>

ለግንዛቤ ያህል፤ ስለ አለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት ሲባል...!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ለግንዛቤ ያህል፤ ስለ አለም አቀፍ ጣልቃ ገብነት ሲባል…!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

ትላንት ጠቅላይ ሚንስትር አብይ ጣልቃ አትግቡብን በሚል የተባበሩት መንግስታት ቻርተር አንቀጽ 2(7)ን በመጥቀስ የጻፉትን ማሳሰቢያ በመቃወም ሃሳቤን  ሁለት የተጋጩ… ገልጬ ነበር። ብዙዎች ያነሳሁትን ሃሳብ በመቃወም ጽፈውልኛል። እንዳብራራውም የጠየቁኝ አሉ። አንዳንዶች ሃሳቡንም በቅጡ ሳይረዱ በስሜት ብቻ እንቧ ከረዩ ያሉ አሉ።
ለማንኛውም ከላይ የተጠቀሰው የቻርተሩ አንቀጽ የሰነዱ አወዛጋቢና ለትርጉም የተጋለጡ ከሚባሉት አንቀጽች አንዱ ነው። ሦስት ለትርጉም አሻሚ የሆኑ ነገር ግን መሠረታዊ ሃሳቦችን የያዘ አንቀጽ ነው። እነሱም ፦ የአገር ሉአላዊነት (sovereignty)፣ ጣልቃ ገብነት (intervention) እና ሊደርሱ የሚችሉ ሰብአዊ ቀውሶችን መከላከል (prevention) ናቸው።
ለጊዜው ጣልቃ ገብነት ብቻ ላይ ላተኩር ውዝግብ የተነሳበት ሃሳብ ስለሆነ። በዚህ አንቀጽ ስር የሚወድቁትና የአገሮች ሉዓላዊነት ላለመድፈር ሲባል ጣልቃ ያለመግባት መርሆዎች የሚነሳባቸው ጉዳዬች ውስን ሲሆኑ እነሱም፤
1ኛ/ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት (military intervention)
2ኛ/ እቀባ እና የንግድ ማዕቀብ መጣል (sanctions and embargo)
3ኛ/ በአለም አቀፍ ፍርድ ቤት ከመንግስት ስምምነት ውጭ ክስ ሲቀርብ (Prosecution of grave crimes at the International Criminal Court)
እነዚህ እርምጃዎች የአንድን አገር ሉዓላዊነት የሚጥሱ ስለሆኑ አገሮች የጣልቃ አትግቡብኝ መርህን አንስተው መቃወም ይችላሉ። እኛ ዘንድ የሆነው ነገር ይሄ አይደለም።
ሰብአዊ እርዳ እናድርግ፣ ተኩስ አቁሙ፣ ሽምግልና፣ ድርድር፣ ወዘተ የሚሉ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ውትወታዎች የሚጠበቁ እና ተቋማቶቹ የቆሙላቸው መርሆዎችም የሚያስገድዷቸው ተግባራት ናቸው። እነዚህ ምክረ ሃሳቦች እና ውትወታዎች እንደ ጣልቃ ገብነት ሊቆጠሩ አይችልም። በአንድ አገር ውስጥ እንዲህ አይነት ግጭት ሲካሄድ፣ ሰዎች ልክ እንደ ማይካድራው በገፍ ሲገደሉ እና የበለጠ እልቂት ሊኖር ይችላል የሚያስብሉ ስጋቶች ሲፈጠሩ፣ ዜጎች ግጭቶችን ሸሽተው አለም አቀፍ ድንበሮችን ሲያቋርጡ፣ በግጭቶቹ የተነሳ ከፍተኛ ሰብአዊ ቀውስ ተፈጥሯል ወይም ሊፈጠር ይችላል ተብሎ ሲታመን