>

ከ ‹‹ጥቅስ›› ወደ ‹‹ክስ››፡- የኦሮሞን ሕዝብ ከኦርቶዶክሳዊነት የማስበርገጊያ አዲሱ ስልት (እዉነት ሚድያ አገልግሎት)

ከ ‹‹ጥቅስ›› ወደ ‹‹ክስ››፡- የኦሮሞን ሕዝብ ከኦርቶዶክሳዊነት የማስበርገጊያ አዲሱ ስልት

እዉነት ሚድያ አገልግሎት

ከዚህን በፊት በኦርቶዶክሳውያንና በሌሎች ቤተ እምነቶች መካከል የነበረው ጦርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ተመስርቶ ነበር፤ ዛሬ ላይ ግን ይህ አቅጣጫ በአብዛኛው ወደ ሌላ ተቀይሯል፡- ከመጽሐፋዊ ጥቅስና መሰል ጫናዎች ወደ ፖለቲካዊ (ታሪክ-ነክ) ክስ!
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውነት ሞግተው ማሸነፍ ያቃታቸው አካላት የአገሪቱን ነባራዊ የፖለቲካ አካሄድ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀምና በተሳሳተ መልኩ በመተርጎም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላትን (በተለይም የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን) ከበረታቸው የማስኮብለል ስትራቴጂው ከእውቀት ይልቅ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ሆኗል!
በተለይም ኦሮሞነትንና ኦርቶዶክሳዊነትን እያጋጩ ትውልዱን የሚወዛግቡ፣ የግድ ከሁለቱ ማንነቶች አንዱን እንዲመርጥ በማስገደድ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የሚሞክሩ አሉ!
‹‹መንግሥትን ሊያስደነግጥ ይችላል›› ብለው ባሰቡት አካሄድና የሕዝቡንም ስስ ብልት በመፈለግ አስመስለው በማውራት ቅድስቲቷን ሃይማኖትና ቤተ ክርስቲያን ለማጉደፍ ደፋ ቀና ይላሉ!
የፕሮፌሰርነቱን ጭምብል አጥልቀው፣ በገዛ ዩኒቨርስቲዎቻችን ውስጥ መሽገው፣ በጥናትና ምርምር ስም አስታክከውና ለሀገር ለወገን እንዲሠሩ በተሰጣቸው ምቹ መድረክ ተጠቅመው የተሳሳተ የታሪክ ትርክትና አፍራሽ ፖለቲካ እየዘሩ የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ፣ የሀገሪቱንም አንድነት የሚንዱ ተግባራትን ሲፈጽሙ በቸልታ መታለፍ አልነበረባቸውም!
ኢትዮጵያ ከ80 በላይ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ሀገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ እነዚህ ሁሉ የጋራም ሆነ የተናጠል ታሪክ እንዳላቸው ግልጽ ነው፡፡ በተለይ የኦሮሞ ሕዝብ እንደ ሕዝቡ ብዛት ሁሉ ሰፊ ታሪክና የካበተ ባህል ያለው መሆኑ አጠያያቂ አይደለም፡፡ እንደ አንድ የሀገሪቱ ሕዝብም መልካምም ይሁን መጥፎ ገጽታ ያላቸውን የአገሪቱን ታሪክ ክስተቶች ይጋራል፡፡ በተከሰተው ታሪክ ይጠቀምም፣ ይጎዳም በሂደቱ ውስጥ አልፏል፡፡ ይህንኑ ታሪካዊ ሂደት ታዲያ እያጠኑና እያረቁ ከመሄድ ይልቅ አንዳንዶች ራሳቸው ተሳስተው ሌላውን ለማሳሳት ብዙ ነገር ፈጥረው ሲናገሩ ይደመጣሉ፡፡
የኦሮሞ ሕዝብ መነሻ ታሪኩና ባህላዊ እሴቶቹ ይመሳሰሉ እንጂ በተለያዩ ቤተ እምነቶች ውስጥ መገኘቱ ግን አጠያያቁ አይደለም፤ ‹‹አንድ ሕዝብ›› መሆን ማለት የግድ አንድ ዓይነት አስተሳሰብና እምነት ይኖረዋል ማለት አይደለምና፡፡
ከዚህን በፊት በኦርቶዶክሳውያንና በሌሎች ቤተ እምነቶች መካከል የነበረው ጦርነት በመጽሐፍ ቅዱስ ጥቅሶች ላይ ተመስርቶ ነበር፡፡ ሲከፋ ደግሞ በዛቻና በሰይፍ እስከማስፈራራትም የሚደርስበት ጊዜ ነበር፤ ይኖራልም፡፡ ዛሬ ላይ ግን ይህ አቅጣጫ በአብዛኛው ወደ ሌላ ተቀይሯል፡- ከመጽሐፋዊ ጥቅስና መሰል ጫናዎች ወደ ፖለቲካዊ (ታሪክ-ነክ) ክስ!
