>

" የአኩሪዋ ጥቁር ኮኮብ ሐገር  ንጉሰነገስት!!! " (በአለባቸው ደሳለኝ)

” የአኩሪዋ ጥቁር ኮኮብ ሐገር  ንጉሰነገስት!!! “

 አለባቸው ደሳለኝ – ለንደን

ባቡሩም ሰገረ…….. ስልኩም ተናገረ ፣
ይህ በማን ግዜ…….. ተደርጎ ነበረ ፣
ምንይልክ ነብይ …….. ነው ሆዴ ጠረጠረ!
 
 : የጥቁሩን ሱናሜ : መሪ : የኢትዮጵያን ንጉሰነገስት መንግስት  በአለም የወርቅ መዝገብ ላይ ስማቸውን ስለፃፉት ገናና የእምዬ ምንይልክ ታሪክ ላወጋችሁ ወደድኩ:-
ዛሬ ከደረስንበት: የዘመነ ሮበት ደረጃ :ላይ ሆነን :የቀድሞ አባቶችንን  የስልጣኔ ፍቅርና : ምኞት : ምን ያህል እንደነበረ ስናጤንው : ለሐገራቸውና :ለህዝባቸው ሲሰሩት : የነበረውን ድካም: መስፈርቱን መለካት ያቅተናል ::
እነዚህን መሰል ቀደምት ፣ አባቶቻችን ያን ግዜ : ሲመኙት የነበረው ህልማቸው : እውን ሆኖ ሳያዩት : አፈር ትቢያ ሆነው በዩ ቤተክርስቲያኑ ታዛ ወድቀው : ቀርተዋል :: ነገርግን እንድሸክላ ዱቄት ሆኖ የፈራርሰው አካላቸው ሲሆን: አፈር የማያበላሸው ታሪካቸውን: ስናገላብጥ የምናገኜው ምስክርነት :ለመንፈሳችን ነፃነት ለአላማችን ፅናት ይሰጠናል ::  ለዛሬው ስለታላቁ የአድዋው የጦር መሪ  የኢትዮጵያ ንጉሰነገስት  መንግስት የነበሩትን እምዬ ምንይልክን እንስታውሳቸው አለን :: ሆኖም ግን ተጨልፎ የማያልቅ ባህር የሆነ ታሪክ ያላቸውን ምንይልክን የመሰለ ገናና ንጉሰንገስት እንደዚህ  ነበሩ ብሎ በአጭር አቀራረብ ለመግለፅ ድካሙ የሰማይ ያህል እንደሚርቅ ወገኖቼ እንደምትገነዘቡልኝ አምናለሁ :: የምዬ ምንይልክ ታሪክ ብዛቱ በህዋው ላይ የፈሰሰን ኮኮብ ከመቁጠር አይተናነስም ::
ለግዜው ግን ነጋድራስ አፈወርቅ ገ/እየሱስ ፣ደጃዝማች ከበደ ተሰማ ዳኛቸው ወልደ /ስላሴ ፣ተክለፃዽቅ መኩሪያ ፣ፓውሎስ ኞኞ በተራራቁ
አመተ ምህረቶች የፅፏቸውን የታሪክ መፃህፍቶች በትዕግስትና በብቃት መፈተሽ ግድ ይላል :: በዚህ ምክኒያት በእጄ ገብተው ያገኘዃቸውን የታሪክ ድርሳናትን  አገላብጨ  ቁምነገሮቹን ብቻ መርጨ ለውድ ወዳጆቼ  ላካፍላችሁ ወደድኩ ::
እምዬ ምንይሊክ
በ1836 ዓ/ም ነሐሴ 12ቀን ቅዳሜ ከአባታቸው ከኃይለመለኮት ሣህለ ስላሴ ከናታቸው ከወ/ሮ እጅጋየሁ ለማ አድያሞ የተወለዱት ንጉስነገስት አፄ ምንይልክ ፣በአባታቸው የንጉስ ሳህለስላሴ፣ የልጅ ልጅ፣ የኃይለመለኮት ሳህለ ስላሴ ልጅ፣ ሲሆኑ እናታቸው ደግሞ፣ የንጉስ ሳህለስላሴ ፣  ሚስት የወ/ሮ በዛብሽ ሰራተኛ ናቸው ::
