>
3:26 am - Friday February 3, 2023

ጥያቄ፤ ስለ ግፍ አረዳዳችን፤ በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጸሙ ተባሉ የግፍ ተግባሮችን ባሰብኩ ጊዜ....!!! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ጥያቄ፤ ስለ ግፍ አረዳዳችን፤

በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጸሙ ተባሉ የግፍ ተግባሮችን ባሰብኩ ጊዜ….!!!

ያሬድ ሀይለማርያም

 

ግፍ በማንም ላይ ይፈጸም፣ በማንም ይፈጸም፣ መቼም ይፈጸም፣ የትም ቦታ ይፈጸም፣ ለምንም አላማ ሲባል ይፈጸም፤ ግፍ ግፍ ነው።ግፍ የተፈጸመብት ሰው ከየትኛውም ዘር፣ ኃይማኖት፣ ጾታ፣ ቀለም፣ ብሔር ወይም አገር የሚመደብ ሰው ይሁን እነዚህ በማንነቱ መገለጫዎች የተፈጸመበትን ግፎች ግፍ ከመባል አይለውጡትም።
ግፍ ፈጻሚው አንድ ግለሰብ ይሁን፣ የተደራጁ ግለሰቦች ይሁኑ፣ አንድ ቡድን ይሁን ወይም መንግስት ለተፈጸመው የግፍ አድራጎት ሁሌም ተጠያቂዎች ናቸው።
አንድ ግፍ ተፈጸመ ሲባል ከአንድ ጤነኛ እና ከሚያመዛዝን ሰው የሚጠበቀው ነገር ድርጊቱ መፈጸሙን በበቂ ማስረጃ ማረጋገጥ፣ ከዛ ድርጊቱን ማውገዝ፣ አድራጊው በሕግ እንዲጠየቅ መጣር፣ ግፉአን እንዲጽናኑ እና እንዲካሱ ከጎናቸው መቆም ነው።
አንድ ግፍ በዚህ ሥፍራ፣ በዚህ ቀን፣ በዚህ ቦታ፣ እከሌ በተባለ አካል ተፈጸመ የሚል ዜና ሲሰማ እያንዳንዳችን ምን እንደሚሰማን እና ከዛም ምን እንደምናደርግ እራሳችንን እንጠይቅ እስኪ።
በማህበረሰባችን ውስጥ አንድ ሥር የሰደደ እና በማህበራዊና በእደበኛ መገናኛ ብዙሃን ጭምር ፍንትው ብሎ እየታየ ያለ አሳሳቢ ነገር ለግፍ አድራጎቶች የሚሰጡ የማህበረሰብ ምላሾች ናቸው። ትንሽ ቆም ብለን እንድናስብም ያስገድዱናል።
እስኪ እነዚህን ጥያቄዎች መልሱልኝ፤
+ አንድ ቦታ ለተፈጸመ ግፍ አለም ሁሉ ካልሰማኝ እያለ የሚጮኽ ሰው ተመሳሳይ ድርጊት በሌላ ሥፍራ ሲፈጸም እንዴት ሽንጡን ገትሮ በደሉ የተፈጸመው በዚህና በዛ ምክንያት ነው እያለ ለግፍ ፈጻሚው አካል ጥብቅና ይቆማል?
+ እንዴት በአንድ ማህበረሰብ ላይ የተፈጸመን ግፍ ከጠዋት እስከ ማታ እያነሳ የሚጥል ጋዜጠኛ፣ የመብት ተሟጋች፣ ተንታኝ እና ምሁር ተመሳሳይ ባህሪ ላላቸው ጥቃቶች ሙሉ በሙሉ ጆሮ ዳባ ልበስ ብሎ እንዳልሰማ እና እንዳላየ ይሆናል?
+ እንዴት አንድ የመንግስት ሹም ለአንዱ ግፍ አደባባይ ወጥቶ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ ተመሳሳይ ግፍ በሌላ ሥፍራ እና ሰዎች ላይ ሲፈጸም ድምጹን ያጠፋል?
