>
8:55 pm - Tuesday June 6, 2023

የዓለማየሁ ገላጋይ ታለ በእውነት ላይ የተሰራ ዳሰሳ...(ያዕቆብ ብርሃኑ)

እግዜርን በጀርባ ማዘል…!!!

ያዕቆብ ብርሃኑ

የዓለማየሁ ገላጋይ ታለ በእውነት ላይ የተሰራ ዳሰሳ…


ዓለማየሁ ገላጋይ በብርሃን ፈለጎች ወጥ ልቦለዱና በኩርቢቷ አጭር ተረኩ ያስደመመኝ ደራሲ ነው፡፡ በተለይ ለኩርቢቷ በዝርግ ውብ አብረቅራቂ ዘይቤዎች የተኳለች ዘለዓለምን የሚገዳደር የጨመተ ቁዘማ የታተመበት አጭር ልብወለዱ አድናቆቴ ወደር የለውም፡፡ ዓለማየሁ በዚህኛው መጽሐፉ የተለየ ሆኖብኛል፡፡ እንደዚህ መጽሐፍ (ታለ-በእውነት ስም) በአማርኛ ቋንቋ ተጽፎ ያደናገረኝ፣ ከራሴ ጋር ያቃረነኝ፣ ያጥበረበረኝ ሌላ መጽሐፍ አልገጠመኝም፡፡ የዚህን መጽሐፍ ስህተቶች ነቅሰው አውጥተው እያብጠለጠሉ መጻፍ ይቻላል፡፡ የዚህን መጽሐፍ ልህቀቶችን ለቅሞ አውጥቶ እያንቆለጳጰሱ መተንተንም እንዲሁ ይቻላል፡፡ በማኅበራዊ ትስስር ገጼ(facebook) ላይ ሁለቱንም በጀብደኝነት ሞክሬያቸዋለሁ፡፡ ሁለቱም ሙከራዎቼ ግን ለራሴ እንኳን የሚያረኩኝ አልሆኑም፡፡ እንደገና ሌላ ሦስተኛ ደርዝ ያለው ሀተታ ለመጻፍ ስጀምር ስተወው ከዓመት በላይ ተቆጠረ፡፡ በመሀሉ ግን አይታክቴውና በእኔ እምነት ብቸኛው የአብደላ ዕዝራ ወራሽ ደረጀ በላይነህ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ‹የአለማየሁ ገላጋይ ቀንዶች› በሚል ርዕስ የሆነች መሰናዘሪያ ስንጥቅ ፈለቀቅ፡፡

‹‹ …ድልድይ አድርጎ በመጣው የድህረ ዘመናይ ቅርጽ ውስጥ መዋኘት ጀምሯል፡፡ ሁለቱም ቅርፆች ለስሜት አይመቹም፡፡ እንደባቡር ሀዲድ ብረት ነክሰው አይሽከረከሩም፡፡ አንዳንዴ ይፈነጠራሉ፤ ያፈነግጣሉ! …የስነ-ጽሑፍ ቅርጹ የተበታተነ፣ የፈራረሰ፣ ተጨባጭነጭነትን ያስፈነጠረ ነው፡፡ ማንም ስለ ትልሙ፣ የትኛውም ጠቢብ ስለምክንያተዊነቱ ሊጠይቀው አይችልም፡፡ ስለዚህ እንደተለመደው የስነ-ጽሑፍ ‹አላባ› ታሪክ ፍለጋ መባተት ወይም (story hunter) መሆን አይቻልም፡፡ …ሁሉም ነገር መሬት አልረገጠም፡፡ እንደ ደመና [እየተንሳፈፈ] እንደ ጅራፍ እየገረፈ የሚጮህ ነው፡፡ …ምዕራብና ምስራቅ የሆኑ ነገሮች ብዙ ናቸው፡›› ደረጀ በላይነህ ሐምሌ 20 2011 ዓ.ም‹‹የዓለማየሁ ገላጋይ ቀንዶች›› አዲስ አድማስ ጋዜጣ::

