>
5:14 pm - Saturday May 1, 8647

እውነት ግን ወራሪው ማነው? ተወራሪውስ? (እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪክ) አሰፋ ሀይሉ

እውነት ግን ወራሪው ማነው? ተወራሪውስ?

(እውነተኛው የኢትዮጵያ ታሪክ)

አሰፋ ሀይሉ

“በመንቃት ላይ ባሉ ፍጡራን መካከል፣
ሕይወት የምንለው እንደ ጥሬ እህል፣
በኑሮ ምጣድ ላይ ቢቆላ ቢማሰል፣
የበሰለው ያራል ጥሬው እስኪበስል፡፡…”
     — ገሞራው (የበሰለው ያራል፣ 1961 ዓ/ም)

በርከት ያሉ የታሪክ መዘክሮች ደጋግመው የሚያወሱት እውነት ነው፡፡ ታሪክ ራሱን እንዴት እንደሚደጋግም ይገርመኛል፡፡ ታሪክ ራሱን ይደግማል፡፡ ጥሩ ጥሩውን መርጦ ቢደግመው መልካም ነበር፡፡ ነገር ግን መጥፎውም ይደገማል፡፡ እንደ አሁኑ፡፡ በኢትዮጵያ የረዥም ዘመናት ታሪክ አንድ ተደጋግሞ የተከሰተ ነገር የማዕከላዊ መንግሥት ሥልጣን የመዳከም ክፉ ዕጣ ፈንታ ነው፡፡
የነገሥታት የእርስበርስ የሥልጣን ሽኩቻና የማያባራ የእርስበርስ ጦርነት የሀገሪቱን አቅም እየደጋገመ እንክት አድርጓት ቆይቷል፡፡ በውጭ እና የሀገር ውስጥ ኃይሎች በነገሥታቱ ላይ የተቃጡ ወረራዎች በተደጋጋሚ ቢቀለበሱም የማዕከላዊ መንግሥቱን ሥልጣን ሳያልፈሰፍሱና የሀገሪቱን ህዝብና ንብረት ሳያራቁቱ አላለፉም፡፡ የግብጾች ወረራ፣ የቱርኮች ወረራ፣ የደርቡሾች (የሱዳን ማዲስቶች) ወረራ፣ የፈላሻዋ የዮዲት ጌዲዮን (የዮዲት ጉዲት) ወረራ፣ የአዳሉ የግራኝ አህመድ ወረራ፣ የጋሎች (የኦሮሞዎች) ወረራ፣ የእንግሊዞች ወረራ፣ የጣሊያኖች ወረራ፣ የሶማሌዎች ወረራ፣ የወያኔና-ሻዕቢያዎች ወረራ፣ …፡፡ አሁንም ከወረራ ታሪክ አላመለጥንም፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡
በነገራችን ላይ የኢትዮጵያ ነገሥታት ብቻም ሳይሆኑ የግብጻውያን ማምሉኮችም ብዙ ወረራዎችን አስተናግደው ከብዙዎቹ ተርፈዋል፡፡ የሱዳን፣ የኬንያ፣ የኡጋንዳ፣ የደቡብ አፍሪካ፣ እና የሌሎችም አፍሪካውያን ታሪክ በወረራዎች የተሞላ ነው፡፡ ነገር ግን በአፍሪካችን የተማከለ የነገሥታት አስተዳደር ታሪክ ውስጥ ምናልባትም እንደ ኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በተደጋጋሚ ብርቱ ወረራዎች እጅጉን የተፈተነ፣ እና ከሁሉም ወረራዎች ተርፎ ራሱን ማሰንበት የቻለ ሀገር የምናገኝ አይመስለኝም፡፡
ወረራ የኢትዮጵያ የ5,000 ዓመት ታሪክ ዋነኛ መገለጫው ሳይሆን አይቀርም፡፡ በብዛት በሰሜን የሀገራችን ክፍል መቀመጫቸውን ያደረጉ የኢትዮጵያ ቀደምት ነገሥታትና የማዕከላዊ መንግሥት አስተዳዳሪዎች እጅግ በሚገርም ፅናት የተቃጡባቸውን ወረራዎች ሁሉ ያለማሰለስ ሲመክቱ ኖረዋል፡፡ መመከት ብቻ አይደለም፡፡ እነርሱም በሁሉም አቅጣጫዎች ተደጋጋሚ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻዎችን ሲያካሂዱ ኖረዋል፡፡ ጥቃት እና መልሶ ማጥቃት፡፡ ወረራ እና መልሶ ወረራ፡፡ እጅ መስጠት የማይታወቅበት የብዙ ወረራዎች (እና ስለዚህም የብዙ መከራዎች) ዘመን አልፈን – እንዳይሆኑ ሆነን፣ ሳንጠፋም፣ ሳንኖርም – የአባቶቻችንን አስገራሚ የፅናት ታሪክ ነጋሪ እንሆን ዘንድ ተርፈን እዚህ ደርሰናል፡፡ ዝርዝሩ ብዙ ነው፡፡ ለታሪክ አጥኚዎች ልተወውና አሁን እየኖርንበት ስላለው የወረራ ዘመን የተወሰነ ነገር ልበል፡፡
