>

ገዳና አዲስ አበባ ምንና ምን ናቸው...!!! (ሰይፉ ታሪኩ)

ገዳና አዲስ አበባ ምንና ምን ናቸው…!!!

ሰይፉ ታሪኩ


የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ መዝገብ መስፈርን ተከትሎ አንድ ተጨማሪ ሁነት ተፈጠረ፡፡ ኦሕዴድ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አዛዥ ናዛዥነት ተሸጋገረ፡፡ “የአባ ገዳ ልጆች” የሚል ማዕረግም ተዋወቀ፡፡ “ሐሮምሳ ፊንፊኔም” ተቋቋመ፡፡ ዓይኖች ኹሉ አዲስ አበባ ላይ ተተከሉ፡፡ የትግሉ አልፋ እና ኦሜጋ ኹሉ “ደቼ ፊንፊኔ” ላይ መኾኑ ተነገረ፡፡ ቻርተር ተሻረ፣ መታወቂያ ታደለ፣ ዴሞግራፊ ተሞከረ፡፡ ከዚህ ኹሉ በኋላ ደግሞ “ገዳ” አንድ የትምህርት ዓይነት ኾኖ ለአዲስ አበባ መጣ፡፡ ድርጊቱ ግን ቀላል የሚባሉ ጥያቄዎችን እንኳን ማለፍ አለመቻሉ አስተዛዛቢነቱን ያጎላዋል..!ከወር በፊት ጆሮ ገብ የኾነ አንድ ዜና አደመጥን፡፡ ዜናው ከኢትዮጵያ የማይዳሰሱ የዓለም ቅርሶች መካከል አንዱ ስለኾነው ገዳ ነበር፡፡ “የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ገዳን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ሊሰጥ እየተዘጋጀ ነው” ይላል፡፡ ከይዘቱ በላይ ይዘቱን ገቢራዊ ለማድረግ ያወጀው አካል ማንነት ያስደነግጣል፡፡ “የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ”፡፡ ልብ አድርጉ የከተማ ትምህርት ቢሮ እንጂ ትምህርት ሚኒስቴር አይልም፡፡ በርግጥ የአሠራር ቅደም ተከተልንም ይኹን የሥልጣን እርከኖችን ወደጎን እየገፈተሩ ሚኒስትር እና ከንቲባ መሾም “ሕግ” በኾነበት ሀገር ይኽ ለብቻው መደነቅን ሊፈጥር አይችልም፡፡ ግን ግን እስቲ አንድ መናኛ ጥያቄ እናንሳ፡፡ ከዐሥሩ የፌዴሬሽን ክልሎችና ከአንዱ የከተማ መስተዳድር ተነጥሎ አዲስ የትምህርት ዓይነት አዲስ አበባ ላይ ተግባራዊ የሚደረግበት አመክንዮ ከየት የመነጨ ሊኾን ይችላል?

ገዳ ኢትዮጵያዊ ቅርስ መኾኑ አይታበልም፡፡ ዛሬም በከፊል የሚገለገሉበት የማኅበረሰብ ክፍሎች መኖራቸውም አሌ አይባልም፡፡ ስለ ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊነት የተነገረውን ያህል፣ ሰልቃጭና ጨቋኝ ስለመኾኑም ብዙ ተጽፏል፡፡ በሞጋሳና ጉዲፈቻ የሌላ የኾነውን የእርሱ በማድረጉ አታሞ የተደለቀለትን ያህል የቋንቋና ኃይማኖት ሕልውናን ደምሳሽ በመኾኑ ደግሞ በእጅጉ ተኮንኗል፡፡ ሥልጣን በየስምንት ዓመት በማፈራረቁ የሚዘንብለት መወድስን ያህል፣ ሴቶችን አግላይ በመኾኑ የትችት መርግ ይወርድበታል፡፡ በአባ ባህርይ ጽሑፍ ውስጥ የተቀመጠለትን አስፈሪ መልክ ያህል፣ በአሥመሮም ለገሠ ጥናት ውስጥ አስደናቂ ኾኖ መሳሉም አልቀረም፡፡ ሀጂ አባስ ገነሞ እጹብ አድርገው ቢኩሉትም፣ ይልማ ደሬሳ ጥፋቶቹን ከመዘርዘር አልተቆጠቡም፡፡ ሌላም ሌላም… ይኽ ኹሉ ተጻራሪ እውነታ በግራና ቀኝ ተነግሮለትም ቢኾን ገዳ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ወደድነውም ጠላነውም የኢትዮጵያዊያን የነበረና ዛሬም የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን የሚገለገሉበት ሥርዓት ነው፡፡

