>
5:16 pm - Saturday May 24, 6217

ከፍ ሲል ሰንደቁ የሚጠሉት ወደቁ...!!! (ታርቆ ክንዴ)

ከፍ ሲል ሰንደቁ የሚጠሉት ወደቁ…!!!

ታርቆ ክንዴ

የጋራ ምልክት፣ በደምና በአጥንት ከፍ ያለ፣ ለዘለዓለም ከፍ ብሎ የተሰቀለ የማይወርድ ኅብረ ቀለም፤ ለክበሩ ደም የተከፈለለት፣ ለዝናው ከዓለም እስከ ዓለም የተዘመረለት፣ ለአሸናፊነቱ የተመሰከረለት ጨርቅ አይሉት ወርቅ፣ ከወርቅም ወቅር ልብን በኩራት የሚሰርቅ፣ ጭቆናን የሚያላቅቅ ልዩ ስጦታ፡፡  በምድር ሲነቅሉት በሰማይ ይሰቀላል፡፡ ከመሰሶው ሲያወልቁት በሸንተረሩ ያዩቷል፡፡ ከምድር ሲቀብሩት  በወንዙና በጋራው ሳይቀር ከሰማይ እስከ ምድር ተዘርግቶ ይታያቸዋል፡፡ ማጥፋት የማይቻል ውብ ስጦታ፡፡
የጥፋት ውኃ ሲጎድል ፍጥትረትን ሁሉ እንዲያድን ስልጣን ለተሰጠው ለታላቁ ኖኅ የምሥራች ይሆን ዘንድ የተሰጠው በዚያች ውብ ሀገር ለዘላለም እንዳይጠፋ ተደርጎ ቃል የተገባለት ነው ይላሉ አባቶች፡፡ ቀስተ ዳመና፣ ስንደቅ ዓላማ፣ ባንዲራ ይሉታል ኢትዮጵያውያን፡፡ በእርግጥ ባንዲራ ኢትዮጵያዊ ስም አይደለም፡፡  የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ክርስትና በሚከተሉ የገጠሪቱ ኢትዮጵያ ነዋሪዎች ደግሞ የማርያም መቀነት ይሉታል፤ አረንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማ ከቀስተ ዳመናው ጋር አስተሳስረው፡፡
ኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ዓላማቸውን ከምንም በላይ ያከብሩታል፡፡ ሳይሰስቱ ይሞቱለታል፤ ሳያመነቱ ለክብሩ ይኖሩለታል፡፡  ቀደም ባለው ጊዜ አሁንም ኢትዮጵያዊነት በልባቸው እንደ እሳት ግለት ባለው ኢትዮጵያውያን በባንዴራው አምላክ ተብሎ እግሩን የሚነቅል አንዳችም ሰው የለም፡፡ በባንዴራው አምላክ ከተባለ ለበቀል የሾለች ምላስ ትታጠፋለች፤ ለጥል የቆመ ጦር ይመለሳል፤ ለግዳይ የተዘጋጄ ቃታ ይዘጋል፡፡ በባንዴራው አምላክ የመጨረሻው ግዝት ነው፡፡ ይሄን አልፎ የሚሄድና ለበቀል የሚነሳ ሀገሩን የከዳ ከእሴቱ የወጣ ስለሚሆን የባንዴራው ስም ከተጠራ ክፉ ነገር ሁሉ ይጠፋል፡፡ በእርግጥ ኢትዮጵያውያን እንኳን ባንዴራቸውን ንጉሣቸውንም በእጅጉ ያከብራሉ፡፡ በንጉሡ አምላክ ሲባሉም ክፉ ነገር አያደርጉም፡፡
ከኢትዮጵያ በቀር በሰማይ ላይ ሰንደቅ ዓላማው የሚታይለት ሀገር የለም፡፡  የሌሎች ሀገራት ባንዴራ ከፍ የሚለው ከአደባባይ ላይ በቆመ መሰሶ ወይም በረጅም ሕንጻ  ላይ ብቻ ነው፤ የኢትዮጵያ ግን ከሰማይ ወደ ምድር ወይም ከምድር ወደ ሰማይ ይዘረጋል፡፡ ከፀሐይ ጋር ተዘርግቶ ለዓለም ይታያል እንጂ፡፡  ይህ መኩሪያና መመኪያ የሆነ ሰንደቅ ዓላማ ንግሡ ከዙፋኑ ወጥቶ በሕዝብ አደባባይ ሲታይ በሰረገላው ላይ ይውለበለባል፡፡ በመኳንቱና በመሳፍንቱ ካባ ሳይቃር ይታያል፡፡ ወታደሩ ለግዳጅ ለእናት ሀገሩ ሲዋደቅ ሰንደቅ ዓላማውን ከፊቱ ያስቀድማል፡፡ ኢትዮጵያውያን በልባቸው ብቻ ሳይሆን በልብሳቸውም ያጌጡበታል፡፡ የቤታቸውን ቀለም በባንዴራው ያሰምሩታል፡፡ ቤተ እመነታቸውን በሰንደቅ ዓላማቸው ያጌጡበታል፡፡ ቡና በሚጠጡበት ስኒ ሳይቀር ሰንደቅ ዓላማው አይለያቸውም፡፡ ይህ ሁሉ ነገራቸው የሆነው ሰንደቅ ዓላማ ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በዓመት አንድ ቀን የሰንደቅ ዓላማ ቀን ተብሎ እንዲዘክሩት እየተደረገ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማውን በዓመት አንድ ጊዜ በየአደባባዩ እያውለበለቡ ያክብሩት እንጂ የነበረው ታላቅ ክብር ግን የቀነሰ ይመስላል፡፡ እርሱን እየቀደሙ በአደባባዩ የሚውለበለቡ የሰፈር አርማዎች እየበዙ መጥተዋልና ነው፡፡
የኢትዮጵያን የሰንደቅ ዓላማ ታሪክና ክብር ምን ይመስላል? 
