>
3:13 am - Friday February 3, 2023

የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት ከ30 ዓመት በኋላ ተናገሩ....!!!  (በአለማየሁ አንበሴ)

የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት ከ30 ዓመት በኋላ ተናገሩ….!!!

 በአለማየሁ አንበሴ

 

* “ሀገር ውስጥ ብንሆንም ሃገራችን ናፍቆናል”
* “በህይወት ኖሮ ይህን ማየት ቀላል አይደለም”
ለ30 አመታት በጣሊያን ኢምባሲ ተጠልለው የኖሩት ሁለቱ የቀድሞ የደርግ ከፍተኛ ባለስልጣናት ሌ/ኮለኔል ብርሃኑና ባየህና እና ሌ/ጀነራል አዲስ ተድላ ከሰኞ ጀምሮ ባሉት ቀናት ከኤምባሲው ቅጥር ግቢ ወጥተው በነፃነት ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንደሚቀላቀሉ ተረጋግጧል።
የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ባለስልጣናቱ ከሚገኙበት የጣሊያን ኢምባሲ በስልክ አግኝቶ በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ አነጋግሯቸዋል። እነሆ፡
ሌ/ጀነራል አዲስ ተድላ ስለ ራስዎ ጥቂት ይንገሩን? የቀድሞ የጦር ሃይሎች ኢታማዦር ሹም ነበርኩ፡፡ ከዚያ በፊት የኢሰፓ የፖሊት ቢሮ አባል በመሆን አገልግያለሁ። ለብዙ ዓመት በተለያየ ደረጃ ሰርተናል። እኔ የመከላከያ ኮሚቴ ውስጥ ነበር … ደርግ ሲቋቋም የምሰራው። ደርግ ከተቋቋመ በኋላ ደግሞ የኢኮኖሚ ዘመቻ መምሪያ ሲቋቋም በውስጡ ዘጠኝ ዓመት ሰርቻለሁ። በ1980 የኢፊድሪ መንግስት ሲቋቋም ተረጋግጧል። ም/ጠ/ሚኒስትር ሆኜ በማገልገል ላይ ሳለሁ በ1981 መፈንቅለ መንግስት ሙከራ ተከናወነ። ከዚያ ተነስቼ ወደ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ሆኜ ሳገለግ ነበር።
በኤምባሲው 30 ዓመት ቆይተዋል አሁን እድሜዎ ስንት ሆነ?
አሁን 77 ዓመት ላይ ደርሻለሁ። እንዴት ነበር ጣሊያን ኢምባሲ የገባችሁት? በአጋጣሚ ነው የገባነው። እኔ በአጋጣሚ የገባሁ እለት ወደ ማታ ላይ ጀነራል ተስፋዬ ገ/ኪዳን ጣሊያን ኢምባሲ ሊቀበሉን ዝግጁ ናቸው ስላለኝ አብሬ መጣሁ። ማታ ምሽት ሁለት ሰዓት ላይ ነበር የገባሁት። ወያኔ
ሃገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላ ከኛ ጋር ጣሊያን ኢምባሲ የገቡ ብዙ ነበሩ እነሱ ሲወጡ እኛ ወስነን እዚያው ቀረን።

የ30 ዓመት ቆይታችሁ እንዴት ነበር?

ቆይታችን በጣም ብዙ ውጣ ውረድ ያለው ነበር። በመጀመሪያዎቹ 10 አመታት ከውጪ ሰው ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት አልነበረንም። ከቤተሰቦቻችን ጭምር። በተለይ ቤተሰቦቻችን ውጭ ሃገር ሄደው ስለነበር በደብዳቤ ብቻ ነው የምናገኘው። ከ10 ዓመት በኋላ የነበረው አምባሳደር ከሃኪሞች ጋር ተነጋግሮ፣ ለነሱም ጤንነት ሆነ እኛም የሰብአዊ መብታቸውን ማክበር ስላለብን፣ ከአንዳንድ ቤተሰቦቻቸው ጋ እንዲገናኙ ብናደርግ ጥሩ ነው በሚል
የመገናኘት እድሉ ተፈጠረ። በወቅቱ የጣሊያን ኢምባሲም ከመንግስት ጋር ቅራኔ ውስጥ ነበር።”አሳልፋችሁ ካልመሰጣችሁ” የሚል ግ ፊትም ነ በር። እ ነሱም “ አንሰጥም በተለይ የሞት ፍርድ የሚያሰጥ አዋጅ እስካለ ድረስ አንሰጣችሁም”። ብለው ከለከሏቸው። በዚህ ብዙ ችግር ተፈጥሮ ነበር።
የሆነው ሆኖ ከ10 አመት በኋላ ቤተሰብ እንዲጠይቀን ተፈቀደ። መጀመሪያ ላይ በጣም በሚስጥር ነበር የሚያገናኙን፤ በኋላ ደረጃ በደረጃ በወር ከሁለት እስከ ሶስት ጊዜ ሰዎቹ መጥተው ለአጭር ደቂቃዎች ብቻ እንዲጠይቁን ተደረገ። በእንደዚህ አይነት ሁኔታ እየሄደ በኋላ ሁኔታዎች ትንሽ ለቀቅ
እያለ ሄዱ ማለት ነው፡፡
ቤተሰቦቻችሁን እንደ ልብ ታገኙ ነበር? ቤተሰቦቻችሁ አሁን በምን ሁኔታ ላይ ይገኛሉ?
