>

ኢትዮጵያ ልጇን መዘንጋት የለባትም! ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)

ኢትዮጵያ ልጇን መዘንጋት የለባትም


በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው የፌዴራል መንግስትና በሰሜን ኢትዮጵያ በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት መሃከል ስለተደረገው ግጭት የግል ምልከታ

ደረጀ መላኩ ( የሰብዓዊ መብት ተሟጋች)


እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ እንደ ሰብዓዊ መብት ተሟጋች የኢትዮጵያ ጉዳይ ያሳስበኛል፡፡ ስለሆነም ባለፉት ሰላሳ አመታት በኢትዮጵያ የተከሰቱ ሁነቶችን በታ ላቅ ትጋት፣ ጉጉትና ፍላጎት (with sympathy and interest) ስከታተል የቆየሁ ነበርኩ፣ አሁንም እየተከታተልኩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡  አንባቢውም  የኢትዮጵያ ጉዳይ እንቅልፍ ከነሳቸው ኢትዮጵዊ ዜጎች መሃከል አንዱ እንደሆንኩ ይረዳል ብዬ እገምታለሁ፡፡ በዚህ ምክንያት በቅርቡ በተከሰተው ግጭት ምክንያት ትኩረቴን በኢትዮጵያ ላይ እንዳሳርፍ አድርጎኛል፡፡ በትግራይ በተደረገው ግጭት ጀርባ ምን አለ ? የእኛ አቋም ምን መሆን አለበት ?

አዲስ አበባ የብዙ ጎሳዎች  ሀገር የሆነችው የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ስትሆን ብዙ የህዝብ ቁጥር የያዙት የኦሮሞና አማራ ብሔር ናቸው፡፡ ሁለቱም 30፣30  ፐርሰንት በድምሩ 60 ፐርሰንቱን የሀገሪቱን የህዝብ ቁጥር ይይዛሉ፡፡ በሰሜን ምስራቅ የሚኖሩት የትግራይ ተወላጆች ቁጥር ደግሞ ወደ 6 ፐርሰንት ይደርሳል፡፡ ሌሎች በርካታ ጎሳዎች (ብሔሮች) ደግሞ በደቡብ ኢትዮጵያና በምስራቅ ኢትዮጵያ ይገኛሉ፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ኢትዮጵያ ወደ 116 ሚሊዮን ቁጥር የሚደርስ ህዝብ መኖሪያ እንደሆነች ይነገራል፡፡ እንደ ጎርጎሮሲኑ አቆጣጠር 2018 ዶክተር አብይ አህመድ በትረ ስልጣኑን ከጨበጡ ወዲህ ለ27 አመታት ስልጣን ላይ የነበሩት የህውሃት ፖለቲካ ፊትአውራሪዎች ተጽኗቸው እየቀነሰ መምጣቱ  በመጨረሻም ከፖለቲካው መድረክ ገሸሽ ማለታቸው የሚታወቅ ነው፡፡

እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1976 ላይ የጠወለዱት፣በ40ዎቹ የእድሜ አጋማሽ የሚገኙት ዶክተር አብይ ስልጣን ከጨበጡ ወዲህ የፖለቲካው ፍልውሃ መቀየሩ የማይካድ ነው፡፡ በመጀመሪያዎቹ አመታት ባመጡት የፖለቲካ ለውጥ ምክንያት በብዙ የፖለቲካ ተንታኞች ዘንድ በአፍሪካ የፖለቲካ ሰማየ ሰማያት ላይ የተንጸባረቁ ኮከብም የሚል ስያሜም ተሰጥቷቸው  ነበር፡፡ በአለም ላይ ዝነኛ የሆነው የኢራን መጽሔት ዤንዩ አፍሪክ  በበኩሉ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 2019  ባወጣው እትሙ ላይ እንዳሰፈረው ከሆነ ‹‹ የአፍሪካ ታላቅ ሰው ›› በማለት አሞግሷቸውም ነበር፡፡ The renowned Parisian magazine Jeune Afrique named him Africa’s leading personality in 2019. 

