>

የኦሮምኛና  የገዳ ሥርዓት ማስተማርያ ትምህርት ቤቶች የመክፈት እና ተጨማሪ የባዕድ ቋንቋዎች ለኦሮሞ ወጣቶች ብቻ  አዋጅ ፤ አፓርታይዳዊና ወቅቱን ያላገናዘብ አዋጅ ነው..(ታጠቅ  መ  ዙርጋ)

በአዲስ አበባ 57 ሺ አስተማርዮች የሚያስቀጥር  የኦሮምኛና  የገዳ ሥርዓት ማስተማርያ ትምህርት ቤቶች የመክፈት እና ተጨማሪ የባዕድ ቋንቋዎች ለኦሮሞ ወጣቶች ብቻ  አዋጅ ፤ አፓርታይዳዊና ወቅቱን ያላገናዘብ አዋጅ ነው

ታጠቅ  መ  ዙርጋ

 


አስተውሉልኝ ፦ በዚህ ትንሽ ጽሁፍ በርካታ እኔ ያላስተዋልኳቸው ግድፎች ሊኖሩ ይችላሉ። የኔ ፍላጎት  የጽሁፉ እክልየለሽነት/ፕርፌክሽንነት ሳይሆን  መልዕክት ማስተላለፉ  ላይ ነው ። ለሎችም ጽሁፎቼ እንደዚሁም ። 

 

የኦሮምኛና የገዳ ሥርዓት ትምህርት ቤትች በአዲስ አበባ  እቅድ ጉዳይ በአደባባይ ከተነገረ ከሁለት ወራት በላይ ያስቆጠረ  ይመስለኛል ። ሰለሆነም  የነፈሰበት ፣የነጋበት፣ ቅራሬ የሆነ፣ ጅብ ከሄደ ውሻ ጮኽ ወዘተርፈ እንደምትሉኝ ይገባኛል ። መልካችን፣ አስተሳሰባችን፣ ባህሪያችን (ግላዊ ማንነታችን፤personality) አንድ ወጥ እንዳልሆነ ሁሉ ፤ እኔም  አንድ አደባባይ በወጣ አነጋጋሪ አጀንዳ ላይ አስተያየት የምሰጠው ወይም የምተቸው በጽሁፍ ስለሆነ  በአፍላው ወይም በሞቅሞቁ ወቅት  ሃሳብ የመስጠት ልምድ የለኝም።    ጠቅላይ ምኒስተር  አብይ አህመድ  የኢትዮጵያ ሕዝብ የሩቁን ይረሳል፤ የአጭር ግዜ ትውስታ ( short memory) አለው ያሉትን ስምቼ ሳይሆን  ድሮም የተረሳውን ወደ ሰዎች አእምሮ ማምጣት እወዳለሁ።

ጠ/ም አብይ ያሉትም እውነት አለው ፤ አንድ ነገር ሲከሰት እንድ አዶከበሬዎች ሆይ ሆይ እንልና ወዲውኑ እርጭ እንላለ ። ያ የተቃወምነው ጉዳይ አስፈጻሚ ሃይል ግን የተነሳበትን ዓላማ እስኪያሳካ ይቀጥላል ።  ። ተላንት በአገራችንና በህዝባችን ላይ የተፈጸሙ ግዙፍ ደባዎችና ግፎች ሲረሱ ይስተዋላል። የአሁኑ የአገራችን ሁለገብ ነቀርሳ ከየት የመጣነው ? በሽታውን የዘሩት እነማናቸው ? የማን ውርስ ነው ? ብሎ መጠየቅ ያቅተናል።  

ዛሬ አንድ የማንወደው ነገር በተፈጸመ ቁጥር – ወያኖች ይሻሉን ነበር፣ ጀግናው መንግሥቱ ሃ/ማርያም በመጣልን ፣ በዚህ ወቅት የኢሳያስ  አፈወርቂ  ከኛ ጋር መሆን በጣም ጠቃሚ ነው ወዘተርፈ ሲሉ ይደመጣል። አሁን ያለንበት ውስብስብ ችግር  ፥ ከፋሽስቱ መንግሥቱ፣ ከኢሳያስና ከወያኔዎች የወረስነው   መሆኑና ፤ወያኔዎች የመንግሥቱ ስጦታዎች መሆናቸውን  ማገናዘብ ያቅተናል። የትላንትና ዲያብሎስ  /ዴቭል ዛሬ የችግራችን ፈዋሽ ይሆናሉ ብሎ የሚመኙም አሉ ። ነገሩ የቸገረው ……….ያገባል ሆኖባቸው ይሆናል ። ይህ በዚህ እንዳለ ትቼ  ወደ ተነሳሁበት አርእስቴ አመራለሁ።  

