>

ዋርካው ሲታወስ....! (ሙክታሮቪች)

ዋርካው ሲታወስ 1

(ሙክታሮቪች)

ፕሮፍ መስፍን እንባ ተናንቋቸው ያለቀሱበት‘ለት 


ፕሮፍ በአፍሪካ ህብረት የአዲሳባ ዩኒቨርሲቲ የቀድሞ ተማሪዎች ንግግር እንዲያደርጉ ይጋበዛሉ። ተገኝተው የሀይለስላሴን መንግስት ተቹ። “በኢትዮጵያ ሀላፊነቱ ያልተወሰነ የግል ድርጅት እንጂ መንግስት የሚባል ለህዝብና ለሀገር የቆመ ተቋም የለም!”
የሚለው የንግግራቸው ክፍል ጃንሆይን አስቆጣ። ወደ ጊንቢ አውራጃ በሹመት ሰበብ ሊያርቋቸው ሲሾሙ አልሄዱም። የጃንሆይን ትዕዛዝ አልቀበልም በማለታቸው ታሰሩ። የታሰሩበት ክፍል መፀዳጃው ንፅህና አልተመቸኝም ስለዚህ ምግብ አይግባልኝ ብለው የረሀብ አድማ ጀመሩ። ቀናት አለፉ።
ሹመቱን እንዲቀበሉ፣ እንዲሁም ምግብ እንዲወስዱ የሚያግባባቸው ቄስ ተላከባቸው። ከቄሱ ጋር ቁጭ ብለው ተግሳፅ እየተቀበሉ ሳለ አንድ የቄሱ ንግግር አልዋጥ አላቸው፣ ምሬት አንገሸገሻቸው።
ቄሱ ያሉት:—
“ልጄ መስፍን፣ አንተ ሁልጊዜ መቃወም ነው። አንዳንዴ ቻል አድርገህ እለፈው። ” እያሉ ሲገስፁ ፕሮፍ እንዲህ አሉ፣ ሳግ እያቋረጣቸው፣ መነፅራቸውን አውልቀው—
“አባ እኔ ሁሉን ነገር አልቃወምም። የማልፈው ነገር ብዙ ነው። ለምሳሌ ልንገሮት፣ በቅርብ ስሙን የማልነግሮት ታዋቂ ባለስልጣን አንዲት እናት ስራ ፍለጋ እሳቸው ቢሮ ገብታ ስትለምናቸው ለአቅመ ሄዋን ያልደረሰች ልጃቸውን ለአንድ ቀን ምሽት ለወሲብ ስለሚፈልጋት ይዛለት እንድትመጣ እና እሳቸው ከዚያ እንደሚቀጠሩ ነገራቸው።
ይህን ሚስጢር ለእኔ መጥተው ሴትየዋ ነገሩኝ። ይህን በደል፣ ይህን ነውር ለማንም ተንፍሼ አላውቅም። ችዬው ዝም አልኩ። ይኸው ዛሬ ለርስዎ ነገርክዎት።
እንግዲህ ከእርስዎ የምጠብቀው እንጦጦ ላይ ወጥተው ኡኡኡ የሀገር ያለህ ይላሉ ብዬ ነው። ይህ ግፍን የሚሰራ ሰው ባለበት ለሀገር የሚያስብ ህሊና ካለን ለህዝባችን መጮህ የለብንም ወይ?
እርስዎ ይኸን ግፍ ሰምተው አርፈው ይተኛሉ? “
እያሉ ፕሮፍ ቄሱን እንባ እየተናነቃቸው ሞገቱ።
ቄሱ አቀርቅረው ቀሩ።
ዛሬ ይህ ለህዝብ የሚያነባው አንደበታቸው ተዘጋ። የማያርፍ የማያሳርፍ ሞጋች አዕምሮአቸው ስራውን አቆመ። የኢትዮጵያ ተቆርቋሪ መስሪያቤት ተዘጋ። ኢትዮጵያ ዛሬ ነጠላዋን ዘቅዝቃ ማልቀስ አለባት። ኢትዮጵያ ፅናቱን ይስጥሽ
ዋርካው ሲታወስ 2
 
