>

ፓይለቱ፤ ሀኪሙና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር አሥራት ወ/የስ ከተማሪነት እስከ ታጋይነት...!!!  (ጋሻው መርሻ ) 

ፓይለቱ፤ ሀኪሙና ፖለቲከኛው ፕሮፌሰር አሥራት ወ/የስ ከተማሪነት እስከ ታጋይነት…!!! 

ጋሻው መርሻ – 

 “አንፀባራቂ ኮኮብ!”


አስራት ወልደዬስ ከአባታቸው ከአቶ ወልደዬስ አልታዬና ከእናታቸው ከወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌ ሰኔ 12 ቀን 1920 ዓ.ም በአዲስ አበባ ከተማ ተወለዱ፡፡ የአስራት አባት አቶ ወልደዬስ አልታዬ በጸሓፊ ትዕዛዝ ኃይሌ ወልደ-ስላሴ አስተዳደር ውስጥ በጸሃፊነትና በአስተዳደር ተግባር የተሰማሩ ነበሩ፡፡ እናታቸውም በአነስተኛ ንግድ የተሰማሩ ነበሩ፡፡ ፕሮፌሰር አሥራት የሶስት ዓመት ህጻን እያሉ ወላጆቻቸው በፍች ምክንያት ስለተለያዩ ከእናታቸው ጋር ወደ ድሬዳዋ አቀኑ፡፡ አስራት ድሬዳዋ በነበሩበት ወቅት ጣሊያን ኢትዮጵያን ትወራለች፡፡ በዚህ ወቅት በእነ ሞገስ አስግዶምና አብርሃም ደቦጭ ግራዚያኒ ላይ የተደረገ የግድያ ሙከራን ለመበቀል ከግራዚያኒ በተላለፈ በቀል በሶስት ቀናት ውስጥ ብቻ ከ33 ሺህ በላይ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች በዶማ፤ በአካፋና በገጀራ ተጨፍጭፈው ተገደሉ፡፡ የአስራት አባት አቶ ወልደዬስ አልታዬም እንደ ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ሁሉ ተጨፍጭፈው በአርበኝነት ሞቱ፡፡ እናቱ ወይዘሮ በሰልፍይዋሉ ጽጌም የባለቤታቸው ሞት ተጨምሮበት ብዙም ሳይቆዩ ታመው በሞት ተለዩ፡፡
ወላጆቹን በሞት የተነጠቀው ታዳጊ ከአያቱ ከወይዘሮ ባንቺወሰን ይፍሩ-ለሱሲሉ ጋር መኖር ጀመረ፡፡ አጎቱ አቶ ዘውዴ ወረደወርቅ እዚያው ድሬዳዋ ይኖሩ ነበርና ታዳጊውን የቄስ ትምህርት እንዲማር አስገቡት፡፡ የቄስ ትምህርት ቤት በነበረበት ወቅት በቀለም አቀባበሉ ጎበዝ ነበር ይላሉ አስተማሪው አለቃ ለማ፡፡ ምስክርነታቸውን ሲሰጡ ‹‹አስራት በልጅነት በጣም ጎበዝ በመሆኑ ዓመት ሳይሞላው ወንጌሉን ከቁጥሩ አንበልብሎ፤ ከፍካሬ እስከ ነቢያት ደግሞ ድቁና ተቀበለ›› ይላሉ፡፡ ከቄስ ትምህርቱ ጎን ለጎን ድሬዳዋ ይገኝ ከነበረው ፈረንሳይ ሚሲዮን ገብቶ ቀለም መቁጠር ጀመሮም ነበር፡፡ የእናቱ አባት ቀኛዝማች ጽጌ ወረደወርቅ ታዋቂ አርበኛ ነበሩ፡፡ በመሆኑም ጣሊያን አርበኞችን ወደ ጣሊያን ሐገር ወስዶ በሚያስርበት ወቅት ቀኛዝማች ጽጌም አንዱ ታሳሪ ነበሩ፡፡ ቀኛዝማች ጽጌ ከሶስት ዓመት ተኩል እስር በኋላ ሐገራችን ነጻ ወጥታ ወደ ኢትዮጵያ ሲመለሱ አስራትን አዲስ አበባ አስመጥተው በ1934 ዓ.