>
5:13 pm - Tuesday April 19, 7842

ከመቀሌ ባሻገር. . .!!! (ያያ አበበ)

ከመቀሌ ባሻገር. . .!!!

ያያ አበበ

 

— 1. ዐቢይ እና አብርሃም —
አሜሪከ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የገጠማት ሕገ-መንግስታዊ ቀውስ ወደ እርስ በርስ ጦርነት አምርቶ አያሌ ሰዎች ሞተዋል።
የዚያ ጦርነት ምክንያቱ ባርነትን ማስቀጠል በፈለጉ የደቡብ ክፍለ ግዛቶችና በሰሜኑ የፕሬዘደንት አብርሃም ሊንከን መንግስት መካከል ነበር።
በሀገራችንም የፌደራል ሕገ-መንግስቱን የጣሰው የእነ ደብረጽዮን አመራር የሰሜን ዕዝ ላይ ያደረሰው የክህደት ጥቃትን ተከትሎ የፌደራል መንግስት የወሰደው የኃይል እርምጃ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስታዊነትን ከማጽናት አንጻር ወሳኝ ሂደት ነው።
 
— 2. ሕገ-መንግስታዊ አንድምታ —
በትግራይ ከሚደረገው ሕገ-መንግስት የማስከበር ዘመቻ አንጻር ፡ “የተጻፈበትን ወረቀት አይመጥንም” ሲባል የነበረው ሕገ-መንግስት ነፍዝ ዘርቷል። ጥርስ አብርቅሏል።
ሕገ-መንግስቱ ደም ፈሶለታል። ህይወት ተሰውቶለታል። የሕገ-መንግስቱ ዋጋ ከመቼውም በላይ ከፍ ብሏል።
የሕገ-መንግስቱ መጽናት ፡ በተለይም የፈደራል ሪፐብሊኩ መሰረት የሆነውን የብሔር ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦችን ሉዓላዊነት ቀድሶቷል ፡ የማይነካ (sacred) አድርጎታል።
ከዚህ አንጻር “ህወሓት ከሌለ ሕገ-መንግስቱ ይሰረዛል” የሚል ቀቢጸ ተስፋ ውስጥ የገቡ ወገኖች ምኞት ከንቱ  ነው።
የሕግ የበላይነት በሀገራችን ገጥሞት የኖረው ዋና ፈተና ፡ ሕገ-መንግስቱን ባረቀቁትና ባጸደቁት ልሂቃንና ድርጂቶች ላይ ጭምር የበላይ የማድረጉ ጉዳይ ነው።
ከዚህ አንጻር እነ ደብረፅዮን ላይ ሕገ-መንግስቱን የበላይ ማድረጉ በሀገሪቱ ታሪክ አዲስና ፡ ድንቅ የሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ ግንባታ ከፍታና ምዕራፍ ነው።
 
