>
5:18 pm - Thursday June 14, 4992

ጥያቄው መሆን ያለበት፡- “ለምን ለይተው አረዱ?” ወይስ “ለምን ረዱ?” (አማን ነጸረ)

ጥያቄው መሆን ያለበት፡- “ለምን ለይተው አረዱ?” ወይስ “ለምን ረዱ?”

አማን ነጸረ

ትሰማለህ፡፡ ሴት ልጅ ላይ ጥቃት ይደርሳል፡፡ ትጮሀለህ፡፡ መጀመሪያ እንደ ሰው በሰብአዊነት ትጮሀለህ፡፡ ጾታ ሳይለይ ሁሉም ይጮሀል፡፡ ትጠይቃለህ፡፡ የሴቶች ቢሮ የት ሄዶ ነው? ምን እየሠራ ነው? ትላለህ፡፡ ሄዶ ሄዶ ሥልጣንና ተግባሩ እማን ላይ ንደሚወድቅ ስለምታውቅ፡፡ መቼም ፋይናንስ ቢሮ የት ሄዶ ነው አትልም፡፡ የጉዳዩ ባለቤት ማን እንደሆነ ታውቃለህ፡፡ እርግጥ ነው! ፋይናንስ ቢሮ እንደ ሀገር ይመለከተው ይሆናል፤ ግን በገደምዳሜ ነው፡፡ መላሹና ምላሹ በአጥቂው ዐላማና ዒላማ ይወሰናል፡፡
የብፁዕ አቡነ ኄኖክን ተግባር እንደዛ እየው፡፡ አንድ ጳጳስ በቅዱስ ሲኖዶስ በአንዲት ሀገረ ሰብከት ሲመደብ እንደ ሀገር ለሁሉም ዜጎች ያስባል፣ ተቆጥሮና ተሰፍሮ የተሰጠው ልዩ ሥልጣን ግን የኦርቶዶክሳውያን ምዕመናንን አካላዊና መንፈሳዊ ደኅንነት መከታተል ነው፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ሰፍሮ ቆጥሮ የሰጠው ሥልጣን እርሱ ነው፡፡ ሰዎች በጾታቸው፣ በብሔራቸው፣ በፖለቲካ አቋማቸው ሲጠቁ ቢያይ እንደ አንድ ለፍትሕ የቆመች ቤ/ክ አባት ሊጮህ ሊናገር ይችላል፤ ከሳሽና ተከሳሽ ሆኖ ለመቆም ግን ውክልና የለውም፡፡ ከሙስሊሙ ወይም ከፕሮቴስታንቱ ተቋም የተለየ ውክልና የለውም፡፡ የሕግ ውክልና ያለው ሀገረ ሰብከቱን ለመወከል ነው፡፡ ሀገረ ስብከት ማለት ደግሞ በውስጡ ያሉ ምዕመናን፣ ካህናትና አስተዳደራዊ አደረጃጀት ድምር ነው፡፡
ጥቃቱ ምን ገጽታ ነበረው? ሃይማኖታዊ ገጽታ ነበረው! ከተጠቂ ተራ ምዕመን ከጥቃት እስከ ዳነ ሊቀ ጳጳስ የሰውና የእይታ ማስረጃ ቀርቧል፡፡ ማስተባበያ ካለ ደግሞ እንየው፡፡ እስከዚያ ግን ጥቃቱ ሃይማኖታዊ ገጽታ ነበረው ለማለት የቀረበው ማስረጃ በቂ ነው፡፡ ተመሳሳይ ጥቃት በጋሞ ጎፋ፣ በስልጢ፣ በሶማሌ፣ … ሲቀርብ ነበር፡፡ ለእነርሱም ተጩኋል፡፡ በቤተ ክርስቲያን በኩል ጩኸቱ ማእከሉ የብሔር ማንነት አልነበረም፤ አሁንም አይደለም፡፡ የሃይማኖት ነበረ፡፡ ስለዚህ ጩኸቱም ሃይማኖታዊ ድምፀት ሊኖረው ግድ ሆነ፡፡ አማሮች ከጉራ ፈርዳ ሲፈናቀሉ ተፈናቃዮቹ 100 ፐርሰንት ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ እንደሆነ ይታወቃል፤ ሆኖም ቤ/ክ እንደ ተቋም የተለየ መግለጫና እርዳታ ማሰባሰቢያ አላደረገችም፤ ምክንያቱም ገጽታው ብሔርን እንጂ ሃይማኖትን ስላላደረገ፤ በመተከልም ከዚህ የተለየ አልነበረም፡፡ እንደ ጥቃቱ ዐላማና ዒላማ ምላሹዋም ይለያያል፡፡ የጉዳዩ ዋነኛ ባለቤት አቤቱታ አሰሚ የምትሆንበት አለ፤ እንደ ሀገራዊ ተቋም ከሌሎች ተቋማት ጋር በያገባኛል የምትቆምለት ጉዳይ አለ፡፡
