>
10:27 am - Thursday March 30, 2023

እምዬ ምኒልክ — የፈውስ ንጉሥ! (አሰፋ ሀይሉ)

እምዬ ምኒልክ — የፈውስ ንጉሥ!

አሰፋ ሀይሉ

 

(የጀግኖቻችን አስደናቂ የፈውስ ተጋድሎ – ከአድዋ ድል መልስ!)
በነገራችን ላይ እነዚያ የአድዋ ጀግኖች እጅጉን የሚያስከብራቸው ጀግንነታቸው በጦር አውድማ ላይ ያሳዩት አይበገሬነት ብቻ አይደለም፡፡ በሠላሙም ጊዜ ህልማቸውና ጥረታቸው ሁሉ በሀገርና ህዝብ ፍቅር የተቃኘ መሆኑ ጭምር ነው፡፡ እነዚያ የአድዋ ጀግኖች ከአንፀባራቂው የአድዋ ተጋድሏቸው መልስ፣ ሀገራችንን ኢትዮጵያን በዘመናዊ አቅጣጫ ለማሳደግ የሚችሉትን ሁሉ አድርገዋል፡፡ ከእነዚህም መስኮች አንደኛው በጦርነቱ የቆሰለውን፣ በተለያዩ በሽታዎች የተጠቃውን የሠላም ጊዜ ቀዳሽ፣ የጦርነት ጊዜ ወታደር ሆኖ የሚያገለግል ምስኪን ህዝባቸውን ከህመሙ ለመፈወስ ያደረጉት ጥረት ሁልጊዜ በአንድናቆት ሲወሳ የሚኖር ነው፡፡
እምዬ ምኒልክ አድዋ ሲዘምቱ ኢትዮጵያችን ውስጥ ባለፍ ገደም ከሚመጡ የፈረንጅ ሃኪሞች በቀር አሌ የሚባል ዘመናዊ ህክምና መስጫ ተቋም አልነበረም፡፡ ዘመናዊ ህክምና፣ በቂ መድሃኒት፣ በቂ የጦር ሜዳ ህመም ማስታገሻና ማስታመሚያ ባልነበረበት ሁኔታ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ ላገሩ ነፃነት ሲል ለመስዋዕትነት (እና ለህመምና ስቃይ) ራሱን አሳልፎ የሰጠው፡፡ ያን መርሳት ጀግኖች አባቶቻችንን እጅ መስበር ነው፡፡ ውለታቸውን ስናስብ ህመማቸውን፣ ሥቃያቸውን ማሰብ የግድ ይላል፡፡ ጀግኖቻችን ለዘለዓለም ይክበሩልን፡፡
እና እምዬ ምኒልክ ይሄ የህዝባቸው ቁስል ውስጣቸው ድረስ ዘልቆ የጠዘጠዛቸው ንጉሥ ናቸው፡፡ በቻሉት ሁሉ የዘመናዊ ህክምናን ለህዝባቸው ተመኝተዋል፡፡ አስተዋውቀዋል፡፡ ተክለዋል፡፡ እና ህዝባቸውን ፈውሰዋል፡፡ እምዬ ምኒልክ – የኢትዮጵያ እናት፡፡ የፈውስ አባት፡፡
ምኒልክ በአድዋ ዘመቻ ወቅትና ከአድዋ ማግሥት ጀምሮ ዘመናዊ ህክምናን በመጀመሪያ ለአድዋ ቁስለኞች፣ ብሎም ለመላ ኢትዮጵያውያን ለማዳረስ በማለም የተጻጻፏቸው ቁጥራቸው ከ20 በላይ የሚሆኑ ኦፊሴላዊ ደብዳቤዎቻቸው በታሪክ ተመዝግበው ይገኛሉ፡፡ ከእነዚያ የመልዕክት ልውውጦች ስለ እምዬ ምኒልክ ሰብዓዊ ማንነት በቀላሉ ማወቅ ይቻላል፡፡
ምኒልክ ከሩሲያ መንግሥት ጋር ተወዳጅተውና ደጅ ጠንተው ወደ ኢትዮጵያ ያስመጡት የመጀመሪያው የሩሲያ የሐኪሞች ቡድን በሩሲያው ንጉሥ ዛር ኒኮላ መልካም ፈቃድ በ1888 ወደ ኢትዮጵያ የተላከው ሰባት ሃኪሞች ያሉት ቡድን ሲሆን፣ በአድዋ ጦርነት የቆሰሉብንን ኢትዮጵያውያን እንዲያክሙልን በቀይ መስቀል ሥር አድርገው መድኃኒትና የህክምና መርጃ ቁሳቁሶችን አስይዘው በጄኔራል ኒኮላዎስ ሸዊደው የሚመሩት እነዚያ ሰባት ሃኪሞች ለጥቂት ወራት የህክምና አገልግሎታቸውን ከሰጡ በኋላ ወደ ሩሲያ ተመልሰዋል፡፡ ከእነዚህ መሐል ሮድዝቪች፣ ብሮቭስቲን፣ ግሊንስኪ፣ ፔርፊሊኖፍና ያክሳቢክቭስኪ የተሰኙት ሩሲያውያን ሀኪሞች ስማቸው ጎልቶ ይታወቅ ነበረ፡፡
