>
5:28 pm - Friday October 10, 5890

ሐረር የጉድ ሀገር . . . ! ! !    ከጄነራል አሊ እስከ ዳግማዊ አል ነጃሺ! (አሰፋ ሀይሉ)


ሐረር የጉድ ሀገር . . . ! ! ! 

ከጄነራል አሊ እስከ ዳግማዊ አል ነጃሺ!

አሰፋ ሀይሉ

የነበሩት ሲናገሩ የብዙዎቹ ያስደምም ነበረ፡፡ ስለ ሐረር የሚናገሩት፡፡ ለምሳሌ የጥንቱን ፈረንሣዊ ገጣሚ የራምቦድ የህይወት ታሪክና ማስታወሻዎች አንብቤያለሁ፡፡ የመንግሥቱ ለማን እና የአባቱን የአብዬ ለማን የህይወት ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ የገብረክርስቶስ ደስታን የህይወት ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ የልዑል ራስ እምሩ ኃይለሥላሴን የሕይወት ታሪክ አንብቤያለሁ፡፡ የደጃዝማች ታከለ ወልደኃዋርያትን፣ እና የጃንሆይ ተፈሪ መኮንንን የሕይወት ታሪኮች አንብቤያለሁ፡፡ እና ሐረርን በውል የሚያውቋት፣ ምድሯን የረገጧትን፣ በተድላም በሀዘንም የተመላለሱባትን የብዙ ፀሐፊያንንና ሠዓሊያንን ትርክቶችና የጉዞ ማስታወሻዎች አንብቤያለሁ፡፡
ኢጣልያኖች ሐረርን በወረሩና ብዙ ግንባታዎችን ባካሄዱበት የኢጣልያ ወረራ ዘመን የሐረር ዋና አስተዳዳሪ የነበረው ጣልያናዊ ሹምን የግል ማስታወሻዎችና ካርታዎችም እንደመታደል ሆኖ አግኝቼ አንባብቤያለሁ፡፡ ቀደምት የካቶሊክ ሚሲዮናውያን ስለ ሐረር በፎቶ እያስደገፉ የጻፏቸውን ማስታወሻዎችም አግኝቼ ተመልክቼያቸዋለሁ፡፡ ሁሉም በሚባል ደረጃ – የድሮዋን ከወታደራዊው መንግሥት በፊት የነበረችዋን ሐረርን ሲገልጹ – ፍፁም እንግዳ ተቀባይ፣ ፍፁም ሁሉም ተስማምቶ የሚኖርባት፣ ማንም ከማንም ሳይመረጥ የረገጣት ሁሉ ቤተኛዋ ተደርጎ በፍቅር ሰምጦ የሚቀርባት፣ ሥጋው የሚቆረጥባት፣ አትክልቱና ፍራፍሬው የተትረፈረፈባት፣ ጫቱ የሚብለጨለጭባት፣ ቆነጃጅቷ በውበት የተምነሸነሹባትን ሐረርን ነው ነግረውን ያለፉት፡፡
በሐረር ኖረው ያለፉ አንዳቸውም በሐረር ውስጥ የዚህ ዘር የበላይነት ነበረ፣ ወይም የዚህ ዘር በተለየ ተጨፍልቆና ተጨቁኖ እየኖረ ነው፣ ወይም የዚህ ዘር ነውረኝነት፣ የዚያ ዘር ሸረኝነት፣ የዚህ ዘር ምናምንነት…. ወዘተ ብለው አንድም ዘረኝነት የተቀላቀለበት ነገር ስለሐረር ገልጸው አያውቁም፡፡ ሁሉም ሐረር የትንሽ ትልቁ፣ የእንግዳው የነባሩ፣ ሁሉም የሚኖርባት መስህብ ያላት፣ በሰዎች ማህበራዊ ህይወት መስተጋብር የደመቀች ከተማ መሆኗን፣ የፍቅር ከተማ መሆኗን፣ የአትክልትና የፍራፍሬ ምድር መሆኗን፣ ሰዉ ነፃ፣ ምድሯ ነፃ መሆኑን ነው የሚናገሩት፡፡ እንዲያውም ፈረንሣዊው ገጣሚ አርተር ራምቦድ ሰው ከጉንዳን፣ ከጊንጥ፣ ከጅብና ከአሞሮች ጋር በሠላም አንድ ላይ ተኝቶ እንደሚያድር በሚያስደምም አገላለጽ እየተቀኘ ነው ያሰፈረው፡፡
በመንግሥቱ ኃይለማርያም ዘመን የነበረችው ሐረር ደግሞ እኔና ታላላቆቼ በአካል የምናውቃት ሐረር ነበረችና መመስከር እንችላለን፡፡ ወያኔዎች ሐረርን ከመርገጣቸው በፊት – አደሬ፣ አማራ፣ ትግሬ፣ ኦሮሞ፣ ከምባታ፣ ወላይታ፣ ጉራጌ፣ ስልጤ፣ ኮንሶ፣ አርጎባ፣ ሱማሌ ኢሳ፣ ምናምን የሚባል የዘር ክፍፍልም፣ የዘር መጠቋቆምም፣ የዘር መቆጣጠርም አልነበረም፡፡ በሚገርም ሁኔታ በህብረተሰብ ትምህርት የመጀመሪያ ደረጃ መማርያ መጽሐፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመሪያ ጊዜ የአደሬን ሴት ከነባህላዊ አልባሷ እንደ አንድ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ እውቅና ሰጥቶ ምስሏን ያወጣው የመንግሥቱ ኃይለማርያም ወታደራዊው መንግሥት ነበረ፡፡
ሌላ ቀርቶ የቀበሌዎቹን ስም እንኳ ሳይቀር አንድም ነገር ሳይነካ እንደ ጥንቱ ነበር የቀጠለው፡፡ እኔ ራሴ ያደኩበት ቀበሌ ‹‹አደሬ ጢቆ›› ነበር የሚባለው፡፡ ‹‹እስላም›› የሚለው ቃል በብዙዎች አንደበት አሉታዊ ትርጓሜ በሚያቃጭልበት ዘመን በሐረር ከተማ ውስጥ የገዛ እናቴ ከ13 ዓመታት በላይ ያስተማረችበት ‹‹እስላም ትምህርት ቤት›› የሚባል ትምህርት ቤት ነበር፡፡ ሌላ ስሙ ልክ እንደ ጥንቱ ‹‹መድረሳ›› ይባላል፡፡ የሐረር ትልልቅ መስጊዶች ግንባታ የተከናወነው በዚያው በወታደራዊው መንግሥት ዘመን ነበር፡፡
