>

ስለ ትግራይ ምርጫ (የአረና ሊቀመንበር አብርሀ ደስታ) 

ስለ ትግራይ ምርጫ

(የአረና ሊቀመንበር አብርሀ ደስታ) 

“ሰሞኑን ስለ ትግራይ ምርጫ ጥሩ ነገር እየፃፍክ ነው። ዓረና በምርጫው አለመሳተፉ ተፀፀትክ እንዴ?” የሚል ጥያቄ ቀርቦልኛል።
አልተፀፀትኩም ግን ተቀብያለሁ!
ትግራይ ምርጫ አካሂዳለች። ምርጫው የፌደራል መንግስት ትእዛዝ ባላከበረ መልኩ የራሷን ፀጥታ አስከብራ በተናጠል የተደረገ በመሆኑ ትግራይ ዲ ፋክቶ ስቴት መሆኗ ማሳያ ነው ማለት ይቻላል። By default, Tigrai has officially become a De facto State.
ሀገራዊው ምርጫ በኮቪድ 19 ወረረሽኝ ምክንያት ከተራዘመ በኋላ በህወሓት የሚመራው የትግራይ ክልል መንግስት በተናጠልም ቢሆን ትግራይ ውስጥ ምርጫ መደረግ አለበት ብሎ ወሰነ። በዚህ ጉዳይ ብዙ ክርክር ተደረገ። የተለያዩ ወገኖች የተለያየ መከራከርያ ነጥብ አነሱ።
1. ህወሓት
ህወሓት በትግራይ ደረጃ ምርጫ እንዲካሄድ የወሰነችበት ምክንያት እልህ እና ስጋት (ዋስትና ማጣት) ነው። ህወሓትና ብልፅግና ፓርቲ ከአንድ ወንዝ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ) የተቀዱ በመሆናቸው አብረው የነበሩ ሲለያዩ መጠፋፋት እንጂ አብሮ በሰላም መኖር አይታያቸውም። በመሐከላቸው መተማመን አይኖርም። እናም ህወሓት ምርጫ ማካሄድ ፈለገች። ምክንያቱም ምርጫ ከተደረገ
(ሀ) ህወሓት በህዝብ የተመረጥኩ ነኝ በማለት በትግራይ ህዝብ ጉያ ውስጥ ለመደበቅ ይረዳታል። የትግራይ ህዝብ የደገፈው ማንም ሌላ አካል ከትግራይ ክልል ስልጣን ሊያባርረው እንደማይችል ትገነዘባለች።
(ለ) በብልፅግና ፓርቲ የሚመራው የፌደራል መንግስት በምርጫ ጫና ውስጥ ይገባል፤ ስልጣኑ እንዳያደላድል ይረዳል። ምርጫው በሐይል ለማስቆም ከሞከረ ደግሞ በትግራይ ህዝብ እገዛ ይሸነፋል ብላ ታስባለች።
(ሐ) “እኔ በህዝብ የተመረጥኩ ሕጋዊ መንግስት ስሆን ብልፅግና ፓርቲ ግን ሕገ ወጥ ነው” የሚል ፖለቲካ በማራመድ ብልፅግናን ማሸነፍ ይቻላል ከሚል እምነት ነው።
እናም ህወሓት ምርጫ ለማካሄድ ቆርጣ ተነሳች።
(2) አዳዲስ የትግራይ ፓርቲዎች (ባይቶና፣ ሳወት እና ውናት)
ምርጫው ከህወሓት በላይ ፈልገውታል። በምርጫም ተሳትፈዋል። አንዳንድ ሰዎች “እነዚህ አዳዲስ የትግራይ ፓርቲዎች የህወሓት አሻንጉሊቶች ናቸው። ህወሓትን ለማጀብ ነው በምርጫ የተሳተፉ” ይላሉ። እኔ ግን አልስማማም። አዲሶቹ ፓርቲዎች የህወሓት አሻንጉሊቶች ሳይሆኑ ራሳቸው የቻሉ የራሳቸው ዓላማ ያነገቡ ድርጅቶች ናቸው። የትግራይ ምርጫ እንዲካሄድ ከህወሓት በላይ የወተወቱ፣ በምርጫ የተሳተፉ የራሳቸው የፖለቲካ አጀንዳ ለማራመድ እንጂ ህወሓትን ለመደገፍና ለማጀብ አይደለም። ሦስቱም አዳዲስ ድርጅቶች ትግራይ ለብቻዋ እንድታስብ ይፈልጋሉ፤ ምርጫ በተናጠል ለብቻ ማድረግ ትግራይ ራሷን ችላ በተናጠል እንድታስብ የሚያግዝ ወርቃማ ዕድል ነው። ለዚህም ትግራይ በተናጠል ምርጫ እንድታካሂድ ወተወቱ፣ ተሳተፉ። ከፖለቲካ ዓላማቸው አንፃር ልክ ናቸው።
 ፍላጎቶቻቸው ባጭሩ፥
(ሀ) ባይቶና
“ትግራይ በሁሉም ረገድ ራሷን ችላ እንድትቆም (ማለትም ራሷን የቻለች ሀገር እንድትሆን) መጀመርያ የኢትዮጵያ ፌደሬሽን ወደ ኮንፌደሬሽን መላላት አለበት” ይላል። ይህን ዓላማ እውን ለማድረግ ታድያ ትግራይ ለብቻዋ ተነጥላ ምርጫ ብታደርግ ትልቅ ዕድል አይደለምን?
