>

የማይሞተው የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት...!!! (ሰይፉ ታሪኩ)

የማይሞተው የኢትዮጵያ የባህር በር ባለቤትነት…!!!

ሰይፉ ታሪኩየዶ/ር ያዕቆብ ኃይለማርያም “አሰብ የማን ናት?” መጽሐፍ ከወሳኝ የታሪክ ማጣቀሻዎቻችን አንዱ ነው። የዛሬው ዓላማዬ በመጽሐፉ የሀገራችን የተለያየ ዘመን መሪዎችና ዕውቅ ፖለቲከኞች ስለአሰብ ወደብና የባሕር በር ባለቤትነታችን የተናገሩትን ለማጋራት ነው፡፡ ይኽ ብቻ ግን አይደለም፡፡ “አሁንስ?” ብዬ ለመጠየቅም እዳዳለሁ። ከትውልድ ስዕለ ሕሊና መቼም ቢኾን የማይሞተውን ይኽን የኢትዮጵያን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ በአስተሳሰብ ልዕልናችን ከመንደር ሽኩቻ የተሻገርን አፍቃሪ-ኢትዮጵያዊያን በድፍረትና በልበ ሙሉነት እንድናነሳም እጎተጉታለሁ፡፡ ይኽን ለማንሳት “ጊዜው አይደለም” የሚሉንን የታሪክ እንከፎች በቃችሁ ብለን አጀንዳውን ወደፖለቲካዊ ዲስኮርስ ማምጣት አለብን ብዬም እሞግታለሁ።

ኢትዮጵያውያን ታሪካዊ፣ ተፈጥሯዊና ዓለማቀፋዊ ሕጎችን ተጠቅመን ገናናውን የባሕር ኃይል ለመመለስ መሬት የወረደ ተግባር ውስጥ ለመግባት ጉዳዩን ወደፊት ማምጣት አለብን፡፡ ይኽ ደግሞ በቀዳሚነት “በሕይወት አለን” የሚሉንን የፖለቲካ ድርጅቶች በነገሩ ዙሪያ ያላቸውን አቋም በመፈተሸ መጀመር ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በኤርትራ ችሮታ የምታገኘው የባሕር በር እንደሌለ ያለልምምጥ ኤርትራውያን እንዲገነዘቡት ማድረግም ሌላኛው ኃላፊነታችን ነው።
ለዛሬ ግን መሪዎችና ፖለቲከኞች ስለባሕር በራችን ተናግረዋቸው የነበሩትን በማጋራት ልጀምር፡፡


“…የዘይላን በር ነገር በሚቻልዎ ነገር ሁሉ ተጣጥረው በእኔ ዕጅ ቢሆን እንኳን በሐረርጌ፣ በአሩሲ፣ በከንባታ፣ በጅማ፣ በከፋ ያለን ነገር ሁሉ በዘይላ አደርገው ነበር። ይህም ማለቴ ለእርስዎ እንዳይቸግርዎ ባውቀው የኢትዮጵያ ልጆች በንጉሥ ኡምቤርቶ ብርታት የዘይላ በር እጃችን ተመልሶ ገባ እንዲሉ ሥምዎ በነገሥታት ታሪካችን ይተከላል፡፡”
ዳግማዊ አፄ ምኒልክ፣ እ.አ.አ በ1876 ዓ.ም ለንጉሥ ኡምቤርቶ ከላኩት ደብዳቤ የተወሰደ

ለብዙ ዓመታት የሁለቱን ወንድማማች ሕዝቦች ለያይቶ የኖረውን የመከራ ምእራፍ በዛሬው ቀን እንዘጋለን”
ቀዳማዊ አፄ ኃይለሥላሴ

“በዚህ በቀይ ባህር ወደብና ጠረፍ ላይ ሆነን ካሌብን ጥንታዊ የባህር ሃይላችንና የንግድ መርከቦቻችን በቀይ ባህር የነበረንን ገናናነት አዱሊስንና መጠራን፣ ዳህላክንና ናኩራን በአጠቃላይ የታሪክ ኩራታችንን አሉላን ጭምር እንመለከታለን፡፡ ቀይ ባህርና የባህር በሮቻችን የታሪካችን ልዩ አሻራዎች ናቸው።”
ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለማርያም

“እነዚህ ኢትዮጵያን ወደብ አልባ የማድረግ ስህተቶች ለኢትዮጵያ ህዝብ የተመረጠ ህጋዊ መንግስት ሳይቋቋም ኤርትራ ነፃነቷን እንድታውጅና ኢትዮጵያ የአሰብን ጉዳይ ጨምሮ በሌሎችም የኢትዮጵያ ህዝብ ፍላጎትና ጥቅምን የሚያስከብር አግባብነት ያለው ስምምነት እንዲፈረም ያለማድረግ ነው”
ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ

“የድንበር ኮሚሽኑን ውሳኔ በመቃወም ባነሳነው የባህር በር ጥያቄ አማካኝነት ውሳኔው የሚለወጥ አይመስለኝም፤ መፍትሄ የሚገኘው ብሄራዊ ጥቅማችንን የሚያስጠብቅ መንግስት ሲመጣ ነው”
ፕሮፌሰር መራራ ጉዲና

“ይህ አሰብን እንይዛለን እንወራለን የሚል አካሄድ ከዚያው ከዘውዳዊው ትምክህታዊ አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። ሁለተኛ ደግሞ ይህ አስተሳሰብ የተጠናወታቸው ሰዎች ከዘመነ ግሎባላይዜሽን ጋር ሊሄዱ ያልቻሉ ከድንጋይ ዘመን አስተሳሰብ ያልተላቀቁ ናቸው። አሰብን ካልያዝን እያሉ ይፎክራሉ፤ ተግባራዊ ለማድረግ በአሰብ ላይ ወረራ እስካልተፈፀመ ድረስ እርምጃ ልንወስድባቸው አንችልም”
ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ

ወዳለንበት ዘመን እንምጣ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ ከሁለት ዓመት በፊት ሎስ አንጀለስ በተገኙበት የድጋፍ ስብሰባ ከጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከቀረበላቸው ሦስት ወሳኝ ጥያቄዎች መካከል አንዱ “ኢትዮጵያ የባሕር በር ባለቤት የመኾን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ተፈጥሯዊ መብት አላት ብለው ያምናሉ ወይ?” የሚል ነበር፡፡ የጠ/ሚኒስትሩ ምላሽ ግን “ጥያቄው ከባድና ስትራቴጂክ በመኾኑ አሁን መመልስ አልችልም” የሚል ነበር፡፡

በርግጥ ጠ/ሚኒስትሩ ከሠላሳ ዓመት በኋላ ኢትዮጵያ ዳግም የባሕር ኃይል እንዲኖራት ጥረት ማድረጋቸው ቢነገርም ጉዳዩ ከፈረሱ ጋሪው በመቅደሙ ወሳኙን ጥያቄ ኢሳይያስ ፊት ይዘው ለመቅረብ አቅሙም ፍላጎቱም እንደሌላቸው ያሳያል፡፡ ከኢትዮጵያዊ መስመራችን ለአፍታም ሸብረክ የማንል ኢትዮጵያዊያን ግን የማይሞተውን የባሕር በር ባለቤትነት ጥያቄ ከፍ አድርገን ማስጮሃችንን እንቀጥላለን፡፡
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic