚ ነገር ሆነ።
የንጉሥ ሳህለስላሴ የልጅ ልጅ… የራስ ዳርጌ ልጅ፤ ወ/ሮ ፀሃየወርቅ ዳርጌ በአልጋ ወራሽ ተፈሪ መኮንን ላይ አስገራሚና የተቀነባበረ፤ የመግደል ሙከራ አስደረጉ። አላማውም አልጋወራሹን በማስገደል፤ ልጅ እያሱን እንደገና ወደ ስልጣን ለማምጣት ሲሆን፤ ተኩሶ ለመግደል ከተመደቡት ሰዎች መካከል መሃመድ አባ ሻንቆ፤ አነጣጥሮ ሲተኩስ ጥይቱ ከሸፈበት። በሌላ አቅጣጫ አልጋወራሹን ለመግደል የተመደበው ሰው ደግሞ፤ ሊተኩስ ሲል እጁ ዝሎበት ስለተንቀጠቀጠ መተኮስ አቅቶት ተያዘ። አልጋ ወራሽ ተፈሪም ከሞት ተርፈው፤ በመግደል ሙከራ የተካፈሉት ሰዎች በሙሉ ታሰሩ። ይህም ሰኔ እና ሰኞ በገጠመበት የሰኔ ወር በመከናወኑ… ህዝቡ “ወይ ሰኔ እና ሰኞ?!” እያለ ይገረም ነበር። አልጋወራሹ ቢገደሉ ኖሮ…. ሊመጣ ከሚችለው የአበቅቴ ቁጣም ህዝቡ ዳነ።
በሌላ በኩል ግን በዚሁ አመት፤ በ1925 የጣልያን አምባገነን አመራር ተመሰረተ። የአገሪቱ ፕሬዘዳንት ቤኒቶ ሙሶሎኒ (ጃኑዋሪ 3 ቀን) የአገሪቱን ፓርላማ በትኖ፤ ብቻውን አምባገነን መሪ ሆነ። ኢትዮጵያንም ለመውረር ዝግጅት ያደርግ ጀመር። በዚህ አመት አዶልፍ ሂትለት እና ፓርቲው ብቸኛ የጀርመን መሪዎች መሆናቸውን አወጁ። በአሜሪካ የነጭ በላይነት ገነነ። በዚሁ አመት ኦገስት 28 ቀን፤ 40 ሺህ የኬኬኬ አባላት ነጭ መለዮዋቸውን ለብሰው፤ በዋሺንግተን የሰልፍ ትርኢት ሲያደርጉ የአለም መጨረሻ አስመሰሉት።
1931- ሰኔና ሰኞ በገጠመ በአመቱ ንግሥተ ነገሥታት ዘውዲቱ ምኒልክ ህይወታቸው አለፈ። ይህ አመት ደግሞ በባህር ማዶ ሰዎች ዘንድ የሚታወቀው የ Great Depression መጀመሪያ በመሆኑ ነው። በአውሮጳ እና በአሜሪካ እንደመጥፎ ዘመን ይቆጠራል።
1936 – በዚህ አመት በኢትዮጵያ አስደንጋጭ ነገር ተፈጠረ። የጣሊያን ወረራ ተደረገ። ሰኔ እና ሰኞ ገጠመ። ጣልያኖች ከስሜን አልፈው፤ ማይጨውን ትሻግረው አዲስ አበባ ገቡ። ዘመኑ ለኢትዮጵያውያን የከፋ ሆነ።
1942 – የሁለተኛው አለም ጦርነት ተፋፍሞ፤ ጀርመን በመላው አውሮፓ ፍጹም የበላይነትን የተቀዳጀችበት አመት ነበር። ከዚህ አመት ጀምሮ ለቀጣይ 3 አመታት ናዚዎች – የአይሁድ ዝርያ ያላቸውን ሰዎች እያደኑ፤ በከፋ እና በሚዘገንን መንገድ ገደሏቸው፤ ዘራቸውን የማጥፋት ስራ ተሰራ በውጤቱም ከ6-11 ሚሊዮን አይሁዶች ተገደሉ።