1. የማስበርገግያ ስልቱን መቀየር የቀየሩበት ምክንያት
———————————————–
የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍሎችን (ጥቅሶችን) በማጣቀስ መከራከር እና ስለ ሃይማኖታቸው በቂ ግንዛቤ ያልነበራቸውን ምዕመናን የመንጠቅ አካሄድ በአብዛኛው በፕሮቴስታንቶች ዘንድ ይዘወተር የነበረ አካሄድ ነው፡፡ በእርግጥም የሚያነሱአቸው ነጥቦች ምንም ይሁኑ ምንም፣ የሚቀበሏቸውም አምነው ይሁን ሳያውቁ ብቻ ዋናው ነገር ትግሉ ‹‹መጽሐፍ ተኮር›› መሆኑ የሥልጣኔ መንገድ ያሰኛል፤ በሠለጠነ አካሄድ፣ በመረጃ ዘመን ውጊያውን በመረጃ ለማድረግ ሞክረዋልና፡፡
ከሃይማኖታዊ ጉዳዮች ጋር የተያያዙ እነዚህ ጥያቄዎች በቀደሙት የፕሮቴስታንቲዝም ክስተት ጊዜያት በአገሪቱ በአጠቃላይ (በተለይ ደግሞ ስለ ሃይማኖታቸው በቂ ግንዛቤ በሌላቸው የኦሮምያን ክልል ምዕመናን በመሰሉት ዘንድ) ጠንከር ብለው ይቀርቡ የነበሩ፣ ከዚያ መነሻ የተነሣም በብዙዎች የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አካላት ዘንድ ‹አሳሳቢ› የሚመስሉ፣ ነገር ግን በአሁኑ ጊዜ ጨርሶ ባይጠፉም ብዙም አንገብጋቢና አሳሳቢ ሊባሉ የማይችሉ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ቤተ ክርስቲያንም ቢሆን በቂ ባይባልም የተሻሉ ሥራዎችን የጀመረችው ይኽንኑ ችግር ከመቅረፍ አንጻር ስለነበር ነው፡፡ የሚጠየቁትን ጥያቄዎችና የቤተ ክርስቲያንን ምላሽ መዘርዘር ግን የዚህ ጽሑፍ ትኩረት አይደለም፡፡
አሁን ኦርቶዶክሳውያኑ ክርስቲያኖች ወደ ቤተ ክርስቲያን መቅረብ፣ ማንበብ፣ ወደ መምህራንንም ቀርበው ለጥያቄዎቻቸው በቂ ምላሽ ማግኘትና መገንዘብ ጀምረዋል፤ በመጽሐፋዊ ግንዛቤም ከእነርሱ በብዙ እጥፍ ተሽለው ተገኝተዋል፡፡ በአንጻሩ እነርሱ ደግሞ ሚዛን የሚደፋ አሳብ፣ የሚያሳምንም ሃይማኖታዊ አመክንዮ አጥተዋል፡፡ እናም የንግዱ ትርፍ ብዙም እንዳላዋጣቸው ስላወቁ አዲስ ስልት መቀየስ አስፈለጋቸው፤ የውጊያ ስልቱን ከመጽሐፋዊ ግንዛቤ እነርሱ ወደማይሰማሩበት የፖለቲካ ሜዳ ማዞር፡፡
በመጽሐፍ ቅዱስ መሠረታዊ እውነት ሞግተው ማሸነፍ ያቃታቸው አካላት የአገሪቱን ነባራዊ የፖለቲካ አካሄድ እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀምና በተሳሳተ መልኩ በመተርጎም የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አባላትን (በተለይም የኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎችን) ከበረታቸው ለማስኮብለል አዲስ ስልት ቀይሰው በመንቀሳቀስ ላይ ናቸው፤ የማሸነፍያ መሣርያውም ከእውቀት ይልቅ የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ሆኗል፡፡