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የሥነ ጽሑፍ መምህሩ ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጋር ቆይታ አድርገናል፡፡ ‘‘የኢትዮጵያውያን ሰንደቅ ዓላማ ለኖኅ ቃል ኪዳን ተሰጠው ተብሎ ይታመናል’’ ነው የሚሉት ፕሮፌሰር ፍቅሬ፡፡ ሰንደቅ ዓላማ ቅደመ ሳባ በነበረው ቅዱስና እና ንጉሥ ካህን እስያኤል እንደተጀመረ ነው የተናገሩት፡፡ እስያኤል  ስመ መንግሥቱ ሰንደቅ ዓላማ ነበር፡፡ ወላጆቹ ኤሴ ወይም አፄ ይሉት ነበር፡፡  እስያኤል የክህነት ስሙ ነው፡፡ ይህ  ካህንና ንጉሥ የሆነ ታላቅ ሰው ኢትዮጵያን እያስተዳደረ አህጉረ እስያን አስገብሮ የራሱን ገዥ ሾሞ እንደተመለሰም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ነግረውኛል፡፡
የዓለማችን ታላቁ አህጉር እስያም በኢትዮጵያዊ ንጉሥ ስም እንደተሰዬመ ነው የነገሩኝ፡፡ እስያኤል በዚያች ምድር ዘምቶ ድል ሲነሳ ምድሩ እስያ ይባል ብሎ እንዳዘዘ ትዛዙ ተፈፀመ፡፡ ዛሬም እስያ እንለዋለን፡፡ በዮቶፕ ኢትዮጵያ ተባለችም ይላሉና ምሁራን፡፡ ኢትዮጵያ ኃያል ስለነበረችና ስልጣኔዋ በመላው አፍሪካ አጥለቅልቆ ስለነበር አፍሪካ በሙሉ ላዕላይ ኢትዮጵያና ታህታይ ኢትዮጵያ ተብሎ ይጠራ እንደነበርም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ነግረውኛል፡፡ እንግዲህ ይህ ታላቅ ንጉሥ ለአባቱ ለኖኅ የተሰጠውን ቀስተ ዳመና እርሱ አውርዶ መገለጫ እና ምልክት አደረገው፡፡ እስያኤል አረንጓዴ፣ ቢጫና ሰማያዊ ቀለም መርጦ ትዕዛዘትን እንዳሰፈረም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ተናግረዋል፡፡ አረንጓዴው ልምለሜያችንና ምድራዊነታችን፣ ቢጫው መንፈሳዊነታችን፣ ሰማያዊ ደግሞ ሰማያዊነታችን የሚገልፅ ነው ብሎ እንዳስቀመጠውም ፕሮፌሰሩ ተናግረዋል፡፡ በኋላ ግን ሰማያዊው ቀርቶ ቀይ ተተካበት፤ ይህም ደምና አርበኝነትን የሚወክል ተደረገ ነው የሚባለው፡፡  ሰንደቅ ዓላማ የተባለውም በቅዱሱ ንጉሥ እስያኤል ስመ መንግሥት እንደሆነ ነው የሚናገሩት፡፡ ይህን ሰንደቅ ዓላማ በሥራው፣ በጉዞው ያላደረገ ሁሉ እንዲቀጣ ትዕዛዝ ተላልፎ እንደነበርም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ያስረዳሉ፡፡
