>
5:18 pm - Saturday June 15, 9297

እምዬ ምኒልክ  ከዘመኑ ቀድሞ የተፈጠረ ጭንቅላት!!! (ሳሚ ዮሴፍ)

እምዬ ምኒልክ  ከዘመኑ ቀድሞ የተፈጠረ ጭንቅላት!!!

ሳሚ ዮሴፍ

  ስለ ማዕድን ማውጣት
ዳግማዊ ምኒልክ ለማዕድን የፍለጋ ፈቃድ የሚሠጡበት የራሳቸው ሥርዓት ነበራቸው። ምኒልክ ማዕድን ቆፍሮ በማውጣት ደረጃ ለውጭ ሀገር ሰው ውል ሲሰጡ፤ ውል ወይም ፈቃድ ተቀባዩ የመጣበት ሀገር መንግሥት በአዲስ አበባ ሌጋሲዮን ወይም ኦፊሴላዊ ወኪል ካለው ወኪሎ በተገኘበት ዋስትና ተሰጥቶ (ዋስ ሆኖት) ስምምነቱ ይፃፋል።
የሀገሩ መንግሥት ተጠሪ በኢትዮጵያ ውስጥ የሌለው የውጭ ሀገር ሰው ከሆነ ደግሞ ከሀገሩ መንግሥት የዋስትና ደብዳቤ ይዞ መምጣት ነበረበት።
ለምሳሌ ኦርናልድ ሆልድ ለተባለ ጀርመናዊ የተጻፈለት ደብዳቤ….
“ከአውሮፓ ሰዎች ጋር የውል ወረቀት ስንጻጻፍ ሥልጣን በተቀበሉ ሰዎች ወይም በመንግሥት ወኪሎችና መልእክተኞች ፊት ነው። የጀርመን መንግሥት በኢትዮጵያ ወኪል ስለሌለው፤ ለመዋዋል የሚቀርብልዎ የመንግሥት ቃል ከመንግሥትዎ ማምጣት ያስፈልጋል። ከዚህ በኋላ ወርቅም ሌላም ነገር ቆፍሮ ለማውጣት እንደ ፈለጉ ነው የውል ወረቀት ለመስጠት የጃንሆይ ፈቃድ አለዎ” ይላል።
ተጻፈ መጋቢት 19 ቀን 1896 ዓ.ም
በወቅቱ ምኒልክ ለወርቅና ለማዕድናት ፍለጋ ይሰጡት የነበረው ፈቃድ ይህን ይመስል ነበር።
ለእንግሊዛዊው ብላንድል የተሰጠ ፈቃድ…
ይድረስ ከሚስተር ዊልድ ብላንድል 
 
ሎንዶን 
“ወርቅና ሚኒራል ከመንዲ አጠገብ ለመፈለግ እወዳለሁ ብለህ ጠይቀኸኝ ነበር። ከደቡብ ጥቁር አባይ፣ ከዴዴሳ ወንዝ እስከ ሦስት ኪሎ ሜትር ከመንዲ ደቡብ እስከ ዴዴሳ ምስራቅና ምዕራብ ከተደረገው መስመር በላይ ወደ ሰሜን ካለው ሀገር መካከል ለሦስት ዓመት ወርቅና ሚኒራል እንድትፈልግና እንድታስፈልግ በዚህ ወረቀት ሙሉ ፈቃድ ለአንተ ብቻ ሰጥቻለሁ። ነገር ግን፤ ከነጆ አንስቶ አምስት ኪሎ ሜትር ድረስ ወርቅና ሚኒራል እንዲፈለግበት ከዚህ ቀደም ለሌላ ሰው ፈቃድ ሰጥቻለሁና ይህ ለአንተ የፈቀድኩልህ ድንበር ይደርስበት እንደሆነ ከሃያ አምስቱ ኪሎ ሜትር ውስጥ መግባት አይቻልም። ይህን ሦስት ዓመት ድረስ ፈልግ ያልኩህ በ 23 ኅዳር 1884 ዓ.ም ይጀምራል። አሁን ካልነው ሀገር ውስጥ ሚኒራልና ሜታል ተገኝቶ አወጣለሁ ስትል ያን ጊዜ ውል እናደርጋለን። ይህንንም ውል በምናደርግበት ጊዜ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚገባውን ግብር ከሙሴ ሊን እቀበላለሁ ካልሁት በላይ አላስበልጥብህም።”
