>

ንጉስ ወቅዱስ ላሊበላ እና ስለ ላ-ሊበላ በአስራ አንድ ነጥቦች ስንዘክር (ግሩም ተበጀ)

ንጉስ ወቅዱስ ላሊበላ እና ስለ ላ-ሊበላ በአስራ አንድ ነጥቦች ስንዘክር
ግሩም ተበጀ

የንጉስ ላሊበላ ገድል ስለትውልዱ እንዲህ ይላል፣ “አባቱ በላስታ አውራጃ የቡግናው ገዢ የነበረው ዣን ስዩም ሲሆን፣ እናቱ ደግሞ አገልጋይ ነበረች…፡፡” አገልጋይቱ ከዣን ስዩም ማርገዟን የሰማችው የዣን ስዩም ሚስት በንዴት ጦፈች፡፡ እመቤቲቱን ፍራቻ ነፍሰጡሯ አገልጋይ ወደ ሮሃ – የዛሬዋ ላሊበላ – ሸሽታ ህፃኑ እዚያ ተወለደ፡፡ እናቲቱ ህፃኑን እዚያው ትታ ወደ ዣን ስዩም ቤት ተመለሰች፡፡
ህፃኑን ፍለጋ፣ ዣን ስዩም ሰዎች ወደ ሮሃ ሲልክ፣ ህፃኑ በንቦች ተከብቦ አገኙት፡፡ ይሄኔ ሰዎቹ፣…ላህሊ..በላ አሉ፤ ንቦች ታላቅነቱን ተረዱለት እንደማለት ነው ይላል ገድለ ላሊበላ፡፡ የቅዱስ ላሊበላ የትውልድ ቀን ታህሳስ 29፣ 1101 ዓ.ም ሲሆን በየዓመቱ ታህሳስ 29፣ የገና ዕለት፣ በስሙ በተሰየመችው በቀድሞዋ ሮሐ፣ ባሁኗ ላሊበላ፣ ታላቅ ክብረ በዓል ይሆናል፡፡
የላሊበላ ወንድም ሀርቤ ለአባቱ ዙፋን ከላሊበላ ይልቅ የተገባ በመሆኑ – ከህጋዊ ሚስት የተወለደ እንደመሆኑ መጠን እና ከላሊበላ ጋር ተያይዞ በሚነሳው ትንቢት ሳቢያ ወንድሙን በበጎ አላየውም፡፡ በዚህም የተነሳ፣ ላሊበላ ሀገሩን ለቅቆ ወደ እየሩሳሌም አቀና፡፡ በዚያም ለብዙ ዓመታት ቆየ፡፡
ከስደት እንደተመለሰ፣ መስቀል ክብራን አገባ፡፡ ቢሆንም ግን፣ ወንድሙ ሀርቤን ፍራቻ ወደ በረሃ ለመሰደድ ተገደደ፡፡ ስለ ላሊበላ ወደ ዙፋን አወጣጥ የሚጠቀሱት ዘገባዎች የተለያዩ ናቸው፡፡ አንድ ምንጭ፣ “ሀርቤ የላሊበላን መንገስ አይቀሬነት ስለተገነዘበ፣ ዙፋኑን ለላሊበላ ለቅቆ፣ ገብረመስቀል ብሎ አነገሰው…” ሲል፤ ሌላኛው ደግሞ፣ “በጦርነት ላሊበላ ወንድሙን አሸንፎ ዙፋኑን እንደወረሰ…” ይገልጻል፡፡
የሆነው ሆኖ፣ ላሊበላ፣ በ1156 ዓ.ም፣ ገብረመስቀል ተብሎ ነገሰ፡፡ ለ40 ዓመታትም ገዛ፡፡ ኢትዮጵያዊ ምንጮች እንደሚሉት ላሊበላ አንድ ልጅ ብቻ ነበረው – ይትባረክ፡፡ ምዕራባውያን ምንጮች ደግሞ ሌላ የይትባረክ ታናሽም ነበር ባይ ናቸው – አትያብ የተባለ፡፡
ላሊበላ ያስተዳድረው የነበረው ግዛት እጅግ ሰፊ እንደነበር ይነገራል፡፡ ይኸውም፣ ከአባይ እስከ ምፅዋ፣ ከወንጪት እስከ መተማ፣ ከሐረር እስከ ዘይላ፣ ከጅማ እስከ ጫጫ፣ ከሲዳሞ እስከ ነጭ አባይ ይዘረጋል፡፡
