>

የእኛ ሠፈር ድሀ አጭር የህይወት ታሪክ ...!!! [በዕውቀቱ ሥዩም]

የእኛ ሠፈር ድሀ አጭር የህይወት ታሪክ …!!!

በዕውቀቱ ሥዩም

 ጎረቤቴ ሞተ !!!! በሞተ በሁለት ሳምንቱ ታሪኩን የመጻፍ ሐሳብ መጣልኝ ። ልቤ ፃፍለት ፃፍለት ብሎ ሲጎተጉተኝ አእምሮዬ ግን ” ድሀ ምን ታሪክ አለው ?” ብሎ ጠየቀኝ ። እውን ድሀ ታሪክ የለውም ?”።
ብድግ ብድግ ማለቱን ትቼ ስለጎረቤቴ ልናገር ። ጎረቤቴ ነጋ ፈጠነ ሞተ። የቀብሩ ስነ ሥርዓት ላይ ምንም ነገር ባለመነበቡ ስለተፀፀትኩ እቤቴ ሆኜ ይሄን ጽፌአለሁ ።
የልደት ቦታና ጊዜያቸው በጥንቃቄ የሚመዘግብላቸው ሰዎች ሀብታሞችና ዝነኞች ብቻ ናቸው ። ለምሳሌ ከመንደራችን መግቢያ ላይ ያሉት ባለአራት ወፍጮው ባለጸጋ የሞቱ ጊዜ እንዲህ ተብሏል ። ”አቶ ለጥይበሉ ይታገሱ በ1927 መጋቢት ሁለት ቀን ልክ ከምሽቱ አራት ሰዓት ተኩል ከሁለት ደቂቃ ከሃያ ሁለት ሰከንድ ላይ ተወለዱ ። እሳቸውን በወለዱ ጊዜ እናታቸው ሰማያዊ ቢጃማ ለብሰው ጥቁር ሻሽም አስረው ነበር። ” ይህ ትልቅ ዕድለኛነት ነው መቼም ፤ የኔ ጎረቤት ግን ይህን ሊታደል አይችልም ። ብቻ ማለት ያለብኝን ልበል። ጎረቤቴ ነጋ ፈጠነ ባንዱ ዘመን የሆነ ቦታ እንደዋዛ ተወለደ ።
ዕድሜው ለእህል ውሀ እንደደረሰ እናቱ ተጡቷ መንጨቃ ወደ ክርስትና አባቱ ዘንድ ወሰደችው። የክርስትና አባቱ ግን አጎራረሱንና፣ አቆራረሱን ክፋኛ በመፍራት እኔ እምበላው ሳጣ ፣ የክርስትና ልጄ ጥርስ አወጣ የሚል ተረት እጀጠባቡ ላይ በመስፋት ወደ ቤቱ አሰናበቱት ።
ነጋ ፈጠነ የጉርምስናና የልጅነት ዘመኑን እንዴት እንዳሳለፈው አይታወቅም ። እንዴት ሆኖ ልጅነቱን እንደጨረሰ እንዴት ሆኖ እንደጎረመሠም ማወቅ ብርቅ ነው ። የድሃና የሀብታም አጎረማመሥ እንደሚለያይ እዚህ ላይ ልብ ይሏል ። ሀብታም በጎረመሠ ጊዜ ከንፈሩ ፂም ያቀመቅማል፤ ድምፁ ይጎረንናል፤ ጡንቻው ይጓጉላል፤ ማታማታም በህልሙ ሴቶች ሲያቅፋት ያያል ። ድሀ ሲጎረምስ ግን ለየቅል ነው። ከንፈሩ ይሰነጣጠቃል፤ ድምፁ እንደ ፊሽካ ይቀጥናል፤ ጡንቻው እንደ ጅማት ይመነምናል ፤ በህልሙ ሴቶች ሲደበድቡት ያያል ። የድሀ ጉርምስናና የሀብታም እርጅና አንድ ናቸው ።
እንግዲህ ነጋ ፈጠነ በዚህ አኳኃን ከጎረመሰ በኃላ እንደዋዛ ወደ ጉልምስና ዘመን ተሸጋገረ ፤ በዚህን ጊዜ ነው ከኔ ቤት ለጥቆ ያለውን የመቃብር ቤት የመሰለ ኩሽና የተከራየው ።
