ኮ/ል መንግሥቱ እና የኮሎኔል አጥናፉ ኑዛዜ!
ተፈሪ ደምሴ
ኮ/ል መንግሥቱ ደርግን ኮትኩተው አሳድገውት ይሆናል። ነገር ግን አልወለዱትም። የደርግ እናትም አባትም ኮ/ል አጥናፉ ናቸው። ኾኖም ደርግ ፈጣሪውን መልሶ ለመብላት የወሰደበት ጊዜ ከ5 ዓመት ያነሰ ነበር፡፡ ኅዳር 3/ 1970 በዕለተ ቅዳሜ አጥናፉ ተገደሉ። “አብዮት ልጆቿን በላች” ተባለ።
ሲያልቅ አያምር ሆኖ እንጂ መንጌና አጥናፉ ጎረቤት ነበሩ። ሚስቶቻቸው ውባንቺና አስናቀች በአንድ ስኒ ቡና ጠጥተዋል። ትምህርትና ትዕግስት ከነሱራፌል አጥናፉ ጋር ኳስ ሲራገጡ፣ መሐረቤን ያያችሁ ሲጫወቱ ይውሉ ነበር። ጨርቆስ፣ መሿለኪያ፣ 4ኛ ክፍለ ጦር ግቢ የሟችም የ’ገዳይ’ም ቤት ነበር።
መንጌ ቀኝ እጃቸው፣ ጎረቤታቸውና ለአጭር ጊዜም ቢሆን አለቃቸው በነበሩት ሻለቃ አጥናፉ ላይ ድንገት “ሲጨክኑ” ሐዘኑ ከባድ ሆነ። የሟች ልጅ ሱራፌል አጥናፉ እንደሚያስታውሰው ከሆነ ገራገሯ ወይዘሮ ውባንቺ ቢሻው ለቅሶ ደርሰዋቸዋል። “ትዝ ይለኛል እማዬ ወይዘሮ ዉባንቺን ‘ባልሽ ባሌን ገደለው!’ እያለቻት ተቃቅፈው ሲላቀሱ” ይላል ሱራፌል።
ለመሆኑ ከኮሎኔል አጥናፉ አባተ መገደል በኋላ ልጆቹ እንደምን ኖሩ? ከ8ቱ ልጆች 5ኛው ሱራፌል አጥናፉ “መንጌ አባቴን ካስገደለ በኋላ እኛን እንዳሮጌ ዕቃ ከቤት አውጥተው ጣሉን…” ሲል ረዥሙን ቤተሰባዊ ምስቅልቅ በአጭር ዐረፍተ ነገር ይጀምራል፡፡
“ሁለቱ ወንድሞቼ በብስጭት ሞቱ”
ሱራፌል አጥናፉ አባተ እባላለሁ። የኮ/ል አጥናፉ 5ኛ ልጅ ነኝ። አሁን እኔ ራሴ አምስት ልጆች አሉኝ። የምተዳደረው በሹፍርና ነው።
የአጥናፉ ልጆች 8 ነን። አሁን በሕይወት ያለነው ግን አምስት ስንሆን ሦስቱ በሕይወት የሉም። የሁለቱ ሞት ከአባታችን መገደል ጋር የተያያዘ ነው። አባታችን አጥናፉ የተገደለው ሁለቱ ወንድሞቼ ራሺያ በሄዱ ልክ በ10ኛው ቀን ነበር።
የታላቄ ታላቅ ሰለሞን አጥናፉ ይባላል። ራሺያ ለከፍተኛ ትምህርት እንደሄደ ያባታችንን ሞት ሲሰማ በዚያው የአእምሮ በሽተኛ ሆነ። እዚህ መጥቶ አማኑኤል ሆስፒታል ተሞከረ፤ አልተቻለም። እናታችን ብዙ ደከመች። አልሆነም።
በጣም ይበሳጭ ነበር፤ በአባታችን ሞት። ለምሳሌ እንደማስታውሰው ድንገት ተነስቶ በእግሩ ጎጃም ድረስ ይሄድ ነበር። አእምሮው ታወከና በመጨረሻ ብዙም አልቆየ ራሱን አጠፋ።
የሁላችንም ታላቅ ዶክተር መክብብ አጥናፉ ይባላል። እሱም እንዲሁ በአባታችን አላግባብ መገደል በጣም ይበሳጭ ነበር። ራሺያ ሕክምና ተምሮ ከተመለሰ በኋላ ብዙ ዓመት ሆሳዕና “መንግሥቱ ኃይለማርያም ሆስፒታል” ሠርቷል። አባቱን በገደለው ሰው ስም በተሰየመ ሆስፒታል ውስጥ መሥራት ምን ስሜት እንደሚሰጥ አስበው።
