>

ታሪክን ወደ ፊት ...!!! (በእውቀቱ ስዩም) 

ታሪክን ወደ ፊት …!!!

(በእውቀቱ ስዩም  ) 

ከምናምን አመታት በፊት በቀዳማዊ ሀይለሥላሴ እና  በጎጃሙ ገዥ ራስ  ሃይሉ  መሀል ሃይለኛ የስልጣን ትግል ይካሄድ ነበር ፤ ራስ ሃይሉ ከብዝበዛና ከውርስ የተገኘ   መአት ብር ነበረው ፤ ተፈሪ  ከጎጄው ጋር ሲወዳደር   እልም ያለ ችስታ ነበር  ማለት ይቻላል  ፤ በዚያ ላይ ተፌ   መላውን ጦቢያ  በስሩ መጠቅለል ይፈልጋል፤   እና መፋጠጥ  መመላለስ ጀመሩ ፤ የተመላለሱበትን ዶሴ አግኝቸ እስካካፍል  በዚህ ግምት አዝግሙ     ::
 ተፌ :- ስማ! ቀዳማዊ ሀይለ ሥላሴ  በሚል ስም  ነግሻለሁ ፤  በአራቱ መአዘን ያለው ሁሉ ፀጥ ለጥ ብሎ  በመገዛት ላይ ይገኛል: በል አንተም የእውቅና ሰርተፍኬቱን ላክልኝ “
 ሃይሉ  ;-  “  ሰውየ! ከመደብ ተነስተህ  አልጋ ወራሽ  ነኝ ስትል  ዝም ብልህ  ጭራሽ የገዛ ስሜን ሰርቀህ  በላዩ ላይ “ሥላሴ “  ጨምረህ ልትነግስ አማረህ”
  ብቻ  የሆነ ጊዜ ላይ ተፈሪ ራስ ሀይሉን ሰበብ ፈልጎ ሸብ አደረገው፤ የተፈሪ ዳኞች   በተከሳሹ ላይ ሞት ፈረዱበት ፤ ተፈሪ  ግን   “ ሞቱን ምረነዋል፤ ታስሮ ይቀመጥ “ ብሎ  ተጎዘጎዘ ፤   በጊዜው እስር ቤት እንደስሙ  ፍርደኛ የሚታሰርበት ቤት ነበር  ፤ ግድንግድ  የብረት ካቴና ፤  ገንባሌ ማሰርያህ ላይ ይገጠምልሀል ፤ብዙ ከቆየህ የታሰርክበት የእግር ብረት እግርህን ይገዘግዝውና ጋንግሪን ይቆርጥልሀል ፤
ብዙም ሳይቆይ ሀይልሻ    ምህረት ሳይሆን ምሬት እንደተቀበለ  ገባው   ፤ ብቻ ራርተው ከእስርቤት ይለቁኛል   ወይም የሆኑ ሰዎች በኮማንዶ ነፃ ይወጡኛል  ብሎ ቢጠብቅም ኮሽ እሚል የለም፤  እና  ራስ ሀይሌ (ሩት)  ከእስር  ስላልተለቀቀ ፤  የሚከተለውን ነጠላ ዜማ ለቀቀ ፤
“ሰው በድየ ነበር እኔም እንደዋዛ
ቁናው ቁናየ ነው ትንሽ ዙሩ በዛ “
ቁምነገሩ ያለው እዚህ ላይ ነው፤
We learn from history that we do not learn from history.” አለ ሄግል !
 አንዳንዴ ሳስበው፤ “ያበራሽን ጠባሳ ያየ በእሳት አይጫወትም “ ያሚለውን ተረት የፈጠረው ሰውየ የሰውን ባህርይ የተረዳ አይመስለኝም!   ሰው እንኳን ከሌላው ከራሱ መከራ አይማርም ፤ አበራሽ ራሷ  እድሉን ብታገኝ  ባዲስ መልክ በሳት መጫወቷ አይቀርም ፤
Filed in: Amharic