ቤተሰቦቻችን አሁን የራሳቸውን ኑሮ እየኖሩ ነው። በወቅቱ ልጆቻችን ገና አፍላ ዕድሜ ነበሩ። አሁን አድገው እነሱም ቤተሰብ መስርተዋል። አሁን ልጆች የልጅ ልጆች አሉን። በየጊዜው እየመጡ ይጠይቁን ነበር።
እርስዎ ስንት ልጆች አለዎት የትስ ነው የሚኖሩት?
ሶስት ልጆች አሉኝ፡፡ ስድስት የልጅ ልጆች አሉኝ። አንደኛዋ ደግሞ በቅርቡ አግብታ አሁን ከጥቂት ወራት በኋላ 7ኛ የልጅ ልጅ ይኖረኛል።
የጣሊያን ኢምባሲ አኗኗራችሁ ምን ይመስል ነበር?
አኗኗራችንን ደህና ነበር። የራሳችን የተለየ ቤት አዘጋጅተውልን ነው የምንኖረው፡፡ እያንዳንዳችን የየራሳችን መኝታ ቤት አለን፣ መታጠቢያ ቤት አለው፣ ኪችን አለው። በዚህ ሁኔታ ደህና ነበር የምንኖረው። የጤንነት ችግር ሲገጥም ግን ለህክምና በጣም አዳጋች ነበር። ሃኪሞች ይመጣሉ ግን ሙሉ ህክምና ማግኘት አንችልም ነበር። እኔ ለምሳሌ አይኔን በአንድ ወቅት በጽኑ ታምሜ ነበር። ይሄን ህክምና ለማግኘት ሃኪሞች ፈቃደኛ ሆነው መምጣት ነበረባቸው።
ሁለተኛ ለኦፕራሲዮን የተመቻቸ ነገር መኖር ነበረበት። ይህ ሁሉ የራሱን ጊዜ ወስዶ ከ1 ዓመት በፊት የተሳካ ኦፕራሲዮን አደረግሁ። አሁን ደህና ነኝ። ሌላ አይነት ህመም ቢሆን ኖሮ እዚህ ኦፕራሲዮን ለማድረግ አይቻልም ነበር። ለህክምና ሁኔታው አይመችም።
ብዙ ጊዜያችሁን በምን ነበር የምታሳልፉት?
በማንበብና በመጻፍ ነበር የምናሳልፈው። አካላዊ እንቅስቃሴም እናደርጋለን። ሚዲያዎች እንከታተላለን። ቴክኖሎጂውም ለዚህ አግዞናል። በቆይታችን ትልቅ ያገኘነው ነገር የቴክኖሎጂ መሻሻል ነው። በተለይ የስልክና ኢንተርኔት መኖር ትልቅ እድል ነበር ያመጣልን። ላፕቶፕ ሲመጣልን፣ ራሳችንን በራሳችን ነበር ያስተማርነው። የስካይፒ ቴክኖሎጂ ሲመጣ ልጆቻችን አጠቃቀሙን አሳይታውን በሱ እንገናኝ ነበር። በሱ ምክንያት ከቤተሰብ ጋር መገናኘታችን ህይወታችንን በጣም ነበር የቀየረው። ቴክኖሎጂ ትልቅ አስተዋፅኦ ነበረው። ያለበለዚያ ህይወት ከባድ ይሆንብን ነበር።
ሃገር ውስጥ ስለሚከናወኑ ጉዳዮች መረጃ ታገኙ ነበር?