(ለ) ሳወት
“የትግራይን ጥቅም ለማረጋገጥ ትግራይን ማእከል ያደረገ ፖለቲካ ማራመድ አለብን። የኢትዮጵያ ፌደሬሽንም ለትግራይ (ለሌሎችም ጭምር) በሚጠቅም መልኩ እንዲስተካከል አዲስ ድርድር (ውል) ያስፈልገናል። የፖለቲካ አስተሳሰባችን ከትግራይ የሚመነጭ መሆን ይኖርበታል” ይላል። ታድያ ይህንን እውን እንዲሆን ትግራይ ለብቻዋ ምርጫ ብታደርግ ጥሩ አጋጣሚ አይሆንም? ትግራይ ከፌደራል መንግስት ቁጥጥር ውጭ የሆነ ክልላዊ መንግስት ሊኖራት አይገባም? ከዚህ አንፃር ሂደቱ መደገፋቸው ልክ ነው።
(ሐ) ውናት
“ትግራይ ወደ ቀድሞ ልዕልናዋ መመለስ አለበት። ይህም ኢትዮጵያ ውስጥ ሆና ልታሳካው አትችልም። የትግራይ ስልጣኔና ዕድገት እውን የሚሆን ትግራይ ከኢትዮጵያ ወጥታ ራሷን የቻለች ሀገር ስትሆን ነው” ይላል። ታድያ ትግራይ ክልልን ከኢትዮጵያ ነጥሎ ራሷን የቻለች ሀገር ለማየት ያቀደ ፓርቲ እንዴት ትግራይ ለብቻዋ ተነጥላ ምታካሂደው ምርጫ አይደግፍም? እንዴት በደስታ አይሳተፍም? ትግራይ በተናጠል ምርጫ አካሄደች ማለትኮ ለመገንጠል (በውናት አጠራር “ሀገር” ለመሆን) ግማሽ መንገድ መጓዝ ነው። ስለዚህ ለውናት ሂደቱ በራሱ ድል ነው።
(መ) ዓዴፓ
ዴሞክራሲያዊት ፌደራላዊት ሪፐፕሊክ ኢትዮጵያ ይደግፋሉ። በምርጫው የተሳተፉት በዴሞክራሲ ሂደቱ የራሳቸው አስተዋፀኦ ለማበርከት ይመስለኛል።
(ሠ) ዓረና
“የኢትዮጵያ ሀገራችን ዋነኛ ችግር ዴሞክራሲ አለመኖር ነው። ዴሞክራሲያዊ መንግስት ስለሌለን በሁላችን ኢትዮጵያውያን መካከል ፍትሕ፣ እኩልነት፣ ነፃነትና አንድነት አልሰፈነም። በዚህ ምክንያት ሁላችን ተጠቃሚ አይደለንም። ስለዚህ ሁላችን ኢትዮጵያውያን በጋራ ታግለን በሀገራችን ዴሞክራሲያዊ መንግስት እንዲመሰረት በማገዝ ፍትሕና እኩልነት ሰፍኖ ሁላችን እኩል ተጠቃሚ ሆነን በጋራ በአንድነት መኖር ለሁላችን ይበጃል” ይላል። ይህን እውን እንዲሆን ምርጫ መካሄድ አለበት፤ ያለ ምርጫ ዴሞክራሲ አይሰፍንምና። ግን ሀገራዊ አንድነታችንን ባከበረ መልኩ እንዲካሄድ ምርጫው አንድ ላይ በሀገር ደረጃ መካሄድ አለበት። አንድ ስለ ሀገር አንድነትና የህዝቦች ደሕንነት የሚጨነቅ ፓርቲ ትግራይ ክልል ለብቻዋ ተነጥላ ምርጫ ማካሄዷ ሊደግፍ አይችልመ። ቀጥታ ከዓላማው ጋር ይጋጫልና። ከዓላማችን አንፃር የተናጠል ምርጫው አለመደገፋችን ልክ ነው።
ታድያ ሰሞኑን ለምን የህዝብን ምርጫ ደገፍኩ? ተፀፀትኩኝ? አይደለም! አልተፀፀትኩም! የህዝቤን ፍላጎትና ድምፅ የመቀበልና የማክበር ግዴታ ስላለብኝ ነው።
ፓርቲዎች ለህዝባችን የተሻለ ነው ምንለው አማራጭ ሐሳብ እናቀርባለን፣ በአቋማችን ፀንተን እንከራከራለን። በመጨረሻ ግን ህዝብ ነው ሚወስነው።