ምኒልክ በአድዋ ለቆሰሉ ዜጎች የነበራቸውን የእናት አባት ያህል ልዩ ትኩረት የሚገባን ሲጀመር በመጀመሪያዎቹ ወራት በቀይ መስቀሉ ለተኙ የአድዋ ቁስለኞች (ለበሽተኞች በሙሉ) በየዕለቱ ምግብ ተዘጋጅቶ እንዲሄድላቸው ያደረጉት የህመምተኞች ምግብ፣ ከራሳቸው ከእምዬ ምኒልክ ጓዳ ወይም ከቤተመንግሥት ወጥቤት እየተዘጋጀ የሚላክላቸው መሆኑን ስናውቅ ነው፡፡ አዝማሪ እንዲህ እያለ ቢገጥምላቸው በሥራቸው ነው፡-
‹‹ጥንትም ጠቢብ ነበር ሠሎሞን አባቱ
ምኒልክ በለጠ ሰው ይዞ መብላቱ፡፡
መድኃኒት ጥቂቱ ይበቃል እያለች
የምኒልክ እናት አንድ ወልዳ መከነች፡፡››
በኋላ ግን የህዝቡ ቁጥር በዝቶ ከቤተመንግሥት ሃኪምቤት ድረስ ውሃና ስንቅ ማመላለሱ እጅግ አዳጋች እየሆነ በመምጣቱ፣ እና ሃኪምቤቱም በብዙ ቁሳቁሶች ራሱን እንዲችል ብርቱ እገዛ ስላደረጉለት፣ እዚያው ሐኪም ቤቱ ክልል ውስጥ ማድቤት ተሠርቶ ለህመምተኞችና ለሃኪምቤቱ ሠራተኞች ምግብ እንዲበስልላቸው ይደረግ ጀመር፡፡ እንዲህም ሲደረግ እኮ ምኒልክ የራሳቸውን የቤተመንግሥት የወጥቤት፣ የግምጃቤት፣ ጥበቃና ሌሎችም አስፈላጊ ሰዎችን መድበው እኮ ነው፡፡
ለሩሲያኖቹ የቀይመስቀል ሃኪምቤት የተመደበች የቤተመንግሥት ወጥ ቤቷ ወይዘሮ አስካለ አጎ ስሟና ጣት የሚያስቆረጥም ሙያዋ ተጠቅሶላት እናገኛለን፡፡ የዘበኛው የአቶ ተመቸ ባለቤት ነበረች፡፡ ሌሎችም በእምዬ ምኒልክ መልካም ፈቃድ ከቤተመንግሥት የተዘዋወሩ ግቢውን በዘበኝነት ተመድበው የሚጠብቁ በአቶ የምሩ ቱፋ ኃላፊነት ሥር ያሉት አቶ ሰናድር ጉሌ፣ አቶ ነፋቀና አቶ ተመቸ የሚባሉ ኢትዮጵያውያን ነበሩ፡፡ ግምጃ ቤት አቶ ነመዋቅ፣ እንዲሁም አራት ውሃ ቀጂ ሴቶችም መድበዋል ምኒልክ ለሃኪም ቤቱ፡፡
ለአድዋ ቁስለኞች ማረፊያ የሚሆኑትን ታዛዎች ራሳቸው እቴጌይቱ በቀጥታ ኃላፊነቱን ወስደው በሃኪምቤቱ ድንኳን አስተክለው ቀኑን ሙሉ ሲለፉ ውለው ማታ ወደ ቤተመንግሥታቸው እንደሚመለሱ እማኝ የውጪ ጸሐፊያን በከተቡልን የታሪክ ማሰታወሻዎች ተጠቅሶላቸው የምናገኘው ነው፡፡ ምኒልክና ጣይቱ ብቻም አይደሉም ደግሞ፡፡ ከአድዋ በህይወት ተርፈው የመጡት የምኒልክ መኳንንት ሁሉ ያለመታከት ቁስለኞቻቸውን ለማሳከምና ከስቃያቸው ለመገላገል የቻሉትን ሁሉ ርብርብ አድርገዋል፡፡ ታሪካቸው ያኮራል፡፡ ለወገን የነበራቸው መንሰፍሰፍ፡፡ የወገንን ህመም እንደራሳቸው ተሰምቷቸው የሚያረጉ የሚጨብጡት የሚደርሱበት ጥግ ራሱ እጅግ ልብ ይነካል፡፡