አዎ! በሚገባ እንከታተል ነበር። ቴሌቪዥን ሬድዮ ሁሉም አለን። በተለይ በቴሌቪዥን በ ሃገር ው ስጥም በ ውጭም ያለውን በሙሉ እንከታተል ነበር። ወያኔ የሚፈፅመውን ሁሉ እየተከታተልን በጣም እናዝን ነበር። ሁኔታውን በሚገባ እንከታተል እንረዳ ነበር።
ከ30 ዓመት በፊት ስልጣን ይዞ የነበረው  ቡድን፣ ዛሬ ተመልሶ ወደ አማፂነት ወርዷል ሲባል ምን ተሰማችሁ?
በጣም አስገራሚ ሁነት ነው። እኛ ለሃገር አንድነትና ለህዝብ እድገት ስንሰራ ነበር። በሂደት ውስጥ ብዙ ችግር ነው የገጠመን። የሶማሌ ጦርነት ቀላል ችግር አልነበረም። በኋላም የኤርትራ ተገንጣይ ቡድን ነበር። ይህን የሃገር አንድነት ለማስቀጠል ብዙ ዋጋ ተከፍሏል። ኢኮኖሚው ብዙ ጥረት ጠይቋል። በወቅቱ በዓለም ላይ ተቀባይነት በነበረው ሶሻሊዝም ነበር የምንመራው። እኔ ለዘጠኝ ዓመት በቆየሁበት የማዕከላዊ ፕላን ስራችን፣ የሃገሪቱን ኢኮኖሚ ይለውጣሉ ያልናቸውን ብዙ ጥረቶች አድርገናል። በግብርና…. በኢንዱስትሪ ልማት ብዙ እቅድ አውጥተን፣ በጦርነት ውስጥ ሆነን ለመስራት ጥረት አድርገናል። በተለይ ኢንዱስትሪዎች ሚዛናዊ በሆነ መንገድ እንዲሰራጩ ሞክረናል። ይህ ሁሉ ግን በነሱ በኩል ዋጋ ቢስ ተደርጎ ነበር የተቆጠረው። ይሄን ጥረት እንኳ እውቅና ሊሰጡት አልፈለጉም። ብዙ የደርግ አባሎች እኮ ለሃገራቸው ሲሰሩ፣ የራሳቸው መኖሪያ ቤት እንኳ አልነበራቸውም። ያችን ደሞዛችንን
በማብቃቃት ነበር እንደ ማንኛውም ሰው የምንኖረው በሃቅና በታማኝነት ለማገልገል ነበር ጥረታችን። ዛሬ ወያኔም ተወግዶ፣ ህዝቡ ከጭቆና ነፃ መውጣቱ ትልቅ ነገር ነው። ደረጃ በደረጃ ደግሞ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ቦታ ሄዶ ሰርቶ፣ ራሱን የመለወጥ ሙሉ መብቱ የሚፈጠርበት ሁኔታ እንዲስተካከል ያስፈልጋል። ለወጣቱ የስራ እድል በመክፈት በኩል አሁን የተሻለ ነገር አለ። ይሄን ማስቀጠል ከተቻለ ሃገሪቱ በአጭር ጊዜ ልትለወጥ ትችላለች።
ውጭው ምን እንደሚመስል የማየቱ እድል ነበራችሁ?
በፍፁም! እኛ በቴሌቪዥን ብቻ ነበር የምናውቀው። በአይን የምናውቀው ነገር የለም።
አሁን ስትወጡ ምን ትጠብቃላችሁ?
በቴሌቪዥን ስንመለከት አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ ተቀያይሯል። እኔ አዲስ አበባ ነው ተወልጄ ያደግሁት፡፡ ድሮ አዲስ አበባን በደንብ ነበር የማውቃት፤ አሁን በቴሌቪዥን ስመለከት በጣም ብዙ ለውጥ ነው ያለው። ሌሎች ቦታዎችም በጣም ተለውጠዋል። እኛም ያኔ እንደዚህ ለመለወጥ ብዙ ምኞት ነበረን። ነገር ግን የኛን አቅም ያሟጥጥ የ ነበረው በ ምስራቁም በ ሰሜኑም የሚደረገውን ጦርነት ነው። ፋታ የሌለው ጦርነት ውስጥ ነበርን። በአጠቃላይ አለም ሁሉ እኛ ላይ ተረባርቦ ነው ሊያመክነን የሞከረው፡፡ እንደዚያም ሆኖ በተወሰኑ ዓመታት የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ተሞክሮ ነበር። ጦርነቱ አቅማችንን በሙሉ በላብን እንጂ አስገራሚ የኢኮኖሚ እቅዶችን ነድፈን ነበር።
በዚህ መንገድ እንፈታለን የሚል ግምት ነበራችሁ? የመፈታት ዜናውን ስትሰሙ ምን ተሰማችሁ?