የእጅጋየሁንም መውለድ ፣ንጉስ ሳህለ ስላሴ ሲሰሙ፣ የልጁን ስም “ምን ይልህ ሸዋ ” በሉት ብለው ስም አወጡለት :: ምን ይልህ ሸዋ ያሉበትም ምክኒያት ፣ የኔ ልጅ ኃይለመለኮት  ከገረድ በመውለዱ ሸዋ ሲሰማ ፣ምን ይል ይሆን ? ለማለት ነው ይባላል ::
በዃላ ግን በህልማቸው፣ ከምን ይልህ ፣ ሸዋ ጋር አብረው ቁመው ከእሳቸው ጥላ የልጁ ጥላ በልጦ፣ በእግር የረገጡት መሬት፣ ሲያለካኩት እሳቸው ከረገጡት ፣ ልጁ የረገጠው ረዝሞ ተመክለከቱ :: ይህን ህልም ካዩ በዃላም፣ ምንይልክ የኔ ስም ሳይሆን የሱ ስም ነው :: ስሙን ምንይልክ ፣ በሉት ብለው በማዘዛቸው ምንይልክ ተባሉ :: ይህንም ያሉበት ምክኒያት ምንይልክ፣ በሚል በሚል ስም የሚነግስ ንጉስ ፣ኢትዮጵያን ታላቅ ያደርጋታል ፣የሚል ትንቢት ስለነበር ሳህለ ስላሴ ሲነግሱ ፣ ስሜ ምንይልክ ይሁን ብለው ነበር :: ነገር ግን አንድ መነኩሴ ፣ በዚህ ስም አትንገስ ፣መጥፎ አጋጣሚ ይመጣብሀል ይሕ ስም የሚስማማው ፣ ከመጀመሪያው ወንድ ልጅህ ከሀይለመለኮት ፣ ለሚወለደው ነው :: ይህም ስም የሚወጣለት የልጅህ ልጅ ኢትዮጵያን አንድ ፣የሚያደርግ ትልቅ ንጉስ ይሆናል: አሏቸው : ይባላል :: በዚህ ምክኒያት የምንይልህ ሸዋ ስም ተቀይሮ ምንይልክ ተባሉ ሲል ” ክብረ ነገስት “ያትተዋል ::
ህርበርት የተባለው ፀሐፊ ስለ ምንይልክ ሰውነት ሲገልፅ እንዲህ ይላል :: ምንይልክ ጥርሶቻቸው ግጥም ያሉ ነጫጮች ናቸው ::ትንንሽ አይኖቻቸው ደስ ይላሉ ፣ የአይኖቻቸው ውስጥም ከነጭነት ይልቅ ወደ ቢጫነት ያደላሉ ፣ግንባራቸው ጠባብ ነው ፣ትኩር ብለው ሲያዋቸው ደግና የተለያዬ ጠባዮች ያሏቸው መሆናቸውን ፊታቸው ያስታውቃል ::
ጢምና ሪዛቸው የተጠጋጋ ቢሆንም ግራጫ ሁነዋል ፣ አነጋገራቸው እንደሌላው አበሻ ሁሉ ረጋ ያለ ነው :: ሲናገሩም ምላስና ጥርሳቸው ይታያል ፣ሲያዳምጡም ደግሞ ራሳቸውን መነቅነቅ ይወዳሉ :: ሲጫወቱ እጃቸውን አያወራጩም ፣አንዳንድ ጊዜ ብቻ ጣታቸውን ይደራርባሉ ::
ሁል ጊዜ ፈገግተኛ ናቸው :: የመወደድ ጠባይ አላቸው ይህም ቢሆን ሲስቁ የሰሟቸው ወይንም ያዩዋቸው ሰዎች ጥቂቶች ናቸው  ይላል ::
ኮንት ግሊኮን በበኩሉ በርዝማኔ ከጫማቸው ሌላ 6ጫማ ይሆናሉ ::
ምንይልክ ጠንካራ አቅም አላቸው፣  ቆዳቸው ጥቁር ነው :: አጠር ያለ ጢምና ሪዝ አላቸው ፣ ፊታቸው ከባድ ነው አስተያዬታቸው የጨዋ አስተያዬት ነው :: ፈገግታቸው ማራኪ ነው ፈገግ ሲሉም ውብ ጥርሶቻቸው ይታያሉ :: አዘውትረው ግንባራቸው ላይ ከምትታሰረው ሻሽ ላይ በወርቅ የተዘመዘመ ጥቁር ካባ ይደርባሉ :: በማለት ገለፃውን ሲያጠቃልል ሌላው የዘመኑ ፀሐፊ ቸያረኒ ፣ ምንይልክ ጨዋና የጦር መሳሪያ የሚወዱ ሰው ናቸው ሲናገሩም ረጋ ብለውና አስበው ነው ::
ሲያዳምጡም በፀጥታ ነው :: ጥሩ ወታደር በመሆናቸው የጦር መሳሪያ መያዝ ይወዳሉ ::ቁመታቸው መካከለኛ ሆኖ ጡንቻቸው የፈረጠመ ነው :: ፊታቸው በፈንጣጣ ምክኒያት ተጉረብርቧል ::ግንባራቸው ሰፊ ነው :: እንዳፋቸው ሁሉ ደስ የሚሉ ጨዋ አይኖች አሏቸው :: አፍንጫቸው ትክክለኛ ሲሆን አገጫቸው ግን ትልቅ ነው :: ጥርሳቸው ትክክል ሆኖ የወጣና ነጭ ነው ሲል ፅሁፉን አጠቃሏል ::
*   *   *
የአድዋውን ጀግና የጥቁሩን ሱናሚ መሪ የኢትዮጵያን ንጉሰ ነገስት መንግስት የዳግማዊ ምን ይልክን የህይወት ጉዞ :-
በመላው አለም ዝናቸው የታወቀው : ታላቁ  የአድዋው ጀግና ዳግማዊ ምንይልክ በ1858 ዓ/ም ነሀሴ 24 ቀን ምንይልክ ሸዋ ተብለው ነገሱ ::
አፈወርቅ ገብረየሱስ እንዲህ ይላሉ ::
“ዳግማዊ ምንይልክ ገና ከናቱ ማህፀን ሲወጣ : በእጁ ሉል :ጨብጦ በራሱ ዘውድ ደፍቶ: የድፍን ኢትዮጵያን ካህናት አስጠርቶ: ከዳርቻ እስከ ዳርቻ : ያለውን መኳንንት ጠርተው : ጥንት የሁልት የሶስት ንጉሶች ፣ የነበረውን ሰራዊት አንድነት አድርገው ፣ ጠጁ የረፋዱ መንገድ በሚያህል ዳስ ሙሉውን ተጥሎ ፣ በጋን መሆኑ ተንቆ በገልድና ፣ በሻንዳ ፣እንደ ሐምሌ ጎርፍ እየጎረፈ ፣ፍሪዳው ፣ድልቡ ሰንጋው ፣ሸህሩ ፣እንደካንቻ ተመቶ፣  የንጉሰነገስት ዘውድ ጫኑ :: በማለት በአይናቸው ያዩትን በጆሮአቸው የሰሙትን ለታሪክ መዘክርነት አስቀምጠውት አልፈዋል ::
 እምዬ ምን ይልክ  በኢትዮጵያውያንም ሆነ በውጭ የታሪክ ተመራማሪ ምሁራኖች ብዙ የሚስደንቁ ባህሪያት እንዳላቸው ተፅፎ ባገኝም
ለዛሬ የማቀርብላችሁ ግን ከማይጠገበው ታሪካቸው ውስጥ ሚዛን የሚደፉትንና እናንተን  ፣ ወዳጆቼን ዘና ያደርጉልኛን፣  ብዬ የመራረጥኳችሁን ብቻ ነው ::
ምንይልክ  በምግብ አመጋገብ ፣ በኩል ከሌሎቹ ኢትዮጵያዊያን ጥቂት ለየት ይላሉ :: ከሁሉም የበሬ ስጋ ፣ አይወዱም በዚህም ምክኒያት የዶሮ ወይንም፣  የአልጫ ወጥ ይሰራላቸዋን :: አይብ መመገብ ወተት መጠጣት ስለሚወዱ ፣ ለእሳቸው ብቻ የሚሆን ወተት ቅቤና አይብ የምታዘጋጅ ሰራተኛ አላቸው ::
በመጠጥ ቡኩልም ፣ አንዳንድ ታሪክ ፀሀፊዎች ፣ ምንይልክ፣  መጠጥ እንደሚጠጡ ሲፅፉ ብዙ ፅሐፊዎችና የሀገራችንም ሰዎች ምንይልክ መጠጥ፣  እንደማይጠጡ ይናገራሉ :: ከመጠጥ የሚወዱት ብርዝና ወተት ሲሆን ፣ በግብር ጊዜ ብቻ ጠጅ ይጠጣሉ :: አንድ መለኪያ አረቂ ወይንም አንድ ብርጭቆ ሻምባኝ : ከጠጡ በቂያቸው ነው :: ከአውሮጳዉያን መጠጥ በጣም የሚወዱት ክሪም ዶ ሜንት የሚባለውን ነበር ::