ከሆሳዕና ሕዝብ ዶክተር መክብብን የማያውቅ የለም ማለት ይቻላል። ተወዳጅ ሐኪም ነበር። ግን በአባታችን ሞት እጅጉኑ ይበሳጭ ነበር። እኔ እጨቃጨቀው ነበር።
‘በቃ አባታችን የሚያምንበትን ሠርቶ አልፏል። እኛ የራሳችንን ሕይወት ነው መኖር ያለብን’ እለው ነበር። እሱ ግን ብዙ ምስጢር ያውቅ ስለነበር አይሰማኝም፤ በጣም ብስጩ ሆነ። በመጨረሻ እሱም ጭንቅላቱ ተነካና ሞተ።
ሟች ወንድሞቻችን ሰለሞንና ዶክተር መክብብ አባታችን ነገሌ፣ 4ኛ ክፍለ ጦር እያለ የተወለዱ ነበሩ። ሌሎቻችን ግን እዚህ መሿለኪያ 4ኛ ክፍለ ጦር ግቢ ውስጥ ነው የተወለድነው። ቴድሮስ፣ ጌታሁን፣ ሳምሶን፣ እንዳለ፣ እህታችን አብነት፣ እኔን ጨምሮ- ሁላችንም የመሿለኪያ ልጆች ነን፡፡
ከመንጌ ልጆች ጋር አብረን ነው ያደግነው
እኛ ቤት ነበር እኮ የሚያድሩት። መንጌ ከሐረር 3ኛ ክፍለ ጦር አባቴ ሲያስጠራው እኛ ቤት ነበር ያረፈው። ደርጉን ያሰባሰበው እኮ አባቴ ነው። በየጦር ክፍሉ እየደወለ፣ ተወካይ ላኩ እያለ…።
በኋላ ነው ነገር የመጣው። እንጂማ ጎረቤት ሆነን ነው የኖርነው። ውባንቺና እናቴ አስናቀች እኮ ቡና ሲጠጡ ነው የሚውሉት።
እኛ ግቢ ቅዳሜና እሑድ ኳስ ስንራገጥ ነበር የምንውለው። የኮ/ል ነጋሽ ዱባለ ልጆች ምሥራቅ ነጋሽ፣ ገብረየስ ወልደሀና የሚባል ነበር፣ የደርጉ ዋና ፀሐፊ ተብሎ የተመረጠ፣ ከ3ኛ ክፍለ ጦር፤ እሱ 2 ልጆች ነበሩት፣ ስማቸው ተረሳኝ። እኛ ግቢ ነበር ኳስ የምንጫወተው።
ደግሞ ሁላችንም ፈለገ ዮርዳኖስ ነበር የምንማረው። ያኔ ፈለገ ዮርዳኖስ የግል ነበር፤ በወር 6 ብር ይከፈል ነበር። ከመንጌ ሴት ልጅ ጋር አብረን ነበርን።
ልክ መንግስቱ ግድያ ሲሞከርበት አባቴን ‘ቤተ-መንግሥት እንግባ’ አለው። አባቴ ‘እኔ 4ኛ ክፍለ ጦርን አለቅም’ አለ። ያኔ እሱ ጥበቃ የለው ምን የለው…። አንድ አቶ ኤፍሬም የሚባሉ ሾፌር ብቻ ነበሩት። ቤተ-መንግሥት ያልገባነው አባቴ ባለመፈለጉ ብቻ ነበር።
የአጥናፉ ኑዛዜዎቹ
በየክፍለሃገሩ የኢትዮጵያ ትቅደም ባንዲራን የሰጠ፣ ሚሊሻን ያደረጀ አባቴ ነው። በየሄደበት ማስታወሻ የመያዝ ልምድ ነበረው። መአት ማስታወሻ ነው ትቶ ያለፈው። ፎቶዎች፣ ካሴቶች…መአት..መአት
ቅዳሜ ገድለውት እሑድ ቤታችን መጥተው በርብረው ብዙ ነገር ወስደዋል። ይሄ ሁሉ ከዚያ እንዴት እንደተረፈ አላውቅም።
ለምሳሌ በ20/10/69 ዓ.ም የፃፈው የግል ማስታወሻ ላይ “ለጊዜው ብቻዬን ብቀርም እውነትን መከተልና መናገር ምንጊዜም እምነቴ ነው” ይላል።
