>
5:13 pm - Thursday April 19, 5010

የቤተክርስትያን ጥበባዊ ሥጦታዎች ለዓለም! (አሰፋ ሀይሉ)

የቤተክርስትያን ጥበባዊ ሥጦታዎች ለዓለም!

አሰፋ ሀይሉ

 

“ዓለምን በጥበቧ ያስደነቀች ብቸኛዋ አፍሪካዊት የሙዚቃ ኖታ ባለቤት – ኢትዮጵያ ናት!”
  – የሀርቫርዷ ፕሮፌሰር (የዛሬዋ ባለ ታሪክ)
ዛሬ ሥራዎቿን ይዤ የቀረብኩት ባለ ታሪክ – በብዙ አካዳሚያዊ ሽልማቶች በክብር የተንቆጠቆጠች የኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ፣ የስታንፎርድ፣ የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮፌሰር ናት። በጥራቱ የዓለማችን ቁጥር አንድ እየተባለ የሚዳነቅለትን የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ የሚዩዚኮሎጂ ዲፓርትመንት ለብዙ ዓመታት በቼርውመንነት መርታለች።
ይህች ርቱዕ ሴት – የዓለምን የሙዚቃ ታሪክ በአንድ መፅሐፍ ያሳተመች፣ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን ዜማዎችና ቅዳሴዎች ላይ ከ30 ዓመታት በላይ የተመራመረች፣ በርካታ መፅሐፎችንና ጥናታዊ ሪከርዶችን በጥንታዊ ኢትዮጵያ የሙዚቃ ጥበባት ላይ ያሳተመች በሥራዋ የተከበረች ዕውቅ ፕሮፌሰር ነች።
ፕሮፌሰር ኬይ ኮፍማን ሸለሜይ። ወይም በብዙዎች አጠራር – ፕሮፌሰር ሸለሜ። በያሬዳዊ የሙዚቃ ቅኝቶች በፍቅር የወደቀች ሴት። የቤተክርስትያንን ለዘመናት የተከማቸ የጥበብ ሀብት ለዓለም ያስተዋወቀች የኢትዮጵያውያን ባለውለታ።
በኢትዮጵያ ለዘመናት የኖሩ ቤተ እስራኤላውያንን የቅዳሴ መዝሙሮች በእየሩሳሌም ካሉ የእስራኤላውያን ጥንታዊ የአይሁድ ቅዳሴዎች ጋር ያላቸውን ተዛምዶ በሙዚቃ ሳይንስ ፍንትው አድርጋ ያሳየች – በኢትዮጵያውያንና በእስራኤላውያን መካከል ያለውን ዝምድና ከሥጋና ደም ከፍ አድርጋ በጥበብ ቋንቋ የገለፀች – የሀርቫርድ ምሁር ነች። ኬይ ሸለሜይ። ሸለሜ። ንግሥተ ሳባ የሰሎሞንን ልብ ከማረከች – የማረከችው አስከትላ በሄደቻቸው ቀዳሾቿ ዝማሬ መሆን አለበት። ትልሀለች። ኬይ ኮፍማን ሸለሜ።
ኬይ ሸለሜ ከ1993 እስከ 1997 ባሉት አምስት ዓመታት ውስጥ ከታዋቂው የፕሪንስተን ዩኒቨርሲቲ ተመራማሪ ከፒተር ጄፍሪ ጋር በጋራ አርታኢ በመሆን – በሶስት መድብል የታተሙ “Ethiopian Christian Liturgical Chants” የሚሉ የኢትዮጵያን የተዋህዶ ቤተክርስትያን ቅዳሴዎች የመዘገቡ እና በሳይንሳዊ/ዘመናዊ መንገድ የሚተነትኑ ሥራዎቿን አበርክታለች።
በእነዚህም ሥራዎቿ ውስጥ – ብዙው የዓለም ሕዝብ – በቃል ብቻ ከትውልድ ወደ ትውልድ ከሚተላለፍ አፍአዊ ኪነተቃል በቀር የተፃፈ የሙዚቃ ኖታ አፍሪካውያን ሊኖራቸው አይችልም ብሎ ቢደመድምም – እነዚህ ከሰሐራ በረሃ በታች የሚገኙ አስደናቂ ኢትዮጵያውያን የቤተክህነት የዜማ ሊቃውንት ግን – ትላለች ፕሮፌሰር ሸለሜ – ልክ በመካከለኛው ዘመን በአውሮፓ እንደተደረገው በመሠለ ዘዬ – የራሳቸውን ኢትዮጵያዊ ቅዳሴያዊ ዜማዎች – በመጀመሪያ በቃል አስጠንተው – ከዚያ ሥርዓትን በተከተለ የምልክት ፅሁፍ ቀመር መሠረት አስጠንተው – በመጨረሻም ያንን ሁሉ ኖታ በቃል አስጨብጠው – በከበሮና በፀናፅል አጅበው – በልዩ ሥርዓታዊ እንቅስቃሴዎች አስደግፈው – ሙዚቃን ከፊል ቃላዊ – ከፊል ንባባዊ – በማድረግ – ለዘመናት ሲቀድሱ የኖሩ የዓለማችን ቀዳሚ የሙዚቃ ጠበብት ናቸው – በማለት የውዳሴና የአግራሞት መዓት ትቸራቸዋለች። ለቤተክርስትያኒቱ ጥንታዊ ቅዳሴዎች።