አንድ እጅግ የማይረሳኝን ገጠመኝ ልናገር፡፡ የሐረሩን ቅድስት ሥላሴ ቤተክርስትያን ተጎራብቼ የልጅነት ዕድሜዬን ሳሳልፍ – አሁን ፀረ-ሐይማኖት እየተባለ ያልነበረ ትርክት የተፈጠረለት ወታደራዊው መንግሥት አንድም ቀን ቅዳሴ አስተጓጉሎ፣ አንድም ቀን ዩኒፎርም የለበሰ ወታደር የመካነ ሥላሴን ቅጥር ግቢ ረግጦት፣ አንድም ቀን ፀረ-ክርስትና ተግባር ፈጽሞበት አያውቅም፡፡ ብዙዎቹ የሐረር ከተማ ቤተክርስትያኖች – መድሃኔዓለም፣ ተክለሐይማኖት፣ ሚካኤል፣ ጊዮርጊስ፣ ሥላሴ – ብዙ አሰርት ዓመታትን ያስቆጠሩና በተለይ የተክለሐይማኖትና የሥላሴ ቤተመቅደሶች በጥንታዊ የጎቲክ አርኪቴክቸር የተዋቡ ስነህንጻዎችም እንደመሆናቸው – እንደ ታሪካዊ ቅርስ ነበር የሚታዩት፡፡ ሐረርን የረገጠ ቱሪስት ሁሉ ጥንታዊዎቹን የአቦከርና ሌሎችም መስጊዶች በጎበኘበት እግሩ፣ እነዚያንም ቤተክርስትያናት በነጻነት ይጎበኝ ነበር፡፡ ጎረቤቶቼና ቤተሰቦቻቸውም አብሮአደጎቼ የሆኑት የሐረሩ ሥላሴ ጳጳስ አቡነ መልዓከ ሠላም ራሳቸው የሰንበት ትምህርትን ሲያሰኛቸው በኦሮምኛ፣ ሲያሰኛቸው በአማርኛ፣ ሲያሰኛቸው በግዕዝ እያጣቀሱ የሚናገሩ አንደበተ ርቱዕ አስተዳዳሪ ነበሩ፡፡ የምናገረው ነገር በወታደራዊው መንግሥት ዘመን በዓይኔ ያየሁትንና የኖርኩበትን እውነት ነው፡፡
ደጋግሜ እንዳልኩት ሐረር የፍቅር ከተማ ነበረች፡፡ የዘር ክፍፍልና ጎጠኝነት አልነበረም፡፡ ገርል ፍሬንድ ልትጠብስ ስትለ አደሬ ናት፣ ሶማሌ ናት፣ ኦሮሞ ናት፣ አማራ ናት የሚል ሳይንስ ሐረር ውስጥ አይታወቅም ነበር፡፡ የሚገርም ይመስላል፡፡ ሐይማኖት በፍቅር ድል የተመታበት ወርቃማ ዘመን ነበረ፡፡ ብዙዎቹ አደሬዎች ከሶማሌና ከኦሮሞ ጋር ወርቅ አድርገው ተጋብተዋል፡፡ ብዙው ኦሮሞ ከሌላው ሕዝብ ጋር ተጋብቶ ተዋልዷል፡፡ ትግሬው፣ ወላይታው፣ ጎጃሜው፣ ጎንደሬው፣ ወሎዬው፣ ጉራጌው… ሁሉም አብሮ ተዋዶ ተከባብሮም ተፈቃቅሮም ተቀላቅሎም ነበረ በሐረር ቀኑብሽ የሆነች ጣፋጭ ኑሮውን የሚመራው፡፡
የአደሬ አገዛዝ፣ የኦሮሞ አገዛዝ፣ የነፍጠኛ አገዛዝ፣ ምናምን የሚባሉ ለምላስም ለጆሮም የሚያቅለሸልሹ የክፍፍልና የጥላቻ፣ የበላይነትና የበታችነት ትረካዎችና ወሬዎች በሐረር ምድር የተጀመሩትም፣ የታወቁትም ወያኔዎቹ የሐረርን ምድር ከረገጡ በኋላ ነው፡፡ ከዚያ በፊት በሐረር አየር ላይ የማንጎ፣ የብርቱካን፣ የሙዝ፣ የለውዝ፣ የጂልቦ፣ የቁርቁራ፣ የወይን፣ የጊሽጣ፣ የአቡካ፣ የኮክ፣ የዋንዛ፣ የሾላ፣ የቴምር፣ እና የሌሎች ፍራፍሬዎች ዘር እንጂ… የሰው ዘር ልክፍት ተዘርቶም፣ በቅሎም አያውቅም ነበረ፡፡ ከየትኛውም ዘር የሚወለድ ማንም ሰው ሐረር ላይ በመምጣቱ የተነሳ በጀጎል ውስጥ የነበሩ አደሬዎችን ቢዝነስ ይጨምርላቸው ነበረ እንጂ የሚያጎድልባቸው አንዳችም ነገር ታስቦም ተሰምቶም አይታወቅም ነበረ፡፡ በዚህ በዱክ በር አልፈን የምናገኛቸው ብዙዎቹ ቢዝነስ ቤቶች ድሮም ሆነ በወታደራዊው መንግሥት ዘመን የአደሬዎች ነበሩ፡፡ ብዙዎቹ ባለ ወርቅ ቤቶች፣ ባለ ልብስ ቤቶች፣ ባለጫማ ቤቶች፣ ባለሸቀጥ ሱቆች፣ ብዙዎቹ ልጆቻቸው የት/ቤት የክፍል ጓደኞቻችን፣ አብሮአደጎቻችን ነበሩ..፡፡
ብሔር ከብሔር ሳንለይ፣ ሐይማኖት ከሐይማኖት ሳንለይ፣ በዚህ በሐረር በር አልፈው ጀጎል ውስጥ የሚኖሩትም ከሐረር በር ውጭ የምንኖረውም ሁላችንም እጅግ የምንዋደድ የአንድ ሞቅ ያለች፣ የደራች፣ ለመጎብኘትም ለመኖርም ደስ የምትልህ፣ እንደ እየሩሳሌም ሁሉም ከሩቅ ሆኖ በፍቅር ዝናዋን የሚተርክላትና ሄዶ ቢያያት የሚመኛት… መዓዛዋ ሩቅ አልፎ እንደሚያውድ ቅመም የሆነች የአንዲት ሥልጡን የሐረር ከተማ ልጆች ነበርን፡፡ የወታደራዊው መንግሥት ዘመን በሐረር ይህን እንደሚመስል ስነግርህ የእነ ጓድ መንግሥቱ ፎቶ በትልቁ ሐረር በር ላይ ቢሰቀል ሊገርምህ አይገባም እያልኩህ ነው፡፡
መንግሥቱ ኃይለማርያምን ያኔ አደሬዎቹም፣ ሌላውም ሕዝብ ይወደው ነበረ፡፡ ከተማውን የሞሉት የእርሱ ጥቅሶች ናቸው፡፡ የምስራቅ ኢትዮጵያ የጦር ዕዝ (ምስራቅ ዕዝ) ከሚገኝበት ወደ ሚካኤል ቤተክርስትያ ከሚወስደው ቀበሌ 16 ጀምሮ፣ እስከ ራስ መኮንን በፈረሳቸው ላይ ሆነው በግርማ ሞገስ ተቀምጠው እስከሚታዩበት አብዮት አደባባይ፣ ወደ አራተኛ መውጫ ላይ ከአጂፕ እልፍ ብሎ ካለው ከሐረሩ ራስ ሆቴል እስከ ሸንኮር የጦርሠራዊት ሙዚቀኛ ኦርኬስትራ ግቢ ድረስ – የሐረር አውራ መንገዶችና የከተማው መግቢያ መውጫዎች በቆራጡ መሪ በኮሎኔል መንግሥቱ ጥቅሶች ያበዱ ነበሩ፡፡
በአንድ አጋጣሚ መንጌ ሐረር ከተማን ሲጎበኝ ውሰዱኝ ብሎ (‹‹ተብሎ››) ቀበሌ 10 አደባባዩ ላይ ወዳለች የትራፊክ ቤቷ ጋር በብዙ አረንጓዴ ቀለም የተቀቡ ዋዝ የሚባሉ ላንድሮቨር መሳይ መኪኖች ታጅቦ፣ እና ከብዙ የኢሠፓ ሰማያዊ ካኪና ወታደራዊ የኒፎርሞች ከለበሱ የጦር መኮንኖች ጋር ሆኖ ከነወታደራዊ ዩኒፎርሙ መጣ፡፡ ያ ቦታ ድድ የምናሰጣበት የሰፈራችን ደጃፍ ነው፡፡ በሰው መሐል ተሹለክልከን ሄደን መንግሥቱ ኃይለማርያምን ጨብጠነዋል፡፡ በእጁ በትረ መንግሥቱን የያዘ፣ ሲቀርቡት በቴሌቪዥን ከምናየውም በላይ ጠቆር ያለ፣ ሰውነቱ ደልዳላ፣ አጠር ያለ ሰው ሞቅ ባለ ፈገግታ አጎንብሶ ሠላምታውን አቀረበልን፡፡