1953 – የዚህ አመት ሰኔ እና ሰኞ በአንድ አበቅቴ (ከ11 አመት በኋላ)የሚመጣ ነው። ከአንድ አበቅቴ በኋላ… ጥንቃቄ ካልተደረገ በቀጣዩ አመታት በኋላ፤ ረብሻ እና ግርግር ይኖራል። ረሃብ እና ጦርነት ይሆናል። ጥንቃቄ መደረግ ያለበት በጾም እና በጸሎት ጭምር ነው። በዚህ የአበቅቴ ዘመን የተፈራው ረሃብ እና ቸነፈር አልመጣም። መልካም ነገር እንዲሆን ምክንያት የሆነው በቂ ዝግጅት ስለተደረገ፤ ህዝቡም በጽናት ወደ ፈጣሪው ጸሎት ስላደረሰ ሊሆን ይችላል። በ’ርግጥም በዚህ አመት ከክርስትና ቤተ-እምነቶች በተጨማሪ የቢላል መስጊድ ተመርቆ፤ እስላም እና ክርስቲያኑ ወደ አምላኩ ጸሎት ያደርስ የነበረበት መልካም ዘመን መሆኑን የታሪክ ድርሳናት ይመሰክራሉ። ለዚህም ይሆናል በአበቅቴው ሰኔና ሰኞ በአገሪቱ ላይ ክፉ ቸነፈር ሳይወርድ የቀረው።
1959 በዚህ ዘመን ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም… “ምን ሊመጣ ይሆን?” መባሉ አልቀረም። ሆኖም በቀጣዩ አመት በ1960ንጉሠ ነገሥቱ ለጉብኝት ወደ ብራዚል በሄዱበት ወቅት፤ የክቡር ዘበኛ ጦር አመጽ አስነስቶ፤ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አደረገ። ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ አይታ የማታውቀውን፤ የተቀነባበረ የመፈንቅለ መንግስት ሙከራ አስተናገደች። በጄ/ል መንግስቱ ንዋይ እና በገርማሜ ንዋይ የተመራው መፈንቅለ መንግስት የ600 ሰዎችን ህይወት ቀጠፈ፤ ብዙዎች ታሰሩ፤ ጥቂቶች ተሰደዱ። በንጉሠ ነገሥቱ እና በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግን ጥቁር ጠባሳ ጥሎ አለፈ – የታህሳሱ ግርግር።
1964 በአባቶቻችን ዘመን አንድ የሚያስታውሱት የ”ሰኔ እና ሰኞ” ገጠመኝ ነበር። በኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1956 ዓ.ም. ሰኔ እና ሰኞ ገጠመ። ይህንኑ ተከትሎ “ምን ይመጣ ይሆን?” ተብሎ ሲጠበቅ፤ አንድ አዲስ የመንገድ አዋጅ ወጣ። ከሰኞ ሰኔ 1 ቀን ጀምሮ፤ በግራ በኩል ይሄዱ የነበሩ ወደ ቀኝ፤ በቀኝ ይሄዱ የነበሩ መኪኖች ደግሞ በግራ በኩል እንዲያሽከረክሩ ህግ ወጣ። ከዚያ ቀን በፊት… መኪኖች በሙሉ አሁን በሚሄዱበት በተቃራኒ መንገድ ነበር የሚሄዱት። ከዚያን ወዲህ ግን… የመኪና መንገድ አካሄድ መቀየሩን በአባቴ እድሜ የነበሩ ሰዎች፤ “ወይ ሰኔ እና ሰኞ” እያሉ በመገረም ሲያወሩ እንሰማ ነበር። በዚሁ አመት 1956 ዓ.ም. አለማችንን ያስደነገጠ ትልቅ ክስተትም ተስተናግዷል። የአሜሪካው 35ኛው ፕሬዘዳንት፤ ጆን ኤፍ ኬኔዲ የተገደሉት በዚሁ ሰኔና ሰኞ በገጠመበት አመት ነበር።
