የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
ከአለፉት 15 ዓመታት ጀምሮ በኢትዮጵያ እና በሱዳን መካከል ያለውን የድንበር ሁኔታ በጥንቃቄና በጥሞና በመከታተል ላይ ያለው የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ሰሞኑን የሱዳን መንግስት መደበኛ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዳር ድንበር ግዛት ጥሶ በመግባት በወገኖቻችን ላይ የፈፀመው ግድያ፣ ንብረት ማውደም እና ዝርፊያ እንዲሁም ሕገ-ወጥ ወረራ አጥብቆ ያወግዛል። ድርጊቱ ለሁለቱ ጎረቤታማ አገሮች መልካም ግንኙነት እንቅፋት በመሆኑ የድንበር ኮሚቴው የሱዳን መንግስት በማናለብኝነት ወርሮ ከያዛቸው መሬቶቻችን ለቆ እንዲወጣ እና ወደ ሰላማዊ ውይይት እንዲመለስ በጥብቅ ያሳስባል።
ታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ/ም (December 15 ቀን 2020) የሱዳን መንግስት ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር ከ20 እስከ 40 ኪ.ሜ. በኃይል ጥሰው ገብተዋል። ሱዳናውያን አልፋሽቃ ብለው የሚጠሩትን ከጓንግ ምላሽ ያለውን ከሑመራ እስከ መተማ የሚዘረጋውን ሰፊ ለም መሬት፤ እንዲሁም በመተማ ዙሪያ የተንጣለለውን ሰፊ የደለሎ ግዛታችንን የያዙበት አኳኋን ከዚህ በፊት ይታይ ከነበረው የጠብ አጫሪነት ባህሪይ ፍፁም የተለየ ሆኖ አግኝተነዋል። ወረራው እንደ ከዚህ ቀደሙ በአካባቢው በሚኖሩ አርሶ አደሮቻችውና ቁጥሩ ትንሽ በሆነ ወታደር የተወሰደ ጥቃት ሳይሆን በከባድ በረት-ላበስ መሳሪያ (Mechanized Army) የተመራ መደበኛ የሱዳን ሠራዊት የፈፀመው ግድያና የንብረት ማውደም እኩይ ተግባር ነው። ይህ ደግሞ የወረራውን አሳሳቢነትና ይዘት በእጅጉ የገዘፈ እንዲሆን አድርጎታል።
ሱዳን ያሳየችው የጠብ አጫሪነት ባህርይ የሚያስከትለው ዕዳ፤ ለሁለቱ ወንድማማች ሕዝቦች ብቻ ሳይሆን በአካባቢውም የሰላም እጦትና አለመረጋጋት እንዲሰፍን ያደርጋል። ለዚህ ደግሞ ሱዳንን ብቸኛዋ ተጠያቂ ስለሚያደርጋት የሱዳን መንግስት በጥሞና ሊያስብበት ይገባል። ሱዳን ከአሁን በኋላ የወደፊት ቋሚ ማካለልን በሚመለከት ካልሆነ በስተቀር በወረራ ስለያዘችው መሬት ጉዳይ ውይይት አላካሂድም በማለት ያሳየችው የማንአለበኝነት አቋም የኋላ ኋላ የሚያስከትለውን ጠንቅ ሱዳንም ሆነች በቀጥታ፤ ከእሷ ጎን የቆመችው ግብፅ ሁኔታውን በረጋ መንፈስ ሊመረምሩት ይገባል።
ኢትዮጵያ በቅርቡ በውስጥ ጉዳይ የገጠማትን ችግር ሱዳን እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር የወሰደችው እርምጃ እንደ ወዳጅ ከምትቆጠር ከአንዲት የጎረቤት አገር የሚጠበቅ ተግባር ባለመሆኑ ድርጊቱ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብን አሳዝኗል። ይህ ተግባር ደግሞ ውሎ አድሮ ሱዳንን ከፍተኛ ዋጋ ሊያስከፍላት እንደሚችል የአገሪቱ መሪዎች በተለይም የወታደራዊው ክንፍ መልሶ ሊያጤነው ይገባል። ሱዳን በተናጠል የወሰደችው እርምጃ፣ በሁለቱ አገሮች መካከል ወዳጅነትን ለመንገባት ወሳኝ የሆነውን የሁለትዮሽ ፍላጎት ተጻራሪ በመሆኑ፣ በኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ በሚደረግ የአንድ ወገን ጥረት የሚፈለገውን ዘላቂ ሰላም ሊያመጣ ይችላል ብለን አናምንም።
በመሆኑም ኢትዮጵያ በታሪኳ በተደጋጋሚ እንደታየው ሉዓላዊነቷንና ዳር ድንበሯን የሚያስጠብቅ ዝግጁ የሆኑ ጀግኖች ልጆቿ ዛሬም በተጠንቀቅ ላይ መሆናቸውን የሱዳን መንግስት ልብ እንዲለውና አላስፈላጊ የሆኑ ከፍተኛ ወታደራዊና ማህበራዊ ቀውሶች ከመፈጠራቸው በፊት በሰከነ አእምሮ ሁኔታውን እንደገና እንዲመረምር በጥብቅ እያሳሰብን:-
1ኛ) የሱዳን መደበኛ ወታደሮችና ሚሊሽያ ከታህሳስ 6 ቀን 2013 ዓ/ም (ዲሴምበር 15/2020) የኢትዮጵያን ድንበር ጥሰው በኃይል የያዙትን ጓንግ ምላሽ እና የደለሎን ሰፊ ለም መሬት ካለአንዳች ቅድመ ሁኔታ በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ።