በጣም ደስ ብሎናል። ጥረት ሲደረግ እንደነበር እናውቃለን። ያው ተሳክቶ አሁን ልንወጣ ነው። ነገር ግን እኛ በዘር ማጥፋት መከሰስ አልነበረንም። የዘር ማጥፋት አልተካሄደም፤ የአሸናፊዎች ፍርድ ነበር የተፈረደብን፡፡ ለዚህ ኢ-ፍትሃዊነት መዳረጋችን ልክ አልነበረም። ዞሮ ዞሮ ዛሬ የመንግስት ለውጥ መጥቶ፣ በዚህ መልኩ ልንወጣ በመሆኑ በእጅጉ ደስተኞች ነን። ለመንግስትና ይሄ እንዲሆን ጥረት ላደረጉ
ሁሉ እናመሰግናለን። ዶ/ር ዐቢይ ከመጡ በኋላ ሁኔታውን በሃዘኔታ ሲመለከቱት ነበር። በርካቶችም ስለኛ ሲሟገቱ ነበር። የቀድሞ የጦር አባሎች የሃይማኖት ሰዎች ሁሉ ስለኛ ሁኔታ ሲሟገቱ ነበር። አሁን የወያኔ ከስልጣን መውረድ ሁኔታዎችን አመቻችቷል። በሌላ በኩል፤ እነ ዶ/ር አብይ ያላቸው አቋምና ሃዘኔታ ለዚህ አብቅቶናል። በጣም ደስ ብሎናል፡፡ በህይወት ኖሮ ይሄን ማየት ቀላል ነገር አይደለም።
ከወጣችሁ በኋላ በምን መልኩ ነው ኑሮአችሁን የምትቀጥሉት?
መንግስት ፈቃደኛ ሆኖ ጡረታችንን ካከበረልን፣ በጡረታ እንኖራለን። ምን እንደምንሰራ ደግሞ ወጥተን የምናየው ይሆናል፤ የተለየ ነገር አላሰብንም። አሁን እዚህ ሆነን ውጪ ስላለው ምንም የምናውቀው ነገር የለንም።
ከውጪው ምን ናፍቋችኋል?
ውጪውን አናውቅም፤ በቴሌቪዥን ከምናየው ውጪ። ሃገራችንን ዞረን ብናይ ደስ ይለናል፡፤ ሃገር ውስጥ ብንሆንም ሃገራችን ናፍቆናል።
ሌ/ኮለኔል ብርሃኑ ባየህ እንኳን ደስ አለዎት?
አመሰግናለሁ፡፡ ደስ ብሎናል እንኳን አብሮ ደስ አለን! በደርግ የስልጣን ዘመን እርሶ የሰሩባቸው ሃላፊነቶች ምን ነበሩ? በአብዛኛው ውጭ ጉዳይ ነበር የሰራሁት። መጨረሻ ላይ የመንግስት ም/ቤት ም/ ፕሬዝዳንት ሆኜ ነበር።
የጣሊያን ኢምባሲ የ30 ዓመት ቆይታዎ እንዴት ነበር? የቤተሰቦችዎ ሁኔታስ? ቆይታችን ጀነራል እንደገለጸልህ ነው። የቤተሰቦች ሁኔታ ላልከው… በወቅቱ ወያኔ ወደ መሃል እየገፋ ሲመጣ፣ እኔ አንድ ውሳኔ ወሰንኩ። ቤተሰቦቼ… ልጆቼና ባለቤቴ በምንም አይነት ሁኔታ በወያኔ ወንበዴ እጅ ወድቀው ሞራላቸው እንዲወድቅ እንዲዋረዱ አልፈልግም። እኔ የፈለገው ቢደርስብኝ እዚሁ ሆኜ እቋቋማለሁ፤ የትም መሄድ አልፈልግም ነበር። “እኔ አልሄድም፤ እናንተ ግን ከሃገር ውጡ” ነው ያኳቸው። ልጆቼን ቀደም ብዬ እንዲወጡ አድርጌያለሁ። ባለቤቴ ግን ጥዬህ አልሄድም ብላኝ ተጣልቻት ነው በመጨረሻው አውሮፕላን የተሳፈረችው። በግድ ነበር እያለቀሰች ነው የሄደችው። መጀመሪያ አሜሪካ ሄዱ ከዚያ ካናዳ ገቡ። አሁን እነሱ ናቸው የሚረዱኝ።
ምን ያህል ልጆች አለዎት?