እነ ተፈሪ በንቲ፣ ኮ/ል ሻምበል ሞገስ፣ ሌ/ኮ/ል ዳንኤል አስፋውና ሌሎችም እሱ ወለጋ ጊምቢ ወታደር ሊያስመርቅ በሄደበት ነው የተገደሉት። ተደውሎ መረሸናቸው ተነገረው።
“እንዴት እንዲህ ይደረጋል። አሁንም ይሄ መግደል አልቀረም? ትናንት አማንን ገደልን፣ ዛሬ ተፈሪን ገደልን፤ ይሄ መግደል የት ነው የሚያበቃው?” ሲል “ና እሱን እዚህ እንነጋገራለን” አለው መንጌ።
ያኔ በ27/5/69 ዓ.ም ጠዋት ከጊምቢ አዲስ አበባ እየመጣ የጻፋት ማስታወሻ እነሱ በተረሸኑ ማግስት መሆኑ ነው።
ላንብብልህ፤
“የተገደልኩ እንደሆን” ይላል ርእሱ።”…በጎሰኞችና በሥልጣን ጥመኞች በሀሰት የተገደልኩ እንደሆን ተመልሻለሁ፤ለጭቁኑ እውነተኛው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሉ እነሆ ኑዛዜዬን በሐቅ አረጋግጣለሁ። ስለሆነም ቤተሰቦቼ የጭቁኑ ወገን ስለሆኑ በሐሰት ታሪክ ታሪካቸውና ሕይወታቸው እንዳይበላሽ፤ እንዳይንገላቱ ለኢትዮጵያ ጭቁን ሕዝብ አሳስባለሁ”
አሁን ሳስበው ከነሱ ጋር ቀላቅለው የገደሉኝ እንደሆን ብሎ ነው የጻፈው።
አባቴ ሁሉን ነገር ልቅም አድርጎ ማስታወሻ የመያዝ ልምድ ነበረው። የየቀኗ ሪፖርት አለች። ብዙ ማስታወሻዎችን፣ ፎቶግራፎችን፣ በካሴት የተቀረፁ ድምፆችን በሙሉ ትቶልን ሄዷል። እንዲያውም ይሄ ነገር በኢትዮጵያ መንግሥት ማኅደር ውስጥ ቢቀመጥ ለመጪው መንግሥት ትምህርት ይሆናል ብዬ አስባለሁ…
እዚሁ የግል ማስታወሻው ላይ ያገኘሁትን ላንብብልህማ…
“እኛ የምናካሄደው አብዮት ነው። በስህተት ንብረት ተወርሻለሁ የሚል ካለ ፍርድ ቤት ይሂድ፤ የተበደለ ካለ ለኛ ሳይሆን ለፍርድ ቤት ይናገር። ማንኛውም ሰው ያለ ፍርድ ቤት ውሳኔ እንዳይገደል አሳስባለሁ” በቀይ እስክሪብቶ ነው የጻፈው።
የመንግሥቱ ልጆች ዶክተር ሆነዋል። እኛ ደግሞ ሾፌሮች ሆንን
እንደነገርኩህ አብረን ነው ያደግነው። ግን እኛ መንጌ አባቴን ከገደለው በኋላ ያላየነው መከራ የለም። ንፋስ ስልክ አጠቃላይ የትምህርት ቤት ክፍያ አቅቶን ተባረናል።
አስታውሳለሁ አንዴ የስፖርት 8 ብር አጥተን ከትምህርት ቤት ስንባረር፣ ልኡል ሰገድ ዘካሪያስ የሚባል ነበር ዲሬክተሩ ያኔ አግኝቶን ሁኔታውን ነገርኩት፤ “ይሄ ክፉ…! ለመሆኑ ጡረታ ሰጥቷችኋል?” ብሎ አዝኖ፣ “ከአሁን በኋላ የአጥናፉ ልጆች ማንም እንዳያባራቸው፤ እኔ አለሁ” ብሎ ወደ ትምህርት ቤት መልሶናል።
ጀርባቸው ይጠና ተብሎ የቀበሌ መታወቂያ ሁሉ የተከልክለንበት ጊዜ ነበር።
እናታችን 3በ5 በሆነች አንዲት ክፍል ቤት ነው ኖራ የሞተችው፤ እሱንም እግዚአብሔር ይስጠው አቶ ወንድሙ የሚባል የከፍተኛ 19 ሊቀመንበር “መንጌ ቢገድለኝም ይግደለኝ” ብሎ ነው ያሰጠን።