1970 – በአውደ ቀመሩ ስሌት መሰረት፤ ከ6 አመታት በኋላ የሚመጣው የአበቅቴው ሰኔ እና ሰኞ፤ በመጪው አመታት በአገሪቱ ጦርነት እና ብጥብጥ ሊነሳ እንደሚችል አመላካች ነው። (በእርግጥ እንዲህ አይነቱን የዘመን ትንቢት ለመናገር የከዋክብት ስነ-ፈለግን ምጥቅዕ እውቀት መጨመር ያስፈልጋል።) የሆኖ ሆኖ በዚህም መሰረት 1962 ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም፤ ለኢትዮጵያ ትልቅ ማስጠንቀቂያ ነበር። በዚህ አመት በኤርትራ በርሃ የመጀመሪያዋ የመገንጠል ጥያቄ ጥይት ተተኮሰች። በውጭ አገር እና በአገር ውስጥ የሚገኙ ተማሪዎች፤ በሶሻሊዝም አደረጃጀት ተመሰረቱ። እንደተፈራውም በቀጣዩ አመታት በአገሪቱ ቁጣ ወረደ። በወሎ እና አካባቢው የረሃብ ቸነፈር መጣ። የተማሪዎቹን እንቅስቃሴ ተከትሎ አመጽ ተነሳ፤ መንግስት ተገለበጠ፤ ትርፍ ቤት እና የግል መሬት ተወረሰ። ተቃዋሚዎች በዙ፤ ቀይ ሽብር ተፋፋመ። ንጉሠ ነገሥቱም ተገደሉ።
1981 – ከአንድ አበቅቴ በኋላ የሚመጣ ሰኔ እና ሰኞ ያስፈራል። ምክንያቱም የአበቅቴውን ሰኔ እና ሰኞ ተከትሎ፤ ከሶስት አመታት በኋላ የሚመጣው የረሃብ ቸነፈር ከበድ ያለ ነው። በመሆኑም በቂ ዝግጅት ካልተደረገ መጪዎቹ አመታት የከፉ እንደሚሆኑ አውደ ቀመሩ ያሳያል። ለኢትዮጵያም … መጪው ዘመን መልካም እንደማይሆን የማስጠንቀቂያ ደወል የተሰማበት ነበር። ጊዜው በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1973 ሲሆን፤ የአበቅቴው ሰኔ እና ሰኞ ገጠመ። እንደሁልጊዜውም ከ3 አመት በኋላ፤ የረሃብ ቸነፈር በኢትዮጵያ ወረደ። ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ የተከሰተው የረሃብ ቸነፈር፤ ከኢትዮጵያ አልፎ በመላው አለም ተሰማ። በሌላ በኩል ደግሞ ከዚህ አመት ጀምሮ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የሚደረገው ጸረ-ደርግ ትግል ተጠናክሮ ቀጠለ።
1987 – ይህ ዘመን ለኢትዮጵያ ክፉ የጦርነት ዘመን ሆኖ ነው ያለፈው። በሰሜን ኢትዮጵያ የሻዕቢያ፣ የወያኔ እና የኢህዴን ተዋጊዎች በጣም የተጠናከሩበት፤ የኢትዮጵያ ጦር ሰራዊት ደግሞ ተስፋ የቆረጠበት እና ብዙዎች በየቀኑ የሚሰዉበት ዘመን ነበር። በተለይም አንድ አመት ቀደም ብሎ የናደው ክፍለጦር መሪ፤ ጄነራል ታሪኩ ከተገደለ በኋላ ሁኔታዎች መልካቸውን ቀየሩ። ጦርነቱ እየተፋፋመ ሄዶ፤ ሻዕቢያ በብዙ ቦታዎች ድል አገኘ። ህወሃት እና ኢህዴን ተዋህደው፤ ኢህአዴግ የሚባል ድርጅት መሰረቱ። ጦርነቱ በጣም የከፋ ነበር። በአመቱ በጄ/ል ፋንታ በላይ የተመራ ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት ቢደረግም፤ ውጤቱ የብዙ ጄነራሎች ሞት ሆነ። በአጠቃላይ ይህ ዘመን እጅግ ተስፋ አስቆራጭ በመሆኑ፤ መጪው ጊዜ ጨለማ ሆኖ የታየበት ወቅት ነበር።