ደግሞ ስለተከሰተ ከዚህም በፊት ብዬዋለሁ፡፡ አሁን የኢትዮጵያን የሺህዎች ዓመታት ታሪክ ሽረን፣ ኢትዮጵያን የኦሮሙማ እናደርጋለን የሚሉ ኃይሎች ከያቅጣጫው ያላቸውን መዋጊያ ሁሉ ይዘው ተነስተዋል፡፡ በማዕከላዊ መንግሥቱና የአስተዳደር መዋቅሮቹ ላይ በኢትዮጵያ በሁሉም አቅጣጫዎች ወረራ ፈጽመዋል፡፡ እየፈጸሙም ነው፡፡ የማዕከላዊ መንግሥቱን ተቆጣጥረው በጉልበታቸው ሥር እስከማዋል ደርሰዋል፡፡ የመሬት ወረራ፡፡ የሥልጣን ወረራ፡፡ የታሪክ ወረራ፡፡ የባህል ወረራ፡፡ የማንነት ወረራ፡፡ የኢኮኖሚ ወረራ፡፡ የብዙ ነገር ወረራ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ተግባሩን ማንም ‹‹ወረራ›› ብሎ ጠራውም አልጠራውም፣ በእኔ እምነት ያውም በዘግናኝ የግፍ ጭፍጨፋ፣ በዝርፊያና በንብረት ማውደም፣ በዘረኛ የተረኝነት ስብከት፣ እና በጦር መሣሪያ ኃይል ጭምር የታገዘና የተሞላ ሁሉን አቀፍ ‹‹ወረራ›› በኢትዮጵያ ውስጥ እየተካሄደ ነው፡፡
ቀድሞ ለዘመናት የሚጠሩበትን ስማቸውን ተፀይፈው አሁን ‹‹ኦሮሞ›› በመባል የሚታወቁት (እና በቀደሙ የታሪክ ማስረጃዎች በሁሉም ላይ ‹‹ጋላ›› በሚል መጠሪያ የምናገኛቸው) ሕዝቦች – በተረጋገጡ የታሪክ ማስረጃዎች ተመዝግቦ እንደምናገኘው – በ16ኛው ክፍለ ዘመን የግራኝ አህመድን አውዳሚ ወረራ ተከትሎ በኢትዮጵያ ውስጥ በተፈጠረው የኃይል ክፍተትና የማዕከላዊ መንግሥት አለመረጋጋት ተጠቅመው – ከደቡብና ከደቡብ ምስራቅ አቅጣጫ ኢትዮጵያን አከታትለው የወረሩ ህዝቦች ናቸው፡፡
በዓለም በታወቀው የአባ ባህሬ “History of the Galla” (‹‹ዜናሁ ለጋላ›› ወይም ‹‹የጋላ ታሪክ››)  መጽሐፍ ላይ እንዲያውም የኦሮሞ የመጀመሪያው የሙከራ ወረራ የግራኝን ወረራ በጥቂቱ ቀድሞ እንደተጀመረ በዝርዝር ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡ ኦሮሞዎች ከነባሩ መናኸሪያቸው ከቦረና ተነስተው ባሌን የወረሩት ከግራኝ ጥቂት ዓመታት ቀደም ብለው ነው፡፡ እውነቱ ይህ ከሆነ – የኦሮሞዎቹ ቀደምት ወረራዎች የተጀመሩት ከግራኝ ጥቂት ቀደም ብሎም ጭምር ነበር ማለት ነው፡፡ ቢሆንም ግን ከግራኝ የዋቢሸበሌን ወንዝ ተከትለው በኦሮሞዎቹ የተካሄዱት ወረራዎች ዕድሜ አጭር እንደነበር እንመለከታለን፡፡ ከግራኝ በፊት ኢትዮጵያን የደፈሩት የኦሮሞ ወራሪዎች ያሰኛቸውን ዘርፈው፣ ያሰኛቸውን ሰልበው፣ የቻሉትን ግብርና ሀብት ሰብስበው፣ የቻሉትን ያህል ሴቶችና ባሮች ማርከው፣ ወደመጡበት ቦረናቸው ይመለሱ ነበር፡፡
ነገር ግን ኦሮሞዎቹ በተለይ ሉባ ቢፎሌ በሚባለው የጎሣ ተዋጊ እየተመሩ ከቦረና በመነሳት በኢትዮጵያ ላይ በሁሉም አቅጣጫዎች ማለት በሚቻል መልኩ ወደ ሰሜን አቅጣጫ ያደረጉትን ዋናውንና ትልቁን ወረራ የፈጸሙት የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት በግራኝ አህመድ ወረራ ውልቅልቁ ከወጣላቸው በኋላ ነበር፡፡ ኦሮሞዎች ኢትዮጵያን ወርረው እስከ ደዋሮና ፋጠጋር፣ እስከ ይፋትና መንዝ፣ እስከ መራቤቴና ወረሴህ፣ ሌላ ቀርቶ እስከ ጎጃምና ጎንደር ለመድረስ የደፈሩትም፣ የቻሉበትም ወቅት – ከግራኝ አህመድ ወረራ በኋላ የነበረው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት አቅም የተሽመደመደበትና ከእጅግ አውዳሚ ጦርነት ማግሥት ራሱን አገግሞ እንደ ሀገር ለመቆም በሚድህበት አስከፊ ወቅት ላይ ነበር፡፡