ለምሳሌ በአዲስ አበባ እምዬ ምኒልክ ለአድዋ ቁስለኞችና ከህዝቡ መሀል በሌላም በሽታ ለተጠቁ ህመምተኞች ያደረገትን መልካም ሥራ ሁሉ በሐረርም ደግሞ ልዑል ራስ መኮንን አድርገውት እናገኛለን፡፡ ራስ መኮንንም ያልተቆጠበ ተመሳሳይ እገዛና ጥረት አድርገው የሩሲያ ቀይ መስቀል ሃኪምቤት የተወሰነ ቡድን በጂቡቲ-ድሬዳዋ በኩል ወደ ሐረር ገብቶ ጊዜያዊ የህክምና ጣቢያ እንዲቋቋምና ብዙ ኢትዮጵያውያን ቁስለኞች ዘመናዊ ህክምናን በወቅቱ እንዲያገኙና ከህመማቸው እንዲድኑ አድርገዋል፡፡
በሩሲያ የታሪክ ጸሐፊዎች በአኀዝ ተጠቅሶ ከምናገኘው የፈውስ ገድል ጥቂቱን እንመልከት፡፡ ሩሲያውያኑ የህክምና ቡድኖች በማስታወሻዎቻቸው በዝርዝር ከመዘገቧቸው አሃዞች መሐል ከአድዋ መልስ በሁለት ወራት ብቻ በአዲስ አበባና በሐረር በሩሲያኖቹ ሃኪሞች የሕክምና አገልግሎት ያገኙ ቁስለኞችን ብዛት የሚያሳየው ሰነድ አንዱ ነው፡፡ በሐረር 15ሺ955 ሰዎች፣ በአዲስ አበባ 18ሺ919 ሰዎች የመጀመሪያ ደረጃ ህክምናና ተደርጎላቸው፣ እና ምክር ተለግሷቸው ለቤታቸው እንደበቁ ተመዝግቦ እናገኛለን፡፡
በቋሚነት ተኝተው፣ እና በተመላላሽ የታከሙ ሰዎች ቁጥር ደግሞ በሐረር ለ7ሺ819፣ በአዲስ አበባ ለ5ሺ237፣ የቀዶ ህክምናና ብርቱ የህክምና አገልግሎቶች ደግሞ ብሶባቸው ለተገኙ በሐረር ለ151 ሰዎች፣ በአዲስ አበባ ለ75 ሰዎች እንደተሰጣቸው የሃኪምቤቱ መዝገብ ያስረዳል፡፡ በወቅቱ ፔትሪ ቩሴፍ የሚባል የህክምና ተማሪ ዋና ዋና የበሽታ ዓይነቶችንና ጠንቃቸውን የሚገልጽ አጭር መጽሐፍ አዘጋጅቶ፣ የወቅቱ የምኒልክ አስተርጓሚ በዛብህ ኤልያስ ወደ አማርኛ እንዲመልሰው እንደተደረገና ለህዝብ ተሰራጭቶ ብዙዎች ስለጤና አጠባበቅ መሠረታዊ ግንዛቤን እንዳገኙበት ተጠቅሶ ስናይ መገረማችን አይቀርም፡፡ እውነት እምዬ ምኒልክ፣ ራስ መኮንን፣ እና ሌሎቹም ኋላ ስማቸውን የምጠቅሳቸው ያገራችን ዘመናውያን አባቶች የ19ኛው ክፍለዘመን መሪዎች ሳይሆኑ፣ ዘመናቸውን ቀድመው የተሻገሩ የ21ኛው ክፍለዘመን ባለ ብሩህ አዕምሮና ራዕይ መሪዎች እንደነበሩ እንረዳለን በእውነት፡፡
አጼ ምኒልክ ለቆሰለ ለታመመ ወገናቸው ይህን ሁሉ አድርገውም ሲረኩ አናገኛቸውም፡፡ ደግሞ ሃኪምቤት መድረስ አቅቶት በየቤቱ ስለቀረው ሰው ሲጨነቁ፣ እና ሩሲያውያኖቹ ጥቂት ሰንብተው ለእነዚያም መምጣት ላልቻሉት ህክምና እንዲለግሱላቸው ሲማጸኑ እናገኛቸዋለን፡፡ በአንዱ ደብዳቤያቸው እምዬ ምኒልክ ገና እርዳታ ያላገኘ ብዙ ኢትዮጵያዊ በየአቅጣጫው እንዳለ ገልጸው ጥቂት ሀኪሞችን እንዲያስቀሩላቸው የሩሲያውን ሃኪሞች አዛዕ ጀኔራል ሸዊደውን ሲማጸኑ እናገኛቸዋለን፡፡ ታሪክ ዘግቦት እንደምናየው ያ ስጋታቸው እውን ሆኖ ብዙ በሽተኞች ዘግይተው እንደደረሱ፣ እና ተማፅኗቸው ውጤት አግኝቶ ለዜጎቻቸው ፈውስን ማዳረስ እንደተቻላቸው እንገነዘባለን፡፡ አንዱ የምኒልክ ደብዳቤ እንዲህ ይላል፡-