በዚህ አመት ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም… ዘመኑ ለራሺያ ጥሩ አልነበረም። የታላቋ ሶቪየት ህብረት አገራት፤ ኢስቶንያ፣ ሊቱንያ፣ ላትቭያ የነጻነት እንቅስቃሴ ጀመሩ። በዚህ አመት የተጀመረውን የነጻነት ጥያቄ ተከትሎ፤ የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት ቀስ በቀስ ተበታተነች። የኢራን እና ኢራቅ ጦርነት እጅግ የከፋ ደረጃ ላይ ደረሰ። የአለማችን የመጀመሪያው የባህረ ሰላጤው ጦርነት ተቀሰቀሰ። የበርሊን ግንብ ፈረሰ። መካ መዲና ለኢድ የሄዱ፤ የኢራን ሙስሊሞች ባስነሱት ረብሻ ምክንያት፤ የሳኡዲ ፖሊሶች 402 ሰዎችን ገደሉ። ይህም ከዚያ በፊትም ሆነ በኋላ ተሰምቶ የማያውቅ ግድያ ሆኖ ተመዘገበ።
1992 – ይህ ዘመን በኢትዮጵያ አቆጣጠር 1984 ነው። በዚህ ወቅት ኢህአዴግ አገሪቱን ተቆጣጥሮ የሽግግር መንግስት ያቋቋመበት፤ ብዙዎች በዘር እና በጎሳ ጸብ ምክንያት የተገደሉበት፤ ኤርትራ የተገነጠለችበት፤ በብዙ መንገድ የኢትዮጵያ ታሪክ የተቀየረበት ነው።
በሌላ በኩል… ይህ ዘመን ለአሜሪካ አስከፊ ዘመን ነበር። በዚህ አመት ሰኔ እና ስኞ ከአምስት አመታት በኋላ እንደገና የሚገጥምመበት ጊዜ ሆነ። አጋጣሚውም እስከዛሬ ድረስ የአሜሪካን ታሪክ ያጠለሸ፤ በጥቁር ቀለም የተጻፈ ቅሌት ትቶ አለፈ። ፖሊስ በጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚፈጽመውን በደል ተከትሎ፤ በሎስ አንጀለስ ከተማ ብቻ (ሌላውን የአሜሪካ ከተሞች ሳይጨምር) በሎስ አንጀለስ ብቻ 3 ሺህ ስድስት መቶ ቦታዎች እሳት ነደደ። አንድ ሺህ አንድ መቶ ህንጻዎች በእሳት ጋዩ። 2ሺህ ሰዎች ተጎዱ፤ ስልሳ ያህል ሰዎች ሞቱ።
1998 – በመቶ አመት አንድ ጊዜ፤ አዲስ ሚሊኒየም ከመጀመሩ በፊት የአበቅቴ ቀመር ይቀየራል። እናም በ5፣ በ6 ኣና በ11 አመት የሚመጣው ሰኔ እና ሰኞ ቀመሩ ይቀየርና ከስምንት አመታት በኋላ… ሰኔ እና ሰኞ ይገጥማል። ይህን ተከትሎ በዚህ አመት ሰኔ እና ሰኞ የሚገጥምበት ጊዜ በመሆኑ፤ በኢትዮጵያ ላይ “ምን ይመጣ ይሆን?” ተብሎ ሲጠበቅ፤ በግንቦት ወር የተሰማው ዜና መልካም ሳይሆን ቀረ። የኢትዮጵያ እና የኤርትራ ጦርነት ፈነዳ። ከሰኔ ወር በኋላ ጦርነቱ ተፋፍሞ ቀጠለ። በጥቂት ወራት እና በአንድ አመት ውስጥ ከመቶ ሺህ በላይ ወታደሮች ሞቱ። ነዋሪዎች ተፈናቀሉ።