አለባበሳቸው ደስ የሚሰኝ የሐገራቸውን ባህል የጠበቀ ፣ሲሆን በሐርና በወርቅ ዘምዘም የተጠለፈ የሐር ካባም ይደርባሉ ::
በሴት በኩል ያላቸው ፀባይ አንዳንድ ሰዎች ከሴት እምብዛም ፍቅር እንደማያውቁ አስመስለው ያወሩባቸዋል ::
ነገርግን እውነት አይደለም :: በእድሜ እንደናታቸው የሚቆጠሩትን የስምንት ልጆች እናት የነበሩትን ወ/ሮ ባፈናን ለ17 አመት በወዳጅነት ብቻ በፍቅር  አብረዋቸው ኑረዋል ::
ምንይልክ ጣይቱን ሲያገቡ እድሚያቸው 30 አመት ነበር :: ማለትም ለጣይቱ አምስተኛ ፣ ባላቸው ናቸው ማለት ነው :: እኔም በመረጃ ተደግፎ ያገኜሁት ይህንኑ ሲሆን ከዚያ በፊት የአፄ ቴውድሮስን ልጅ ልዕልት አልጣሽ ቴውድሮስን ፣ የንግስት ዘውዲቱን እናት ወ/አብችውን ፣ የጉራጌዋን ባላባት ወ/ወለተ ስላሴን አግብተው ፈተዋል ::
ምንይልክ ሹመት በዘር እንጅ በስራ  ባልነበረበት ዘመን የተገኙት እሳቸው ከነገሱ በዃላ መሳፍንቱንም ሆነ ባላባቱን በወዳጅነትና በፍቅር ስለተቃረቡት አብዛኛው ያለ ምንም ደም መፍሰስ ሲገብርላቸው እንቢ ይለውንም በጦር ሐይል እያስገበሩ የወጋቸውንም መልሰው በመሾም ፍቅር በዝቶ የተበታተነችው ኢትዮጵያን  አንድ አድርገው መሰረቷት ::
ምንይልክ በአስተዳደር ዘመናቸውም ሁሉ የሰውን ልጅ መብት የሚገፉ አልነበሩም :: ምንይልክ በሰላም ጊዜ የቤተክርስቲያን አባል በጦርነት ጊዜ ደግሞ ተዋጊም ነበሩ ::
ምንይልክ ደግ ሰው ነበሩ :: ለድሀው ሁሉ በገዛ እጃቸው እንጀራውን እያጠፉ እህሉን እየዛቁ ካልመጠዎቱ በሌላ ሰው እጅ ማስመጥወት ከልባቸው አይደርስላቸውም ነበር :: በዚህም ደግነታቸው የተነሳ
ምንይልክ ይወቁት አይኔ ጠፋበዎ ፣
የፈተፈቱበት ነክቶብኝ ጣተዎ ፣
በማለት በሞቱ ጊዜ ህዝቡ በእንጉርጉሮ ሐዘኑን ገልፆላቸዋል: : ምንይልክ ከደግነታቸውም አልፈው ሩህሩህም ሰው ነበሩ ::
ምንይልክ የአፍሪካን አሁጉር ለመከፋፈልና ለመቀራመት ከሩቅ ሐገር የተነሱ ሐያላን መንግስታት ሲመጡ ገለልተኛ ሆነው ሳይሆን የተቀመጡት በመላው አለም የታወቀውን ታላቁን የአድዋ ዘመቻ የመሩና በድል ያሸበረቀ ታሪክ በወርቅ መዝገብ የፃፉ መላውን የጥቁር ዘር ያኮሩና ኢትዮጵያን ለአለም ያሳወቁ ታላቅ ንጉሰነገስት ነበሩ ::
ከዚህም አልፈው ተርፈው የስልጣኔን በር ለሐገራቸው የከፈቱና ዘመናዊ ኢትዮጵያን የቆረቆሩ ገናና ንጉሰ ነገስት ናቸው ::
ስመ ጥሩው ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪው ጳውሎስ ኞኞ እንዲህ በማለት ይቀጥላል ::