ይህን ታሪክ ስፅፍ ነጋ ምን አይነት አለባበስ ያዘውትር ነበር ? የሚል ጥያቄ ከአንባቢያን እንደሚሰነዝር አውቃለሁ ፤ የነጋ ልብስ እንደለማኝ እህል ከዚያም ከዚያም የተጠረቃቀመ ነው ። አንዱ ጎረቤታችን አሮጌ ጅንስ ሰጠው ። ሌላው ጎረቤታችን ባለጥርብ ኮሌታ ሸሚዝ ሰጠው ። ለነገሩ እኔም በበኩሌ ሁለት ጥንድ አሮጌ ካልሲዎች ሰጥቼው ነበር ። ጫማ የለኝም ሲለኝ ወስድኳቸው።
የነጋ ፀባይ እንዴት ነው ? የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችላል ፤ ጎረቤት መባል ከቻለ ጥሩ ጎረቤት ነበር።( ጓሮ ቤት ቢባል ይሻለው ይሆን ?)
ፀጥተኛ ነው ።ይገባል ፤ ይተኛል ፣ ይገባል ፣ ይተኛል ፣ይገባል ፣ ይተኛል፤ በቃ ሌላ ነገር የለውም ? የሚል ጥያቄ ይነሳል ፤ ለጊዜው የማስታውሰው ይሄን ብቻ ነው ፤ ብቻ ….ብቻ አልፎ አልፎ ያፏሽካል፤…ሰው ሆኖ መማረሩ አይቀር ! አልፎ አልፎም ይነጫነጫል ። ”ምነው ድምፃችሁን ቀንሳችሁ ብታላምጡ!” ይላል በእራት ሰአት።
በባለፀጎች ቤት ጥቅሶች እንዳሉ ታውቃላችሁ ። ዋናው ጥቅስ አልጋ አጠገብ ይጻፋል ። ”ዛሬ ምን ሠራሁ ?” የሚል ይሆናል ጥቅሱ። ነጋ ግን ድሀ ነው ። ከምንጣፋ ፊት ለፊት በአተላ የተፃፈ ጥቅስ አለ” ዛሬ ምን በላሁ?” ይላል ፤ ሀብታሙም ደሃውም ለጥቅሱ የሚሰጡት መልስ አንድ ነው ”ም…ን…ም” ። ልዩነት ግን አለ ። ሀብታሙ ”ምንም” ብሎ ይተኛል ። ድሃው ”ምንም” ብሎ ያለቅሳል ።
{የጥቅስ ነገር ከተነሳ ሀብታሙ ቤት ”የረዳኝን እግዚአብሔርን አመሰግናለሁ” የሚል ሲለጠፍ ፣ እንደ ነጋ ዓይነቱ ድሀ ቤት ደግሞ ”የሚረዳኝ የለምና ከእኔ አትራቅ” የሚል ይሰቀላል።}
ታሪኩን ለማሳጠር ሲል እግዜር የነጋን ዕድሜ አሳጠረው። ሰላሳ ዓመት ይሆነዋል በግምት ፤ ድሀ ሰላሳ ዓመት ከሞላው ማቱሳላ ሆነ ማለት ነው ። ሞተ ።
የዚያን ቀን የዕድሩ ለፋፊ ጥሩንባ አልነፋም፤ ዳገት ላይ ወጥቶ ካጨበጨበ በኃላ ” እዚህ ግድም የሞተ ሰው ስላለ ፣ ሥራ የሌለባችሁ ቅበሩ ተብላችኋል !” ብሎ  አንድ ጊዜ ከተናገረ በኋላ ወደ ጠጅ ቤት ሄደ ።
የቀብሩ ሥነስርዓት በአስር ሰዎች አማካኝነት ተካሄደ ። አምስቱ የኔ ልጆች ናቸው ። እግረ መንገዳቸውን ሊሳለሙ የመጡ ሌሎች አምስት ሰዎችም ቀብሩ ላይ ተገኙ ።
መቃብር ቆፋሪዎች በነፃ መቆፈር ስላልፈለጉ ነጋ የተቀበረው ፍልፈል በማሠው ጉድጓድ ውስጥ ነው ።በእውነት ጉድጓዱ ጠባብ በመሆኑ ተቀበረ ከማለት ይልቅ በራሱ ቆመ ማለት ይሻላል ።
Filed in: Amharic