+ እንዴት የእምነት አባቶች እና የአገር ሽማግሌዎች መንግስት ባወገዛቸው የግፍ አድራጎቶች ላይ ተሰባስበው በአደባባይ አውጋዥ፤ መንግስት ተጠያቂ በሚሆንባቸው የግፍ አድራጎቶች ላይ በራቸውን ዘግተው ሱባዔ ይገባሉ?
ሌሎች ተመሳሳይ ጥያቄዎችን መዘርዘር ይቻላል። ስለ ግፍ እና የግፍ ተግባር ያለን አረዳድ እንደ ማህበረሰብ ሊፈተሽ የሚገባ ይመስለኛል። የግፍ እርምጃ በሕግ ብቻም ሳይሆን በሞራልም እንደ ነውር እና በእምነት ደግሞ እንደ ሃጢያት ስለሚቆጠር በምድርም ሆነ በሰማይ ያስጠይቃል።
ግፍን መሸፋፈን፣ በሌሎች ላይ የሚፈጸም ግፍን ማጣጣል እና ማራከስ፣ ለተፈጸሙ የግፍ አድራጎቶች ሰበብ እየፈለጉ ድርጊቱን ሕጋዊ ወይም የጽድቅ ለማስመሰል መጣር እራስን ከግፍ ፈጻሚው ተርታ እንደማሰለፍ ነው የሚቆጠረው። በአንድ ግለሰብም ላይ ሆነ በሕዝብ ላይ የሚፈጸሙ የግፍ ተግባራት፤ ግድያ፣ ማፈናቀል፣ ማሰር፣ አስሮ ማሰቃየት፣ መዝረፍ፣ በዘር ለይቶ ማዋከብ እና ዜጎችን ለስቃይ መዳረግ ሁሉ የግፍ ተግባራት ናቸው።
+ በሻሸመኔ፣ በአርሲ፣ በመተከል፣ በማይካድራ እና ሌሎች ቦታዎ የተፈጸሙ ግፎችን ያወገዘ ሰው በትግራይ ክልል ውስጥ በኤርትራ ሠራዊት አማካኝነት ግፍ ተፈጽሟል ሲባል እንዴት ድምጽ ያጥረዋል? ከድምጽ ማጥፋትም አልፎ አንዳንዱ ሃፍረት በጎደለው እና በነውረኝነት ስሜት ይበላቸው ይላል? አንዳንዱም ድርጊቱ ለአገር ህልውና ሲባል የተወሰደ ቅዱስ ተግባር አድርጎ ሊያቀርበው ይሞክራል?
+ ችግሩ ተቋማዊ እና መንግስታዊ ቅርጽ እንደያዘ የምታዩት በማይካድራ የተፈጸመውን አሰቃቂ ተግባር የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው ቅድመ ሪፖርት ድርጊቱ በስብዕና ላይ ያነጣጠረ ወንጀል (Crime Against Humanity) ነው ብሏል። ያንን መግለጫውን ተከትሎ ሳይውል ሳያድር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሪፖርቱን አስመልክተው አንዲት ደብዳቤ ለሕዝብ ይፋ አድርገዋል። በደብዳቤያቸውም ላይ በማይካድራ የተፈጸመውን ግፍ ጠቅሰው እና የኮሚሽኑን ሪፖርትም በማድነቅ ወንጀል ፈጻሚዎቹ ‘ጁንታዎች’ ለፍርድ እንዲቀርቡ ኢትዮጵያዊያን እና የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ከመንግስታቸው ጎን እንዲቆም ጥሪ አድርገዋል። ሚዲያዎችም የኮሚሽኑን ሪፖርት ለወር ያህል ሲያራግቡት ቆይተዋል። ይህ በሆነ በወር ጊዜ ውስጥ መሰለኝ ኮሚሽኑ በኦሮሚያ ክልል 40 ከተሞች