የአለማቀፍ ማህበረሰቡ፣ በተለይም የተባበሩት መንግስታት እነዚህን ምክረ ሃሳቦች የማቅረብ እና በግጭቱ ውስጥ ባሉት አካላት ላይ የዲፕሎማሲ ጫና የመፍጠር ግዴታ አለበት። እነዚህን ሃሳቦችን ማቅረብ ግን በአገሮች ሉዓላዊነት ላይ የተቃጣ ጥቃት ወይም ጣልቃ ያለመግባት መርሆችን እንደመጣስ ተደርጎ አይቆጠርም። ጣልቃ መግባት የሚባለው ከላይ ከተጠቀሱት ሦስት ነገሮች አንዱ ወይም ሁሉም ሲከሰቱ ነው።
የእኛ የወቅቱ ጉዳይ እዛ የደረሰ አይደለም። ፍሬ ነገሩን ስታችሁ ለምትንጨረጨሩ የሕግ ሰዎች አቧራ የጠጣውን ሰነዳችሁን ፈልጋችሁ አንሱና እንደገና እረጋ ብላችሁ አንብቡት።
ከዚያ ይልቅ ለመንግስት ምክረ ሃሳብ ማቅረብም ካስፈለገ እኔ ከዚህ በታች ያሉት እርምጃዎች ቢወሰዱ መንግስት የጀመረውን ወንጀለኞችን በሕግ ጥላ ሥር የማዋል እርምጃ ያጠናክርለታል፤
1ኛ/ የአለም አቀፍ ማህበረሰቡ፤ በተለይም UN በማይካድራ እና በመከላከያ ሰራዊቱ ላይ የተፈጸሙትን በሰው ዘር ላይ የተነጣጠሩ እኛ የጦር ወንጀሎች የራሱን ባለሙያዎች ልኮ እንዲያረጋግጥ መጋበዝ፣
2ኛ/ የህውሃት ባለሥልጣናት እና የጦር አበጋዞቻቸው በአለም አቀፍ ተፈላጊ ወንጀለኞች ሊስት ውስጥ እንዲገቡ እና አለም እነዚህን ሰዎች ለፍርድ እንዲቀርቡ ትብብር እንዲያደርግ መጠየቅ፣
3ኛ/ እነዚህ በስም እና በፎቶ ተለይተው የሚፈለጉ የከፍተኛ ወንጀል ተፈላጊዎች ድርጊታቸው የአለም አቀፉን ሕግ ጭምር የጣሰ እና በአለም አቀፍ የወንጀል ችሎት ጭምር የሚያስከስስ ስለሆነ ወደ የትኛውም አገር አምልጠው ቢሰደዱ ወይም ከጦርነቱ በፊት ቀድመው የተሰደዱም ካሉ አገራት አሳልፈው ለኢትዮጵያ መንግስት እንዲሰጡዋቸው መጠየቅ እና የተባበሩት መንግስታት የስደተኖች ድርጅት በስደተኝነት እንዳይመዘግባቸው መነጋገር፣
4ኛ/ መንግስት ግለሰቦቹን ብቻ ሳይሆን የተሰባሰቡበትንም ድርጅት በሽብርተኛነት እና በአለም አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቅ ወንጀል የፈጸመ ተቋም መሆኑን ለአለም ማሳሰብ እና ሌሎች ተመሳሳይ እርምጃዎችን መውሰድ ይበጃል።
ሽምግልናን እና የተኩስ አቁም ጥሪን እንደ ጣልቃ ገብነት እና የአገሪቱን ሉዓላዊነት እንደመጋፋት ተደርጎ መቆጠሩ ግን በተቃራኒው አላስፈላጊ ትኩረት መሳብ እና የመንግስትንም ተአማኒነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል።
ሙግቴ የሚጠቅመውን መንገድ እንድንይዝ እንጂ ህውሃትን ለመጥቀም የመሰላችሁ ካላችሁ የዋሆች ናችው። ግራም ነፈሰ ቀኝ ህውሃት ስትከስም እና የህውሃት ሹመኞች ለፍርድ ሲቀርቡ ለማየት የእኔን ያህል የጓጓ ያለ አይመስለኝም። ግፈኞች ለፍርድ የሚቀርቡበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
Filed in: Amharic