አሉባልተኞቹ የሐሰት ትርክትንና የውንጀላ ክሶችን ኦሮሞን ከኦርቶዶክሳዊነቱ ለማንሸራተት በዋና ስልትነት የሚጠቀሙበት ቁልፍ ምክንያት በተቻለ መጠን ሰዎች ይህቺን ሃይማኖት ‹‹በርቀት›› እንዲሸሹአት ለማድረግ ነው፤ ቀርበው ያዩአት እንደሆነ እውነታውን ስለሚረዱ ዒላማቸው ከግብ እንደማይደረስ ይፈራሉና፡፡ እናም ትልቁ ጥረታቸው ኦርቶዶክሳውያኑ ቀርበውና ወደ ውስጥ ገብተው መጻሕፍትን እየመረመሩ እንዳይረዱ ማድረግ ነው፡፡
2. በ ‹‹ምሁራዊ ጥናትና ምርምር›› ስም የሚሠሩ ትንኮሳዎች
———————————————————
አዲሱ የጦርነት ስልት ፊት ለፊት ከሃይማኖት ተቋማትና አማኞቻቸው ጋር፣ ያውም የሃይማኖት መጻሕፍቱን መሠረት አድርጎ የሚካሄድ አይደለም፡፡ ይልቁንም በግልም ሆነ በቡድን ሆኖ የፖለቲካ ‹‹ታሪክ›› ድርሰቶችን በተንሻፈፈ አረዳድ እየበረዙ በሕዝብ ሚዲያዎች ላይ ቀርቦ መደስኮር፣ በመጻሕፍት መልክ መጻፍና በጥናትና ምርምር መጽሔቶች ላይ ‹‹ምሁራዊ ትንታኔዎችን›› እያቀረቡ ማሠራጨት ነው፡፡
ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶችም ሐሰቱን እውነት እያስመሰሉ በተለያዩ ማኅበራዊ ሚዲያዎች ሲያራግቡ፣ በመጽሔትና መጻሕፍት መልክ እያሳተሙ ሲያሰራጩ፣ በተለቪዥን መስኮቶችም ብቅ እያሉ ሲወራጩ ቆይተዋል፡፡ ነገሩንም ከሀገራዊ አድማሱ አሻግረው ‹‹ዓለም አቀፋዊ›› ለማድረግ “International Journal of Oromo Studies” የሚል መጽሔት ላይ ‹‹የጥናትና ምርምር ውጤቶች›› በሚል የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ስም የሚያጠለሹ የውንጀላ ጽሑፎችን ለትውልዱ አስተላልፈዋል፡፡ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ደግሞ ይህንኑ መጽሔት በኦሮምያ ክልል ውስጥ ከሚገኙ አንዳንድ የሀገሪቱ ዩኒቨርስቲዎች ጋር በመመሳጠር በሀገር ውስጥ ጭምር ማሳተምና ማሠራጨት ጀምረዋል፡፡
መሰል የጥላቻ ፖለቲካና የዘረኝነት አመለካከቶችን እየፈበረኩ የትውልዱን ንጹህ አእምሮ የሚበርዙት ደግሞ ‹‹ምሁራን›› የሚባሉቱ መሆኑ ይበልጥ አሳሳች፣ አሳዛኝም ጭምር ነው፡፡ ምንም እንኳን ዱላው የተቃጣው በዋናነት በኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሳዊነት ላይ ቢሆንም ጦሱ ግን ለሁሉም እንደሚተርፍ መዘንጋት አልነበረበትም፡፡ የፕሮፌሰርነቱን ጭምብል አጥልቀው፣ በገዛ ዩኒቨርስቲዎቻችን ውስጥ መሽገው፣ በጥናትና ምርምር ስም አስታክከውና ለሀገር ለወገን እንዲሠሩ በተሰጣቸው ምቹ መድረክ ተጠቅመው የሕዝቡን ሰላም የሚያደፈርሱ፣ የሀገሪቱንም አንድነት የሚንዱ ተግባራትን ሲፈጽሙ በቸልታ መታለፍ አልነበረባቸውም፡፡