/በነገራችን ላይ ይህን የኦሮሞ ተዋጊዎች ኢትዮጵያን ለመውረር በታሪክ በተደጋጋሚ የሚጠቀሙት ጊዜ (‹‹ታይሚንግ ኦፍ ኦል አውት ኢንቬዥን››) የኢትዮጵያ መንግሥት ጉልበት ሲዳከምላቸው ጠብቀው መሆኑን በመታዘብ ነበር ከዚህ በፊት ‹‹የጋላ ቀደምት ጦረኞች ለኢትዮጵያ ዘውዳዊ ግዛተ መንግሥት እንደ ‹‹ኦፖርቹኒስቲክ ዲዚዝ›› በድካም ሰዓት የሚያጠቃ፣ በሌላ ጊዜ አድፍጦ የሚጠባበቅ የጎን ውጋት ሆነውበት ኖረዋል – በማለት ከዚህ ቀደም አስተያየት የሰጠሁት፡፡/
የአክሱም ነገሥታት በፈላሻዋ ዮዲት ጉዲት ለ40 ዓመት በቆየ የገዢነት ዘመን የታወጀባቸውን ፀረ-ክርስትና ውድመትና እልቂት ለማምለጥ፣ የሙሴን ፅላት በምስጢር ወደ ዝዋይ ገዳም አሽሽተውት እንደነበረ የሚያወሱ የታሪክ ድርሳናት አሉ፡፡ በአፄ ገላውዲዮስ ዘመንም የኦሮሞ ወራሪዎች ንጉሡን በወረራ ወጥረው ቢያስጨንቁት እዚያው የአክሱም ቀሳውስት ሸሽተው የተጠለሉበት ገዳም ሸሽቶ ለመጠለል ተገደደ፡፡ ወደ አቢሲኒያ ምድር የዘለቁት የፖርቹጋሎቹ አሳሾች ፍራንሲስኮ አልሜዳ እና የፖርቹጋሉ ንጉሥ ዮሐንስ ዳግማዊ ልዩ መልዕክተኛ የነበረው ፔዬሮ፣ እንዲሁም አባ ባህሬይና ጄምስ ብሩስ፣ ሌሎችም የታሪክ ፀሐፊዎችና ተጓዦች ሁሉም በሚባል ደረጃ በተቀራራቢ ቃል የሚመሰክሩት የታሪክ እውነትም ይህንኑ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የግራኝ አህመድ ወረራ – የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ክፉኛ በማሽመድመድ – ለተከተለው ተከታታይና መጠነ ሰፊ የጋሎች ወረራ መንገድ ጠራጊ ሆኖ አገልግሏል፡፡
ግርግር ለብዙ ነገር ያመቻል፡፡ ለሌብነትም፡፡ ለዝርፊያም፡፡ ለውንብድናም፡፡ እና በተለይ ለወረራ ያመቻል፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ኦሮሞዎች ግርግር ለወረራ ያመቸው ሕዝብ የለም ብል ፈጽሞ ማጋነን እንዳይደለ ይታወቅ፡፡ ኦሮሞ ኢትዮጵያን የወረረው በግራኝ አህመድ በተፈጠረው መጠነ ሰፊ ሀገራዊ ግርግር ተጠቅሞ ነው፡፡ የግራኝ ጦስ ሳይበርድ፣ በግራኝ ጦርነት የተማገደው ህዝብ እፎይ ሳይል፣ ሁሉም ቅስሙንና የተሰበረ ጉልበቱን ለመሰብሰብ ጊዜ በሚፈልግበት በዚያ ክፉ የምጥ ሰዓት – የቦረና ተዋጊ ኦሮሞዎች እየገሰገሱ ያለምንም የረባ ተቀናቃኝ ኢትዮጵያን በያቅጣጫው ወረሩ፡፡ ዛሬ ላይ በመራቤቴ የምናገኛቸው የሚዳ ኦሮሞዎች፣ በጎጃም፣ በሸዋ፣ በወሎ፣ በባሌ፣ በሐረር፣ በወለጋ፣ በሌሎችም የኢትዮጵያ ሥፍራዎች ተሰራጭተው የምናገኛቸው ኦሮሞዎች – በዚያ የግራኝ አህመድን ወረራ ተከትሎ በተከናወነው መጠነ ሰፊ የጋሎች ወረራ በኢትዮጵያ ምድር ለመስፈር የበቁ የኦሮሞ ዘርማንዘሮች ናቸው፡፡
አንዳንድ የታሪክ ፀሐፊዎች በኦሮሞዎቹ ወረራ ግሥጋሴ ፍጥነት እስከመደነቅ ደርሰው ርቀቱን ከደቡብ ምስራቅ ቦረና አሁን በኤርትራ አካባቢ እስከሚገኙት እስከ ሳሆዎች የደረሰ ያገኘውን ሁሉ በኃይል እየጨፈለቀ፣ ማንነቱን እያለበሰ የተከናወነ እጅግ ውጤታማ ወረራ ነበር – ብለው ይገልጹታል፡፡ ጀምስ ብሩስ ባሳተመው የጉዞ ማስታወሻ በጎንደር እያለ ስላጋጠመው በንግሥና ስሙ ራሱን ‹‹ጓንጉል›› ብሎ ስለሚጠራ የጋላ ተዋጊዎቹ መሪ ያተተው ነገር እጅግ ያስገርማል፡፡ የጀምስ ብሩስ ትረካ እውነት ከሆነ – ከጎንደር ነገሥታት ጀርባ ሆኖ ሀገሪቱን ይመራ የነበረው ራስ ሚካኤል ስሁል – ምናልባትም ጊዜ ለመግዛት ከኦሮሞዎቹ ጋር ሠላም የመፍጠር ሙከራ ማድረጉን ያመላክታል፡፡
