ያልተለመዱ የጠቢባን አሟሟቶች!!
ሄኖክ በላይነህ
አቤ ጉበኛ
አቤ ጉበኛ በሕይወት የነበረበት የመጨረሻው ወር ጥር 1972 ዓም ነበር። በዚሁ ወር አቤ ከባህርዳር ወደ አዲስአበባ ሲመጣ አዲስ መፅሀፍ ለማሳተምና ከነበረበት ችግር ለመውጣት በተስፋ ተሞልቶ ነበር፤ ነገር ግን ነገሮች እንደተጠበቁት ተስፋ ሰጪ አልነበሩም፤ አልተሳኩም። በሕይወት በነበረበት የመጨረሻ ቀን ከጠዋቱ ጀምሮ እየጠጣ እንደነበር አንዳንድ ሰዎች ይናገራሉ ፤ የቀድሞ ሚስቱ ግን “ግራ ተጋብቶ ነበር እንጂ አልጠጣም አልሰከረም ነበር” ብላ ታስተባብላለች። እኩለ ሌሊት ላይ አንድ መጠጥ ቤት ለመግባት ሞክሮ ነበር፤ መጠጥ ቤቱ ግን ከእኩለ ሌሊት ጀምሮ እስከ አስራ አንድ ሰአት ድረስ በሚዘልቀው ሰአት እላፊ ምክንያት ሊዘጋ ነበር። ጠባቂዎች መግባት ቢከለክሉትም ነገሩ ተጋግሎ ወደ ጠብ በማምራቱ አቤ ጭንቅላቱን ተመቶ እራሱን ሳተ። ይህ የሆነው አዲስአበባ ውስጥ ጎጃም በረንዳ በሚባለው አካባቢ ነው።
የቀበሌ ታጣቂዎች አቤን ሆስፒታል ማድረስ ከመቻላቸው በፊት ሞተ። ሬሳው በጥር 30 ቀን 1972ዓም ከዳግማዊ ምኒልክ ሆስፒታል ወጥቶ ወደ ባህርዳር ተወሰደና ጥቂት ጓደኞቹ እና ዘመዶቹ በተገኙበት ተቀበረ። ሌላ ምንጭ ደግሞ የሞተው የካቲት 2 ፣ የተቀበረው ደግሞ የካቲት 5 መሆኑን ይናገራል። አቤ ጉበኛ ሲሞት የ45 አመት ሰው ነበር።
ፕሮፌሰር አሸናፊ ከበደ
ፕሮፌሶር አሸናፊ ከበደ የ፷ኛ የልደት በዓላቸው ዕለት በመኖሪያ ቤታቸው ግልጽ ባልሆነ ምክንያት ሞተው የተገኙ ሲሆን፤ ምናልባት የራሳቸውን ሕይወት ሳያጠፉ እንዳልቀሩ ብዙዎች ይገምታሉ።
አቶ አበራ ሞልቶት የተባሉት ወዳጃቸው ለኢትዮጵያ ቴለቪዥን ቅንጅት በሰጡት ቃለ-ምልልስ ላይ ከዕለተ ሞታቸው በፊት ጽፈውላቸው እንደነበረና ደብዳቤውንም በመጥቀስ፦ «ጋሽ አበራ፤ ስለዚህ ወረቀት ምን ትላለህ? ይህ አዲሱ ሙከራዬ ነው። ግን እንደራዕይ የሚታየኝ ከመጪው ሐምሌ በፊት ወደሌላ አኅጉር እሄዳለሁ። ሞቼ፣ ሥጋዬን ትቼ ከዚህ ወደኒርቫና እሸጋገራለሁ።» እንደሚል አስረድተዋል።
ዘመዳቸው አቶ በቀለ አሳምነው ደግሞ በዚሁ የቴሌቪዥን ቅንብር ላይ ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራሩ፦ «“ባባቱ በኩል ታናሽ ወንድም አለው፤ ታዲያ አሸናፊ ወንድሙ ጋ ደውሎ “ከሣምንት በኋላ የለሁም…. ለሰው ልጅ ከስልሳ ዓመት በላይ መኖር ምንድነው ጥቅሙ?» ብሎት ነበር ይሉና ፖሊሶች ከምናየው ሁኔታ የራስን ነፍስ የማጥፋት ድርጊት ይመስላል ማለታቸውን ገልጸዋል።
በአሉግርማ
