>
5:13 pm - Saturday April 19, 0397

ወስዶ ጣለኝ ደሞ.. ከጎንደር ሑመራ.. መንገደኛው ልቤ... ! (አሰፋ ሀይሉ)

ወስዶ ጣለኝ ደሞ.. ከጎንደር ሑመራ.. መንገደኛው ልቤ… !

አሰፋ ሀይሉ

መንገደኛው ልቤ። ሰሞኑን አላርፍ ብሏል። የሚሰማውን ወሬ እያላመጠ ተነሳሳብኝ። እንዳመሉ። ለጉዞ። ወደ ጎንደር። እና ወደ ለምለሚቷ ሑመራ። እነሆኝ እንደ ወፍ እበራለሁ። ከጎዳናው በላይ። የትዝታ ክንፎቼን ዘርግቼ።
ጎንደር ላይ ነኝ። ከምወደው የመኺናው ጌታ። ብዙ ሀገር በቀን በጨለማ አብረን ካቆራረጥነው። ከጎንደሬው ጓደኛዬ ጋር።
አንድ ቀን እኔና ጓደኛዬ እንዲህ ሆንነ። ጎንደር ላይ እዚህም እዚያም ውሃውን የጨዋ ልጅ መጠጡን እየቀማመስን አምሽተን (የምን አምሽተን?! አጋምሰን) በመጨረሻ ወደ ታድላ ቤት ሄድን። ታድላ የገበያው ባልተቤት። ጀግናዋ አንጎራጓሪ። ታስረቅርቀው እሷስ ድምጿን፣ ከመሰንቆው ጋር። ከጎንደርኛው ችክችካ የከበሮ ምት ጋር። አይጣል ነው እሷ ቤት የሚጠራው ጀግና ብዛቱ፣ የሚወደሰው ሽፍታ ብዛቱ፣ የኢትዮጵያውያን ሜሞሪ  አጭር ነው መባሉን ስሰማ ትዝ ያለችኝ ጎንደሬዋ ታድላ ነች። ከሷ በቀር የዚያን ሁሉ ጀግና ስም በቃሉ የሚወጣው ባለ ሜሞሪ እስከዛሬ ገጥሞኝም አያውቅ!
ብቻ አመሻሽተን ወደሷ ቤት ልንደርስ ስንል ጠበኛ ገጠመን። የማይሸሽ ነገር ሆነና ጓደኛዬ አጠገቡ የቆመውን የአፄ ቴዎድሮስ ሀውልት እያየ ፎከረባቸው ጠበኞቹ ላይ። ትዝ የሚለኝ ግን “ማን መሠልኩህ! ጎንደሬው ነኝ እኔ!” የሚለው ነው። አቅመደካማ መሆኔን ያየው ፈጣሪ ረድቶን ነው መረል ጠቡ በረደ በገላጋይ።
የጓደኛዬ “ጎንደሬው ነኝ!” ፉከራ ግን አበርድ አለ። ሞቅ ብሎናል መሠል። ቶሎ የማንግል፣ ቶሎ የማንበርድ ሆነናል። እና መረረኝ የጎንደሬነት ፉከራው አለማባራት። እና እኔም ቱግ ብዬ ተነሳሁ። ጮክ ብዬ። “እኛምኮ ጎንደሬዎች ነን!” ብዬ ፎከርኩ። ከኋላዬ የቆመው የቋራው አንበሳ በምናምኔ ሹክ ሳይለኝ አይቀርም። እንጂ በጤናዬማ እኔ-ጎንደሬው ለማለት አልደፍርም ነበር።
ልክ ያን ቃል ሳወጣ ጓደኛዬ ቀጥ አደረገው። ፉከራውን። እና ጆሮውን አላመነም መሠል ደግሞ ጠየቀኝ። ምን አልክ?! ብሎ። ደገምኩለት። “እኛምኮ ጎንደሬዎች ነን!”። ጨመርኩበት። “አታግልለን እንጂ!”። በሳቅ ሊሞት ከዚያማ። ሁለታችንም። እና ሁላችንም መሳቅ ብቻ ሆነ። ከዚያን ቀን ጀምሮ መሠለኝ ጎንደሬ ሆኜ ያረፍኩት። ወንድሜ እመነኝ! ከሐረር ጎንደር ድረስ ተጓጉዤ ጎንደሬነትን የተቀበልኩት በዚህ መልኩ ነው። ድንገት። እና በቃ ሆኜ ቀረሁ!!