3. የማስበርገግያ ክሶቹ ዋና ዋና ጭብጦች
————————————–
ኦርቶዶክሳውያን የኦሮሞ ልጆችን ከእምነታቸው ለማስኮብለል የሚያደቡ አካላት ብዙ ነገር ፈጥረው ይናገራሉ፤ በዚህች ጽሑፍ ዘርዝሮ መዝለቅም የሚሞከር አይደለም፡፡ ነገር ግን በተለይ የኦሮሞ ‹‹ምሁራን›› ከሚባሉት አካላት በኦርቶዶክሳዊነት ላይ ከሚሰነዘሩ የማስበርገጊያ የክስ ጭብጦች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ቀንጭበን ለማሳየት ያህል፡- ((ለእያንዳንዱ ክስና ውንጀላ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮና የታሪክ ምላሽ በሌሎች ጽሑፎቻችን በስፋት እንመለስበታለን))
• ኦርቶዶክሳዊነት አንድ ግለሰብ አመዛዝኖ በመወሰን የሚመርጠው መንገድ ሲሆን ኦሮሞ ሆኖ መወለድ ግን የማይመርጡት የተፈጥሮ ጉዳይ ሆኖ ሳለ ኦሮሞነትን ከኦርቶዶክሳዊነት በማጋጨት እንዲሁም ትውልዱን የግድ ከሁለቱ እንዲመርጥ በማስገደድ የፖለቲካ ትርፍ ለማጋበስ የሚሞክሩ አሉ፡፡
• የአገሪቱም ሆነ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ሁሉ ተረት ተረት እንደሆነ ደጋግሞ በማስወራት ‹‹ኦሮሞን ማእከል ያደረገ አዲስ ታሪክ መጻፍ አለበት›› ሲሉ ይደሰኩራሉ፡፡ ይህንኑም ‹‹አዲስ ታሪክ›› በራሳቸው ፍላጎትና ስሜት መሠረት ለመጻፍ ይፈልጋሉ፤ ‹‹ታሪክ›› ባይሆኑም ይህንን ርዕስ ይዘው የተሠራጩ የፕሮፖጋንዳ ጥንቅሮቻቸውም አሉ፡፡
• ‹‹የኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የሀገሪቱን ነገሥታት ቀብታ እያነገሠች፣ ከእነርሱም ጋር ተጣብቃ፣ መሣርያቸውም በመሆንና ሁኔታዎችንም እያመቻቸችላቸው የኦሮሞን ሕዝብ ስትጨቁን ኖራለች፤ እነርሱ በኦሮሞ ሕዝብ ላይ ሲዘምቱም እንኳንስ ልትቃወማቸው ታቦት ይዛ እየባረከች ተከትላቸዋለች›› የሚል ክስ ያዘወትራሉ፡፡
• ይልቁንም በሕወሓትና ጽንፈኛ የኦሮሞ ፖለቲከኞች የፈጠራ ትርክት መሠረት አጼ ምኒልክ በአርሲ (አኖሌ) እና በሐረርጌ (ጨለንቆ) ኦሮሞን ጨፍጭፈው ኦርቶዶክስን እንዳስፋፉ፣ ኦርቶዶክስም ‹‹የምኒልክ ሃይማኖት›› እንጂ የኦሮሞ እንዳልሆነች ከፍተኛ የፖለቲካ ፕሮፖጋዳ በመንዛት የትውልዱ አእምሮ በጥላቻ እንዲበረዝ አድርገዋል፡፡
• ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቱ እስካሁንም ድረስ የምኒልክን ባንዲራ እንደ ‹ንዋይ ቅዱስ› ቆጥራና አክብራ መያዟ የነፍጠኛውን ፖለቲካ ሥርዓት እንደምትናፍቅ ማሳያ ነው›› ይላሉ፡፡
