>

በጉንደት፣ በጉራዕና በዶግዓሊ ታሪኩን በደሙ ያጻፈው ንጉሰ ነገስት...!!! (ኢ.ፕ.ድ)

 በጉንደት፣ በጉራዕና በዶግዓሊ ታሪኩን በደሙ ያጻፈው ንጉሰ ነገስት…!!!

 
ኢ.ፕ.ድ

 

*   አፄ ዮሐንስ ከደርቡሽ ጋር በተዋጉበት (በኋላ ዮሐንስ ተብሎ በተሰየመው) ተራራ አናት ላይ “ዮሐንስ 4ኛ ከደርቡሾች ጋር የተዋጉበት ስፍራ” ብሎ የደርግ መንግስት መታሰቢያ ያቆመላቸው ከ39 ዓመታት በፊት ሰኔ 14 ቀን 1973 ዓ.ም ነበር።
አፄ ዮሐንስ አራተኛ ሐምሌ 5 ቀን 1825 ዓ.ም በትግራይ ተምቤን ልዩ ስሙ ማይ በሀ ተብሎ በሚታወቅ ሥፍራ ተወለዱ። ርዕሰ መኳንንት ደጃዝማች በዝብዝ ካሳ ሐምሌ 6 ቀን 1863 ዓ.ም አፄ ተክለ ጊዮርጊስን አድዋ አካባቢ አሳም የሚባል ሥፍራ ላይ ወግተው ድል ካደረጉ በኋላ ለንግስና መዘጋጀት ያዙ። ከዚያም ጥር 13 ቀን 1864 ዓ.ም አክሱም ላይ ሥርዓተ ንግሣቸው ተፈጽሞ ‹‹ሞአ አንበሳ ዘእምነገደ ይሁዳ ግርማዊ ዮሐንስ ራብዓዊ ስዩመ እግዚአብሔር ንጉሰ ፅዮን ንጉሰ ነገስት ዘኢትዮጵያ›› ተብለው ነገሡ።
አፄ ዮሐንስ በተለያዩ ጦርነቶች አገር ለመውረር የመጣ ጠላትን አሳፍረው በመመለስ የአገራቸውን ድንበር አስከብረዋል። በዘመናቸው ከነበሩት ጦርነቶች በጉንደት፣ ጉራዕና ዶግዓሊ የተካሄዱት ይጠቀሳሉ። የጉንደትና ጉራዕ ጦርነቶች መንሥኤ የግብፅ መሪ ከዲቭ ኢስማኤል ነበር። በርካታ የአውሮፓ ተወላጆች በገንዘብ እየቀጠረ ማዕረግ በመስጠት የግብፁ ወታደር ላይ መሪ አድርጎ ራሱ በቱርክ እየተገዛ ኢትዮጵያን ወሮ ከሱዳንና ሱማልያ ጋር በመቀላቀል ግዛቱን ከሜዲትራንያን ባህር እስከ ህንድ ውቅያኖስ የማስፋት ምኞት ነበረው። አባ በዝብዝ ካሳ አፄ ዮሐንስ ድባቅ መተው ህልሙን አስጣሉት እንጂ።
ሁለት ጊዜ ግብፆችን ድል በማድረጋቸው ስማቸው ገናና ሆኖ ነበር። የንግስና ዘመናቸውን በጦርነቶች ያሳለፉት አጼ ዮሐንስ ህይወታቸውን ያጡት ከደርቡሾች ጋር በተደረገ ጦርነት ከጠላት ጋር እየተዋጉ ነው። በ1881 ዓ.ም በመጋቢት መባቻ በውጊያው የሚመሩት ጦር ድል እየተቀዳጀ ባለበት ወቅት ንጉሡ ተመተው ወድቀው በማግስቱ ህይወታቸው አለፈ። የአጼ ዮሐንስን ሞት የሰሙ አንዲት አልቃሾች ተከታዩን ግጥም መደርደራቸው ይነገራል።
አፄ ዮሐንስ ሞኝ ናቸው
እኛም ሁላችን ናቅናቸው
ንጉሥ ቢሏቸው በማሀሉ
ወሰን ጠባቂ ልሁን አሉ
አጼ ዮሐንስ ይዋሻሉ፣
መጠጥ አልጠጣም እያሉ፤
ሲጠጡም አይተናል በርግጥ፣
ራስ የሚያዞር መጠጥ፤
በጎንደር መተኮስ፣
በደምቢያ መታረድ አዝኖ ዮሐንስ፣
ደሙን አፈሰሰ እንደ ክርስቶስ፤
እንዳያምረው ብሎ ደሃ ወዳጁን፣
መተማ አፈሰሰው ዮሐንስ ጠጁን፤
የጎንደር ሃይማኖት ቆማ ስታለቅስ፣
አንገቱን ሰጠላት ዳግማይ ዮሐንስ።
እጅግ ደስ ይለኛል ያንተ ስም ሲነሳ
የቁና አፈር ንፉግ አንተ ነህ ወይ ካሳ?!
ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት ‹‹In­novation and Misoneism during the Reign of Emperor Yohannes IV(1872.1889)›› በተሰኘ ጥናታቸው እንደገለጹት አፄ ዮሐንስ የኢትዮጵያን ብሔራዊ ሰንደቅ ዓላማ በሥርዓት በማዘጋጀትና በማስተዋወቅ ቀዳሚ ተጠቃሽ ናቸው። ደብረ ታቦርና ደሴን የመሰሉ ከተሞችን በማልማት፤ በጎንደርና አድዋ ክሊኒክ በመመስረትና በክትባት ዘመናዊ ሕክምና በማስፋፋት፤ ክብረ ነገሥትና ዕደ ጥበባትን የመሰሉ ቅርሶችን ከእንግሊዝ በማስመለስና የባርያ ንግድን የሚያስቆም ድንጋጌን በማውጣት ተጠቃሽ ስራዎችን አከናውነዋል።
Filed in: Amharic