🤣🤣 ወንድሜ! ደሞ በቁምነገር ከጎንደር ጋር እየተፎካከርኩ አይምሰልህ! ያው እንደ ወጉ በውስጤ የሰረፀውን እና ብቅል ያወጣውን ማለቴ ነው! ከዚያማ ጎንደር በመሄዴ “ጎንደሬው ወንድማችን” ከሚሉኝ እህቶቼ ሌላ አንድ ተጨማሪ ምስክር አገኘሁ። ጓደኛዬን። እና ጨዋታ ሲያምረው። አንተማ ጎንደሬ ነህ። ይላል። ያቺን ፉከራ እያስታወስን እንስቃለን።
አሁን ወጣሁልህ ከታድላ ባህል ቤት። ከፋሲል ለገር ከጎንደር። ከጎንደር ከተማ በስተሰሜን ምዕራብ አቅጣጫ። በብልኮ በኩል አድርገን። ከጓደኛዬ ጋር። መድረሻችን ሑመራ ናት። የትናንቱ ድካም አለቀቀኝም። እና ከጎንደር ሳንወጣ ጥቂት ብጣቂ ቅጠላቅጠል ቢጤ ሸመትኩ። መንገዴን በሠላም፣ በፍቅር፣ በጨዋታ ጀባ እንዲልልኝ አስቤ። አንድዬ። እና የደባርቅን መንገድ ትተን በቤተ እስራኤሎች መንደር በኩል አድርገን ወደ ትክል ድንጋይ አቅጣጫ ነጎድን።
ትኩሱ አየር። የባህር ዛፎች። ፅዱ። ሣሩ። ነፍሳችንን መለስ ማድረግ ጀምሯል። በመሐል ግን ጓደኛዬ አባዱላውን ወደ አንዱ በአጣና ግንድ ወደ ታጠረ ቤት አስጠግቶ አቆማት። ምንድነው? አልኩት። ቁ.ም.። ቁርስና-ምሳ ብጤ። ያለፍላጎቴ እሺ ብዬ ገባሁ። የሚገርም ዱለት። ቀመስኩ።
ከዚያ ግን የቤት ጠላ። ወቸጉድ! ይሄም አለ ለካ? ጠላ ቢሉህ ጠላ ነው እንዴ ወንድሜ?! እናቴ ቤት ለመጨረሻ ጊዜ ጠላ ከቀመስኩ ዓመታት ተቆጥረዋል። እና ጎንደር ሳታቀምሰኝ ልትለቀኝ አልፈለገችምና ሁለት የክቡር ዘበኛ ብርጭቆ አዘራረድኩ። ወደ ደረቀ ጉሮሮዬ። እሱ ደግሞ በውሃ ፕላስቲክ አንቆረቆረው። ስለምነዳ ኋላ ላይ ነው የምጠጣው ብሎ። የጠጣም ያልጠጣም አብረን አመስግነን ተሰናብተን ወጣን።
ቀጠለ መንገዳችን። የፋሲል ደሞዝን ዘፈን ጮክ አድርገን ከፍተን። ፋሲል ደሞዝ… “አለ ነገር .. ዘንድሮ አለ ነገር…!” ይላል በሚስረቀረቅ ፍፁም ባህላዊ፣ ፍፁም ቀበሊኛ ለዛ ባለው ድሞፁ…:። ይሄ ዘፈን ይገርመኛል። ፋሲል ደሞዝ የሥርዓቱን ያደባባይ ቀማኛነት ፊትለፊት ባደባባይ የገለፀበት ዘፈኑ ነው። ጎንደሮች ነፍሳቸው ነው። ታክሲ ውስጥ ትሰማዋለህ። ምግብ ቤት። ሱቅ። ሰፈር። በየቤቱ። ጭራሽ ይውጣልህ ሲለኝ ፋሲል ደሞዝ ፋሲል ግንቡ ጋር ባለው ሰፊ ሜዳ ላይ ኮንሰርት ሲያዘጋ፣ ራቅ ከፍ ብዬ እንደ አሞራ፣ ከሴንትራል ጣሪያ ላይ ሆኜ ነቅነቅ እያልኩ ለመታደም በቃሁ። ይነሽጣል። ፈገግታም ይለግሳል። የፋሲል “ዘንድሮ አለ ነገር…!”
“አረሱት ይሉኛል የሑመራን መሬት
አረሱት አረሱት ያውም የኛን መሬት
ያውም የእኛን ዕጣ
እነሱ ምን ያርጉ ከኛ ሰው ሲታጣ?!!…
“ለእኛ እስከሚመጣ የሚበጀን ነገር
አለ ነገር
ዘንድሮ አለ ነገር…!”
አለ ነገርን እየሰማን ትክል ድንጋይ ልንደርስ ጥቂት ሲቀር ወጠምሻ ወጣቶች ከበው በዱላ መሬት ላይ የሆነ ነገር ከምረው ይወቁታል። በትራቸውን የሚያነሱትና የሚመቱት ልክ በተጠና (ኬሪዮግራፍድ የተደረገ በሚመስል) ስልታዊ ውዝዋዜ ዓይነት ነው። ገረመኝ። ምንድነው መሬት ላይ አስጣጥተው የሚነርቱት? – ጌሾ ነው። ለካ የጌሾ ወቀጣ ነው። እነዚህ የጎንደር ወጣቶች አንድ ቀን ይሄን ቀማኛ ሥርዓት እንደ ጌሾ ይወቅጡታል…። እያልኩ እያሰብኩ አለፍኳቸው። የጠጣሁት ጌሾ ይሆን እንዲያ ያሳሰበኝ?! የኔ ነገር! ገለባ ልብ! እንደመሩት ነው! አወይ እኔ!
ትክል ድንጋይ ደረስን። ትልልቅ የተራራ ጉማጆች እንደ ጢያ ድንጋዮች ተተክለው በከተማው መግቢያ ቆመዋል። ያስደምማሉ። ትክል ድንጋይ የጀግኖች ሀገር ነው። የቆራጦች። አይታለፍም። አረፍ አልን እዚያም። የሆነ ነገር ጎንጨት ብሐን ላመል፣ ጓደኛዬ ወዳጆቹን የወጪ ምናምን ገባብዞ ወጣን። ወጣን ሳይሆን ወረድን ቁልቁለቱን። ወደ ሁመራ።
ወንድሜ?! ሑመራን እንዲሁ ባንዴ ዘለህ አትደርስባትም። ለምሳሌ “ሳንጃ” አለችልህ በመሐል። ሳንጃ ምንድነው? ካልከኝ – ሳንጃ ከጥንት የነበረች፣ አሁንም ያለች፣ ወደፊትም የምትኖር የጀግኖች ከተማ ነች። ከጭልጋ ቀጥሎ ብዙ ቅማንት ጎንደሬዎች የሚኖሩባት ምድርም ናት። ጭልጋ። አነስ ያለች። ግን ድምቅ እና ሞቅ ያለች ከተማ ናት።
አንድ ከሳንጃ የገረመኝ ነገር ሰዎች መሣሪያ ታጥቀው ነው የሚንቀሳቀሱባት። ባህል ነው መሠል። የመጀመሪያ ጊዜ ሻይ ቤት በረንዳ ላይ ሁሉም ክላሹን ካጠገቡ እያስደገፈ ቁጭ ሲል በሠላም ሻይ ቡና ቀምሶ ሊሄድ – በሽፍታ የተከበብን እየመሠለኝ ስንት ጊዜ ዕጢዬ ዱብ አለ። ኋላ ግን ለመድኩት። እንዲያውም ይናፍቀኝ ጀመር። የታጠቀን። ጀግናን ማየት። ወንድ ከሆኑማ መታጠቅ ነው እንጂ። እንዲህ እንደ ሳንጃዎች።
ምናልባት በወታደራዊው ደርግ ዘመን “ሳንጃው ሰው በላ” ተብሎ የተገጠመላት ይህች ሳንጃ ትሆን፣ ወይስ የወታደሩ መውጊያ ሳንጃ?! በምን አውቄው? ይቺን ከተማ የብአዴኑ አዲሱ ለገሰ ከወያኔ ጋር ጫካ እያለ ሁነኛ መሰንበቻው ነበረች አሉኝ። ሳንጃ ሴቶቿም ውቦችና ተግባቢዎች መሆናቸውን አስተውዬአለሁ። ሳንጃን ከረገጥካት ጊዜህን ሳትበላብህ አትለቅህም። ተሰናበትናት። ከከተማዋ ስንወጣ ከባድ የፍተሻ ኬላ አልፈን ነው። ጓደኛዬ ሁሉም ዘመዱ ነው። እዚያም ዘመዱን አገኘና ፍተሻችንን አቀለለልን። ጎንደር የምትኖረው በእምነት ነው። በክሯ ነው። ትተዋወቃለህ። እና ትተማመናለህ። የሚገርም “ቦንዴጅ” አያለሁ በየሰዉ መሐል። በጎንደር በሞላ። ይገርመኛል። የድሮዋን ሐረር፣ ወይ የድሮዋን አዲሳባ ያስታውሱኛል።