አሁንም ግን ይህንን መጽሐፍ የተንተራሱ ጥያቄዎቼን ማስከኑ አልሆነልኝም፡፡ እንዲያውም ትኳሮዬ ቅስቱን በመጠኑ ወደ ደራሲውና ድርሰቱ ግንኙነት ያዞረም መሰለኝ፡፡ ራልፍ ኤመርሰን(Ralph Waldo Emerson-1803-1882) በ1841 እ.ኤ.አ በጻፈው history በተሰኘ አስደናቂ መጣጥፉ እንዲህ ይላል፡፡ ‹‹There was neither history nor fiction- ONLY biography. If the whole of history is one man, it is all to be explained from individual experience.›› ሳሙኤል በትለር በበኩሉ ‹‹every man’s work, whether it to be literature or music or architecture or anything else- is always a portrait of himself.›› ይለናል፡፡ እናስ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ከምናነባቸው ውጥንቅጦች የትኞቹ ናቸው በትክክል የደራሲውን ነፍስ የዳሰሱት? የትኛው ፍንዳታ? የቱ ሽሽት? የትኛው ሽንፈት? የትኛው የብቻ ልቅሶ? የትኛው ሳቅ? የትኛው ዘመቻ? የቱ አባሮሽ? ታለ፣ ለገነት፣ ረቂቅ፣ ጠናጋሻው፣ ሊሊ፣ ረድ ሰርዌ… ሁሉም በራሳቸው መንገድ ተብሰልሳይ፣ ተሸናፊዎች ናቸው፡፡ አንዱ የአንዱ አገልጋይ፤ አንዱ የአንዱ ሎሌ… ደራሲው በተለይ በኩርቢቷ የአጭር ልቦለድ ተረኩ ወደ ምናቡ ዓለም ርቆ ቢመንንም ‹በታለ› ለጥላችን ይቀርባል፡፡ ግን ደግሞ ታሪኮቹ ሁሉ እንዲሁ ሌጣ ሀቆች አይደሉም፡፡ በኩሸት የታሹ፣ ከተረትም የረቀቁ ሌሎች ገጾች አሏቸው፡፡

ዓለማየሁ ገላጋይ በድርሰት ይትባህሉ ሙከራዊ አጻጻፍን የሚወድ ደራሲ ነው፡፡ ‹የብርሃን ፈለጎች› ላይ የተጠቀመውን ሥልት ‹ወሪሳ› ላይ ሲደግመው አናይም፡፡ ‹በፍቅር ስም› ደግሞ ራሱን የቻለ ሌላ ቀለም ያለው፣ ግለ ታሪክ የሚመስል ሥራው ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ የዛሬ የዳሰሳ መነሻዬ የሆነው መጽሐፉ ታለ-በዕውነት ስም የበፍቅር ስም ተከታይ ነውም አይደለምም ልንል እንችላለን፡፡ በአንድ በኩል ‹ታለ› ከበፍቅር ስም የተሻገሩ ሀቲቶች፣ ገጸባህሪያትና መቼቶችን ይዟል፡፡ በሌላ በኩል ልብወለዱ በፍቅር ስምን መደገፍ ሳያስፈልገው ራሱን ችሎ መቆም የሚችል፣ ግልጽ የግለ ታሪክ አጻጻፍ ስልትን የተከተለ፣ የድህረ ዘመናዊ(postmodernism) ልቦለዶች ባህሪያት ጎልተው የሚታዩበት መጽሐፍ ሆኖብኛል፡፡ ካስፈለገ እኮ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ ‹ወደ ሰባራ ባቡር ሰዎች› በሚለው ምዕራፍ ስር የሚነበበው ልብን የሚከብድ ሀቲት ራሱ ከብርሃን ፈለጎች- ‹የሞጆ ቀትሮች› የተሻገረ ትርክት የሚመስል ቀለም እንዳለበት መናገር ይቻላል፡፡

በዓለማየሁ የብዕር ከአጥቢያ እስከ ወሪሳ ስንሻገር አራት ኪሎ ዘወትር ሌላ ናት፡፡ ሲገለጥ ሌላ የሕይወት ፈርጅ፣ ሲገሸለጥ ሌላ የጉስቁልና ሰቀቀን፣ ሌላ ትርጉም፣ ሌላ የሚጎመዝዝ ኮስታራ የንባብ ጣዕም፣ ሌላ አምጰርጵር፣ ሌላ እማማ ጉዶ፣ ሌላ ኮምሬድ፣ ሌላ ሽንፈት፣ ሌላ ገመና፣ ሌላ ምስለት፣ ሌላ መደመም፣ ሌላ ዓለማየሁ ገላጋይ… ሌላ፣ ሌላ ዘወትር ሌላ ነው፡፡ ይሄን ይሄን እንግዲህ አንድ ጀግና ሐያሲ ታሪኮችን እያናበበ በጥልቀት ምርምሮ እስኪያስደምመን እኛ እንደጀመርነው ገብስ ገብሱን እንጫወት፡፡