ብሔራቸው ማተባቸውን አላልቶባቸው በእምነታቸው ላይ 5ኛ ረድፈኛ የሆኑ ወዳጆቻችንን ጨምሮ አንዳንድ ጠያቂዎች ግን ለጉምዙ፣ ለቅማንቱ፣ ለትግራዋዩ ለምን አትጮህም? ይላሉ ፡፡ ትግራይ በኦርቶዶክሳዊነቱ ተጠቅቶ ዝም ካለች ትወቀስ፡፡ ቅማንት በኦርቶዶክሳዊነቱ ከተጠቃም እንዲሁ (በቅማንትና አማራ የነበረው ግጭት ኦርቶዶክሳውያን አበው ባይኖሩ ከዚህም በላይ እልቂት ይደርስ ነበር!)፡፡ ጓዶች፡- በብሔር ጥቃትና በሃይማኖት ጥቃት መካከል ያለውን ድንበር እየለየን፡፡ የብሔር ጥቃትን ከሃይማኖት በማቀላቀል ፋላሺየስ መከራከሪያ እየዘበዘብክ ሙስሊሙ፣ ፕሮቴስታንቱ፣ አድቬንቲስቱ፣ … ሳይወቀስ ኦርቶዶክሳዊት ቤ/ክ ላይ እያመጣህ መደፍደፍ … ነጥብ ለማስቆጠር መጋጋጥ … ይደብራል፡፡ የብሔር ጥቃቶችን በሚመለከት ቤ/ክንን ከሌሎች የሃይማኖት ተቋማት በተለየ መውቀስ የምንቀበለው ነገር አይደለም፡፡ ሲጀመር በማንኛውም የቤ/ክ ሰነድ ላይ የብሔር ማንነት ቅጽ የለም፡፡ ቤ/ክ ዳግም ወልዳ ነው የምትቀበልህ፤ የምታውቅህም በክርስትና ስምህ ነው፡፡ በዚያ ስምህ የተነሣ ስትጠቃ ትጮሀለች፤ የሞትህ ምክንያት የእርሷ እናትነት ጋር ሲገናኝ የበለጠ ታዝናለች፡፡ አለቀ! ቢገባህ በውስጡ ‹‹ምክንያተ ሞት›› የመሆን አንድም ፀፀት፣ አንድም ‹‹ተሠዋብ/ል/ኝ›› የሚል ውስጣዊ የማንነት ትስስር አለ፡፡
እውነት ለመናገር፡-  ቤ/ክ በዋናነት ሁማኒተሪያን ወይም ሲቪክ ተቋም አይደለችም፡፡የራሷ ሃይማኖታዊ ቁመና (‹‹ኮንስቲትዊንሲ›› ልትለው ትችላለህ) እንዳላትም አትርሳ! የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ እንደ ዜጋ ማንኛውም ዜጋ ላይ ጥቃት ሲደርስ ትጮሃለች፣ ልጆቿ በሃይማኖታዊ በማንነታቸው ሲጠቁ ደግሞ የበለጠ ትጮሀለች፡፡ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሞጣ ላይ ለተጠቁ ሙስሊም ወንድሞቻችን እንደ ጮሁት፣ ፕሮቴስታንታውያን ሰሜን ሸዋ ላይ ለተጠቁ ፕሮቴስታንቶች እንደ ጮሁት፡፡ ሁሉም አካሏ ቢሆንም የበለጠ የምትጮኸው ግን የተመታችበት አካል ላይ ነው፡፡ ያላመመህ ቦታ ላይ አትታሽም! ሲጀመር ጥያቄው መሆን የነበረበት፡- ለምን ለይተው ረዱ ሳይሆን ለምን ተለይተው ታረዱ ነበር፡፡ ፎልስ ባላንሱን ተወውማ! ሁሉንም ማንነት በብሔር እርሾ ማቡካት ማቡካታቱን ተወውማ! ምናለብህ! ላንተ ማንነት ማለት ብሔር ብቻ ነው፤ ሌላው ንዑስ ማንነት ነው!
Filed in: Amharic