እንደ ጀምስ ብሩስ ትረካ ይሄ የኦሮሞዎቹ ‹‹ጓንጉል›› አምስት መቶ ተዋጊዎቹን አስከትሎ ወደ ጎንደር ቤተመንግሥት ሲጠጋ – ፀጉሩን እንደ ቃልቻ አፈርዞ፣ ከከብት ቆዳ እንደ ቋንጣ ተደርጎ የተሠራ እና ከፀጉሩ ለመለየት የሚያስቸግር የተንዠረገገ መርገፍ በአናቱ ላይ ደፍቶ፣ በደረቱ እና በወገቡ ላይ የተቆረጠ የላም ጡት አስሮ እንዳንጠለጠለ፣ እና በአንገቱ ካሠረው የላም ጡት ሥር በደረቱ ላይ ባሰፋው ነጭ የጥጥ ፈትል ላይ ቅቤ አስጋግሮበት ቅቤው በሰውነቱ ቁልቁል ወደመሬቱ እየወረደ፣ በላም ላይ ተሳፍሮ በሚገርም ተዓምር ሆዱን ወደፊት አንፈራጦ፣ ወደ ጀርባው እጅግ ተለጥጦ፣ ላሟን እየጋለበ፣ መላ ሰውነቱ በእርጥበት ተሞልቶ፣ ልክ በሆነ ምትሀት ኃይል እንደሚሄድ ሁሉ ከሩቅ አውሎ ነፋሱን እያስነሳ ወደ ጎንደር ቤተመንግሥት ሲቃረብ – ለወትሮው ስሜቱን መግራት ይችል የነበረው እና ለጭካኔም ወደ ኋላ የማይመለሰው ራስ ሚካኤል ስሁል ጓንጉልን ከሩቅ ተመልክቶት – ሳቁን መቆጣጠር እንዳቃተውና ሰምቶት የማያውቀውን ሳቅ አቅሉን እንዳጣ ሰው እያሽካካ ወደ ሌላ የቤተመንግሥቱ ሣሎን እየሮጠ እንደተደበቀ – ጄምስ ብሩስ ገጠመኙን ያትታል፡፡
ጄምስ ብሩስ ጓንጉልን ሲገልጸው እግሩ የተቆለመመና ከሰውነቱ ጋር ሲነጻጸር እጅግ ቀጭን፣ ጭንቅላቱ ትልቅ፣ እና ዕድሜው 50 ዓመት የሚሆነው – በማለት ይናገራል፡፡ ጄምስ ብሩስ በእርግጥ እርሱ ሳይደርስ ከሩቅ ቤተመንግሥቱ ደጃፍ ላይ የደረሰውን የቅቤውን ሽታ እያነሳ በጋላው መስፍን በጓንጉል ላይ ብቻ ተሳልቆ አያበቃም፡፡፣ ራስ ሚካኤል ስሁል በጓንጉል አንገት ላይ በታሠሩት የላም ጡቶች ይሳለቅ እንጂ፣ ራሱም ከጦርነት ሲመለስ በርከት ያሉ የወንድ ልጅ ብልቶችን ሰልቦ እንደ ግዳይ እያውለበለበ የሚመለስበት ጊዜ እንደነበረ ጨምሮ ጽፎት እናገኘዋለን፡፡
እና እኛስ ጀምስ ብሩስን እንመነው? ወይስ አንመነው?፡፡ ጄምስ ብሩስ እኮ አክሱም ሄዶ ሁለት ትግሬዎች ላሟን በህይወት እያለች ከቂጧ ላይ ካለው ሥጋ ሁለት ቦታ በቢላዋ ቀደው ቦትርፈው እንደበሉና፣ ቁስሏን ጠራርገው መልሰው ቆዳዋን አልብሰው የተረፈችውን ከብት አስነስተው ለራት ለሚጠብቋቸው ጌቶቻቸው ማታ ላይ ሊያርዷት ከነሥቃይዋ እየነዷት እንደሄዱ ጭምር የጻፈ የፈጠራ ጀግና ነው፡፡ ብዙዎች የሀገሩ ሰዎች የጻፋቸውን አንዳንድ በሬ-ወለደ ታሪኮች አላመኑትም፡፡ እኛንም ለማመን የሚያስገድደን የለም፡፡ ብዙዎቹ የተናገራቸው ግን ልክ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ የእምነት ጉዳይ ብቻ አይመስለኝም፡፡
ከጀምስ ብሩስ በኋላ በመጡ ተጓዦች የተረጋገጡ ብዙ ፍሬነገሮች ሰውየው በወጉ ሳይመሰገንና ሳይታመን ኖሮ ህይወቱ እንዳለፈች አመላክተዋል፡፡ የሚገባውን ክብር ሳያገኝ ያለፈ ጀግናም ተደርጓል በሀገሩ፡፡ ላገሩማ ጀግና ነው፡፡ እኛን ሰለለ፡፡ መጽሐፈ ሄኖክን ሰርቆም ኮርጆ ፅፎም ይዞ ሄደ፡፡ እና ለእነርሱ ጀግናቸው፣ ለእኛ ደሞ ስለ ኦሮሞውም ስለ ምኑም ጽፎልን የሄደ ማጣቀሻችን ነው፡፡ ጀምስ ብሩስ ነገሮችን ከመጠን በላይ ቢያጋንንም ያላየውን ግን አልጻፈም፡፡ ይህ የብዙዎች አረዳድ ነው፡፡ የሚናገረው ብዙ ነው፡፡ ማመን መብት ነው፡፡ አለማመንም፡፡ በበኩሌ ከጉራዎቹና ከግነቶቹ ባሻገር  ብዙውን ነገሩን ተቀበልኩት፡፡