• ‹‹የኦሮሞ ምንጩ ኩሽ እንጂ ሴማዊ ስላልሆነ ከሰሜን ኢትዮጵያ ሕዝቦች ጋር በሃይማኖትም ሆነ በባህል ምንም ቁርኝት/አንድነት ሊኖረው አይገባም›› ባይ ናቸው፡፡
• እናም ‹‹ኦሮሞ የሰሜናውያንን ሃይማኖትና የነፍጠኞቹን ሥርዓት ትቶ ከኦርቶዶክስ መውጣት፣ ወደ ጥንት እምነቱ ‹ዋቄፋና› መመለስ አለበት›› የሚል አቋም አላቸው፡፡
• ይኸው ‹‹ዋቄፋና›› ከክርስትናው እንደሚቀድም (በዕድሜ እንደሚቀድመው)፣ መነሻም እንደሆነው፣ ዛሬ በክርስትናው ውስጥ ያሉት መልካም እሴቶችም ከዋቄፋና የተወሰዱ አሻራዎች እንደሆኑ መጻፍ ጀምረዋል፡፡
• ‹‹ክርስትና የኦሮሞ አይደለም፤ ኦርቶዶክሶች በኦሮሞ ላይ ውኃ እየረጩ አማራ አደረጓቸው እንጂ›› ብለው በተለቪዥን ላይ ወጥተው በግልጽ ለሕዝብ እስከማወጅ ተዳፍረዋል፡፡
• ከዚህ በታች የተጠቀሱትን ነጥቦችም በመዘርዘር ኦርቶዶክስ የኦሮሞን ማንነት የሚያጠፋ ሃይማኖት እንደሆነ እየደሰኮሩ ነው፡-
‹‹በኦርቶዶክስ መስፋፋት ምክንያት የኦሮሞ ባህል ተንቋል፡- አልባሳቱ አይለበሱም፣ አመጋገቦቹ በአጽዋማት ምክንያት ተወግዘዋል፣ ጨሌውም በባዕድ አምልኮነት ተፈርጇል፡፡››
በአፋን ኦሮሞ ሃይማኖታዊ ይዘቶችን መጻፍ፣ መስበክና ማገልገል እንደተከለከለ ያስወራሉ፡፡
‹‹ኦሮሞ በጥንት እምነቱ ጥላ ሥር ተሰብስቦ ለነጻነቱና ለመብቱ በአንድነት መቆም አለበት፡፡››
‹‹በኦሮምያ ክልል ውስጥ ያሉት በርካታ ቦታዎች ስሞቻቸው ወደ ‹ባዕዳን› ቋንቋ ተቀይሯል፤ ይህ ደግሞ የኦሮሞን ማንነት ለማጥፋት የተደረገ ሤራ ነው፡፡››
‹‹የክርስትና ስም የሚባለው እምነትን የሚያመለክት ሣይሆን ኦሮሞን ወደ ትግሬነት ለመቀየር የታሰበ የፖለቲካ አካሄድ ነው፡፡››
• ‹‹ቤተ ክርስቲያኒቱ ኦሮሞን የሚሳደቡ መጻሕፍትን አሳትማ አሠራጭታለች›› በሚል በሕጋዊ መዋቅሯ ያልታወቁ፣ በመሠረታዊ አስተምህሮዋ ያልተደገፉ፣ በአንድ ወቅት ግለሰቦች የግል ስሜታቸውን ያንጸባረቁባቸው፣ ዛሬ ግን በተጨባጭ በቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ላይ የሌሉትን ጽሑፎችን (እንደ 1960 ዓ.ም ‹‹ራእየ ማርያም›› ያሉትን) በማሳያነት ያቀርባሉ፡፡
• በሌላ መልኩ ደግሞ መልካም መስለው የታዩአቸውን አስተሳሰቦች፣ እሴቶችና ድርጊቶች ሁሉ ‹‹ድሮ የኦሮሞ ነበሩ›› ብለው ለመውሰድ ሲሯሯጡ፣ በአንጻሩ የሚያስነቅፉትን ነገሮች ሁሉ ደግሞ ‹‹ሌላው ሕዝብ በቅርቡ የጫነበት እንጂ ኦሮሞ ጥንቱን እንዲህ ዓይነት ልማድ አልነበረውም›› በማለት ከደሙ ነጻ ሊያደርጉት ሲጥሩ ይስተዋላሉ፡፡
