>

ቀናትን በሰቆቃ  (ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ)

Dr. Bekalu Atnafu

ቀናትን በሰቆቃ 

ዶ/ር በቃሉ  አጥናፉ  ታዬ


መንግስት ተብሎ የተሰየመ አካል ባለበት ሀገር ዛሬም እንደ ትናንቱ ዜጎች በኦሮሚያ እና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በሰቆቃ እንደሚኖሩ ይታያል፣ ይሰማል፡፡

ታላቁ ፈላስፋ አሪስቶትል እንዲህ ብሏል፡ ‘’Educating the mind without educating the heart is no education at all, Aristotle’’ አዕምሮዓዊ ብቃት ወይም አዕምሮዓዊ ስልጡንነት ብቻውን ፋይዳ የለውም፡፡ የአሜሪካውን የህዋ የምርምር ጣቢያ (ናሳን) ወይም ታላላቅ የምርምር ተቋማትን የሚያስደምም ወይም የሚያናውጥ ዕውቀት ቢኖረን የሰዎችን ስሜት መረዳት ካልቻልን ስልጡንነታችን ከንቱ ነው፡፡ ዜጎች ሲጎዱ፣ ሲሞቱ፣ ሲፈናቀሉ፣ ምንም አይነት ጉዳት ሲደርስባቸው በቀና መንፈስ ከተጎዳው ተጠቂ ጎን ሁነን የተጎጅውን ስሜት አለመረዳት ከሰው-ተራ እንድንወጣ ያደርገናል፡፡

ስሜት ከፈረጠጠት አዕምሮ የሚያመነጭ እሳቤ የጨነገፈ ነው፡፡ ሰውን ማዕከል ያላደረገ እና ለሰው ህይወት ዋጋ የማይሰጥ አመራርም ቅቡልነቱ ከንቱ ነው፡፡ የቤተሰቦቻቸውን አባላት በሞት የተነጠቁባቸው ቤተሰቦች፣ ቤታቸው ፈርሶባቸው በየ ቤተ-ክርስቲያኑ ተጠልለው ባሉበት ሁኔታ ስለ ልማት፣ ስለ መዝናኛ ማሰብ እና ይህን ትኩረት አድርጎ መስራት ከሰው ልጅ ህይወት ይልቅ ለቁሳዊ ነገር ዋጋ እንደምንሰጥ ማሳያ ነው፡፡ ሰውን ያህል ፍጡር ቀናትን በሰቆቃ እያሳለፈ ስለ ገበታ ለሀገር፣ ስለ ፓርክ ማውራት ፌዝ ይመስላል፡፡ በማንነታቸው የሰቆቃ ህይወትን ለመምራት የተበየነባቸውን ዜጎች ጩኸት ዛሬም ድምፀቱ እየተሰማን እያለ ሰምተን እንዳልሰማን፣ አይተን እንዳላየን መሆን ስለ ዜጎች ብቻ ሳይሆን ስለ ቦታው ክብር እንደሌለን ማሳያ ነው፡፡ የተጎዳን ስሜት ቁሳዊ ነገር አያክመውም፣ የደማን ልብ አፋዊ ተረቶች አያቀኑትም ዳሩ ግን በተሰበረ ልብ፣ በቀና መንፋስ እና በእውነተኛ ስሜት ሁነን የተጎዳን ህሌና ስነ -ልቦናዊ እና መንፈሳዊ ፈውስ ልንሰጠው ይገባ ነበር፡፡ 

Filed in: Amharic