በነገራችን ላይ የኦሮሞ ወራሪዎች አንድ የሚገርም ልዩ ልማድ ነበራቸው፡፡ የረገጡትን መሬት ሁሉ በስማቸው ሳይሰይሙ ያለማለፍ ልማድ፡፡ ኦሮሞዎች ከግራኝ ወረራ ማግሥት ባካሄዱት ወረራ የረገጡትን መሬት ሁሉ በስማቸው ሰይመዋል፡፡ ሀገሩ፣ መንደሩ፣ ወንዙና ተራራው፣ ሰዉና ሰብሉ፣ የእነርሱ ሆነም አልሆነ ጉዳያቸው አልነበረም፡፡ ኦሮሞ የረገጠውን ምድር ሁሉ ‹‹ወረ-››፣ ‹‹ለገ-››፣ ‹‹ገንደ-››፣ ወዘተ የሚል ‹‹ሰፈር›› ወይም ‹‹ሀገር›› የሚል የኦሮምኛ ትርጓሜ የያዙ ቅጽል ቃሎችን እየለጠፈ ሀገር ምድሩን የመሰየም ባህል አለው፡፡ እና ኋለኛ ኦሮሞዎች የኛ ነው ብለው የሚፎክሩባቸው የብዙዎቹ የኦሮሞ ወራሪዎች የተሠራጩባቸው ሥፍራዎች የኦሮምኛ መጠሪያ ስሞች ወራሪዎቹ በየተላለፉባቸው ቦታዎች ሁሉ እያወጧቸው የሄዷቸው የዳቦ ስሞች ናቸው፡፡
በዚህ ልማዳቸው ከታዩ የኦሮሞዎቹ የ16ኛው ክፍለዘመን ወራሪዎች የረገጡትንና ያስገበሩትን ምድርና ውሃ በራሳቸው የክርስትና ስም ተክተው የቀሩትን የአውሮፓውያንን አሳሾችና ቅኝ ገዢዎች ያስንቋቸዋል ብንል ምንም ማጋነን የለውም፡፡ ይሄን ሥር የሰደደ ልማድ ስናይ ቤተክርስትያናትን በመላዕክታት ስም እየሰየሙ ከማሠራትና፣ የተለያዩ የከበሩ ሥጦታዎች ላይ ስማቸውን ከማስቀረጽ በቀር ከጥንት የኖረን የሥፍራ ሥያሜ በራሳቸው ቃል የመለወጥ ታሪክ ላልነበራቸው ለኢትዮጵያ የሰሜን ነገሥታት ራሱ ለከተሞች አዳዲስ ስም ማውጣት ያስተማሩት እነዚያ የኦሮሞ ወራሪዎች ሳይሆኑ አልቀሩም ያሰኛል፡፡
ይህን ስል ወያኔዎችና ሻዕቢያዎች ተጣምረው የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ከወረሩ በኋላ (ማለትም በድኅረ 1983 ዓ.ም.) ብዙዎቹ ኦነጋውያን ኦሮሞዎች የአማራ ነፍጠኞች በራሳቸው መጠሪያ ቀይረውብናል ብለው የሚፎክሩባቸውን ሥፍራዎች፣ ከተሞችና ተቋማትን በኦሮምኛ ቃላት ከመሰየም አልፈው፣ ሌላ ቀርቶ ለገዛ ልጆቻቸው ራሱ ካለንበት ዘመንና ከባቢ የከተሜ ባህል ጋር አብሮ የማይሄድ የኦሮምኛ ስም መሰየምን ፋሽን አድርገው ይዘውት እንደነበር ስናስታውስ – የታሪክን መደጋገም በጥቂት አብነቶች እንረዳለንና ሳያስገርም አይቀርም፡፡ ዛሬ አዲስ አበባን በስሟ ላይ ስም ደርበው ‹‹ፊንፊኔ›› ብለው የሚጠሩት፣ አሊያም አዲስ አበባ ብለው ላለመጥራት ‹‹ሸገር›› ወዘተ እያሉ በተለያዩ ቅጽል ስሞች ዓለም ያወቃትን አዲስ አበባን የሚጠሩት፣ ወይም የተለያዩ የኦሮምኛ ቃሎችን እየመረጡ የተለያዩ መናፈሻዎችን የመኖሪያ ሳይቶችንና ተቋማትን ለመሰየም እየተሟሟቱ ያሉትን የኦሮሙማ ‹‹የኦሮማይዜሽን›› ሠራዊቶች አጉል ልማድ አስተውለን ስናይ – ምንጩ ያው ነባሩ የኦሮሞ ወራሪዎች አጉል ልማድ መሆኑን ማንም የሚስተውው አይመስለኝም፡፡
ብቻ ጉዱ ብዙ ነው፡፡ ሁሉን ቢናገሩት ፀሐፊን ያታክታል፡፡ አንባቢን ያደክማል፡፡ እንጂ ስለ ወራሪነትና ተወራሪነት ነክ ነገሮች ብዙ የምንናገረው ነበረ፡፡