በጣም የማልረሳው መንጌ የተጫማውን ጫማ ልብ ብዬ ማየቴን ነው፡፡ ከለሩ ከጥቁር ይልቅ ወደ ጥቁር ቡኒ የሚወስደው እንደ እስፖንጅ የሚመስል ወፍራም ተረከዝ ያለው ጫማ ነበር ያደረገው፡፡ እና ከሰፈሬ ልጆች አንዱ ጫማውን እየጠቆመ በጆሮዬ ‹‹የአየር ወለድ ጫማ ነው!›› አለኝ፡፡ ምናልባት በልጅነት አጭር ቁመት ከሁሉ ነገሩ ዓይኔ የገባችው መሬት የረገጠችው ጫማው ትሆን ይሆናል፡፡ ብቻ ያቺ የተወለወለች የመንጌ ከስክስ ጫማ ሁሌ ትዝ ትለኛለች፡፡ አካባቢው ላይ ለተወሰኑ ደቂቃዎች ግርግር ከፈጠሩና ከጎበኛኙ በኋላ ከሥላሴ ቤተክርስትያን አለፍ ብሎ ወደሚገኘው ወደ ኢሠፓ ህንጻ አመሩ፡፡ ደስታችን ወደር አልነበረውም፡፡ የምናገረው እውነቱን ነው፡፡ ምንም መወሻሸት አልነበረውም፡፡ ሐረር ሀገር ወዳዱንና ወኔያሙን የኢትዮጵያ ልጅ መንጌን በሙሉ ቀልቧ ትወደው ነበረ፡፡ መንጌም ሐረርን ከልቡ የሚወዳት ይመስለኛል፡፡ የኦጋዴን አንበሣው፡፡ ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም፡፡ አሁን ስለ ሐረር ትዝታው ቢጠየቅ ምን ይል ይሆን? በህይወት እያለ ስለ ሐረር ሲናገር ለመስማት እጓጓለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ሐረር የሠላምና የፍቅር ከተማ እንደሆነችው ሁሉ የኢትዮጵያ ቀደምት ወታደራዊ እምብርትም ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ ከተማዋ ከሶማሌ ወረራ በፊት ጀምሮ የወታደር ቤተሰብ የሚበዛባት ከተማ ነበረች፡፡ የራሴ አያት (የእናቴ ወላጅ አባት) ሻምበል ብርሃኔ በጃንሆይ ዘመን ከአዲስ አበባ ወደ ሐረር ከተማ መጥተው በፖሊስ መኮንንነት አገልግለዋል፡፡ አጎቴ ከጃንሆይ ዘመን ጀምሮ በሐረር ከተማ በፖሊስ መኮንንነት እስከ ጡረታ ዕድሜው ያገለገለ ነው፡፡ የአክስቴ ባል በሶማሌ ጦርነት ሕይወታቸውን ያጡ የጦርሠራዊት አባል ነበሩ፡፡ የአጋጣሚ ሆኖ እኔ የሁለት አስተማሪዎች ልጅ ነበርኩ፡፡ ነገር ግን ብዙ የወታደር ቤተሰብ የነበራቸው ወዳጅ ዘመዶቻችን ነበሩ፡፡
ሐረር፣ እና ኦጋዴን፣ ከጃንሆይ ዘመን ጀምሮ፣ ከሶማሊያም ወረራ በኋላ – ጦርነት ካልተለየው የሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በመቀጠል ዓይነተኛ የወታደር መናኸሪያም ነበረች ማለት ይቻላል፡፡ የጃንሆይ ታዋቂ የጦር አካዳሚ ያለው በሐረር ከተማ ውስጥ ነው፡፡ መንግሥቱ ኃይለማርያም የወጣበትን የኦጋዴን አንበሣን ጨምሮ ብዙ የምድርጦር፣ መድፈኛ፣ እግረኛ፣ ሜካናይዝድ ክፍለጦሮች፣ የፖሊስ ሠራዊት ዋና መምሪያ፣ ታጠቅ የጦርሠፈር፣ የምሥራቅ ኢትዮጵያ ወታደራዊ ዕዝ፣ እነዚህ ሁሉ ሐረር ከተማ ውስጥ የነበሩ ከብዙ ጥቂቶቹ – እና በማንኛውም የከተማዋ ነዋሪ የሚታወቁ – ወታደራዊና ተያያዥ ተቋማት ነበሩ፡፡ እና ወያኔዎች ሐረር ሲገቡ ሕዝቡ አበባ አንጥፎ አልጠበቃቸውም፡፡ ወደ ጀግኖች ሀገር ነው የገቡት፡፡ በግድ ነው የገቡት፡፡ ተዋግተውም፣ አታልለውም፡፡
ወያኔዎች ሐረር ሊገቡ ሲሉ ከሐረር ዋና የጦር ግምጃ ቤት አዳዲስ የጦር መሣሪያ ወጥቶ ለማንኛውም መሣሪያ ለሚፈልግ ነዋሪ ሁሉ በፊርማ በነፃ ታደለ፡፡ አዲስ አበባ ግንቦት 20 ላይ ተይዛለች፡፡ ሐረር ግን አልተያዘችም፡፡ እና ሁሉም የሀገር ፍቅርና የእናት ሀገር ቁጭት ያደረበት የሐረር ነዋሪ ሁሉ መሣሪያውን በየደጃፉ ላይ ይዞ እየወጣ ወደ ሠማይ ይተኩስ ነበር፡፡ እኔም ጓደኛዬ ቤት ልቀላውጥ ሄጄ ታላቅ ወንድሙ ወደ ሠማይ ሲያንደቀድቀው ከጎኑ ቆሜ በዓይኔ የተመለከትኩት ያኔ ነበር፡፡ ሳልተኩስም የቀረሁ አልመሰለኝም፡፡ የፌስቡክ ምስክርነቱ አስፈላጊ አልመሰለኝምና ተውኩት፡፡
በመጨረሻ ግን የሐረር ጦርሠራዊት አባላት በወታደራዊ ተሽከርካሪ ከተማውን እየዞረች በሃሎ ሃሎ (ድምጽ ማጉያ) ለነዋሪው መልዕክት አስተላለፈች፡- ‹‹ጀግናው የሐረር ሕዝብ ሆይ፣ አንድ ጥይት አንድ ጠላትን መግደያ ትሆናለችና፣ ጥይትህን አታባክን! ጥይትህን ሳታባክን በተጠንቀቅ ከተማህን ጠብቅ፣ ራስህን ጠብቅ፣ ሀገርህን ጠብቅ!››፡፡ ለምን እንደሆነ አላውቅም እንዲህ ያሉት የወቅቱ መልዕክቶች አስገራሚ የጀግንነት ስሜት በውስጤ ይነዙብኝ ነበር፡፡ ልጅነት ይሆን? አላውቅም፡፡ እርግጠኛ አይደለሁም፡፡ ለቤተሰቦቻችን ግን የታላቅ ጭንቀት ንግርቶች ነበሩ፡፡ ደርግ ልጅና ቤተሰብን አለያየ የሚሉት እንዲህ እንዲህ ያለውን ጭምር እያዩ ቢሆን ደስ ይለኝ ነበር፡፡ አባባሉ የመጣው ግን በቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር ጎራ ለይተው የተጋደሉ ቤተሰቦችን ለማለት ነበር፡፡
የሐረር ሕዝብ ሀገር ገንጣዩንና አስገንጣዩን ወያኔን (እና ሻዕቢያን) ሊዋጋ ያለውን መሣሪያ ታጥቆ ወጣ፡፡ ታጣቂው የከተማዋን ዙሪያ አጥሮ ዘብ ቆሞ፣ ሐረር ከተማ በጀግንነት መፈክሮች ደምቃ፣ ከተማዋ በወገን ባሩድ ስትርበደበድ ሐረር ነበርኩ፡፡ የሐረር ሕዝብ ልብ ያለው ህዝብ ነው፡፡ ወኔው ጥግ ድረስ ነበር፡፡ ፍርሃት አይታወቅም፡፡ ችግሩ አንድ ወር ሲቆይ ሁሉንም ነገር የመርሳት ዕድሉ ከፍተኛ መሆኑ ብቻ ነው፡፡ በቃ ‹‹ነገር አት..ዳብን›› ነው የሚሉህ ሐረሮች፡፡ ነገር አትብላ እንደማለት፡፡ ነገርን ለረዥም ጊዜ ማኘክ በሐረሮች ዘንድ ነውር ነው፡፡ አኞነት ነው፡፡ እና በሐረር ችኮነት አይወደድም፡፡ ፈሪነት አይታወቅም፡፡ ቂም በቀል ብሎ ነገር ከናካቴው የለም፡፡ አሁን ሀገር ይያዝልኝ ብሎ፣ ወዲያው አቦ ነገር አታካብዱ ሠላም ስጡና የሚል ሰው ካገኘህ – በትክክል እርሱ የሐረር ሰው ነው፡፡ ለወኔ የፈጠነ፡፡ ለመብረድ የፈጠነ፡፡ የፍቅር ጀግና፡፡