እዛች ክፍል ተደራርበን ነበር የምንተኛው። ከፍ ስንል ረዳት ሆንን፣ ከዚያ እንደምንም መንጃ ፍቃድ አወጣን። አባታችን ቢኖር እኛም ዶክተር እንሆን ነበር…ብቻ መንግሥቱ ያላስደረገን ነገር የለም። በመጨረሻ እንዲህ አገር ጥሎ ሊሄድ…
ጄ/ል ጃጋማ ኬሎና አጥናፉ አባተ
በንጉሡ ጊዜ ጃጋማ ኬሎ አለቃው ነበሩ፤ ነገሌ 4ኛ ክፍለ ጦር። በኋላ ከ60ዎቹ ጋር ሊገደሉ ተብሎ እንዳይገደሉ ያደረገው አባቴ ነው። ይሄን ራሳቸው ነው የተናገሩት። እንኳን መገደል፣ እንዳይታሰሩ ብሎ ነው አባቴ ያዳናቸው። ይወዳቸው ነበር። አሁን በቅርብ ጊዜ ነው የሞቱት። እንደመሰከሩለት ነው የኖሩት።
በተደጋጋሚ ‘እኔ ከደርግ የተረፍኩት በኮ/ል አጥናፉ ነው’ ሲሉ ተናግረዋል። መንግሥቱ ግን ሥልጣን እንደያዘ የ3ኛ ክፍለ ጦር አለቃውን ማዕረግ ከልክሎኛል ብሎ ወዲያው ነበር ያስረሸነው። ቂመኛ ይመስለኛል መንግሥቱ።
አባቴ ግን እንደዛ አልነበረም። አባቴ ስለሆነ አይደለም እንደዚያ የምልህ፤ በተደጋጋሚ ማስታወሻውን አይቻለሁ፤ አንብቢያለሁ፤ “እኛ ያመጣነው ለውጥ እኮ ሰው ለመግደል አይደለም” ሲል ጽፏል በተደጋጋሚ፤ ግድያን ተቃውሟል። ያስገደለውም ይኸው አቋሙ ነበር።
ያኔ ከደርጎቹ መሐል ትንሽ ትምህርት የቀመሰውም እሱ ነበር። አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲም፣ አሜሪካም ድረስ ሄዶ ተምሯል።በቁጣም በችኮላም የሚያምን ሰው አልነበረም። ሰከን ያለ ሰው ነበር።
ሁለት ነገር ነው በዋናነት ጥርስ ውስጥ ያስገባው።
ሶሻሊዝም አይሆነንም። የኢትዮጵያ ሕዝብ ሃይማኖተኛ ነው። ታሪኩም፣ ባሕሉም አይፈቅድለትም። ሶሻሊዝም ብለን ባዕድ ነገር አንጫንበት። ሶሻሊዝም ለእኛ አይሆነንም ነበር ያለው። ሌላው ደግሞ ‘እኛ ወታደሮች ነን፤ ሥልጣን ለሕዝብ አስረክበን ወደ ካምፓችን እንመለስ’ የሚል አቋም ነበረው። ያኔ ነው ጥርስ የተነከሰበት። ኮሚቴ አዋቅረው “ባንተ ጉዳይ እስክንወስን ጠብቅ” አሉት።
አጥናፉ ያቺን ሰዓት
ሕዳር 3/1970 ዓ.ም ቅዳሜ ነበር፤ አስታወሳለሁ። ዝም ብሎ ቁጭ ብሎ ሲጽፍ ትዝ ይለኛል። ሦስት ቀን ከቤት አልወጣም። እኔ ጉንፋን አሞኝ ይመስለኛል ቤት ነበርኩ ያን ሰሞን። ሐሙስ አርብ ቅዳሜ ቤት ነው የዋለው፤ ሲጽፍ።
ቅዳሜ ጠዋት ሲወጣ ትዝ ይለኛል። ቶሎ ላንደሮቨሩ ውስጥ አልገባም። አቶ ኤፍሬም አሉ ሾፌሩ። ዝም ብሎ በረንዳ ላይ ቆመ። ኳሴን ይዤ እሱ ጋር ቆምኩ። ጭንቅላቴን እየዳበሰ ለእማዬ፤ “…በይ እንግዲህ ካልመጣሁ የልጆቼን ነገር አደራ” እያለ ተናገራት። መኪና ውስጥ ከመግባቱ በፊት ሁላችንንም እየጠራ ሳመን።
