ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ፤የኢትዮጵያ ጎሳ ፌዴራሊዝምና የሞራል አጣብቂኝ
ደረጀ መላኩ ( የሰብአዊ መብት ተሟጋች)
መንደርደሪያ
ምንም እንኳን የላቀ አካዳሚክ እውቀት ቢኖራቸውም፣ ለጎሳ ፌዴራሊዝም (ፖለቲካ ) ፍልስፍና የጸና አቋም ወይም ድጋፍ ስላላቸው የአካዴሚክ ብቃተቸው ላይ በብዙ ሰዎች አኳያ ክሬዲት አሳጥቷቸዋል፡፡
እንደ መግቢያ
ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በዛሬዬቱ ኢትዮጵያ አወዛጋቢ ወይም አነጋጋሪ የአደባባይ ምሁር ይመስሉኛል፡፡ አንዳንዶች በከፍተኛ ደረጃ ሲያደንቋቸው፣ ሌሎች ደግሞ የሞራል ድቀት ያለባቸው ፣ እንደ ምሁር የማይቆጠሩ በማለት ይከራከራሉ፡፡ ምክንያታቸውንም ለማስቀመጥ የሚሞክሩ ሞለተው ተርፈዋል፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የአደባባይ ምሁር አይደሉም በማለት በሚከራከሩ ግለሰቦች አስተሳሰብ መሰረት ፕሮፌሰሩ ፣ የአደባባይ ምሁር ለመባል የሚያስችሉ ደረጃዎችን ከማሟላት አኳያ አልተሳካለቸውም፡፡
በእንዲህ አይነት ትችት መሰረት የአደባባይ ምሁር መስፈርት ከሞራል ልእልና ጋር ይጣመራል፡፡ ይህም ማለት ግለሰቡ የማይሰበር፣ የማይከፋፈል ሙሉነት ሊላበስ ግድ ይለዋል፡፡ በሌላ አነጋገር ለማህበረሰቡ አገልግሎት ሳይሰጥ የራሱን ጥቅም ብቻ የሚያስቀድም ግለሰብ የአደባባይ ምሁር ካባ መልበስ አይቻለውም፡፡ ስለሆነም ፕሮፌሰር አንድርያስ የማይከፋፈል፣ የማይሰበር የግል ሰእብና (he has failed the test of personal integrity. )
መላበስ ያልቻሉ በመሆናቸው የአደባባይ ምሁር ተብለው መጠራት አይችሉም ሲሉ ይከራከራሉ፡፡
በዛሬው ጽሁፌ ላይ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ከአደባባይ ምሁር አኳያ ስላበረከቱት አስተዋጽኦ የግል አስተያየቴን ለመስጠት እሞክራለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር በምሁሩ ላይ የተሰነዘሩ ትችቶችን ለመመርመር እሞክራለሁ፡፡ ከዚህ ባሻግር ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ላይ የተነሱ የሞራል ተጠያቂነትን ነጥቦች ለመተንተን እሞክራለሁ፡፡ እንደምገምተው ፕሮፌሰር አንድርያስ ከሞራል አኳያ ለተሰነዘረባቸው ትችት በአደባባይ መልስ ይሰጣሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁኝ፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ እንደ ፈላስፋ
ፕሮፌሰር አንድርያስ በፍልስፍና የትምህርት ዘርፍ የዶክትሬት ድግሪያቸውን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1970 ከስመ ጥሩው የየል ዩነቨርስቲ Yale University ከተቀበሉ በኋላ Andreas earned his Ph.D. in philosophy from Yale University (1970) በታወቁ የተባበረችው አሜሪካ ዩንቨርስቲዎች ፣ ማለትም በፔንስልቫኒያ ዩንቨርስቲ University of Pennsylvania ፣ ኡስላ, UCLA ፣ በዩሲ በርክሌይ UC Berkeley እና ብራውን Brown University ዩንቨርስቲዎች በመምህርነትና ተመራማሪነት አገልግለዋል፡፡ ከተጠቀሱት ነጥቦች በመነሳት ከየል ዩነቨርስቲ በፍልስፍና የትምህርት ዘርፍ በዶክሬት ዲግሪ የተመረቁት፣ ኋላም በታወቁት የተባበረችው አሜሪካ ዩንቨርስቲዎች በፍልስፍና መምህርነትና ተመራማሪነት ያገለገሉት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ከፍተኛ እውቀት ያላቸውና ምጡቅ አእምሮ ያላቸው እንደሆኑ እንረዳለን፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ በታወቁ የፍለስፍና ጆርናሎች ላይ የተለያዩ የፍልስፍና የምርምር ውጤቶችን እንዳሳተሙ መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ከዚህ ባሻግር ምሁሩ በነቢብም ሆነ በተግባር የፖለቲካል ሳይንስ ፈላስፋ a political philosopher ናቸው በማለት መደምደም ይቻላል፡፡ ከንድፈ ሀሳባዊነት አኳያ ሲፈተሸ ፕሮፌሰሩ የጥናት ውጤቶቻቸውና የፍልስፍና ጽሁፎቻቸው የሚያሳዩን ነገር ቢኖር የፍልስፍና ፍላጎታቸውን ነው፡፡
እንደ ዶክተር ተድላ የመሰሉ ስመጥር የፍልስፍና ጠበብት ባቀረቡት ጥናት መሰረት ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ከተማሪነት ህይወታቸው ጀምሮ ለኢትዮጵያ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሲፈተሸ በተለይም የኢትዮጵያን ህገመንግስት ከማዘጋጀት አኳያ ያደረጉት ተሳትፎ፣በህግ መንግስቱ ላይ ለብዙ ግዜያት ያቀረቡት አስተያየት፣ ወዘተ የሚያሳየን ነገር ቢኖር በፍልስፍና የትምህርት ዘርፍ በንድፈ ሃሳብ ደረጃ ያቀረቡትን ስራዎች amply demonstrate that he put to work his theoretical work in philosophy. ያመላክተናል፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ ፈላስፋና የአደባባይ ምሁር ስለመሆናቸው ለመረዳት የሚፈልግ ኢትዮጵያዊ ምሁሩ የጻፉትን በርካታ የፍልስፍና ምርምር ስራዎቻቸውን ማንበብ ግድ ይለዋል፡፡ ዋነኛ ፍላጎታቸው በፍልስፍና ምርምር የደረሱበትን የንድፈ ሃሳብ ግኝት ከኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ጋር በማስማማት ገቢራዊ ማድረግ ነው፡፡