ያኔ ወያኔዎች ተደራዳሪዎቻቸውን ልከው ስሙን በውል ከማላስታውሰው ከሐረሩ የምስራቅ ዕዝ አዛዥ (በወቅቱ የኮሎኔልነት ማዕረግ ከነበረው) ጋር በአወዳይ ከተማ ህቡዕ በሠላም እጅ የመስጠት ድርድር አካሂደው ነበር፡፡ የሐረር ደህንነትና ኢሠፓ አባላት፣ እና ከጦር ክፍል የተላኩ ጓዶች በምስጢራዊ ውይይቱ ላይ ተካፋይ ነበሩ፡፡ እና ሀገሪቱ በወያኔ ከተያዘች ሐረርን አላስነጥቅም ብሎ ህይወት መጠፋፋቱ ትርጉም የለውምና በሠላም ከተማዋን እናስረክብ የሚል ሀሳብ ብልጫውን አግኝቶ የተደረገ የሰላም ስምምነት ነበረ፡፡ በመሐል ከወያኔና ሻዕቢያ ሀገር አስገንጣይ ወንበዴዎች ጋር ቁጭ ብሎ ሀገርን አሳልፎ ለመስጠት የመደራደሩ ሀሳብ እንደ ኮሶ የመረራቸው፣ ከሶማሌ ጋር ሀገሬን አላስነካም ብለው አንገት ለአንገት ሠይፍ ተማዘው ሀገሪቱን ያዳኑ ጀግኖች ቁጭትና ንዴት ውስጣቸውን አንገበገባቸው፡፡ እና ሀሳባቸውን ለወጡ፡፡
ሐረር ተያዘች ማለት በሐረር በኩል አልፈው ጂጂጋን፣ መላው ኦጋዴንን ያዙ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ጦራችንን አስተባብረን፣ 22ኛውን ክፍለጦር ከጂጂጋ አስመጥተን፣ ሐረርን ባለን ኃይል መክተን ከቁልቢ ላይ ከመለስናቸው – ኢትዮጵያ ነፃ እስክትወጣ ድረስ ድሬዳዋን ይዘን ከሐረር እስከ ጂጂጋ የሚደርስ – በጂቡቲና በሶማሊያ የምትዋሰን ራሷን የቻለች የሐረር ግዛት ከጠላት ተከላክለን አስጠብቀን መቆየት እንችላለን – የሚል የመጨረሻ የቁርጥ ሃሳብ አመጡ፡፡ ወይም አፈለቁ፡፡ ወቅቱ የስሜት ነው፡፡ በእርግጥ ወያኔ ገና ሀገር አልተቆናጠጠችም፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብ ሀገር አስገንጣይዋን ወያኔን አናቱ ላይ አንግሶ ያስቀምጣታል ብሎም ብዙ ሰው አልጠረጠረም ነበረ፡፡ እና ወኔና ቁጭት ከሰላም ሀሳብ በልጦ ተገኘ በሐረር ምድር፡፡
እና ከወያኔዎች ጋር በምስጢር በአወዳይ ላይ ስምምነት የተፈራረመው የምስራቅ ዕዙ የጦር አዛዥ እንደ ከሃዲ ተቆጠረ፡፡ መትረየስ የደገነ ከኋላ ክፍት ፓትሮል መኪናውን ይዞ ከጃንሆይ ዘመን ጊዜ ጀምሮ እውነተኛ አንበሶች በፍርግርግ ብረት የሚኖሩበትን የምስራቅ ዕዝ ግቢ መውጫ በር ላይ እንደደረሰ – ማንነቱ ባልታወቀ የበላይ ትዕዛዝ በቅፅር ግቢው ጠባቂ ወታደሮች በተኩስ እሩምታ ከነመኪናዋ ወንፊት አደረጉት፡፡ እና ሐረር በተረኛ ሮንድ (የከተማ ጥበቃ ዘቦች) ቅኝት የሚደረግባት የጦርነት ጥላ ወዳጠላባት ከተማ ተቀየረች፡፡
ከተማዋ ሌሊት ሌሊት አልፎ አልፎ ከሚሰሙ የመሣሪያ ተኩሶች፣ የምስራቅ ዕዝ አንበሣ የሚያጓራ ጩኸት፣ እና ከሐረር ጅቦች ኡውዉታ በስተቀር የሚሰማ ነገር አልነረበም፡፡ ቀን ቀን ሲቪልና ወታደራዊ ዩኒፎርም የለበሱ ሰዎች ይዞሯታል፡፡ በየመሐሉ የሚያዙ ሰላዮችም ነበሩ፡፡ በኤጀርሳ ጎሮ ቤርጎ ውስጥ፣ በራስ ሆቴል እና በቀይ መስቀል አካባቢ የተያዙ ሰላዮች በጀማ ፍርድ እዚያው በዚያው ሲረሸኑ በዓይኔ በብረቱ ተመልክቼያለሁ፡፡ አሰቃቂ ነበር፡፡ ግን እንደ ልጅ ደግሞ የሆነ የሚያጓጓ ልብ አስደንጋጭ ነገርም ነበረው፡፡ ልብ በልልኝ ፈይሳ፡፡ የሰላይ ፊልም አይደለም እየነገርኩህ ያለሁት፡፡ ይሄ የቀውጢ ቀን የሐረር እውነተኛ ታሪክ ነው፡፡
ወያኔዎች የሰላም ስምምነቱ መጨናገፉን አልሰሙም፡፡ እንደሚሰማው ከሆነ በስምምነታቸው መሠረት ወያኔ በሶስት የህዝብ ማመላለሻ ተሸከርካሪዎች ነባር ታጋዮቿን ጭምር ጭና ሐረርን በሠላም ልትረከብ ወደ ሐረር ከተማ ላከች፡፡ ሐረሮች ደግሞ መድፍና ታንክ ደግነው ጠበቋት፡፡ ወያኔዎቹ የፍቅር ከተማነቷን ዝና ከሰሙላት ከሐረር ከተማ የሚደረግላቸውን በዘንባባ ዝንጣፊ የታጀበ አቀባበል እያሰቡ ይመስለኛል ይጓዙ የነበሩት፡፡ ብቻ ግን የ40 ቀን ዕድላቸው ሆኖም ይሁን ምን ብቻ ሀገር አማን ብለው ወደ ሐረር መጡ፡፡ ደንገጎ ላይ ግን ያላሰቡት የታንክ ዝናብ ወረደባቸው፡፡ እና ሁሉም አለቁ፡፡ በሐረር ቋንቋ ‹‹እምሽክ›› ብለው ቀሩ፡፡ ያሳዝናል በእርግጥ፡፡ ግን ጦርነት ነው፡፡ ሐገር ነው፡፡ ማታለልም ያለበት አደገኛ የህይወት ቁማር ነው፡፡ ልብ ማለት የሚያሻው ወያኔዎቹ ብቻ አይደለም እምሽክ የተደረጉት፡፡ ከወያኔዎቹ ጋር የተስማሙትም እንደ ምስራቅ ዕዙ አዛዥ ያሉት አንዳንዶቹም ከሃዲ ተብለው እምሽክ ተደርገዋል፡፡ ወያኔ ከሞቱት ሁሉ የቆጯት አንዲት ሴት ታጋይ ጭምር ያለችበት የነባር ታጋዮቿ ከድል ጫፍ ላይ ደርሰው የገጠማቸው መራር ሞት ነበር – እየተባለ ይወራ ነበር በሐረር፡፡ ወሬ! ብዙ ነው ወሬው! ይኸው ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በወሬ ቀረን!