ትንሽ ቆይታ እናቴ በቢሮው ስልክ ደጋግማ ስትደውልለት እያነሳ “አለሁ፣ ደህና ነኝ” እያላት ነበር። የሆነ ሰዓት ላይ መልሳ ስትደውል አንድ ሌላ ወታደር ስልኩን አንስቶ “ጓድ አጥናፉ የለም፤ ካሁን በኋላ መደወል አይቻልም፤ ማታ በቴሌቪዥን ተከታተይ” አላት።
ታውቋታል። ማታ በቴሌቪዥን “አብዮቱን ለመቀልበስ ሲሞክሩ… ምናምን…” እያሉ አወሩ። ለቅሶ ጀመርን። የመንግሥቱ ሚስት ወይዘሮ ውባንቺ ቢሻው ጠዋት ለቅሶ መጣች። የእማዬ ወዳጅ ነበረች። ማልቀስ ጀመረች። እናቴ እሷን አቅፋ “ባሌን ባልሽ ገደለው” እያለች ተያይዘው ተላቀሱ።
የወይዘሮ አበበች መታፈሪያ ውለታ
ሬሳውን አልሰጡንም። ለቅሶ እንዲለቀስ ያስፈቀዱልንም…ኮ/ል ነጋሽ ዱባለ ይመስሉኛል።
ለቅሶው እንዳለቀ ብዙም አልቆየንም፤ የመንግሥት ቤት ነው ልቀቁ ተባልን፤ ከ4ኛ ክፍለ ጦር። የት እንግባ? እናታችን 8 ልጆች ይዛ ወዴት ትሂድ? ማን ያስጠጋን? ምናለ አባታችንን እንደሁ ገድለውታል፣ አይመለስ…ለውለታው፣ ለዚህ ስላበቃቸው እንኳ የቀበሌ ቤት ቢሰጡን?
የአገሩን ሰው ሁሉ የመሬት ባለቤት ያደረገ ሰው ነው፤ እኛ ቤተሰቦቹ የምንቆምበት መሬት ማጣት ነበረብን?
በኋላ እዚህ ሐኪም ማሞ ሰፈር በፍቃዱ ተሰማ የሚባል የእናታችን ዘመድ እሱ “ከገደሉኝም ይግደሉኝ” ብሎ አስጠጋን። አቶ በፍቃዱ 12 ልጅ አለው፤ እኛ ስምንት ነን፤ ሃያ ሰው ሆነን አንዲት ቤት ውስጥ መኖር ጀመርን። 20 ሰው አንድ ቤት እንግዲህ አስበው።
ብቻ በእንዲህ አይነት ሁኔታ አደግን፤ ችግሩ ምግብ ምናምን ነበር።
አንዲት አይዳ በቀለ የምትባል የእናት ያባቷን ቤት የወረሰች ልጅ ታሪካችንን ታውቅ ስለነበር አስጠጋችን። እማዬ እሷ ቤት ምግብ መሥራት ጀመረች። እዚህ ዮሴፍ ቤተ-ክርስያን ጋር አንድ ድርጅት ነበረ። የድርጅቱ ሠራተኞች ሽሮ እናቴ ጋ እየመጡ በኮንትራት መብላት ጀመሩ። ያችን እየሸጥን እንደምንም አደግን።
በመሐል ምን ይሆናል መሰለህ! አንድ ቀን ወይዘሮ አበበች መታፈሪያ የሚባሉ ሴትዮ የተጠለልንበትን ቤት አፈላልገው ይመጣሉ፤ የለገሀር ሚኒ ባለቤት ናቸው። ያኔ ዝነኛ ካፌ ነበር፤ ትዝ ይለኛል በሬኖ መኪና ነበር የመጡት።
‘የኮ/ል አጥናፉን ልጆች አሳዩኝ’ ብለው ገቡ፤ እማዬ ‘ይቅርታ አላውቆትም’ አለቻቸው።
“አዎ አታውቅኚም፤ እኔ ታስሬ ሞት የተፈረደብኝ ሰው ነበርኩ፤ አንድ ስድስት ሰባት እንሆናለን ሞት ተፈርዶብን (አየህ! ያኔ ኮ/ል አጥናፉ በየእስር ቤቱ በየክፍለ አገሩ ይጎበኝ ስለነበር ድንገት ደርሶ ሲገባ ያያቸዋል)፤ ‘ደግሞ እናንተ ምን አድርጋችሁ ነው?’ ሲላቸው፣ ‘አይ እኛ ሞት ተፈርዶብን ነው’ ይሉታል።
‘ምን አድርጋችሁ?’
