>

የአብርሃ ደስታ ሁኔታ አሳሳቢ ነው

Abrha Desta 3

ኪዳኔ ኣመነ

አብርሃ ደስታ ጥላቻን በፍቅር የሚታገል፤ ከስሜት ይልቅ ምክንያት የሚያስቀድም፤ ከብሄርተኝነት ይልቅ ለሰው እና ለሰብአዊነት ልዩ ክብር ያለው፤ የብሄር አጥር በጣጥሶ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ለሁለንተናዊ ለውጥ በጋራ እንዲሰለፍ ብዙ መስዋእት የከፈለ የዘመኑ ዘመናዊ ማንዴላ ነው፡፡
የኔ ትውልድ ካፈራቸው ምርጥና ምጡቅ ፖለቲኮኞ አንዱና ምናልባትም ግምባር ቀደሙ አብርሃ ደስታ ነው፡፡ አብርሽ ኢሰብኣዊነትን በእውቀቱና በብእሩ በሰላማዊ መንገድ ብቻ የሚታገል ምርጥ ኢትዮጵያዊ ነው፡፡ ልክ የ60ዎቹ ትውልድ ተብለው የሚጠሩት እነ ሀይለ ፊዳ፣ ብርሃነ መስቀል ረዳ ፣ ጌታቸው ማሩ ፣ ጥላሁን ግዛው….ምርጥ ወጣቶች ተብለው እንደሚጠሩ ሁሉ አብርሃ ደስታ፣በቀለ ገርባ፣ ሃብታሙ አያለው፣ ….የአሁኑ ትውልድ ምርጥ ወጣቶችና የትውልዱ ውጤቶች ናቸው፡፡ እነዚህ ጀግኖች ሰው አይደለም አይጥም ሳይገድሉ ነው ወደ ወሀኒ የተወረዎሩት፡፡ አንዳች ንብረትም አላወደሙም፡፡ ሀጥያታቸው ፍቅርን መስበካቸውና አምባገነንነትን በማርያም መንገድ መታገላቸው ብቻ ነው፡፡
የስርዓቱ ሰላማዊ ተቀናቃኝ ፖለቲከኞች ለማጥመድ ሆንተብሎ የፀደቀው የፀረሽበር ህግ አብርሃ ደስታ ያለ አንዳች መረጃ አጥምዷል፡፡ ፖሊስ እስከ አሁን ያቀረበው ጠብ የሚል መረጃ የለም፡፡ ሁሌ ተጨማሪ ጊዜ ይሰጠኝ እያለ ሰውን እያሸ ነው፡፡ ወጣቱ ፖለቲከኛ በሃሰት ለማስወንጀል በመቀሌ የተደረጉ አሳፋሪ ደራማዎችም አይተናል፡፡ ዓረና ትግራይ ህወሓት ያደረጋቸው እያንዳንዷ እርምጃ እግር በግር እየተከታተለ ነው፡፡ ጊዜው ሲደርስ ከነጭብጦቹ ይፋ ይደረጋል የሚል ግምት አለኝ፡፡
ከወደ ሰሞኑን ደግሞ ለአበርሀ ምግብ እያመላለሰች ስትጠይቀውና ስትከታተለው የነበረች የአክስቱ ልጅ እንዳትጠይቀው ተከልክላለች፡፡ እቺ እህታችን ከዚህ በፊት በሳምንት አንድ ጊዜ እንድታገኘው ተፈቅዶላት ትጠይቀው ነበር፤ አሁን ግን ከእናቱ፣አባቱ፣ወንድሙ፣እህቱ ውጪ ሌላ ማንም ሊጠይቀው አይችልም አንቺም አትችይም ተብላለች፡፡ የአብርሀ ቤተሰቦች ደግሞ ውክልና ለሷ ነው የሰጧት፡፡ ቤተሰቦቹ በሀውዜን ስለሚኖሩ ሊከታተሉትም ሊጠይቁትም አይችሉም፡፡ ልትጠይቀውም ልትከታተለውም የምትችለው በአደስ አበባ የምትኖረው የአክስቱ ልጅ ብቻ ናት፡፡ ከዚህ የተነሳ መላ ቤተሰቡ ተጨንቀዋል፡፡ ይህ ወጣት ፖለቲከኛ ከሌሎች የህሊና እስረኛች በተለየ መልኩ ጫና እየተደረገበት ነው፡፡ ሌሎች በየ ቀኑ እንዲጠየቁ ተፈቅዶላቸው አብርሃ ግን ያቺ በሳምንት አንዴም ተከልክሏል፡፡ እናም ወንድማችን እኛም ቤተሰቦቹም በምን ሁኔታ እንዳለ ማወቅ አልቻልንም፡፡ ብርታቱ እና ፅናቱ ይስጠው፡፡

Filed in: Amharic