” በኢትዮጵያ ውስጥ ለመጀመሪያ ግዜ የመጀመሪያዋን አውቶሞቢል የነዱና በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ፐርፌክት ድራይቭር የሚለውን የመጀመሪያውን መንጃ ፍቃድ  የተቀበሉት ምንይልክ ናቸው ::
በመኪና የሚፈጨው እህል ጋኔል ነው፣ተብሎ ይታመን በነበረበት ግዜ ጋኔን ያለመሆኑን ለማሳወቅ የመጀመሪያም የመጨረሻም ኢትዮጵያዊ ዱቄት አስፈጭ ንጉስ ምንይልክ ናቸው የመጀመሪያውን ስልክ አስገብተው ጋኔን ከዙፋን አጠገብ ይውጣ ብለው የዘመኑ ጳጳስ ጭምር ከባድ ተቃውሞ ቢያነሱባቸውም ታግለው ስልክ የመሰረቱት ምንይልክ ናቸው ::
ሆቴል መብላት ነውር አለመሆኑን ለማስተማር በአድስ አበባ የመጀመሪያውን ሆቴል ከፍተው ሚስታቸውን ጣይቱን ወጥ ቤት አድርገው በገንዘባቸው መኳንንቱን እዬጋበዙ :መብላት ያስተማሩ ምንይልክ ናቸው :: ዘመናዊ የውጭ ሐገር ት/ቤት ኤሌትሪክን ባቡርን ያስገቡ ምንይልክ ናቸው :: የዛሬውን ሰንደቅ አላማ በ1888 አ/ም
በአውጅ አውጥተው አረንጏዴው ከላይ ቢጫው ከምሐል ቀዬ ከስር እንዲሆን አደራደሩን ቅደም ተከተል እንዲሰጠው ያደረጉት ምንይልክ ናቸው ::የአበባ የኮክ የእንጆሪ የወይን የመሳሰሉት የአትክልት ዘሮች እያስመጡ ያራቡ ምንይልክ ናቸው :: ሰው ሲባል እኩል ነውና ሰውን ባሪያ እንዳይባል ብለው የባሪያን ነፃነት ያወጁ ፣ሰው እንደ ከብት እንዳይሸጥ እንዳይለወጥ ብለው የታገሉ ምንይልክ ናቸው ::
ከታላላቅ አስደናቂ  ስራዎቻቸው አንዱን ብቻ ልጥቀስ:-
 በአድስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ የሆነችው  አውቶሞቢል በ1900 ዓ/ም ከንግሊዝ ሀገር ተነስታ አድስ አበባ ገባች :: መለያ ታርጋ ቁጥሯ ዲ 3130 ከሀገሯ በወጣች በ 2 ወሯ በመርከብ ተጭና በባህር ላይ በመንሳፈፍ 27 ቀን ከወሰደባት በዃላ ጅቡቲ ወደብ ተራገፈች ::  ጉዞዋን በእንግሊዝ ሱማሊያ በማድረግ ድሬዳዋ ስትገባ ለእንግዳዋ አውቶሞቢልና  ለአሽከርካሪዎቿዋ እንግሊዛውያን ስለክብራቸው ታላቅ አቀባበል የተደረገላቸው በከተማዋ ምሀል ግራና ቀኝ የኢትዮጵያና የእንግሊዝ ባንድራ እየተውለበለበ እሩምታ ተኩስ እየተኮሰላት ሲሆን ይችው አውቶሞቢል ከሀገሯ በተነሳች በ7ኛው ወሯ በ1900 ታህሳስ 20 ቀን አድስ አበባ የገባችው መንገድ እየተሰራላት አንዳንድ ግዜም በብቅሎ እየተጎተተች ተራራ ሲሆን እየተገፋች ነበር ::
አድስ አበባም ስትደርስ የከተማው ከንቲባ እና ሁለት ሽህ ሰው ያህል ፈረሰኛ ሲቀበላት ቁጥሩ ያልታወቀ : መድፍ ተተኩሶላታል ::