‘ኢዲዩ ናችሁ ተብለን…’
‘እንዴ! እኛ እኮ ለውጥ ያመጣነው ሕዝቡን ገድለን ለመጨረስ አይደለም፤ ማነው ይሄን ያዘዘው…? አንቺ ምንድነሽ? አለኝ፤ ‘እኔ የለገሐር ሚኒ ባለቤት ነኝ’፤ አልኩት፤ ‘በሉ እሺ ፍቷቸው…’ ብሎ ከሞት ያስጣለን ያንቺ ባለቤት ነው…” ብላ ለእማዬ ነገረቻት።
እሳቸው ተከታትለው፣ አፈላልገውን ነው እንግዲህ የእሱን ውለታ ለመመለስ የመጡት።
“በሉ እንግዲህ! እኔ ካሁን በኋላ አልመጣም፣ ለማንም ትንፍሽ እንዳትሉ ብለው አስጠንቅቀውን፤ በወር 300 ብር ተቆራጭ አድርገውልን ሄዱ። 71/ 72 ዓ.ም ይመስለኛል።
300 ብር በዚያን ጊዜ አስበው፤ አባታቸን አገር ሲመራ እኮ ደመወዙ 800 ብር አይሞላም። እሷንም 500 ለቤት ተቆራጭ ያደርጋል፣ ሌላውን ለኪሱ ይወስዳል። እሳቸው ግን 300 ብር በየወሩ በዚያን ጊዜ በጣም ብዙ ብር ነው።
እውነቱን ንገረኝ ካልከኝ በሳቸው 300 ብር ነው ያደግነው!
አፅሙን ፍለጋ ያልሄድንበት የለም። ያልጠየቅነው የለም። እኔ እንዲያውም በየሳምንቱ ከርቸሌ እየሄድኩ የደርግ ባለሥልጣናትን ብስኩትና ውሃ እየያዝኩ እጠይቃቸው ነበር።
85 ላይ ይመስለኛል፤ ሳሌም የምትባል መጽሔት ላይ ደበላ ዲንሳ እጃቸውን ወደላይ አድርገው “ያስገደልኩትም የገደልኩትም የለም” በሚል የወጡባት መጽሔት ገዝቼ ሳነብ ጋዜጠኛው መጨረሻ ላይ “እንደው በከንቱ ሞተ የምትሉት ሰው አለ ወይ?” ብሎ ጠየቃቸው።
እሳቸው ሲመልሱ “አጥናፉ ያሳዝነኛል። አስታውሳለሁ ለምሳ ስንነሳ አንዴ የምናገረው አለ ቁጭ በሉ ወንድሞቼ ብሎን አንዲት ወረቀት አውጥቶ ንግግር አደረገ። ‘ካምፕ የምንገባበት ቀን ትወሰን፤ ሚክስድ ኢኮኖሚ እናድርግ፤ ሶሻሊዝም የማይሆነን ነገር ነው’ ብሎ ተናገረ። እሱ ለኢትዮጵያ የሚጠቅም ሰው ነበር በከንቱ ሞተ የምለው እሱን ነው” ብለው የተናገሩትን አንብቤ ከርቸሌ ሄጄ አገኘኋቸው።
“የእሱ ልጅ ነህ? አሉኝ። “አዎ!” ስላቸው ገረማቸው። ደጋግሜ ጠይቂያቸዋለሁ። ስለአባቴ ይንገሩኝ እያልኩ…።
ደኅንነቱ ተስፋዬ ወልደሥላሴንም አገኝቼዋለሁ። እሱን እንኳን ሥልጣን ላይ እያለም አግኝቼዋለሁ። ቤቱ እዚህ ሩዋንዳ ነበር። ከእማዬ ጋር አምድ ቀን በጠዋት ሄደን “አባቴን አጥቻለሁ፤ ሥራ አስቀጥረኝ” ብዬው አውቃለሁ።