መጋቢት 20 ቀን 1883 ዓ.ም አዲስ ዓለም ከተማ ተጻፈ።
ምኒልክ ለማዕድን ፈላጊዎች ፈቃድ ሲሰጡ የፈቃድ ደብዳቤው የሚከተላቸው ደንቦች መደበኛ ናቸው ከዚህ ቀጥሎ ለአሜሪካዊው ዊሊያም ኤሊስ የተሰጠውን ፈቃድ እንመልከት
ይድረስ ከሙሴ ኤሊስ 
“ሰላም ላንተ ይሁን። ወርቅና ሁሉ ዓይነት ሚኒራል ከኢትዮጵያ መሬት እንድፈልግ እወዳለሁ ብለህ ስለጠየከኝ ቀጥሎ በተጻፈው ሀገር ውስጥ ለሁለት ዓመት እንድታስፈልግ ለአንተ ብቻ ፈቃድ ሰጥቻለሁ። የምትፈልግበት ሀገር በገናሌ ወንዝና በዳዋ ወንዝ ወርደህ ነው። ይህም ሁለት ዓመት ያልኩህ በ 1897 ዓ.ም በየካቲት ይጀምራል። አሁን ካልነው ሀገር ውስጥ ወርቅና ሚኒራል፣ ክቡር ድንጋይም ተገኝቶ አስወጣለሁ ስትል ያኔ ውል እናደርጋለን። ይህንንም ሲፈልጉ #ሠራተኞችህ ከባላገሮቹ እንዳይጣሉ፤ ከሀገር ሹም ዳኛ እየተቀበሉ ይሁን። ውል በምናደርግበት ጊዜ ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚገባውን መጀመሪያ (በቤንሻንጉል) ከሰጠሁት ፈቃድ አላስበልጥህብም።
መስከረም 7 ቀን 1897 ዓ.ም አዲስ አበባ ተጻፈ።
ከ20 በላይ የፈቃድ ደብዳቤዎች ውስጥ ሁሉም ጋር የማይቀሩ ነጥቦች አሉ…
– የፍለጋው ጊዜ ተወስኗል። በአብዛኛው ለሦስት ዓመት ነው። ጊዜ አነሰን ይጨመርልን ብለው የተከለከሉም ነበሩ።
– የፍለጋው ቦታ በተፈጥሮ ምልክቶች ለፈላጊው ተወስኖለታል። ከዚያ መውጣት አይችልም። ለአንዱ የተሰጠው ቦታ ፍለጋ ኮንትራቱን እስቲጨርስ ለሌላ አይሰጥበትም።
– ፈቃዱ የተሰጠው ለጠያቂው ብቻ መሆኑ ተገልጿል።
” ለአንተ ብቻ ፈቃዴን ሰጥቻለሁ” የሚለው፤ የተሰጠውን ፈቃድ ለሌሎች መሸጥ፣ መለወጥ፣ ማውረስ እንደማይችል ለመግለፅ ነው። ኮሎኔል ሊዎንቴፍ ይህን መሳይ ስህተት በፈጸመ ጊዜ፤ ምኒልክ ለቦልሾክ ኩባንያ በጻፉት ደብዳቤ
“…የሰጠሁትን ፈቃድ ለሌላ ሰው ወይም ለሌላ ኩባንያ አሳልፎ እንዲሰጥ ፈቃዴን አልሰጠሁትም። በሀገራችንም እንዲህ ያለ ልማድ የለም” ብለዋል።
– ፈቃድ የተሰጠው ሰው ወርቅም ሆነ ሌላ ማዕድናት ቢያገኝ፤ ለማውጣት ሌላ ውል መዋዋል እንደሚያስፈልገው በሁሉም ውሎች ላይ ተገልጿል። ሌላ ውል ሳይዋዋል አንድም ማዕድን ማውጣትም ሆነ መውሰድ አይችልም።