በሌላው አለም ደግሞ ጂሃድ ታወጀ። ኦሳማ ቢን ላዲን በአሜሪካውያን የሚፈለግ ሰው ቢሆንም፤ እስካሁን ጂሃድ አላወጀም ነበር። በዚህ አመት ግን በእስራኤል እና አሜሪካውያን ላይ ጅሃድ አወጀ። በዚህ ጂሃድ ምክንያት የብዙ አሜሪካውያን ህይወት ጠፋ። በዚሁ አመት በኬንያ እና በታንዛንያ በአንድ ቀን (ኦገስት 7) በአሜሪካ ኢምባሲ ቦምብ ፈንድቶ፤ 224 ሰዎች ተገደሉ፤ 4ሺህ 500 ሰዎች ላይ ጉዳት ደረሰባቸው። በተለይ ይህን የጂሃድ መልዕክት ተከትሎ፤ ከ3 አመታት በኋላ… ማለትም በ2001 ላይ፤ በኒው ዮርክ እና በሌሎች የአሜሪካ ክፍለ ግዛቶች፤ ሴፕቴምበር 11 ቀን ጥቃት ተፈጸመ።
2009 – ይህ በአንድ አበቅቴ የሚመጣ የሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ እንደመሆኑ መጠን፤ በሚቀጥሉት አመታት ሊያመጣ የሚችለው የሃዘን፣ የጦርነት እና የረሃብ ቸነፈር ያስፈራል። አዲሱ ሚሊኒየም ከገባ በኋላ ሰኔ እና ሰኞ የገጠመው በ2009 ዓ.ም ነበር። ከላይ እንደገለጽነው ከአንድ አበቅቴ በኋላ የሚመጣው ጊዜ፤ ለአንድ አገር የማስጠንቀቂያ ዘመን ነው። ጦርነት እና የረሃብ ቸነፈር እንዳይመጣ መጪውን ሶስት አመት በጥንቃቄ መጠበቅ ያስፈልጋል። በኢትዮጵያ አቆጣጠር 2001 ዓ.ም ነበር። በቀጣዩ 3 አመታት ውስጥ ምን ሊመጣ እንደሚችል ሲጠበቅ፤ ያልተጠበቀ ነገር ሆነ። ፓትሪያርኩ አቡነ ጳውሎስ እና ጠ/ሚ መለስ ዜናዊ ተከታትለው በሞት ተለዩ። በተለይ የመለስ ዜናዊን ሞት ተከትሎ፤ “መጪው ጊዜ ብጥብጥ እና ጦርነት ይዞ ሊመጣ ይችላል” ተብሎ ብዙ ስጋት ነበር። ብዙዎች እንደሚያስታውሱት፤ በዚያን ሰሞን ህዝቡ በጸሎቱ ተግቶ ወደ ፈጣሪው አለቀሰ፤ አምላክም ጸሎቱን ሰማ። የተፈራውም የርስ በርስ ጦርነት ሳይከሰት ቀረ።
በሌላ በኩል ደግሞ… ከሁለተኛው የአለም ጦርነት በኋላ አለማችን በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ የገባችው በ2009 ነበር። ይህ የኢኮኖሚ ድቀት የተከሰተውም በ- 2009 ነው።
2015 – ከአምስት አመታት በኋላ በ2015 ሰኔ እና ሰኞ ሲገጥም፤ አዲስ እና አስገራሚ ዜና በአሜሪካ ተሰማ። ሰኔ እና ሰኞ ተገጣጥሞ ባለፈ ማግስት ዶናልድ ትራምፕ ለአሜሪካ ፕሬዘዳንትነት እንደሚወዳደሩ በይፋ አሳወቁ። ይህም የመጥፎው ቀን ምጽአት፤ የመጀመሪያው ምልክት ሆነ።