— 3. ፓለቲካዊ ፈተናዎች —
ከመቀሌ ባሻገር የዐቢይም ሆነ የብልጽግና ፓርቲ ቅቡልነት ይጨምር ይሆናል እንጂ አይቀንስም።
ከዚህ አንጻር የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፓለቲካዊ ወረትና የገዢው ፓርቲ ስልጣንን በሕገ-መንግስቱ የመግራት ትግል ከመቼውም በላይ ወሳኝ ጉዳይ ነው።
ይሄን ጉዳይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ልዩ ትኩረት ሊሰጡትና በምርጫ ወቅት ብልጽግና ፓርቲን ለመፎካከር እንዲችሉ አቅማቸውን ቢያስተባብሩ ለሀገሪቱ ፋይዳው ትልቅ ነው።
የዜጎች ማህበራት (civic societies) ንቁ ተሳትፎና ጫና ፤ የመገናኛ ብዙሃን የሀሳብ ልዩነትን ማስተናገድ ፤ እንዲሁም የፓለቲካ ድርጂቶች ሕገ-መንግስታዊ አርበኝነት ለሕገ-መንግስታዊ ዴሞክራሲ በቀጣይነት መዳበር ወሳኝ ናቸው።
ለጠ/ሚ ዐቢይ እና ለብልጽግና ፓርቲ የሚመጥን ብቁና ወቅቱን ያገናዘበ የተቃዋሚ ጎራ መኖሩ በገዢው ፓርቲ እጅ ውስጥ የተከማቸው የፓለቲካ ጉልበት ለሙስናና ለብክነት አገሪቱን እንዳይዳርግ ጫና ለማድረግ አስፈላጊ ነው።
— 4. የትግራይ ክልል ፓለቲካና አስፈላጊው ጥንቃቄ —
በትግራይ ክልል ተጠርጣሪዎችን ለሕግ የማቅረቡ ጉዳይን ተከትሎ የክልሉ ፓለቲካ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ከሚሹ ጉዳዮች ውስጥ ጥቂቶቹ፦
4.1 ትርክታዊ ጥንቃቄ፦
ቅጽበታዊ ፡ ፈጣንና የህዝቡን ስነ-ልቦና የሚያስበረግጉ የትርክት ለውጦችን ከማድረግ መቆጠብ ከ33 አመታት በላይ በአንድ ፓርቲ ስር ለኖረው የትግራይ ህዝባችን አስፈላጊና ጠቃሚ እንክባቤ ነው።
የቂም ፡ የበቀልና የሂሳብ ማወራረድ ጉዳይን የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ እና አመራራቸው አስቀድመውና ደጋግመው ቀይ መስመር ሊያሰምሩበት ይገባል።
የቀደምት ሰማዕታት ታጋዮችን ክብር ከሚያረክሱ ኃላፊነት የጎደላቸው ቃላትና ፍረጃዎች በመቆጠብ የህዝቡን ስነ-ልቦና ማክበርን ጉዳይ በዋናነት የብልጽግና ፓርቲ ፡ በተጨማሪ የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች እጂግ በጣም ሊቆጠቡ ይገባል።
በተጋሩ ልቦና ውስጥ ግዙፍ ቦታ ያላቸውን ሰማዕታትን ታጋዮችን (እነ አቶ መለስ ዜናዊን ጨምሮ) የማርከስ ዝንባሌዎችን በማክሰም የህዝቡን ስሜት በጊዜያዊ አስተዳደሩ ወቅት ከእንግልት መጠበቅና የክልሉን ፓለቲካ ከዋልታረገጥነት መታደግ አስተዋይነት ነው።
ያለፉ ስኬቶችን ከጉዳቶች መለየት ሲቻልና ፡ በስኬቶች ላይ በመገንባት “መደመር” እንጂ ስር-ነቀል መሳይ ዝንባሌዎች ለክልሉ ፓለቲካ አቅም ከአጭር ጊዜ አንጻር አይመጥኑም።
4.2 የሹመት አደጋዎች (ከአማራ ክልል ስህተት መማር)፦
የጊዜያዊ አስተዳደሩ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ሙሉ ነጋ በቅርቡ መግለጫቸው ያነሱት ቁልፍ ጉዳይ በክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊነት ላይ የሚሾሙ ግለሰቦች ጀርባን የሚመለከት ነው።
