>

አራሽ፣ ቀዳሽ፣ ተኳሽ ሦስቱም አንድ ናቸው - በዘመኑ ቋንቋ ይመጋገባሉ....!!! (ያየህ ይራድ ደግነቱ)

አራሽ፣ ቀዳሽ፣ ተኳሽ ሦስቱም አንድ ናቸው – በዘመኑ ቋንቋ ይመጋገባሉ….!!!

ያየህ ይራድ ደግነቱ

ከዕለታት አንድ ቀን ከሞጣ (ጐጃም) ገበያ መልስ ሁለት ሰዎች ይገናኛሉ፡፡ ከሁለቱ አንደኛው “ቀ” ማለት አይችልም፡፡ ስለዚህም በቦታዋ “ፀ” የምትለዋን ፊደል ይተካባታል።
አንደኛው ሰውዬ፡- “እንደምን ውለሀል ወዳጄ?”
ሁለተኛው ሰውዬ፡- “ደህና እግዚአብሔር ይመስገን፤ ከወዴት እየመጣህ ነው?”
አንደኛው -“ከሞፃ”
ሁለተኛ – “ምን ይዘሃል?”
አንደኛው – “ድግፃ” (ከድግጣ ዛፍ የተመለመለ በትር ስለያዘ ነው)
ሁለተኛው – “ሞጣ ምን አለ?”
አንደኛው – “ሞፃ፤ ፆርነት በፆርነት ሆኗል”
ሁለተኛው – “ታዲያ ምን ተሻለን?”
አንደኛው – “ፀሎት! ሠላም እንዲመጣ መፀለይ እና ፀባይ ማሳመር! ፀጽታ ይመፃ ዘንድ ፀሐይ ጊዜ አምፃልን ብሎ መፀለይ”
ሁለተኛው- “በል ወዳጄ ትንሽ አገልግል ይዣለሁ፤ ምግብ እንብላ” አለውና አንድ ጥላ ቦታ ተቀምጠው፣ አገልግሊቱን ፈታና መብላት ጀመሩ፡፡ እንዳጋጣሚ ወጡ ጨው የለውም ኖሯል፡፡
አንደኛው – “አይ ፀው የለውም፤ ፀው ከየት እናምጣ?” አለና ጠየቀው፡፡
ሁለተኛው ሰው – “አይ እንግዲህ ወዳጄ” “ፀ”ን ምንም ብንወዳት፣ ወጥ ውስጥ አንጨምራትም” አለው ይባላል፡፡
*   *   *
የሼክስፒር ሃምሌት፣ ሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን እንዳለው፣ እንዲህ ይለናል፡-
“ዛሬ ለወግ ያደረግሽው፣ ወይ ለነገ ይለምድብሻል
ልማድ ፊት እንዳሳዩት ነው ወይ ይጠፋል ወይ ያጠፋል
ከርሞውም የሰለጠነ እንደሁ፣ ተፈጥሮ ይሆናል ይባላል፡፡”
አብዛኛውን ጊዜ የልማድ ተገዢዎች መሆናችን እርግጥ ነው፡፡ አንድም በባህላችን ተጽእኖ፣ አንድም በሰውነት ባህሪያችን ሳቢያ፣ ተቀብለን ያቆየናቸውም ሆኑ እያቆየን ያለናቸው ባህሪያት፤ ውለው አድረው፣ የለት የሰርክ ህልውናችን አንድ አካል ይሆኑና እንደ ተፈጥሯአዊ ጉዳይ አድርገን እንቀበላቸዋለን፡፡
በእድገታችን መሽከርክሪት ላይ የትምህርትን ሚና ቸል ካልን ብዙ ነገር ይጐድልብናል። በተለይ ትምህርትን እንደ ለውጥ ዋና መዘውር አድርገን ካልተገለገልንበት፣ የተመራቂ ቁጥር መጨመር ብቻውን ረብ – ያለው የመሻሻል ምልክት አይሆነንም፡፡ ምክኑስ ቢባል ለዋጭ – ተለዋጭ ሃይል የማፍራት አቅም አላበቃንምና! ከትምህርቱ በተጓዳኝ የጤናን ወሳኝነት አበክረን በተለይ ለወጣቱ ትውልድ ማስጨበጥ ዋና ነገር መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ ተረካቢም ትውልድ የማዘጋጀት ታላቅ ኃላፊነት መወጣት ነው፡፡
የፖለቲካ ፀሐፍት “The new invincible” ይሉናል፡፡ አዲሱ አሸናፊ ማለታቸው ነው፡፡ የአሮጌውን መሞትና አዲሱን የመቀበልን ፀጋ በሙሉ ልብ መጨበጥ፣ አገርን ከመቆርቆዝና ከመንቀዝ (Crises and degeneration) ያድናል፡፡ እንደው በደመነፍሳዊ መንገኝነት (Herdism) የመንጋጋት አካሄድ ጠያቂ – ህብረተሰብ (inquisitive Society) እንዳንፈጥር ይገድበናል፡፡
ደጋግመን ስለ ትምህርት ወሳኝነት የምናነሳው ስንመኝ የኖርነውን ጠያቂ ትውልድ ለማምጣት ሁነኛው መሣሪያ ትምህርት ብቻ በመሆኑ ነው። በጥንቱ አባባል፤ “የኛ መማር መማር መማር አሁንም መማር” ስንል የነበረው ያልተማረ፣ ያልበሰለና በሃሳብ ያልበለፀገ ወጣት፤ ቅኝቱ ውጭ አገር የመሄድ፣ ደጅ ደጁን የማየት፣ ሄዶም የትም የትም እደርሳለሁ ሳይል “ከሀገር መውጣት” በሚል መፈክር ስር ብቻ ታጥሮ፣ የአእምሮ – ዘረፋው አካል (Brain Drain)  የእጅ መስጠቱ ሰለባ (Defeats Mentality) አዙሪት ውስጥ የሚባዝን ይሆናል!
“በመሠረቱ ሌሎችን የማያዳምጥና እኔ ያልኩት ብቻ የሚል ካድሬ ነው” በቀኖና ታጥሮ እውነታውን ብቻ የሚል ደግሞ ዲያቆን ብቻ ነው፡፡” ይለናል የስነ ተውኔቱ ፀሐፊ ፀጋዬ ገብረመድህን፡፡ ሁለቱም ባልተሰናሰለ መንገድ የግትርነት ሠለባ ከሆኑ አደጋ ናቸው ማለት ነው፡፡ አገር፣ አንድ አራሽ፣ አንድ ቀዳሽ፣ አንድ ተኳሽ ሊኖራት ግድ ነው ይሏልና አምራች፣ ውዳሴ – ሰጪና ድንበር – ጠባቂ በሌሉበት፤ ሀገር አለኝ ማለት የዋህነትም መሀይምነትም ነው! አምራቹ የኢኮኖሚ ህልውናችንን ጠባቂ፣ ቀዳሹ የመንፈሳዊ ህልውናችን ረካቢ፣ ወታደሩ ዳር ድንበር አስከባሪ፣ ነውና እኒህ ኃይላት ዛሬም አንድም ሦስትም ናቸው እንላለን፡፡

Filed in: Amharic