ፕሮፍ ጃንሆይን ስለ ሶማሌ ህዝብ መብት የሞገቱ‘ለት
ወቅቱ የአፍሪካ ሀገሮች ነፃ እየወጡ የነበረበት ወቅት ነበረ። ፕሮፍ የሶማሌን ህዝብ የአርብቶ አደርነት አኗኗር በጥልቀት ተዘዋውረው አዩት። የህዝቡን ኑሮ ተመለከቱ። የህዝቡን ሰራተኛነት፣ ታታሪነት ተመለከቱ። በጃንሆይ አስተዳደር የህዝቡ መብት እየተከበረ አለመሆኑንም አስተዋሉ።
 የሆነ ስጋት ብልጭ ብሎባቸው ለጃንሆይ ደብዳቤ ፃፉ።
በደብዳቤያቸው ላይ በአፅንኦት የገለፁት ኢትዮጵያውያን ሶማሌዎችን ነፃነትና መብት ማክበር አለብን። ህዝቡ የሚበደል ከሆነ ችግር ይገጥመናል። የኢትዮጵያን አንድነት ያናጋብናል። እንደምመለከተው የሶማሌ ህዝብን መብት እያከበርን አይደለም። አስተዳዳሪዎች ላይ የህዝቡን የአርብቶ አደርነት ኑሮ ባለማወቅ ንቀት ይታይባቸዋል። የመብት ጥሰትና ጭቆና ይስተዋላል። ይህ ተገቢ አይደለም።
ሶማሊያ ከኢንግሊዝ ነፃ ከወጣች። የእኛ ሀገር ሶማሌዎችን እኛ ነፃነታቸውን ካላከበርን ወደ አዲሷ ነፃ ሀገር እንቀላቀል የሚል ጉጉት ይመጣል። በባህልና በቋንቋ የሚመሳሰል ህዝብ አንዱ በአዲስ ሀገር ነፃነት ካገኘ ነፀነት ያላገኘው የሀገራችን ሶማሌ መንፈሱ ወደ ጎሮቤት ሀገር ይሸፍታል። ኢትየጵያ ህዝቧን እና ሰፊ ግዛቷን ታጣለች። አመፅ ይቀሰቀሳል። ቶሎ አስተዳደሩን እናስተካክል።
በማለት
ጃንሆይን በደብዳቤ መከሩ። ምክሩ ተግባራዊ ሳይሆን ቀርቶ ፕሮፍ የተነበዩት እየተንፏቀቀ መጣ። ሶማሊያ ኢትዮጵያን ለመውረር የተደፋፈረችው ኢትዮጵያ ውስጥ የኦጋዴን አመፅ አደፋፍሯት ነው። ቀልባቸው ወደ አዲሷ ሶማሊያ የማለለ ብዙ ሰዎች በጃንሆይ አስተዳደር የህዝብ መብት አለመከበሩን እያነሱ ወደ ሶማሊያ ለመጠቃለል በማሰብ ነው።
ፕሮፍ በወጣትነታቸው የሰጉት እና የተነበዩት ነገር ኋላ የኢትዮጵያ ችግር ሆኖ ቀጠለ።
ነገሩ አበበ ቶላ እንደገለፀው ነው።
ስለፕሮፍ አበበ ያለው እውነታ ይህ ነው።
“ነገር ግን በአብዛኛው ፕሮፍ መስፍን ከሚናገሯቸው ነገሮች መሬት ጠብ የሚል ነገር ካለ እርሱ በቃይ ነው!”
 