የራስን ሰንደቅ ዓላማ መቅረፅና በማውለብለብ በዓለም ታሪክ የመጀመሪያው ሳይሆን እንዳልቀረና ለዓለምም ያስተማሩ ኢትዮጵያውያንን ሊሆኑ እንደሚችሉ ነው ፕሮፌሰሩ የተናገሩት፡፡ ታላቁ ንጉሥ እስያኤል ሰንደቅ ዓላማ ከማበጀቱም ባለፈ ‘‘አንድ ንጉሥ ከአስር ዓመታት በላይ መግዛት የለበትም’’ የሚል አቋም እንደነበረውም ነው ያብራሩት፡፡ ይህንም በራሱ ላይ አሳይቷል፡፡ አስርት ዓመታትን ከገዛ በኋላ ለተከታይ ንግሥ ዙፋኑን አስረክቧል፡፡ አሁን ላይ ሰለጠነ የሚባለው ዓለም የሚመጻደቅበትን ፕሬዘዳንታዊ ሥርዓትና የስልጣን ዘመን በምርጫ መገደብ እርሱ  ሲተገብረው ነበር፡፡ ንጉሱ ቅዱስ በመሆኑ ለፈጣሪው ቅርብ ነበርና ዕድሜው ረጅም እንደነበርም ይነገራል፡፡ ዕድሜውን የሚያረዝም ከዛፍ ስር የምትፈልቅ ልዩ ውኃ ይጠጣ ነበር፡፡ ዙሪያውንም ብርታትና ጥንካሬ በሚሰጡ ለእርሱ የተፈቀዱ ድንጋዮች ይከበብ ነበር፡፡ ፈጣሪውንም ስለሚያከብርና ስለሚገዛ ረጅም ዕድሜ እንደሚያኖረው ቃል ገብቶለት ነበር፡፡ ንጉሡም ከአራት መቶ ዓመታት በላይ እንደኖረ ነው የሚነገርለት፡፡ በዕድሜው እርዝመት ምክንያት አስርት ዓመታትን ገዝቶ የተውው ዙፋን ዳግም ደርሶት ኢትዮጵያን ንጉሠ ነገሥት ሆኖ እንዳስተዳደረም ፕሮፌሰር ፍቅሬ ተናግረዋል፡፡
እስያኤል ጠቢብ ነበር፡፡ በጥበቡ የዛሬውን ዓለም በዚያን ጊዜ ኖሮታል፡፡ የማይታወቅ አሳውቋል፡፡ መመራመርና ተፈጥሮን መመልከት ይወድ ነበርና አንድ ቀን ጉንዳንና ምስጥ ሲናከሱ ተመለከተ፡፡ በንክሻውም ጉንዳን አሸነፈ፡፡ ሁለት ትንንሽ ነብሳት ተናከሱ ብሎ ዝም አላለም፡፡ ጉንዳንን ከምስጥ ጋር አዳቅሎ የተለዬ ፍጡር መፍጠር ቻለ ይባልለታል፡፡  እፅዋትንም አዳቅሎ የተሻለ ዕፅዋት መፍጠር ችሏል፡፡ ዛሬ ላይ የምዕራቡ ዓለም የእኛ ናቸው ብሎ የሚመጻደቅባቸውን ሁሉ እርሱ ከብዙ ሺህ ዓመታት በፊት ሠርቷቸዋል፡፡  ይህ ንጉሥ ረጅም ዓመታትን በምድር ላይ መኖር ሰለቸኝ በማለት የምንጯን ውኃ አቆመ፡፡ ድንጋዮችንም ከአጠገቡ አነሳ፤ ለሞትም ተዘጋጄ፡፡ ምድር ይብቃኝ ፈጣሪ ወዳለበት ወደሰማይ ልሂድ ብሎ ፈቀደ፡፡ ቀኑም ደረሰ ወደ ተመኜውም ሄደ፡፡ ሞትን ቀመሰ ይባላል፡፡
‘‘ጀግኖች አርበኞች ለሰንደቅ ዓለማው ሲሉ ተዋድቀዋል’’ የሚሉት ፕሮፌሰሩ ሰንደቅ ዓላማው የሚወክለው ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያውያንን መሆኑንም አብራርተዋል፡፡ አርበኞች በጭንቅ ጊዜ እንደሚሞቱ ሲያውቁት ሰንደቅ ዓላማውን ለብሰው ሞትን ይቀበላሉም ይባላል፡፡ ስለ ሰንደቅ ዓላማው ኖረው፣ ስለ ሰንደቅ ዓላማቅ ሞተው፣ ሰንደቅ ዓላማውን ለብለሰው የሚቀበሩም አሉ፡፡ ሰንደቅ ዓላማው ወደቀ ማለት ኢትዮጵያ ወደቀች ማለት ነውም ይላሉ፡፡ ለምን ካሉ ወካይዋና መገለጨዋ ነውና፡፡ ዳሩ ግን ሰንደቁም ኢትዮጵያም አይወድቁም፡፡ በዘመነ ኃይለሥላሴ ወራሪው ጣልያን የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ አውርዶ የራሱን ሰቅሎ ነበርና አርበኞች በትግላቸው