ለመሆኑ ደረጀ በላይነህ የዓለማየሁ ገላጋይ ታለ- በዕውነት ስምን ድህረ ዘመናዊ ልቦለድ ነው ሲል ምን ማለቱ ይሆን? ድህረ ዘመናዊነትስ(postmodernism) ምንድን ነው? ራሱን የቻለ ፍልስፍና ወይስ የኪነት ዘውግ? ድህረዘመናዊነት መጀመሪያ ዘመናዊነት(modernismንም) ከመቃረን ጠባብ ነጥብ ተነስቶ ዛሬ ሁሉንም የጥበብ ዘርፎች የሚዳስስ ይትባህል እስከመሆን ደርሷል፡፡ የድህረ ዘመናዊ ልቦለዶች አንደኛው ባህሪያቸው እውነታን(non-fiction) እና ፈጠራን(fiction) ማጨባበጥ መቻላቸው ነው፡፡ ሆኖም ይህ ስነ-ይትባህላዊ ባህሪይ በዋነኝነት የሱሪያሊዝም(surrealism) ስልተ ጥበብ መገለጫም እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በዚህ መጽሐፍ ውስጥ በመጀመሪያው ክፍል ‹ጡረታ ድልድይ› በሚለው ምዕራፍ ስር ደራሲው ዓለማየሁ ገላጋይ በገጸባህሪው ታለ ይህንን ግለ ታሪኩን እንዲያዘጋጅ ስለረዳው ሲመሰገን እናነባለን፡፡ በዚሁ ሳያበቃ በገጽ 183 ላይም ዓለማየሁ የታሪኩ አካል ይሆን ዘንድ በተራኪው ታለ ወደ ምናቡ ዓለም በድጋሜ ይጠራል፡፡ ታሪኮቹ ሆነ ተብለው በአግባቡ ያልተሰደሩና እርስበእረስ እያናበቡ የሆነ ዓይነት ትርጉም ለመፈለግ የሚያስቸግሩ ናቸው፡፡ ይህ የደግሞ የድሕረ ዘመናዊያን ልቦለዶች ሌላኛው መገለጫቸው ይመስላል፡፡ ድህረ ዘመናዊ ልቦለዶች በጽሑፍ ውስጥ ሀሳብ የማስተላለፍ፣ ትርጉም የመትለምን የዘመናዊያን ልቦለዶች ባህሪ ይሳለቁበታል፡፡

መጽሐፉ በርካታ የድህረ ዘመናዊ መገለጫዎችን ይዟል፡፡ ዓለማየሁ ገላጋይ በዚህኛው መጽሐፉ ሌላኛውን ዓለም ለመዳሰስ ጥሯል፡፡ የሌላኛውን ዓለም ድንበር ለመጣስ ሞክሯል፡፡ የገጸባህሪያት ህልውና ሲሻር፣ ሲጣረስ፣ በእውነተኛ ዓለም ከሚኖሩ ሰዎች ጋር ሲፋለስ እናነባለን፡፡ ጊዜ የአሰላለፍ ሀዲዱ ተዘበራርቆ ጥንት፣ ትናንትና ዛሬ ያደናግሩናል፡፡ በትክክልም መጽሐፉ ጠጋ ብለው እያገላበጡ ለሚያጠኑት ዝብርቅርቅ ነው፡፡ ፈርጁ ብዙ ሕብሩም የተሳከረ ሰርቦላ ነው… እንኳንም ያስብላል፡፡

ዓለማየሁ ገላጋይ ‹ከአጥቢያ› እስከ ‹ታለ› በተራመደበት የጥበብ ፍኖቱ የተወው አሻራ ጠያቂ ምናብን የሚቀሰቅስ ነው፡፡ ይሄው የዓለማየሁ ጥበባዊ እርምጃ የቀሰቀሰውን መደነጋገር ተተግነን ይህችን ጥያቄ እንጠይቅ እስቲ… ለመሆኑ ግን ጥበብ በመሰረታዊነት ምንድን ነች? ጥበብ ሕይወታችንን ከአሳሞችና እሪያዎች ኑረት ጥቂት እንኳን የተለየ ለዛ እንዲኖረው ለማድረግ ከጊዜ ፈረስ ጋር እየተሸቀዳደሙ ቁርጥራጭ የትርጉም ሀቲቶችን የማፍካት መውተርተር አይደለምን? በእኔ አረዳድ ነገሮች ሁሉ ልክ መሄድ ሲጀምሩ ጥበብ ታንቀላፋለች፡፡ ኢፍትሃዊነት፣ መገፋት፣ መጨቆን የመሳሰሉ ከኑረት ዛቢያ ገደድ ያሉ የሕይወት ቅኝቶች ባይኖሩ ጥበብም ያን ያህል አስፈላጊ አትሆንም ነበር፡፡ ጥበብ ከእነዚህ የጠየመ ሀዘን የተጫናቸው የሕይወት ሀቲቶች አለላዎችን እየነቀሰች ለክዋኔዋ ትኳኳልባቸዋለች፡፡ ሆኖም ጥበብ ኢፍትሀዊነቱን ለመቅረፍ፣ መገፋቱን ለማስቀረት ታግላ አታውቅም፡፡ ለዚህ ዓላማ የሚገለገሉባት ካሉም እንደሸረሞጡባት ትቆጥረዋለች፡፡

እግዜርን በጀርባ ማዘል

‹‹ሊሊ የደጃፌን መከፈት ልትጠቁምበት ማትደፍራቸው እህቶቼን እያለፈች ትመላለስ ጀመር፡፡ አንድ ቀን ሲያለቅስ ሰምቼው የማላውቀውን ልጅ እያባበለች፡፡ አንድ ቀን ነቅቶ የላየሁትን ልጅ ለማስተኛት እየወዘወዘች፡፡ ረሀብተኛ አይኖቿ ያስፈራሉ፡፡ እኔን ለማፍቀር ሳይሆን ለመብላት የጎመጀች ያስመስሉባታል፡፡ በበሬ እንዳለፈች ሳትመለስ በፊት መለስ አደረግኩት፡፡ በእኔ መጨነቅ እግዚአብሔር እየሳቀ ነው፡፡ እንዴት ከእኔ ከፍጡሩ ያንሳል? እንደ ልጅ ኢያሱ በልጅነቱ በውርስ የተሾመብን ሌላ አምላክ ይኖር ይሆን? የፈጠረን የሚያውቀንስ በዚህ ድክመታችን አይሳለቅም፡፡ እኔን ይተው ሊሊን አያይም? አሁን የእርሷ ኑሮ ፍቅር የሚያሻው ነው? እኔ ያየሁትን እንዴት እግዚአብሔር ሳያይ ቀረ? …›› ገጽ 178

የዓለማየሁ ገላጋይን ‹ታለ-በዕውነት ስምን› ካነበብኩ እነሆ ሁለት ዓመት ሊሆነው ነው፡፡ ዓለማየሁ በዚህ መጽሐፉ ልርሳሽ ብል እንኳን መቼም የማረሳት ነፍሴን ቀስፋ ይዛ ዘወትር በጽሞና ሰዓቴ የማብሰለስላት አንዲት ገጸ ባህሪ አለችው፡፡ ስለዚህች ገጸባህሪው እንዲያው ላመል ያህል ጥቂት መስመሮች ለመጻፍ ፈልጌ በርከት ላሉ ወራት ሳመታ ነበር፡፡-ምናልባት ያኔ መርሳቱ ቢቀር እንኳን ልዘነጋት ቢቻለኝ በሚል… ይህች ገጸባህሪ ሊሊ ናት፡፡ ያቺ ወንድሟንና እግዚአብሔርን በጀርባዋ የተሸከመችው ሊሊ…