በአጠቃላይ ስንመለከተው ምንይልክ ታዋቂነታቸው በፓለቲካው ብቻ ሳይሆን የሳይንስ ውጤት በሆነው ጥበባዊ ስራዎች በመደነቅ ያዮትን የሰሙትን ሁሉ ወደ ሐገራቸው ለማስገባትና ሐገራቸው በዘመኑ የሳይንስ ውጤት ተጠቃሚ ለማድረግ የነበራቸው ምኞት ከሌሎቹ ነገስታት የሳቸው አይሎ ይታያል ::
 ይህን የመሰለ ታላላቅ ስራዎች የሰሩት ንጉሰ ነገስት  ምንይልክ የውጭን ፅሐፊዎችን  ትኩረት ሳይስቡ እንዳልቀሩ አንጋፋው ጋዜጠኛና የታሪክ ተመራማሪ ጳውሎስ ኞኞ  ይቀጥላል ::
ለምሳሌ ሮድ የተባለው ፀሀፊ ምንይልክ የማያውቁትን ነገር ሁሉ ማየትና ማጥናት ይወዳሉ ሲል ፣ ዶክተር መረብ በበኩሉ ከምንይልክ እረፍት በዃላ ፣ ” አለም ምንይልክን ያህል ታላቅ ኢንጅነር ማጣቷን እመሰከረክራለሁ ” ብሏል  ::
ኢጣሊዊ ዶክተር ካስትሮም በአለም ላይ ያሉ ትልልቅ ተራማጅ (ፕሮግሬሲቭ) ሰው ናቸው :: ምንይልክ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ከሆነ  ከመሬት ጨረቃ ድረስ የሚደርስ የመገናኛ መሰላል   አለ  ቢሏቸው   የሚቻል ከሆነ እንስራው በማለት ያበረታታሉ እንጅ አይጠቅመንም እንተወው የሚል ሀሳብ እንደማያቀርቡ   ታላላቅ. የአለማች የታሪክ ፀሀፊዎች   የየግል ሀሳባቸውን ዘርዝረው መስክረውላቸዋን  ::
እምዬ ምንይልክ እርጅናና በሽታ እያጣደፈ ቢያስቸግራቸውም በወገንና በሐገር ፍቅር የተማረከ ልባቸው ገና አልተሰበርም ነበር ::
አለምን አርቆ የሚያየው አዕምሮአቸው ሐገርንና ወገንን በቅንንነት ከማገልገልና ከማስተዳደር የበለጠ ደስታ አልነበረውም :: ጦርና ጋሻ ይዞ በውርጭና በሐሩር እየተቃጠለ ንጉሰነገስቱንና ሀገሩን ሲጠብቅ ለኖረው ህዝባቸው የተለየ ፍቅርና አክብሮት ነበራቸው :: ለውለታው ስልጣኔ ሲመኙለት ፣ ለደግነቱና ለአገልግሎቱ ወረታ ሜዳይና ሹመት እየሸለሙ ሲያስደስቱት ኖረው የዃላ ዃላ እለተ እረፍታቸው  መድረሱን ባሰቡ ግዜ አፈር ሳይጫናቸው መቃብር ሳይዘጋባቸው በፊት እንዲህ በማለት አደራ ጥለዋል ::
” ያገሬ የኢትዮጵያ ሰዎች ልጆቼ ወዳጆቼ እግዚአብሄር የገለፀልኝን ምክር ልምከራችሁ አንዱ በአንዱ ምቀኝነት ይቅር ፣ እስካሁን በፍቅር እንዳኖርኳችሁ ተስማምታችሁ በፍቅር እንድትኖሩ እለምናችሁ አለሁ ::
እናንተ አንድ ልብ ከሆናችሁ በምቀኝነት እርስ በእርሳችሁ ተዋግታችሁ ካላለቃችሁ በቀር  ፣ ኢትዮጵያን ለሌላ ባእድ አትሰጧትም :: ንፋስ እንዳይገባባችሁ ፣ ከእንግዲህ የኢትዮጵያን ዳር ደንበር ፣ እንዲሰፋ እንጅ አንድም  ጋት መሬት እንዳይጠብ አታድርጉ ::  ነገር ግን አንድ ት ጋት  መሬት አሳልፎ  ለሌላ የሰጠ ፣የኢትዮጵያ ውቃቢ ያጥፋው ጥቁር ውሻም ይውለድ :: ከነ ልጁጅ ልጁ የተሩገመ ይሁን ::