ጉዳያችን ግን ወዲህ ነው፡፡ በጨዋ ቋንቋ ገዳ እና አዲስ አበባ ምንና ምን ናቸው? የሚል ነው፡፡ ገዳን እንደ አንድ የትምህርት ዓይነት ከአዲስ አበባ መጀመርስ ለምን አስፈለገ የሚል ነው፡፡ ጥያቄው የተለየ ሽብልቅ የለውም፡፡ የconvince እና confused አንጎበር ባለቀቀው የኢትዮጵያ አሁናዊ ሁኔታ፣ “ፊንፊኔ”ን ማዕከል ባደረገው የኦሮሞ ፖለቲካ ስለምን ይኽ ጉዳይ አዲስ አበባ ላይ ሊጫን ተፈለገ ነው? ጥያቄው፡፡ ገዳ “ምንጩ ነው” የሚባለው የኦሮሞ ሕዝብ ሳይማረው አዲስ አበቤ እንዲጋተው የተፈለገበት ምክንያትስ ምን ይኾን? ይኽ ኹሉ ሲወሰን የከተማዋ ሕዝብ “ስልቻ ቀልቀሎ፣ ቀልቀሎ ስልቻ ፤ ዝም ብለህ ተቀበል የሰጡህን ብቻ” የተባለውስ ከየት በመጣ ድፍረት ነው? እነኚህና መሠል ጥያቄዎች የቱንም ያህል ከዕቅዱ ጀርባ የተቀደሰ ዓላማ ቢኖር ተደጋግመው እንዲጠየቁ ያስገድዳል፡፡

ስናፍታታው

ከአንድ ዓመት በፊት የተሰማ አንድ የዜና ይዘት እንዲህ ይል ነበር፡፡ “በኦሮሚያ የገዳ ዜግነት አገልግሎት ሊጀመር ነው”፡፡ ጉዳዩ ልክ እንደ “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ኹሉ ኹለት ተጣምረው ሊኼዱ የማይችሉ ቃላትን አብሮ የያዘ ነበር፡፡ “ገዳ” እና “ዜግነት”፡፡ የኹለቱ ቃላት አብሮ መገኘት ለነጻ ትርጉምም ኾነ ጸጉር ስንጠቃ ተመችቶ ነበር፡፡ የኹለቱ ቃላት አንድ ላይ መገኘት ለአንዳንዱ “በኦሮሞ ብሔርተኝነት የኋላ ኪስ ውስጥ የተደበቀው ሪፐብሊክ የመኾን ሕልም መንደርደሪያ ነው” የሚል ማፍታቻ ተሰጠው፡፡ ለሌላው ደግሞ “በገዳ አቃፊነት የታነጸ ትውልድ ለመገንባት ያመች ዘንድ ለቀና ዓላማ ተደረገ ነው” የሚል ትርጉም ተጎናጸፈ፡፡ ይኽ በኾነ ወራት ውስጥ ደግሞ ሌላ እንግዳ ዜና ተደመጠ፡፡ “በጉራጌ ለ250 ዓመት ተቋርጦ የነበረው የገዳ ሥርዓት ዳግም ተመሠረተ” የሚል ዜና፡፡ ዜናው ብዙ ውዝግብ ፈጠረ፡፡ አንድ የብሔረሰቡ ድምጻዊ ሳይቀር በቴሌቭዥን ተሰይሞ “ጉራጌ በሰባት ቤት የጆካ፣ በመስቃን የፈርአገዘኘ፣ በዶቢ ጎጎት ስኖና የሚባል የራሱ የሽምግልናም ይኹን የእርቅ ሥርዓት እያለው ይኽ መደረጉ ስህተት ነው” አለ፡፡

