>

አንድ አንድ እሁድ አለ ቅዳሜን የሚያስንቅ...

በመሠረት ደሞዜ:- ኔልሰን ማንዴላ ኢትጲያ ለመጀመርያ ጊዜ በመጣበት ግዜ የተሰማውን ሲገልፅ “ንጉሡን መጨበጥ የ3000 ዓመት ታሪክን የመጨበጥ ያህል እንዲሰማኝ ያደርጋል::” ሲል ራሱ በፃፈው LONG WALK TO FREEDOM በተሰኘው መፅሀፉ ላይ ገልፆታል:: እኔና ፌስ ቡክ (መካነ ፊት እንዲለው ሃብታሙ ስዩም) ያገናኘን ወዳጆቼ ማንዴላ የንጉሰ ነገስቱን እጅ በጨበጠ ጊዜ የተሰማው ስሜት ይሰማን ዘንዳ እጅግ በጣም የምናከብራቸው ቆፍጣናው ጀግና ልንጎበኝ ዕለተ ዕሁድ መጋቢት 21 ቀንን መርጠን ወደ ምንወዳቸው ብርቅዬ ኢትዮጲያዊ ቤት ገሰገስን፡ ፡ ገስግሰንም ወደ መኖሪያቸው ዘለቅን፡፡ የእኚህ ጀግና ልጅ የሆነችው ወ/ሮ ፀዳለ ጃገማ ሞቅ ባለ መስተንግዶ ተቀበለችን፡፡ ባየችው የወጣት ስብስብ መገረሟንና መደሰቷን ገልፃልን እየተጨዋወትን ሳለ ጀግናችን መጡ፡፡ ሁላችንም ከመቀመጫችን ተነስተን በአክብሮት ተቀበልናቸው፡፡ በዛ ቅዳሜን በሚያስንቀው እሁድ ከሰዓት የሌቴናል ጄኔራል ጃገማ ኬሎን ጉልበታቸውን ስንስም የተሠማን ስሜት ማንዴላ ከተሰማው ስሜት አይለይም፡፡ በቃ ከዛ ትውልድ ዘንድ በአካል የመገኘት ያህል ነው የተሰማን:: ልባችን በደስታ ፈነጠዘች ጨዋታችንን አደራነው፡፡ ሌ/ጄነራል ጃገማ በሚደንቅ ንቃትና የማስታወስ ችሎታ እንዲሁም ጤንነት ነው ያገኘናቸው:: ለእጅ መንሻ እንደየአቅማችን የልጅነት ፎቷቸውን እና የቅርብ ጊዜውን ጎን ለጎን አድርን አሳጥበን ነበር፡፡ የልጅነት ፎቷቸውን እንዲሁም በደራሲ ፍቅረ ማርቆስ ደስታ የተፃፈውን “የበጋው መብረቅ” የተሰኘውን መፅሐፍ ጃገማ ኬሎ ሲያዩ የሚያምር መልካቸው ላይ ያስተዋልነው ፈገግታ ቃላት አይገልፀውም፡፡ ልንጎበኛቸው የመጣነው ሁላችንም ወጣቶች መሆናችን ሲያዩ ያሳዩንን ፈገግታም እንዲሁ፡፡ ጉልበታቸው ስር ቁጭ ብለን ከሚጣፍጠው አንደበታቸውም ታሪክን ከምንጬ ጠጣናት:: ላካፍላችሁም ወደድኩኝ፡፡
1. ሌ/ጀ/ጃገማ ኬሎ የተወለዱት በጥር 21ቀን 1913 ዓ.ም ነው:: ለቤተሰባቸው የመጨረሻ ልጅ ቢሆኑም ከሁሉም ጎበዝ ብርቱ ነበሩና አባታቸው የቤተሰቡ አለቃ አደረጓቸው:: ስማቸውንም ያገኙት ብርቱ መሆናቸውን አባታቸው በማወቃቸው ገና ሳይወለዱ ለወላጅ እናታቸው ‹‹ጥር 21 ቀን ትወልጃለሽ ስሙንም ጃጋማ ብየዋለሁ›› በማለት ነበር ጃገማ ብለው የጠሯቸው:: “ጃገማ” የአባታቸው የፈረስ ስም ሲሆን ሀይለኛ ማለት ነው:: ሌ/ጀ/ ጃገማ እሲኪወለዱ ድረስ የፈረሳቸውን ስም የሚሰጡት ሁነኛ ልጅ አላገኙም ነበር::