ም ተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት አስገቡት፡፡ ትምህርት ቤት በገባ በአመቱ በ1935 ዓ.ም በተፈሪ መኮንን ትምህርት ቤት ከአጠቃላይ ተማሪዎች አንደኛ በመውጣት የካሜራ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል፡፡ በወቅቱ የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ ወጣቶች መካከል ላቅ ያለ ውጤት ያስመዘገቡትን ወደ ውጭ ሐገር ልኮ ማስተማር ተጀምሮ ነበርና አስራትም በዚሁ የትምህርት ዕድል ምክንያት ግብጽ ወደሚገኘው የእንግሊዞች ቪክቶሪያ ኮሌጅ ተላከ፡፡ በቪክቶሪያ ኮሌጅ ለአምስት ዓመታት ትምህርቱን ከተከታተለ በኋላ በስኮላሽፕ ለከፍተኛ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሐገር እስኮትላንድ ኤደንብራ ዩንቨርስቲ አቀና፡፡ በወቅቱ ህግ እንዲያጠና ከትምህርት ሚንስቴር ቢነገረውም አሻፈረኝ ብሎ ህክምና ኮሌጁን ተቀላቀለ፡፡
ትምህርቱን እንደጨረሰም ፈጥኖ ወደ ሐገሩ ተመለሰ፡፡ በወቅቱ የጤና ጥበቃ ሚንስተር የነበሩት አውቁ አርበኛ ደጃዝማች ጸሐይ እንቁስላሴ አስጠርተው የጤና ሚንስትርነቱን ቦታ እንዲይዝ ይጠይቁታል፡፡ ዶክተር አስራት ግን አይሆንም ሲል ተቃወመ፡፡ በዚሁም የተነሳ የልዕልት ጸሃይ ሆስፒታልን ተቀላቀለ፡፡ ለአምስት ዓመታት በልዕልት ጸሐይ ሆስፒታል ካገለገለ በኋላ ለተጨማሪ ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሐገር አቀና፡፡ አደንብራ ዩንቨርሲቲ ገብቶ ቀዶ ህክምናን አጠና፡፡ በቀዶ ህክምና ዘርፍ አስራት የመጀመሪያው ኢትየጵያዊ ሐኪም ነው፡፡ ከዚህ በኋላ አስራት በእድሜም በማዕረግም እያደገ ስለሆነ አንቱ አያልን አንናገራለን፡፡ እነ ዶክተር አስራት እስኪተኩት ድረስ የሀገራችን የህክምና ዘርፍ በነጮች የተያዘ ነበር፡፡ ዶክተር አስራት ከጓደኞቻቸው ጋር በመሆን የህክምና ማሰልጠኛ እንዲከፈት በመወትወታቸው ምክንያት የጥቁር አንበሳን ሆሰፒታል እውን አደረጉ፡፡ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲቋቋም የቴክኒክ ኮሚቴውን የመሩት ዶክተር አስራት ነበሩ፡፡ እ.ኤ.አ በ1965 ዓ.ም የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እውን ሲሆን ፕሮፌሰር አስራት ተባባሪ ፕሮፌሰር በመሆን የመጀመሪያ ኢትዮጵያዊ ዲን ሆኑ፡፡ በደርግ ወቅትም በካድሬዎች ይደረግባቸው የነበረውን ከፍተኛ ጫና ተቋቁመው ሐገራቸውን ሳይለቁ ህዝባቸውን ሲያገለግሉ ቆይተዋል፡፡ በወቅቱ በተደጋጋሚ ዘመቻ የተላኩ ሲሆን የሄዱበትን ዘመቻ በክብር ለመወጣት በቅተዋል፡፡ በዚህም መሰረት በ1968 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1969 ዓ.