ከሳንጃ ኮረዶች እንክብካቤ እንደምንም ራሳችንን አላቀን መንጭቀን ተነሳን። ወደ ለምለሚቱ ሁመራ። ወንድሜ! አሁንም አትቸኩል። ሁመራ ባንዴ ተዘልሎ አይደረስም። ብዙ ኪሎሜትሮች ተጉዘህ፣ ብዙ ተራራና ቁጥቋጦ፣ ብዙ የአርማጬሆን ሜዳና ጫካ አልፈህ መሄድ ይኖርብሀል።
በነገራችን ላይ በዚህ ሁሉ ዓመታት ውስጥ ይህ የጀግኖች ሀገር – “ታች አርማጭሆ” (እና “ላይ አርማጭሆ”) – በዘሠነ ኢህአዴግ በሙሉ እስካሁንም ድረስ ከምሽቱ 12:00 ሰዓት ጀምሮ በልዩ ፍቃድ ካልሆነ በቀር መኪና አይንቀሳቀስበትም! ምክንያት? “ሽፍቶች!”። የአርማጭሆ ሽፍቶች – ራሷ ከሽፍትነት ተነስታ መንግሥት የሆነችውን ወያኔን በጨረቃ ሰዓት አያሳልፏትም። አርበኝነታቸው ይገርመኝ ነበር።
በእነዚህ ሁሉ ዓመታት “ቀኑን ለሠራዊት፣ ሌቱን ለአራዊት” ብሎ እኩል 12-12 ሰዓታትን ከሽፍቶች ጋር ተካፍሎ የሚኖር መንግሥት ባለም ላይ ከጣልያን ሲሲሊ እና ከብራዚል ፋቬላዎች ቀጥሎ አርማጭሆ ሶስተኛው አስገራሚም፣ አስደንባሪም ሀገር ሳይሆን አይቀርም። ጀግና። የጀግና ሀገር ነው። ሁሉም እንደነሱ ቢሆን…!! (ኧረ በተሰቀለው!)። እንዲህ ተብሎ የተቀነቀነው ለእነሱ መሆኑን አትዘንጋ፦
“ማረሻው ምንሽር መጎልጎያው ጓንዴ
ሰሜን አርማጭሆ ወልቃይት ጠገዴ”
ብዙ ጊዜ በሽፍታ የተዘረፉ ያጋጥሙናል። እየተዘረፈም አጋጥሞን ያውቃል መሠለኝ። የምስኪኖች አምላክ አንድዬ ፀሎቱንም ዱአውንም እየሰማን መሠለኝ እኛን ተተናኩሎን ያወቀ ሽፍታ የለም። የሚገርመኝ መንገዱን በምሽትም ተዳፍረን እናውቃለን። የእንጀራ ገመድ ሆኖብን። አያድርስ እኮ ነው።
ድንገት ሽፍታ ቢይዘን ደሞ ዘርፎ ብቻ አይለቅህም። ዘርፎህ ሲሄድ እንዳታየው – ፊትህን ወደዚያ አዙርና አዲሱን የፋሲል ደሞዝን ዘፈን ዝፈንልኝ – ይልሀል። እስክስ እያልክ ነዋ ያውም የምታስነካው። ካልዘፈንክ ሽፍታ በሰው ተመርሮ፣ ተገፍቶ የወጣ ሰው ነው። ካመረረ ጭካኔው ከባድ ነው። ዕድለኛ ከሆንክ በእሾህ ገርፎ ይለቅሀል። ካልሆንክም ቀንድቦ ይገላግልሀል።
አልዋሽህም። ለመጠባበቂያ የሚሆኑ ብዙ አዳዲስ ዘፈንችን አጥንቼያለሁ። ኧረረረረ.. ምንድነው ነገሩ?! የሚለውን የፋሲልን። የአምሳል ምትኬን። ወዘተ ዘፈኖች። ግን ድምፄን ሳልፈትሽ ወጣሁ። ለኛስ ሠላም ነበረ። ምድሩ። መንገዱ። ሰዉ። ሳሩ ሁሉ። ፈጣሪ ብድራቱን አይንሳቸው ማለት ማንን ገደለ!? አዎ አይንሳቸው!