ዓለማየሁ ገላጋይ በሌሎቹ መጻሕፍቱ (በቅበላ፣ የብርሃን ፈለጎች፣ ወሪሳ…) እንዳደረገው ሁሉ በዚህም መጽሐፉ በቀላሉ ልንረሳቸው የማንችላቸውን እንግዳ ገጸባህሪያትን ያስነብበናል፡፡ ምናልባት ገጸባህሪያትን ጉልህና አይረሴ አድርጎ በመቅረፅ ጥበብ ተወዳዳሪ የለውም መሰለኝ። የአልበርት ካሙን ሞገደኛ ገጸ ባህሪያት የሚመስለው ረድ ሰርዌ፣ ወትሮውንም ለወዲያኛው ዓለም የቀረበች የምትመስለውና እንደ ቢራቢሮ ሽልምልሟ ረቂቅ፣ የሙህርና የወታደር ድቅል መልክ የሚታይበት ጠና ጋሻው… ከእነዚህ ሁሉ በላይ ምናልባትም በቀደሙት መጻሕፍቱ ሁሉ ካነበብኳቸው ሙና፣ ቹቹ፣ አንጰርጵር፣ ሽትርገጥ፣ ጦጤ፣ ሲፈን በላይ ሊሊ ግን ትለያለች፡፡

ሊሊ አስራ ስድስት ዓመት የሆናት ታዳጊ ነች፡፡ ወንድሞቿን ሁሉ አዝላ ያሳደገቻቸው እሷ ነች፡፡ ታለ መኖሪያውን ቀይሮ እነ ሊሊ ሰፈር ሰባራ ባቡር ሲገባ በእይታ ብቻ ወደደችው፡፡ ወንድሟን እዳዘለች የታለን አንዲት ውልብታ ለማየት ያህል በር በሩን ስትመለከት ትውላለች፡፡ ነገሩ ለየት ያለ የሚያነውር የሚመስል እንግዳ መልክ አለው፡፡

ከተወለደች ጀምሮ ከቤት ወጥታም ሆነ ትምህርት ቤት ሄዳ አታውቅም፡፡ ሊሊ እስከ ጽንፍ በተዘረጋው ህዋ ውስጥ እየኖረች አንዲት ቀን ብቻ ልጅ ሳታዝል ከሰባራ ባቡር ወደ ሞንትራሌ ሄዳለች፡፡ እንድታወራ በተጋበዘች ቁጥር ያችኑ የአንድ ቀን ጀብዷን፣ የአንዲት ዕለት ነጻነቷን ትደጋግማለች፡፡ ‹‹ጉድጓድ ውስጥ የምትኖር እንቁራሪት በቀዳዳ የምታየው ሰማይ መላው ዓለም ይመስላታል›› እንዲሉ አበው የሊሊ ዓለም ከሰባራ ባቡር እስከ ሞንትራሌ(አትክልት ተራ?) ብቻ የተዘረጋ ይመስላል፡፡ ጉስቁልናዋ፣ መገፋቷ፣ መገደቧ ብዙ ነው፡፡

ነገር ግን እግሮቿ፣ አካሏ ቢተበተብም ቅሉ ልቧን ግን ማንም ማሰር አልተቻለውም፡፡ እናም ዘመኗን ቆጥራ መውደድን ተመኘች፡፡ ግንችሬ ወንድሟን በጀርባዋ እንዳዘለች በነፍሷ የተሸከመችውን የመውደድ ሲቃ ለማስታመም ተፍገመገመች፡፡ በጀርባዋ አንድ ወንድሟ ብቻ ሳይሆን ታለ፣ እግዜሩ ራሱ፣ እኔ እናንተ ሁላችንም በየተራ ታዘልን፡፡ በዚህ ሁሉ የሚያሰቅቅ ትዕይንት መሀል እግዜር አምላክነቱን ትቶ በፍጡራኑ ላይ ከንቱ ብሽሽቅ የሚጫወት ጅላጅል ሸክላ ሰሪ ሆኖ ቀረበ፡፡ እንከኑ የራሱም መሆኑን ረስቶ በፍጡራኑ ጉድለት የሚያላግጥ ….