ንጉስ ላሊበላ ይህን ሰፊ ግዛቱን በአራት ከፍሎ በአራት አስተዳዳሪዎች ያስተዳድር የነበረ ሲሆን፤ አቡ ሳሊህ የተባለ የወቅቱ ፀሃፊ የላሊበላን ግዛት በተመለከተ፣ “በዓለም ካሉ አራት ታላላቅ ነገስታት አንዱ … የትኛውም ንጉስ ክንዱን አይቋቋመውም” ብሎለታል፡፡ ላሊበላ፣ በንግስና ዘመኑ ከሌሎች ሀገራት ጋር መልካም ወዳጅነትን ፈጥሮ ነበር፡፡ በወቅቱ ከግብጽ ጋር ተቋርጦ የነበረው የንግድ ግንኙነት ተጀምሯል፡፡ በግብጽ በነበሩት ክርስቲያኖች ላይ የሚደርሰው መከራም ጋብ ብሏል፡፡
መንፈሳዊው ንጉስ ላሊበላ፣ ከሚታወቅባቸው ነገሮች አንዱና ዋንኛው፣ በዘመኑ ከአንድ ወጥ ድንጋይ ያስፈለፈላቸው አስራአንድ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ናቸው፡፡ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ በሶስት መደብ የተከፋፈሉ ሲሆኑ፤ ሁሉም የመሬት ውስጥ ለውስጥ መተላለፊያ ያላቸው ናቸው፡፡ በመጀመሪያው መደብ ውስጥ፣ ቤተ መድኃኒዓለም፣ ቤተ ማርያም፣ ቤተ-መስቀል፣ ቤተ-ደናግል፣ ቤተ-ጎለጎታ እና ቤተ-ሚካኤል ሲገኙ፤ በሁለተኛው መደብ ውስጥ ደግሞ፣ ቤተ-አማኑኤል፣ ቤተ-መርቆሪዮስ፣ ቤተ-ሊባኖስ እና ቤተ-ገብርኤል ይገኛሉ፡፡
በሶስተኛው መደብ ውስጥ የሚገኘው ቤተ-ጊዮርጊስ ነው፡፡ ቤተ-ጊዮርጊስ ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት በስተመጨረሻ የተሰራና እጅግ ያማረ፣ በኪነ ህንፃ ውበቱም ከሁሉም የላቀ ነው፡፡
ይህም፣  የአብያተ ክርስቲያናቱ ሰሪዎች በስራቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተራቀቁ የመምጣታቸው ምስክር ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜም የላሊበላ አብያተ ክርስቲያናት ሲወሱ የሚታየው ምስል የዚሁ የቤተ-ጊዮርጊስ ምስል ነው፡፡ ገድለ ላሊበላ እንደሚያስረዳው፣ የፍልፍል አብያተ ክርስቲያናቱ ስራ የተጀመረው፣ በላሊበላ አስረኛ ንግስ ዘመኑ ነው፡፡
ስራውን ለማጠናቀቅም 23 ዓመት ፈጅቷል ይላል – ገድለ ላሊበላ፡፡
፭  ንጉስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ለማነፅ ምን አነሳሳው?
