>
5:01 pm - Wednesday December 2, 6207

የይሁዳ ድንቁርና - በእኛ ሀገር ጎዳና...!!! (ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ)

የይሁዳ ድንቁርና – በእኛ ሀገር ጎዳና…!!!

ዲያቆን ብርሃኑ አድማስ

ዘመነ ዮሐንስ አኔን የአራት ዐመት ያህል ከብዶኝም ረዝሞብኝም አለፈ፡፡ አስቀድሜ የጠበቅሁት ቢሆንም ግን እንደከበደኝ ከረመ፡፡ ዛሬ እንኳ ይህን ስጽፍ የቀረችን አንድ ቀን ምን ታመጣ ይሆን? እያልኩ ነው፡፡ ነገሩ ግን ከቅዱስ ዮሐንስ አይደለም፤ ከእኛ ነው እንጂ፡፡ እርሱም እንደ ተወለወለ መስታወት ንጹሕ ስለሆነ ጉድፋችንን አሳየን፤ በራሳችንም ጉድፍ ደነገጥን እንጂ ምን አደረገ? በርግጥ ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በተለይ ከጌታ ስቅለት በኋላ ዝምተኛና ሐዘንተኛ ሆኖ እንደኖረ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይናገራል፡፡ ታዲያ እንኳን በዘፈን በመዝሙርም ሳይቀር ድለቃ የምንወድደውን ሰዎች እስኪ ተመለሱ፥መጀመሪያ የውሰጥ ቆሻሻችሁን አንሡ ቢል ምን አጠፋ፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ጌታ የሚወድደው ንጹሕ ድንግል ስለነበረ ንጽሕተ ንጹሐን እመቤታችን እናት ሆና ተሰጠችው፡፡እርሷን ንጽሕና የሌለው እንኳ ቢሆን መንጻትን የማይወድ ሊቀበላት አይችልምና፡፡ ከዚህም የተነሣ ሽንገላን አጥብቆ የሚጸየፍ  ክቡር ንጹሕ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በወንጌሉም ላይ የይሁዳን ሽንገላ ያጋለጠው ለዚሁ ነው፡፡ “ነገር ግን ከደቀ መዛሙርቱ አንዱ አሳልፎ ሊሰጠው ያለው የስምዖን ልጅ የአስቆሮቱ ይሁዳ። ይህ ሽቱ ለሦስት መቶ ዲናር ተሽጦ ለድሆች ያልተሰጠ ስለ ምን ነው? አለ። ይህንም የተናገረ ሌባ ስለ ነበረ ነው እንጂ ለድሆች ተገድዶላቸው አይደለም፤ ከረጢትም ይዞ በውስጡ ከሚገባው ይወስድ ስለ ነበረ ነው” /ዮሐ 12፤ 4-5/ ሲል እንደገለጸው ይሁዳ በድሆች አመካኝቶ ለጌታ የተደረገውን እስከመተቼትና ሽንገላውን የማያውቁ ቅኖችን እስከማታለል የሄደበትን አጋልጦ ነበር። ዘንድሮም ያደረገው ይህንኑ ይመስለኛል፡፡
በሀገራችን ሽንገላ በዝቷል፡፡ ልክ እንደ ይሁዳ ተቋርቋሪ መስሎ ለራስ ጥቅም መንገብገብ መሠረት ጥሏል፡፡ መዝሙረኛው ዳዊት “እርስ በርሳቸው ከንቱ ነገርን ይናገራሉ፤ በሽንገላ ከንፈር ሁለት ልብ ሆነው ይናገራሉ” /መዝ 11(12) ፤ 2/ ሲል እንደተናገረው ከምንሰማው አብዛኛው የሽንገላና የላይ ላይ እንደሆነ ይሰማኛል።  ነገር ግን ቅዱስ ዮሐንስ በዘመኑ የይሁዳን ሽንገላና አዛኝ መስሎ መታየት እንደ ገለጠው።