ዶክተር አብይ የሚንስትሮችን ቁጥር ብቻ በመቀነስ ሳይገቱ፣ ከ20 ሚንስትሮች ውስጥ የ10ሩ የሚንስትርነት ስልጣን ለሴቶች እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡ ከዚህ ባሻግር በሀገሪቱ ወህኔ ቤቶች ውስጥ ታስረው የነበሩ በርካታ የፖለቲካ መሪዎችና አባላት እንዲፈቱ መንግስታቸው ወስኖ ነበር፡፡ ከኤርትራ ጋር ሰላም እንዲፈጠርም አድርገዋል፡፡ የመንገድና ባቡር ግንባታዎች ተጠናቀዋል፡፡ የሐይል ማመንጫ የውሃ ግድቦች እየተገነቡ ሲሆን ኢትዮጵያ ለወደፊቱ ለሱዳን፣ኬንያ፣ዲጂቡቲ እና ለምስራቅ አፍሪካ የሀይል ማመንጫ አቅርቦት ማእከል እንደምትሆን ተስፋ ይደረጋል፡፡ ከቻይና እና ህንድ ጋር የሚደረገው ግንኙነት እኩል ጥቅም ያለው ነው፡፡ ቻይና ከኤሽያ ሀገሮች መሃከል ዋነኛዋ የኢትዮጵያ ኢኮኖሚክ አጋር ስትሆን፣ ህንድ ከኢኮኖሚክ ሸሪክነቷ ባሻግር ለኢትዮጵያ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ምሁራንን ትልካለች፡፡ 

ሆኖም ግን ይሁንና  ዶክተር አብይ በሀገር ውስጥም ሆነ በአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ክብርና ዝናን የሚያስገኙ ልእለ ስራዎችን ቢያከናውኑም የስልጣን ዘመናቸው በብዙ ችግሮች የተተበተበ ወይም የተሞላ ነው፡፡ ለአብነት ያህል እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2019 በ10 ሺህዎች በሚቀጠሩ ደጋፊዎቻቸው ፊት የመግደል ሙከራ ተደርጎባቸዋል፡፡ ለደጋፊዎቻቸው ምስጋና ይግባቸውና እርሳቸው አልተጎዱም ነበር ነገር ግን በርካቶች የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ የተገደሉም ነበሩ፡፡ ከአንድ አመት ግድም በኋላ ( እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ሰኔ 2020 ) በባህር ዳር ተፈጸመ በተባለ ኩዴታ ምክንያት የሰዎች ህይወት አልፏል፡፡ በብዙ የሀገሪቱ ክፍሎች ደግሞ የጎሳ ግጭቶች ተስፋፍተዋል፡፡ የታዋቂውን የኦሮምኛ ሙዚቃ አቀንቃኝ መገደል ተከትሎ በፖለቲካ ቅስቀሳ ምክንያት የበርካታ ንጹሃን ዜጎች ህይወት ተቀጥፏል፡፡ ንበረታቸው ወድሟል፡፡ በኮሮና ቫረስ በሽታ ወረርሽኝ ምክንያት ደግሞ እ.ኤ.አ. 2020 ላይ መደረግ የነበረበት የሀገሪቱ ብሔራዊ የምርጫ ውድድር ለ 2021 እንዲተላለፍ ተደርጓል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የትግራይ ክልል መስተዳድር የማእከላዊ መንግስትን ውሳኔ በመቃወም ክልላዊ የምርጫ ውድድር ማድረጉ ለፌዴራል መንግስቱ ደንቃራን ፈጥሮ ነበር፡፡ በሌላ አነጋገር በፌዴራል መንግስትና በትግራይ ክልላዊ መስተዳድር መሃከል የነበረውን አለመግባባት ወይም ፍጥጫ በሰላማዊ መንገድ መፍታት አልተቻለም፡፡ 