ከታወቁት የምርምር ጽሁፎቻቸው መሃከል ‹‹ወንድማማችነት >> በተሰኘው ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ ያፍታቱትን ሀሳብ በኢትዮጵያ ገቢራዊ ለማድረግ ሞክረዋል፡፡ ከሶስቱ የፍልስፍና ንድፈ ሀሳቦች መሃከል (ማለትም ነጻነት፣ እኩልነት እና ወንድማማችነት) ቅድሚያ የሚሰጡት ‹‹ ነጻነት ›› እና እኩልነት ለተሰኙት የፍልስፍና ንድፈ ሀሳቦች ብቻ ሲሆን ‹‹ ወንድማማችነት›› ለተሰኘው ንድፈ ሀሳብ እምብዛም ትኩረት አይሰጡትም፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ በበኩላቸው ከነጻነትና እኩልነት ንድፈ ሀሳብ ጋር ‹‹ ወንድማማችነት›› የሚባለው የፍልስፍና ንድፈ ሀሳብ መኖር አለበት ብለው የሚከራከሩበት ዋነኛ ነጥብ የአሜሪካንን የነጻነት ትግል ታሪክን በመጥቀስ ነው፡፡ ‹‹ በአሜሪካን ውስጥ ነጻነት እና እኩልነት ከመታወጁ በፊት ባርነት ነበር ስለሆነም የ‹‹ ወንድማማችነት ›› ንደፈሀሳብን ሃሳብን ከተጠቀሱት የፍልስፍና ንድፈ ሃሳብ መለየት አዳጋች ነው፡፡ ››በአንድ ማህበረሰብ ውስጥ በጣም ተቃሚ የሆነው ወይም በህዝብ ዘንድ እንድ የሞራል የበላይነት የሚቆጠረው ወንድማማችነት ከአሜሪካ ነጻነት በፊት ዋጋ አልተሰጠውም ነበር፡፡ ምክንያቱ ደግሞ በአሜሪካ ምድር በነጮች ባርነት ስር ወድቀው የነበሩት ጥቁር አፍሪካውያን ከነጮች እኩል የሰውነት ደረጃ ላይ አልደረሱም የሚል ትምክህት ነበራቸው፡፡ ስለሆነም ነጮች እና ጥቁሮች ወንድማማች ሊሆኑ አይቻላቸውም ብለው ያምናሉ፡፡
Fraternity as a public virtue was not the focus for slaveholding Americans since slaves were considered less than humans to enter into a fraternal relationship with the white slaveholders
ከላይ ከተጠቀሰው የምእራባውያን አስተምህሮ በተቃራኒው ወይም በምእራባውያን የተዘነጋውን ጽንሰ ሀሳብ ( ወንድማማችነት) በተመለከተ ትኩረት ሰጥተው አጥንተውታል፡፡ በዚህ ምክንያት ፕሮፌሰር አንድርያስ ‹‹ ወንድማማችነት፣ እኩልነት እና ነጻነት›› የማይለያዩ ንድፈ ሀሳቦች እንደሆኑ ይሟገታሉ፡፡ ከዚህም እልፍ በማለት በኢትዮጵያ ምድርም ቢሆን የወንድማማችነት ጽንሰ ሀሳብ ለብዙ ዘመናት ገቢራዊ ሳይሆን እንደቀረ በጥናት ወረቀታቸው ላይ አስቀምጠውታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ብሔርተኝነት አንዱ የወንድማማችነት ተምሳሌት እንደሆነ፣ ብሔርተኝነት የሲቪል ማህበረሰቡን አንድ አድርጎ የሚያያዝ ነው ብለውም Argue ያደርጋሉ፡፡
በኢትዮጵያ የጎሳ ፌደራሊዝም አውድ በእያንዳንዱ ጎሳ ( ተመሳሳይ ቋንቋ እና ባህል ያላቸው) አኳያ ወንድማማችነት ገቢራዊ ሊሆን ይቸላዋል በማለት ይከራከራሉ፡፡
ብሔርተኝነትን ‹‹ በጎሳ ማንነት ›› በመቀየር፣ የጎሳ ማንነት የወንድማማችነት ተምሳሌት ሊሆን ይቻላል የሚል ድምዳሜም ያላቸው ይመስላል፡፡
ከላይ ከሰፈረው ምሳሌ በመነሳት ኢትዮጵያ ተመሳሳይ ባህልና ታክ ያለቸው የብዙ ጎሳዎች ሀገር እንደመሆኗ መጠን ‹‹ ወንድማማችነት ›› የተሰኘው ንድፈ ሀሳብ ከኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ጋር ማጣመር የሚቻል ይመስለኛል፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ እንደ አደባባይ ምሁር (Andreas as a public intellectual )
በእኔ አስተሳሰብ መሰረት የፕሮፌሰር አንድርያስ ንድፈ ሀሳባዊ የምርምር ስራዎቻቸው በኢትዮጵያ የፖለቲካ አውድ ላይ በነቢብም በገቢርም ታይተዋል፡፡ ወይም በመሬት ላይ በእውን ታይተዋል፡፡
የኢትዮጵያን ህገመንግስት ማንሳት ይቻላል፡፡ በግዜው የኢትዮጵያን ህገመንግስት ( አሁን በስራ ላይ ያለውን ህገ መንግስት ማለቴ ነው፡፡ ) ያረቀቁትና ያጸደቁት የፖለቲካ( ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ መለስና ሌሎች ይጠቀሳሉ፡፡) ሰዎች ህገመንግስቱ ተረስተውና ትኩረት ያልተሰጣቸውን የኢትዮጵያ ጎሳዎች እውቅና የሰጠ ነው በማለት በአደባባይ ሲናገሩ ሰምተናል፡፡ ይህን ተከትሎ ከወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ በፊት የነበሩት የአገዛዝ ስርአቶች ዘመነ መንግስት ተረስተውና ሲጨቆኑ የነበሩ ጎሳዎችን ችግሮችና መፍትሔውን ጭምር ፍንትው አድርገው ጽፈው አሳይተዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር ‹‹ የጎሳ ፌዴራሊዝም ›› ( በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር አንድርያስ ‹‹ የጎሳ ፌዴራሊዝም ›› የሚለውን ቃል አይጠቀሙም እርሳቸው በደምሳሳው ‹‹ ፌዴራሊዝም›› የሚለውን ቃል ይጠቀማሉ፡፡) ለምን ለኢትዮጵያ የፖለቲካ ችግር መፍትሔ ሆኖ ተመረጠ ለሚለው ለብዙ ኢትዮጵያውያን መሰረታዊ ለሆነው ጥያቄ የራሳቸውን መልስ ሰጥተዋል፡፡ ለአብነት ያህል የህገመንግስት አርቃቂ አባል በነበሩበት ጊዜ ‹‹ የጎሳ ፌዴራሊዝም ›› ይበጃታል የሚል ሀሳብ አቅርበዋል፡፡
የጎሳ ፌዴራሊዝም ለምን ?