ይህንን እርእስ በተመለከተ የተነሱትን የተቃውሞ ፣የድጋፍ፣የመሃል ሰፋሪ ወዘተ አስተያየቶችና ትችቶች በተለያዩ  ማኅበራዊ ሚዲያ ሲስተናገዱ ለመስማትና ለማየት ችዬአለሁ። በመጀመርያ እቅዱና ወሬው አደባባይ እንዲወጣ የተኬደበት መንገድ በሁለት መልክ እፈርጀዋለሁ ።

1.በርግጥም  ሺመልስ አብዲሳ የኔ ናቸው ለሚላቸው ወገኖቹ ለማስደሰት  ያወራውን ሚስጠር እንደ ኮረና ቫይረስ ተምዘግዝጎ ፤ እነኚያ  በሚላቸው  ባዕዳን ጆሮ ገብቶ ፣ ይፋ ወጥቶና አደባባዩን/ፕብሊኩን የሚለውን ከሰሙ በኋላ ፤ ምን ትሆና ላችሁ የተባለው ይኽው እውን እናደርገዋለ ለማለት

  1. ውሳኔውና መርሃግብሩን የሚመለከታቸው   የኦሮሞ ባለሥልጣኖች ተወያይቶበት፣ ዜናው ሾልኮ እንዲወጣ አስድርገውና የህዝብን ስሜትና እይታ ከለኩ በኋላ ፣ ወደዳችሁም ጠላችሁም እቅዳችንና መርሃግብራችን በይፋ ስሙት በማለት መግለጫ ያወጡ  ይመስለኛል ፤ ወይም  ይሆናል በዬ እገምታለሁ።

የውጭ ዜጎች ወደ ጎን ለተውና ፣ አዲስ አበባ የ83+ ብሄር ብሄረሰቦች አባላት የሚኖሩበት ከተማ መሆኑን መንገር የቀባሪ መርዶ ማርዳት ይሆናል። የአዲስ አበባ ነዋሪ ኦሮሞች ከየትኞቹም ብሄር ብሄረሰቦች አባላት ቁጥር አይበልጥም ። ለምሳሌ ከአማራ ፣ከትግሬ ፣ከጉራጌ፣ ከዶርዜ ፣ ከስልጤ ወዘተርፈ ። ታዲያ በምን መስፈርት ነው ለኦሮሞች ብቻ የተለየ ጥቅም/መብት(privilege) የሚሰጠው? 

 በአዲስ አበባ ለሚኖሩ ለሌሎች ብሄር ብሄረሰቦችየአፍ መፍቻ ቋንቋቸውና ባህላቸውን የሚማሩበት ትምህርት ቤት ለምን አይከፈትላቸውም ? የብሄር ብሄረሰቦች የአፍ መፍቻ ቋንቋና ባህል በዘመናዊ ት/ቤት ማስተማርና መማር መብትም ሳይንሳዊም ነው ። 

ነገር ግን አሁን ለኦርሞች ብቻ በተሰጠው ልዩ መብት ዓይነት የሚተገብር አይደለም/አይሆንም ። የብሄር ብሄረሰቦች አውደ ህዝቡ  መሠረት በሆነበት፣ በበቀለበትና በሚኖርበት አካባቢ በተመሰርቱ ት/ቤቶች የሚተገበር ይሆናል፤ እንደውም ቢያንስ እስከ ስድስተኛ ከፍል የሚሰጡ ትምህርቶች በአፍ መፍቻ ቋንቋቸውን ሊማሩ  ይችላል ። 

ይህ ሊሆን የሚቻለው ፣ኢትዮጵያውያን በዲሞክራሲያዊ  መርህ ሕዝባዊ  ሕገመንግሥትና ተቋማት ሲኖራቸው ወይም ሲመሠርቱ፣ በሕዝብ ተወካዮችና በሕግ መወሰኛ  ም/ቤትች  ውይይት ተደርጎበትና በሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ጸድቆ ሥራ ላይ የሚውል  ይሆናል  ። 