ገድለ ላሊበላ፣ ንጉስ ላሊበላ አብያተ ክርስቲያናቱን ለማነፅ ስላነሳሳው ምክንያት ሲያትት፣ “ወደ መንግስተ ሰማያት አርጎ እጅግ የሚያማምሩ ህንጻዎችን በመመልከቱና እግዚአብሔርም እነዚህን ህንጻዎች የመሰሉ አብያተ ክርስቲያናት እንዲያንፅ ስላዘዘው፣ ቦታውንም ስለጠቆመው ነው…” ይላል፡፡
ሌሎች ምንጮች ደግሞ፣ “ላሊበላ ለረጅም ዓመታት እየሩሳሌም እንደነበረ፣ እየሩሳሌምንና ሌሎች ሃይማኖታዊ ፋይዳ ያላቸውን ቦታዎችን በመጎብኘቱና ባየው ነገር እጅጉን በመመሰጡ፣ ሌላኛዋን እየሩሳሌም ለመገንባት በማሰቡ ነው…” ባይ ናቸው፡፡
እኒህ ወገኖች እንደሚሉት፣ “በወቅቱ፣ በርካታ ኢትዮጵያዊያን እየሩሳሌምን ለመጎብኘት በሚያደርጉት ጉዞ የሚደርስባቸውን እንግልት ለማስቀረት እየሩሳሌምን፣ አካባቢውንና መንግስተ ሰማያትን ሁሉ በተምሳሌትነት የሚያሳይ ታላቅ ግንባታ ለመስራት ስላሰበ ነው” ይላሉ፡፡
ለዚህም አብነት የሚሆነው በሶስት የተከፈሉት አብያተ ክርስቲያናት ተምሳሌትነት ነው፡፡
የመጀመሪያው ምድብ አብያተ ክርስቲያናት የምድራዊ እየሩሳሌም ተምሳሌት ናቸው፡፡ ይህም፣ ቤተ-ማሪያም ጌተሰማኒን፣ ቤተ-ጎለጎታ የክርስቶስ መቃብርን፣ ቤተ-ደናግል ክርስቲያናዊ ፍቅርና እምነትን ይገልጻሉ፡፡
የሁለተኛው ምድብ አብያተ ክርስቲያናት ደግሞ መንግስተ ሰማያትን እንዲወክሉ ታስበው የተሰሩ ናቸው፡፡ ቤተ-ገብርኤል የመንግስተ ሰማያትን መንገድ፣ ቤተ-ሊባኖስ የእግዚአብሄርን ዙፋን የሚሸከመውን መልአክ ኪሩቤልን፣ ቤተ-መርቆርዮስ ገሃነምን፤ የገነት ተምሳሌት ሰማያዊ እየሩሳሌም ሆኖ የታነጸው ደግሞ ቤተ-አማኑኤል ነው፡፡
ከነዚህም በተጨማሪ ቀራኒዮ፣ የአዳም መቃብር፣ ክርስቶስ የተያዘበት፣ የተፈረደበት፣ ቢታኒያ ሁሉ በተምሳሌትነት የተወከሉበት ቦታ በላሊበላ አለ፡፡ መች ይህ ብቻ፣ በላሊበላ የሚገኘው ዮርዳኖስ ተብሎ የተሰየመው ወንዝም ክርስቶስ የተጠመቀበት የዮርዳኖስ ወንዝ ተምሳሌት ነው፡፡
፮  ውቅር አብያተ ክርስቲያናቱን ማን ሰራቸው?
በዚህ ጥያቄ ዙሪያ የተለያዩ ምንጮች የተለያዩ ገለጻዎችን ይዘው ቀርበዋል፡፡ ገድለ ላሊበላ፣ ራሱ ንጉስ ላሊበላ እንደገነባቸውና መላዕክት የህንጻውን ሰራተኞች ይረዷቸው እንደነበር፣ ሰራተኞቹ በቀን የሰሩትን መላዕክት በማታ እጥፍ ጨምረው እንደሚሰሩ ይገልጻል፡፡
በ16ኛው ክፍለ ዘመን ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ የነበረው ፖርቹጋላዊው ተጓዥ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ በበኩሉ ደግሞ አንድ ካህን የህንጻዎቹ ስራ የተከናወነው በግብጻውያን መሆኑን እንደነገሩት ጠቅሶ ጽፏል፡፡ ከዚህም ጋር ተያይዞ፣ ከ4 እስከ 5ሺ የሚሆኑ በግብጽ ያሉ ክርስቲያኖች በወቅቱ በሀገራቸው በሚደርስባቸው መከራ እና እንግልት ሳቢያ በስፋት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር የሚገልጹ መረጃዎችም አሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በስፋት የጻፉት ስርግው ሀብለማሪያም በበኩላቸው፣ ከላሊበላ በፊት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በርካታ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የመኖራቸው ጉዳይ፣ ንጉስ ላሊበላ በውጭ ሀገር ሰዎች አሰራው የሚለውን ገለጻ አጠራጣሪ ያደርገዋል ይላሉ፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፣ ትሪሚንግሃም የተባሉ ፀሃፊ፣ በላሊበላ አካባቢ ሁለት መቶ ያህል ሌሎች ውቅር አብያተ ክርስቲያናት መኖራቸውን ገልፀው፣ አብያተ ክርስቲያናቱ በውጭ ሀገር ሰዎች ታነፁ የሚለውን አስተሳሰብ አጠራጣሪ ያደርገዋል ባይ ናቸው፡፡ እኚሁ ፀሃፊ፣ ጉዳዩን ሲያጠቃልሉ፣ በውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ላይ  የሚታየው የአክሱማዊ ህንጻዎች ተፅዕኖና የግዕዝ ፊደላት አብያተ ክርስቲያናቱ በኢትዮጵያውያን ለመታነፃቸውና የአክሱማዊ የግንባታ ጥበብ ቀጣይ አካል እንደሆኑ ጠቋሚ ቢሆንም፣ አብያተ ክርስቲያናቱ ውስጥ የሚታዩት ቅርጾች ግን በግንባታው ላይ አንዳች የባዕዳን ተፅዕኖ ሳይኖር እንደማይቀር ጠቋሚ ነው ይላሉ፡፡
፯  ቤተ ማርያም
ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ውስጡ በበርካታ ስዕሎች ያሸበረቀው ቤተ ማርያም ነው፡፡ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን መሃል ላይ ደግሞ ሙሉ ለሙሉ ከታች እስከ ላይ በጨርቅ የተሸፈነ ምሰሶ ይገኛል፡፡
ምሰሶው እስከ 16ኛው ክፍለ ዘመን ድረስ በግልጽ ይታይ እንደነበርና በላዩ ላይም የእየሱስ ክርስቶስ ስም በተለያዩ ቋንቋዎች – ግዕዝ፣ አረብኛ፣ ሂብሩና ሌሎችም የተቀረፁበት እንደሆነ የሚገልጹት አስጎብኚ ካህናት፣ በ16ኛው ክፍለ ዘመን የነበሩት የቤተ-ክርስቲያኑ አስተዳደሪ ባዘዙት መሰረት እስካሁን ድረስ እንደተሸፈነ ይገልጻሉ፡፡
መሸፈኛው ጨርቅ ቢያረጅ እንኳን ጨርቁን ለመለወጥ ማንሳት ሳያስፈልግ፣ በላዩ ላይ እንዲደርቡበት ያስተላለፉት ጥብቅ ትዕዛዝ እስከዛሬ ድረስ እንደተጠበቀ አለ፡፡ ይሁን እንጂ፣  በ1966 ለጥቂት ጊዜያት ምሰሶው ተገልጦ አራቱም ጎኖቹ ፎቶግራፍ መነሳቱ ይነገራል፡፡ ባሁኑ ወቅት እንደተለመደው ከታች እስከ ላይ ተሸፍኗል፡፡
፰  ቤተ መድኃኔዓለም
ቤተ መድኃኔዓለም ከሁሉም አብያተ ክርስቲያናት ትልቁ ነው፡፡ በዚሁ ቤተ ክርስቲያን በስተሰሜን በኩል የቤተ ክርስቲያናቱ ዋና አርክቴክት እንደሆነ የሚነገርለት የሲዲ መስቀልና የሁለት ጓዶቹ መቃብር ይገኛል፡፡
፱  ቤተ ጊዮርጊስ፣ ቤተ ገብርኤል
በቤተ ጊዮርጊስ ውስጥ ንጉስ ላሊበላ የራሱን ዕቃዎች ለማስቀመጥ ይጠቀምበት ነበር የሚባል የዕንጨት ሳጥን አለ፡፡ በሚገርም መልኩ የእንጨት ሳጥኑ በባለ እንጨት ብሎን የሚዘጋ ነው፡፡ በተመሳሳይ መልኩ፣ የቤተ ገብርኤል በሩ በእንጨት መዘውር (Wheel and Axel)