‹‹ይድረስ ከትልቁ የመስኮብ ቀይ መስቀል እንደራሴ
ኒኮላ ሸዊደው፡፡ ሰላምታየን እልካለሁ፡፡
ከአንተ ጋራ የመጡ ሐኪሞች ሥራቸውን እጅግ
ስላሳመሩ ብዙ ደስ አሰኙኝ፡፡ ነገር ግን ቁስለኛው
ሁሉ እስከ ዛሬ ድረስ ክረምቱን ፈርቶ ሳይገባልኝ
ስለቀረ ሦስት ሐኪሞች ወር ያህል ከኔ ጋር
እንዲቀሩ ማድረግ ቢመችህ እጅግ ደስ ይለኝ ነበር፡፡
የተቻለህን ሁሉ እንደምታደርግ አልጠራጠርም፡፡
የተመኘሁት እንዲሆንልኝ ብዬ ተስፋ አለኝ፡፡
መስከረም 24 ቀን አዲስ አበባ ከተማ ተጻፈ 1889 ዓ.ም.፡፡››
የምኒልክ ዋና ሃሳብ አገልግሎቱን ሰጥቶ ወደመጣበት በሚሄደው ጊዜያዊ ህክምና መገኘቱ ላይ ብቻ ያተኮረ አልነበረም፡፡ የንጉሡ ዋና ዓላማ የመስኮብ ቀይ መስቀል ሥራውን ጨርሶ ወዳገሩ ሲመለስ፣ እርሱን የሚተካና ህዝቤን በቋሚነት የሚያክምልኝ ዘመናዊ ሃኪምቤት እንዴት ባደርግ አገኛለሁ የሚል ነበር፡፡ በመስኮቦቹ ቀይመስቀል ማህበር ሃኪምቤት ፈንታ፣ ተመሳሳዩን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል መታከሚያ አቋቁሞ የፈውስ አገልግሎቱን ለህዝቡ ማበርከቱን እንዲቀጥል ለማድረግ ነበረ ህልማቸው ሁሉ፡፡ በዚህም ሀሳብ ላይ ጀኔራል ሸዊደው ስለተስማማ አንድ ዋና ሀኪም፣ ሁለት ረዳት ሃኪሞች፣ አንድ አስታማሚና አንድ አስተርጓሚ ኢትዮጵያ ላይ እንዲቀሩ አድርጎላቸው ወዳገሩ ሄዶዋል፡፡ ይህን አጋጣሚ በመጠቀም አጼ ምኒልክ ለጄነራል ሸዊደው ከጻፉት ሰፋ ያለ የደብዳቤ መልዕክት፣ ምስጋናቸውንና በልባቸው ያሰቡትን ውጥን ያሰፈሩባትን የመግቢያ ክፍል ብቻ መርጠን እንይ፡፡ እንዲህ ይላሉ እምዬ፡-
‹‹ይድረስ ለክቡር ጀኔራል ኒኮላ ሻዊደው የመስኮብ
መንግሥት ቀይ መስቀል ማኅበር አለቃ፡፡
ወዳጃችን ጀኔራል ሆይ!
ከብዙ ብልሃት ከሚያስደንቅ ብልሃት ጋር የመስኮብ
መንግሥት የቀይ መስቀል ማኅበረተኞች ቁስለኞቻችንን
በሽተኞቻችንን አስታማችሁ ስለ አዳናችሁልን ከእርስዎም ጋራ
የመጡትን የቀይ መስቀል ማኅበረተኞች ሐኪሞችና የሐኪም
ረዳቶች በኔና በሠራዊቱ ስም በብርቱ አመሰግናለሁ፡፡
እግዚአብሔር ያመስግናችሁ፡፡ ደግሞም ለቀይ መስቀል
ማኅበረተኞች የሚገባውን ሁሉ መሣሪያ የሚያስፈልግ
መድኃኒት ሁሉ ትታችሁ መሔዳችሁን አይተን የተደነቀው
አሳባችሁን አስተውለን እናመሰግናችኋለን፡፡
አሁንም የኢትዮጵያ መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ የመስኮብ
መንግሥት ሰንደቅ ዓላማ ተክቶት የቀይ መስቀል ማኅበርን
አጠገብ ስፍራውን ስለያዘ ሁላችሁንም በልባችን ታትሟል እንጂ
አልተለያችሁትም፡፡…››