2. ጃንሆይ እና ሌ/ጀ/ጃገማ ኬሎ

ጃንሆይ ለመጀመሪያ ግዜ እንዴት ነበር የተገናኙት? ብለን መጠየቃችን አልቀረም፡ ፡ ምላሹን እንዲህ ነበር ያጫወቱን… “የጣሊያ መንግስት የኢትዮጲያን ነፃነት ገፎና ወሮ ስለያዘ ጃንሆይ ለተባበሩት መንግስታት ሊያመለክቱ ወደ እንግሊዝ ሄደው ምንም ውጤት ሣያገኙ ቀሩ:: ነገር ግን እግዚአብሔር ኢትዮዺያን ስለሚወዳትና ጥሎ ስለማይጥላት ሁለተኛ የዓለም ጦርነት ጊዜ እንግሊዝ ኢጣሊያን ከአፍርካ እንድታስወጣ ተወሰነ:: ጉዳዩ ኢትዮጲያንም ይመለከታልና ከንጉሡ ጋር ሆነው ሲመጡ የከዳውም ባንዳ እየተመለሠ ጣሊያን ተባረረ:: ከዚያ በኋላ ንጉሡ ተመልሠው ዙፋቸው ላይ ቢቀመጡም ጎንደርና ጅማ አልተለቀቁም ነበርና የጎንደሩ ይቀመጥ መጀመሪያ የቅርቡን እናስለቅቅ ተብሎ ወደ ጅማ ሲሄዱ ጀኔራል ጋዜራል የግቤን ድልድይ ቆርጦ መከላከል ጀመረ:: በዚህ ግዜ ደጃዝማች ገረሱ ዱኪ ያውቁኝ ነበርና ለጃንሆይ “ጃገማን ቢያዙልኝ በአምቦ መንገድ ሄዶ በኃላ ይቆርጥልኛል” በማለታቸው ጃንሆይ እኛ ሰውዬ (ወደ ፎቷቸው እያመለከቱ) ከደጃች ገረሱ ጋር እንድትዘምት ብለው ደብዳቤ ላኩልኝ:: እኔ በወቅቱ 3500 ወታደኖች ነበሩኝ፡ ፡ መሣሪያውን ግማሹን ማርኬ ግማሹን ገዝቼ ያከማቸሁት ነውና መሳሪያ የመንግስት ነው ስለተባለ ሲፈልጉ መሣሪያውን ይውሰዱ ብዬ እምቢ አልኩ:: ወ/ሮ ሸዋረገድ ገድሌ የተባሉ የውስጥ አርበኛ ያውቁኝ ነበርና ለጃንሆይ “ህፃን የሚያምር ልጅ ነው እንዴት ከሞት ወደ ሞት ይልኩታል፡፡ ያሰናብቱት ጦሩን ቢያዩለትም መልካም ነው” ብለው ተናገሩ:: ጃንሆይም “እውነት ነው ተሣሥተናል እናያለን” አሉ:: “ጦርህን መጥተን እናያለን ተዘጋጅተህ ጠብቅ ፉከራም ታሰማለህ” ብለው መልዕክት ላኩብኝ፡፡ መጡ:: እኔም ታወር ሰርቼ ጠበኳቸው:: ፎክር ተብያለሁና ፉከራ ባልችልም ‹‹አባቱ ኦሮሞ እናቱ ኦሮሞ ግዳዩን አስቆጠረ ከምሮ ከምሮ›› ብዮ ፎከርኩ፡፡ ከዛ በኃላ ምሣ አብረን በልተን ከሳቸው ጋር አዲስ አበባ ቤታቸው መጣሁ:: 25.000 ብር እና የወርቅ ሠዐት፤ ሙሉ ገበርዲን ሱፍ ሰጡኝ:: ከዛ ደጃች ገረሱ ጋር ዘምቼ አጋሮ ወርጄ ድልድዩን ዘጋሁት:: መኮንኖቹ ተማረኩ:: ጋዚራም እጁን ሰጠ:: ጠቅላላ 600 እስረኛ ተቀብዬ ጦርነቱ አበቃ::”
3. ሌ/ጀ/ ጀገማ ከኢጣሊያ ጋር 5 ዓመት ሲዋጉ አንድም ቀን ድል ሆነው አያውቁም:: ጥይት ሲያልቅባቸው ብቻ ቦታውን ለቀው ይሄዳሉ:: ጥይት መልሶ ለማግኘት እንዴት ያደርጉ እንደነበር እንዲህ አጫውተውናል፡፡ “ጥይት ሲያልቅብን ማታ ምሽግ ላይ እንተኩሳለን:: አስራ አምስት ተኩሰን ከሆነ ሃያ ተኩሻለሁ ይልና አምስቱን ይሸጣል:: ጥይቱን የሚሸጡት ባንዳዎች ናቸው::”