‹‹እግዚአብሔር ቀልድ ሲያመረው እኔን በሊሊ እንድፈቀር አደረገ፡፡… ሊሊ በሬን ስትፋጭር እግዜሩ (እ)ላይ ሆኖ ይስቅ ይሆን? እንዴት ያለ ቀልድ ነው?…››

በዓለማየሁ የብዕር ፍትጊያ እግዜር ዘመኑን ጨርሶ ጃጅቶ ቀረበ፡፡ ነብይ መኮነን ‹ስውር ስፌት› ቁጥር 2 የግጥም መጽሐፉ ላይ ‹ጊዜም ቀን ይጎድልበታል› ከቋጠራቸው ስኖችን ቀንጭቤ ልጥቀስ፡፡ (ባለቅኔ አንቱ አይባልም፡፡)

… የሚገርመው ጊዜም እኮ እንደሰው ፊት ሲያረጅ ይጨማደድና ገጹን ማዲያት ይወራዋል

…እና አትርሱ ጊዜም ቀን ይጎድልበታል ጥቁር መስታውት እንደሚያይ ልቡን ጽልመት ይሞላዋል፡፡
አትመኑት እንደኛው ነው ሰባራም ሙሉም ፊት አለው!

ገጽ 52

ጉደኞቹ እኛ ዘመናችን አጃጀን፤ እግዜርንም እንደኛው አስረጀን፡፡ በእነዚህ ገፆች መሃል ጊዜን ጊዜ ሲያጥጥበት እግዜርም ዘመኑን ጨርሶ ጨርጭሶ ታዬ፡፡ ለእኛም ጊዜ እንደ ሸሚዝ እንደ ካኔትራ ላያችን ላይ አለቀ፡፡ ዘመናችን ከመገርጀፉ የተነሳ የትናንት በጎነታችን ዓይናችን እያዬ ዛሬ ነውር ሆኗል፡፡ እግዜርም እንደኛ ከዘመኑ ጋር መታደስ ተስኖት ‹ፋሽኑ› ሊያልፍበት ይመስላል፡፡ እግዚአብሔርን እዚያ ከደመና በላይ በሩቅ ሰማይ ሰቅለው አጉል የሚጎናበሱ እነሱ ምንኛ ጂሎች ናቸው፡፡ እግዜር እኮ እኛው ነን፡፡ እኔ፣ አንተ፣ አንቺ… እግዜርን ማየት ስትፈልግ ስለምን ወደ መቅደስና ምኩራብ ትኳትናለህ? ይልቅስ መስታውት ፊት ቅረብ፡፡ እሱ ስትከፋ ክፉ ነው፤ ስትለግስ ለጋስ…

የሆነስ ሆነና ዓለማየሁ በሊሊ መነጽር ሊነግረን የፈለገው ምንድን ነው? አንድም ቀን ተንቀሳቅሶም ሆነ አልቆሶ የማያውቀው የታዘለው ልጅ ምስለቱ ምንድን ነው? ሁላችንም ልባችንን ገልጦ ማየት ለሚችል ሰው እንደ ሊሊ የሆነ የማንፈልገውን በዓድ ክቡድ ሬሳ ተሸክመን የምንከረፈፍ ፍጥረቶች አይደለንምን?

ከአስር ዓመታት በፊት የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሚያሳትመው ‹ሰላምታ› መጽሔት ላይ ባነበብኩት አንድ ትንታኔ መሰረት ‹ሊሊ› ከጥንታዊ ግብጻዊያን ዘመን ጀምሮ እንደ ብርቅ የሚታዩ፣ ለአማልክት የሚበረከቱ የአበባ ዓይነቶች ናቸው፡፡ ሊሊ አበቦች በአብዛኛው ውኃ ባቆሩ አካባቢዎች እንደ አልጌ ውኃው ላይ እየተንሳፈፉ ይበቅላሉ፡፡ እነዚህ ሚጢጢ ጌጠኛ አበቦች የድንግልና፣ የንጽህና፣ የውበት፣ የጥንካሬ መገለጫዎች ናቸው፡፡ እናስ ካልጠፋ ስም ለዚህች መከራን ሁሉ ጠቅልላ በጀርባዋ የተሸከመች ጉስቁል ታዳጊ ይህንን ስም ማሸከም ምን ዓይነት መራር ምጸት ነው?! እንጃ! ዘወትር ስለሊሊ ባሰብኩ ቁጥር በቁጭት ወደ አዕምሮዬ የሚመጣው ስም አብደላ ዕዝራ ነው፡፡ አቤት ያመለጠን ዝርው ቅኔ!

Filed in: Amharic