ከዚህ በፊት “ምርጫው በተናጠል ማድረግ የለብንም” አልን። ህዝብ ግን ለመምረጥ ተመዘገበ፤ በሙሉ ወኔ መረጠ። ስለዚህ ህዝባችን በተናጠል ምርጫ መካሄዱ ደግፏል ማለት ነው። የፓርቲና የህዝብ ፍላጎት ከተለያየ የህዝብ ውሳነ ይፀናል። ፓርቲዎችም የፈለገ የተለየ ሐሳብ ቢያራሙድም የህዝብ ፍላጎት ማክበር አለባቸው።
የህዝቤን ፍላጎት አከበርኩ፤ አደነቅኩ! የውዴታ ግዴታዬ ነው።
የትግራይ ህዝብ ኢትዮጵያዊ አንድነቱን ጠብቆ እንዲቆይና ከሀገሩ ሀብት እኩል ተጠቃሚ እንዲሆን እፈልጋለሁ፣ እታገላለሁ፣ አሳምናለሁ። የኔን ሐሳብ ተቀብሎ ኢትዮጵያዊነቱን ካስቀደመ ደስ ይለኛል። ትግራይን ለመገንጠል የሚታገሉ ጓደኞቼን ጨምሮ ኢትዮጵያ ውስጥ እንቆያለን። የትግራይ ህዝብ የኔን ሐሳብ ሳይቀበል የጓደኞቼን የመገንጠል (ሀገር የመሆን) አማራጭ ሐሳብ ከደገፈ ደግሞ ሀገር ይሆናል። እኔም ከትግራይ ህዝብ ጋር አብሬው እገነጠላለሁኝ፤ የትግራይ ህዝብ አካል ነኛ። የትግራይ ህዝብ ገደል ቢገባ እገባለሁ፣ ሲታገል አብሬው እታገላለሁ፣ የገባበት እገባለሁ። ከትግራይ ህዝብ ተነጥዬ አልቆምም፤ ህዝቤ የሆነውን ነው ምሆነው። ከህዝቤ ውጭ ሌላ አጀንዳ የለኝም። ለህዝቤ ይበጃል የምለውን አማራጭ ሐሳብ ከማቅረብ ወደኋላ አልልም፤ የህዝቤን ፍላጎት ደግሞ አከብራለሁኝ። ለዚህ ነው የትግራይ ህዝብን የመምረጥ ፍላጎትና ውሳኔ ደግፌ ከህዝቤ ጎን የቆምኩት!
የምርጫ ሂደቱ
በምርጫ ሂደቱ ባንሳተፍም ከውጭ ሁኜ እንደታዘብኩት ከሞላ ጎደል ጥሩ ነበር ማለት ይቻላል።
(ሀ) የፖለቲካ ምሕዳሩ በተወሰነ መልኩ ተከፍቶ በትግራይ ክልል ለመጀመርያ ግዜ በሚባል መልኩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚድያ ዕድል አግኝተው ተከራክረዋል፤ አማራጭ ሐሳባቸው በአግባቡ አቅርበዋል።
(ለ) ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ጥሩ የሚባል በጀት ተመድቦላቸው ባጭር ግዜ ብዙ ቦታዎች ተንቀሳቅሰዋል።
(ሐ) በርካታ ተጋሩ ወጣት ምሁራን ወደ አዲሶቹ ፓርቲዎች በመቀላቀል ተሳትፈውበታል። አኩሪ ነበር። በትግራይ አዲስ የፖለቲካ ምዕራፍ ተከፍቷል። በዚሁ ረገድ የዓረና ትግል ፍሬ አፍርቷል።
(መ) በዚህ አጭር ግዜ ምርጫው እውን እንዲሆን ሌት ተቀን ለሰራ የትግራይ ምርጫ ኮሚሽን ምስጋና ይገበዋል።
በምርጫው ቀን የመራጩ ህዝብ ወኔ (defiance ዓይነት) ታዝቤኣለሁ። “እንዴት አትመርጡም እንባላለን? መምረጥኮ ዋጋ የከፈልንበት መብታችን ነው። ከመምረጥ የሚያስቁመን ሐይል እስቲ እናያለን! ራሳችን የመረጥነው እንጂ ከፌደራል የሚላክልን አስተዳዳሪ አንፈልግም” የሚሉ ወኔ እና እልህ ያዘሉ ስሜቶች አንብቤያለሁ። በጣም ነው የተደሰትኩኝ። በቃ እንዲህ ነው ለመብት መቆም! የዴሞክራሲ ግንባታ ለመብት ከመቆም ይጀምራል!
