>
5:18 pm - Monday June 14, 4055

የቤተኛው ፕሬዝዳንት ሰሞነኛው ጉብኝት...?!? (ሰይፉ ታሪኩ)

የቤተኛው ፕሬዝዳንት ሰሞነኛው ጉብኝት…?!?

ሰይፉ ታሪኩ


የሃያ ዓመቱ የኢትዮ-ኤርትራ የጠብ ግድግዳ “ፈረሰ” መባሉን ተከትሎ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ አፈወርቂ እና የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ወዳጅነት ቀጥሏል፡፡ አሥመራ እና አዲስ አበባ ላይ የነበረው የግንኙነታቸው መቼትም ጎንደርን፣ አርባምንጭን፣ መቂንና ዝዋይን አልፎ አሁን ደግሞ ጅማ ደርሷል፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ባለፉት ሁለት ዓመታት ወደ ኢትዮጵያ የመጡባቸው ጊዜያት ከይፋዊ ጉብኝትነታቸው ይልቅ አጋጣሚያዊ ክሱትነታቸው እየጨመረ መጥቷል፡፡ ይኽ ደግሞ ኢትዮጵያን የረገጠው ኮቴያቸው ኹሉ ፖለቲካዊ ትርጉም በእጅጉ እንዲጎናጸፍ ምክንያት ኾኗል፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድም ቢኾኑ አሥመራ የተመላለሱባቸው ወቅቶች ከተጤኑ የሁለትዮሽ ጎረቤታዊ ጉዳይን ከማሳለጥ የገዘፈ ዓላማ አይታጣላቸውም፡፡ የኾነው ኾኖ ከወራት በፊት የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ማኅበረሰቡን የወል ድንዛዜ ውስጥ በከተተበት ጊዜ ሳይቀር ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ “የመቂ መስኖን ለመጎብኘት” ተጣድፈው የመጡበትም ኾነ ጠ/ሚኒስተር ዐቢይ ከቅርብ ጊዜ በፊት ሳዋን ጎብኝተው የተመለሱበት አመክንዮ ከዜና ማጣፈጫ የተሻገረ ዒላማ እንዳለው መጠርጠር ነፍስ ያወቀ ዜጋ ሁሉ ግዴታ ነው፡፡

ኢሳይያስ ከመስከረም 30 ማግሥት

የኢትዮጵያ ነገር ግራና ቀኙን እያስፏጨ ቀጠለ፡፡ ሕግ ፍተላው፣ ሴራ ትንተናው ተጠናከረ፡፡ የመስከረም 25 ወ30 ፖለቲካ ላንዱ መዛቻ፣ ለሌላው መገዘቻም ኾነ፡፡ ተግባር ጥያቄ ኾኖ በኖረባት ሀገር “መርኅ” ወደፊት መጣ፡፡ የጌታቸው ረዳ ግለት፣ የአስመላሽ ወ/ሥላሴ ጩኸት በዛ፡፡ የሕዝቅኤል ገቢሳ ፉከራ፣ የጸጋዬ አራርሳ ሽለላ ናረ፡፡ የህወሓት መግለጫ፣ የፌዴራሊስት ኃይሎች ሩጫ ጨመረ፡፡ በዚህ በኩል ደግሞ የብርሃኑ ጁላ መድፍ፣ የእንዳሻው ጣሰው ሰልፍ ሥራ በዝቶበት ከረመ፡፡ መስከረም 25 ወ30 አልፋና ኦሜጋ ነች ተባለ፡፡ ከሳምንት በፊት “ሕገወጥ” የተባለው አካል፣ ከሳምንት በኋላ “ዕውቅና ሰጪ” ኾነ፡፡ የአዲስ አበባው መንግሥት አጥሩን አጠባበቀ፡፡ እንኳን ሁከት ርችት ከለከለ፡፡ መስከረም 25 ኾነ 30 ግን የታሰበው ኹሉ ሳይኾን አለፈ፡፡ ኢሳይያስ አፈወርቂም “ሕገወጥ” ለተባለው መንግሥት የመጀመሪያውን ይፋዊ የሥራ ጉብኝት ለማድረግ ተከሰቱ፡፡

