የእንጦርጦስ ካፒታሊዝም – ከደጃችን ቆሞ እያንኳኳ ይሆን?
አሰፋ ሀይሉ
«አንድዬ …በራችን ላይ ቆሞ ለሚያንኳኳው ክፉ ዲዛስተር-ካፒታሊዝም በራችንን ከሚበረግድ የራሳችን ወገን ይጠብቀን። ከችግር የምንወጣበትን ሀገራዊ ልቦና፣ እርጋታና ጥበብን አብዝቶ ይስጠን።» — ከጽሑፉ የተወሰደ
“ዲዛስተር ካፒታሊዝም” ብላዋለች ስሙን። “የመቀመቅ ካፒታሊዝም” እንደማለት። የለንደኗ የኢኮኖሚ ተንታኝ፣ በኢራቅ የጦርነት ወቅት ዘጋቢ ጋዜጠኛ እና በ28 ቋንቋዎች ይህ መፅሐፏ የተተረጎመላት ናኦሚ ክሌይን። ልጂቱ ቀልድ አታውቅም። ሃሳቧ ከነደፈህ እልም ጭልጥ ነው። ወለም ዘለም የለም። ለሁሉም እንደየሥራው እቅጭ እቅጩን ነው። “አካፋን አካፋ፣ ዶማን ዶማ”። ነገር አበቃ። በ29ኛ የትርጉም ቋንቋው በአማርኛ እኔም ደግሞ የእርሷን “የመቀመቅ ካፒታሊዝም” ስሙን አሻሽዬ “የእንጦርጦስ ካፒታሊዝም” ብዬ በጥቂቱ ዋነኛ ነጥቧን እገልፀዋለሁ።
ደራሲዋ – ናኦሚ ክሌይን – የምትነግረን እውነት ይህ ነው፦ ታላቅ አደጋ ባለበት ሥፍራ ሁሉ – አንድ ታላቅ ያደፈጠ የካፒታሊዝም ቆሪጥም አለ። ጥርሱን በመንግስት ላይ እያፋጨ (አሊያም እያፏጨ)። አደጋው የተፈጥሮ ጎርፍ፣ ሰው ሠራሽ ጦርነትና መፈናቀል፣ አሊያም የዜጎች አመፅና የህዝባዊ ተቃውሞ ግርግር፣ የመንግስት ለውጥ፣ ወይም የአንድ ሀገር በታላቅ የዕዳ አዘቅት ውስጥ ተዘፍቆ መገኘት ሊሆን ይችላል።
ይሄ ዓይነቱ ካፒታሊዝም ምሱ መቀመቅ ነው። መቀመቅ የገቡትን ሁሉ እያነፈነፈ ባሉበት ቀድሞ ይገኛል። ግን በቅድሚያ መቀመቅ። ሰፊና ጥልቅ የሆነ፣ ብዙ ህዝብን የችግር (እና የድረሱልኝ) ማጥ ውስጥ የከተተ፣ ዜጎችን በፍርሃት እንዲሸበቡ ያደረገ ማናቸውም ሀገራዊ ጥቃት፣ የከፋ አደጋ፣ ህዝባዊ አብዮት፣ ከፍ ያለ ትርምስ፣ አሊያም አብዮተኛ መፈንቅለ-መንግስት፣ ወዘተ. ወዘተ.።
እነዚህ መቀመቆች ካሉለት – ትላለች ናኦሚ – እነዚህን ካገኘ – “ዲዛስተር ካፒታሊዝም” አጓጊ ተስፋውን (ከረብጣ ብድር ጋር!) በታላቅ አቁማዳ ተሸክሞ የሀገርን፣ የክልልን፣ የተቋምን፣ የመንግስትን በር ጫን አድርጎ ያንኳኳል። ከተጨነቀው መሐል አንድ የሚከፍትለት አያጣምና።
/እኔ ይህን ባህርዩን ሳስበው “መለመላውን አግጦ አፍጦ በችግር ቤት በር ላይ የቆመው ካፒታሊዝም – በቃ የኢኮኖሚ ሞዴል ከመሆን አልፎ – በቃ አንዳች “ኦፖርቹኒስቲክ ዲዚዝ” (የሰውነትህ ተፈጥሯዊ በሽታን የመከላከል አቅም ሲዳከም ቀን ጠብቆ የሚመጣብህ የሆነ የ’አ.ተ.ት.’ – «አጣዳፊ ተቅማጥና ትውከት» – ዓይነት!) መስሎ ይታየኝ ጀምሯል።