ሁላችንም አንደምናስታውሰው የአጼ ሀይለስላሴ መንግስት ከወደቀ በኋላ ስልጣኑን የጨበጠው በኮሎኔል መንግስቱ ይመራ የነበረው አምባገነኑ ኮሚንስት ወታደራዊ መንግስት ( ደርግ) ነበር፡፡ ይህ አገዛዝ ይደገፍ የነበረው በቀድሞዋ ሶቪዬት ህብረት ሲሆን እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር 1991 የምስራቁ ጎራ በመዳከሙ ምክንያት አምባገነን የበረውና በሰብዓዊ መብት ጥሰት የሚወቀሰው የደርግ አገዛዝ ከአስከፊ ጦርነት በኋላ በትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ስልጣኑን መልቀቅ ግድ ብሎታል፡፡ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ደግሞ በተራው ለ27 አመታት ኢትዮጵያን ገዝቷል፡፡ ከትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊትአውረሪዎች ደግሞ አንደኛው ተጠቃሽ እንደ ጎርጎሮሲያኑ አቆጣጠር ወደ ዚች ምድር የተቀላቀሉት ዶክተር ደብረጽዮን ገብረሚከኤል ናቸው፡፡ የቴሌኮሚንኬሽን ሚንስትር፣ የኢንተለጀንስ ሀላፊ፣ እና ከሟቹ ጠቅላይ ሚንስትር አቶ መለሰ ዜናዊ ስልጣን የሚለጥቀውን ምክትል የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚነስትር የጨበጡ ነበሩ፡፡ አቶ መለሰ አምባገነን የነበሩ ሰው ሲሆኑ የኢትዮጰያን ኢኮኖሚ ማሳደግ ሳይችሉ ሞት ቀድሟቸዋል፡፡

ይህን ተከትሎ ከጥቂት አመታት በኋላ የሕዝቡ ጸረ ኢህአዲግ ፍልሚያ በመጠናከሩ ምክንያት በኢህአዲግ ውስጠ ትግል መካሄድ ጀመረ ፣ በውጤቱም ኢህአዲግ አባል ድርጅቶች መሃከል የመሪ ምርጫ ተደርጎ ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዲግ ሊቀመንበር፣ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር እንዲሆኑ ከተሰየሙ በኋላ  የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት ስልጣን ( በማእከላዊ መንግስቱ የነበረውን የአንበሳውን የስልጣን ድርሻ ማለቴ ነው) እየተቦረቦረ መጣ፡፡ የዶክተር ደብረጽን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚንስትር የመሆን ህልም አከተመለተ፡፡ የተካሄደውን የጠቅላይ ሚነስትርነት አንቀበልም፣ ህጋዊ አይደለም በማለት እንደ ጎርጎሮሲያኑ መስከረም 2020 የድርጅታቸውን መቀመጫ መቀሌ አደረጉ፡፡ ይህ የመጀመሪያው አለመግባባት ነበር፡፡ ግን ለግዜው የፌዴራል መንግስት እና በትግራይ መስተዳድር መሃከል የመሳሪያ ግጭት አልተከሰተም   ነበር፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና በዶክተር ደብረጽዮን የበላይነት የሚመራው የትግራይ ሚልሻ ጦር ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጦር አንድ አካል በሆነው እና ትግራይ ክልል መሰረቱን ባደረገው  የሰሜን እዝ ላይ ባልታሰበ ጊዜ ጥቃት በማድረስ በርካታ የሰራዊቱን አባላት በመግደሉ ምክንያት በትግራይ የጦርነት ቋያ እንዲቀሰቀስ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሰላም ግዜ በብሔራዊ የጦር አባላት ላይ የተፈጸመው ግድያ ብዙዎች ኢትዮጵያውያንን ማስቆጣቱ ይታወቃል፡፡ እንደ ሰብዓዊ መብት አስጠባቂ ድርጅቶች የምርመራ ውጤት ከሆነ በትግራይ ሚሊሻዎች በማይካድራ ከ600 በላይ ንጹን ዜጎች ተገድለዋል፡፡ አንዳንድ የመብት አቀንቃኞች ይህን የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት አባላት የፈጸሙትን የንጽሁን ግድያ ‹‹ በቦስኒያሄርዞጉቢኒያ ከተፈጸመው የዘር ማጽዳት ጋር ያመሳስሉታል፡፡

. A massacre reminiscent of the so-called “ethnic cleansing” in Bosnia-Herzegovina.  