ብቻ ይገርሙኛል እምዬ፡፡ ይገርሙኛል በዚያን ጊዜ የነበሩ አርበኞች አባቶቻችን፡፡ ምን ያህል ልባሞች እንደነበሩ፡፡ ምን ያህል አርቆ አስተዋዮች እንደሆኑ፡፡ ግሩም ነው በእውነቱ፡፡ ምኒልክ በዚያ ብቻ ያቆሙ ከመሰለህ፣ ገና ምኒልክን አላወቅካቸውም ማለት ነው ወንድሜ! ምኒልክ ጥቂት ሃኪሞች ቀርተው በኢትዮጵያ ምድር ህክምና እንዳይቋረጥ አደረጉ፡፡ ከዚያስ? ከዚያም ኢትዮጵያውያንን ደግሞ ዘመናዊ የህክምና ጥበብ እንዲቀስሙላቸው አጥብቀው ፈለጉ፡፡ እና ከፈጣሪ በታች የቻሉትን ሁሉ ጥረት አደረጉ፡፡ ተሳካላቸውም፡፡
ከአድዋ ማግሥት በኢትዮጵያ የመጀመሪያዎቹ የውጭ ሃገር የሃኪሞች ቡድን ገብቶ ለህዝባቸው የህክምና አገልግሎቱን እንዲያደርግ የውጭ መንግሥታትን ደጅ በመጥናት የተጻጻፏቸው ከ20 በላይ ታሪካዊ ደብዳቤዎች ይገኛሉ ብያለሁ፡፡ ከእነዚያ ደብዳቤዎች በአንደኛው ሩሲያ ለሁለተኛ ዙር ሃኪሞችን ወደ ኢትዮጵያ መላኳን አስመልክተው ዳግማዊ ምኒልክ ለሩሲያው አቻቸው ለንጉሠ ነገሥት ዳግማዊ ኒኮላ በየካቲት 13 ቀን 1892 ዓ.ም. በጻፉት ደብዳቤ ውስጥ እንዲህ የሚል ሐረግ ይገኝበታል፡-
‹‹… ደግሞ ከሥራቸው ይልቅ ባሕርያቸው የተወደደ በዘመቻም
በከተማም የመንግሥትዎን ወታደሮችና ሕዝቦች ያገለገሉ
የመንግሥትዎን ሐኪሞች ስለ ሰደዱልን እግዚአብሔር
ያመስግንልን፡፡ ዛሬ ደግሞ ከፊተኛው ይበልጥ የኢትዮጵያን
መንግሥት እስከ መጨረሻው መርዳትዎን ሲገልጡልን የፊተኞቹ
ሐኪሞች ቢሔዱ እንደገና ሌሎች ሐኪሞች በመተካት ለእኔ ብቻ
አይደለም በኢትዮጵያ ሕዝብ ፊት ትልቅ ደስታ ተደረገ፡፡››
በሌላኛው የይለፍ ደብዳቤያቸው ውስጥ ደግሞ እምዬ ምኒልክ ወደ ሩሲያ ተወስደው በህክምና ሙያ የሚሰለጥኑ አምስት ኢትዮጵያውያንን፣ ምኒልክ ከጫኑለት የተለያዩ የሥጦታና መገልገያ ቁሳቁሶች ጋር ይዞ ለሚጓዘው የሩሲያ ሃኪም እንዲህ ጽፈውለት እናገኛለን፡-
‹‹ይድረስ የሌለው (ይህን ለሚያዩ ሁሉ)፡-
ተመስኮብ መንግሥት ተልኮ የመጣ ሐኪም ዶክተር
ካርሰንስኪ ወደ ሀገሩ እንዲሔድ ፈቅጄለታለሁ፡፡
የዘጠኝ በቅሎ ጭነት አምስት የሀበሻ ልጆች ይዞ
ይሔዳልና ይለፍ አትከልክሉት፡፡
17 ቀን መጋቢት አዲስ ዓለም ከተማ በ1893 ዓ.ም.
ተጻፈ፡፡››
እነዚያ ወደ ሩሲያ በተለያየ የህክምና ሙያ እንዲሰለጥኑ በአጼ ምኒልክ የተላኩት 5 ኢትዮጵያውያን ስማቸውንና ሠልጥነው ስለተመለሱበት የሙያ መስኮች፣ ስላነሳነው ጉዳይ ብዙውን ታሪክ ሰንደው ለትውልድ ባኖሩልን በልሂቁ ኢትዮጵያዊ ፕሮፌሰር ሥርግው ሀብለሥላሴ በተጻፈው ‹‹ዳግማዊ ምኒልክ የአዲሱ ሥልጣኔ መሥራች›› መጽሐፍ ላይ እንዲህ ተጠቅሶ እናገኘዋለን፡-
1) ሃኪም ግዛው (የውስጥ ህክምና)
2) ሃኪም ታችበሌ (የውስጥ ህክምና)
3) ሃኪም ጴጥሮስ (የውስጥ ህክምና)
4) ሃኪም ሳላ (መድኃኒት ቅመማ)
5) ሃኪም ቦና (መድኃኒት ቅመማ)