የህወሓት ቤት ልመናና ጩኸት

በኤርትራው መሪ ድርጅት ህግደፍ እና ህወሓት መካከል ላለፉት ሁለት ዐሠርት የነበረው መቋሰል ድርጅቶቹ አሁን ባላቸው አሰላለፍ ላይ ትልቁን ድርሻ ይወስዳል፡፡ በአቶ መለስ ዜናዊ ይመራ የነበረው የኢትዮጵያ መንግሥትም ቢኾን ኤርትራዊያንን “የዓይናችሁ ቀለም አላማረኝምና ውጡልኝ” ካለበት ጊዜ አንስቶ እስከመጨረሻው ደቂቃ ድረስ ኤርትራ ከከባቢውም ኾነ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንድትነጠል ብርቱ ጥረት አድርጓል፡፡ ነገሮች ሁሉ ግን እስከ ፍጻሜው ቅርጻቸውንና ይዘታቸውን ይዘው አልዘለቁም፡፡ ጠ/ሚኒስትር መለስ ለሞት፣ ህወሓትም ለውድቀት ተዳረጉ፡፡ ፕሬዝዳንት ኢሳይያስና ህግዴፍ ግን ቀጠሉ፡፡ የሃያ ዓመት ቂም ማወራረጃው ሰዓት ደረሰ፡፡ ኢሳይያስ “ጠቤ ከወያኔ እንጂ ከኢትዮጵያ አይደለም” አሉ፡፡ የአማርኛ ጾማቸውንም በአደባባይ ፈቱ፡፡ “ኢትዮጵያ እና ኤርትራ ሁለት ናቸው አትበሉም” አሉ፡፡ የአያቴ አጽመ ርስት ነው ወዳሉት ጎንደርም አቀኑ፡፡ ሌላም ሌላም…
ይኽ ሁሉ ሲኾን ግን ኢሳይያስ የህወሓቷን ትግራይ ሊረግጧት አልወደዱም፡፡ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በአንድ መድረክ ላይ “ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ በመቀሌ ጎዳናዎች ላይ ዎክ ማድረግ ይፈልጋሉ” ብለው ቢናገሩም ትንቢቱ ይፈጸም ዘንድ ጊዜው ገና ኾነ፡፡ እርግጥ ነው ህወሓቶችም ኢሳይያን እንደመልዐክ መቀበል፣ ኢሳይያስም ህወሓቶችን እያጓጉ መቅረት የቆየ ልማዳቸው መኾኑን ትግራዊያኑ ጸሐፍት ነግረውናል፡፡ ይኼኛው ግን በዓላማም በአመክንዮም ከበፊቱ ይለያል፡፡ የጠነነ ቂም፣ የከረረ የበቀል ፍላጎት እንዳለበት ያስታውቃል፡፡ ምናልባትም የጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አርቆ ተመልካችነትን ማሳያ ከሚኾኑ ጉዳዮች መካከል ህወሓት የሥልጣናቸው ዘላቂ እንቅፋት መኾኗን ተረድተው በሲመታቸው ማግሥት ከኢሳይያስ ጋር ለመታረቅ የሄዱበት ርቀት ነው፡፡ በአራዶች ቋንቋ ዐቢቹ “ህወሓትን ገትሮ ለመያዝ” ከኢሱ የተሻለ አማራጭ አልነበረውም፡፡

ህወሓትም ቢኾን ቀላል ኾና አልተገኘችም፡፡ ከኢሳይያስ ጋር ሠላም ለማውረድ ያልመዘዘችው ካርድ የለም፡፡ ለኤርትራ ነጻነት ታጋዮቿን ስለመገበሯ ደስኩራለች፤ በኤርትራ ሉዓላዊነት እንደማትደራደር በአጽንዖት ተናግራለች፤ ህወሓትና ህግደፍን ለማስታረቅ ሽማግሌ አቋቁማለች፤ ማኅበረ አግኣዚያን ብላ ከዘመናት በፊት የከሰመውን “የትግራይ ትግሪኝ” ሀገር ለመፍጠር ተንተፋትፋለች፡፡ ይኽ ኹሉ ግን ጠብ አልል አለ፡፡ ቢኾንም ተስፋ አልቆረጠችም፡፡ ፊታውራሪ ጌቶቿን ወደፊት እያመጣች ለመለማመን አላመነታችም፡፡ አቶ ጌታቸው ረዳ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ወደተለያዩ የኢትዮጵያ ክልሎች መመላለስን አስመልክቶ “ወደ እኛ ቢመጡ እኮ አስተርጓሚ አይቸገሩም ነበር” እስከማለት ደርሷል፡፡ ከጥቂት ወራት በፊት ደግሞ አቶ አባይ ፀሐዬ “የኤርትራ ሕዝብ ወንድማችን ነው፣ ከኤርትራውያን ጋር እንደቀድሞው የቅርብ ግንኙነት እንፈልጋለን፣ የትግራይ ሕዝብ ቅያሜውን ረስቶታል፣ ህወሓትም ረስቶታል፣ ምናለ ፕሬዚዳንት ኢሳይያስም ቢረሱት” ሲል ተማጽኗል።