አራት ናቸው፡፡ ሁለት የልጅ ልጆች አሉኝ። እጅግ የተባረኩ ልጆችን ፈጣሪ ሰጥቶኛል።
በዚህ መንገድ መውጣቶትም ምን ስሜት ፈጠረብዎት?
በጣም ነው ደስ ያለን። በተለይ የህዝቡ አቀባበል ደስ አሰንኝቶናል። ሃገር ውስጥም ውጭም ያለው በመውጣታችን ደስተኛ ነው። ብዙዎች ቤተሰቦቻችን ና እኛ ጋ፣ እየደወሉ ደስታቸውን እየገለጹ ነው። በዚህ መልኩ የኛ ጉዳይ ትኩረት ማግኘቱ ደስ ብሎናል። በተለይ ደስታዬን ከፍ የሚያደርገው ይህ የሆነው ጠላታችን በተደመሰሰ ማግስት መሆኑ ነው።
ከወጡ በኋላ ምን ማድረግ ይፈልጋሉ?
ዋናው ነገር ከሃገሬ ወጥቼ መኖር አልፈልግም። እዚሁ ነው መኖር የምፈልገው። ቤተሰቦቼም ለመምጣት ያስባሉ። የህይወት ታሪኬን ፅፌ አጠናቅቄያለሁ፤ ማሳተም ይቀራል፤ እሱን እሰራለሁ።
የምታመሰግኗቸው አካላት ካሉ?
በመጀመሪያ ደረጃ ዶ/ር አቢይ አህመድን በእጅጉ እናመሰግናለን። ወደ ስልጣንእንደመጡ፣ ባህር ዳር ይሁን ጎንደር የሄዱ ጊዜ፣ ስለኛ ጉዳይ ሲጠየቁ፣ ይወጣሉ ብለው የመጀመሪያውን ተስፋ ሰጡን፡፡ በዚህም ደስ ብሎን ነበር። በኋላ ያሥቸገራቸው ነገር እንደነበር እንረዳለን። ያም ሆኖ እሳቸውን
በመጀመሪያ ደረጃ እናመሰግናለን። በመቀጠል የኖርንበት የጣሊያን ኢምባሲና የጣሊያን መንግስት ይህን ያህል ዓመት እየተንከባከበ በጥሩ ሁኔታ ይዞን ቆይቷል። እኛም በጥሩ ስነ-ምግባር ወታደሮች ስለነበርን በዲሲፕሊን ነበር የቆየነው። ወያኔ “አሳልፋችሁ ካልሰጣችሁ” ብሎ በሚያስቸግርበት ጊዜ “የሞት ፍርድ ባለበት ሃገር ህጋችን አሳልፎ መስጠትን አይፈቀድም” ብለው ተከራክረው ነው ያቆዩን። ለዚህ እጅግ እናመሰግናለን። ወደ ኢምባሲው ስንገባ ለተቀበሉንና አሁንም በድጋሚም እንዲሁም አምባሳደርነት ተሹመው ለመጡት አምባሳደር አርቱሮ ሉዚ እንዲሁም ለጣሊያን ኤምባሲ ሰራተኞች
በሙሉ ምስጋና እናቀርባለን፡፡ የሃይማኖት አባቶች እንድንፈታ ጥረት ያደርጉ ነ በር፤ ቀደም ብ ሎም ዶ /ር አግደው ረዲ ብዙ ጥረት አድርገዋል፣ ዶ/ር ጳውሎስ ሚልክያስ እነዚህም እንዲሁም፤ አቡነ ጳውሎስም ጥረት አድርገው ነበር፤ ሁሉንም እናመሰግናለን። ቤተሰቦቻችንንም እንዲሁም እናመሰግናለን።
Filed in: Amharic