ሁነቱ ግን ወልቂጤ ላይ በመንግሥት ሚዲያዎች ጭምር ታግዞ የተነገረ መኾኑ ጎላ ብሎ ከመሰማት አላገደውም፡፡ ያም ኾኖ አወዛግቦ አለፈ፡፡ ከሌላ ወራት በኋላ ደግሞ ጠ/ሚኒስትሩ “የመደመር ምንጩ ገዳ ነው” ሲሉ ተደመጡ፡፡ ነገሩ የቱንም ያህል የመመሰል (Analogical Expression) ተብሎ ሊታለፍ የሚችል ይመስላል፡፡ ነጠብጣቦች በሚገጣጠሙባት የዛሬዋ ኢትዮጵያ ግን የንግግሩ ዐውድ ከጉዳያችን ጋር የሚተሳሰርበት ቀጥተኛ ምክንያት ላይኖረው የሚችልበት ምክንያት የለም፡፡

ደግሞ እንደገና …

ከለውጡ በኋላ ታኅሣሥ 9 ቀን 2011 ዓ.ም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የክብር ዶክትሬት ያገኙት ኤርትራዊው ፕ/ር አሥመሮም ለገሠ ከቢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ “ገዳ የወደፊቱ የፖለቲካ ሥርዓት ሊኾን ይችላል” ሲሉ ምሥክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ “Gadaa in the future of Oromo democracy” የሚባል አዲስ መጽሐፍ አዘጋጅተው መጨረሳቸውንም ይናገራሉ፡፡ አያይዘውም “ይኽኛው መጽሐፍ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ እንዴት መፍጠር ይቻላል የሚለውን ስትራቴጂ ይቀይሳል፡፡ እኔ ሃሳቤን አቅርቤያለሁ፣ እንግዲህ የኦሮሞ ሊቃውንት ተከራክረውበት አሻሽለው ግብር ላይ ሊያውሉት ይችላሉ፡፡” ሲሉም ይገልጻሉ፡፡

በኦሮሚያ ክልል ፖለቲካ ፓርቲዎች እንቅስቃሴ ውስጥ ራሱን “የገዳ ሥርዓት አራማጅ ፓርቲ” ብሎ ከሚጠራ አንድ ድርጅት ውጪ “ገዳ”ን እንደ ሥርዓት ለማንበር የሚታገል ድርጅት አይገኝም፡፡ ይኽ በራሱ ለብዙ ትርጓሜ ክፍት የኾነ እውነታ ነው፡፡ ከሃያ የማያንሱት የክልሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ከማይታሙበት የከረረ ዘውገኝነት አኳያ “ገዳ”ን እንደ ግብ አስቀምጠው ለመንቀሳቀስ ያልደፈሩበት ምክንያት “ምንድነው?” ያስብላል፡፡ ቁርጥ ያለ ምላሽ ለመስጠት ቢቸግርም ለተሳካ መላምት ግን ክፍት ነው፡፡ ገዳ በዐሥራ ስድስተኛው መቶ ክፍለዘመን የብሔረሰቡ እንቅስቃሴ ውስጥ የጎላ ድርሻ ነበረው፡፡ ኾኖም ወደተለያዩ አቅጣጫዎች የተስፋፉት የብሔረሰቡ አባላት የኋላኋላ የተለያየ ሥርዓት ባለቤት ኾነው ቀርተዋል፡፡ ለአብነትም ወደምዕራቡ ክፍል የተንቀሳቀሰው ቡድን መጨረሻ አምስቱ የጊቤ ንጉሣዊ መንግሥታትን መፍጠር ኾኗል፡፡