ከመድፍ የተረፉት ወያኔዎች ምን አደረጉ? እነሱም የዓለም አቀፉን ህግ ተላልፈው የሚገርም ማጭበርበር ሰርተው ሐረር ገቡ፡፡ በወቅቱ የዩኤን (በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት) ጥበቃና ከለላ ተሰጥቷቸው በሐረር ከተማ መሐል አልፈው ወደ ጂጂጋ የሚያቀኑ የእርዳታ እህል ጫኝ መኪኖች ነበሩ፡፡ የሐረር ልጅ የነበረ ሁሉ ያውቃቸዋል፡፡ ዕለት በዕለት ነበር የሚንቀሳቀሱት፡፡ ወደ ሐረር ሲመጡ እህል ጭነው፡፡ ሲመለሱ ባዷቸውን፡፡ የእርዳታ መኪኖች እጅግ ግዙፍ ነበሩ፡፡ ሁሌ ነጭ የዩኤን ባነር በላዩ ላይ በታተመበት ሰማያዊ ድንኳን ሸራ እንደተሸፈኑ ነው፡፡ በሐርትሼክ የስደተኞች ጣቢያ ለሰፈሩ የሶማሊያ ተፈናቃዮች የእርዳታ እህል ጭነው የሚጓጓዙ ትላልቅ የጭነት ካሚዮኖች ናቸው፡፡ ወያኔዎቹ ወደ ሐረር ለመግባት የተጠቀሙት እነዚያን የተመድ ካሚዮኖች ነበር፡፡
ማንም በወቅቱ ሐረር ከተማ የነበረ ሰው እንደሚያውቀው በዩኤን ተጎታች ካሚዮኖች ውስጥ ታጉረው ነው ወያኔዎች ሐረር ከተማ ገብተው የተራገፉት፡፡ የዩኤን መኪኖች ኢንተርናሽናል ኢሚዩኒቲ ስላላቸው አይፈተሹም ነበር፡፡ ኢህአዴጎች (ማለትም ወያኔዎች) ሐረር ሊገቡ ጥቂት ቀናት ሲቀራቸው የዩኤን መታወቂያ የያዙ የወያኔ ሰላዮች በሐረር ራስ ሆቴልና ኤጀርሳ ጉሮ መኝታ ይዘው – የቴሌግራም መልዕክት ሲለዋወጡ በዓይን እማኞች በመታየታቸው – እዚያው ህዝብ በተሰበሰበበት እንዲረሸኑ ተደርገዋል፡፡ በቦታው ነበርኩ፡፡ በዚያኑ ዕለት ማታ የቪኦኤ የአማርኛ ዜና ሁለት የዩኤን ሠራተኞች በሐረር ከተማ መገደላቸውን ዘግቦት ነበር፡፡ እንግዲህ ይህ ከሆነ በጥቂት ቀናት ልዩነት ነው ደንገጎ ላይ የወያኔ ሠራዊት የታንክ ጥይት ሲሳይ ሲሆን፣ የቀረው ብዙው ጦር ግን በዩኤን ትልልቅ የእርዳታ እህል ጫኝ ካሚዮኖች ታጉሮ ወደ ሐረር ከተማ ገብቶ የተራገፈው፡፡
ይሄ የማታለል ድርጊት ከዓለማቀፍ ህግ አኳያ ከታየ ዩኤንን የሚያስጠይቅ አሳፋሪ ተግባር ነበር፡፡ ድርጊቱ ይፋ ከሆነበት፣ ተገድጄ ነው ብሎ ማስተባበሉም አይቀርም ለነገሩ፡፡ ግን ነውረኛ ድርጊት ትናንትም ሆነ ዛሬ በእርዳታ ስም የሚንቀሳቀሱ የውጭ ለጋሾችና ዓለማቀፍ ድርጅቶች በሀገራችን የውስጥ ጉዳይ የሚጫወቱትን አደገኛ ቁማር ገና በጊዜ በቀላሉ ያሳየኝ የማልረሳው ክፉ አብነት ነበረ፡፡ ጉዳዩን እንደ ዘመናችን አስገራሚ የጦርነት ‹‹ትሪክ›› ለቆጠረው ሰው ግን ያ የወያኔዎች ድርጊት የጥንቶቹን የአቴናውያንን ‹‹የትሮይ ፈረስ›› ታሪክ የሚያስታውስም ነገር ነበረው፡፡ በሐረር ከተማ፣ በሰኔ ወር 1983 ዓመተ ምህረት፣ የዩኤን መኪኖች ለወያኔዎቹ እንደ ትሮይ ፈረስ ሆነው አገልግለዋል፡፡ ይህን ያየ፣ የሰማ፣ የታዘበ የወቅቱ የሐረር ከተማ ነዋሪ ሁሉ የሚመሰክረው ሀቅ ነው፡፡
ለማንኛውም ሐረር ገቡ ወያኔዎች፡፡ እና ጀመሩ፡፡ ቂም መወጣታቸውን፡፡ ሐረሮች የመንግሥቱ ኃይለማርያም ታማኞች መሆናቸውን በድርጊታቸው መስክረዋል ብለው ያሰቡ ይመስለኛል ወያኔዎቹ፡፡ ስለተዋጓቸው፡፡ ያልገባቸው ነገር – ሰዉ – ራሴንም ጨምሮ – ለመዋጋት ዝግጁ የነበረው – ሀገርን የሚገነጣጥል፣ ወያኔ የሚባል ገንጣይ ወንበዴን ነበር – በብሔራዊ ስሜት ተሞልቶ ኢትዮጵያን ከእነዚህ ገንጣይ አስገንጣዮች አድናለሁ ብሎ በደመነፍስ የመጨረሻውን ተጋድሎ ለማድረግ የተነሳ ሀገሩን አፍቃሪ ህዝብ ነበር የተዋጋቸው፡፡ እና ህዝቡን መጥላትና ቂም መያዝ አልነበረባቸውም፡፡ ቄጠማ ጎዝጉዞ፣ አበባ እየታቀፈ አይቀበላቸውም መቼም፡፡ ጦርነት ነው፡፡ ወታደሩ ደግሞ ለሀገሩ ዘብ ሊቆም የማለለት ቃልኪዳን አለበት፡፡ እና ወያኔዎቹ እንዴት ቢያስቡ ሐረርን እንደተቀየሙ አልገባኝም፡፡ ምናልባት ሐረር የሠላም፣ የፍቅር፣ የጨዋታ ከተማ  ነች ሲባል እነሱ የገመቱት፣ የጫት እቅፍ ከአበባ እቅፍ ጋር ይዞ ሰዉ በግራና በቀኝ ተሰልፎ የሚጠብቃቸው መስሏቸው ይሆን? እላለሁ አንዳንዴ! አዎ ነበር፡፡
የሆነ ሆኖ ወያኔዎቹ በዩኤን ተሽከርካሪ ካሚዮኖች ተጭነው ሐረር ላይ ሲዘረገፉና ከተማዋን ሲቆጣጠሩ – ከከተማው ወጥቶ የከተማዋን ዳርቻ ይጠብቅ የነበረው የሀረር ሕዝብ መርዶውን ካለበት ሆኖ ሰማ፡፡ እና የወታደር ልብስ የለበሰ ፋቲጉን በቲሸርት እየቀየረ፣ መሣሪያውን ጥሻ ውስጥ እየጣለ፣ በሶስተኛውም ቀን፣ በሳምንቱም፣ በወሩም ኩስስ ምስስ ብሎ አንገቱን አስልቶ ወደየቤቱ ተመለሰ፡፡
የማስታውሰው ከሥላሴ ጀርባ ከነበረ ቤታችን ኮቴዬን አጥፍቼ ወጥቼ በሌሊት ተነስቼ ወሬ ስለቃቅም ከግቢው በር ውጪ ለቆሻሻ መጣያ በተቆፈረ አነስተኛ ጉድጓድ አንድ ረዘም ያለ ሰው ክላሹን ሲወረውር ተመለከትኩት፡፡ እርሱም ተመለከተኝ፡፡ እና ግባ ወደቤትህ እዚህ ምን ትሠራለህ! ብሎ በኃይለቃል አስመለሰኝ፡፡ ትንሽ ቆየሁ፡፡ ወጣሁ፡፡ ሰውየው ሄዷል፡፡ ክላሹ ግን አለ፡፡ አንስቼው ወደቤት ገባሁ፡፡ የገጠመኝ እኔ ነኝ ያለ የእናቴ ጥፊ፣ የአባቴ ርግማንና ካገኘህባት ቦታ መልስ! የሚሉ ተግሳፆች ነበሩ፡፡ እስካሁን ሳስበው የሚያስቀኝ – አልመልስም ብዬ ለተወሰኑ ደቂቃዎች የማንገራገሬ ነገር ነው፡፡ ልጅ ነኝ፡፡ የመሣሪያ ፍቅር ከየት አደረብኝ? ነፍጠኝነት ውስጤ ነበር እንዴ?!! ሀሀሀሀ! ካገኘሁባት መለስኩ፡፡
የእኛ ቤት አስተዳደር አንዳንዴ የናዚ አስተዳደር የሚመስለኝ በእንዲህ ዓይነቶቹ ጊዜዎች ነበር፡፡ አንዴም ከመሐረብ ውስጥ 10 ብር ከሩቢያ (ከሰባ አምስት ሳንቲም) ወደ ሸዋበር በማዘጋጃ ቤት ዛፎች መሐል በሚያስኬደው የእግር መንገድ ላይ ወድቆ አገኘሁ፡፡ እየፈነደቅኩ ወደቤት ሳመጣ የገጠመኝ ተመሳሳይ ትዕዛዝ ነበር፡፡ ካገኘህባት መልስ! አቤት የተቃጠልኩት መቃጠል! አንዳንዴ እነዚህን አስተዳደጎቼን ሳስብ ቅር ቅር ይለኛል! በዝርፊያ ዘመን፣ በወያኔ ዘመን – ቄስ አድርገው ያሳደጉን ወላጆቻችን የጠቀሙን አልመሰለኝምና ነው! እንዲህ እንዳሁኑ ዘራፊነት መከበሪያ፣ ጨዋነት መዘባበቻ ሆኖ ስናየው ምን እንበል? የጨዋ አስተዳደጋችንን እናማርር እንጂ!!