ከጊዜ ወደ ጊዜ በምኒልክ ወደ ሩሲያ ተልከው በመድኃኒት ቅመማ፣ በውስጥ ህክምና፣ በአስተርጓሚነትና በሆስፒታል አስተዳደር የትምህርት መስኮች ወደ መስኮብ ተልከው ሠልጥነው የተመለሱ የሀበሻ ልጆች ቁጥራቸው እየጨመረም ነበረ፡፡ በእነዚህ ሁሉ ግንኙነቶችና የውጭ እገዛዎች የምኒልክ የምስጋና ደብዳቤዎችና ውለታቸውን ለመመለስ በቻሉት ሁሉ የሩሲያን መንግሥት ለማስደሰት ያደርጉ የነበረው ጥረት ሁሉ እጅግ ያስደንቃል፡፡ የኢትዮጵያ ህዝብም የምኒልክን ልብ ያገኘው ይመስላል፡፡ በወቅቱ በውጭ ሰዎች ላይ ያለው የህዝቡ እምነት ገና ሥር ያልሰደደ ስለነበረ፣ በራሱ የሀበሻ ዘመናዊ ሀኪሞች እጅ የመታከሙን ብሥራት በደስታ ነበር የተቀበለው ህዝቡ፡፡ አንዳንዴ ይህን ከአሁኑ የተገላቢጦሽ ምኞታችን ጋር እያወዳደርኩ እገረማለሁ፡፡
በኢትዮጵያችን የመጀመሪያውን የህዝብ ሀኪም ቤት የሆነውን (ምኒልክ ሆስፒታልን) እምዬ ምኒልክ በ1903 ዓ.ም. ሲያቋቁሙ በዋና ሃኪምነት ሆስፒታሉን እንዲመራ የራሳቸው ሃኪም የነበረውን የጉዋዳሉፕ ተወላጅ የፈረንሳይ ዜጋ ጥቁር ሃኪም ዶክቶር ቪታሊየን የሚባል ቀጠሩት፡፡ በእርሱ ሥር በሃኪምነት የተሰማሩት እነዚህና ሌሎችም ምኒልክ ሩሲያ ልከው ያስተማሯቸው ኢትዮጵያውያን ሀኪሞች ነበሩ፡፡ ትንሽ ቆይቶ ዶክተር ጋርጊዮና ዶክተር ሄርሜኒየር የተባሉ ሁለት ሃኪሞችም ተቀጠሩ፡፡ ይህን ታሪክ ዶክተር ሜራብ ቪታሊየን ‹‹ሐኪሞችና ሕክምና በኢትዮጵያ›› በሚል ርዕስ በፈረንሳይኛ ቋንቋ በጻፈው መጽሐፍ ላይ በዝርዝር አስቀምጦት እናገኛለን፡፡
በፕ/ር ሥርግው መጽሐፍ ተጠቅሶ የምናገኘው መክብብ ደስታ ስለ ዳግማዊ ምኒልክ ሀኪሞች በጻፈው የምሥጋና ቃል እንዲህ የሦስቱን ሀበሻ ሐኪሞች ስም በግጥም አወድሶት እናገኘዋለን፡-
‹‹የጥንቱን አገልጋይ ከዚህ ልጻፈው
ምስጋና ይግባው ለሐኪም ግዛው፡፡
ብልሆቹን ሳልጽፍ መች እላለሁ ዝም
ለኃይሌ በላቸው ለኃይሌ ግሩም፡፡››
ምኒልክ ሀበሻን በዘመናዊ ህክምና ተምሮ እንዲመጣ ማድረግ ቻሉ፡፡ እንግዲህ አሁንስ ምን ቀራቸው? – ወንድሜ ሰውየው እኮ ምኒልክ ናቸው! እንዴት ምን ቀረ ብለህ ትጠይቃለህ? የቀረውማ የኛው የራሳችን የኢትዮጵያውያን ሆስፒታል ነዋ! ኢትዮጵያዊ ሃኪም ቤት! የኛ፣ በኛ፣ ለኛ የሚሆን ሀኪምቤት! እና ሩሲያኖቹ በወጡ ማግሥት የሚመለከታቸው መሀንዲሶች የሀኪም ቤት ፕላን እንዲያዘጋጁ ምኒልክ ትዕዛዝ አስተላለፉ፡፡ እና ፕላኑን በቶሎ ተዘጋጅቶ ቀረበላቸው፡፡ ሥራውም በ1903 ዓመተ ምህረት ተጀምሮ በዚያው ዓመት አለቀ፡፡
ለህክምና የተሠሩትን እነዚያን ሞላላ ትላልቅ አዳራሾች ማን ሠራቸው? ማን ጀመራቸው? አንዱን አጼ ምኒልክ ራሳቸው ቆመው ማሠራት ጀመሩ፡፡ ምኒልክ ሲጀምሩ የተቀሩትን አዳራሾች ለማሠራት መኳንንቱ ተከፋፈሏቸው፡፡ አርዓያ የሚሆን ሁለነገሩን ለሀገሩ ለህዝቡ የሰጠ መሪ – ማን እንደ እምዬ ምኒልክ!? የምኒልክ ወገን በመሆኑ የህይወት ዘመን ኩራቴ ነው! የኢትዮጵያውያን ኩራት! ናቸው እምዬ ምኒልክ በእውነት!