ዋርካው ሲታወስ 3
 
ፕሮፍ ለአክሊሉ ሀብተወልድ ገራሚ መልስ የሰጡ‘ለት
ፕሮፍ መስፍን የጃንሆይ አስተዳደርን ብልሹ አሰራር በይፋ ይተቹ ነበረ። ለተወሰነ ጊዜ የአዲስ ዘመን አምደኛም ነበሩ። ጠንካራ ትችታቸው የጎረፈባቸው አክሊሉ ፕሮፍን የጊሚራ አውራጃ አስተዳዳሪነት እንደታጩ ይነግሯቸዋል።
እኔ በማስተማር ስራዬ ተመችቶኛል፣ ለምን ሌላ ሰው አትፈልጉም ብለው ይጠይቃሉ።
እነ አክሊሉ ሀብተወልድ መልሳቸው
“ሀገር የማስተዳደር መንገዱን እያስታዳደርክ አሳየን፣ ያንተ ነገር ትችት ብቻ ከሚሆን ብለን ነው”
ይሉታል።
ፕሮፍ ምናላቸው?
“አንድ በአውሮፕላን እየተጓዘ ያለ ሰው የአውሮፕላኑ መንገጫገጭ ምቾት እየነሳው ቢቸገር፣ ይህን ቅሬታውን አውሮፕላኑን ለሚያበሩት ሰዎች ቢገልፅላቸው፣ አብራሪዎቹ የአውሮፕላኑን ሁኔታ አጥንተው እንደማስተካከል፣ ቅሬታ ያቀረበውን ተጓዥ ና አብራሪ ሆነህ የፓይለትነትን ቦታ ያዝ ሊባል አይገባም።”
በማለት መልሰውላቸዋል።
ፕሮፍ ወደ ቦስተን ሄደው ጂኦግራፈር የሆኑት በአክሊሉ ሀብተወልድ ምክር ነበረ። ፕሮፌሰርነት ማዕረግ እና የእድሜልክ የዩኒቨርሲቲ ቴኑር በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያገኙት በአክሊሉ ጊዜ ነበረ።
ፕሮፍ ደፋር እና ሞጋች መሆናቸው ማንም ያውቃል። የድፍረታቸውን ልክ ለማሳየት አንድ ምሳሌ እናንሳ—
በጃንሆይ ዘመን ለፕላን ኮሚሺን በምስራቅ አፍሪካ የተነሳ የአንበጣ መንጋ ሰብል ሊያጠፋ ስለሚችል፣ በፕላን ኮሚሽን ዝግጅት እንዲደረግ የዛንዚባርን (?) ሀገር ምሳሌ በማንሳት ምክረ ሀሳብ የለግሳሉ።
የፕላን ኮሚሽኑ አስተዳዳሪ መልስ:—
“እግዚያብሄር ይጠብቀን፣ እሱ ይሁነን እንጂ ምን ይደረጋል” የሚል መልስ ይሰጣቸዋል።
በዚህ መልስ የተበሳጩት ፕሮፍ አጭር ማስታወሻ ፅፈው ላኩ።
“እናንተ በሳይንስ የታገዘ መፍትሄ እንድታመጡ እንጂ የፃፍኩላችሁ። መልሳችሁ ይህ መሆኑን ባውቅ ኖሮ ለጳጳሱ ብፅፍላቸው ከእርስዎ የተሻለ ፀሎት እናገኝ አልነበረ ወይ?!”
ለኢትዮጵያ እንደሞገቱ አልፎላት ሳያዩ እርር እንዳሉ ሄዱ
ዋርካው ሲታወስ 4
 
 
መፅሃፍ የሚወጣውን ሀሳብ በአንዲት  አረፍተነገር ያነበብኩ‘ለት
ፕሮፍ ግዙፍ ሀሳብን በአጭሩ ቅንብብ አድርገው በማስፈር የሚደርሳቸው ሰው የለም።
ለምሳሌ ይህን ሀሳብ ተንትኖ ለመግለፅ አንድ መፅሃፍ አይበቃም።
“በትምህርትና በእውቀት ላይ ያልተመሰረተ #አገዛዝ፣ በነፃነትና በእኩልነት ላይ ያልተመሰረተ #የህዝብ ስብስብ፣ በእድገትና መሻሻል ላይ ያልቆመ #ኑሮ በየፈርጁ እና በየደረጃው #መክሸፍ እንደሚጠብቀው ታሪካችን ያሳያል”
አፍታቶ ለመፃፋ እጅግ ከባዱን ሀሳብ እንዲህ እንደነገሩ ወርወር ያደርጉታል። ከእውቀት ውቅያኖስ ይጨልፉታል!
ዛሬ አሳቢ አዕምሮአቸው ማሰቡን አቆመ
ዋርካው ሲታወስ 5
 