እንደ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የፍልስፍና ንድፈ ሀሳብ የምርምር ውጤት እና አስተሳሰብ ከሆነ የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ እንዲካተት የፈለጉት በሚከተሉት ምክንያቶች ነበር፡-
- በእርሳቸው አስተሳሰብ ከኢህአዲግ አገዛዝ በፊት በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ከማእከላዊ መንግስቱ የስልጣን ውድድር ተገፈተዋል፣ ወይም ተጨቁነዋል፡፡ ወይም ተረስተው ቆይተዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነት በግዴታ ተጭኖባቸዋል፡፡ የራሳቸውን ማንነት በተመለከተ በአደባባይ እንዳይናገሩ ተከልክለዋል( የጎሳ ማንነታቸውን ማለታቸው ነው፡፡)
- ከኢትዮጵያዊነት ማንነት በፊት የጎሳ ማንነት መቀደም አለበት ባይ ናቸው፡፡ ለዚህም የጎሳ ፌዴራሊዝም ፍቱን መድሀኒት እንደሆነ ይከራከራሉ፡፡
- ከዚህ ባሻግር የኢትዮጵያ ህገመንግስት ረቂቅ በሚዘጋጅበት ግዜ ተሳታፊ በመሆናቸው የሚከተሉት ሀሳቦች በህገመንግስቱ ላይ እንዲሰፍሩ ሀሳብ አቅርበው ነበር፡፡ ለአብነት ያህል እጠቅሳለሁ፡፡
- ‹‹ ለእኔ ይህ ህገመንግስት ጠቃሚ ነው፡፡ ይህ ሌላ አዲስ ነገር ለመጀመር ሌላ እድል ይሰጣል፡፡ ያለንን ሁሉ መስጠት አለብን፡፡ ህገመንግስቱ ለፖለቲካ ሰዎች ብቻ እውነተኛ ስልጣን ለመስጠት ብቻ መዘጋጀት የለበትም፡፡ ህገመንግስቱ ለተራ ዜጎች ሁሉ እውነተኛ ነጻነት በሚሰጥበት መልኩ መዘጋጀት አለበት፡፡ ይህ አዲስ እድል ነው፡፡ በንጹህ አይምሮ መጠቀም አለብን፡፡ አክለው እንደገለጹት ‹‹ የጎሳ ፌዴራሊዝም›› ‹‹Ethnic federalism,›› በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ ከተካተተ ለፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮቻችን መፍትሔ ያስገኛል ሲሉ ሀሳብ አቅረበው ነበር፡፡ እውን የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ለተከሰቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መፍትሔ አምጥቶ ይሆን ? መልሱን ህሊና ለፈጠረባችሁ ከመተው ውጪ ለግዜው የምለው የለኝም፡፡ በአጭሩ ግን የፕሮፌሰር አንድርያስ አስተምህሮ ሀገሪቱን ዛሬ ድረስ ከባድ ዋጋ እያስከፈላት መሆኑን መግለጽ እወዳለሁ፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ ጥልቀት ባለው ሁኔታ የጎሳ ፖለቲካ ለኢትዮጵያ ጠቃሚ እንደሆነ ለብዙ ገልጸዋል፡፡ የርሰቸውን ሀሳብ መደጋገሙ አስፈላጊ ስላልሆነ ትቼዋለሁ፡፡ የዛሬውን ጽሁፍ ለማዘጋጀት መንፈሴን ያነሳሳውን ምክንያት ግን መግለጽ ያለብኝ ይመስለኛል፡፡ ጸሃፊው የፕሮፌሰሩ የፍልስፍና ንድፈ ሀሳብ ሳይንሳዊ ነው ወይም ኢሳይንሳዊ ነው ለሚለው መልስ ለመስጠት ጊዜም ሆነ አቅሙ የለውም፡፡ ሆኖም ግን የፕሮፌሰሩ የፍልስፍና ንድፈሀሳባዊ አመለካከት( በተለይ የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ይበጃታል የሚለው የፕሮፌሰሩ ሀሳብ ) ምን ያህል ሀገራችንን እንደጎዳት ለማመላከት እንደሆነ አንባቢውን ያስታውሳል፡፡ ምንም እንኳን የፕሮፌሰሩን አስተምህሮ የሚደግፉ አንዳንድ ምሁራን በኢትዮጵያ ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን የፖለቲካ ጭቆና፣ የኢኮኖሚና ማህበራዊ ችግር ለመፍታት ‹‹ የጎሳ ፌዴራሊዝም›› በህገ መንግሰቱ ውስጥ ይሁንታ ማግኘቱ ተገቢ ነው በማለት የተለያዩ ጥናታዊ ጽሁፎች ቢያቀርቡም፣ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ለህገመንግስቱ መርቀቅ ሁነኛውን ሚና የተጫወቱ ስለሆነ ሊመሰገኑ ይገባል በማለት ቢከራከሩም፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ያመጣላት መከራና ችግርን እንጂ ተድላና ደስታን አይመስለኝም፡፡ እርግጥ ነው፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ የየጎሳው አምበሎችና የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኝ ጥቂቶች ኑሮአቸው ሰማየ ሰማያት ደርሶ ይሆናል፡፡ በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ የየጎሳው አባላት ደግሞ የተስፋ ዳቦ ገምጠው ይሆናል፡፡ አንድ መርሳት የሌለብን ቁምነገር ግን የጎሳ ፌዴራሊዝም የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጎሳዎችን ባህል፣ ሙዚቃ ወዘተ አሳድጓል፡፡ ይህ የማይካድ ሀቅ ነው፡፡ በሌላ የሳንቲሙ ግልባጭ ግን ‹‹ የጎሳ ፌዴራሊዝም›› በብዙ የኢትዮጵያ ክፍሎች ምናልባትም በግጦሽ ሳር፣ በድንበር ይገባኛል፣ በዝርፊያ ወዘተ ወዘተ ምክንያት በተለያዩ ድንበርተኛ ጎሳዎች መሃከል የሚነሱ ግጭቶችን ማቀጣጠል እንጂ ማብረድ አልተቻለውም፡፡ በሌላ በኩል አንደኛው ክልሉ የእኔ ብቻ ነው የሚለው ጎሳ ፣ ሌሎች ከሌላ አካባቢ ኑሮ እያዳፋቸው የመጡ ኢትዮጵያውያን የባይተዋርነት ስሜት እንዲሰማቸው በማድረግ ክልሌን ለቃችሁ የምትሄዱበት ሂዱ እንዲል የልብ ልብ የሰጠ ነው፡፡ በአጭሩ የጎሳ ፌዴራሊዝም በርካታ ህጸጾች የታጨቁበት ንደፈሀሳብ ነው፡፡
እስቲ አሁን ደግሞ ፕሮፌሰር አንድርያስ የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ይበጃታል የሚለውን ሌላውን ምክንያታቸውን እንፈትሽ፡፡