በመጨረሻ አንድ ሰሞኑን እያነበብኩት ስላለ – እና የቀደምት ጋሎችን (የአሁን ኦሮሞዎችን) ታሪክ አስረግጦ ስለሚናገር የአፍሪካ ታሪክ መጽሐፍ – የተወሰኑ ነገሮች ብዬ ልሰናበት፡፡ ‹‹መስከረም ሲጠባ – አደይ ሲፈነዳ – እንኳን ሰው ዘመዱን – ይጠይቃል ባዳ›› እንዲሉ – እኔም ባዳ ልጠይቅ እንደ ልማዴ ወደ ፀጉረ ልውጥ ደራሲዎች ፊቴን አቀናሁ፡፡ በማርክ ቪሊየርስ እና በሼይላ ኸርትል የተጻፈውን ‹‹INTO AFRICA – A Journey through the Ancient Empires›› የሚል ዳጎስ ያለ መጽሐፍም አገኘሁ፡፡ ባለ በሌለ አቅሜ እየገፋሁት ነው፡፡ ጊዜ ከሚባል ጠላት ጋር እየተጋፋሁ፡፡ ሁለቱም የታወቁ ጥልቅ ተመራማሪዎች ናቸው፡፡ አንደኛው በአፓርታይዷ ደቡብ አፍሪካ ከጥቁሮች በላይ ከነጮች በታች እንደ ሁለተኛ ዜጋ ይቆጠሩ የነበሩት ትውልደ ደቡብ አፍሪካውያን ወይም ‹‹አፍሪካነርስ›› ተወላጅ ነው፡፡ ይሄም በራሱ ደስ የሚል ቅኔ ሆነብኝ፡፡ የዘመኑ አቃፊ-ወራሪዎች እኛን ማድረግ የሚፈልጉት እንደ አፍሪካነሮቹ ሁለተኛ ዜጋ ይመስለኛልና ነው የአንደኛው ደራሲ ማንነት በራሱ ቅኔ የሆነብኝ፡፡
ጣምራ ደራሲዎቹ በራሳቸው ሲቀልዱ እንዲህ ይላሉ፡- ‹‹እኛ ዘር ማንዘራችን እስከ ሰባተኛው ትውልድ ቢቆጠር ከአፍሪካ ምድር የበቀልን ነን ብለን አንዋሽም፣ ስለ አፍሪካ መጠነ ሰፊ ዙረቶችንና ምርምሮችን አካሂደናል፣ የታሪክ ሰነዶችን አገላብጠናል፣ የተወሰነ ነገር እናውቃለን፣ እና ያወቅናትን ትንሽ እውነት እነሆ በረከት ብለናል!››፡፡ ደስ ይላል፡፡ ይህ መጽሐፍ የተጻፈው በፈረንጆች 1997 ላይ ነው፡፡ በቅርብ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በእኛ አቆጣጠር በ1989 ዓመተ ምህረት አካባቢ፡፡ ከሚያውቅ ሰው ጋር ነው መጫወት ብዬ ይኸው አፍሪቃን በአዲስ መልክ እየኮመኮምኩ ነው፡፡
ወደ መሰጠኝ ነገር ስሸጋገር – ፀሐፍቱ ስለ እኛ በሚተርኩበት አንድ ክፍል ላይ የሌላን ከእነርሱ ቀድሞ ስለ አፍሪካ አሰሳው ሁነኛ መጽሐፍ ያሳተመ ደራሲ በመጽሐፉ የጠቀሰውን የዓይን እማኝ ማስታወሻ እንደወረደ ያጣቅሳሉ፡፡ የሚጠቅሱት የዴቪድ ማውንትፊልድን በ1976 እ.ኤ.አ. በሀገር እንግሊዝ የታተመ ‹‹A History of African Exploration›› የሚል መጽሐፍ ነው፡፡ በዚያ መጽሐፍ ላይ ከጂቡቲ ምድር ባቡር ጣቢያ በመነሳት ወደ አዲስ አበባ የተጓዘችን ተጓዥ ቃል ከትቦ ያስቀመጠው መረጃ አለ፡፡ተጓዧ በ1930ዎቹ ላይ ያየችውን ነው፡፡ እንዲህ ይላል፡-
‹‹የኢትዮ-ጂቡቲ ምድር ባቡር የሚጓዘው በቀን ብርሃን ብቻ ነው፣
በማታ አይንቀሳቀስም፣ ለምን እንደሆነ ምክንያቱን ስጠይቃቸው
ለመንገደኞች ደህንነት እንደሆነ የባቡር መንገዱ ባለሥልጣናት
ነገሩኝ፣ ምክንያቱን ሳጣራ ምክንያቱ ጋላዎቹ በየመንገዱ
አሳቻ ሰዓት እየጠበቁ የባቡሩን ሃዲድ በመነቃቀል ለጦር ጫፍ
መሥሪያ እያዋሉት በመሆኑ እንደሆነ ተረዳሁ፣ በጭለማ ስትጓዝ
በማንኛውም ሰዓት ባቡሩ ሊገለበጥና ለአደጋ ልንጋለጥ እንችላለን፣
ስለዚህ ነው የቀኑ ጉዞ ለደህንነታችን ተመራጭ የሆነው…፡፡››