“ሹፍርና ትችላለህ?” ብሎኝ አልችልም ስለው ያኔ ሠራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ለሽመልስ አዱኛ ደውሎ የሥራ አጥ ወረቀት አሰጥቶኝ ነበር። ሽመልስ የአጥናፉ ልጅ መሆኔን ሲያውቅ አክብሮ ተነስቶ ነው የሥራ አጥነት ወረቀት የሰጠኝ።
(ኢህአዴግ ከገባ በኋላ)ተስፋዬን እስር ቤት ሳገኘው በቀኝ ጎኑ ፓራላይዝድ ሆኖ ነበር። ከአባቴ ጋር የአንድ ኮርስ ሰልጣኞች ነበረ።፡ እሱና አጥናፉ 17ኛ ኮርስ ነበሩ። መንጌ 19ኛ ኮርስ ነው። ብቻ አሳዘነኝ።
ከዚያ በኋላማ ቅዳሜና እሑድ ቤቴ ከርቸሌ ሆነ። ደርጎችን ተራ በተራ እያስጠራሁ ውሃና ኩኪስ እየገዛሁ ላዩ ላይ “ከኮ/ል አጥናፉ አባተ ቤተሰቦች” ብዬ አጽፍበትና እሰጣቸዋለሁ።
አንድ ጊዜ ለገሰን አስጠራሁትና ሱራፌል አጥናፉ እባላለሁ አልኩት። ‘የኮ/ል አጥናፉ ልጅ ነህ?’ አለኝ። ‘አዎ!’ አልኩት። ብዙ አወራን ከለገሰ ጋር። ‘ምናለ አባዬን ባትገድሉት?’ ስለው ‘እኔ አይደለሁም እኮ! መጽሐፍ አንብበህ ነው የመጣኸው?’ አባትህን እኔ አላስገደልኩትም” አለኝ። ሁሉም እንደዛ ነው የሚሉህ።
“እዚህ ጋ ነው ከነወታደር ጫማው የቀበሩት”
የተገደለ ቀን ከቤት ሲወጣ ሁለት መቶ ብር ኪሱ ውስጥ ነበረች። የጋብቻ ቀለበትና ሌላ አንድ የጉልላት ቀለበት ነበረ ያደረገው። እሱን ወስደው መቶ ብሩን ወስደው መቶ ብር ብቻ ነው ለእማዬ የመለሱላት። 100 ብሩ የጥይት መሰለኝ።
የት እንደቀበሩት ለማወቅ ብዙ ጣርኩ!
ኢህአዴግ ሲገባ እኔና እማዬ ሆነን ዊንጌት ሄድን። አፅሙን ፍለጋ።
ዊንጌት የሄድነው ምስክርነት የሚባል መጽሐፍ ላይ “አጥናፉን መንጌ ራሱ ዊንጌት ድረስ ሄዶ ቆሞ ቀብሮታል” የሚል ነገር አንብበን ስለነበረ ነው። የቀይ ሽብር ሬሳ በጅምላ ሲወጣ እኛም እድላችንን እንሞክር ብለን ነው የሄድነው።
አንድ የግቢው ጠባቂ ነገር ነው ጠቆር ያለ ቀጭን ሰውዬ፤ “እኔ ኮ/ል አጥናፉን ሲቀብሩት አስታወሳለሁ’ ብሎ፤ ‘እዚህ ጋ ነው የቀበሩት፤ ከነወታደር ጫማው፤ ከነምኑ” ብሎ አሳየን። እንግዲህ ምንም ምልክት የለም። እንዴት ሊያውቅ ቻለ…? ሰውየውንም ማመን ተቸገርን…ለነገሩ ማስቆፈርያም አልነበረንም ያኔ…በቃ ተውነው።
ዞሮ ዞሮ ለሱ ይሄ አይገባውም ነበር!