– “ከባላገር እንዳትጣላ ከሀገር ሹም ዳኛ እየተቀበልክ ይሁን” የሚለው የመቆጣጠሪያ አሠራራቸው ነበር። ማዕድን ፈላጊውን ከአካባቢው ሹም ተመድቦለት ፍለጋ እንዲያካሂድ መደረጉ፤ በሥራ ላይ ግጭት እንዳይፈጠር የሚረዳ ብቻ ሳይሆን፤ የሚደረገውን እንቅስቃሴ ሁሉ የሚያይ (የሚሰልል) የመንግሥት ተጠሪ መሆኑ ነው።
ከእነዚህ በተጨማሪ ከ1893  እስከ 1897 ዓ.ም ፍለጋ ፈቃድ ከተሰጣቸው መሀል …
* ሰርናር ኩባንያ (ለንደን)..በጎንደርና ጣና መሀል ለ3 ዓመት ተሰጥቶታል።
* ካቢሊየሪ ጃዊና ሳንግ (ኤደን ከተማ)…ከጎንደር በስተምስራቅ እስከ አሸንጌ ለ3 ዓመት ተሰጥቶታል።
* ሙሴ ለጋርድ (ፈረንሳዊ)..በባሮና ቦንጋ አካባቢ ለ3 ዓመት ተሰጥቶታል።
* ለአርሎፍ (ሩሲያዊ)… ከብርብር ወንዝ እስከ ሱዳን ጠርፍ ለ3 ዓመት ተሰጥቶታል።
* ለሚኒራል ኢጣልያ ሲንዲኬት…ጨጨሆ አካባቢ ለ2 ዓመት ተሰጥቶታል።
* ለሙሴ ሳምበርስና ሰርኪስ ተርዚያን (ፈረንሳዊና አርመናዊ) ምኒልክን በብዙ ረገድ ያገለገሉ ሁለት ሰዎች ለሌሎች ያልተሰጡ ቦታ መርጠው ሲያሳውቁ፤ ለሌሎቹ የአውሮፓ ሰዎች በተሰጠው ደንብ አይነት ከገንት ከተማ በየካቲት 26 ቀን 1896 ዓ.ም ተሰጥቷቸዋል።
* ለሙሴ አልበርቶ ፕሪስ…ከጁባ ወንዝ እስከ ጉሙዝ ድረስ ለ3 ዓመት ተሰጥቶታል።
* ለሙሴ ዳሱ ዶግስ በሙገርና በአባይ ወንዝ መካከል ለ2 ዓመት ተሰጥቶታል።
እንግዲህ ምኒልክ ለእነኚህ እና ለሌሎች በተሰጠ ፈቃድ በኢትዮጵያ ውስጥ የማዕድናት ፍለጋ እንዲያካሂድ አድርገዋል።
የወርቅና የማዕድናት ፍለጋ ፈቃድ ከተቀበሉት መሀል ምን ያህሉ እንዳገኙ የተሟላ መረጃ የለም። ፍለጋው የሚካሄደው በፈላጊው ወጪና ኪሳራ ስለሆነ፤ አንዳንዶቹ ገንዘባቸውን ጨርሰው፣ ሌሎች ደግሞ በሥራው አስቸጋሪነት ተስፋ ቆርጠው፣ አቋርጠው የተዉም ነበሩ። የገንዘብና የድርጅት አቅም ሳይኖራቸው ፈቃዱን ከተቀበሉ ወዲያ፤ አውሮፓ ላይ ፈቃዱን ለሌሎች ባለ ሀብቶች ለመሸጥ ሞክረው በምኒልክ ተቀባይነት ሳያገኝ፤ በዛው የጠፉም ነበሩ። ወርቅ ያለባቸውን ቦታዎች ፈልገው ያገኙም ነበሩ።
የፍለጋ ፍቃድ ተሰጥቷቸው ወርቅ አገኘን ካሉት የውጭ ሀገረ ሰዎች መሀል መክረስ ኢማኑኤል አንዱ ነው። ይህ ሰው በተጉለት አገኘሁ ያለውን የወርቅ አፈር ለማንጠርና ለማውጣት ምኒልክ የሰጡት ውል ይህን ይመስላል…
እኔ ዳግማዊ ምኒልክ ከመክረስ አማኑኤል ጋር ቀጥሎ የተጻፈውን ውል ተዋውለናል። 
 
የመጀመሪያ
ተጉለት ውስጥ የወርቅ አፈር አግኝቻለሁና ኮንትራቱን ሃምሳ ዓመት ሰጥተውኝ ላውጣ ቢለኝ፤ ወርቅ መገኘቱ እውነት ከሆነ፤ ወርቁን እንዲያወጣ ፈቅጄለታለሁ።
ሁለተኛ