“A Song of Longing: An Ethiopian Journey” የሚል መፅሐፏም ተጠቅሶላት እናገኛለን ኬይ ሸለሜ። በዚህም መፅሐፏ – ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ ሙዚቃን ማጥናት እንዳለብኝ፣ በህይወቴ የማፈቅረው ሙያ ምን እንደሆነ የገለፀችልኝና ያሳመነችኝ የጥበብ ዓይኖቼን የከፈተች ልዩ ሥፍራ ናት – በማለት ትመሠክራለች።
ኬይ ሸለሜ ወደ ኢትዮጵያ በ70ዎቹ ለጥናት መጥታ ሳለ ጃክ የሚባል ኢትዮጵያን መቀመጫው ያደረገን – እና ኋላ የትዳር አጋሯ የሆነውን ሰውም ትተዋወቃለች። እዚችው አዲስ አበባ ላይ። እና እንደ መቀለድ እየቃጣት ምን ትላለች? – ኢትዮጵያ የጥበብ ዓይኖቼን ገለጠችልኝ፣ የዶክትሬት ዲዘርቴሽኔን የምሰራበትን ታላቅ ኦሪጂናሌ ዕውቀት ገለጠችልኝ፣ እና የማፈቅረውን የህይወት ዘመን ባሌን ከጓዳዋ ገልጣ ሰጠችኝ። በማለት ለኢትዮጵያ ያላትን ልዩ ፍቅር ትመሰክራለች።
ሸለሜ ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊ የሙዚቃ ጥበብ ማወቅ ለሚፈልጉ ሁሉ ያሏትን የጥናት ሰነዶችና የድምፅ ሪከርዶች ስታካፍል ኖራለች። በሀርቫርድና በሌሎች በረገጠችባቸው የት/ት ተቋማት ብዙ ተማሪዎቸን ብዙ አድናቂዎችን አፍርታለች። ተደምማ ታስደምማለች። በኢትዮጵያ። ስለ ኢትዮጵያ። ስለ ታላቋ ቤተክርስትያኒት።
በአንድ ወቅት የኮለምቢያ ዩኒቨርሲቲ የመፅሔት ክፍል ታላቅ አካዳሚያዊ ሽልማት የተቀዳጀችውን ሸለሜን በዩኒቨርሲቲው መፅሔት ላይ ቃለምልልሷን ሊያወጣ ካሜራና መቅረፀ ድምፁን ይዞ ወደ ሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ ቢሮዋ አመራ። እና የገረመው ነገር በፕሮፌሰር ኬይ ሸለሜ ቢሮ ግድግዳ ላይ የተሰቀሉት ብቸኛ ሁለት ስዕሎች ነበሩ። አንዱ የኢትዮጵን ባህላዊ የሙዚቃ መሣሪያ ተጫዋቾች የሚያሳይ የኢትዮጵያ ባህላዊ ስዕል። ሌላው ደግሞ የቅዱስ ያሬድን ቅዳሴ ከሌሎች ቀዳሾች ጋር የሚያሳይ የብራና ላይ ሥዕል።
ይህች የሙዚቃ ጥበባት ተመራማሪና ምሁርት – የኢትዮጵያ ኦርትዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስትያን – ጥንታዊዎቹን የብሉይ ዘመን ዜማዎች – ከራሷ የሀዲስ ዘመን የመካከለኛ ዘመን ዜማዎች ጋር – በአስደናቂ ሕብረዜማ በማዋሀድ – በዓለም ላይ እጅግ ልዩ የሆነ – የራሷን ጁዲኦ-ክርስትያናዊ ዜማዎች የፈጠረች – ድንቅ ዘመን ተሻጋሪ አፍሪካዊት የጥበብ ቤት ናት እያለች ምስክርነቷን በተመስጦ ትገልጣለች።