ም እንደገና በቃኘው ሆስፒታል አስመራ፤ በ1970 ዓ.ም በራዛ ዘመቻ በቀዳጅ ሐኪምነት እና ቡድን መሪነት በመቀሌ ሆስፒታል፤ እንዲሁም በሰኔ 1971 ዓ.ም በቀዳጅ ሐኪምነት ምጽዋ ዘምተው ግዳጃቸውን ተወጥተዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በህክምናው ዘርፍ ‹‹አስራት የተባለ ጸበል ፈልቋል›› እስከመባል የደረሰ አንቱታን ያተረፉ ብቁ ሐኪም ነበሩ፡፡ ኢህአዴግ ከሌሎች 42 ምሁራን ጋር ከአዲስ አበባ ዩንቨርስቲ በ1985 ዓ.ም እስከሚያባርራቸው ድረስ በትጋት ያገለገሉ የሐገር ባለውለታ ነበሩ፡፡ በሙያቸው የተለያዩ ሽልማቶችን ያገኙ ሲሆን ጥቂቶቹን ለመዘርዘር ያክል የኢትዮጵያ የክብር ኮከብ የፈረሰኛ ደረጃ፤ የዳግማዊ ምኒልክ ኒሻን የፈረሰኛ ደረጃ፤ የአብዮታዊ ዘመቻ አርማ ፤ አለም አቀፍ የወርቅ ሜርኩሪ (በግል አስተዋጽኦ)፤ የቀይ ባህር ኒሻን አንደኛ ደረጃ ይገኙበታል፡፡
የደርግ ስርዓት ተሸንፎ ኢህአዴግና ሻዕቢያ ስልጣኑን በተቆጣጠሩበት ወቅት ሰኔ 24 ቀን 1983 ዓ.ም በተደረገው የሽግግር መንግስት ቻርተር ውይይት ላይ የከፍተኛ ትምህርት ተቋማትን ወክለው የተገኙት ፕሮፌሰር አስራት ‹‹ሐገር ላስገነጥል ተወክዬ አልመጣሁም›› በማለት ተቃውሞ ያሰሙ ብቸኛው ሰው ነበሩ፡፡ ‹‹ይህ ጉባኤ በኢትዮጵያ ህዝብ ስም ምንም ጉዳይ ሊወስን፤ ሊያግድ ወይም ሊሰርዝ አይችልም›› በማለት ጉባኤው እያደረገው ያለው ውሳኔ ኢ-ዲሞክራሲያዊ መሆኑን አስረግጠው ሞገቱ፡፡ በዚህ ንግግራቸውም የተነሳ ከጉባኤው ሲወጡ ብዙ ማስፈራሪያና ዛቻ ያካሂዱባቸው ነበር፡፡
በወቅቱ በኮንፈረንሱም ሆነ በሽግግር መንግስቱ ምንም ውክልና ያልነበረው የአማራ ህዝብ በየአካባቢው ግፍና መከራን ማስተናገድ ጀመረ፡፡ ይህ ሁኔታ ያሳሰባቸው ምሁራን በመነጋገር የመላው አማራ ህዝብ ድርጅትን ታህሳስ 2 ቀን 1984 ዓ.ም መሰረቱ፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርም ፕሮፌሰር አስራት ሆነው ተመረጡ፡፡ ፕሮፌሰር አስራት የተጣለባቸውን አደራ ለመወጣት በሐገር ውስጥና ከሐገር ውጭ ድርጅታቸውን ማስተዋወቅና የተቃጣውን የዘር ፍጅት ለመመከት ጥረት አደረጉ፡፡ ከሐገር ውጭ ጉዞ በማድረግ በስዊድን፤ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ፤በሎሳንጀለስና ኒዮርክ በመዟዟር የድጋፍ ቻፕተሮችን አቋቋሙ፡፡ በሐገር ውስጥ በነበረው የህዝብ ጥያቄ መሰረት በደብረ ብርሃን ዘርያዕቆብ አደባባይ ታህሳስ 11 ቀን 1985 ዓ.