እነዚያ በታሪክ ስማቸው ሰፍሮ የምናገኛቸው ለህዝባችን ፈውስን እናምጣለት ብለው ካዝናቸውን፣ ጉልበታቸውን፣ ጥረታቸውን፣ ፍቅራቸውን ሁሉ አስተባብረው የመጀመሪያውን ኢትዮጵያዊ ሃኪም ቤት ከምኒልክ ጎን ተሰልፈው ተከፋፍለው የገነቡት መኳንንት እነማን ናቸው ለመሆኑ? ቁጥራቸው 6 ነው፡፡ የአንዱን ግን ዶ/ር ሥርግው በወቅቱ በህይወት አልነበረም ብለው ያስታውሱናል፡፡ እነዚያ የፈውስ አባቶቻችን፣ ሁሉም ስመጥሩ የአድዋ ጀግኖቻችን ናቸው፡፡
1) ራስ መኮንን ወልደሚካኤል፣
2) ራስ ወልደ ጊዮርጊስ አቦዬ፣
3) ራስ ተሰማ ናደው፣
4) ራስ ጎበና ዳጨ፣
5) ፊታውራሪ ሀብተ ጊዮርጊስ ዲነግዴ፣ እና
6) ደጃዝማች አባተ ቧያለው፡፡
/በዚህ መልኩ ነበር የምኒልክ ሃኪምቤት የተቋቋመው፡፡ ፋሺስት ጣሊያን አዲስ አበባን ሲይዝ ከሃኪምቤቱ ግድግዳዎች ላይ ምኒልክ የሚለውን ስም በሙሉ አጥፍቷቸው አንድ ቦታ ላይ ብቻ ‹‹ም›› የምትለው ፊደል ለታሪክ መቅረቷን ልብ ይሏል፡፡ በተረፈ ስማቸው ከላይ በ4ኛ ተራ ቁጥር የተገለጸውን ራስ ጎበና ዳጨን ግን – የታሪክ ምሁሩ ዶ/ር ሥርግው ሀብለሥላሴ – በወቅቱ በህይወት አለመኖራቸውን ይጠቅሱታልና – ምናልባት በእርሳቸው ስም ከልጆቻቸው የተበረከተ አስተዋፅዖ ይሆናል ብለን እንለፈው፡፡/
የምኒልክ መኳንንት በሙሉ እጅግ የሚያስገርም ቀናዒ ልብ ነበራቸው ማለት እንችላለን አፋችንን ሞልተን፡፡ ምኞታቸው ሁሉ በየሚያስተዳድሩት ግዛት ለሚኖረው ህዘባቸው በተቻለ መጠን ዘመናዊ ነገሮች እንዲቋቋምለት ነበረ፡፡ ይህ ሁሉ የመኳንንቱ ቀናዒነት የምኒልክን የዘመናዊነት ግስጋሴ ህልም እውን መሆን በእጅጉ አግዟል፡፡ ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያ ህዝብ ከዘመናዊ ህክምና ጋር በበቂ ሁኔታ እንዲተዋወቅና ሰው ሲታመም ወደ ሐኪም ቤት መሄድ እንዳለበት እንዲያምንበት ያደረጉት ታላቅ የአስተሳሰብ ለውጥ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ አንዱ የዘመኑ አዝማሪ ግጥም እንዲህ ይላል፡-
‹‹ኧረ እናንተ ሆየ በሽታየ ጠና
ሐኪሞቹ ሰፈር ውሰዱኝ ቀበና፡፡››
የሚያሳዝነው ግን በአድዋ ማግስት ሰለቸኝ ደከመኝ ብለው ሳይቀመጡ ለሕዝባቸው የዘመናዊ ህክምና ፍላጎት መሟላት ቀን ተሌት የተጉት እምዬ ምኒልክ – በሚያሳዝን ሁኔታ የልጅ ልጃቸውን ወሰን ሰገድን በበቂ ህክምና እጦት አጡ፡፡ የልጅ ልጃቸው ወሰን ሰገድ ቀዶ ጥገና ተደርጎለት ስለ አልተፈወሰ በቀዶ-ጥገና የነበረው ህክምና አጥጋቢ እንዳልሆነ ለመግለጽ ሕዝቡ ስሜቱን በሚከተለው ግጥም መግለጹን ታሪክ ያወሳናል፡-
‹‹አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ
እንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊፈጥር መጣ፡፡››