ይህን በመጽሐፍ የታተመ የቆየ የኤቨሊን ዋገ የዓይን እማኝነት ሳነብ የታወሰኝ እኔ በዕድሜዬ የደረስኩበት የ1984-1985ቱ የኦነግ ተመሳሳይ ድርጊት ነው፡፡ ኦነግ ከወያኔ ጋር ውጊያ በገጠመበት ወቅት የኦሮሞ ወጣት ገበሬ ጀሌዎቹን ማንኛውንም የመንግሥት ንብረት እየነቃቀሉ እንዲወስዱ ያበረታታቸው ነበር፡፡ በዚህ ሳቢያ ኦሮሞዎቹ ከአለማያ ይመጣ የነበረውን በፋሺስት ጣሊያን ወራሪዎች አማካይነት ለሐረር ከተማ የመጠጥ ውሃ ማስተላለፊያነት የተሰራውን የውሃ ትቦ በየቦታው እየቆረጡ ይወስዱት ነበር፡፡ ውሃው ለቀናት እንደ ጉድ ሲፈስ የሚቆይበት ጊዜ ነበር፡፡ አንዳንዶቹም ትቦውን ሰብረው ብቻ የጫት እርሻቸውን ያጠጡበት ነበር፡፡ ያሳዝናል፡፡
የአለማያ ሀይቅ የደረቀው በተፈጥሮ ክስተት ብቻ ሳይሆን በእንዲህ ዓይነቶቹ እኩይ ዘረኝነት የወለዳቸው ክፋቶች ጭምር እንደነበር ግልጽ ነው፡፡ የአለማያ ሀይቅ የውሃው መጠን እየቀነሰ ህዝብ የውሃ ያለህ፣ የመፍትሄ ያለህ በሚልበት በዚያ ሰዓት – ጊዜ የሰጣቸው የኦነግ ወራሪዎች – አለማያን ‹‹ዓለም-ማያ›› ብሎ የሰየመው ነፍጠኛው ልዑል ራስ መኮንን ስለሆነ – ‹‹ሀሮማያ›› ብለን እንሰይመዋለን የሚል ግብግብ ላይ ነበሩ፡፡ ከግብግባቸው ሲነቁ – ሀይቁ ደርቋል፡፡ ስሙን ሰየሙ፣ ሀይቁን አደረቁ፡፡ ፋሺስቶች እንኳ ጥሩ ሆነው የሰሩትን የውሃ ማስተላለፊያ፣ በክፋት ከፋሺስቶቹ ከፍተው የተገኙ የኛው የራሳችን የጓዳ ፋሺስቶች እየሰበሩ፣ እየዘረፉ፣ በህዝብ ህልውና ላይ ሲጫወቱ ስናይ ከማሳዘንም በላይ ነበር፡፡ ግን በትክክል የተደረገ፣ የሆነ ታሪክ ነው፡፡
በቅርቡ ታዲያ የእነ ጃዋር ቄሮ ተብዬ የኦሮሙማ ጀሌዎች የአዲሳባን ሕዝብ ለመበቀል የለገዳዲን ውሃ እናቆማለን፣ እንሰብራለን ፉከራቸውን ለተመለከተ ሳይወድ በግድ ብዙ ነገር ማስታወሱ አይቀርም፡፡ በስም እየተመረጠ የእነ እገሌን የነፍጠኞችን ንብረት ዝረፉ፣ ውረሩ፣ ንቀሉ፣ አቃጥሉ፣ ስበሩ፣ ወዘተ የሚሉ የቅርብ ጊዜያችን የሻሸመኔና መሰል የህዝብ ዝርፊያዎች የሚረሱ አይደሉም፡፡ እንዴ! ታሪክ እኮ እኛ ዘንድ ራሱን ይደግማል ብቻ አይደለም መባል ያለበት፡፡ ይደጋግማል እንጂ፡፡ ያውም አስር ጊዜ፡፡ መቶ ጊዜ፡፡ ሺህ ጊዜ ነዋ፡፡ ዘወር ብለን ታሪካችንን እንይ እስቲ፡፡ ከሉባ ቢፎሌ ወራሪዎች እስከ ዘመነ ቄሮ ወራሪዎች የሚሰናሰል እንዲህ የሚገራርም ምስስሎሽ እናገኛለን፡፡ የቦረና ወራሪዎቹ ከኦነጎቹ ወራሪዎች ጋር፣ የኦነጎቹ ጦረኞች ከአሁኖቹ የኦሮሙማ (ቄሮ) ጦረኞች ጋር – ብዙ የሚያመሳስላቸው ነባርና የቀጠለ ተያያዥ ነገር አላቸው፡፡ ከዚህ በላይ ምንም ልል አልችልም፡፡ ዝም ብሎ ብቻ ይገርመኛል፡፡
ሀሳቤንና ዳሰሳዬን ለመደምደም በመጨረሻ የማነሳቸው ሁለት ነጥቦችን ነው፡፡ አንደኛው በኢትዮጵያ ታሪክ ተደጋግሞ እንደታየው የኦሮሞ ወራሪዎች ለወረራቸው አመቺ ጊዜ ሆኖ የሚያገኙት የማዕከላዊውን መንግሥት በጉልበትና በአንድነት ሀገሪቱን ማስተዳደር የማይችልበትን አስከፊ ጊዜውን ጠብቀው መሆኑን (ሀገሪቱ በውስጥም ሆነ በውጭ ወራሪዎች ምክንያት ስትዳከም፣ በሽብር ስትታመስ፣ በጦርነት ስትደቅ፣ በእርስበርስ ክፍፍልና መናቆር ስትማስን – ወረራቸውን የሚያካሂዱት በዚያ የመዳከም ሰዓት እንደሆነ)፡፡
ሁለተኛው ነጥብ ደግሞ በኢትዮጵያ ታሪክ ጸሐፊያን በኩል በዝንጋታም ሆነ በሌላ እንደ ወገን በመቆርቆር ስሜት በበቂ ሁኔታ አትኩሮት ተሰጥቶት ተጽፎበት ያላጋጠመኝ ጉዳይ በተለይ የግራኝ አህመድን ወረራ ተከትሎ ኢትዮጵያን የወረሩት የኦሮሞ ወራሪች አንድም እርስበራሳቸው የተከፋፈሉ በመሆናቸው አንድ ሆነው ሀገሪቱን ሊያስተዳድሩ ባለመቻላቸው፣ ሁለትም የኢትዮጵያን ህዝብ በሙሉ እንደምኞታቸው በኦሮሙማ አምሳል አቅልጠው ቀጥቅጠው ለማስገበር ጉልበቱ ኖሯቸው ባለማወቁ የተነሳ – ከግራኝ አህመድ ቀጥሎ እስከ ዘመነ መሳፍንት ማብቂያ ለቀጠለው የኢትዮጵያ ማዕከላዊ መንግሥት መዳከም፣ እና በጎጥና በጎሳ የተከፋፈለች እርስ በእርስ የምትናቆር ኢትዮጵያ ለመፈጠሯ ትልቁን ድረሻ የተጫወቱት እነዚሁ የኦሮሞ ወራሪዎች መሆናቸው – ከታሪክ ማህደራችን በሚገርም ሁኔታ የተዘነጋ ወሳኝ ታሪካችን ነው፡፡