- ይሄኛው ምክንያታቸው የሚመነጨው በተባበረችው አሜሪካ ካገኘቱ የሕይወት ልምድ ፣ በተለይም ተማሪ በነበሩበት ዘመን እንደነበር ከዶክተር ተድላ አንድ ጥናታዊ ጽሁፋቸው ላይ እንዳነበብኩ አስታውሳለሁ፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ የአፍሪካ- አሜሪካውያን ያደርጉት በነበረው የሲቪል መብት እንቅስቃሴ ላይ ንቁ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ራሳቸውን ልክ እንደ አንድ የአፍሪካ- አሜሪካዊ ሰው አድርገው ይቆጥሩ ነበር፡፡ ስለሆነም እነርሱ ( አፍሪካ- አሜሪካዊያን) ዘረኝነትን ለመወጋት በሚያደርጉት ፍልሚያ አንጻር ፕሮፌሰሩም የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያደርጉ ነበር፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በጊዜው የአጼ ሀይለስላሴን አገዛዝ ለመገርሰስ ይደረግ በነበረው የተማሪዎች እንቅስቃሴ ወይም ትግል ውስጥም ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ከዚህ ጋር በተያያዘ ነጥብ ነበር በተባበረችው አሜሪካ በአፍሪካ- አሜሪካውያን ይፈጸም እንደነበረው የዘር መድሎ ሁሉ በኢትዮጵያም በብዙ ጎሳዎች ላይ ይፈጸም ነበር በማለት እምነት ያደረባቸው፡፡ በአጭሩ በኢትዮጵያ የብሔር ጭቆና ነበር ሲሉ ነበር እምነት ያደረባቸው፡፡ በግዜው እንደነበሩት አብዛኞቹ ተማሪዎች ሁሉ ፕሮፌሰሩም በኢትዮጵያ ጨቋኝ ብሔርና ተጨቋኝ ብሔር እንደነበሩ አመኑ፡፡
ለፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የጎሳ ፌዴራሊዝም በህገመንግስቱ ይሁንታ ማግኘቱ እርሳቸው ተጨቁነው ለነበሩ ለሚሏቸው የተለያዩ ጎሳ አባላት ስልጣን የሚሳጭበጥ ነው፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰሩ እንዲህ አይነት ድምዳሜ ላይ እንዲደርሱ ያስቻላቸው ሁነት በአሜሪካ ይኖሩ በነበሩ አፍሪካ- አሜሪካዊ ዜጎች ላይ ይፈጸም የነበረው የዘር መድሎ እና በኢትዮጵያ ተማሪዎች የትግል እንቅስቃሴ ላይ ያደርጉት በነበረው እንቅስቃሴ ይመስለኛል፡፡
ከላይ የተለያዩ ምክንያቶችን ወይም ምሳሌዎችን በማንሳት ፕሮፌሰር አንድርያስ አሸቴ ለምን የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ህገመንግስት ውስጥ ይሁንታ እንዲያገኝ የራሳቸውን ድርሻ እንደተወጡ ለማስረዳት ሞክሬአለሁ፡፡ ከዚህ በማስከተል ደግሞ ፕሮፌሰር አንድርያስ ለምን በተለይም ሙሰኛ እና አምባገነን ከሆኑት ከሟቹ የቀድሞ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አብረው ለምን ሰሩ ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄ የራሴን አስተያየት አቀርባለሁ፡፡ በነገራችን ላይ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ከሙሰኞች ጋር አብረው ለብዙ አመታት በመስራታቸው ምክንያት የሞራል የበላይነታቸውን ያጡ ይመስለኛል፡፡
አጭር ማስታወሻ፡- ፕሮፌሰር አንድርያስ ለሰሩት ሀጢያት ንጹህ ሰው ናቸው ወይም ነበሩ የሚል እሳቤ የለኝም፡፡ ላበረከቱት መልካም ተግባር ደግሞ ውዳሴ ከንቱ የማቀርብ ሰው አይደለሁም፡፡ በአጭሩ ‹‹ አካፋን አካፋ ›› ለማለት ብእሬን መምዘዜን አንባቢውን አስታውሳለሁ፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ በተማሪነት ዘመናቸው ኢትዮጵያን ለመርዳት ሲነሱ በቀና መንፈስ ነበር፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ሊበጃት ይችላል ብለው ሲነሱም በአሜሪካ የተማሪነት ዘመናቸው የነጭ ዘረኝነት እና በተማሪዎች እንቅስቃሴ ላይ ተሳታፊ በመሆናቸው ያሳደረባቸው ተጽእኖ እንደነበር ከዶክተር ተድላ ጥናታዊ ጽሁፍ ላይ በመቀንጨብ ለማካፈል ሞክሬአለሁ፡፡
አንድ የታወቀ ምሁር ለሀገሬ ይጠቅማል የሚለውን ንድፈሀሳብ ለማካፈል ሲል ወይም ገቢራዊ ለማድረግ ሲል ከሙሰኛና አምባገነን መንግስት ጋር አብሮ ለመስራት ወይም ያንን ጠቃሚ ነው የሚለውን ምክረ ሀሳብ ለመሞከር በጀመረበት የመጀመሪያ አመታት ውስጥ ሊወቀስ ወይም እርሱም ሙሰኛ ነው ሊባል አይችልም፡፡ ያንን አምባገነን መንግስት በምክር እመልሰዋለሁ በማለት ለተወሰነ ጊዜ አብረው ሊሰሩ ይችላሉ፡፡ አንዳንድ ምሁራን ለተወሰኑ አመታት ወይም ጥቂት ጊዜያት ከአምባገነን መንግስታት ጋር አብረው ከሰሩ በኋላ ውለታቸውን አቋርጠው ወይም አምባገነን መንግስታቸውን በመኮነን ወደ ሌላ ሀገር በስደት ይሄዳሉ ፣ ከቻሉ ደግሞ የግል ምርምር ስራቸውን በሀገራቸው ቁጭ ብለው ያከናውናሉ፡፡ እውን ፕሮፌሰር አንድርያስ እንዲህ አይነት ምሁር ነበሩን ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ እውን ፕሮፌሰር አንድርያስ በወጣትነት የእድሜ ዘመናቸውና ኋላም ይዘውት የተነሱት ሀሳብ ለሀገር መድህን መሆን የሚችል፣እየቆዩ ሲሄዱ ግን የአምባገነኖች የቅርብ ወዳጅ ነበሩን ? መልሱን በያለችሁበት ተወያዩበት፡፡ በእኔ በኩል አስተያየቴን እንደሚከተለው ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በሞራል አጣብቂኝ ውስጥ (a moral dilemma for andreas )
ከዚህ በታች ዝቅ ብዬ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ለብዙ ግዜያት ስለጎሳ ፌዴራሊዝም አስፈላጊነት የተከራከሩበትን ጭብጥ፣ ከሟቹ የቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሰ ጋር በቅርበት ስለበራቸው የስራ ግንኙነት በተመለከተ የግል አስተያየቴን ለማቅረብ እፈልጋለሁ፡፡ በነገራችን ላይ አቶ መለሰ ዜናዊ አምባገነን ከመሀኖቸው ባሻግር በነጻ ውይይት የሚያምኑ ሰው አልነበሩም፡፡
ስለ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የሞራል ውድቀት በተመለከተ በርካታ ሰዎች አብክረው የሚናገሩትን አድምጫለሁ ወይም ሰምቻለሁ፣ ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች ደግሞ ስለ ፕሮፌሰር አንድርያስ አሸቴ የሞራል ውድቀት የጻፉትን ጥናታዊ ጽሁፎች አንብቤአለሁ፡፡ ሌሎች በርካቶች ደግሞ እንደ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ አይነት ምሁር ለመሆን የሚፈልጉ ምሁራኖች ለሌሎች ምሁራኖች መጥፎ ምሳሌ ናቸው ይላሉ፡፡ ከዚህ ባሻግር ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴን የሚከሱ ሰዎች እነደሚሉት ከሆነ ፕሮፌሰሩ የእውነተኛ ምሁራን ተምሳሌት መሆን አይችሉም፡፡ since those who accuse him think that he is a corrupt intellectual.
