>
5:13 pm - Friday April 19, 8712

የትናንቷ ኢትዮጵያ - አደሬዎችና ሱማሌዎች እንደማሳያ...!!!”   (ሄኖክ ገለታ)

የትናንቷ ኢትዮጵያ – አደሬዎችና ሱማሌዎች እንደማሳያ…!!!”  

ሄኖክ ገለታ

ይህን ጽሁፍ ርዕሱን “የትናንቷ ኢትዮጵያ” በሚል ለመሰየም የተገደድሁትም በ”ብሔር ፣ ብሔረሰብ” ሀቲት በምትታመሰው የዛሬዋ ኢትዮጵያ “ነገርን ከሥሩ ውኃን ከጥሩ” እንዲሉ የጭቆናና የበደል ትርክት የተጣባው የሃምሳ ዓመቱ የማርክሲስት ፖለቲካ የጦስ ዶሮ ባደረጋቸው “ብሔር ብሔረሰቦች” ውስጥ ኢትዮጵያዊ ማንነት የነበረውን ውድ ቦታና የተከፈለለትን ክቡር ዋጋ በአጭሩ ለማሳየት እንዲያመቸኝ ነው።

ለዚህ አጭር ጽሑፍ የመረጃ ምንጭ አድርጌ የተጠቀምሁት የዶክተር ላጲሶ ጌ.ድሌቦ “የኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም” የተሰኘውንና በ1983 ዓ.ም የታተመውን ሥራ ነው (በነገሬ ላይ በ”ደጉ” ዘመን የእኚሁ ምሁር ተማሪ የነበረ አንድ ወዳጄ “ለመሆኑ ዶክተር ሥሞት ላይ ላጲሶ ጌ.ድሌቦ ብለው “ጌ”ን በአህጽሮት ለመጠቀም የፈለጉት ለምን ይሆን?” ብሎ ላቀረበላቸው ጥያቄ “ጌ” ማለት “ጌታነህ” መሆኑን ገልጸው “መሬቴ ተወስዶ ሃብቴ ተቀምቶ የባላባት ርስት በሆነበት ጌታነህ ተብዬ መጠራትን በራሴ ላይ የመሳለቅ ያህል ስለቆጠርኩት ነው” ብለው እንደመለሱለት የነገረኝ ታሪክ አግራሞትን እንደጫረብኝ ዛሬም አለ)

አደሬዎችና ሱማሌዎች

ታሪክን አጣሞ ፤ ሲያሻም ፈልስሞ እርባና ለሌለው የጎሣ ፖለቲካ ጭዳ የማድረግ ዘልማድ እግሩን ካሳረፈባቸው የሀገራችን አካባቢዎች በምስራቅ የሚገኙት አደሬና ሶማሌ ይጠቀሳሉ። የጭቆናና የተበዳይነት ትርክቱ በተጠቀሱት ቦታዎች በዘመናት ተላውጦዎች ውስጥ ለኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት የተከፈሉ ክቡር መስዋዕትነቶችን ከመጋረዱም በላይ የመነጠልና የተገንጣይነት መንፈሶች የረበቡበት ከባቢ አድርጎ በመሳል ኢትዮጵያዊ መልኩ እንዲደበዝዝ ሆነ ተብሎ ተሰርቷል።

ቅድመ ዘመነ መሣፍንት (መካከለኛው የኢትዮጵያ ታሪክ) የአደሬና እስከ ሞቃዲሾ ጫፍ የሚደርሰው የሱማሌ ሕዝብ የኢትዮጵያው ንጉሠ ነገሥት የግዛት አካል ሆኖ የኖረበት በርካታ የታሪክ ማስረጃዎች ባሉበት ፤ በዘመናዊው የኢትዮጵያ መልሶ አንድ የመሆን (Reunification) ሒደት ውስጥ ከግብጾች የአሥር ዓመታት ቅፍደዳ(Annexation) በኋላ ተረኛዋ ፈረንሳይ ከጅቡቲ ተስፈንጥራ ሐረርን ለመያዝ ሁለቴ ባላሰበችበት የታሪክ አጋጣሚ ውስጥ የሸዋው ንጉሥ ምኒልክ ጦር ገስግሶ ወደ ግዛቱ መቀላቀሉ “ሲፋጅ በማንኪያ ሲበርድ በእጅ” ሆነና የጎሣ ፖለቲከኞችና ልሂቃን የሙሿቸው ኦሜጋ ሆኖ ቀጥሏል። በዚህ የታሪክ አጋጣሚዎችን ለፖለቲካ ጥቅም የማዋል(Making politicize) መጥፎ ልማድ መነሻነት ታሪካዊቷ የሐረር ከተማ በመልሶ አንድ መሆን(Reunification) የኢትዮጵያ መንግሥት የግዛት አካል መሆን “ጨለንቆ” የተባለውንና በሸዋው ንጉሥ በኩል ሰባ አምስት በመቶ የሸዋና ጅማ ኦሮሞ ዘማች ፤ በሐረሩ አሚር አብዱላሂ በኩል ደግሞ የአደሬ ተወላጆች የተሳተፉበትን ውጊያ አንድን ዘር የማሳሳት (Ethnic Cleaning) አድርጎ ከማቅረብም በዘለለ “አስከፊ የብሔር ጭቆና” የተተከለበት መጥፎ የታሪክ ምዕራፍ አድርጎ በመሳል ረገድ ተስተካካይ አይገኝለትም። እውነትን ገልጦ ከመመርመር ይልቅ የተነገረውን እንደ በቀቀን ለማስተጋባት ቁጥሩ ቀላል ባልሆነ ትውልድ ውስጥ ኩሸታቸው የደነደነ ቢመስልም ሀቁ የታሪክ በር ሲከፈት ግን የምናየው ተቃራኒ መሆኑን ሳይሰለቹ መንገር ፤ ሳይታክቱ መጮህ ያስፈልጋል።