ምንም እንኳን የትግራይ የሚሊሻ ጦር ( አንድ የሚሊሻ ጦር ሊታጠቅ ከሚችለው በላይ ልክ እንደ አንድ መደበኛ የጦር ሀይል ወይም ልክ እንድ አንድ የሀገር መከላከያ ሀይል ዘመናዊ የጦር መሳሪያ የታጠቀ ጦር እንደነበር ልብ ይሏል፡፡) መላውን የትግራይ ክፍል ተቆጣጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ በትግራይ ክልል በተከፈተው ጦርነት ከተለያዩ ከተሞች የነበራቸውን ይዞታ እየለቀቁ መሸሽ ግድ ብሏቸዋል፡፡  በቅርቡ ማለትም ሚያዚያ 6 ቀን 2013 ዓ.ም.  የኢትዮጵያ ከፍተኛ የጦር አዛዦች በመገናኛ ብዙሃን ቀርበው እንደገለጹት ከሆነ የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ሚሊሻ ወታደሮች በትግራይ የተለያዩ በርሃማ እና ተራራማ አካባቢ መሽገውበት የነበረውን ስፍራዎች፣ ማለትም፣ የነበራቸውን ይዞታ በጦርነት ስለተሸነፉ ለቀው መሸሻቸው ተሰምቷል፡፡ ግራም ነፈሰ ቀኝ ባለፉት ወራቶች በተደረጉት ግጭቶች ወይም ጦርነት ምክንያት በርካታ የሰው ህይወት እንዳለፈ የታወቀ ጉዳይ ነው፡፡ ይህም ብቻ ጦርነት የእግርኳስ ጨዋታ ባለመሆኑ  ምክንያት፣ አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽሟል፡፡ ንጹሃን ኢትዮጵያዊ ዜጎች( ሲቪሎች ) አካላዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፣ንብረታቸው ወድሟል፡፡ እንዲሁም የመኖሪያ አከባቢያቸውን ለቀው መሄዳቸውን የሚያሳዩ መረጃዎች  ከተለያዩ የዜና አውታሮች ተሰምቷል፡፡ እንደ አለም አቀፍ የዜና አውታሮች ዘገባ ከሆነ ከ60,000 በላይ ኢትዮጵዊ ዜጎች ወደ ጎረቤት ሀገር በስደት እየኖሩ ይገኛሉ፡፡

በብዙ የፖለቲካ አዋቂዎች ተደጋግሞ እንደሚነገረው በዶክተር ደብረጽዮን የሚመራው የትግራይ ነጻአውጪ ድርጅት ማእከላዊ ኮሚቴ ( በበቀደሙት ወራቶች 11 የማእከላዊ ኮሚቴ አባላት ነበሩት፡፡) ለረጅም ግዜ በሽምቅ ተዋጊነት ለመቀጠል ያሰቡ ይመስላል፡፡ ይህ አደገኛ እቅዳቸው ደግሞ የሚመነጨው በሚከተሉት መሰረታዊ ምክንያቶች ነው፡፡

  1. በስልጣን ጥመኝነት ( በስልጣን ስካር)
  2. ሰይጣናዊ ባህሪ ( ለሰው ህይወት ደንታ ስለሌላቸው)
  3. ከፍተኛ ጭንቀት
  4. ለኢትዮጵያ አንድነት የሚደማ ልብ ስለሌላቸው
  5. እኔ ከሞትኩ…..በሚል ብሂል የታበዩ ስለሆኑ
  6. ከሌሎች መሰል ፍጹም አምባገነን ገዢዎች ውድቀት ለመማር መንፈሳዊ ወኔ የላቸውም
  7. የሰብዓዊ ስሜት ስለሌላቸው ወዘተ ወዘተ

በነገራችን ላይ ዶክተር ደብረጽዮንና የትግል አጋሮቻቸው የኢትዮጵያን ሉአላዊነት ደፍረዋል፡፡ የኢትዮጵያን ህልውና የሚጻረር ከባድ ወንጀል ስለመፈጸማቸው ከኢትዮጵያ መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ካወጡት መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ሆኖም ግን ይሁንና የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፖለቲካ ፊተአውራሪዎች ለፈጠሩት ችግር ሁነኛ መፍትሔው የፖለቲካ ውይይት ነው ብሎ ጸኃፊው ያምናል፡፡ በአሁኑ ዘመን እሾህን በእሾህ የሚለው ዘዴ ችግር ፈቺ ነው ብዬ አላምንም፡፡ የኢትዮጵያ መንግስት ከአሁን በኋላ ወደ ሰላማዊ መንገድ መፍትሔ፣ ወደ ሰለጠነ የፖለቲካ አፈታት መንገድ ቢጓዝ ለሀገሪቱ መረጋጋት ይበጃል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሌሎችም የአለም አቀፍ ድርጅቶች እና የአለሙ ህብረተሰብ በተለይም የአውሮፓ ህብረት እና የተባበረችው አሜሪካ እንደው ዝም ብለው በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የሚያደርጉትን ተገቢ ያልሆነ ጫና በመቀነስ፣ የትግራይ ነጻ አውጪ ድርጅት የፈጸመውን የጦር ወንጀል እና አስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰት በተመለከተ መረጃ በመሰብሰብ ውግዘት ማውርድ፣ ለፍርድ የሚቀርብበትን መንገድ መፈለግ፣ ለጥቆም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ውይይት እንዲደረግ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ሳስታውስ በታላቅ ትህትና ነው፡፡