4.የጀ/ጃገማ መልዕክት ለወጣቱ “ዛሬ ነገሮች ቀሏል ትምህርት አለ፤ ታነባላችሁ፤ ባህላችሁን ሳትለቁ ሀገራችሁን ጥንት አባቶቻችሁ እንደጠበቁት የምትጠብቁ ያድርጋችሁ:: ባህላችሁንም ሳትለቁ ሀገራችሁን ጠብቁ!”
5. ጀነራሉ ጨዋታ አዋቂ ናቸው:: አብራን ስታጫውተን የነበረችው ልጃቸው ፀዳለ “አባባ እንደው ህይወትህን ከድሮ ጀምረህ ስታየው ምን ይሰማሃል?” ብላ ጠየቀቻቸው “እንግዲህ በጋዜጠኝነት ደንብ ተምዝግበሽ ነይ” ብለው በቀልድ መልክ መለሱላት፡፡ ከኛ መሃል አንደኛው ጓደኛችን ሲጠይቃቸው ድምፁ አልሠማ አላቸውና “ድምፁ ለራሱም አይሰማውም” ብለው አሳቁን:: የጠየቃቸው ጥያቄ “ልጆት ጣሊያናዊ በማግባቷ ምን ይሰማዎታል?” የሚል ነበር እንዲህ ሲሉ መለሱለት..“ከኢጣሊያ ጋርማ ታርቀን አማች ሆነናል ምን ነገር ትቆሰቁሳለህ?” :: በመጨረሻም ጉብኝታችንን አጠናቀን ምርቃታቸውን ተቀብለን ስንሰነባበት ኢትዮጲያ ደማቸውን ላፈሰሱላት እኚህ ጀግና አሁን ምን አድርጋ ካሰቻቸው? ብለን እራሳችንን ጠየቅን:: ምንም! መልሣችን ሆነ:: በራፋቸው ላይ አስተዳደሩ የተከለውን የቆሻሻ ትቦ አይተን አዘንን::
እኔ ደግሞ መለስ ብዬ ሁሌም መልስ አግኝቼለት ከማላውቀው ጥያቄ ጋር ተፋጠጥኩ፡፡ ለምንድነው ኢትዪጲያ ውስጥ ሀገሩን የሚወድ ደሃ የሚደረገው? እስከ መቼ ነው
‹‹ኢትዮጲያ ሀገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ››
እያልን የምንተርተው? የምንቆዝመው? ያው እንደሁልግዜው ምላሽ የለውም፡፡ ሀገሩን የሚወድ ካበረታታ፤ ለሀገሩ ያገባኛል ያለ በጥሩ ካልተካሰና የሚገባውን ክብር ካልተለገሰ ያገባኛል የሚሉ አዕምሮዎች ምን አገባኝ ማለት አይጀምሩም? ምን አገባኝ የሚሉ በበዙ መጠን ሀገር በስግብግቦችና ግድየለሾች ተሞልታ ህልውናዋ አደጋ ላይ አይወድቅም? ይወድቃል! መቼ ነው ክብር ለሚገባው ክብር መስጠት የምንጀምረው? መልስ የሌለው ጥያቄ፡፡ አንዳንዴ ሀገሬን ሳስባት ለክብሯ የተዋደቁ ልጆቷ ተረስተው ክብራቸው ጠፍቶ ስታይ ከሀዘን ብዛት እምባዋ ደርቆ ወደ ውስጧ እያለቀሰች ያለች ሆና ትታየኛለች፡፡ ያኔ የኔ ልብ በሀዘን ይቆረፍዳል፡፡ እስኪ ልቦና ይስጠንና ሁላችንም ጀግና አስታዋሽ፤ ለከፈሉት ዋጋ ክብር ሰጪ ያድርገን፡ ፡ የኋላው ከሌለ የለም የፊቱ አይደል ያለው ድምፃዊው፡፡

ዘላለማዊ ክብር ለሌ/ጀ/ጃገማ ኬሎ! እና ለጓደኞቻቸው!

           ኢትዮዺያ ለዘላለም ትኑር!

Filed in: Amharic