የበለጠ ለማብራራት አንድ ሰው የተማረ ነው፣ ወይም ምሁር የሚለውን ስያሜ ለመጎናጸፍ ካልተማሩ ሰዎች በበለጠ የሞራል የበላይነት ሊኖረው ግድ ነው፡፡ ፊደል መቁጠር ብቻውን ምሁር የሚለውን ስያሜ ሊያጎናጽፈን አይቻለውም፡፡ ሆኖም ግን የጽሁፌ ዋና ማጠንጠኛ የምሁራን ስያሜ ብያኔ መስጠት አይደለም፡፡ አንድ የተማረ ሰው ምሁር ነው አይደለም ለሚለው መሰረታዊ ጥያቄም ለመወሰን አይደለም፡፡ ስለ ምሁር ትርጉም በተመለከተም ለመስጠትም አይደለም፡፡ ምሁር ማለት ምን ማለት እንደሆነ ለመስኩ ባለሙያዎች ትቼዋለሁ፡፡
ወደ ጎሳ ፌዴራሊዝም መመለስ
ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ የኢትዮጵያ ህገመንግስት ሲዘጋጅ ዋና ተዋናይ ስለመሆናቸው፣ የጎሳ ፌዴራሊዝም ጠንካራ ደጋፊ ስለመሆናቸው ከላይ በሰፊው የሄድኩበት ይመስለኛል፡፡ ይሄን በተመለከተ የማነሳው ጥያቄ የለኝም፡፡ ፕሮፌሰርን ጨምሮ ማንም ሰው የራሱን ሀሳብ ማንሸራሸሩ መብቱ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ወይም ፕሮፌሰር አንድርያስ ለጎሳ ፌዴራሊዝም እውን መሆን ሥላላቸው ቀናኢነት በተመለከተ ጥያቄ አላነሳም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ፕሮፌሰሩ መጀመሪያ ይዘውት የተነሱት ሀሳብ ማለትም የጎሳ ፌዴራሊዝም ለኢትዮጵያ ይበጃታል ያሉት ሀሳብ ብዙም ሳይቆይ በኢትዮጵያ የተለያዩ ክፍሎች ለሚነሱ የጎሳዎች ግጭቶች እንደዋነኛ ምክንያት ይቆጠራል፡፡ በኢትዮጵያ እውን በሆነው የጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት በተነሱ ግጭቶችና ብጥብጦች ምክንያት በብዙ ሺህ ኢትዮጵያውያን ተገድለዋል፣ በብዙ መቶ ሚሊዮን የሚገመት የአፈር ገፊውና ከተሜው ኢትዮጵያዊ ዜጋ ዶግ አመድ ሆኖ ቀርቷል፡፡ ቁጥራቸው እንዲህ በቀላሉ የማይገመት ዜጎች አካለቸው ጎድሏል፡፡ ለዚህም አርባ ጉጉ፣ ኮፈሌ፣ ምእራብ ሀረርጌ፣ ጉራፈርዳ፣ ቡራዩ፣ ቤንች ማጂ ዞን፣ ጋምቤላ፣ ወደ ሲኦል ምድርነት እየተቀየረ ያለው ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተክል ዞን ወዘተ ወዘተ ቋሚ ምስክሮች ናቸው፡፡ ዛዲያ ለምንድን ነው ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በኢትዮጵያ በየጊዜው ስለሚከሰቱት የጎሳ መጽዳት፣ የጎሳ ግጭቶች መባባስ በተመለከተ በፍጥነት በአደባባይ የማይናገሩት ለምንድን ነው በርካታ ኢትዮጵያውያንን እንቅልፍ ስለነሳው የጎሳ ፌዴራሊዝም አደገኛነት በአደባባይ የማይናገሩት የእድሜ እኩዮቻቸው እና የእውቀት አቻዎቻቸው ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ( ነብሳቸውን ይማር)፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ፣ዶክተር ሀይሉ አርአያ ወዘተ ወዘተ ዶክተር ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ አይናቸው ደም እስኪመስል፣ እጃቸው እስኪዝል በኢትዮጵያ ስለሰፈነው የጎሳ ፌዴራሊዝም አደገኛነት በተመለከተ ላለፉት ሰላሳ አመታት ያለመቋረጥ ሲጽፉ፣ ምክረ ሀሳብ ሲያቀርቡ እርሳቸው ግን አንድም ቀን ለመተቸት መንፈሳዊ ወኔ ከድቷቸዋል፡፡
ለአብነት ያህል ባለፉት ጥቂት አመታት ውስጥ በሀዋሳና በተለያዩ የኦሮሚያ አከባቢዎች ስለተከሰቱ የጎሳዎች ግጭቶች በተመለከተ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በአደባባይ በመውጣት ያደረባቸውን ስጋት ሲገልጡ አልተሰማም፡፡ ለምን ? ህሊና ያላችሁ ጠይቁ፡፡ የአማራ ፣ጋሞ፣ ወላይታ፣ ጉሙዝ፣ቅማንት ተወላጆች በማንነታቸው ምክንያት ጥቃት ሲደርስባቸውም ወይም ሲገደሉ የፕሮፌሰሩ ድምጽ አልተሰማም ነበር፡፡ ምናልባት ከላይ ላነሳኋቸው ጥያቄዎች የአንዳንዶች መልስ በጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት ለሚከሰቱ የጎሳዎች ግጭቶች ፕሮፌሰሩ አንድ ግለሰብ ስለሆኑ መፍትሔ ማምጣት ይቸግራቸዋል ሊሉ ይችላሉ፡፡ ሆኖም ግን ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ በሀገሪቱ ውስጥ ካላቸው ተደማጭነትና ከነበራቸው ስልጣን በመነሳት ተጽእኖ መፍጠር የሚችሉ ሰው ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በሌላው የሳንቲሙ ግልባጭ ደግሞ ላለፉት ሃያ ስምንት አመታት የሀገሪቱን ማእከላዊ መንግስት ስልጣን ተቆጣጥረውት የነበሩት ወያኔዎች ሥለ ጎሳ ፌዴራሊዝም አደገኛነት ቢነገራቸውም፣ ቢዘከሩም የሚሰሙ ሰዎች አልነበሩም፡፡ ሆኖም ግን አመሻሽ የእድሜ ዘመናቸው ላይ የሚገኙት ፕሮፌሰር አንድርያስ ባለፉት ሁለት አመታት በኢትዮጵያ የታየውን የለውጥ ነፋስ ተከትለው ምክረ ሀሳባቸውን ማቅረብ ይጠበቅባቸው ነበር፡፡ እኔ እስከማውቀው ድረስ ፕሮፌሰር አንድርያስ በጎሳ ፌዴራሊዝም ምክንያት የሚከሰቱ የጎሳ ግጭቶችን በተመለከተ በአደባባይ መናገር አልቻሉም ነበር፡፡ ይህ ደግሞ ቀላል ተግባር ነበር፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ በታወቁ መገናኛ ብዙሀን በመቅረብ ህዝብን ማስተማር ይችሉ ነበር፣ እንደ ብዙ ኢትዮጵያውያን ምሁራን ሁሉ ( ለአብነት ያህል ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም፣ አቶ ያሬድ ሀይለማርያም፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው ሀይሌ፣ ልበ ሙሉው ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ ወዘተ ወዘተ) ተከታታይነት ያላቸውን በሳል ጽሁፎችን ማዘጋጀት ይችሉ ነበር፡፡ ግን አላደረጉትም፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ የሃሳብን ሀይል በጥልቀት የሚያውቁ ሰው ናቸው፡፡ በተለይም ባለፉት ሁለት አመታት የተከሰቱት የጎሳዎች ግጭቶችን ምክንያቶች በተመለከተ በጥልቀት የሚያውቁም ሰው ናቸው፡፡ ስለሆነም የጎሳዎች ግጭቶች ለወደፊት እንዳይከሰቱ የሚረዱ ዘዴዎችን በተመለከተ ምክረሀሳብ ማቅረብ የሚችሉም ሰው ነበሩ፡፡ በሌላ አነጋገር ስለወንድማማችነት ንድፈ ሀሳብ፣ በሰላምና ፍቅር ስለመኖር፣ የባህል ልዩነት ውበት ስለመሆኑ፣ እንዲሁም የፌዴራል ስርአት ለአንድነት የሚበጅ እንጂ ወደ መለያየት እንደማይወስድ፣ የጎሳ ፌዴራሊዝም ስልጣን የሰጣቸው የአካባቢው ተወላጆች በሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው ላይ ጥቃት ማድረስ እንደሌለባቸው በተመለከተ በታወቁ መገናኛ ብዙሃን ሲያስተምሩ አልታዩም፡፡ ይህ አንዱ የአደባባይ ምሁር ባህሪ መሆኑን ማወቅ አለብን፡፡
ሌላው የፕሮፌሰር አንድርያስ አስተሳሰብ ከባዱ ስህተት በትላልቅ ከተሞች ውስጥ የጎሳ ፌዴራሊዝም የማይስረ ስለመሆኑ ነው፡፡ ወይም በትላልቅ ከተሞች ውስጥ የሚኖረውን ከብዙ ጎሳዎች የተወጣጣውን ኢትዮጵያዊ መጉዳቱ ነው፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም በሀረርና እና ድሬ ነዋሪዎች ላይ ያስከተለውን መዘዝ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በከባድ ሀዘን እናስታውሰዋለን፡፡ ለአብነት ያህል በሀረር ከተማ ከሚኖሩት ሌሎች ኢትዮጵያዊ ወንድሞቻቸው ቁጥራቸው ትንሽ የሆኑት የሀረሬ ጎሳ ተወላጆች ለብዙ አመታት በብዙ መልኩ ተጠቃሚዎች ናቸው፡፡ የምስራቅ ኢትዮጵያ አንጸባራቂ ኮከብ የነበረችው ድሬ አብዛኛዎች ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያዊ ዜጎች የጎሳ ፌዴራሊዝም ባስከተለው መዘዝ ተጎጂዎች ናቸው፡፡ በአጭሩ የጎሳ ፌዴራሊዝም ሕብረብሔራዊ በሆኑ ከተሞች ፈጽሞ ሊሰራ እንደማይችል ፕሮፌሰር አንድርያስ በአደባባይ መናገር ነበረባቸው፡፡ ሆኖም ግን አላዳረጉትም፡፡
እንደ ፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ አስተምህሮ ከሆነ የጎሳ ፌዴራሊዝም በትላላቅ ከተሞች ውስጥ ከጊዜ በኋላ ተቀባይነት ያጣል ባይ ናቸው፡፡ ይህ እውን የሚሆነው ደግሞ ዲሞክራሲ ከጊዜ በኋላ ገቢራዊ ሲሆን ነው ይላሉ፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የፕሮፌሰሩ አስተሳሰብ አሁን ድረስ መሬት ላይ አልታየም፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ ዲሞክራቲክ ስርአት እስካለ ድረስ የግጭት ምክንያት ሊሆን አይቻላውም ቢሉም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ኢትዮጵያዊ ዜጎች በጎሳቸው ማንነት ብቻ ጥቃት ይደርስባቸዋል፡፡ ፕሮፌሰሩ የጎሳ ፌዴራሊዝም ዲሞክራቲክ ህገመንግስት ለማንበር ያስችላል የሚል አስተሳሰብ ቢኖራቸውም ከግጭት በቀር ያስገኘው ቁምነገር አልነበረም ወይም የለም፡፡ ኢትዮጵያ ከጎሳ ፌዴራሊዝም ያተረፈችው ነገር ቢኖር በተለያዩ አካባቢዎች የሚከሰቱ የጎሳዎች ግጭትና መፈናቀልን ብቻ ነው፡፡ በእኔ አስተሳሰብ የፌዴራሊዝም ሥርአት ለኢትዮጵያ ይበጃታል ባይ ነኝ፡፡ ሆኖም ግን መሰረቱን በጎሳ ማንነት ላይ ያደረገው የጎሳ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን አደማት እንጂ አልጠቀማትም፡፡ ማንም ሰው የፈለገውን አስተሳሰብ መያዝ እንዳለበት አምናለሁ፡፡ የሰብአዊ መብቱም ነው፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና አለም ወደ ታሪክ የቆሻሻ መጣያ ቅርጫት ውስጥ አሽቀንጥሮ የጣለውን በጎሳ ማንነት ላይ የተመሰረተውን የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት በኢትዮጵያ ላይ ያስከተለው ዳፋ በእጅጉ ያሳስበኛል፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ ቁጭ ብለው፣ በሰለጠነ መንገድ በመነጋገር የጎሳ ፖለቲካ የሚመክንበትን መንገድ እንዲፈልጉ ሀሳብ አቀርባለሁ፡፡ ሀሳብ ነው የሚጥመውን የሚያውቀው የኢትዮጵያ ህዝብ ነው፡፡ የሩዋንዳና ኬኒያ ህዝቦች ከደረሰባቸው ብሔራዊ ውርደት በመነሳት የጎሳ ፖለቲካን ማምከናቸውን ግን ልብ ልንል ይገባል፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስና አቶ መለሰ ዜናዊ
ፕሮፌሰር አንድርያስ ከሟቹ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር አብረው እስከመጨረሻው ድረስ በመስራታቸው ምክንያት የሞራል የበላይነታቸውን ተገፈዋል በሚል የሚተቿቸው ኢትዮጵያዊ ምሁራን ሞልተው ተርፈዋል፡፡ ለምን ይሆን ፕሮፌሰሩ ከቀድሞው የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚንስትርን በማማከርም ሆነ በሌሎች ስራዎች ላይ በመሳተፋቸው ለምን ይኮነናሉ ? ሁላችንም እንደምናስታውሰው አቶ መለሰ አምባገነን እና የጎሳ ፖለቲካ ሊቅ ነበሩ፡፡ በተለይም ከግንቦት 1997ቱ ታሪካዊ የምርጫ ውድድር ውጤት በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያን ውጤቱን አንቀበልም በማለት አደባባይ ስለወጡ፣ ዜጎች ሀሳባቸውን በመሰንዘራቸው ብቻ፣ የተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላትና ደጋፊዎች በመሆናቸው ብቻ በአደባባይ እንዲገደሉ የጦር ሀይላቸውን አዘው ነበር፡፡ የሰጡትንም ትእዛዝ ፍትሃዊ እንደነበር በአደባባይ ተናግረው ነበር፡፡ ፕሮፌሰር አንድርያስ ዜጎች የዲሞክራሲና ሰብአዊ መብቶቻቸውን እንዲከበሩ በመጠየቃቸው ብቻ በጊዜው በነበረው የአቶ መለስ ወታደሮች ሲገደሉ፣ በጥይት ሲቆስሉ፣ ሲታሰሩ ለምን ብለው አልጠየቁም፡፡ አቶ መለስ በሕይወት በነበሩት ዘመን አገዛዛቸው የፈጸመው ሰይጣናዊ ስራ ሁሉ ፍትሐዊ ነበር ብለው ያምናሉ፡፡ እንዴት ሁሉም ሠይጣናዊ ተግባር ፍትህን ለማስፈን ይፈጸማል ? በእኔ አስተሳሰብ ንጹሃን ዜጎች ሀሳባቸውን በነጻነት ስለገለጹ፣ መብታቸውን ለማስከበር ብቻ ስለተነሱ መግደልና ማሰር፣ ማሰቃየት የሞራል ውድቀትን የሚያሳይ ነው፡፡ በየትኛውም የመንግስት ሥርአት ዜጎችን ማሰቃየት ፍትሃዊ አይደለም፡፡
In Meles’ mind, all the evils committed under his leadership were justified. On what ground all the evils committed under the leadership of Meles are acceptable or justified? I submit that there is no morally acceptable justification for killing and torturing innocent people because of their political views or for exercising freedom of expression and working for the press. There is no justification under any system of government for brutally treating its own citizens.
የአደባባይ ምሁራን ሚና
ከላይ የፕሮፌሰር አንድርያስን ዳተኝነት እንደምሳሌ አነሳሁኝ እንጂ ዛሬም ቢሆን ፍትህ ሲጓደል ምሁራን ዝምታቸውን ሰብረው ፍትህ ከተነፈጋቸው ዜጎች ጋር እንዲቆሙ ማሳሳብ ሌላኛው መልእክቴ ነው፡፡ በጣም በትንሹ የአደባባይ ምሁራን ተግባር ከህዝብ ጋር መወገን፣ እንዲሁም በመንግስት ውሳኔ የስብአዊ መብታቸው ከተጣሰባቸው ወገኖች ጋር ሰልፋቸውን ማድረግ ያለባቸው ይመስለኛል፡፡ ፕሮፌሰሩ ባመኑበት የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት ገቢራዊነት አኳያ ከህገመንግስት ማርቀቅ ጀምሮ ጉልህ አስተዋጽኦ አድርገዋል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና እርሳቸው በፊትለፊት መስመር ቆመው እውን እንዲሆን በብዙ የባጁበት የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት በኢትዮጵያ ምድር ላይ ስላስከተለው ጠንቅ በተመለከተ በአደባባይ ለመተቸት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ አልተቻላቸውም፡፡ በዚህም የአደባባይ ምሁርነት ካባቸውን የተገፈፉ መሰለኝ፡፡
ፕሮፌሰር አንድርያስ በሞራል አጣብቂኝ ውስጥ ለምን ?