ይኽም የሣህለሥላሴም ይኹን የምኒልክ “ገብር አልገብርም” ዘመቻ ከመካሄዱ ዘመናት በፊት ሸዋ፣ ወለጋ፣ ኢሉ አባቦራ፣ ባሌና ሌሎችም ቦታዎች በሚኖሩ ኦሮምኛ ቋንቋ ተናጋሪዎች መሃል የባህል፣ የአስተዳደርና የዕምነት ለውጥ (Dynamism) ክሱት እንዲኾን አስገድዷል፡፡ ስለዚህ ገዳ በነቢብ እንጂ በገቢር የአንድ አካባቢ ሥርዓትና ማንነት ብቻ የመኾኑ ሀቅ ተፈጥሯል፡፡ “ዋቄፈታ” የገዳ ሥርዓት ኃይማኖት መኾኑ ደግሞ ከእስልምና ተከታዩ ሰፊ የባሌ፣ አርሲና ሐረርጌ ማኅበረሰብ እውነታ ጋር የሚጣጣም አልኾነም፡፡ በክርስትናውም ቢኾን ቀላል የማይባል አስተሃቅሮ ገጥሞታል፡፡ የእነኚህና ሌሎች አጋጣሚዎች መበርከት በኦሮሞ ልኂቃንም ኾነ የፖለቲካ ድርጅቶች ዘንድ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ “ገዳ” የተዋስዖዋቸው አካል ሊኾን አልቻለም፡፡

አሁን ምን መጣ?

የገዳ ሥርዓት በዩኔስኮ የማይዳሰስ ቅርስ መዝገብ መስፈርን ተከትሎ አንድ ተጨማሪ ሁነት ተፈጠረ፡፡ ኦሕዴድ ከአጀንዳ ተቀባይነት ወደ አዛዥ ናዛዥነት ተሸጋገረ፡፡ “የአባ ገዳ ልጆች” የሚል ማዕረግም ተዋወቀ፡፡ “ሐሮምሳ ፊንፊኔም” ተቋቋመ፡፡ ዓይኖች ኹሉ አዲስ አበባ ላይ ተተከሉ፡፡ የትግሉ አልፋ እና ኦሜጋ ኹሉ “ደቼ ፊንፊኔ” ላይ መኾኑ ተነገረ፡፡ ቻርተር ተሻረ፣ መታወቂያ ታደለ፣ ዴሞግራፊ ተሞከረ፡፡ ከዚህ ኹሉ በኋላ ደግሞ “ገዳ” አንድ የትምህርት ዓይነት ኾኖ ለአዲስ አበባ መጣ፡፡ ድርጊቱ ግን ቀላል የሚባሉ ጥያቄዎችን እንኳን ማለፍ አለመቻሉ አስተዛዛቢነቱን ያጎላዋል፡፡ “ለምን ገዳን ብቻ?” ምናልባት መልሱ “የማይዳሰስ ቅርስ ብሎ ዩኔስኮ ስለመዘገበው” ሊኾን ይችላል፡፡ ተዳሳሽ ያልኾነና ዓለም በመዝገቡ ያሰፈረው ኢትዮጵያዊ ቅርስ ግን ገዳ ብቻ አይደለም፡፡
ከገዳ ጋር የሚቀራረቡ የአካባቢ አስተዳደርም ይኹን ሌሎች ባሕላዊ ሥርዓቶች በደቡቡም ኾነ በሰሜኑ ክፍሎች አልጠፉም፡፡ ኹሉም ደግሞ “የእኔ” ለሚለው ዋጋና ክብር ይሰጣል፡፡ ታዲያ በምን ስሌት ነው የአንዱ ተመርጦ ሀገር አቀፉ ትምህርት ሚኒስቴር ባልወሰነበት ሁኔታ በአንድ ከተማ ላይ ተፈጻሚ የሚኾነው? የሚሰራው ኹሉ ስሜት ብቻ ሳይኾን ስሌት ጭምር አለበት የምንለውም ለዚህ ነው፡፡ አሁንም ግን እንላለን፣ ገዳን መማርም ኾነ ማወቅ ክፋት የለውም፡

Filed in: Amharic