ለዚሁ ወርቅ ማውጫ መኪናውን…ገዝቶ ካሁን ጀምሮ በአንድ ዓመት በ 1897 ዓ.ም መስከረም 4 ቀን ተጉለት ድረስ ያመጣል።
ሦስተኛ
ይህንንም የወርቅ ማውጫ መኪና አገጣጥሞ፤ በመኪናው የሚሠራ ሠራተኛ አምጥቶ፤ ደሞዙንም ችሎ ሥራ ከጀመረ ወዲያ የሚያወጣው ወርቅ ሃምሳ ዓመት ድረስ አንድ እጅ ለኢትዮጵያ መንግሥት፣ ሁለት እጅ መክረስ አማኑኤል ሊወስድ ተዋውለናል። ከሃምሳ ዓመት ወዲያ ግን ይህንን የወርቅ ማውጫ መኪና ከነመሣሪያው መክረስ አማኑኤል ለኢትዮጵያ መንግሥት ለቅቆ ይሄዳል።
አራተኛ
መኪናውን ተጉለት ድረስ አስመጥቶ ከተገጣጠመለት በኋላ ለሥራው የሚቀጥረውን ደሞዝተኛ ሰው፤ ሌላም የሚያስፈልገው ነገር ቢኖር፤ የሁሉንም ኪሳራ መክረስ አማኑኤል እንጂ የሚችል የኢትዮጵያ መንግሥት በደሞዝ፣ በመሣሪያ፣ በሌላም ነገር ሁሉ ኪሳራ የለበትም።
አምስተኛ
የወርቅ ማውጫ እስቲመጣለት ድረስ ሥራ እንዳይፈታ፤ አንድ የወርቅ መሀንዲስ ይዞ፤ በእጁ እየሠራ የሚያወጣውን ወርቅ እንደውሉ ከሦስት አንድ ለኢትዮጵያ መንግሥት ይሰጣል።
ስድስተኛ
ከአሁን ጀምሮ እስከ አንድ ዓመት ድረስ የወርቁን ማውጫ መኪና አምጥቶ በ 1897 ዓ.ም በመስከረም 4 ቀን ድረስ ያመጣው መኪና ተጉለት ላይ ወርቅ ማውጣት ያልጀመረ እንደሆነ ግን የተዋዋልነው ውል ይቀርበታል። የውሉም ወረቀት ይመለሳል። ይህንንም የውል ወረቀት ሊመልስ ዋሱ ባላምባራስ ጊዮርጊስ ነው።”
ተጻፈ መስከረም 6 ቀን 1896 ዓ.ም አዲስ አበባ ከተማ።
በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ውስጥ በተላያየ ቦታዎች ወርቅና ልዩ ልዩ ማዕድን ያሉባቸውን ቦታዎች ፈልገው ያገኙ የተለያዩ የውጭ ሀገር ዜጋዎች ነበሩ። በወለጋ፣ ሐረር፣ ሲዳሞ፣ በአባይ ተፋሰስ አካባቢና አንዳንድ ቦታዎች ተገኝተዋል። ሆኖም ሥራው የሚጠይቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂና ድርጅት ማቅረብ ባለመቻላቸው የሀገሪቱም የትራንስፖርት ችግር ከባድ መሰናክል በመሆኑ፤ ግዙፍ ኩባንያዎችና ባለ ሀብቶች ሊገቡበት አልቻሉም። በአነስተኛ ካፒታል ለሚሄዱ የንግድ ጀብደኞች (Commercial Adventures) ሁኔታው የሚያዋጣ አይደለም። በቂ ካፒታል ላላቸው አልሚዎች ግን ሀገሪቱ ከሚገመተው በላይ እምቅ ሀብት ይዛለች፤ መስተንግዶዋም አጥጋቢ ነው። በማለት አሜሪካዊው ስኪነር ተናግሯል።
ምንጭ
ታላቁ ጥቁር ኢትዮ- አሜሪካ ዘዳግማዊ ምኒልክ። 
ንጉሴ አየለ ተካ 
ክብር ለእምዬ ምኒልክ!!!
Filed in: Amharic