እኛም – ዘመንን ከዘመን – ሕዝብን ከሕዝብ – ጥበብን ከጥበብ – ሀገርን ከሀገር – ዓለምን ከመንፈስ ጋር ስታገናኝ ዘመናትን እንዳስቆጠረች – በአባቶቻችን ተጠብቀው እስከ አሁን ለኛ ዘመን በቆዩልን ጥበባት በነፃ ጥበቧን እየታደምን የምንገኘው እኛ ምዕመናቷ ደግሞ – ለዚህች ተደንቃ ላስደነቀችን፣ ከብራ ላስከበረችን – ለዚህች ጥበባዊት የሀገር ኩራት ታሪካዊት አፍሪካዊት ተዋህዶ ቤተክርስትያናችን – በተመስጦ፣ በአግራሞትና በሐሴት መንፈስ ተሞልተን – ደጋግመን ምስጋናችንን እነሆ አልን።
በነገራችን ላይ – ኔልሰን ማንዴላ ከእስር ከተፈቱ በኋላ በኮለምቢያ ዩኒበርሲቲ አስተባባሪነት በአሜሪካ የተዘጋጀ የቴረሴንቲኔያል የዕውቅና ዝግጅት ነበረ። በዚያ መድረክ ላይ ስለ አፍሪካ ጥበባት የቀረቡትን የጥናት ፅሑፎች ያስተባበረችው እና ዝግጅት የተደረገበትን አፍሪካዊ ኢትዮጵያዊ ቅዳሴ (ወረብ) በቤተክርስትያን ሊቆች፣ በሌሎች የሙዚቃ ባለሙያዎችና ኬሮግራፈሮች አስጠንታ በመድረኩ ያቀረበችው ደግሞ ፕሮፌሰር ኬይ ሸለሜይ ነበረች። እና በአንደኛው ፅሑፏ ላይ ስትናገር እንዲህ ትላለች፦
“ከቴረሴንቲኔያሉ ዝግጅት በኋላ ኔልሰን ማንዴላን ቀረብ ብዬ ሳናግራቸው እንዲህ በደስታና እርካታ ስሜት ተሞልተው እንዲህ አሉኝ፦ ያንን በከበሮና ፀናፅል የታጀበ የኢትዮጵያውያን የቅዳሴ ሙዚቃ ስሰማ ለመጀመሪያ ግዜ የትውልድ ሀገሬ፣ ቤቴ ያለሁ ያህል ተሰማኝ – “It really made me feel like home for the first time!” ብለው አክብሮታቸውንና አድናቆታቸውን ለግሰውኛል።”
ታሪኳ ብዙ ነው። ከእኔ ይልቅ ለሙያዋ ቅርበት ባላቸው የሙዚቃ ምሁራን አንደበት ቢነገር (ወንድሜ Simeneh Betreyohannes ይሰማል ወይ?) ታሪኳ ከቀረበው እጅግ የሚልቅ ቁምነገር ይገኝበታል ብዬም አስባለሁ። ፈረስ ያደርሳል እንጂ አይዋጋም ነውና – የሰማችሁ የማውቃችሁም (እና የማላውቃችሁ) የሙዚቃ እና የቤተክርስትያን ምሁራን ወዳጆቼን – በዚህ በኩል – እነሆ የቤት ሥራችሁን አስቡበት እላለሁ።
ለማንኛውም የቅዳሴን ሙዚቃዊ ስልቶች ከኢትዮጵያውያን አጥቢያ ቤተክርስትያናት እስከ ሀርቫርድ ላስጓዘችው፣ ብዙ ዕድሜዋን ቅዳሴዎቻችንን በማጥናትና በመመርመር ላሳለፈችው፣ የኢትዮጵያውያንን ጥንታዊ የዜማ ጥበባት በማጠናበት ወቅት “ሙዚቃ ታሪክን መመልከቻ መስኮት!” መሆኑ ስለተገለፀልኝ ከኢትዮጵያ አልፌ የዓለምን ታሪክ በሙዚቃ አንፃር ለመፃፍ በቅቼያለሁ እያለች – በቤተክርስትያን የተቀመጠልንን ጥበብ ተጠቅመን መመልከት ከቻልን – ብዙ በእጃችን ሆነው ያላየናቸው ፀጋዎች እንደሚከፈቱልን ምሳሌ ሆና ላሳየችን፣ ለኢትዮጵያ ወዳጇ – ለፕሮፌሰር ኬይ ኮፍማን ሸለሜይ – ልባዊ ምስጋናዬን ከወገቤ በአክብሮት ጎንበስ ብዬ አቀረብኩ።
(በነገራችን ላይ ስለ ፕ/ር ሸለሜ የቅርብ ጊዜያት መረጃ የለኝም… በሕይወት ትኖር ይሆን? ?… በእርግጠኝነት አላውቅም። የምታውቁ ብታሳውቁኝ ምስጋናዬ የላቀ ነው።)
ዋናውን መልዕክቴንም አልዘነጋሁም፦
ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስትያን የጥበብ መስኮታችን ነች። የታሪክ መስኮታችን ነች። የሀገር፣ የዓለም ሀብት ነች።
እጃችሁን ከቅድስቲት ቤተክርስትያን ላይ አንሱ!!
      
ፈጣሪ የጥበብ ማደሪያውን ኢትዮጵያን ይባርክ።
መልካም ዕለተ ሰንበት –  ለሁላችን ይሁን።
Filed in: Amharic