ኢትዮጵያ በአስቸጋሪ የፖለቲካ አጣብቂኝ ውስጥ ብትገኝም፣ በፖለቲካ ተፎካካሪዎች መሃከል ስር የሰደደ ልዩነት ቢኖርም፣ በገዢው ፓርቲዎች ስብስብ  መሃከል ልዩነት አለ ቢባልም፡ አፍሪካ፣ የአፍሪካ አጋር የሆኑ በአለም ያሉ ሀገራት መረዳት ያለባቸው ቁምነገር ቢኖር ኢትዮጵያ የተረጋጋ፣ህጋዊ የሆነ፣ ብዙ ውጣውረዶችን ያለፈ ማእከላዊ አመራር ( መንግስት) በአዲስ አበባ መኖሩን ነው፡፡

There is – fortunately for Ethiopia, for Africa and for Africa’s friends in Europe and around the world – a stable, legitimate, successful political leadership in Addis Ababa, a leadership that has repeatedly reached out, even across deep divides.

እንደ መደምደሚያ

የኢትዮጵያ ታሪክ የጦርነት ታሪክ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በረዥም ዘመን የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ እጅግ ብዙ ጦርነቶች ተደርገዋል፡፡ በቅርብ ግዜ ታሪካችን ውስጥ ለመጥቀስ ያህል እብሪተኛው የዚያድ ባሬ ጦር የከፈተብን ጦርነት፣ ኢትዮጵያ ከገንጣይ አስገንጣዮች ጋር ያደረግችው የ30 አመታት ጦርነት፣ የወያኔ ኢህአዲግ አገዛዝ የስልጣን ኮርቻ ላይ ከተፈናጠጠ በኋላ ከኤርትራ አገዛዝ ጋር ያደረገው ጦርነት፣ ወዘተ ወዘተ የኢትዮጵያን አንጡራ ሀብት አፈርድሜ አስጋጠው እንጂ፣ ለኢትዮጵያ እርምጃ አልጠቀማትም፡፡ የዶክተር አቢይ መንግስት አሁን በያዝነው አመት ከትግራይ ነጻአውጪ ሚልሻ ጦር ጋር ያደረገው ጦርነትም፣ ቢሆን ውጤቱ አያምርም፡፡ ጦርነት ሰብዓዊ ቀውስ የሚያስከትል፣ ንብረት የሚያወድም ነው፡፡ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ማእከላዊ መንግስት ተገዶ በትግራይ ክልል ጦርነት ውስጥ ቢገባም፣ በመጨረሻም ተቀናቃኙን የትግራይ ነጻአውጪ ጦር በብዙ ግንባሮች ላይ ድል ነስቻለሁ በማለት በመገናኛ ብዙሃን ለኢትዮጵያ ህዝብ ቢያሳውቅም መጨረሻው አያምርም፡፡ ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ ክልልም ሆነ በሌሎች አካባቢዎች ብረት አንስተው ከሚፋለሙ ሀይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ከመግባት ወደ ሰላማዊ ድርድር፣ ወደ ጠረቤዛ ዙሪያ ውይይት ቢገባ ዘላቂ ሰላማዊ መፍትሔ ማምጣት ይቻላል የሚለው የግል አስተያየቴ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ልጆቿን መዘንጋት የለባትም፡፡ በትግራይ የተከሰተው ሰብዓዊ ቀውስ የኢትዮጵያውያን ሁሉ ጉዳይ ነው፡፡

 

 

 

Filed in: Amharic