እንዴ?! እኔ ብቻ’ኮ አልምሰልህ እንዲህ ይታየኝ የጀመርኩት። ይሄን መፅሐፏን ያደነቀው እና ቀደም ሲል በፃፈችው “ኖ ሎጎ – ቴኪንግ ኤይም አት ብራንድ ቡሊስ” በተሰኘ ዓለማቀፍ ተነባቢ መፅሐፏ የተማረከ የፑሊትዘር ተሸላሚ ጋዜጠኛ የመሰከረለትን ልጥቀስ ቆይ። እንዲህ ነው የሚለው፦ “Naomi Klein has once again written a book that changes the way we see the world.”።
ይሄ የእንጦርጦስ ካፒታሊዝም መገለጫው ምንድነው? ብሎ ለሚጠይቅ አንዱ መገለጫው ከላይ እንደጠቀስኩት ሀገራዊ መቀመቅን ተከትሎ የሚመጣ መሆኑ ነው። ይሄ ዓይነቱ ካፒታሊዝም ሁለተኛ መገለጫው ደግሞ መቀመቅ መክተትን ወይም ማብዛትን ዓላማውን ለማራመድ እንደ ዓይነተኛ ስልት የሚጠቀም መሆኑ ነው። “ዘ ሾክ ዶክትሪን” የተባለውም ስልቱ ለዚያ ነው። ዒላማውን የሚመታው በቅድሚያ ሰለባዎቹን በተደራራቢ አስደንጋጭ የችግር ማዕበሎችና ሀገራዊ ድንጋጤዎች ውስጥ በመክተት ስለሆነ።
ሶስተኛው መገለጫ ባህሪው፦ የካፒታሊዝም የገበያ መዘውር የመንግስት ጣልቃ-ገብ እጅ ከገባበት እጅ-እጅ ብሎ ይቀራል ብሎ በግልና በግል ተዋንያን ብቻ የተያዘ ሀገራዊ ኢኮኖሚን የሚቀበል “የገበያ ፍፅምናን” (የነጋዴን እንከን የለሽነት) አምልኮቱ ነው።
ናኦሚ ስለዚህ ስለ ሶስተኛው የመቀመቅ ካፒታሊዝም ባህርይ ስታስረዳ – መሸጥ እስከቻለ ድረስ ልክ ሀገራዊ መቀመቅ ከተከሰተ በኋላ ያን ሰበብ በማድረግ ሁሉንም ነገር ለግለሰብ ነጋዴዎች እንደያቅማቸው ይቸረችረዋል፦ የመንግስት ት/ቤቶችን ለግል፣ የመንግስት ሆስፒታሎችን ለግል፣ የመንግስት ዩኒቨርስቲዎችንና የጥናት ማዕከሎችን ለግል፣ የመንግስት ቴሌኮምን ለግል፣ የመንግስት ኤሌክትሪሲቲን ለግል፣ መንገድን፣ ውሃን፣ መብራትን፣ መድሀኒትን፣ ጨርቅና አልባሳትን፣ ምግብን፣ መድኀኒትን (“ፋርማሴዩቲካልስ”ን) – ለትርፍ ወደሚሰሩ የግለሰብ ነጋዴዎች ይሸጣቸዋል።
ሌላ ቀርቶ የአረጋውያንን መጦሪያ፣ የመከላከያን የግንባታና ሶፍትዌር ፕሮጀክቶች፣ የየከተማውን ህዝብ የእግር ኳስ ቡድኖች፣ ጋዜጣና ህትመቱን፣ የኮንግረስ አባላቱን፣ ቤተ-እምነቶችን፣ ሎቢስቶችንና ሲንዲኬቶችን ሳይቀር – ሁሉንም ታላቅ የገደል አፋፍ ላይ ሆነው ለመውደቅ ሲፍገመገሙ (ወይም የመውደቅ ፍርሀት ሲያይልባቸው) – ባለቤትነታቸውን ለትርፍ ወደሚሰሩ የግለሰብ ነጋዴዎች ይሸጣቸዋል፣ ያዘዋውራቸዋል።