የጣልያንን ሰንደቅ ዓላማ አውርደው መልሰው ሲሰቅሏት በዚያ ዘመን የነበሩ ኢትዮጵያውያን ሰውን ሲገዝቱ ‘‘ወድቃ በተነሳችው ሰንደቅ ይዤኃለሁ’’ ይሉ እንደነበርም ፕሮፌሰሩ ነግረውኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን አርንጓዴ፣ ቢጫ ቀዩን ሰንደቅ ዓላማ ከሌላው አርማ ጋር ማቀላቀል እንደማይገባና ልዩ ክብር መስጠት እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
ሰንደቅ ዓላማ ሲወርድና ሲወጣም ከመቀመጫ የሚነሳው፣ ሲሄዱ የነበረው የሚቆመው ልዩ ክብር ስለሚሰጠው ነው፡፡ ‘‘ሰንደቃችን እንኳን እኛ ግመሎቻችንም ያውቁታል’’ የሚባለውም ልዩ ክብርና ልዩ ተምሳሌ ስለሆነ ነው፡፡ ነጻ አውጭ ነን እያሉ የራሳቸውን አርማ ይዘው የሚመጡትንና መገለጫውንና ኢትዮጵያውያንን አንድ የሚያደርገውን መለዬት እንደሚገባም ፕሮፌሰሩ መክረዋል፡፡ ‘‘ነጻ አውጪዎች ነን የሚሉት ወይም ዛሬ ላይ ክልል የሚባለው የሚጠቀምበት ሰንደቅ አካባቢውን እንጂ ሁሉንም ስለማይወክል ለአረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ ልዩ ክብር ያስፈልጋል’’ ነው ያሉት፡፡ የየአካባቢዎች አርማዎች ቢኖሩ እንኳን አረንጓዴ ቢጫ ቀዩ ሰንደቅ አላማ ካፍ ብሎ ሌሎቹ ዝቅ ብለው መውለብለብ እንዳለባቸው ያስረደሉ፡፡ እንደምሳሌ የአሜሪካውያንን ሰንደቅ ዓላማ ያነሱት ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ‘‘ለእያንዳንዳቸው ግዛት የራሳቸው መለያ አላቸው፤ በየመስሪያ ቤታቸውና በየአደባባዩ ግን የጋራ የሚያደርጋቸውን ሰንደቅ ዓላማ ከፍ አድርገው ያለውለበልቡታል’’ ነው ያሉት፡፡ ሰንደቅ ዓላማ አንድ የሚያደርገንና የሚያሰባስበን ነውም ነው ያሉት፡፡ በአንዲት ሀገር ውስጥ አንድ ሰንደቅ ዓላማ ብቻ ነው ሊኖር የሚችለውም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሰንደቅ ዓለማ  ቀን ዛሬ እየተከበረ ነው፡፡ ሰንደቅ ዓላማው በቀኑ ታስቦ ይዋል እንጂ፡፡ በጦር ግንባሩ፣ በመሥሪያ ቤቱ በየአደባባዩና በሁሉም ስፍራ ሳይታሰብ የዋለበት ቀን ያለ አይመስልም፡፡ በደም ከፍ ስላለ በምንም ዝቅ አይልምና፡፡ ከፍ ሲል ሰንደቁ የናቁት ይወድቃሉ፡፡ ያከበሩት ይከብራሉ፡፡  በሰማይ የሚውለበለብን ሰንደቅ ዓላማ በምድር ሆኖ ማውረድ አይቻልም፡፡ በየሸንተረሩ የሚታይን ምልክት ማዳፈን አይታሰብም፡፡ ደምና አጥንት፣ ፍቅርና እንድነት፣ ነጻነትና ተምሳሌት የተገናኙበት ነውና ከፍ ብሎ ነበር፤ ከፍ ብሏል፡፡ ከፍ እንዳለ ይኖራል፡፡
እንኳን ለሰንደቅ ዓላማ ቀን አደረሳች!
Filed in: Amharic