በሃኪምቤት ብቻም አልተወሰኑም እምዬ ምኒልክ፡፡ ከውጭ ያመጧቸውን ሃኪሞችና በአዲስ አበባ የሚገኙ ቆንሲሎችን በማግባባት፣ ፈዋሽ መድሃኒቶችን ከቀረጥ ነጻ በማድረግ፣ እና በተለያዩ ማበረታቸዎችና ማትጊያዎች እንደ ምንም ብለው ሁለት ፋርማሲዎች (በዘመኑ አጠራር ‹‹መድሃኒት ቤቶች›› ወይም ‹‹የመድሃኒት መሸጫዎች›› በአዲስ አበባ፣ አንድ ደግሞ በሐረር እንዲከፈቱ አድርገዋል፡፡ መረጃው ስለሌለኝ ብቻ ሳልጠቅስ ባልፈውም በሌሎችም የሀገራችን ጠቅላይ ግዛቶች ተመሳሳይ አብነቶች እንደሚኖሩ አምናለሁ፡፡
በታሪክ በፎቶግራፍ ቀርተውልን ከምናገኛቸው የምኒልክ ዘመን የፋርማሲ ማስታወቂያዎች በጣም ልብን የሚነካው (ፈገግታም የሚያጭረው) ቀደም ብለን ስሙን አንስተነው የነበረ እምዬ ምኒልክ ለምኒልክ ሆስፒታል ዘግየት አድርገው የቀጠሩት ዶክተር ሚራብ ጊዮርጊያ የተባለው ሃኪም የከፈተው መድኃኒት ቤት ማስታወቂያ ነው፡፡ እንዲህ ይል ነበር የሃኪም ጊዮርጊዮ ማስታወቂያ፡-
‹‹የሐኪም ሜራብ ጊዮጊዮ መድኃኒት ማሰታወቂያ፡-
የሐኪም ሜራብ ጊዮርጊዮ መድኃኒት ቤት ከ700
የሚበልጥ ሁሉም መጀመሪያ ዓይነት መድኃኒት በመልካም
ዋጋ መሸጡን በማክበር ለሕዝብ ሁሉ ያስታውቃል፡፡ ከሱ ዘንድ
የሚጠጣው ኮሶ የወስፋት መድኃኒት ሁሉ ነው፡፡ ደግሞም
የሐኪም ጥሩ ሽቱ አለ፡፡››
በጣም ያሳቀኝ ሌላኛው መድሃኒት ቤት ነው፡፡ በአዲስ አበባችን የጊዮርጊዮ መድሃኒት ቤት ብቸኛው ተፎካካሪ የሆነው የ‹‹ቅዱስ ጊዮርጊስ መድኃኒት መሸጫ ቤት››፡፡ ይሄኛው ፋርማሲ የተከፈተው በግንቦት ወር 1907 ዓ.ም. ሲሆን፣ ባለቤቱ ዛን የሚባል የጀርመን ተወላጅ ነበር፡፡ የሚገርመው ዛን በሙያው ሃኪምም መድሃኒት ቀማሚም ሳይሆን፣ የሲኒማ ተዋናይ ነበረ፡፡ ተዋናይ መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡
ይህን የህክምና ሙያ አለማወቁን ለመሸፈን ‹‹ሐኪም ዛን›› ብላችሁ ጥሩኝ እያለ ለሰዉ የተለያየ ማባበያ ይሰጥ ስለነበር፣ ህዝቡ በወደደው ስሙ ‹‹ሐኪም ዛን›› እያለ መጥራት ጀመረ፡፡ ያን ማዕረግም የአዲስ አበባ የአራዳ ልጆች አፀደቁለት፡፡ እና እስከ መጨረሻው ሃኪም ዛን እያለ ነበር በደብዳቤዎቹ ግርጌ የሚፈርመው፡፡ ሃኪም ዛን ብዙ ደንበኞች ለመሳብ ችሎ እንደነበር ታሪኩ ያወሳል፡፡ አንዳንዴ በአሁን ዘመን ብዙ የፋርማሲ ጉዶችን እየሰማሁ፣ ብዙ ሃኪም ዛኖችን አስባለሁ እና እሳቀቃለሁ፡፡ ወይ ሃኪም ዛን!?
በመጨረሻም በምኒልክ ያላሰለሰ ጎትጓችነት የተነሳ በመዲናችን አዲስ አበባ ከሚኖሩ የውጭ ሀገራት ሌጋሲዮኖችና ቆንሲሎች መካከል ጥቂቶቹ ለህዝቡ የህክምና እርዳታና መድሃኒት ይለግሱ እንደነበር ታሪክ ዘግቦላቸው እናገኛለን፡፡
ለሁሉም ውለታቸውን ፈጣሪ ይመልስልን! ለእምዬ ምኒልክ፣ ለኢትዮጰያ እናት፣ ለአድዋ ጀግኖች አባቶቻችን፣ ስለህመማችን ለቆሰሉት፣ ስለቁስላችን ለተጨነቁት ለተጠበቡት ጀግኖች ሩኅሩኅ አባቶቻችን፣ ክብረት ስጥልን! የኢትዮጵያ አምላክ ነፍሳቸውን በገነተ አፀዱ በክብር ሥፍራ ይቀበላት! ለትውልዳችን የእነርሱን የአባቶቻችንን ብልሃት፣ ሩህሩህነት፣ ሀገር ወዳድነት፣ ጀግንነት፣ ልብ፣ እና ልባምነት አብዝቶ ይስጥልን ፈጣሪ አምላክ!
ጽሑፌን በትዕግሥት ለዘለቃችሁ ወደጆቼ ሁሉ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 
Filed in: Amharic