በአሉ ግርማ ኦሮማይን በሚፅፍበት ወቅት የማስታወቂያ ሚኒስቴር ዋና ፀሐፊ ሲሆን የሐሀገሪቱ ፕሮፖጋንዳ ክፍል በሱ ቁጥጥር ስር ነበር። ነገር ግን መጽሐፉ ከወጣ ከጥቂት ግዜ በኋላ በመፅሀፉ ምክንያት ከስራ ታገደ። ይህ ሁሉ የሆነው በነሐሴ 1975 ዓ ም ነበር። ለ6 ወይም 7 ወራት ያለ ያህል ስራ ሳይሰራ እንዲሁ ሲንዘላዘል “ተንሳፍፎ” ከረመ። ከፊት ለፊቱ ምን እንደሚገጥመው ያላወቀው በአሉ በ1976 የካቲት ድንገት “ጠፋ”። በአሉ ከስራ በታገደበት ወቅት ምኞቱ “የህዝብ ተቀባይነት እና የሌሎች ደራሲያን አክብሮት ማግኘት ብቻ እንደሆነ” ተናግሮ ነበር።
በአሉ በመጨረሻው “የነፃነት” ቀኑ አንድ ጓደኛው ከቤቱ መጥቶ ሻይ ቡና እያሉ እንዲጫወቱ ጥያቄ አቀረበለት። የበአሉ ሚስት ግን ቀልቧ አንዳች ክፉ ነገር ሊመጣ እንደሆነ ነግሯት ፣ በአሉ ከቤት መውጣት እንደሌለበት በመቃወም ተናገረች ፤ በመጨረሻ ግን ተሸንፋ እጇን በመስጠቷ በአሉ ከጓደኛው ጋር ተያይዞ ወጣ። ሁለቱም ወደሚያዘወትሩበት መጠጥ ቤት አመሩ። ከበአሉ ቤት የወጡት ከምሽቱ አንድ ሰአት አካባቢ ሲሆን ፣ በአሉ ሳይመለስ ቀረ። የበአሉ ሚስት ይዞት የወጣው ጓደኛው ጋር ስትደውል በጊዜ እንደተለያዩ ፣ ከዚያ በኋላ ግን በአሉ የት እንደሄደ ወይም ምን እንደተፈጠረ እንደማያውቅ ነገራት። ለሌሎች ሰዎች ግን በአሉ ከመጥፋቱ በፊት ጭራሽ ለሁለት ሳምንት እንዳላየው በመናገሩ፣ የበዓሉ ሚስት ከተናገረችው ጋር የተፈጠረው መጣረስ ብዙዎችን አስገረመ። በኋላ ጓደኛ ተብዬው ለአቢዮቱ ላበረከተው አስተዋጽኦ የኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ስራ አስኪያጅ ሆኖ ተሾመ። የበአሉ መኪና ከአንድ ሳምንት በኋላ ደብረዘይት መንገድ ፣ ቃሊቲ አካባቢ ተገኘች። ከዚያ በኋላ በአሉ ያለበትን አይቻለሁ የሚል አንድም ነፍስ አልተገኘም። በአሉ ግርማም የደረሰበት ቦታ ወሬ የውሃ ሽታ ሆኖ ቀረ።
በአሉ ግርማ ከጠፋ በኋላ መንግስት በአሉ የኛ ወገን ነበረ ፤ አሁን ግን በአድሃሪነት ከድቶን ተሰወረ የሚል ወረቀት በመላ ሐገሪቱ በተነ። ያለበትን የሚያውቅ ለመንግስት ማሳወቅ እንዳለበት ተገለፀ። ይህ ሁሉ ሽርጉድ መንግሥት በአሉ የት እንዳለ እንደማያውቅ ወይም እጁ እንደሌለበት “ለማስመሰል” የተደረገ ነበር።
በእምነት ገብረአምላክ
በእምነት ጥልቅ ምኞት ስላለው ፣ ጠንካራ ሰራተኛ ስለሆነ ፣ ሀሳባዊነት ስለሚያጠቃው ፣ ምናልባት ደግሞ ጥብቅ አስተዳደግ ስለነበረው ሳይሆን አይቀርም ችግርን መቋቋምና ሽንፈትንና ውድቀትን መቀበል ይከብደው ነበር። በመጨረሻ ከህይወት ቤት በገዛ እጁ ሕይወቱን በማጥፋት ወጣ። ነገር ግን ወደ መጨረሻ አካባቢ ጭንቅላቱ በትክክል መስራቱ አጠራጣሪ ነው ይላሉ ቤተሰቦችና ወዳጆቹ ፦ ልጆቹን ለመንከባከብ ሲል ስራውን አደጋ ላይ ጥሎ ትምህርቱን ከሰሜን ከአሜሪካ አቋርጦ የተመለሰ ሰው ፣ እንዴት ሕይወቱን በማጥፋት ልጆቹን ያለ አባት ያስቀራል?