እነሱን ታግሎ ለዚህ ያበቃ ሰው፣ ሶሻሊዝም ለኢትዮጵያ አይሆንም ባለ፣ የኢትዮጵያን ገበሬ የመሬቱ ባለቤት ባደረገ፣ ሰው ዝም ብለን አንግደል ባለ፣ ስልጣን ለሕዝብ መልሰን ወደ ካምፕ እንመለስ ባለ፤ እንዲህ መሆን አልነበረበትም። ምናለ ከሚገድለው ቢያሰድደው፣ ምናለ ጡረታ ቢያስወጣው…!
“ነበር”ን የጻፈው ገስጥ የሚባል ሰው አንዴ በአካል አግኝቼው ምን አለኝ…”ቆጥ ላይ አንድ አውራዶሮ ነው የሚሰፍረው፤ ለዚያ ነው እንጂ አባትህ ከእሱ አንሶ አይደለም…።”
የሟችና ‘ገዳይ’ ልጆች ወዳጅነት
ሱራፌል ለቢቢሲ እንደተናገረው ታናሽ ወንድሙ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ከጓድ መንግሥቱ ሴት ልጅ ጋር ይደዋወሉ፣ ለሰዓታትም ያወጉ ነበር። ጥሩ የበይነ-መረብ ወዳጆች ሆነው ቆይተዋል፤ ግን ወንድሜ እየቆየ ሆድ ይብሰዋል። በተለይ አባቷ አባቱን ‘እንዳስገደለ’ ሲያስብ…።
አንድ ቀን እንደተለመደው በበይነ-መረብ ሲያወጉ ይቆዩና “ታውቂያለሽ ግን እኛ ቤት እኮ አንቺ፣ መንጌ፣ የእናትሽ ዉባንቺና የእኔ ወንድሞች ድሮ 4ኛ ክፍለ ጦር አብራችሁ የተነሳችሁት ፎቶ አለ…” ይላታል።
“እውነትህን ነው? በናትህ ላክልኝ?” ትለዋለች፤ “…እማማ ብታየው በጣም ደስ ይላታል፤ እንደውም ሃራሬ ልሄድ ስለሆነ ላክልኝ…” ትለዋለች።
ፎቶውን እልክልሻለሁ ግን እኮ… አባትሽ አባቴን ካስገደለው በኋላ እኛ ጎዳና ወጥተን፣ የሚላስ የሚቀመስ አጥተን፣ የትምህርት ቤት መክፈል አቅቶን ነበር…”አባትሽ ግን እንዴት ጨካኝ ሰው ናቸው? ይላታል።
ከሀራሬ ወደ ለንደን ስትመለስ ታዲያ መልሳ ትደውልለታለች…
“አባቴን እኮ አናገርኩት፤ ከአባታችሁ ሞት በኋላ ይሄን ያህል መቸገራችሁን በፍፁም አያውቅም። እውነቴን ነው የምልህ…በጣም ነው የገረመው ስነግረው…።
“ውሸታም በይው! ሁሉንም ያውቃል፣ እሱ የማያውቀው ነገር የለም…። ሁሉንም ያውቃል”
የመንጌ ልጅ የአባቶች ጦስ ወደ ልጆች እንዳይወርድ የሰጋች ይመስላል። ለምሳሌ ለአጥናፉ አንደኛው ልጅ “ለልጆቹ ኮምፒውተር እንደምትልክለት፣ ሕክምና ትምህርት ከጀመሩ ደግሞ በርከት ያሉ መጻህፍት እንደምትልክለት ቃል ገብታለትም ነበር” ይላል ሱራፌል።
ሱራፌል ጨምሮ እንደመሰከረው የመንግሥቱ ሴት ልጅ ከሐራሬ ስትመለስ ለወንድሙ እንዲህ ብለዋለች።
“አባቴ በሕይወቱ ባደረገው ነገር አንዴም ሲፀፀት ሰምቼው አላውቅም። ነገር ግን በአባታችሁ አጥናፉ ሞት ያዝናል። ‘እሱን ከጎኔ ካጣሁ በኋላ ነው ነገሮች የተበላሹት’ ሲል ሰምቼዋለሁ።
ያማል በብዛት!