በአጠቃላይ እነዚህን ሁሉ የፈጠራ ክሶችና አዳዲስ የማንሸራተቻ ስልቶችን የሚጠቀሙት ለጊዜያዊ ጥቅም የተባበሩት አጽራረ ኦርቶዶክሳውያን (የዘመነኛ ፕሮቴስታንታውን፣ የአክራሪ ሙስሊሞችና የጽንፈኛ ኦሮሞ ፖለቲከኞች) ሁሉ ናቸው፡፡ ‹‹የጋራ አቋም መግለጫ›› እስኪመስል ድረስ ሲያሻቸው ማንነትን እና ሃይማኖትን በማገናኘት፣ ሲያሻቸው ደግሞ ሁለቱን በመለያየት ኦርቶዶክሳውያኑን የብሔሩ ተወላጆችን ከሃይማኖታቸው ለመነጠል በይፋና በጋራ ይረባረባሉ፡- ከነጠሉት በኋላ ግን ‹‹የምርኮኛ ክፍፍል›› ላይ በስውር መነታረካቸው አልቀረም፡፡
አሁን አሁን ‹‹ሃይማኖታዊ ጥያቄዎች›› መስለው በውስጥም ሆነ በውጭ ካሉት አካላት በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ የሚሰነዘሩት እነዚህ ጥያቄዎችና ክሶችም በሁለት መንገድ የሚታዩ ናቸው፡- በአንድ በኩል የብሔረሰቡ ተወላጅ የሆኑ ምዕመናን በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነው ስለሃይማኖታቸው ጠለቅ ያለ ግንዛቤ ለማግኘት ሲሉ (ከልባቸው ለማወቅ/ለመዳን ዓላማ) በቀናነት የሚጠይቁት ሲሆን በሌላ መልኩ ደግሞ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኒቱ ተቃዋሚ አካላት እነዚህኑ ምዕመናን ከበረታቸው ለማስበርገግ (ለአባግዕ ሥርቆት ዓላማ ሲሉ) ጉዳዮቹን ፖለቲካዊ ቅርጽ እያስያዙ፣ የተቆርቋሪነትን ቅላጼ እያላበሱ የሚልኳቸው ናቸው፡፡ በሁለቱም መንገድ ቢጠየቅ የሚሰጠው ምላሽ ግን በተጠናና ዘመኑን በዋጀ መልኩ መሆን እንዳለበት አያጠያይቅም፡- የራስን በድኅነት መሥመር ላይ ለማቆየት፣ ሌሎችንም በቅንነት መንፈስ ከስህተት መንገድ ለመመለስ፡፡
4. እነዚህ የሐሰት ትርክቶችና የውንጀላ ክሶች ምን አስከተሉ?
——————————————————-
ከእነዚህ አካላት ‹‹ሃይማኖተኞች ነን›› የሚሉቱ በእምነታቸው ጥንካሬ በሚያምኑት አምላክ ከመታመን ይልቅ በምድራዊ የሐሰት ፕሮፖጋንዳና የከሰረ ፖለቲካ አካሄድ አንዲት የሆነችውን ጉባኤ ምዕመናን ለመከፋፈል ሲሯሯጡ ቅንጣት ታህል እንኳን ኀፍረት አልተሰማቸውም፡፡ በፖለቲካው ዘርፍ ላይ ያሉቱም በርዕዮተ ዓለም ጥበባቸው የሀሳብ ልዕልና አግኝተው ዜጎችን ወደራሳቸው መማረክ አልተቻላቸውም፡፡ እናም ሁሉም ‹‹መንግሥትን ሊያስደነግጥ ይችላል›› በሚመስላቸው አካሄድና የሕዝቡንም ስስ ብልት በመፈለግ አስመስለው በማውራት ቅድስቲቷን ሃይማኖትና ቤተ ክርስቲያን ለማጉደፍ ደፋ ቀና ይላሉ፡፡ በዚህም ለጊዜው የጠበቁትን ያህል ባይሆንም ተሳክቶላቸዋል ማለት ይቻላል፡፡ በዋናነት፡-
አስቀድመው የተጠቀሱትንና መሰል የፖለቲካ ፕሮፖጋዳዎችን እያቀናበሩ መንዛት ትውልዱ ኦርቶዶክስና ኦርቶዶክሳዊነትን ከሩቁ እንዲሸሽ፣ በኦርቶዶክሳውያን ላይም መፈናቀልና ግድያ እንዲደርስ፣ የአብያተ ክርስቲያናት ቃጠሎና ንዋያት ቅድሳት ዝርፍያ እንዲባባስ ከፍተኛ መንሥኤ መሆኑን ማንም የሚረዳው ነው፡፡
