>
5:29 pm - Friday October 10, 4036

"••ጣናነሽን"እንቦጭ ይነቃት...??? (ተመስገን ባዲሶ)

“••ጣናነሽን እንቦጭ ይነቃት…???>

ተመስገን ባዲሶ

*  ለ40 አመታት ያልተበገረችው ጣና-ነሽ ጀልባ እንዲህ የማርያም-መንገድ እስክትጠይቅ በእንቦጭ ታንቃለች። ህልውናዋም እያከተመ ይመስላል! ከጥቂት አመታት በኋላ ግን እንቦጩ በዚህ ከቀጠለ <•ጣና-ነሽ•> ጀልባ ይቅርና <ጣና-ሓይቅ•> ስለመኖሩ ራሱ እንጃልን…!!!!
 
….፦በጣና ኃይል ላይ ከሚገኙ ጀልባዎች ትልቋ <•ጣና-ነሽ•> ናት። ጣና ነሽ ደከመኝ ሳትል በጣና ኃይቅ ላይ ግልጋሎት መስጠት ከጀመረች ወደ 40 የሚጠጋ አመት ይዛለች። በአብዛኛው የምትጠራው እና የምትታወቅባት ቅፅል-ስሟ <•የጣና-አድባር•> በሚል ሲሆን፤ ወደ 27 ሜትር ስፋት እና 8 ሜትር ቁመት ያላት ጣና-ነሽ ባለሁለት ፎቅ ወይም Ground +-2 ተክለ-ቁመና ያላት ጀልባ ናት። በውስጧ ሁለት መፀዳጃ-ቤቶች፤ የሠራተኞች ማደሪያ መኝታ ክፍሎች እና የሻይ-ማፍያ ጭምር ያላት ጣና-ነሽ…..ወደ ውስጥ ገብተን ስናያት ግራውንዷ ውስጥ ዕቃ ይጫንባታል፤ በተጨማሪም ውኃ ሰርጎ እንዳይገባ የሚቆጣጠር Air Bag ወይም የአየር-ቦርሳ አላት። ጣና-ነሽ ግዙፍ እንደመሆኗ ሁለት ሞተር ያላት ጀልባ ነች። ወደ መሪ ክፍሏ ስንዘልቅ ሁለት መሪ ያላት ሲሆን፤ ሦስት ሰዎችን አደላድላ የምታስቀምጥበት ቦታን ይዛለች። ዋየርለስ-ቴሌፎን ወይም ገመድ አልባ ስልክ፤ እንዲሁም ጀልባዋ የት አካባቢ እየተንሳፈፈች እንደሆነ የሚጠቁም የጂፒኤስ መሳሪያም ተገጥሞላታል። ግራውንድ+-2 ላይ የፈለገ መንገደኛ ያለምንም ጭማሪ ክፍያ መጓጓዝ የሚችልበት ክፍል ያላት ጣና-ነሽ ለመንገደኞች የሻይ ቡና መስተንግዶ የምትሰጥበት ካፌም አላት።
🚤•…….፦ጣና-ነሽ መጀመሪያ ተፈብርካ የመጣችው ከጀርመን ሀገር ሲሆን፤ ምፅዋ ትንሽ ጊዜ ቆይታ… እ.ኤ.አ ከ1968 አመተ-ምህረት ጀምሮ ለ10 አመት ያህል መኖሪያዋ እና እንቅስቃሴዋ አርባ-ምንጭ አካባቢ ነበር። በጊዜው በነበረው አወቃቀር መሰረት የባህር እና ትራንስፖርት ተቋም የምፅዋን እና የአሰብ ወደብን ጨምሮ የሀገር ውስጥ የውሃ ላይ ዝውውርን ይቆጣጠር ስለነበር ከጣና አንዲት ተለዋጭ አነስተኛ ጀልባ ወደ አርባ ምንጭ ተልኮ፤ በምትኩ ጣና-ነሽ ወደ ጣና እንድትመጣ ተደረገ።
🚤•……፦ጣና-ነሽ በጉዞዋ ወደ ሰባት ወደቦችን የምታካልል ሲሆን፤ መነሻዋን ከባህር-ዳር አድርጋ ወደ መሀል ዘጌ በማቅናት እዚያ ስትደርስ መንገደኛ እና የጫነችውን ዕቃ አራግፋ ወደ አራት ሺህ የሚጠጉ አባራዎች ወደሚገኙበት <•ደቅ-ደሴት•> ትደርሳለች። አመሻሽ ላይ ቆንዝላ ገብታ የምታድረው ጣና-ነሽ ሁለት መዳረሻዎችን በማካለል በመጨረሻ በርበራ ትደርስና ተመልሳ ከውቢቷ ማረፊያዋ ባህርዳር ትመለሳለች። ረጅሙ የጉዞ መዳረሻዋ <•ዴልጌ•> ሲሆን፤ በአንደኛው ሞተሯ ብቻ በሰአት 11 ኪሎ-ሜትር የምትጓዘው ጣና-ነሽ ቢያንስ በግማሽ-ቀን ከረጅም መልህቅ መጣያ መዳረሻዋ ዴልጌ በሰላም ትደርሳለች። በውስጧ የጀልባዋ ካፒቴንን ጨምሮ ስድስት ሠራተኞችን ይዛ የምትጓዘው ጣና-ነሽ ያን ያህል የአደጋ አጋጣሚ አስተናግዳ አታውቅም። የጀልባዋ ክብደት ወደ አንድ መቶ ቶን ስለሆነ ጣና ላይ ነውጥ ይዞ ይህን የሚነሳን ማዕበል የሚቋቋም አቅም ይዛለች። አልፎ አልፎ በጣና-ነሽ ላይ ተፈጠረ የሚባል ችግር ቢኖር በጀልባው ተሳፍረው የማያውቁ ሰዎች ማዕበል ሲነሳ የሚያስመልሳቸው መሆኑ ብቻ ነው። በሰው ላይ ደረሰ የተባለው አደጋ በአንድ ወቅት የአእምሮ-ህሙማን መሆኑ ያልታወቀ አንድ መንገደኛ ድንገት ሳይታሰብ ወደ ሃይቁ ራሱን ከወረወረ በኋላ የነብስ-አድን ጥረት ቢደረግም ሳይገኝ ቀርቶ ከሰባት ቀን በኋላ አስክሬኑ በፍለጋ ሊገኝ ችሏል። በወቅቱ ፖሊስ የጀልባዋን ሠራተኞች እስኪጣራ ብሎ ቢያስርም በመንገደኞች የምስክርነት ቃል ነፃ ሊወጡ ችለዋል።
🚤•…….፦ሌላው እንደ-ችግር ከተቆጠረ ምናልባት በ1994 እና 1995 አመተ ምህረት በነበሩት ጊዜያት ውስጥ የኃይቁ ውኃ በከፍተኛ መጠን ጎድሎ ስለነበር፤ በጉድለቱ ሳቢያ  የጣና-ነሽ የሞተር ተርባይን ከአንድም ሶስቴ በመቀወሩ የተነሳ ወደ ሁለት ሚሊየን ብር የሚደርስ ወጪ ለጀልባዋ ህክምና ሊወጣ ችሏል። በዚያ ላይ ውኃው መጉደሉን መረጃ የሚነግር እና ዴፕዝ-ኢንዲኬተር የተባለው የውሃ ስምጠት መለኪያ መሳሪያ ስለሌለ እና ውኃ በሚጎድል ጊዜ አደጋ ሊፈጠር ይችላል በሚል ስጋት የጣና-ነሽ የጉዞ ፕሮግራም በተደጋጋሚ የተሰረዘበት አጋጣሚ አለ። በኢትዮጵያ በትልቅነቱ አቻ የሌለው የጣና-ኃይቅ ቢያንስ ከ100 ያላነሱ ገባር-ወንዞች በአመት አንዴ በሚገብሩለት ውሃ የሚሞላ ሓይቅ እንጂ፤ ከውስጥ የሚመነጭ ራሱን የቻለ ተፈጥሯዊ የውኃ-ጸጋ የለውም። ከባህር-ወለል በላይ በ1ሺህ 860 ሜትር ላይ የሚገኘው የጣና-ኃይቅ ከላይ እንደተጠቀሰው ከሌሎች ወንዞች አመታዊ ግብር ሰብስቦ ይሙላ እንጂ ምንም የውሃ ሃብት በራሱ የለውም። በዚህም የተነሳ የኃይቁ ትልቁ ችግር የሚባለው የደለል-ሙላት ነው። በአንድ ወቅት አንድ ጥናት እንዳለው….ጣና ከ18ሺ አመት ከ100 ሜትር ጥልቀት በላይ የነበረው ሲሆን፤ አሁን ግን በብዙ ሜትሮች ጥልቀቱ ቀንሶ በደለል አንገቱ ታንቋል። ከዚህ ቀደም ሓይቁ ባለቤት-አልባ ሆኗል ተብሎ ተደጋጋሚ ስሞታ ይቀርብበት የነበረ ሲሆን፤ ማንም እንደፈለገ ቆሻሻ ወደ ኃይቁ ቢደፋ፤ ሓይቁን ታኮ ማንም ባለ ገንዘብ ህገ-ወጥ ግንባታ ቢያካሂድ፤ አንዳንድ በካይ ነገሮች ወደ ውሃው ቢለቀቅ ተው-ባይ ያልነበረው ሲሆን፤ ይሄ አልበቃ ብሎ ባለፉት ጥቂት አመታት የእምቦጭ-ወረርሽኝ ከፍተኛው የኃይቁ ሥጋት እና የህልውናው ማክተሚያ እስከመሆን የደረሰ ሲሆን አሁንም ችግሩ አልተፈታም። እኛም ሆንን፤ መንግስት የተወሰነ ጊዜ ግርግር እንፈጥርና ወይም የፖለቲካ ከበሮ እንደልቅና የታመመውን ጣና መልሰን እንረሳዋለን። ባለፈው የተወሰነ እንቅስቃሴ ተሞከረና አሁን ደግሞ ፀጥ ተብሏል። እኛ ፀጥ ባልን ቁጥር ደግሞ እንቦጭ ግዛቱን ያሰፋል። እንደገና ደንግጠን ኡኡኡኡ …..እንላለን። እንዲህ እያልን ለአመታት ዘለቅን። መፍትሔው ግን ሩቅ ሆነ።  አሁንም ከአንድ ሰሞን ግርግር ውጪ ስለ-ሃይቁ ጤንነት የሚጠይቅም-የሚያነሳም የለም። ጋዜጠኛ ካሳሁን አሰፋ ስለ-ጣና እየተሟገተ በንዴት እና በብስጭት ህይወቱ አለፈ። አሁን ለ40 አመታት ያልተበገረችው ጣና-ነሽ ጀልባ እንዲህ የማርያም-መንገድ እስክትጠይቅ በእንቦጭ ታንቃለች። ህልውናዋም እያከተመ ይመስላል።  ከጥቂት አመታት በኋላ ግን እንቦጩ በዚህ ከቀጠለ <•ጣና-ነሽ•> ጀልባ ይቅርና <ጣና-ሓይቅ•> ስለመኖሩ ራሱ እንጃልኝ!!!!!!
Filed in: Amharic