የአዕምሮ ጂምናስቲክ መምህሬን ያስታወስኩ‘ለት
 
ልዩነት እና አንድነት
በሀገራችን ፖለቲካ ስለ ልዩነትና አንድነት ብዙ ይባላል። ብዙ ይፃፋል። እንደሳቸው ቅልብጭ ባለ መልኩ ያስቀመጠ ግን የለም።
ልዩነት ያለ አንድነት፣ አንድነት ያለ ልዩነት ትርጉም የለውም ይላሉ። ልዩነትን የማይቀበል ወደ አንድነት አይደርስም የሚለውን በቀላል አቀራረብ እንዲህ አስቀምጠውታል።
አምስት የሁለት እና የሶስት ድምር ናቸው። 2 እና 3 ተደምረው 5 ለመሆን መጀመሪያ 2 እና 3 ለየብቻ ከነልዩነቶቻቸው መቆም አለባቸው።
2 የ 3ን የብቻ ህልውና መቀበልና ማክበር አለባት ተደምራ 5 እንድትሆን።
ሁለት የሶስትን ልዩነት ተቀብላ እስካላከበረች ድረስ አምስትን ስታስስ ትኖራለች እንጂ አታገኛትም። ወደ አምስት ለመድረስ መጀመረያ ወደ ሶስት መጠጋት ያስፈልጋል።
አንድነት ልዩነትን የሚያስር ወርቃማ ገመድ ሲሆን ልዩነት ውበት፣ አንድነት ሀይል ይሆናል።
ስለአንድ ሀገር ሲወራ ጭፍለቃ የሚመስላቸው ሰዎች የቤትን ትርጉም ስለሚስቱት ነው እንጂ ስለአንድ ቤት መናገር ቤቱ የተለያየ ክፍል የለውም ማለት አይደለም። በአንድ ሀገር በርካታ እምነት፣ ባህል፣ ቋንቋ፣ አመለካከት መኖር አለበት። ቤቱ ግን አንድ ነው።
ፕሮፍ አዕምሮአችን ማሰብን እንዲለምድ የአዕምሮ ጂምናስቲክ መምህራችን ነበሩ።
የሳቸው የአዕምሮ ጂምናስቲክ የትምህርት ክፍለጊዜ ዛሬ አበቃ
ዋርካው ሲታወስ 6
 
ከህሊናው ጋር የኖረውን ፕሮፍ ባሰብኩ ጊዜ
ፕሮፍን አንድ ወዳጃቸው የሚሸጥ ቤት አለ፣ ሴትየዋ ተቸግረው የሚሸጡት ነው ብለው እንዲገዛ ይጠይቁታል። ተስማምቶ ቤቱን ለማየት ይሄዳል።
ቤቱ ትልቅ ነው። ሴትየዋ ባለቤታቸው ታስሮ አልያም ሞቶ ይመስለኛል (?) ቤቱን ሽጠው ልጆቻቸውን እዚያ ግቢ ውስጥ ባለ ኩሽና በሚያክል ትንሽዬ ቤት ሊኖሩ ስለተገደዱ፣ ቤቱን ለቀው በዚያ ደሳሳ ቤት ውስጥ አገኟቸው።
የቤቱ ዋጋ ርካሽ ነበረ።
ፕሮፍ ቤቱን ቢፈልጉትም፣ መግዛት ቢችሉም፣ ከህሊናቸው ጋር ተሟገቱ።
ይህችን ሴትዮ ከቤቷ አውጥቼ በዚህ ደሳሳ ቤት ልጆችዋን ስታሳድግ እኔ ከዚህ ቤት ስወጣ እና ስገባ እያየኋት፣ የኑሮ መከራ ወርዶባት በሸጠችው ቤት መኖር ህሊናዬ ይቀበለዋል ወይ!?
ብለው ጠየቁ።
አይ! አልገዛም ብለው ሄዱ።
በማግስቱ አንድ ባለስልጣን ቤቱን ገዛው።
ፕሮፍ መስፍን የግል ቤት ሳይኖራቸው፣ የግል መሬት ሳይኖራቸው በሚወድዋት ሀገራቸው ላይ በኪራይቤት ኖረው አለፉ።
ከህሊናቸው ታርቀው፣ ከትራሳቸው ጋር ተስማምተው በሰላም ተኝተው በሰላም አሸለቡ ።
እኛ በሞታቸው ባዶነታችንን ታቅፈን ቀረን
ዋርካው ሲታወስ 7
 