አሁንም መንገድ ላይ ነን። ብዙ ከተጓዝን በኋላ ድንገት ለምለሙ መስክ አልቆ ተዳፋቱ የሚጀምርባት ወይናደጋ ቦታ ላይ ደረስን። ለምለም ማድጋዋ የማይጎድልባት፣ ሌማቷ የማይደርቅባት፣ መሶቧ የማይራቆትባት ለምለም ከተማ። አሸሬ። አሸሬ ሁሉም ከሩቅ ሀገር የመጣ መንገደኛ ከመኪናው ወርዶ ምሳውን የሚበላባት ትንሽዬ ከተማ ነች።
አሁን ስሟ ተዘነጋኝ የአንድ ሁነኛ ምግብ ቤት ባለቤት። አሁን በልቶ ካጅ እንደኔ ያለ ይገኛል? እንዴት ልርሳት? ይሄ አልዛይመርስማ በሥነሥር ዓት ሳይጀማምረኝ አይቀርም። ስንቱን ነገር ነው እየረሳሁ የተቸገርኩት! ብቻ አሸሬ – እርጎዋ ይምጣብኝ – አቤት ሙያ! አቤት እንጀራው! ቅቤው! ቸርነታቸው! ስስት አይታወቅም በአሸሬ። ሁሉም ዘር፣ ቋንቋ፣ ኬት መጣህ፣ ወዴትነህ ሳይጠየቅ በልቶባት ጠጥቶባት ይሄዳል። አንዳንዴ በሉ ሲላቸው ሂሳብ ላለመቀበል ሁሉ ያግደረድሩሀል። ምርጥ ደግ ሰዎች!! ሌማታቸው ይለምልምላቸው! አሸሬን ሽርርርር ያድርጋት አንድዬ። ብዬ መረቅኳት።
ወንድሜ! መንጥከህ ካልተነሳህ ያሰብክበት አትደርስም። እና ተነስ። ራሳችንን ከምቾት መሐል እንደምንም አጀግነን ተነሳን። ወደ ቀጣይዋ መዳረሻ ወደ ሰሮቃ። አይ ሰሮቃ! ሰሮቃ ትንሽዬ ፍልቅልቅ ያለች የድንበር ከተማ ነች። የሰሮቃን ወንዝ ታክካ የተቀለሰች ዘመን ያስቆጠረች ወረዳ ነች። የዕድሜዋን ያህል ግን አላደገችም። የመጣ ሥርዓት ሁሉ ባለችበት አስረግጧታል ማለት ነው። እንዲያም ሆና ግን በአቅሟ የደራች ነች። የከተማነት ግርማ አላት። እና ከምንም በላይ የትግራይ ክልልን እና የአማራ ክልልን የምትለይ ከተማ ነች። ያ የሰሮቃ ወንዝ የከፈለው ድንበር ቀልድ አይምሰልህ። የአማራን ሕዝብ ላለፉት 20 ዓመታት ደሙን ሲያንተከትክ የኖረ የተሸናፊነት ምልክት ነው ድንበሩ። የትግራይና የጎንደር መለያያ ድንበር። ሰሮቃ።
የትግሬና የጎንደር መለያያ (ወይም በትክክለኛ ቃሉ መዋሰኛቸው) ተከዜ ወንዝ ነበረ። በየትኛውም ዘመን ከተከዜ ወዲህ -ሁመራ፣ ወልቃይት፣ ፀገዴና ጠለምትን – እስከ ሰሮቃ ድረስ ያለውን የትግሬ ገዢ አስተዳድሮት አያውቅም በታሪክ። ይህ ሁሉም የሚመሰክረው ሀቅ ነው። ድንገት ግን በ90ዎቹ መጀመሪያ ላይ ራሺያዋ ወያኔ መጣችና አካባቢውን ክሪሚያ አድርጋው አረፈች። ከሰሮቃ እስከ ተከዜ ወንዝ (ማለትም እስከ ኤርትራና ሱዳን ድንበር ድረስ) ያለውን ሰፊ ሜዳማና ሞቃታማ የሠሊጥና ጥጥ ማሽላ አብቃይ ግዛት በመትየሷ ቀማቻቸው። ከአማሮች ላይ። ወያኔ የግዛቱ አስተዳዳሪ ሆነችና፣ ብአዴንን ከሰሮቃ እንዳታልፍ አለችው። ቢያንገራግር የሚደርስበትን ያውቃል። ኦነግን ያየ ከወያኔ ጋር አይቀልድም። እና በተከዜ ሜትክ በተሰመረለት የሰሮቃ ወንዝ ድንበሩ ስር አርፎ ኩርምት ብሎ ተቀመጠ። ብአዴን።
ከሰሮቃ ወንዙ አልፎ “ፀገዴ” ተብሎ ተሰይሟል። ከወንዙ ወዲህ ደግሞ “ጠገዴ” ተብሎ ነው የሚጠራው። ወያኔ በታጣፊ ክላሽና በመትረየስ አንድ ወረዳን ለሁለት ከፍላ አንዱን “ጠ” አንዱን ደሞ “ፀ” ብላ በፊደል ለየቻቸው። ፀ – የትግራዩ ነው። ፂላ – እንደሚባለው – ፀን ለራሷ ወሰደች። ጠን ሰጠቻቸው። ጠገዴ እና ፀገዴ። አማራ ሁሉ እዚህች ሰሮቃ ላይ ሲደርስ ልቡ ይሸበራል። ምስክርነቱን ይሰጥሀል። እና አንድ ቀን እስከ ተከዜ ያለውን መሬታችንን ከወያኔ ላይ ማስመለሳችን አይቀርም ይልሀል። ወልቃይት አማራ ነው ይልሀል። እና ወያኔን አላስኬድ አላስቀምጥ ያሉትን ሽፍቶች ማታ ላይ ቀግጥምና ዜማ ያወድሳል።
ወያኔ የዓለማቀፉ የድንበር ዳኛ የኢሮብ ወረዳዎችን ሁለት ቦታ ቆርሶ – ግማሹን ለኢትዮጵያ ግማሹን ለኤርትራ ሲደለድል ወያኔዎች እሪሪ ብለው ነበር። አንድን ሕዝብ ሉለት ብታ ከፍሎ የነጣጠለ ውሳኔ ነው በማለት። እነሱ ግን ከዓለማቀፉ የዳኝነት ተቋም ቀድመው ዳኛም ጠበቃም በሌለበት አንድን ሕዝብ ፀ እና ጠ ብለው ሁለት ቦታ ከፍለው የሌላን ሕዝብ ግዛት ቀምተዋል። ይሄ ቅሚያ ሕዝብና ሕዝብን አቃቅሮ ማለፉ ብቻ ሳይሆን የወደፊት የግጭት መንሥዔ እንደሚሆን ብዙዎች መክረው ነበር። ወያኔ ግን መስሚያ ጆሮ አልነበራትም።
ወደ 700 ሺህ የሚሆኑ የትግራይና ኢሮብ ተወላጆችን ከሽረ፣ አሊቴና፣ አዲግራት፣ ዛላንበሳ፣ ሽራሮ፣ ወዘተ እያመጣች፣ የቀድሞ የህወሀት የቆሰሉ ታጋዮችን እያመጣች.. በቀማችው ምድር ላይ አሰፈረቻቸው። እና የሥራ ቋንቋውን በራሷ ቀየረች። የተቀናቀኗትን ሁሉ በጥይት ፈጀቻቸው። ሌሎቹን አርቃ ሰደደቻቸው። የቦታዎቹን ስሞች ቀያየረች።  አሁን ከሚሊየን በላይ ትግራዮች በዚህ መሬት ላይ ሰፍረው፣ ቤተሰብ መሥርተው እየኖሩ ነው። እና ልክ ሩሲያ ክሪሚያን ስትወስድ እንዳደረችው – ወያኔንም ሑመራን፣ ወልቃዬትን፣ ፀለምትን፣ ፀገዴን መልሺ ስትላት – “የኔ ነው፣ ምዕራባዊ ትግራይ ነው፣ ካላመንክ ነዋሪዎቹን ጠይቃቸው!” ትልሀለች። አይ ወያኔ!