2ኛ) እ.ኤ.እ. በ1972 እና በ2005 ዓ.ም በሁለቱ መንግሥታት የተደረጉ የመግባቢያ ሰነዶች በግልፅ እንደሚያሳዩት፤ ድንበሩ በሁለቱ ሃገሮች የጋራ የድንበር ኮሚሽን እስኪካለል ድረስ የሁለቱ ሃገሮች ገበሬዎች በይዞታ ከሚጠቀሙባቸው ቦታዎች ላይ ፀንተው እንዲቆዩ ያመለክታል። የሱዳን መንግሥት ግን ይህን ተቃርኖ ከ25 አመታት በፊት የተያዘብኝን መሬቶች በሃይል አስለቀኩ ማለቱና ከኢትዮጵያ ጋር የተደረጉትን የመግባቢያ ውሎችንና ሰነዶችን በመጣስ በኢትዮጵያ ገበሬዎች ይዞታ ፀንተው የቆዩ መሬቶችን በኃይል ሰራዊት አዝምቶ መያዙ በአለም አቀፍ ሕግ የሚያስጠይቀው መሆኑ ሊታወቅ ይገባል።
3ኛ) ሱዳን ጊዜንና ወቅትን እየጠበቀች ለምትጭረው እሳት በአንደኛ ደረጃ የግብፅ ሁለንታዊ ድጋፍ የተቸራት መሆኑ ገሐድ የወጣ ሃቅ ነው። በመሆኑም የግብፅ መንግስት በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ የምታደርገውን ጣልቃ ገብነት የኢትዮጵያ የድንበር ጉዳይ ኮሚቴ እያወገዘ፤ ግብፅ ከመሰል እኩይ ድርጊቷ እንድትቆጠብ በጥብቅ ያሳስባል። የኢትዮጵያ መንግስትም ግብፅ አካባቢውን የጦርነት ቀጠና ለማድረግ የምታሴረውን ሴራ ለአህጉራዊና ዓለም አቀፍ መንግስታትና ተቋማት ሊያጋልጥ ይገባል ብለን እናምናለን። በተጨማሪም ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ይህንን የሱዳን ወረራና የግብፅን ደባና ተንኮል የአገራችንን ሰላም የሚነሳ ተግባር መሆኑን በመንገንዘብ ለዓለም ህብረተሰብ የማሳወቅ አገራዊ ኃላፊነትና ግዴታ እንዳለበት ማስገንዘብ እንወዳለን።
4ኛ) የሱዳን መንግሥት ሁልግዜ ለድርድር ከሚያቀርባቸው “መረጃዎች” እ.ኤ.አ. በ1902 ዓ.ም. እንግሊዝና ኢትዮጵያ ተፈራረሙ የሚባለው ስምምነት የሻለቃ ጉዌን በተናጠል ያሰመረው መስመር አንዱ ነው። ይህ ሰነድ በወቅቱ የነበሩት አፄ ምኒልክም ሆኑ ከእሳቸው በኋላ እስከ ዛሬ በተከታታይ አገራችንን የመሩ መንግስታት በሙሉ አንዳቸውም ሰነዱን ያልተቀበሉትና እውቅና ያልሰጡት በመሆኑ ኢትዮጵያም ዛሬም ሆነ ወደፊት ይህን በአንድ ወገን ብቻ የተቀነባበረ ሰነድ መቀበል እንደሌለበት የድንበር ኮሚቴው አሁንም በድጋሚ በከፍተኛ አፅንኦት ያሳስባል።
5ኛ) የኢትዮጵያ መንግሥት የችግሩን ውስብስብነት ግምት ውስጥ በማስገባት በሰላማዊ መንገድ ትውልድ ተሻጋሪ የሚሆን መፍትሄ ለማስገኘት የሚያደርገውን ጥረት የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ሙሉ በሙሉ ይገነዘባል፣ ይደግፋልም። ጥረቱ ይሳካ ዘንድም የድንበር ኮሚቴው አቅሙ በሚፈቅደው ሁሉ የበኩሉን ድርሻ ለማበርከት ምን ግዜም ዝግጁ መሆኑን በድጋሜ ያረጋግጣል::
6ኛ) በድንበሩ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮቻችን የሱዳን መንግስት ወታደር፣ ሚሊሽያ እና ጃንጃዊዶች (ቅጥረኛ ወታደሮች) በሚሰነዝሩት ጥቃት ገፈት ቀማሽ ስለሆኑ መንግሥት በቂ ጥበቃ እና ከለላ እንዲሰጣቸው እያሳሰብን፤ ዓመት ሙሉ የለፉበት የዘንድሮው ምርታቸው እና እንስሳዎቻቸው በሱዳን ሰራዊት በመዘረፋቸው፣ ንብረታቸውም በወራሪው ሰራዊት የወደሙ በመሆናቸው አስፈላጊው እርዳታ እንዲደረግላቸው ማስታወስ እንወዳለን። ኢትዮጵያ በየአቅጣጫው የገጠሟትን ችግሮች በድል እየተወጣች በተሟላ መልኩ በልማት እንደምትዘምን የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ ያለውን ፅኑ እምነት ይገልፃል።
ኢትዮጵያ ዛሬም እንደ ትናንቱ በጀግኖች ልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘለአለም ትኖራለች!
የኢትዮጵያ ድንበር ጉዳይ ኮሚቴ
Ethiopian Border Affairs Committee
P. O. Box 9536 Columbus, Ohio 43209 USA
E-mail: ethiopianborders@gmail.com
ታህሳስ 19 ቀን 2013 ዓ/ም (December 28, 2020)