ብቻ ለማንኛውም ለዩኤን ምስጋና ይግባው – ጥይት ሳይተኮስ ጦርነቱ በሽንፈት ተጠናቀቀ! (ማለቴ በወያኔ አሸናፊነት!)፡፡ በእርግጥ ተመስገን ማለትም ጥሩ ነው፡፡ ጦርነቱ እንደታሰበው ቢካሄድ ኖሮ ብዙ የሰው እልቂት ሊከተል ይችል ነበር፡፡ ከዚያ በኋላማ ወያኔዎች የሐረርን ሕዝብ ተበቀሉት፡፡ መጀመሪያ በቀላቸውን እስኪያሰናዱ ድረስ ሐረርን፣ አዲሳባንና ድሬዳዋን በሽግግር መንግሥቱ ቻርተር ጊዜ ‹‹ነፃ ክልል›› ብለው ሰየሙ፡፡ ቀስ ብለው የኦሮሞውን ኦፒዲኦን ወደ ሐረር አመጡ፡፡ ኦነግንም ሞከሩት፡፡ ሁሉም አልሆነም፡፡ በመጨረሻ ፊደል የቆጠሩ አደሬዎችን ከጀጎል መሐል ከያሉበት እያፈላለጉ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ሹመት መስጠት ጀመሩ፡፡ እያሉ በፖሊስ፣ በከተማ አስተዳደር፣ በንግድ፣ በመጨረሻ ከተማዋ የአደሬዎች ከተማ ናት ብለው እርፍ አሉ፡፡
በየቀኑ ወደ ትምህርት ቤት ስሄድ ከሸመደድኳቸው አዳዲስ የወያኔ-ኦፒዲኦ የሐረር መፈክሮች መካከል፡- ‹‹አዳፍ ሴናን ኡመተ ኦሮሞ ኦፒዲኦ ቲን ኢፋት ኢንባኣ!›› የሚል፣ ‹‹በደርግ መቃብር ላይ ኢህአዴግ ያብባል!›› የሚል፣ እና በጣም ቆይቶ ሐረር የአደሬዎች መኖሪያ ብቻ ነች መባሉን ተከትሎ፡- ‹‹ሐረር ዚሐረሪያች ሁስኒ!›› (‹‹ሐረር የሐረሪዎች ትሆናለች!››) የሚሉ መፈክሮች ትዝ ይሉኛል፡፡ ‹‹ከቆራጡ መሪ ከጓድ መንግሥቱ ኃይለማርያም አመራር ጋር ወደፊት!››፣ እና ‹‹ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር!›› የሚሉ መፈክሮችን በለመዱ ዓይኖቼ እነዚህንም አየሁ፡፡ ጊዜ ሁሉን ያሳያል፡፡ ሐረር የሐረሪዎች ትሆናለች ሳይሆን  – ሐረር የሐረሮች ትሆናለች – የሚል መፈክር የምናይበት ጊዜ ይናፍቀኛል፡፡
ለማንኛውም የወያኔ በቀል እንዴት በሐረር ከተማ ላይ እንዳረፈ ወደጀመርኩት ጨዋታ ልመለስ፡፡ ልብ በሉ፡፡ በሽግግር መንግሥቱ ጊዜ – የድሬዳዋ አስተዳዳሪ ተደርገው የተሾሙት ሁለት ተከታታይ አስተዳዳሪዎች የሐረር ነዋሪዎች ነበሩ፡፡ አደሬም ኦሮሞም አልነበሩም፡፡ ብሔራቸው አልተፈለገም፡፡ ሐረርም ድሬዳዋም የቻርተሩ ነፃ ከተሞች ናቸው፡፡ እና ኢትዮጵያውያን ብቻ መሆን በቂ ነበር፡፡ ወያኔዎቹ ከነዚያ ሙከራዎቻቸው ምን የብሔር ክሽፈት እንዳገኙባቸው አላውቅም፡፡ ወዲያው ብቻ ምጽዋን ለሻዕቢያ ሸጧል በሚል በሐረር ሕዝብም በወታደራዊው መንግሥት የቀድሞ የጦር መኮንኖች ዘንድም ከፍተኛ ጥላቻ ያተረፈን አንድ ጄነራል አሊ የሚባል ዕድሜ-ጠና ሰው አምጥተው የሐረር ዋና አስተደዳሪ አድርገው ሾሙት፡፡ ጄነራሉ የአደሬ ተወላጅ ነው፡፡ ብዙው ሰው የሚለው ምጽዋን ሲሸጥ እንደ ውለታ የአደሬ ክልል ይመሰረትልሃል ብለው ቃል ገብተውለት ነበር – እያለ ነበረ፡፡ እውነት ሳይሆን አይቀርም፡፡ ስለዚህ ጄነራል ጉዳይ የታደሰ ቴሌ ሳልቫኖን ‹‹አይ ምፅዋ›› መጽሐፍ ያገኘ ሰው ቢመለከተው ደስ ይለኛል፡፡
ሻጩ ሰው – ሰውየው – ‹‹ጄነራል አሊ›› – በአደባባይ አይታይም፡፡ ሁሌ በከፍተኛ ጥንቃቄ ፋሺስት ጣልያን በገነባቸው ከሐረር በር ከፍ ብሎ በሚገኘው የከተማው አስተዳደር ቢሮው ውስጥ መሽጎ ነው የሚንቀሳቀሰው፡፡ እስከ ስንት ጊዜ በአስተዳዳሪነት እንደቆየ ትዝ አይለኝም፡፡ በመጨረሻ በሐረር ያሉ ነዋሪዎች በሙሉ መምረጥም መመረጥም አትችሉም የሚል መመሪያ ወጣ፡፡ የሚመርጡትም የሚመረጡትም አደሬዎችና ኦሮሞዎች ናቸው – የሚል መመሪያ አስተላለፉ ወያኔዎቹ፡፡ ቀጠሉና ደግሞ ያንን አሻሽለው – ሌላው የሐረር ኗሪ መምረጥ ይችላል – መመረጥ ግን አይችልም – የሚል ፋሺስታዊ ‹‹ህግ›› ደነገጉ፡፡ እስካሁን በሥራ ላይ ያለው ይኸው ህግ ይመስለኛል፡፡
እና ወያኔ የኦሮሞና የአደሬ ፖለቲከኞችን በአምሳሏ ፈጥራ የሁሉም ከተማ ለመሆን የበቃችው የሐረር ከተማ የበላይ ገዢ ዘሮች አደረገቻቸው፡፡ በ1999 ዓመተ ምህረት በሠራሁት የጥናት ፅሑፍ ላይ ይህንኑ ሁኔታ አስመልክቼ ‹‹አፓርታይድ ኦቨርቶን›› የሚል መጠሪያ ሰጥቼ መደምደሜ ትዝ ይለኛል፡፡ የፕ/ር መስፍን ወልደማርያምን ‹‹የክህደት ቁልቁለት›› የሚል መጽሐፍም ያገኘው ሰው ቢያነበው የከተማዋን ህዝብ ቁጥርና ወያኔ ያነገሰችውን የአደሬ የአናሳዎች አስተዳደር በሚገባ አስቀምጠው ኮንነውታል፡፡ እና ወያኔ – ጥይት ተኮሱብኝ ያለቻቸውን የመንግሥቱ ኃይለማርያምን የኦጋዴን አንበሶች ሀገር – የጃንሆይን ሀገር – ሐረርን ለመበቀል – የከተማውን ምክር ቤት 50 በመቶ ለአደሬዎች፣ ቀሪውን 50 በመቶ ደግሞ ለኦሮሞዎች ሰጠች፡፡ እና አንዳቸው ሲያንገራግሩባት – ዋ! ምክርቤቱን ለኦሮሞዎቹ ጠቅልዬ እንዳልሰጠው!፣ ዋ! ለአደሬዎቹ እንዳልሰጠው! እያለች የዘር ፖለቲካ ፔንዱለሟን ስትጫወትባቸው ኖረች፡፡ አይ ወያኔ!
ረሳሁት በሞቴ፡፡ እና የእነ ጓድ መንግሥቱ፣ ብሬዥኔቭና ካስትሮስ ፎቶ? መጨረሻው ምን ሆነ? የነመንጌ ፎቶማ በነጭ ኮላ ተለቅልቆ ጠፋ፡፡ እና ለብዙ ጊዜ ባዶውን ነበር፡፡ ወያኔዎች በመንጌ ፎቶ ምትክ የመለስ ዜናዊን፣ የበረከት ስምዖንና የሐየሎምን ስዕል አለማሳላቸው እስካሁን ይገርመኛል፡፡ በዚህ በዚህስ ትሁቶች ነበሩ ማለት ይቻላል ወያኔዎቹ፡፡ ሥራቸውን ይሠራሉ፡፡ ፎቶ ምናምኑ ላይ ብዙ ትኩረት አልነበራቸውም፡፡
በነገራችን ላይ ኋላ እንዲህ ሞቡቱ ሴሴሴኮን የሚያስቀኑ የዝርፊያ ንጉሥ ሊሆኑ – ወያኔዎቹ ሲገቡ ሌብነትን እንደ መጨረሻው ከፍተኛ ኃጢያት የሚፀየፉ ‹‹ባህታውያን›› ነበሩ፡፡ ሐረር ውስጥ ጋሽ ተመስገን የሚባሉ ጡረተኛ ሻምበል በጧት ተነስተው ደጃፋቸው ላይ ለፍየል ሳር ሲቆርጡ ሌባ መሰሉን ብለው በጥይት ደፍተዋቸዋል የወያኔ ታጋዮች፡፡ የሰፈራችን ከቀድሞ አየር ወለድ ሠራዊት የተመለሱ – እና ለውንብድናም የማይመለሱ ጎረምሶችን – (እነ ተስፉን፣ እና ሌሎችንም) ወያኔ ዘራፊዎች እያለች ያለፍርድ በጥይት ግንባር ግንባራቸውን እያለች ነው ምድሪቱን ያሰናበተቻቸው፡፡ ባሊስትራ ከፖሊስ ጋራሽ የሰረቀን ባሌስትራውን አሸክመው በላብ ተጥለቅልቆ ከተማውን ሲዞር ትዝ ይለኛል፡፡ የሰረቀውን መቶ ብር በጥርሱ አስነክሰው በፓትሮል ከተማውን ያዞሩት ልጅ እስካሁን መልኩ በፊቴ አለ፡፡ በጥርሱ ነክሶ ብሩን ሲታይ እየሳቀ ይመስል ነበረና በወቅቱ ሌባው እያሳዘነኝም አስቆኝ እንደነበሩ ትዝ ይለኛል፡፡ ሸዋበር ውስጥ እህቱ ከምትሸጠው ቆሎ ላይ ዘግኖባት ሲሮጥ እያለቀሰች ትከተለው የነበረችን ቆሎ ሻጭ ልጅ ብላቴና ወንድም – የወያኔ ታጋዮች ተኩሰው ገበያ መሐል ገድለዋል፡፡ ግፋቸው እንደተጠበቀ ሆኖ – ነገር ግን ስርቆትን ምን ያህል የሚፀየፉ ሰዎች እንደነበሩ እነዚህ ሁሉ ምስክሮች ናቸው፡፡ የአሁኖቹ የሞቡቱ የመንፈስ ልጆች፣ የያኔዎቹ የቀበሮ ባህታውያን፣ ወያኔዎች!
እና ወደ ጨዋታዬ ስመለስ – ወያኔዎች በሐረር በር ላይ የነበረውን የመንጌን ምስል በመለስ አልተኩትም፡፡ ያኔ ታይታ ብዙም አይወዱም ነበር፡፡ መፈክር ነፍሳቸው ነው፡፡ ፎቶ ግን አይወዱም ነበር፡፡ መለስ ከሞተ በኋላ ነው በሙት መንፈስ ሀገሪቱን ለመምራት ሲሉ የመለስን ፎቶ በየቦታው እንደ አሸን ያፈሉት፡፡ ለሥልጣንና ከሥልጣን ለሚገኘው ጥቅም እንጂ ለፎቶስ ብዙም ግድ አልነበራቸውም፡፡ በመጨረሻ ግን አደሬዎቹ የእነ መንጌን  ምስል ተኩት፡፡ በኢሚር አብዱላሂ ምስል፡፡ ኢሚር አብዱላሂ ማን ናቸው?
ኢሚር አብዱላሂ የምኒልክን ‹‹ወራሪ›› ሠራዊት ለመመከት ጨለንቆ ድረስ አደሬዎችን እየመሩ የተዋጉ – እና በምኒልክ ሠራዊት ላይ መድፍ የተኮሱ – እና በሀብተጊዮርጊስ የሚመራው የምኒልክ ሠራዊት 30 ደቂቃ ባልፈጀ ጦርነት ድምጥማጣቸው የጠፋ – እና እሳቸውም እዚያው በጨለንቆው ጦርነት ላይ ሰማዕት የሆኑ የአደሬ ኢሚር ናቸው፡፡ አደሬዎች በታሪካቸው የሚያውቁት ከጦርነት መሸሽን ነው፡፡ በውስጡ በመቶዎች የሚቆጠሩ ጠመዝማዛ መንገዶችን የያዘው ታሪካዊው የጀጎል ግንብ አደሬዎች ከቱርኮች ወረራ ቢቃጣባቸው እየተሸለከለኩ ለመደበቅ የሠሩት ትልቅ ሕዝባዊ ምሽግ ነበረ ማለት ይቻላል፡፡ አደሬዎች በታሪካቸው ሁሉ የንግድ እና የሠላም ሠዎች ናቸው፡፡ ጦርነት አድርገው አያውቁም፡፡ አንድ ጦርነት አደረጉ፡፡ ከምኒልክ ሠራዊት ጋር፡፡ እና አለቁ፡፡ እና ከነፍጠኛ ጋር ሲዋጋ የተሰዋ አንድ አደሬ ሠማዕት አገኙ፡፡ ኢሚር አብዱላሂ፡፡
እና የኢሚር አብዱላሂን ምስል በዱክ በር ላይ – በመንጌ ፎቶ ፋንታ ሰቀሉት፡፡ ደስ ይላል፡፡ ያስቃልም፡፡ አንዱ ቀረብ የሚለኝ ወዳጄ ሲነግረኝ ግን – የመንጌን ምስል የተካው ምስል – የሰማዕቱ ኢሚር አብዱላሂ ምስል አይደለም፡፡ የኢሚር ኑር ምስል ነው፡፡ ኢሚር ኑር ማን ናቸው? ኢሚር ኑር ደግሞ የአደሬዎች የመጀመሪያው አስተዳዳሪ (አሚር) ናቸው፡፡ ዌል፡፡ ከሆኑስ እኚህ ይሻላሉ፡፡ ድሮስ መንግሥቱ ኃይለማርያም እዚያው የጦር ካምፑ ላይ ፎቶው ይሰቀል እንጂ – ኢሚር ኑር ሊገቡ ሊወጡበት ባስገነቡት የሐረር በር ላይ ምን ፊጥ አደረገው?