ይኽ ኹሉ የልመና ቄጤማ ተጎዝጉዞም ቢኾን “ኢሱ ጭሱ” ፊቱ ሊፈታ አልቻለም፡፡ ይባስ ብሎ የኢትዮጵያን ማዕከላዊ መንግሥት ዙፋን ለመገዳደር የሚሻ ማንኛውንም ኃይል አንታገስም፣ እጃችንንም አጣጥፈን አንቀመጥም እስከማለት በቃ፡፡ አሁን የህወሓት ልመና ወደ ጩኸት ተቀየረ፡፡ ሃያ ዓመት የተደፈረው ሉዓላዊነት በግዙፍ አጀንዳነት ተነሳ፡፡ ባድሜን አስረክቦ ሕዝቡን በስላቅ ያጨፈረው ሰው “ሀገሬ ተደፈረች አለ”፡፡ ስዬ አብርሃ ሳይቀር “ኢሳይያስ ስለሰው ቤት ጉዳይ መፈትፈቱን ትቶ የራሱን ቤት ያተካክል” ሲል አስጠነቀቀ፡፡ “እናንት የህወሓት ሰዎች ከአንድ ፋብሪካ እንደተመረተ ሳሙና ናችሁ?” ያሉት ማን ነበሩ?…

ሰሞነኛው ጉብኝት

ፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ሰሞኑን ለሦስት ቀናት ጉብኝት በምዕራቡ የኢትዮጵያ ክፍል ከርመዋል፡፡ የጅማ ቡናን፣ የኮይሻ ሀይቅን፣ የሕዳሴ ግድብን ተሸከርክረውበታል፡፡ ድንገቴው ጉብኝት ግን ኢኮኖሚያዊ ትብብርን ከማሳለጥ ይልቅ ፖለቲካዊ መጠነ ሙቀትን ለመለካት የታለመ ይመስላል፡፡ የኢሱም ኮቴ እየጦዘ ከመጣው የዐቢይ እና ህወሓት አጀንዳ ጋር በሰፊው ተሰናስሏል፡፡ የቀድሞ የአሜሪካ የአፍሪካ ጉዳዮች ኃላፊ ኸርማን ኮኸን የቲውተር ጽሑፍም ለዚህ ጥሩ አባሪ ይመስላል፡፡ ጽሑፉ እንደወረደ “Eritrean President’s current state visit to Ethiopia sends a strong signal to the Tigrean regional authority to not even think about using military force to resist the Ethiopian central government under Prime Minister Abiy.” የሚል ነበር፡፡ “የአሁኑ የፕሬዝዳንት ኢሳይያስ ጉብኝት የትግራይ ሹመኞች የዐቢይን መንግሥት በጦር ለመመከት እንዳያስቡ ጠንካራ ምልክት ይሰጣል” የሚል ጭምቅ ትርጉም አለው፡፡ በርግጥም ፌዴራል መንግሥቱ ከዚህ ወር ጀምሮ ለትግራይ ክልል በጀት መስጠቱን እንደሚያቆም በገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ በኩል ነግሮናል፡፡ ትግራይ ውስጥ ለሚገኙ የወረዳና ከተማ መዋቅሮች ገንዘቡን ፈሰስ እናደርጋለን ማለቱ እንቆቅልሽ የኾነባቸው በርካቶች ቢኾኑም በዐቢይ አሕመድ መንግሥትና በህወሓት ጁንታ መሃል የድብድቡ የመጀመሪያ ፊሽካ አድርገው የቆጠሩት ቀላል አይደሉም፡፡ የኢሳይያስ ሰሞነኛ ጉብኝት ዓላማውም ዒላማውም ሌላ የኾነው በእዚህና ተያያዥ ምክንያት ነው፡፡

በስተመጨረሻም

የኤርትራ ነገር ግራ ገብ መኾኑ አልቀረም፡፡ የኢሳይያስና የዐቢይ ፍቅር ግለሰባዊ ኾኖ መቀጠሉም አሳሳቢ ነው፡፡ ባለፈው ሃምሳ ዓመት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ሻዕቢያና ህወሓት የኢትዮጵያ ማኅበረ ፖለቲካዊ ሥሪት እንዲንኮታኮት የነበራቸው ድርሻ ግዙፍ ነው፡፡ ነገር ግን በአሳቻ ፍቅር መሃል በተፈጠረ የዝኾን ጸብ ጭዳ የኾነ ሕዝብ ከዚህም ከዚያም መኖሩ አይታበልም፡፡ ሴራን፣ ደባን፣ ተንኮልንና ሸፍጥን ገንዘባቸው ያደረጉት እነኚህ ሁለት ድርጅቶች ግን ዛሬ የቆሙበት መሬት የተራራቀ ነው፡፡ አንዱ ሀገር ይመራል ሌላው ክልል ይዟል፡፡ ያደረው ቂም ግን በነበረበት ነው፡፡ ቂሙስ የድርጅቶች ነው ይባል፣ ሳሩ ባለበት መኖሩን ግን መዘንጋት አይገባም፡፡ ኢትዮጵያም ለፖለቲከኞቿ የማይጠረቃ የሥልጣን ጥም መድማቷ ቢበቃ ይሻላል፡፡ ይታሰብበት፡

Filed in: Amharic