ፈላጭ ቆራጭ ገዢ በነበረው በህወሃቱ  -ኢ.ህ.አ.ደ.ግ በሹመት መልክ ወይም የሌሎችን  የምርጫ ኮሮዦ  ተገልብጦ ወደ እነሱ  ኮሮዦ በመጨመር  በምክር ቤቱ በተኮለኮሉበት ፣ ከዝንጆሮ ቆንጆ ምን ይመራርጡ ዓይነቶች ባሉበት  ለመተግበር የሚቃጣ ተራና ቀላል ጽንሰ ሃሳብ አይደለም ።          

በአዲስ አበባ  የኦሮምኛና የገዳ ሥርዓት   ማለት የኦሮሞ ባህል ማስተማርያ  ትምህርት ቤቶች ብቻ  ለመክፈት የታቀደው በምን ጽንሰ ሃሳብና  መስፈርት ይሆን ?  

  አዲስ አበባ የኦሮሚያ ክልል ነው ከሚል የባለቤትነት ጽንሰ አሳብ ይሆን? 

 አዲስ አበባ የሁሉም ኢትዮጵያውያን፣ የሉዓላዊ አገራችን፣ የአፍሪካም ፣ የተለያዩ አገራት ዲፕሎማቶች ወዘተርፈ ዋና  ከተማ ነው በማለት የሚነሱ ክርክሮች ማናናቄያ/ማጣጣያ (show down) ይሆን? 

ኦሮምኛ  ሁለተኛ የመንግሥት የስራ ቋንቋ ለማድረግ በሃሳብ ደረጃ የተነሳው አጀንዳ፣ ሕዝብ ሳይመክርበት ፣ ለአውንታ /አሉታ  ለ( referendum) ሳይቀርብ  ተሽቀዳድሞ እውን ለማድረግ መሞከር፤ 

በቋንቋና ባህል ማስተማር ሰበብ ከየገጠሩ ወደ አ/አ በማስኖገድ  በአዲስ አበባ የኦሮሞ ተወላጆችና  ፣ኦሮምኛ ተናጋሪዮችን ቁጥር ለማሳደግ ይሆን?

 የሥራ ማስታወቄ ሲወጣ ፤ኦሮሞች የአንበሳን ድርሻ እንዲኖራቸው  ታስቦ ይሆን ? ወይስ  ከላይ ለተጠቀሱትን ሁሉ ጥቅሞችና ፍላጎቶች ታሳበው? 

 በአገር ደረጃ  በቁጥር ኅዳጣን ብሄር  ስለሆን  ፥ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማቶች፣የ መንግሥታዊ ፣ የኢ-መንግሥታ ዊ፣  የንግድ ወዘተ..  ድርጅቶች መናኽሬያ በሆነው አዲስ አበባ ፤ ቋንቋችንና  ባህላችን ጎላ ብሎ መታየት አለበት ከማለት ይሆን? 

የህጣዳጣን ብሄር ስለሆን ይህንን የማድረግ ሥልጣን አለን ከማለት አኳያ ክሆነ  ፦

1) ከላይ እንደገለጥኩት ኅዳጣንነታቸው በገጠሩ ኢትየጵያ እንጂ በአዲስ አበባ አይደለም ። በአዲስ አበባም የእኛ ቁጥር ይበዛል ቢሉ እንኳን ፣ ዲሞክራሲያዊ መርህ  አናሳዎች የብዝኋንን መብትና ጥቅም  መደፍጠጥ አይፈቅድም እንጂ ፤ አናሳዎች ብዙሃንን ያገኙትን መብትና ጥቅም አያግኙ አይልም ።  

2) ጀርመንኛ፣ፍራንሳይኛ ፣ቻይንኛና አረብኛ  ወዘተርፈ  በኦሮሞ ክልል ትምህርት ቤቶች  ብቻ  ሊሰጥ መታቀዱን በይፋ ተነገረ ። ይህ አካሄድ በአንዳ አገር መአከላዊ  መንግሥት ሥርዓተ ትምህርት ፖሊሲና የውጭ ቋንቋ የማስተማር መማር ፖሊሲ የሚመራ አይደለምን? 