በድምፅ አሰጣጥና ቆጠራ ሂደቱ ግን አስቂኝ ነበር። የህዝቡ ድምፅ በአግባቡ የተከናወነ አይመስለኝም። የህወሓት ባህሪ እናውቀው የለ! ደግነቱ ህዝቡ የመምረጥ መብቱን ማረጋገጥ እንጂ ማን ያሸንፍ የሚል አጀንዳ ጉዳዩ አልነበረም።
ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በምርጫ ውጤቱ  አዝነዋል ብዬ አስባለሁ። ግን ምንም ይላሉ ብዬ አልጠብቅም። በቃ! ወደ ውስጥ ያነባሉ!
ከምርጫው በኋላ ትናንት ማታ በተከናወነው የአዲስ አመት ዋዜማ ዝግጅት ለያንዳንዱ በምርጫ የተሳፈ ፓርቲ በሽልማት መልክ 2 ሚልዮን ብር ተበርክቶላቸዋል። ጥሩ ውሳኔ ነው።
አንድ ወዳጄ ግን “ሽልማቱ የተሰጣቸው የምርጫ ውጤቱ አንቀበልም እንዳይሉ አፍ መዝግያ ነው” የሚል ሐሳብ አንፀባርቋል። እኔ ግን አልስማማም። ሽልማት ባይሰጣቸውም፣ የምርጫ ውጤቱ ለመቀበል ቢከብዳቸውም ወደ ውስጥ እያነቡ ስለ ምርጫው መጥፎ ነገር ሳይናገሩ የተሰጣቸውን ተቀብለው ዝም የሚሉበት ምክንያቶች አሉ።
(ሀ) በምርጫው ባያሸንፉም፣ ምርጫው እንደተጭበረበረ ቢያውቁም ምርጫው በተናጠል መካሄዱ በራሱ ለነሱ ድል ነው። ስለዚህ “ምርጫው ችግር ነበረበት” ብለው የራሳቸውን የሠርግ ድግስ አያበላሹም። “ምርጫው ትክክለኛ፣ ፍትሓዊና ዴሞክራሲያዊ ነበር” ቢባል የበለጠ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ምርጫውም የበለጠ ትርጉም ይኖረዋል።
(ለ) “ምርጫው ልክ አልነበረም” ብለው አካኪ ዘራፍ ቢሉ ምን ይጠቀማሉ? በምርጫ ሰበብ ትግራይ ብትረበሽ፣ ብትበጠበጥ ምን ይጠቀማሉ? ይጎዳሉ እንጂ! በዚህ ግዜ ትግራይ እንድትበጠበጥ የሚፈልግ ትግራዋይ የለም። ከብጥብጥ ጉዳት እንጂ ጥቅም አይገኝም!
(ሐ) “የምርጫ ውጤቱ አንቀበልም” ብለው ግርግር ቢፈጥሩ በመሐል ብልፅግና ፓርቲ ገብቶ ጋማ ይላቸዋል። የምርጫው መካሄድ የደገፉበት አንዱና ዋናው ምክንያት የፌደራል መንግስት (ብልፅግና ፓርቲ) ጣልቃ ገብነት ለመከላከል ነው። ፌደራል መንግስት በትግራይ የፖለቲካ ጉዳይ ላይ ጣልቃ ገብቶ እንዳይፈተፍትና የትግራይ ህዝብን ራስን በራስ የማስተዳደርና የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብቶች እንዳይጋፋ ይፈልጋሉ። ስለዚህ ምርጫው እንከን ቢኖረው እንኳ ተፎካካሪ ፓርቲዎቹ በምርጫ ሰበብ ከህወሓት ግብግብ ገጥመው የብልፅግና ፓርቲን ጣልቃ ገብነት ስለማይጋብዙ ምርጫው እንዳለ ይቀበሉታል።
የህዝብን ፍላጎት እና ውሳኔ እቀበላለሁ፤ አከብራለሁ!
Filed in: Amharic