በነገራችን ላይ ስለ አደሬዎች የጨለንቆ ጦርነት ሲነሳ እስከዛሬም ድረስ እንደቀልድ የሚነገር – ከጦርነቱ በኋላ የምኒልክ ወታደሮች በኢሚሩና አደሬዎቹ ድፍረት በጣም ስለተበሳጩ ሁሉንም በህይወት የተረፉ ወንድ አደሬዎች ሰብስበው ሊረሽኗቸው አሰቡ፡፡ ግን መካሪ ሽማግሌ መጥቶ ሃሳባቸውን አስቀየራቸው፡፡ እና በምትኩ አስፈረሟቸው፡፡ የፈረሙት ሁሉ በህይወት ተለቀው ወደየቤታቸው ገቡ፡፡ ያልፈረመ የአደሬ ወንድም የለም ይባላል፡፡ የፈረሙት ምን ብለው ነው? ‹‹እኔ ሴት ነኝ›› እያሉ፡፡ እንግዲህ – ለወንድ ሴት መሆን በወቅቱ እጀግ አሳፋሪ ነገር ነበረ፡፡ ‹‹ሴት ነኝ›› ብለው ምህረት ከተደረገላቸው – ሁለተኛ ወንድ ነኝ ብለው ሊነሱ አይችሉም ማለት ነው፡፡ እና በዚያ ታሪክ የተነሳ እስከቅርብ ጊዜ ‹‹የአደሬ ወንድ – የሴት አልጫ ማለት አይደለ ወይ!›› እየተባለ ይተረባል በሐረር፡፡
በወታደራዊው መንግሥት ዘመን የአደሬ ወንዶች የብሔራዊ ውትድርና ምልመላን ለማምለጥ ቀሚስ ለብሰው ይንቀሳቀሱ ነበር፡፡ በእርግጥ የፊታቸው መልክ የብዙዎቹ ኬክ የመሰለ፣ አረብም የሚመስል፣ የሚያምር መልክ አላቸው፡፡ እና ቀሚስ ከለበሱ፣ ሻሽ ካሰሩ ሴት መስለው ሊያሳስቱ እንደሚችሉ አስባለሁ፡፡ እና አንዴ አንዱን አደሬ በጥርጣሬ የደርግ ወታደሮች ከነቀሚሱ ያዙት፡፡ ቀሚሱን በግድ ቢገልቡት ከነ ቱልቱላው ነው፡፡ ወታደሮቹ፡- ‹‹አንተ?! ሴት ነኝ አላልክም? ይሄ ምንድነው!?›› ይሉታል፡፡ ‹‹ወላሂ! ካለዛሬ አላየሁትም!›› አለ – እየተባለ ይፈተላል፡፡ ሐረርን በፍተላ ማን ይችላታል፡፡ እነዚህ ታሪኮች ግን ፍተላዎች ብቻ አይመስሉኝም፡፡ እውነት በሌለበት ጭስ አይጨስም፡፡
ወንድሜ! አዎ የድሮው የአደሬ ወንድ ህይወቱን ለማትረፍ ‹‹ሴት ነኝ!›› ብሎ ፈርሞ ሊሆን ይችላል፡፡ ሴት ነኝ ብለው የፈረሙበት ሰነድም እስከዛሬ አለ ይባላል፡፡ ማን ዘንድ እንዳለ በበኩሌ አላውቅም፡፡ ወንድሜ! እየሰማኸኝ ነው አይደል?! የድሮው ብቻ አይደለም፡፡ የአሁኑም የአደሬ ወንድ ሴታሴት (አልጫ) ሊሆን ይችላል! (ሴቶች እንዳትቀየሙኝ!)! ነገር ግን የሐረርን ሕዝብ ረግጦ፣ ሰጥ ለጥ አድርጎ፣ አንቀጥቅጦ፣ ልክ አስገብቶ እንዲገዛ ወያኔ ቀብታ የሾመችው – እርሱን ነው፡፡ አሁን ወንድ ነኝ የሚል እስኪጠፋ ድረስ ሐረርንና ሐረሮችን አስተኝተው የሚገዙት – እነዚያ ‹‹ሴት›› የተባሉት – እና አሁን ከሌላው ሰው የበለጠ ብዙ ልብ ያላቸው መሆናቸውን ያረጋገጡት የአደሬ ወንዶች ናቸው!!
ዛሬ ላይ ብዙ በዘመኔ የማውቃቸው – ብዙ የሐረር ሰዎች – ሐረርን ጥለው ወጥተዋል፡፡ በአዲሳባ፣ ናዝሬት፣ አዋሳ፣ ድሬዳዋ፣ – ከሐረር የፈለሰ የሐረር ህዝብ – በብዙ ከተሞች ታገኛቸዋለህ፡፡ ሌላ ቀርቶ ከኢትዮጵያም ውጭ በመላው ዓለም ላይ ተበትነዋል የሐረር ልጆች፡፡ አደሬዎች ግን በትውልደ አደሬነት ብቻ – የሐረር ልጆች ያልሆኑም አደሬዎች ከየትም ዓለም መጥተው በሐረር የበላይ ዜጋነት የሰጣቸውን እርከንና ኑሮ እያጣጣሙ እየኖሩ ነው፡፡ ሕዝቡ ራሱ ቆርቁሮ፣ ራሱ ትልቅ ሥልጡን ከተሜ ካደረጋት ከሐረር በነቂስ እየተሰደደ እየወጣ፣ አደሬዎቹ ከጥንታዊ ጀጎላቸው ወጥተው ሕዝቡን እያስገበሩ አሁንም እንዳሉ አሉ፡፡ ለውጡ መጥቷል፡፡ ነገር ግን እነዚህን ምንም ጉልበት የሌላቸውንና ለመጣ ጉልበተኛ በማሽቃበጥ ብቻ ህልውናቸውን የሚያቆዩትን እንደ አደሬ ክልል ያሉትን የሁልጊዜ ‹‹አሜን ባይ›› ወይም ‹‹አጫፋሪ›› ደጋፊዎች ከምንም ጊዜ በላይ የአሁኑ መንግሥት በእጅጉ ይፈልጋቸዋል፡፡
ስለዚህ ‹‹ለውጡ›› አደሬዎቹንም፣ የጋራ ተጣማሪ ገዢዎቹን ‹‹ኦሮሙማዎቹንም››፣ በሐረር በወያኔ የበቀል ሠይፍ ተተክሎ የቆየውን የአፓርታይድ አገዛዛቸውንም የሚነካው ምድራዊ ኃይል ያለ አይመስልም፡፡ ሕይወት እንደነበረችው ትቀጥላለች፡፡ ሁሉም ባሉበት ይቀጥላሉ፡፡ የኢሚር አብዱላሂ ወይም የኢሚር ኑር ፎቶ ግን ቀጣይነታቸው ያጠራጥራል፡፡ ባለፈው አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር – አብይ አህመድ አሊ – ሐረር ከተማ ሊመጣ ነው ሲባል ለእርሱ አቀባበል የኢሚሩን ምስል በሸፈነ በትልቅ ፖስተር ከጠቅላዩ ፎቶ ጋር እንዲህ የሚል መፈክር ሰቅለው ነበር አደሬዎቹ፡- ‹‹ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ – ዳግማዊ አል ነጃሺ!››፡፡ (ፎቶውን ስክሪን ሻቱን ለታሪክ አስቀርቼዋለሁ!)፡፡
ወቸው ጉድ! አይ ጊዜ! ጊዜ የማያሳየን ነገር የለም! ከአያሆሆ ወንዲሜ ጓዲ መንጊሥቱ … እና ከአባታችን መለስ ዜናዊ… አሁን ደሞ በአክሮባት ወደ ዳግማዊ አል ነጃሺ! ወቸው ጉድ! ጊዜ ጀግና! ማየት ነው! ገና ብዙ ያሳየናል! አንዴ የሐረር አማኑኤል ቤተክርስትያን የሚባሉ የፕሮቴስታንት ዘማሪዎች (እነ ካሥዬና ሌሎች) ‹‹ወንጌል ለሁሉም!›› በሚል መንፈሳዊ መፈክር ለአደሬዎች ወንጌልን እንሰብካለን ብለው የአደሬኛ መዝሙር አሳትመው ነበር፡፡ ‹‹ሄሊቄ ኦር ጎይተይ ጎይተይ ኢንታህ! መትናፋስ ኢስጢዛል!..›› የሚል፡፡ ‹‹እግዚአብሔር መልካም አምላክ ነው! ዕረፍትን የሚሰጥ!›› የሚል፡፡ በሐረር በወንጌል ተሰብኮ ወደ ፕሮቴስታንትነት የተቀየረ አደሬ መኖሩን በበኩሌ አላውቅም! ይኸው ግን ከእስልምና ራሱን ወደ ፕሮቴስታንት ሰባኪነት የቀየረውን ጠቅላይ ምኒስትር ‹‹ዳግማዊ አል ነጃሺ›› ብላ ተቀብላለች ሐረር፡፡ ነገ ደግሞ በሐረር በር ላይ ፎቶውን እናየው ይሆናል! ወቸ ጉድ! የማታሳይህ ጉድ የለምኮ! ሐረር!!
ሐረር ተወርታ አትጠገብም፡፡ ለጊዜው ግን አበቃሁ፡፡
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ!
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!  
Filed in: Amharic