የሚከፈትና የሚዘጋ ነው፡፡ ይኸው ቤተ ገብርኤል ሌላም እንግዳ የሆነ ነገር አለው፡፡ ይህም፣ መግቢያው በየት በኩል እንደሆነ አለመታወቁና ባሁኑ ወቅት ያለው መግቢያ በላሊበላ ዘመን የተሰራ አለመሆኑ ነው፡፡
ትክክለኛው ሳይሆን አይቀርም ተብሎ በሚገመተው በታችኛው መግቢያ ክፍል በኩል ዋሻ ሆኖ በውሃ የተሞላ ነው፡፡
ይህ ቤተ ክርስቲያን ቤተ ክርስቲያን ለመባል የሚያበቃ ምንም ዓይነት የመስቀል ምልክት እላዩ ላይ ባለመኖሩና፣ ከተለመደው የቤተ ክርስቲያን አሰራር ወጣ ባለ መልኩ ከምዕራብ ወደ ምስራቅ አቅጣጫ ይልቅ፣ አሰራሩ በሰሜን-ደቡብ አቅጣጫ በመሆኑ፣ ብዙዎች የላሊበላ ቤተ መንግስት ሆኖ ሲያገለግል የነበረ ሳይሆን እንደማይቀር ይገምታሉ፡፡ ከውቅር አብያተ ክርስቲያናቱ ውጪ የላሊበላ ቤተ መንግስት ነው የሚባል ምንም አይነት ነገር አልተገኘም፡፡
፲  የኢኮኖሚ ቀውስ
ላሊበላ ለአብያተ ክርስቲያናቱ ሥራ ታላቅ ወጪ እንዳወጣ ይገመታል፡፡ ከዚህምጋ በተያያዘ ስራው ወደ መጠናቀቁ ግድም የላሊበላን መንግስት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ቀውስ አጋጥሞት ነበር ይባላል፡፡ እንደ ገድለ ላሊበላ ዘገባ፣ አብያተ ክርስቲያናቱ የተፈለፈሉበትን ቦታ፣ ንጉስ ላሊበላ፣ ከመግዛቱም በተጨማሪ ለግንባታው ሰራተኞች ጻድቁ ንጉስ የጠየቁትን ያህል ይከፍል እንደነበር ተጠቅሷል፡፡
፲፩  በስተመጨረሻ
አስደናቂዎቹን የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት ዩኔስኮ በዓለም ቅርስነት መዝግቧቸዋል፡፡ አንዳንዶችም፣ 8ኛው የአለም አስደናቂ ነገር ሲሉ ያሞካሿቸዋል፡፡
እነዚህ አብያተ ክርስቲያናት ከአህመድ ግራኝ ወረራ ጥፋት እንዴት እንዳመለጡ አይታወቅም፡፡ ንጉስ ላሊበላ በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ተብሏል፡፡
ገድሎች የታሪካዊ ሰዎችን በጎ ጎን እጅጉን አግዝፈው ስለሚያቀርቡ ተዐማኒነታቸውና ሚዛናዊነታቸው የሚጠራጠሩ ቢኖሩም፣ ገድለ ላሊበላ ጻድቁ ንጉስ የመንግስትን ንብረት ለግሉ ተጠቅሞ እንደማያውቅና ፍጹም መንፈሳዊ የሆነ ህይወት እንደመራ ያትታል፡፡ የሆነው ሆኖ፣ ገድለ ላሊበላ እንደሚያስረዳው ላሊበላ፣ ሰኔ 12፣ 1172 ዓ.ም ዓረፈ፡፡
አስክሬኑም በቤተ ጎለጎታ ውስጥ ይገኛል፡፡ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት ሲታሰቡን፣  በ1521 ወደ ሀገራችን መጥቶ የነበረው ፖርቱጋላዊው ተጓዥ ፍራንሲስኮ አልቫሬዝ ስለ አብያተ ክርስቲያናቱ የፃፈው ምን ጊዜም የሚታወስ ነው፡፡
አልቫሬዝ፣ ስለ አብያተ ክርስቲያናቱ በስፋት ከዘረዘረ በኋላ፣ ድንገት፣ ትንታኔውን ገታ አድረጎ እንዲህ ይላል፣ “ከዚህ በላይ እንዳልጨምር ሰዎች አያምኑኝም ስል እስጋለሁ … በእግዚአብሄር ምህረት እምላለሁ፣ ከፃፍኩት ውስጥ አንዳችም ውሸት የለበትም …”
Filed in: Amharic