2020 – በዚህ አመት እንደተለመደው፤ በፈረንጆቹም ሆነ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ሰኔ እና ሰኞ ገጥመዋል። ግጥምጥሞሹ ግን… ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን፤ ለመላው አለም ኮሮና ቫይረስን ተሸክሞ፤ የበሽታ ቸነፈር ይዞ ነው የመጣው። ይህ ጥናታዊ ጽሁፍ በተጠናቀረበት ወቅት፤ በመላው አለም ሶስት መቶ ሺህ ሰዎች ህይወታቸው ሲያልፍ፤ ከመቶ ሺህ በላይ የሚሆኑት አሜሪካውያን ናቸው። በዚሁ አመት በአሜሪካ የሚደርሰውን የቀለም ልዩነት ምክንያት በማድረግ፤ ሰፊ የሆነ ሰላማዊ ሰልፍ እየተደረገ ነው። ሁኔታው ሁሉ የአለም መጨረሻ ሊመስል ይችላል። አመቱ ምን እንደሚመስል አብረን እያየነው ስለሆነ ማብራሪያ አያስፈልገውም ይሆናል። ነገር ግን ሰኔ እና ሰኞ ገጥሞ የአለማችን አውደ ህይወት ቀጥሏል።
መጪውን ዘመን መተንበይ የሚፈልጉ ሰዎች ካሉ፤ በሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥም አመታት ላይ፤ የከዋክብትን ስነ ፈለጋዊ እውቀት ጋር ቢያቀናጁት የተሻለ ውጤት ሊያገኙ ይችላሉ። ከጊዜ በኋላ የስነ ከዋክብት እውቀት እየደበዘዘ በመምጣቱ እንጂ፤ ከባቢሎን ዘመን በፊት ጀምሮ፤ ሊቃውንት እቀት እና ጊዜያቸውን በከዋክብት ቀመር ላይ ያጠፉ ነበር። በውጤቱም በአገራቸው ላይ ሊመጣ የሚችለውን የረሃብ፣ የበሽታ፣ የድርቅ እና የጦርነት ዘመን ቀድመው መተንበይ እና መናገር ይችሉ ነበር። ጥሩ ምርት የሚገኝበትን ተድላ እና ሃሴት የሚሆንበትን፣ ታዋቂ ሰዎች እና ነገስታት የሚሞቱበትን፤ ያንን ተከትሎ የሚመጣውን ውጣ ውረድ ጭምር ይናገራሉ፤ ማስጠንቀቂያም ይሰጣሉ። እውቀቱ አሁንም አለ።
ለማንኛውም ከዚህ በታች ሰኔ እና ሰኞ የሚገጥምባቸውን አመተ ምህረቶች አስቀምጠናል (ሁሉም በፈረንጅ አቆጣጠር ነው) ትንቢት መናገር የሚፈልጉ ካሉ፤ በነዚህ አመታት የከዋክብትን ተፅእኖ (ማለትም መጪው ጊዜ፣ የጦርነት፣ የረሃብ፣ የበሽታ) መሆኑን በመተንበይ፤ ጸሎት እና ምህላ የሚያስፈልግበት ዘመን ካለም፤ ሁሉም እንደየእምነቱ ወደፈጣሪው ኤሎሄ የሚልበትን ወቅት ሊነግሩን ይችላሉ። ከዚህ በታች ያሉት አመታት ሰኔና ሰኞ የሚገጥምባቸው ናቸው።
2026፣ 2037፣ 2043፣ 2048፣ 2054፣ 2065፣ 2071፣ 2076፣ 2082፣ 2093፣ 2099 – በየ11 አመት በሚመጣው የአበቅቴ ጥሎሽ ወይም በሰኔ እና ሰኞ ግጥምጥሞሽ ማመን ወይም አለማመን የግል ምርጫ ነው። እኛ ግን እንላለን 2026 እስከሚመጣ ድረስ… መጪው ዘመን የሰላም ይሁንልን።
Source DKW
Filed in: Amharic