ወያኔ የሰው ግዛትን ሳትቀማ የትግራይ ተወላጆችን በሠላም አምጥታ ብታሰፍር ኖሮ ሀገራቸው ኢትዮጵያ ነው ማን ይናገራቸው ነበር? ብአዴን መሬቱን እያስተዳደረ ሌሎች ሕዝቦችም ሳይበደሉ የቸገረውን የትግራይ ሕዝብ ማስፈርና በሠላም ማኖር አይቻልም ነበር ወይ? ታዲያ ወያኔ ሠላምንና ጥበብን ትታ ልክ እንደ ወራሪ ሀገር በጉልበት የሰውን መሬት ወደራሷ መጠቅለል ለምን አስፈለጋት? የታላቋ ትግራይ ሪፐብሊክ ህልም ይሆን ያን ያስደረጋቸው? ወይስ የድርቅና ልማድ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሶባት? አላውቅም በእውነቱ ምክንያቱን። አንድዬ ይወቅ። የጎንደር ሰው ግን እንዲህ እያለ ያንጎራጉራል፦
“ወልቃይት ፀገዴ
ወልቃይት ፀገዴ
ከሃያ ዓመት በፊት
ትግራይ ነበርክ እንዴ?”
በወያኔ ቅሚያ ላይ የተደረደረው ግጥሙና ስንኙ ብዙ ነው። አንዱ ደሞ የአማራው መደፈር ያንገበገበው እንዲህ ይላል፦
“ወይ ሀገሬ ዳባት፣ የነጋታው ሀገር፣ ሀገሬ ወገራ
ሀገሬ ወፍ አርግፍ፣ ወልቃይት ጠገዴ፣ ዳንሻና ሑመራ
ወይ ሀገሬ ጭልጋ፣ ወይ ሀገሬ ቋራ
አባ ታጠቅ ጎንደር፣ የጀግኖቹ ጎራ
እንደምን ይደፈር፣ በራበው አሞራ?”
የራበው አሞራ የተባለችው ወያኔ መሆኗ ነው መሠል። ወይ አሞራ?! ይኸው ስትመከር አልሰማ ብላ ጩልሌ ሆናለች። ከዚህም ከዚያም ተጠራርቶ የወያኔን ክንፍ ሊሰብር ተነስቶባታል በሆዱ ችሏት የኖረው ሁሉ ዛሬ። አንዱን ግጥም ለዛሬ የመጨረሻዬ ላድርገውና፣ በቀጣይ ደግሞ በትዝታ በረራዬ ካቆምኩበት ከሰሮቃ ጀምሬ – ዲቪዥንን፣ ማይ ዴሌን፣ ዳንሻን፣ ረዊያንን፣ ሁመራንና ተከዜን (ሩባ ተከዘን) ላነሳሳ ዳግመኛ እመጣለሁ። የዚያ ሰው ይበለን። ቸር ቸሩን ያሰማን። ሠላም ለሀገራችን ለሕዝባችን ይሁን።
“ተላላ ነው ሀገር፣ ሀገር ተላላ ነው፣
ይጓዛል እንደሰው
በየበሩ ቆሞ ጀግና ካልመለሰው”
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን አብዝቶ ይባርክ።
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር።
ሠላም።
Filed in: Amharic