የኢ ህ አ ዴ ግ  ሕገመንግሥት (ለኔ ሕገጥፋት)  ለዘጠኙ ጎሳ ተኮር የአገዛዝ  ክልሎች የውጭ ፖሊሲ እንዲኖራቸው ይፈቅዳልን? ማለት (የኢ.ፌ.ድ.ሪ  መንግሥት )ተብዬው  ወደጎን ትተው (by pass) አድርገው ፤ በቀጥታ ከውጭ መንግሥታት ተደራድረው የሚፈልጉትን  ወደ ከልላቸው ማስገባት የሚያስችል ሥልጣን ሰጥቷቸዋለን? 

ያ ከሆነ ሌሎች ክልሎች ከላይ የተጠቀሱትን ቋንቋዎችም  ሆኑ ሌሎች ለክልላቸው ወጣቶች ይጠቅማሉ የሚሏቸውን ቋንቋዎች ከባዕድ መንግሥታት ጋር ተነጋግረው  ወደ ክልላቸው  ለምን አያስገቡም? ሕገመንግሥት ተብዬው  የማይፈቅድ ከሆነ ለምን ለኦሮሞ ክልል ብቻ ይፈቀዳል? እነዚህን የባዕድ ቋንቋዎች ለምን ለኦሮሞ ክልል ወጣቶች ብቻ ተመረጡ? 

የኦሮሞ ወጣቶች በእነዚህ ቋንቋዎች የመጠቀም አፍቅሮት ስላላቸው ይሆን? እነዚህን ቋንቋዎች ካልተማርን ትምህርት ቤት አንሄድም ስላሉ ይሆን? በክልላቸው እነዚህን ቋንቋዎች ተናጋሪዮች ስለሚበዙ እነዚህን ቋንቋዎች መማር ግድ/necessity ሆኖ ስለተገኘ ይሆን? ወዘተርፈ። እነዚን ጥያቄዎች ያሰፈርኩት ለምጸታዊ ትችት/satire እንጂ ፤ እነዚህን የባዕድ ቋንቋዎች ለኦሮሚያ ክልል ትምህርት ብቻ የታቀደበት ምክንያት ለምን ጥቅም እነደሆነ  ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ አያውቅም ወይም ያደናግራል  ከማለት አይደለም።

የበርካታ ቋንቋዎች ባለቤት መሆን፣ በበርካታ ቋንቋዎች መገናኘት መቻል፣ በበርካታ ቋንቋዎች -መናገር፣ ማንበብና መጻፍ መቻል ቀላል ዕድልና ቀላል ሃይል አይደለም። እስካሁን ከሚሰጡ  ከአገራችን የሥርዓተ ትምህርት ዓይነቶች በተጨማሪ ፣ ፈራንሳይኛ፣ጀርምንኛ፣ ቻይንኛና አረብኛ  ለኦሮሞ ክልል ወጣቶች ብቻ የሚሰጥ ከሆነ ፤ በሌሎች ክልሎች ከሚማሩ ወጣቶች  ምን ምን የተለየ እድል/opportunity  እንዲያገኙ ታቅዶ ይሆን?

በጥናት ተምርኩዤም ባይሆን ለግዜው የሚታዩኝን ጥቅሞች የሚከተሉትን  ይሆናሉ። 

1.በአገራችን እነዚህን ቋንቋዎች በሚጠቀሙ ድርጅቶች ተቀጥሮ የመስራት ዕድልና ቅድሜያ ይኖራቸዋል

2.ከእነዚህ አገራት የሚገኙ ነጻ የከፍተኛ ትምህርት ዕድል ቅድሜያ ያሠጣቸዋል

3.በእነዚህ አገራት ተቀጥሮ መስራት ያስችላቸዋል

  1. በእነዚህ አገራት ዲፕሎማት ሆኖ ለመሥራት ቅድሜያ ያሰጣቸዋል

5.ለዘመኑ በሚያስፈልጉ የዕድገት ዘርፎች ባደጉ  ሃያል አገራት  መንግሥታት ተፈላጊ ሊሆኑ ይችላሉ፤ ለስለላም ሆነ ለሌላ ተልዕኮ ሊቀጥሯቸው ይችላሉ 

6.ጠለቅ ያለ ምርምርና ጥናት ለሚያስፈልጋቸው ጽሁፎች በእነዚህን ሃገራት ሁሉ  ቋንቋ የተጻፉትን የእውቀት ምንጮች በመጠቀም ከሌሎች የተለየ ውጤት ማግኝት ይችላሉ 