ፕሮፌሰር አንድርያስ በሚከተሉት ምክንያቶች በሞራል አጣብቂኝ ውስጥ የተዶሉ እንደሆኑ ይሰማኛል፡፡
- እንደ አንድ የአደባባይ ምሁር ኢትዮጵያዊ የዜጎች መብት ሲገፈፍ፣ ዜጎች ፍትህ ሲነፈጉ ተከታታይነት ባለበት ሁኔታ መተቸት አልቻሉም፡፡ ወይም እርሳቸውና ሌሎች ምሁራኖች የጎሳ ፌዴራሊዝም ይበጃታል በማለት ሀሳብ ቢያቀርቡም የጎሳ ፌዴራሊዝም መዘዝን በተመለከተ በአደባባይ ሀሳብ ማሰማት አልቻሉም፡፡ ወይም የጎሳ ፌዴራሊዝም በኢትዮጵያ እውን መሆኑ ስህተት ነበር ለማለት መንፈሳዊ ወኔ መታጠቅ አልቻሉም ነበር፡፡ ከዚህ ባሻግር ከሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አምባገነን ከነበሩት አቶ መለሰ ዜናዊ ጋር ለብዙ አመታት አብረው በመስራታቸው በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ይወቀሳሉ ፡፡ ለአብነት ያህል የአቶ መለስ አገዛዝ ለብዙ አመታት የኢትዮጵያን ህዝብ ሲጨቁን ዝምታን መርጠዋል፡፡ ዜጎች ሀሳባቸውን በነጻነት ስለገለጹ፣ የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አባል ስለነበሩ በወያኔ ታጣቂዎች ሲገደሉ፣ ሲታሰሩ ፕሮፌሰሩ ዝምታን መርጠው ነበር፡፡
- ፕሮፌሰር አንድርያስ ለአመታት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ያ ሁሉ መአት ሲወርድ ዝምታን በመምረጣቸው ምክንያት የተነሳ በብዙ ኢትዮጵያውያን ዘንድ ያላቸው ቅቡልነት መውረድ አላሳሰባቸውም ነበር፡፡
እኔ እንደማስበው የፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ለምን እንደሆነ ራሳቸው ያስረዱናል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ወይም የሞራል ዳይሌማ ውስጥ ለምን እንደተዶሉ ሀሳባቸውን ቢያካፍሉን መልካም ይመስለኛል፡፡
A personal notes
የግል ማስታወሻ
ከፕሮፌሰር አንድርያስ እሸቴ ጋር በግል ተገናኝቼ ለመነጋገር እድሉን አላገኘሁም፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና ፕሮፌሰር አንድርያስ በአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ እና በጎቴ የባህል ማእከል ተገኝተው ያቀረቡትን የተለያዩ ጥናታዊ ጽፎቻቸውን አድምጫለሁ፡፡ በእውነቱ ለመናገር ለፕሮፌሰር አንድርያስ ከፍተኛ ከበሬታ አለኝ፡፡ የላቀ አካዴሚክ እውቀት ባለቤት እንደሆኑም ይገባኛል፡፡ እንደ ዶክተር ተድላን የመሰሉ በርካታ ምሁራን በጥናት ወረቀቶቻቸው ላይ እንዳስቀመጡት ፕሮፌሰር አንድርያስ በርካታ የጥናት ወረቀቶችን ለህትመት ብርሃን ለማብቃት ባለመቻላቸው የተነሳ አካዴሚካሊ ወድቀዋል ሲሉ ይተቿቸዋል፡፡ ምናልባት እኔ እንደምገምተው ከሆነ የፕሮፌሰር አንድርያስ የምርምር ስራዎች በፍልስፍና ላይ ያተኮሩ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ የፍልስፍና ምርምር ውጤቶች ደግሞ የሚታተሙት በፍልስፍና የምርምር መጽሔቶች ላይ ብቻ ነው፡፡ ስለሆነም ከመስኩ ባለሙያዎች በቀር በርካታ ሰዎች የፕሮፌሰሩን የአይምሮ ጭማቂ የጥናት ውጤቶች አግኝተው ላያነቧቸው ይችላሉ፡፡
እንደ መደምደሚያ
የጎሳ ፌዴራሊዝም ስርአት በኢትዮጵያ ምድር እውን እንዲሆን በብዙ መንገድ አስተዋጽኦ ካደረጉት ኢትዮጵያዊ ምሁራን አንዱና ዋነኛው ፕሮፌሰር አንድርያስ ስለመሆናቸው የሚያከራክር አይመስለኝም፡፡ መሰረቱን ጎሳና ቋንቋ ላይ ያደረገው የጎሳ ፌዴራሊዝም ኢትዮጵያን ከባድ ዋጋ አስከፍሏታል፡፡ እያስከፈላትም ይገኛል፡፡ የጎሳ ፌዴራሊዝም ከኢትዮጵያ እንዴት መመልከን እንዳለበት ከኢትዮጵያ መንግስት አኳያ በዚህ አስጨናቂ ግዜ እንኳን የታሰበበት አይመስልም፡፡ በነገራችን ላይ የጎሳ ፖለቲካ ዋጋ ያስከፈላቸው ኬንያና ኡጋንዳ መሰረታቸውን ጎሳ ላይ ያደረጉ የፖለቲካ ፓርቲዎችን በህግ አግደው በሰላምና በሰከነ መንፈስ መጓዝ ከጀመሩ ሰነበቱ፡፡ በተቃራኒው ከሁለቱም ሀገራት መሪዎችም ሆነ አስተዳደር መልካም ግንኙነት ያለው የኢትዮጵያ መንግስት የሁለቱን ሀገራት ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለምን በኢትዮጵያ ገቢራዊ ለማድረግ እንደማይሞክር ሲታሰብ ግራ ያጋባል፡፡ ለአብነት ያህል የፌዴራል ስርአት ተከታይ በሆነችው የተባበረችው አሜሪካ ምድር የስፓኒሽ አሜሪካውያን፣ አፍሪካ አሜሪካውያን፣ ሜክሲኮ አሜሪካውያን ወዘተ ወዘተ በሚል ስያሜ የሚጠሩ ግዛቶች የሉም፡፡ የተባበረችው አሜሪካ የሚገኙ ግዛቶች መጠሪያ ጎሳን ወይም ቋንቋን መሰረት ያደረጉ አይደሉም፡፡ ፊላደልፊያም ሆነ ካሊፎርኒያ፣ ዋሽንግተንም ሆነ ቴክሳስ፣ ፍሎሪዳም ሆነ አላስካ፣ ኒውአሪዞናም ሆነች ዳላስ ወዘተ ወዘተ የተባበረችው አሜሪካ ዜጎችም ሆኑ ኑሮ እያዳፋ ከመላው አለም የመጡ ሰዎች በነጻነት ይኖራሉ፡፡ ( በጥቁር አሜሪካውያን ላይ የሚፈጸሙትን አንዳንድ የነጭ ትምክህተኞችን ጥጋብና ግፍ ሳንዘነጋ ማለቴ ነው፡፡) የኢትዮጵያው ፌዴራሊዝም ስርአት ግን ከአሜሪካው የፌዴራሊዝም ስርአት አኳያ በብዙ መልኩ ተጻራሪ ነው፡፡ የኢትዮጵያው ፌዴራሊዝም ስርአት ቋንቋና ጎሳን መሰረት ባደረጉ አሰር ክልላዊ መስተዳድሮችን የያዘ ነው፡፡ በብዙ መልኩ ከጎሳ ክልሉ ውጪ የተወለዱ ናቸው ለሚባሉ ኢትዮጵያዊ ዜጎችን መብት የሚደፈጥጥ ነው፡፡ ስለሆነም ኢትዮጵያውያን ሁሉ በሰከነ እና መከባበር በተሞላበት መንፈስ ቁጭ ብሎ በመነጋገር የጎሳ ወይም ቋንቋ ፌዴራሊዝም በመልክአ ምድራዊ ወይም በሌላ አይነት የፌዴራሊዝም ሥርአት ስለሚቀይርበት መንገድ በወጉ ቢመክሩ መልካም ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ስለ ጎሳ ፖለቲካ ጥቅምና ጉዳት ለማወቅ ሰላሳ አመት በቂ ነው፡፡ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተክል ዞን ብቻውን ከእብድ ውሻ በከፉ አረመኔዎች በኢትዮጵያዊ ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ግፍ ትምህርት ሊሆነን ይገባል፡፡ ከመከራ ለመማር በግድ መከራው እቤታችን ድረስ እስኪመጣ መጠበቅ ያለብን አይመስለኝም፡፡ አቤቱ አምላኬ ሆይ የኢትዮጵያን ክፉዋን አታሳየን፡፡