ከፍ ባለው መሸጋገሪያዬ የዛሬው አጭር ጦማሬ የመረጃ ምንጭ የሆኑት ዶክተር ላጲሶ ጌ.ድሌቦ “በኢትዮጵያ የገባር ሥርዓትና ጅምር ካፒታሊዝም” በተሰኘው ሁለተኛ የታሪክ ምርምር ሥራቸው ፤ በ1879ዓ.ም ከጨለንቆ ጦርነት በኋላ በንጉሥ ምኒልክና በአደሬ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል በተደረገው ስምምነት የብሔረሰቡ ኃይማኖት፣ ቋንቋ፣ ሕግና ባህልን በሚመለከት እስከ ሁለተኛው የኢጣልያ ወረራ ዘመን ድረስ አደሬዎች በማዕከላዊ መንግሥቱ ሥር የውስጥ አስተዳደር ሥልጣን እንደነበራቸው ይተርካሉ። እስከ ተጠቀሰው የኢጣልያ ወረራ ድረስም ሐጂ የሱፍ ባርከሌ፣ ሐጂ አብደላህ አሊሰዲቅ፣ ቀኛዝማች ሐጂ አሕመድ አቦንና የመሳሰሉት የአደሬ ተወላጅ የመንግሥት ሹሞች ነበሩ።

በሌላ በኩል ከ1917-1927 የኢትዮጵያ መንግሥት በአዲስአበባና በክፍለ ሃገር ከተሞች የውጪ ሀገር መምህራንና ዘመናዊ ትምህርትን በፈረንሳይኛና በእንግሊዝኛ ቋንቋዎች የሚያስተምሩ ከሀያ በላይ የአንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች በሰራበት ወቅት አደሬዎች በሐረር የራሳቸውን ልማት ማኅበር አቋቁመው በፕሮግራማቸው መሠረት በ1921ዓ.ም የራሳቸውን ዘመናዊ የሐረር እስላም ት/ቤት አቋቁመው ለወጣቶች በአማርኛ፣ አረብኛና እንግሊዝኛ ዘመናዊ ትምህርት ማስተማር እንደጀመሩ የትምህርት ቤቱ የመጀመርያ ምሩቃን አንዱ የነበሩት በ1980ዎቹ የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ጉባዔ ተቀዳሚ ምክትል ሊቀመንበር ሐጂ ኢብራሂም አብዱሰላም ለመጽሐፉ ደራሲ ዶክተር ላጲሶ መናገራቸው ተጠቅሷል።
ይህ እንግዲህ ከዚህ ቀደም በጻፍሁት ጦማር ላይ ሩሲያዊው አሳሽ አሌክሳንደር ቡላቶቪች ኢትዮጵያውያን ግዛት በማዋሀድና በማስገበር ውስጥ ውጠት(Assimilation) ፈጽሞ ባህሪያቸው እንዳልሆነና ውስጣዊ ነጻነትን መስጠት ሁነኛው ከአውሮውያን መለያቸው ስለመሆኑ የገለጸበትን ዓውድ እንድናስታውስ ይገፋናል።

የፋሽስት ኢጣሊያ የአምስት ዓመታት የወረራ ቆይታ ታዲያ በዘረኛና ከፋፋይ ፕሮፓጋንዳ ምክንያት በኢትዮጵያና ኢትዮጵያውያን ማኅበረ ፖለቲካዊ ሥሪት(Landscape) ላይ ቀላል የማይባል ጉዳት አስከትሏል። ይህ ከንቱ የኢጣሊያ ነጣጣይና ከፋፋይ ቄሳራዊ መርዝ በተንኮለኛዋ እንግሊዝም ተሞክሮ መክሸፉን የምንረዳው ደግሞ ተከታዩን ደማቅ ታሪክ ስንመለከት ነው።

በመጋቢት 1933 በጄኔራል ካኒንግሀም አዛዥነት በኬንያ ደቡብ ግንባር ወደ ኢትዮጵያ የገባው የእንግሊዝ ጦር የሐረር ከተማን ከፋሽስቶች ከወሰደ በኋላ የእንግሊዝ ጦር ባለሥልጣኖች የአደሬ ብሔረሰብ ተጠሪዎችን ሰብስበው እንዲህ የሚል ጥያቄ አቀረቡላቸው “ከኢትዮጵያ ተለይታችሁ በእንግሊዝ ድጋፍ የራሳችሁን ነጻ ሐገር ለማቋቋም ትፈልጋላችሁ ወይ?” የአደሬ ሕዝብ በውል ያልተነገረው ደማቅና ታሪካዊ ምላሽ ግን “እኛ ኢትዮጵያውያን ስለሆንን በኢትዮጵያ ሰንደቅዓላማና ንጉሥ ላይ የውጭ ድጋፍ አንፈልግም” የሚል ነበር። (ገጽ 155)

ይህ በእንዲህ እንዳለ ሆኖ ጠላት ከሀገራችን ከወጣ በኋላ በእንግሊዝ ጦር ባለሥልጣኖች በሚተዳደረው ሶማሊያ(የሞቃዲሾው) በሚያዝያ 27 ቀን 1935 የሀገሩ ዜጎች “የሶማሌ ወጣቶች ክበብ” የሚል ማኅበር አቋቁመው ከኢትዮጵያ ጋር አንድ ለመሆን እንፈልጋለን በማለት ለእንግሊዙ ዋና አስተዳዳሪ ዊክሃም ጥያቄ አቀረቡ። አጼ ኃይለሥላሴን “ንጉሣችን” ናቸው በማለት ተናገሩ። በተጨማሪም በወቅቱ ለኢትዮጵያና ሶማሊያ አንድነት የሚታገል በሱማሌ ተወላጁ ኡመር ኢብራሂም መሪነት “የኢትዮጵያና ሶማሌ አንድነት ማኅበር” ተቋቁሞ አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ ትግል ያካሂድ ነበር። ይህ ማኅበር “የሶማሌዎች ጩኸት” በሚል ርዕስ በ1939 በፓሪስ ከተማ በቀድሞ የኢጣልያ ቅኝ ግዛቶች ሊቢያና ኤርትራ ጉዳይ ለተሰበሰበው የመንግሥታቱ ማኅበር ያቀረበው የአቤቱታ ደብዳቤ ታሪካዊ በመሆኑ እዚህ ጋር መጠቀሱ ጠቃሚ ነው የሚል እምነት አለኝ።

የደብዳቤው ቃል ፦
“እኛ የኢጣልያ ሶማሊያ ይባል የነበረው ሱማሌ ተወላጆች ስለ ሰላምና ስለዓለም ሕዝቦች ነጻነት በፓሪስ ከተማ በጉባኤ ላላችሁ ባለቃልኪዳን መንግሥታት ከእናት ሀገራችን ጋር አንድ እንድንሆን ቁርጥ ሀሳባችን መሆኑን እየገለጽን ያገራችን ዕድል እስከ አንድ ዓመት ድረስ እንዲቆይ የቀረበውን ሀሳብ በፍጹም የማንቀበለው መሆናችንን በማክበር እናመለክታለን። በዘር፣በልማድ፣በባህል፣በታሪክ፤ በሀዘን በደስታ ኢትዮጵያውያን ነን። እናት እያለችን ሞግዚት ልንቀበል አንችልም። ጉባዔው ሳይመለስ የኢጣሊያ ይባል የነበረው ሱማሌ ከእናቱ ከኢትዮጵያ ጋር አንድነትን እንዲያገኝ እንጠይቃለን።”
ፊርማ ፤ የኢትዮጵያና የሶማሌ አንድነት ማኅበር ፕሬዚዳንት
ኡመር ኢብራሂም (ገጽ 158) የሚል ነበር።

ይህ ብቻ ሳይሆን በወቅቱ ተቀማጭነታቸውን በአዲስአበባ ያደረጉ የኢትዮጵያና የኤርትራ አንድነት ማኅበር እና የኢትዮጵያና የሶማሌ አንድነት ማኅበራት ለፓሪሱ የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ያቀረቧቸው የ”አንድ እንሁን” አቤቱታዎች ቃል በተጠቀሰው መጽሐፍ ሰፍሮ መገኘቱን ስናጤን “ኢትዮጵያዊነት” ብዙ የተከፈለበት ውድና እጹብ ማንነት መሆኑ ላይ መግባባት እንድንፈጥር ይገደናል። የምስራቁ የሀገራችን ክፍል የዘመናት የኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የተጋድሎ አውድማነቱ ተጋርዶ በእርባና ቢሱ የጎሣ ፖለቲካ ምክንያት በተዋስዖዋችን መድረክ ኮስሶ የመነጠል ትርክት ማስፈራሪያ መሆኑን ዛሬ ላይ ልብ ስንል አሳዛኝ ቁጭት ላይ መውደቃችን ባህሪያዊ ነው።

(ይቀጥላል…)

Filed in: Amharic