ዘንድሮም የኢትጵያውያንን ሽንገላችንን እና ማስመሰላችንን በዘመኑ ግልጥልጥ አደረገብን።ልክ እንደ ይሁዳ ለጌታም ቢሆን የማንመለስ ጨካኞች መሆናችንንም ገላለጠው፡፡ ምንም እንኳ ለድኅነታችን ብሎ ጌታ በፈቃዱ ቢቀበለውም ይሁዳ ለጥቅሙ ብሎ ንጹሐ ብሕርይ ጌታን አሳልፎ እንደሰጠ የእኛ ሀገር የሺንገላና የይስሙላ ፖለቲካም ብዙ ንጹሐን ምስኪኖችን አስገደለ።ሠርተው ያገኙ ሰዎችንም በአንድ ጀንበር ምንም የሌላቸው ድሆች አደረገ፡፡ በንግግራችን አቃፊ፣ ደጋፊ፣ … እያልን ገፊና ገፋፊ መሆናችንን አጋለጠን፡፡ ይህ ሁሉ ግን በሆኑ አካላት እየተመካኘ የሚደረግ ተንኮል ሳይሆን አይቀርም፡፡ በልጅ አመካኝቶ ይበላሉ አንጉቶ ማለት ይህ ነው፡፡ ኧረ እንዲያውም “ልጅ” የሚለውን ፊደላቱን አለዋውጠን “በጅል አመካኝቶ ይፈርዳሉ አዳልቶ፥በሕዝብ አመካኝቶ ይበላሉ አንክቶ” ብለን ልንተርጉመውም እንችላለን፡፡ ምክንያቱም ጥቃትና ጥፋቶች በሆኑ በተነዱ ሞኝ ሰዎች ይመካኛሉ፤ ዘረፋዎችና ማግበሰበሶችም በሕዝብ ጥቅም ስም ይመካኛሉ፤ ልክ እንደ ይሁዳ ማለት ነው፡፡ ይሁዳ ይህ ሽቶ ተሸጦ ለድሆች ለምን አልተሰጠም ነበር ያለው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ እንዳጋለጠው ግን ለድሆች ተገድዶላቸው ሳይሆን ሌባ ስለነበረ ነው፡፡ እንደ ይሁዳ ለጌታ የቀረቡ መስለው ቢታዩም ልባቸው ግን የራቀ መሆኑን በግብራቸው ገልጠውታል፡፡ ለድሆች በማሰብ ሰበብ ጌታን እስከ መሸጥ ለገንዘብ ይንገበገባሉና፡፡
አሁንም ያለው ልክ ያንኑ የሚመስል ነው፡፡ እነዚህ ተቆርቋሪ የሚመስሉ አካላት በኋላ ደግሞ ልክ እንደ ይሁዳ መካዳቸው የማይቀር ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ግን ዋዛ አይደለም፤ የይሁዳ ንግግር የበጎነት ሳይሆን የሽንገላና የሌብነት መሆኑን እንደ ገለጠ በእኛም ሀገር ዘንድሮ ስንቱን ገላለጠው፡፡ አባ ጊዮርጊስ በሰዓታት ጸሎት ኵሎሙ ዘዘወትር ላይ ቅዱስ ዮሐንስን “ዘንስር ዮሐንስ ዘልዑለ ይሰርር ወልዑለ ይሰብክ፤ … ይኔጽር ወያጸምዕ ትእዛዘ ዘእምቃለ ነጎድጓድ” እንዳለ እርሱ ከፍ ብሎ በመብረርና ታላቁን ነገር በመናገር  ከቃለ ነጓድጓድ ጌታ ትእዛዛትን እያየ እያደመጠ ይነግራል፣ ያደርሳል፤ የሆነውም እንደዚህ ይመስላል፡፡
 የኋላ የኋላ ግን ቅዱስ ዳዊት “የሽንገላን ከንፈሮች ሁሉ እግዚአብሔር ያጠፋቸዋል፥ ታላቅ ነገርን የምትናገረውን ምላስ” /መዝ 11፤3/ ሲል እንደገለጸው እየሸነገሉ የሚያጠፉ እንደ ይሁዳም የሚክዱ ሁሉ ልክ እንደርሱ የወሰዱትን ሳይበሉት ያሰቡትን ሳያገኙት መጥፋታቸውም አይቀርም፡፡ ጌታ ሆይ የሚያደርጉትን አያዉቁምና ይቅር በላቸው፡፡ ሁላችንንም ይቅር በለን፡፡