ይህን ሁለተኛውን ነጥብ በተመለከተ ማርክ ቪሊየርስና ሼይላ ኸርትል በመጽሐፋቸው ቃል በቃል እንዲህ አስቀምጠውት እናገኛለን፡-
“In the aftermath of the Gragne campaigns
the country fell once more into chaos, and
out of the chaos came the Galla, now called
the Oromo., the wild pagans of the south
and southeast. The Galla were never
powerful enough or unified enough to
rule the country, but they helped keep it
in political turmoil for several centuries
thereafter….”
አሁንም የወረራ ታሪካችንን እናጥና፡፡ ታሪክን ማወቅ ሌላውን ወራሪ የሚለው ራሱ ወራሪው መሆኑን በጥቂቱ ለመገንዘብ ያስችላል፡፡ ታሪክን ማወቅ ሚዛናዊነትን ያላብሳል፡፡ ቢያንስ በወራሪነት እርስበርስ ከመካሰስ ያድነናል፡፡ ከምንም በላይ በወራሪነት ጦስ አሁንም ህዝባችን እየከፈለው ያለውን የታሪክ ዕዳ ምንነት ለመረዳት ያስችለናል፡፡ ተወራሪነታችን የፈጠረብንን ሀገራዊ እንከን ማወቅ፣ ዳግም የተቃጣብንን ወረራ ለማክሸፍ መንገዱን አመላካች፣ የመፍትሄውም ጅማሮ ነው፡፡
ከታሪክ መማር ካለብን፣ ታሪክ ምሉዕ ሆኖ እውነት እውነቱ በአደባባይ መነገር፣ መሞገት፣ ለውይይት መቅረብ አለበት፡፡ በአሁን ዘመን ላይ ሆነው ወራሪው ምኒልክ ጡታችንን ቆረጠ እያሉ በውሸት ታሪክ ህዝባችንን በቁሙ የሚያርዱ፣ የሚቆርጡ፣ አካሉን የሚዘለዝሉ፣ የንጹሃን ምስኪን ወገኖቻችንን ህይወት እንደ ዘበት የሚቀጥፉ ብዙዎች በመንግሥት ደረጃ የሐሰት ትርክታቸውን እውነተኛ ታሪክ አስመስለው ኦፌሴላዊ ኃውልት አቁመው፣ በትምህርት ካሪኩለም ቀርጸው፣ ለዳግም ወረራና ጥፋት አቆብቁበው በምንገኝበት በዚህ አስጊ የታሪክ ኩርባ ወይም አደገኛ ምዕራፍ ላይ ሆነን – እውነተኛ ታሪካችንን በትክክል መረዳት – ትልቅ የህልውና ማስጠበቂያ መሠረታችን ነው፡፡ ስላለፈው የማያውቁ የወደፊቱን አያውቁትም፡፡ ከየት እንደመጡ የማያውቁ ወደየት እንደሚሄዱ አያውቁም፡፡
በበኩሌ – ይህን አጥፊ የኦሮሞ ወራሪዎች ታሪክ እንደሆነውና እንደነበረው በሀቅ መዝግቦ ያላካተተ የኢትዮጵያ ታሪክ መቼውኑም ምሉዕ እየተባለ ሊቀጥል እንደማይችል መገንዘቡ – ለጠላትም ለወዳጅም ተገቢ ይመስለኛል፡፡ ታሪክን መድገም ባይቀርልን እንኳ – ቢያንስ ያለፈውን ወደ ውርደት ቁልቁለት የጨመረንን የወረራ ታሪካችንን እንደሆነውና እንደነበረው ጠንቅቀን ማወቃችን – ቢያንስ ከእንግዲህ ወዲያ – ያን የታሪክ ጠንቅ በጣም ብዙ ጊዜ ደጋግመን እንዳንኖረው የሞራልና የህሊና ስንቅ ሆኖ እንደሚያግዘን እምነቴ የፀና ነው፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር፡፡
Filed in: Amharic