እና በመጨረሻም – መንግስትን ራሱ ፕራይቬታይዝ ያደርገውና ወደ ግል ይዞታነት ያዛውረዋል (“ፕራይቬታይዝድ ጋቨርመንት”) – ሀገር የነጋዴዎች ትሆናለች። ይህ ማለት በስተመጨረሻ መንግስት የሚባለው ተቋም የሚሰማውና የሚታዘዘው ለብዙሀኑ ዜጎች ጩኸት ሳይሆን – ለፈርጣማ ባለሀብቶችና ለወፋፍራም ለጋሽ ተቋማትና ሀገሮች ቀጭን ትዕዛዝ ይሆናል – እንደማለት ነው።
ችግሩ ግን የሚፈጠረው የንግዱ ዓለም ሁሉም ነግዶ የሚያተርፍበት ዓለም ያለመሆኑ እኮ ነው ባይ ናት ደራሲዋ፦ ጥቂቶች በወፋፍራሙ ይበለፅጋሉ። ጥቂቶች ደግሞ በመቀመቁ ጎርፍ ይወሰዳሉ። እነዚህ ለመሰንበት አቅሙን ያላደላቸው ተሰናባቾች ናቸው። ብዙሀኑ ሕዝብ ደግሞ – የሸቀጦችና አገልግሎቶች ተቀባይና ማራገፊያ ሆኖ – ትርፍ-የለሽ – ነፃ-የለሽ – አቅመ-ቢስ ማኅበረ-ሰብዕ ይሆናልና።
በነገራችን ላይ አሁን በዓለማችን ላይ እየተንሰራፋ ላለው ለዚህ የእንጦርጦስ ካፒታሊዝም ዋነኛ የአይዲዎሎጂ መሠረቶች የሆኑትን “የንፁህ ሌዜ-ፌይር አሰርቱ ትዕዛዛት”ን ቀምሮ የፃፈውና በላቲን አሜሪካ በ70ዎቹ በኦጉስቶ ፒኖሼ ትመራ በነበረችው ቺሊ በተግባር የኢኮኖሚ ኤክስፐርመንቱን ሞክሮ ያረጋገጠው፣ በ94 ዓመቱ ገደማ ከሃሪኬን ካትሪና ትንሽ ቆየት ብሎ የሞተው፣ ታላቁ የኖቤል ሽልማት አሸናፊ የኢኮኖሚ ቀማሪና የቺካጎ ዩኒቨርሲቲ እጅግ የተከበረ የኢኮኖሚክስ ዶ/ርና ፕሮፌሰር ሚልተን ፍሬድማን ነው።
በተለይ ከሰውየው ስራዎች መሐል ልክ ሙሴ ከፈጣሪ እንደተቀበለው “የትዕዛዛቱ ድንጋይ” ተደርጎ በኢኮኖሚ ፍልስፍናና ስልቱ ተከታዮች የሚጠቀስለት በ1962 (እ.ኤ.አ.) ያሳተመው (እና በ1982 ድጋሚ በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ ፕሬስ የታተመለት) “ካፒታሊዝም ኤንድ ፍሪደም” የተሰኘ መፅሐፉ ነው።
ትናንት ባሳለፍነው የታሪክ ምዕራፍ እና ዛሬም ላይ ፕ/ር ሚልተን ፍሬድማን በቺካጎ ያስተማራቸው (በአስተምህሮቱ ያጠመቃቸው) ታላላቅ ኢኮኖሚስቶች የመንግስታት መሪዎችና አማካሪዎች ሆነዋል። የአይ ኤም ኤፍ እና የዎርልድ ባንክ ዋነኛ ባለስልጣናት ሆነዋል። የየሀገሩ ዩኒቨርሲቲዎች አንቱ የተሰኙ መምህራንና የሚደመጡ ሰዎች ሆነዋል።
ጊዜና ቦታ ገድቦኝ እንጂ ናኦሚ ክሌይን በመፅሐፏ …ከዘመነ ሬገን እስከ ሴፕቴምበር ኢለቨን ማግስት፣ ከካትሪና ጎርፍ ማግስት እስከ ኢራናዊ መፈንቅለ መንግስት፣ “ዶ/ር ሾክ” እየተባለ ከሚጠራው የሳይካትሪ ሳይንቲስት አስከታወቁ የኢኮኖሚና ማኅበራዊ ሳይንቲስቶች፣ የሩሲያን ሶሻሊስቶች በተቀመጡበት ፓርላማ በታንክ ከደረማመሱት ቦሪስ የልሲን እስከ ሰዳም ሁሴንና የኢራቁ ዘመቻ ማግስት የእንጦርጦስ ካፒታሊዝምን ዓይነተኛ ባህርያትና አውሬያዊ አይምሬ ጦሶች እያስጣጣች ታሳየናለች፡፡