እኔም ሳለሁ ከፍቃዴ የወጣውን እረግሜውአለሁ :: “
1900 ዓ/ም ግንቦት 10 ጃን ሜዳ :: ምንይልክ ሐገራቸውን አንድ ለማድረግና በስልጣኔ ሌሎች የደረሱበት ደረጃ.ለማድረስ ሌትና ቀን ደፋ ቀና ሲሉ የውጩን አለም የሰው ስሜት እየ ማረኩ ስልጣኔውን ለማሳየት ሐገር አቋርጦ ባህር ተሻግሮ ከሚመጣው አውሮጳዊ ሌላ
በአስተዋይነታቸውና በጀግንነታቸው እየተደነቁ የምንይልክን ገፅ ለማየት እጃቸውን ለመጨበጥ አያሌ ህዝቦች ፍቃድ እየጠየቁ የምንይልክን እልፍኝ አረጋግጠዋል ::
አቶ ጳውሎስ ኞኞ በማስረጃ አስደግፎ ያቀረበውን ላስነብባችሁ ::
” ንጉሰነገስት ምንይልክ በሐገራቸው ሰዎች ብቻ ሳይሆን የሚወደዱት  በጥቁር አሜሪካውያን ዘንድ የተለየ መወደድና አክብሮት ነበራቸው ::
አሜሪካውያኖቹ ፣ ምንይልክን የሚወዱበት ምክኒያት በዘመኑ በጥቁሩ አለም የተገኙ በአፍሪካ ውስጥ በነፃነቷ የምትኖር ሀገር ያለችው
** የአኩሪዋ ጥቁር ኮኮብ ** ንጉስ** በማለት ይጠሯቸዋል ::
ለምሳሌ ጥቁሩ ቱጃር ሐብታም ዊሊያም ኢችን ኤሊስ ስለ ኢትዮጵያ የተፃፉ መፃሕፍትን ከሞላው አውሮጳ እየገዛ ካጠና በዃላ የምንይልክ እንግዳ ለመሆን ጉዞውን ወደ ኢትዮጵያ ሲያደርግ በአለም ላይ ምንይልክን የሚወዳደር የለም በማለት በልዩ ትእዛዝ በንፅህ ወርቅ የተሰራ ሽጉጥ ሲያሰራ የሽጉጡ እጄታና አንዳንድ ክፍሉ በአልማዝ ፈርጥ አስጊጦት ነበር ::
ጥቁሩ ኤሊስ ለጥቁሩ ንጉስ የሚወስደውን የሽጉጥ ስጦታ እያሳየ
 ** እናንተ ነጭ አሜሪካኖች ደርሳችሁ ትንቁን አላችሁ እንጂ እኛ ጥቁሮች ትልቅ ህዝቦች ነን ፣ ለአሁን የጥቁር ህዝቦች ማስረጃ የሚሆኑም ምንአልባት ሳይንቁኝ የሚቀበሉኝ ቢሆን ይህንን ከወርቅና ከአልማዝ ያአሰራሁትን ሽጉጥ እንዳ አቅሜ የማበረክትላቸው
ለታላቁ ንጉሰነገስት ምንይልክ ነው ይል ነበር ::
ዊልያም ኢች ኤሊስ ወደ ኢትዮጵያ ያደረገውን ጉዞ ፈፅሞ ወደ ሐገሩም ከተመለሰም በዃላ የተደነቀበትን ነገር ለጋዜጠኞች ሲገልፅ በዚያች በተፈጥሮ የበለፀገች ሐገር የተፈጠሩት ንጉስ ስለ አበሻ ነፃነት ምን ያህል እንደደከሙ ካጫወቱኝ በዃላ ** አበሻ ምን ጊዜም  ነፃ ሐገር ሁና የምትኖር ናት ፣ በክርስቲያን ደንብ አገራችን እንዳትለማ የሚቀርቡንን ሁሉ በታላቅ ደስታና በአክብሮት እንቀበላቸው አለን ::
በሌላ ለሚመጡብን ግን ሁላችንም እናልቃለን እንጅ እኛ ሳናልቅ አገራችንን ለሌላ አሳልፈን አንሰጥም አሉኝ ፣ በማለት የጉዞውን ዝርዝር ሁኔታ በሰፊው ገልፆታል ::