ም በተካሄደው ህዝባዊ ስብሰባ ታሪካዊ ንግግር አደረጉ፡፡ የድርጅታቸው በአጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነት ማግኘት እረፍት የነሳው የሽግግር መንግስት ፕሮፌሰሩን ‹‹ጦርነት ቀስቃሽ ንግግር›› አድርገዋል ሲል ከሰሳቸው፡፡ የዚህን ንግግር ጦርነት ቀስቃሽ መባል የሰማ የአካባቢው ህዝብም  ‹‹እስካሁን አማርኛ እናውቃለን ስንል ኖረናል፡፡ አሁን ግን በሽግግር መንግስቱ በአዲስ መልክ መማር ሊገባን ነው›› ሲል ምጸቱን ገልጾ ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ ተጠርተው በ50 ሺህ ብር ዋስና ከአገር
እንዳይወጡ እገዳ ተጥሎባቸው ተለቀቁ፡፡ በዚያው ዓመት ከጎጃም ከመጡ አርሶ አደሮች ጋር አሲረዋል በሚል ‹‹ለጥያቄ ይፈለጋሉ›› ተብለው ሐምሌ 5 ቀን 1985 ዓ.ም ተጠርተው ለ24 ሰዓታት ከታሰሩ በኋላ በ20 ሺህ ብር ዋስትና ተለቀቁ፡፡ ከዚያ በኋላ ሐምሌ 12 በነበረው ተለዋጭ ቀጠሮ ዋስተናቸው ተነስቶ ለ43 ቀናት ከታሰሩ በኋላ ነሐሴ 24 ቀን 1985 ዓ.ም ሊፈቱ ችለዋል፡፡ በወቅቱ በተደጋጋሚ እየተጠሩ ዋስትና ከመጠየቃቸው የተነሳ ‹‹የዋሶች ባንክ ማደራጀት ሳይኖርብኝ አይቀርም›› ሲሉ ምሬታቸውን ገልጸው ነበር፡፡
ከተደጋጋሚና አሰልች የፍርድ ቤት ምልልስ በኋላ ሰኔ 20 ቀን 1986 ዓ.ም የዋለው ችሎት ከጎጃም ገበሬዎች ጋር አስረዋል በሚለው ክስ የሁለት ዓመት እስር ተፈረደባቸው፡፡ ሐገራቸውን በታማኝነት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያገለገሉ ሽማግሌ በጡረታ እድሜያቸው ከርቸሌ ወረዱ፡፡ በወቅቱ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፕሮፌሰሩን ‹‹የህሊና እስረኛ›› ሲላቸው የፍርድ ሒደቱንም ‹‹መረጃ አልባ›› ሲል አጣጥሎታል፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ በእንጥልጥል የቆየው ደብረ ብርሃ ንግግር ክስ ተቀስቅሶ በሳምንት እስከ ሶስትና ሁለት ጊዜ ፍርድ ቤት እየተመላለሱ የሰላቻቸው ፕሮፌሰር አስራት ‹‹የምታውቁትን ውሳኔ የዛሬ 6 ወይም 9 ወር ከምትሰጡኝ ዛሬውኑ አሳውቁኝና እስር ቤት ቁጭ ብዬ መጽሐፍ ላንብብ›› ሲሉ ለችሎቱ በምሬት ተናግረው ነበር፡፡ ታህሳስ 18 ቀን 1987 ዓ.ም በዋለው ችሎት ፕሮፌሰሩን የ3 አመት አስር በየነባቸው፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ፕሮፌሰር አስራት ከ150 ጊዜ በላይ ፍርድ ቤት ተመላልሰዋል፡፡ ከርቸሌ ታስረው በነበረበት ወቅት ከፖለቲካ እስረኞች ተለይተው ከፍታብሔር እስረኞች ጋር እንዲቆዩ የተደረገ ሲሆን መጽሃፍትና ጠያቂም በፈለጉት መጠን አያገኙም ነበር፡፡