ከቺሊ እስከ ቻይና፣ ከፈረንሳይ እስከ ኡራጓይ፣ ድሮም ሆነ አሁን በተለይ የላቲን፣ የአፍሪካና የኤዥያ (በተለይ በቋፍ ባለ ኢኮኖሚ ላይ ህልውናቸውን የመሠረቱ ሀገሮች እና ህዝቦቻቸው!) በላያቸው የተጋረጠባቸውን መቀመቃዊ የእንጦርጦስ ካፒታሊዝም ከታሪክና ከተጨባጭ ማስረጃዎች ጋር እያዛነቀች ለሁሉም መሸጫ መሸጫውን እያነሳሳች ስትፅፍ ያነበበ ሁሉ ጉድ! ማለቱ፣ አሊያም ከጉድ እንዴት እንውጣ? – ወዴትስ እየሄድን ነው? – ብሎ ራሱን መጠየቅ አይቀርለትም።
ናኦሚ ክሌይን ደግሞ እንደዚህ ትላለች፦
«ከሰባዎቹ አጋማሽ ጀምሮ የዓለምን ሁኔታ እንመርምር፤ ድሮ ድሮ በአፍሪካና በመላው ዓለም ያዩትን ጥሬሀብትና ጉልበት በላቀ ዘዴና ጭካኔ በተሞላ ኃይል ተጠቅመው ለመመዝበር ከአውሮፓውያኑ መንግስቶቻቸው ቀድመው ኮሎኒያሊዝምን የጀመሩት ካፒታልንና የንግድ ትርፍን እጅግ የተጠሙ ዓለምአቀፍ ርቀቶችን ያህል ቆርጠው የሚጓጓዙ የግል ‘መልታይናሽናል’ ካምፓኒዎች ነበሩ። ዘመኑ ቢቀየርም፣ ኮሎኒያሊዝም ቢቀርም፣ አሁንም ግን (በዘመነ ግሎባላይዝድ ኒዮኮሎኒያሊዝም) መቀመቃዊ የእንጦርጦስ ካፒታሊዝምን ይዘው ድንበር ሳይገድባቸው ብሔራዊ አደጋና በገንዘብ ድርቅ የተመታ ሀገር ባዩበት የዓለም ጥግ ሁሉ የኢኮኖሚ ክንፎቻቸውን ዘርግተው እየበረሩ ይመጣሉ፡፡
«ሁሉንም ህዝብና ሀገር ያፈራውን አንጡረ ሀብት ሁሉ – መንግስትን ሳይቀር – እጃቸውን ጠምዝዘው በገንዘብ በመግዛት (ፕራይቬታይዝ በማድረግ) – ትርፍ ለማግኘት፣ ነጭ ካፒታሊዝምን ለማስፈን በቀጥታም ሆነ በእጅአዙር እየተጣጣሩ ያሉት እነዚያው ዓይነት የግል ዓለማቀፍ ካምፓኒዎች ናቸው፤ ስልታቸው ብቻ ነው ትንሽ የሚለየው፤ ችግሩ ግን፤ ይህ የመቀመቅ ካፒታሊዝም እና የሚያራምደው የሾክ ዶክትሪን ፤ በየደረሰበት የዓለም ጥግ ሀገር በማፈራረሱ እንጂ፤ ካፈራረሰ በኋላ በካፒታሊስት ዘዬ በመገንባቱ በኩል ሲሳካለት አልታየም።»
አንድዬ ሀገራችንን ከእንጦርጦስ አፋፍ ይሰውር። ህዝቦቿን ከገባንበት መቀመቅ ያውጣን። በራችን ላይ ቆሞ ለሚያንኳኳው ክፉ ዲዛስተር-ካፒታሊዝም በራችንን ከሚበረግድ የራሳችን ወገን ይጠብቀን። ከችግር የምንወጣበትን ሀገራዊ ልቦና፣ እርጋታና ጥበብን አብዝቶ ይስጠን።
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ።
ቸር እንሰንብት።