ያሬድ ሀይለማርያም
ጋዜጠኞች፣ የመብት አቀንቃኞች፣ ለውጥ አራማጆች እና ማህበረሰብ አንቂ የሆኑ ግለስቦችን በሃሰት በመወንጀልም ይሁን ስማቸውን በማጠልሸት ዝም ለማሰኘት መሞከር የማህበረሰቡን ልሳን እና የግፉአንን ድምጽ እንደማፈን ነው።
የመብት ተሟጋቾች እና የለውጥ አቀንቃኞች ብዙን ጊዜ የመንግስት እና የመንግስት ደጋፊ የሆኑ ግለሰቦች እና ሚዲያዎች ሂላማዎች ናቸው። ህውሃት በሃያ ሰባት አመታት ውስጥ ትልቁ ጸቧ ከመብት አቀንቃኞች እና የለውጥ አራማጅ ከሆኑ ግለሰቦች ጋር ነበር። ብዙዎቹን አስራ ገርፋለች፣ አሰቃይታለች፣ በሽብር ከሳለች፣ ከአገር አሰድዳለች፣ ንብረት ወርሳለች፣ ስም አጠልሽታለች። ምክንያቱም ጸጥ ለጥ ብሎ በሚገዛ ማህበረሰብ ውስጥ እነዚህ የለውጥ አቀንቃኞች እና የመብት ተሟጋቾች የሥርዓቱን ገበና ለአለም ከማሳጣት ባለፈ የተኛውንም ሰፊውን ሕዝብ በመቆስቆስ ለለውጥ ስለሚያነሳሱ ይፈራሉ።
ሰብአዊ መብቶች በገፊ በሚጣስባት አገራችን ውስጥ የሕዝብ ድምጽ ሆነው እና ማናቸውንም መከራዎች ተጋፍጠው ስለ እውነት በአደባባይ እሚቆሙ፣ የግፉአን ድምጽ የሆኑ፣ የጎበጠው እንዲቃና መንግስትን እና ማህበረሰቡን ሌት ተቀን የሚወተውቱ፣ የሌሎችን በደል በራሳቸው ላይ እንደተፈጸመ በደል አድርገው በመቁጠር ፍትሕን አበክረው የሚጠይቁ የመብት ተሟጋቾች፣ የለውጥ አራማጆች እና ንቁ የፖለቲካ ተሳታፊዎች በጠአት የሚቆጠሩ ናቸው። ይሁንና እነዚህን ደፋር እና ንቁ የመብት ተሟጋቾች ለማሸማቀቅ እና ጸጥ ለማሰኘት ዛሬም ከመንግስት አካላት ከሚሰነዘርባቸው ዛቻ፣ ማስፈራሪያ እና ቁጣ አልበቃ ብሎ የመንግስት ደጋፊዎች እና በተቃርኖ የቆሙ ሌሎች ግለሰቦች የሚሰነዝሩባቸው ስድብ፣ ዛቻ፣ ስም ማጥፋት እና ማስፈራሪያ በአገሪቱ ውስጥ እያገገመ ያለውን ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን ዳግም ያዳፍነዋል።
መንግስት እና የመንግስት ባለሥልጣናት ለምን ተተቹ፣ ለምን ተወቀሱ፣ ለምን ተጠያቂ ተደረጉ በሚል ጠያቂዎቹን ግለሰቦች ማዋከብ እና ኢላማ ማድረግ በአገሪቱ ውስጥ ያለመጠየቅ ባህል እና አንባገነናዊ ሥርዓት እንዲጎለበት ያደርጋል።
በቅርቡ በማህበራዊ ድህረ ገጾች በመምህርት መስከረም አበራ፣ ጋዜጠኛ መአዛ እና ሌሎች ጋዜጠኞች ላይ ጭምር የሚሰነዘሩት የማዋከብ እርምጃዎች ሊቆሙ ይገባል።