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አድርባይ ሙህራንን ፕሮፍ ያሳፈረበትን ታሪክ ባስታወስኩ ጊዜ
ፕሮፍ ለሀቅና ትክክለኛ ሀሳብ አንገቱን እንደሚሰጠው ለስህተተኛ ሀሳብም እንዲሁ በመፋለም ለሚያምነው ሀሳብ በፅኑነት ይቆም ነበረ።
ይህ ታሪክ ድንቅ ታሪክ ነወ። ወቅቱ ደርግ ሶሺያሊዝምን ተጠቅሞ ባለሀብትን ለማዋረድ የሚሻበት ጊዜ ነበረ።
ቤት ወረሰ፣ መሬት ወረሰ። ባለሀብትን አዋረደ።
ይህ አልበቃውም።
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሙህራን ከግል ትቤቶች፣ ከእነ ሴንትጆሴፍ እና ሊሴ የዩኒቨርሲቲ መግቢያ ውጤት አምጥተው ወደ ዩኒቨርሲቲ የሚገቡ ተማሪዎች ላይ ውጤት መንግስት ይቀንስ የሚል ሀሳብ አቀረቡ። ከማትሪክ ውጤቱ ላይ ሁለት ነጥብ ይቀነስ።
ሀሳቡ በሀብታም ቤተሰብ ስለተማሩ የነሱን የዩኒቨርሲቲ ቦታ ዝቅተኛ ውጤት ላመጡ የደሃ ልጆች እንስጥ የሚል ነበረ መነሻው።
ፕሮፍ ይህን ሀሳብ አምርረው ተቃወሙ። በርካታ መከራከሪያዎችን አንስተው ሞገቱ።
ሙግተቸው:—
ቤተሰባቸው ሀብት ቢኖራቸውም፣ እነዚህ ጥሩ ውጤት ያመጡ ተማሪዎች ተግተው ተምረው ያመጡትን ውጤት መቀነስ ኢፍትሃዊ ጭካኔ ነው። የቤተሰባቸው ሀብት በትጋት የመጣ ቢሆንም፣ በወንጀል የመጣ ቢሆንም፣ ይህን ሳናውቅ፣ ምንም ይሁን ምን፣ ተማሪዎቹን በዩኒቨርሲቲ ተቀብለን ለሀገር ተቆርቋሪ ዜጎች አድርገን የማውጣት ሀላፊነቱ የእኛ ነው። በቤተሰባቸው ሀብት ሳይዘናጉ ተግተው ተምረዋል። በባለሀብት አባቶቻቸው ምክንያት እነዚህ ጎበዝ ተማሪዎችን ከትምህርት ማገድ ኢፍትሃዊነት ነው።
ብለው ሞገቱ።
ፀረ አብዮት ነው መስፍን ተብሎ ዘመቻ ተከፈተባቸው።
ኋላ ይህን ሀሳብ ሌሎች ሀገሮች ሰሙ። ሶሺያሊዝም የጨቋኝ መሳሪያ የሆነውን ፋብሪካ ለሀገር ጥቅም ይወርሳል ስትባሉ፣ የተማሪን ነጥብ ልትዘርፉ ነው ወይ? የሚል ስላቅ መጣ!
ደርግ ተረበሸ።
በሉ ይህን የእብደት እቅድ እንተወው ተባለ።
ፕሮፍ በሀሳብ አሸነፉ። ካድሬ ሙህራን ተዋረዱ።
ዛሬ ሞጋች ሰው አጣን
መካሪ አጣን
ተቆጪ አጣን
ዋርካው ሲታወስ 8
 
በ97 ምርጫ ወያኔው የቃሊቲ ጠባቂ ፕሮፍን በጥፊ የመታቸውን ነገር ባሰብኩ ጊዜ
ወያኔ ከቅንጅት መሪዎች ጋር አሰራቸው። ቂሊንጦ በር ላይ እስረኞችን የሚያስገባው ወያኔ ፕሮፍን “መንግስታችንን በህገወጥነት እንዲወድቅ ቢያሴሩም አልተሳካም” ብለው በጥፊ መታቸው። ፕሮፍ ምንም ሳይመስላቸው በንቀት አዩትና:
“አንተ እኔን ትመታኝ? እኮ አንተ እኔን መታኸኝ?” ብለው ሳቅ አሉ።
ወያኔው ምን አለ?
“እርስዎን ለመምታት የግድ የፕሮፌሰር ክንፈ አብረሃ እጅ መሆን አለበት እንዴ” ብሎ ሳቀ። ፕሮፍ ክንፈ አብረሃ ከፕሮፍ ጋር የሚግባቡ ወዳጆች ነበሩ። ፕሮፍ ሰውን በሀሳብ እንጂ በዘር አያስቡትም እንደ ወያኔው ደንቆሮ።
ፕሮፍ ወደ መታሰሪያ ክፍላቸው አመሩ። አንድ የወያኔ ደንቆሮ መታኝ ብለው አላዘኑም። በዚህች ሀገር ተገረሙንጂ!
ጥሩው ነገር የወያኔን ተንኮታክቶ መቃብር መግባት ባያዩም። ከ4 ኪሎ ተባረው፣ መቀሌ መሽገው፣ ሲወራጩ አይተዋል።
በዚህም እንፅናናለን።
ይቀጥላል
Filed in: Amharic