በተመሳሳይ ሁኔታ በሰብአዊነት ላይ ያነጣጠረ  ወንጀል (Crime Against Humanity) መፈጸሙን በሰፊ ሪፖርቱ ለሕዝብ እና ለመንግስት ይፋ አድርጓል። ሁለቱም፤ በማይካድራውም ሆነ በኦሮሚያ ክልል የተፈጸሙት የወንጀል አድራጎቶች አንድ አይነቶች ናቸው። ከተጎጂዎቹ ቁጥር መበላለጥ በስተቀር። ጠቅላይ ሚኒስትሩን ጨምሮ አንድም የመንግስት ባለሥልጣን በዚህ በሁለተኛው ሪፖርት ላይ ድምጹን ሲያሰማ ግን አላየሁም። የተወሰኑ የግል ሚዲያዎችም በስተቀር የመንግስት ሚዲያዎች ከዜና ባለፈ በኮሚሽኑ ሁለተኛው መግለጫ ላይ ዘገባ ሲሰሩ ወይም የኮሚሽኑን ኃላፊዎች ሲያናግሩ አላየሁም። ለምን?
+ በአገሪቱ ውስጥ ብዙ ግፎች ሲፈጸሙ በአንድ ወይ በሌላ መንገድ መንግስት ተጠያቂ ስለሚሆን ብዙ ጊዜ የመንግስት አካላት ነገሩን በዝምታ ሊያልፉ ይችላሉ። በመንግስት ጥላ ሥር ያሉ ሚዲያዎችም እንደዚሁ። አንጻራዊ ነጻነት አላቸው ተብሎ የሚታሰቡ የግል ሚዲያዎች ለአንዱ ግፍ እያነቡ ሌላውን በጨረፍታ እንኳ ለመዘገብ የሚሰንፉት ለምን ይሆን?
+ መንግስት ላወገዘው ግፍ፤ ልክ እንድ ማይካድራው አይነት ወይም በሰሜን ዕዝ በመከላከያ ሠራዊት ላይ የተፈጸምውን አይነት አሰቃቂ የነውር ተግባር ከሊቅ እስከ ደቂቅ ሲያወግዝ ማህበረሰባችን ግፍን ይጠየፋል ያስብላል። የሚበረታታም በጎና ትክክለኛ ነገር ነው። የኪነጥበብ ባለሙያዎች፣ ምሁራን፣ ጋዜጠኞች እና የቀረው የህብረተሰህ ክፍል ከመንግስት ጎን ቆሞ የማይካድራውን ግፍ ባወገዘ ማግስት ሌላ ግፍ ሲፈጸም ለምን መልሶ ዋሻው ውስጥ ይገባል? በመንግስት ያልተወገዘ ግፍ ግፍ አይደለም ማለት ነው? ወይስ ግፍን ለማውገዝ፣ ለማዘን፣ ሃዘንን ለመግለጽ፣ ነጠላ ለመዘቅዘቅ ዛሬም የመንግስት ፈቃድ የሚጠብቅ የማህበረሰብ ክፍል ለምን ተፈጠረ?
ያሳለፍናቸው ሁለት አመታት መንግስትን ብቻ ሳይሆን ማህበረሰባችንንም በብዙ መልኩ እንድንታዘብ የሚያስገድዱ ብዙ ክስተቶችን ያስተናገድንባቸው ናቸው። ግፍን በግፍነቱ የመጠየፍ ባህል ገና አላዳበርንም ወይም የነበረውን ባህል ይህ የጎጥ ፖለቲካ ቦርቡሮታል። እንደ ማህበረሰብ ግፍን በግፍነቱ ብቻ መጠየፍ ካልቻልን የሌላው ግፍ የኛ ገድል እንደሚሆነው ሁሉ በእኛም ላይ የሚፈጸም ግፍ ለሌላው ገድሉ እየሆነ ይቀጥላል። ይህ አይነቱ ማህበረሰብ ብዙ ግፈኞችን ያፈራል። ግፈኞች በበዙ ቁጥር የግፉአንም በብዙ ሺህ እጥፍ ይሆናሉ። ኢትዮጵያም የግፉአን፣ የብሶተኞች፣ የተሰዳጆች፣ የጉዳተኞች አገር እንደሆነች ትቀጥላለች።
ግፍን እንጠየፍ፤ ግፈኞችን እናውግዝ፣ ሁሌም ከግፉአን ጎን እንቁም።
Filed in: Amharic