በአማራ ክልል እነ ዶ/ር አምባቸው ላይ እና ተያይዞም እነ ጄ/ል ሰዓረ ላይ የደረሰው አይነት ውስጣዊ ክህደትና ጥቃት እንዳይደርስ አስቀድሞ ለመከላከል እንዲቻል ፡ ከተቃዋሚውም ሆነ ከነባሩ የክልሉ ገዢ ፓርቲ ውስጥ የሚሾሙ ግለሰቦች በጣም ያፈነገጠ መስመር ውስጥ ያልነበሩና በተለያየ ምክንያት ከሀገሪቱ ውስጣዊ ፓለቲካ ለረዥም ጊዜ ርቀው የኖሩ አይሁኑ።
በተጨማሪም ጊዜያዊ አስተዳደሩ የሚሾማቸው ግለሰቦች ከዚህ ቀደም ያሳዩዋቸው ስነ-ምግባራዊና ፓለቲካዊ ጨዋነታቸው እንደ ዋና መስፈርት ሊካተቱ ይገባል።
በአንጻሩ ግን ፡ በተቃዋሚው ጎራ ውስጥ ከክልሉ ፓለቲካ ጋር ተያይዞ ብዙ በደል የደረሰባቸውን ግለሰቦች በጊዜያዊው አስተዳደር ውስጥ ኃላፊነት ውስጥ ከመሾም መቆጠብ አላስፈላጊ መወሳሰብን አስቀድሞ ለመከላከል መወሰድ የሚገባው ጥንቃቄ ነው።
4.3 ምስራቅ አፍሪካዊ ስጋቶች
የምስራቅ አፍሪካ ወቅታዊ ፓለቲካዊ ቁመናዎች ለኢትዮጵያ ጥቅም ዛሬ ባላቸው ተስማሚና ምቹ ደረጃ በዘላቂነት የመቀጠላቸው ጉዳይ አጠያያቂ ነው።
የኤርትራ ፕሬዘደንት እድሜ ፤ የሁለቱም ሱዳኖች መንግስታት ውስጣዊ ቀውሶች ፤ የሶማሊያ ነባር አለመረጋጋት ፤ የግብጽ ውስጣዊ ፓለቲካዊ ውጥረትና በኢትዮጵያ ጉዳይ ጣልቃ ገብነት ተዳምረው የምስራቅ አፍሪካን ቀጠና ፓለቲካ ከኢትዮጵያ ጥቅም አንጻር የ10 አመታት ትንታኔ ለመስራት አስቸጋሪ ያደርጉታል።
ከዚህ አንጻር የሕገ-መንግስት ማስከበር ዘመቻው የሚፈጥራቸው ጀግኖች ሊያነሱት የሚችሉትን የይገባኛል እና ‘የባለርስትነት’ ጉዳዮችንም ሆነ ሌሎች የሚያቆጠቁጡ ፍላጎቶችን አስቀድሞ መግራት ወደፊት ሊነሱ የሚችሉ ፓለቲካዊ ቅራኔዎችን አስቀድሞ የመቆጣጠሪያ ቁልፍ ስልት ነው።
ማንኛውም የማንነትና የወሰን ጥያቄ ከሕገ-መንግስት ማዕቀፍ ውጪ መፍታት እንደማይቻል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የብልጽግና ፓርቲ ደጋግመው ማስረጽ ያለባቸው ጉዳይ ነው።
ማህበራዊ ሚዲያዎች ከነውጥ ነጋዴዎች መሳሪያነታቸው አንጻር ክልሉ እስኪረጋጋ ድረስ ለጥቂት ወራት ተዘግተው ቢቆዩ ዘላቂ ሰላምና መረጋጋት ከማስፈን አንጻር ስልታዊ ፋይዳ አለው።
በትግራይም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች የሚወሰዱ ፓለቲካዊና ወታደራዊ እርምጃዎች ወደፊት በሚፈጠሩ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ቀውሶች እንዳይበዘበዙ ለመጠንቀቅ ፡ ወቅታዊ ፓለቲካዊ ሂደቶችን አስቀድሞ መቆጣጠርና ሚዛን ማስያዝ “የመቀሌ ባሻገር” ሀገራዊ የቤት ስራችን ነው።
——-
ማስታወሻ
የሕግ ማስከበር ዘመቻው የወንድማማቾች ቅራኔ በመሆኑ በየትኛውም ወገን የሞቱትንና የቆሰሉትን ወገኖች ፡ የተንገላቱ ዜጎችንና የወደሙ ንብረቶችን በቁጭት እናስታውሳለን እንጂ ሀሴት የምናደርግበት አንዳች ምክንያት የለንም ፡ አይኖረንምም።
Filed in: Amharic