የእስር አያያዛቸው የከፋ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በ1972 ዓ.ም የጀመራቸው የልብ ሕመም ተባብሶ እንዲሁም የስኳር መጠናቸው በመጨመሩ ከፍተኛ የጤና ችግር ላይ ወደቁ፡፡ ለብዙ በሽተኞች መድኀኒት የነበሩት አስራት ህክምና ተከልክለው የበሽታ መጫዎቻ ሆኑ፡፡ ከስኳራቸው ከፍ ማለት ጋር ተያያዞ አይናቸው ማዬት አልቻለም፡፡ ሰውነታቸውም እንደፈለጉ ሊታዘዛቸው አልቻለም፡፡ የልብ ድካማቸው ጨምሯል፡፡ ሕክምና እንዲያገኙ ለጠቅላይ ሚንስትሩ ሳይቀር ደብዳቤ ጻፉ፡፡ መፍትሄ ግን አላገኙም፡፡ የኋላ ኋላ ሲዳከሙ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቢወሰዱም ህመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ በመሆኑ መፍትሄ ሊያገኙ አልቻሉም፡፡ በመጨረሻም እ.ኤአ ታህሳስ 27 ቀን 1998 ዓ.ም ወደ ውጭ ሐገር ሄደው እንዲታከሙ ተፈቀደ፡፡ በከፍተኛ ሁኔታ በመድከማቸው አውሮፕላን ውስጥ በሐኪሞች እየታገዙ ወደ ለንደን ሆስፒታል በረሩ፡፡ ከ3 ቀናት ቆይታ በኋላ ወደ አሜሪካ ሆስተን አመሩ፡፡ በአሜሪካ ቅዱስ ሉቃስ ኤጲስቆጳል ሆስፒታል በነበሩበት ወቅት እንደተሻላቸውና ከልቡ ሲያስባቸው ለነበረው ህዝብ መልዕክት አስተላልፈው ነበር፡፡ ትንሽ እንደተሻላቸው ዘመዶቻቸው ወደሚገኙበት ፊላደልፊያ ከወር በፊት ተዛውረው በነበረበት ወቅት ባልታወቀ ምክንያት ህመማቸው ተባብሶ ተዳከሙ፡፡ ሞትን ድል ሲያደርጉት የኖሩት ሐኪም ግንቦት 6 ቀን 1991 ዓ.ም ፊላደልፊያ በሚገኘው ፔኒሲለቫኒያ ዩንቨርሲቲ ሆስፒታል በህክምና ሲረዱ ቆይተው በዕለተ አርብ በተወለዱ በ71 ዓመታቸው አረፉ፡፡ በወቅቱ የፕሮፌሰሩን ሞት ትልልቅ የአለም መገናኛ አውታሮች ሰፊ ሽፋን ሰጥተው ነበር፡፡
የፕሮፌሰሩ አስከሬን ታላላቅ እግንዶች፤ ቤተሰቦቻቸውና አድናቂቆቻቸው በተገኙበት ግንቦት 15 ቀን አሸኛኘት ተደርጎለት ከዋሽንግተን ዲሲ ጉዞ ጀመረ፡፡ ግንቦት 15 የተነሳው የፕሮፌሰሩ አስከሬን ሮም አርፎ ግንቦት 17 ቀን 1991 ዓ.ም ከቀኑ 11፡30 ሲሆን ቦሌ አለም አቀፍ አየር ማረፊያ ደረሰ፡፡ በስፍራው ሲጠባበቅ የነበረው ህዝብ አስከሬኑን በከፍተኛ አጀብ ለገሐር ወደሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው አደረሰው፡፡ ግንቦት 17 ቀን ሌሊቱን ጸሎተ ፍትኃት ሲደረግ አድሮ በማግስቱ አስከሬናቸው በመሰረቱትና በኋላም በሞቱለት ድርጅታቸው (መአህድ) ጽ/ቤት ጥቂት ቆይታ ካደረገ በኋላ ወደ ስላሴ ካቴድራል አመራ፡፡ በስላሴ ካቴድራል ፍትሃትና ጸሎት ከተደረገላቸው በኋላ ስላሴ እንዳይቀበሩ መንግስት በመከልከሉ ምክንያት በባለወልድ ቤተክርስቲያን እንዲያርፉ ተደረገ፡፡ ይኸው ላለፉት 18 ዓመታት በባለወልድ የቆየው አጽማቸው ዛሬ ወደሚገባው ቦታ ስላሴ ካቴድራል ሊዛወር ችሏል፡፡ ፕሮፌሰር አስራት ወልደዬስ የሁለት ወንዶች ልጆች አባትም ነበሩ፡፡
Filed in: Amharic