በእነዚህንና በሌሎች ለግዜው ወደ አእምሮዬ  ባልመጡ ጥቅሞች  ተጠቃሚና ተፈላጊ እንዲሆኑ ፤ የረዥም ግዜ እቅድ ስሌት  ወይም  የአቅም ግንባት/ empowerment  እስትራተጂ ነው ባይነኝ ። 

 

ለመሆኑ እንደ እኛው ብዙ  አገር በቀል/ኢንዲጅነስ  ብሄር ብሄረሰብ  ባሉበት – የትኛው አገር ዋና ከተማ ነው  የገዢው መደብ ብሄር ወይም ብሄረሰብ አባላት ብቻ  ቋንቋና ባህል ማስተማርያና መማርያ ት/ቤቶች የሚኖራቸው? በየትኛው እንደ እኛው በርካታ አገር በቀል/ኢንዲጅነስ  ብሄር /ብሄረሰብ ባሉበት ሉዓላዊ አገር ነው  የገዢዩ መደብ  ብሄር አባላት ብቻ ፤ በርካታ የውጭ ቋንቋዎች እንዲማሩ የሚታቀደውና በአዋጅ የሚነገረው ?  በየትኛው ሉዓላዊ አገር ነው  ሁለት ዓይነት የትምህርት ፖልሲ ያለው ? ማለት የገዢው መድብ  በሄር አባላት የመማር- ማስተማር ፖልሲና  የሌሎች ብሄር/ብሄረሰቦች የመማር ማስተማር ፖልሲ የሚለይበት? አሁን በአገራችን እንዲሆን የታቀደው ፖልሲ የቅኝ ገዢዮች የትምህርት ፖልሲ/መመርያ አይደለምን?  

 

እጅግ በጣም ወደኋላ ቀር አስተሳሰብነቱ፣መድሎአዊነቱ፣ኢዲሞክራሲያዊነቱ ወዘተርፈ እንዳለ ሆኖ፤ በዚህ ወቅት ኢትዮጵያና የኢትዮጵያ ሕዝብ እነዚህን ማስተናገድ የሚችል አቅም አላቸውን? ከእነዚህ የሚቀድሙ ችግሮች የሉብንም? 

  1. የ 2020  የዓለም የሰባዊ ምግብ ድርጅት (W.H.F.O ) በአገር ወስጥ ከቄያቸው የተፈናቀሉትን  ጨምሮ 8 ምሊዮን የመሰረታዊ ምግብ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ይጦቁማል
  2. በአንበጣ ወረርሽኝ ከፍተኛ የሰብል አዝመራ በወደመበት 
  3. በጎሳና በሃይማኖት ጸንፈኞች በሺዮች የሚቆጠሩ የንጹሃን ሕይወት በጠፋበት፣ በጥቃቱ አካለ ስንኩላንና ተፈናቃይ በበዛበት፣ ሃብት ንብረት በወደመበት ወዘተ.. 
  4. ኢትዮጵያውያን በህዳሴ ግድብ ወጪ በተወጠሩበት 
  5. ከህዳሴ ግድብ፣ ከተገንጣዮች፣ ከሽፈቶች ፣ ከጭንጋፍ የፍትህና የአገዛዝ ሥርዓት፣ክሥልጣን ተቀናቃኞች ወዘተ.. በተያያዘ  የአገራዊ ሉዓላዊነታችን አዳጋ አፋፍ ላይ በሆነበት ወቅትና ዓመት፤
  • በአዲስ አበባ በሺዮች የሚቆጠሩ የኦሮምኛና የገዳ ሥርዓት ማስተማርያ ት/ቤቶች ማስራት
  •  የመማርያ መሳርያዎችና ቁሳቁሶች ማደራጀት
  • የ57 ሺ አስተማሪዮች ፦ ደሞዝ መክፈልና የመኖርያ ቤትች ማስራት
  • ፍራንሳይኛ፣ ጀርመንኛ፣ ቻይንኛና አረብኛ  ለማስተማር ወዘተርፈ  ማሰብም ሆነ ማቀድ ዕብደት ወይም በሥልጣን መስከር ይሆናል። ወይስ ሲሾም የእኔ ናቸው የሚላቸውን ያልጠቀመ/ ያላቀናጣ ሲሻር ይቆጮዋል ዓይነት ነው ። 

በዲሞክራሲያዊ መርህና ሥርዓት እመራችኋለሁ  ብሎ መማልና መገዘት ለዚህ ነውን? 

Filed in: Amharic