ይህንን የመሰሉት የኢትዮጵያ ገናናው  ንጉስ ነገስ5 ምንይልክ ሐገራቸው ከኩራዝና ከጧፍ መብራት ተላቃ በኤሌትርክ ብርሐን ስትንቦገቦግ ህዝባቸው ፣ ከበቅሎ ኮርቻ ወርዶ፣  በመኪና ሲንፈላለስ ፣ ለማየት እንደ ጏጉ መላ ሰውነታቸው ፓራላይዝድ ሽባ ሆኖ ለብዙ ጊዜ ከታመሙ በዃላ ፣ አለምን አርቆ የሚመለከተው  አይናቸው እንደተከደነ አንደበታቸው እንደተዘጋ ከተኙበት የበሽተኛ አልጋ ሳይነሱ ታህሳስ ሶስት ቀን 1906  በእለተ አርብ ቀን  በተወለዱ በ69 አመት ከአራት ወር ከዚህ አለም በሞት ተለዩ ::
እምዬ ምንይልክ በአለም ላይ ገናና በሆነው የአድዋው ጦርነት በአለም አቀፍ ደረጃ መታዎቃቸው ጉልህ የስራ ውጤት ቢሆንም ለነፃነት ዘላቂ ዋስትና የሚሆነው እንደሰለጠኑት ሐገሮች ሰልጥኖ መገኜት መሆኑን በመገንዘብ ከአድዋ በፊት የወጠኑት የልማት ስራ ከአድዋ በዃላ የሰላምና የጤንነት ዘመን ተጎናፅፈው ቢሆን ኑሮ ኢትዮጵያን በስልጣኔ ምን ያህል ሊያራምዳት ይችሉ እንደነበሩ መገመቱ አያዳግትም :: ዳሩ ግን በእድሚያቸው ከሁሉ አንፃር የታደሉ ንጉሰነገስት ጠባያቸውን ከነችሎታቸው ወርሶ ምኞታቸውንና የስራ ውጥናቸውን ወደ ፍፃሜ የሚያደርስ አልጋ ወራሽ በማግኜት ረገድ ባለመታደላቸው እንዳሰቡትና እንደተመኙት ሐገራቸውን ወደ ስልጣኔ ጎዳና የማምራቱ ጉዳይ የምዬ ምንይልክ ምኞት ሆኖ ከሳቸው ጋር አብሮ ተቀበረ :: .
የሚገርመው ነገር ግን ይህን የመሰሉት ንጉሰነገስት ስልጣኔ እዬተመኙ ከውጭ ወራሪ ጠላት ሲጠብቁት የኖሩት ሕዝባቸው እንባ ሳይራጭላቸው ደረት ሳይመታላቸው መሞታቸው ለማንም ሳይገለፅ  የቤተመንግስት ሚስጥር ሆኖ በህይወት አሉ እየተባለና እየ ተወራ እስከ ሰገሌ ዘመቻ ድረስ ሁለት አመት ከአስር ወር ተደበቀ ::
አስከሬናቸውን ግን አሽከሮቻቸው እንደነገስታቱ ማእረግ አምሮ በተሰራ ብረት  ሳጥን ውስጥ አድርገው በቤተመንግስት ግቢ ውስጥ ባለችው በስዕለ ቤተ ኪዳነ ምህረት ቤተክርስቲያን በክብር አስቀመጡት :: ምንይልክ የተወክለዱት ነሐሴ 12 ቀን 1836 ዓ/ም ስለሆነ በሞቱበት ጊዜ ከላይ እንደ ጠቀስኩት እድሚያቸው 69 አመት ከአስር ወር ነበር :: ነገርግን ይህን የመሰለ ታላቅ ገናና ንጉሰነገስት የኢትዮጵያን ታሪክ ጠንቅቀው በማያውቁ ፣ የእናታቸውን ሽንት ጨርቅ እንኳን  በቅጡ ያልጣሉ፣  በአስተተዳደግ የተበደሉ  ወፈፌ ጫታሞች  በሕዝብ ታሪክ ላይ ሲያላግጡ የሞያ ስነምግባርብ ከለላቸው ጋዜጠኞች  ጋር ተባብረው ሐገርና ሕዝብ ሲሳድቡ ማየትና መስማት እጅግ ያሳዝናል ::
እኔም ለሀገራችሁና ለታሪካችሁ ክብር ለምትሰጡ ያገሬ ልጆች ይህ ካልኳችሁ የተረፈውን እናንተ ጨምሩበት ::  ለዛሬው በዚሁ አበቃሁ :: በሌላ ዝግጅት እስክንገናኝ ቸር ይግጠመን ::
Filed in: Amharic