በርካታ ኦሮሞ ኦርቶዶክሳውያን በአፍ የተነገሩ፣ በመጽሐፍ የሰፈሩ ትርክቶች ሁሉ ተደጋግመው ከመነገራቸው የተነሣ እውነት ስለመሰላቸው፤ የአንዳንድ ግለሰቦች ድርጊትም እንደ ተቋማዊ አቋም ስለተቆጠረ፤ በአንጻሩ ቤተ ክርስቲያናቸው ደግሞ በቂና ብቁ ምላሽ በተገቢው ጊዜ ባለመስጠቷ የተነሣ ሃይማኖታቸውን ጥለው ለመኮብለል ተገደዋል፡፡
ከእነዚህ ሁሉ የኦርቶዶክሳዊነት ጠላቶች የዘመናት ጥፋት ጥረቶች የተነሣ የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት ተፈትኗል፡- በክልላዊ ቤተ ክህነቶች ውጥንና በቅብዓት ኑፋቄ እንቅስቃሴዎች አማካይነት የሕወሓትን ‹‹የኦርቶዶክስን አከርካሪዋን እንሰብራለን›› መፈክር እውን ለማድረግ እየተሞከረ ነው፡፡
በጣም የሚያሳዝነው እነዚህን ችግሮች ለመቅረፍ እሰራለሁ የሚለው ‹‹የኦሮምያ ቤተ ክህነት›› እንኳን ክሶቹ (ትርክቶቹ) ትክክል መሆናቸውን ይቀበላል፤ እንደ አንድ የቤተ ክርስቲያኒቱ አካል ትክክለኛውን ኦርቶዶክሳዊ አቋም እያንጸባረቀ ትውልዱን ከስህተት ከመታደግ ይልቅ ከጠላት ጋር ተባብሮ ኦርቶዶክስን በማጥላላት ላይ ይገኛል፤ ጥያቄው ‹‹የአገልግሎት መዋቅር›› ይምሰል እንጂ ድርጊቱ ሁሉ የሚመሰክረው የፖለቲካ ተልእኮ መሆኑም ግልጽ ሆኗል፡፡
ሲጠቃለል፡- በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ ሰዎች የዘመናችንን የአካሄድ አቅጣጫና የፖለቲካውን ትኩሳት በመጠቀም በተለይም የኦሮሞን ሕዝብ ከወገኑ፣ ከሃይማኖቱና ከአገሩ ለመነጠል ሳይታክቱ መሯሯጣቸው የሚያሳዝን ነው፡፡ ብሔረሰቡ ግን የተማሩና እውነተኛውንም ታሪክ የሚመረምሩ፣ እውነቱን ከሐሰቱ ለመለየት የሚችሉ ምሁራን ስላሉት ለጊዜው እንጂ በማስመሰል አካሄድ ረጅም ርቀት የሚሄድላቸው አይሆንም፡፡ ታሪክን በማጣመም ተርጉሞ ውኃ የማያነሣ ፕሮፖጋንዳ መንዛትም ለጊዜው ውዥንብር ይነዛ፣ ብዥታም ይፈጥር ይሆናል እንጂ ብዙ አያራምድም፡፡ ያለው እውነት አንድና አንድ ብቻ ሆኖ ሳለ በ ‹‹ታሪክ›› ስም ወሬና አሉባልታ የሞላባቸውን ጽሑፎች ማሠራጨት እየተለመደ መምጣቱ የሚያሳዝን ነው፡፡
ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያንን ወሬና አሉባልታ የሚንዳት ቢሆን ኖሮ ግን ብዙ ሺህ ዓመታትን ተሻግራ ላለንበት ዘመን ባልደረሰች ነበር፡፡ መሥራቿ ክርስቶስ ራሱ ‹‹እውነት›› ነውና ጥንቱን በእውነት ላይ ተመሥርታ እውነትን ስትመሰክር ኖራለች፤ ዛሬም ያንኑ እውነት ሳትቀንስ ሳትጨምር ትመሰክራለች፤ ነገም እስከ ዓለም ፍጻሜ እንዲሁ እውነትን ይዛ ትዘልቃለች፡፡ በሐሰት የሚከሷትና የሚቃወሟት ሁሉ አልፈዋል (ጠፍተዋል)፤ እርስዋ ግን እስከዛሬ አለች፣ ትኖራለችም፡፡
Filed in: Amharic