ለዚህ ሁሉ ምግባረ ቢስነትና ወራዳነት ያጋለጠን ግን ዋናው ድንቁርና ይመስለኛል፡፡ ከተሜዎችና ፊደል ቀመሶች ያለብን ድንቁርና ልክ እንደ ይሁዳ ያለ ደንቁርና ነው፡፡ ይሁዳ ከሐዋርያት ጋር እየተማረ በተማረው እንዳልተለወጠ፣ ተእምራት እያየና እያደረገም ነገር ግን እርሱ በጌታም ላይ ሳይቀር ብልጥ ሊሆን የሞከረ የተማረ ደንቆሮ ነበር፡፡ በእርሱ ቤት ጌታን በሰላምታ ሲጠቁም እንኳን ሌላው ሰው ጌታም የሚያውቅበት ያልመሰለው በሁለት ቢላ ሊበላ ያቀደ በእውነት የተማረ ያየና የሚያውቅ ደንቆሮ ነበር ማለት ይቻላል፡፡ በእኛ ሀገርም ከተራው ሕዝብ እስከባለሥልጣናት፤ ከኢአማኒው እስከ ሃይማኖት መምህሩ ድረስ ከሚያደርገው አብዛኛው ነገር ከዚህ የተለየ አይደለም፡፡ በተለይ ተምረናል ብለን የምናስበው በይሁዳ ድንቁርና እጅ ተወርች የታሰርን እስኪመስል ድረስ ልክ እንደ እርሱ እንኳን ሰውን ፈጣሪን አሁንም ደግመን ልናታልለው ከመሞከር አልተመለስንም፡፡ ያሳዝናል፤ ዮሐንስ ግን አሁንም በእርሱ ዘመን ሁለንተናችንን አጋለጠ፡፡ ከገባን በሽንገላና በማስመሰል ልብስ ከሚሽሞነሞን ድንቁርና እንውጣና ዘመኑ ሲለወጥ አብረን እንለወጥ፡፡
ዘመነ ዮሐንስ ሆይ በእውነት በሰላም ዕለፍ፡፡ እንኳን የእኛን ኮረና አምጥተህ የዐለምንም ግብዝነቷን ገለጥክባት፤ ሃያላን ነን የሚሉትም ሳይቀር መሳቂያ መሳለቂያ ሆኑ፡፡ እነ ሁሉን በእጄ ተንበርክከው ለመኑ፡፡ ዐለም በሙሉ እንደ  ሰብአ ትካት አንተን ለመውጋት ሲያንጋጥጥ  መደበቂያ አጥቶ እቤቱ ቁጭ እስኪል ድረስ ገመናውን ገለጥክበት፡፡ ይህን ለፍላፊ ዐለም ውስጡ ዝም ስላላለ መለፍለፉን ባያቆምም አፉን በማስክ አስለጎምከው፡፡ በእውነት የዘንድሮ ዘመነ ዮሐንስ ያልገላለጠውና ያልገለባበጠው ነገር የለም፡፡ የእኛም ድንቁርና ድቅድቅ ጨለማ መሆኑ ታይቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ከዚህ ለመውጣት የምናስብ አይመስልም፡፡ እንዲያውም እንደ ይሁዳ ራሳችንን የሚያጠፋ ጦርነትና መዓት የምንፈልግ ሳንሆን አንቀርም፡፡ ይሁዳ ከጌታና ከደቀመዛሙርቱ ሳይለይ በተሰጠው ተግሣጽ ቢስተካከል ኖሮ ያ ሁሉ አይገጥመውም ነበር፡፡
የእኛም የእርሱን ይመስላል ያልኩት ድንቁርናችን ከመጽናቱ የተነሣ የምናደርገው ሁሉ ራሳችንን የሚያጠፋ መሆኑን የማናውቅና በሰላሙ ጊዜ ስንመከር የማንሰማ ስለመሰለኝ ነው፡፡ ምናለ በተሳሳትኩና ከጥፋት ባመለጥን፡፡ ለማንኛውም እንኳን ለዘመነ ማቴዎስ አደረሰን፡፡ መጪውን ዘመን ከሺንገላ፣ ከማስመሰልና ከጥልቅ ድንቁርና ለመላቀቅ የምንጀምርበት፣ እንደ ግለሰብም ሆነ እንደ ሀገር ከጥፋትም የምንድነበት ዘመን ያድርግልን፡፡ አሁን በአዲስ ዘመን ይህን ሁሉ ምን አሰኘህ የሚል አካል ልቡና አሳቡ አሮጌ ለሆነ ሰው ምን አዲስ ዘመን ይኖረዋል ብዬ እመልስለታለሁ፡፡ እኛ አዲስ ልብ ይዘን ዘመኑን አዲስ ለማድረግ ያብቃን፡፡ ለማንኛውም መልካም በዓል ይሁንልን፤ አሜን፡፡
Filed in: Amharic